2013 ኦክቶበር 5, ቅዳሜ

ለስሕተታቸው ሊቃነ ጳጳሳትን ይቅርታ የጠየቁ ግለሰቦች ጉዳይ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ቀኖና በጠበቀና ባገናዘበ መልኩ ሊወሰንበት ይገባል!

በቤተ ክርስቲያናችን ዐውደ ምሕረት ሰፍነውና በቢሮክራሲዋ ውስጥ ተሰግስገው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን ለሚያራምዱ ድርጅቶች ተልእኮ አስፈጻሚና የቅስቀሳ ኃይል የኾኑ ሕገ ወጥ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመመከት በኦርቶዶክሳዊ ቀናዒነትና በበጎ ፈቃድ ተሰባስቦ በጥቅምት ወር ፳፻፫ ዓ.ም አገልግሎቱን የጀመረው የፀረ – ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት÷ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ወቅታዊ ጉዳዮችን የገመገመበትንና ቀጣይ የአገልግሎት አቅጣጫዎችን የተለመበትን የግማሽ ቀን ውይይት አካሂዷል፡፡
ከጥምረቱ መምህራን አንዱ የኾኑት መ/ር ያረጋል አበጋዝ÷ ‹‹ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የወጡ(ያፈነገጡ) ሰዎች የሚመለሱት እንዴት ነው?›› በሚል በመድረኩ ያቀረቡት ጽሑፍ የውይይቱ ዋነኛ መነሻ ነበር፡፡ የጽሑፉን ዋና ዋና ክፍሎችና ተያያዥ ሐሳቦች በማስቀደምና ሙሉ ይዘቱን በማስከተል አቅርበነዋል፡፡ እንዲመለከቱት ተጋብዘዋል፡፡
*             *           *
የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መሠረት ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ ሃይማኖት ደግሞ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አንድና ብቸኛ እውነት ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ የሰጠውን የመዳን ጸጋ ሰዎች በሃይማኖት ዐውቀውና ተረድተው ይጠቀሙበት ዘንድ፡- የምሥራቹን ለዓለም ሁሉ የመናገር(የማስተማር፣ የመግለጥ)፤ ያመኑትን ምእመናን የመጠበቅና ምስጢራትን የመፈጸም፤ በራሳቸው ስንፍናና በመናፍቃን ቅሰጣ ከበረቷ የጠፉትን የመፈለግ፤ ኑፋቄ በተባለ የእምነት በሽታ የታመሙትንና የተለከፉትን የማከምና የማይድኑ ከኾነ ስለመንጋው ጤንነትና ስለ መናፍቁ በጎ ስትል እያዘነች በውግዘት የመለየት ተግባር አላት፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት ወካይና መገለጫ ናት፡፡ ስለዚህ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ተቀላቅሎና ተመሳስሎ መግባት እንደሌለ ሁሉ በዚህ ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያንም የዚያ ወካይና መገለጫ ናትና የእርሷ ወገኖች ያልኾኑትን ትለያቸዋለች እንጂ፣ ጭፍን የምድራዊ መንግሥት ካድሬዎችና በመንግሥት የፀረ – አክራሪነት አጀንዳ ስም ስሑታኑ ከእነ ኑፋቄያቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው እንዲገቡና የልዩ እምነት ፍላጎታቸው የኾነውን የቤተ ክርስቲያናችንን መዳከምና መከፈፋል እንዲያሳኩላቸው ‹‹የአስተምህሮ መቻቻል ዴሞክራሲ›› ከንቱ ፕሮፓጋንዳ እንደሚነዙት አንዳንድ ባለሥልጣናት በዝምታ ወይም በግዴለሽነት አታዝላቸውም!!!
አንድ ምእመን በቤተ ክርስቲያን የሚኖረው በእውነትና በሃይማኖት እስከተገኘ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ያን እምነትና እውነት ሲክድና ሌላ ባዕድ ነገር ውስጥ ሲገባ ግን ያንጊዜውኑ ከቤተ ክርስቲያን ራሱን በራሱ ያወጣል! በራሱ ድርጊት ራሱን ከድኅነት ውጭ ያደርጋል!! በመኾኑም በዚህ ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የምትለየው ቀድሞውንም ራሱን በኑፋቄ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ከቤተ ክርስቲያን የእውነት መሠረትና ዓምድ የለየውን ሰው ነው፡፡
ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ግልጽ ተቃርኖ የያዘ ኑፋቄ ሁሉ በአጠቃላይ የተወገዘ ነው፡፡ የታወቀና የተወገዘ ኑፋቄ ይዘው የሚነሡ ሰዎች አዲስ ነገረ ሃይማኖታዊ ውይይት አያስፈልጋቸውም፤ በቀደመው ውግዘት እስከ ዕለተ ምጽአት የሚነሡት ሁሉ ተወግዘዋልና፡፡ ለእንዲህ ዐይነቱ ኑፋቄ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም፡- ያን ኑፋቄ የሚያራምደው ግለሰብ በትክክል ያን ኑፋቄ መያዝ አለመያዙን፣ የሚመለስ መኾን አለመኾኑን ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ከተረጋገጠ በኋላ ያ ሰው ከቤተ ክርስቲያን መለየቱ(ማውገዙ) በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ወይም በአገረ ስብከት ደረጃ ሊፈጸም ይችላል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በኑፋቄ ተወግዘው (ይፋዊ በኾነ ውግዘት ይኹን ራሳቸውን በኑፋቄ በመለየታቸው) የተለዩ ሰዎች የመመለሳቸው ዜና ታላቅ የምሥራች ነው!! ከኑፋቄያቸው እንዲመለሱ የቤተ ክርስቲያን ናፍቆቷና ምኞቷ ነው፡፡ ቀድሞም እንዲወገዙ የሚደረገው፣ ነፍሳቸው በምጽአት ቀን እንድትድን ራሳቸው ሰዎቹን ለመርዳት ሲባል እንጂ እንዲጠፉ አይደለም፡፡ ስለኾነም በኑፋቄያቸው ጠፍተው ሲባዝኑ የቆዩቱ ስሕተታቸውን በርግጥ አምነው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ከመመለሳቸው የበለጠ ደስታ የለም፡፡
ነገር ግን፣ መናፍቃን የነበሩ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንመለሳለን ሲሉ ሊደረጉ የሚገባቸው ዋና ዋና ጥንቃቄዎች እና ተግባራት አሉ፡፡ እኒህም፡-
  • እንመለሳለን የሚሉት ሰዎች በትክክል ከልባቸው ነው? ወይስ በንስሐ፣ ዕርቅና ይቅርታ ሰበብ እንደ ግብር አባቶቻቸው እንደ አርዮሳውያንና እንደ ሕንድ ማር ቶማ ቸርች ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተገንጣዮች ውስጥ ገብተው ለመበጥበጥና ለመከፋፈል ነው? የሚለውን በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እያንዳንዱ ምእመን ሊያተኩርበትና ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡
  • የጅምላ ንስሐ የለም! እንመለሳለን የሚሉ ወገኖችን ጉዳያቸውን በየግለሰቡ/እያንዳንዱ ጥፋቱ ምን እንደነበር፣ ለምን እመለሳለሁ እንዳለ፣ ወዘተ በዝርዝር መለየት፣ ማጥናትና መወሰን ይገባል እንጂ በጅምላ ከዚህ ወዲያ ወይም ከዚያ መለስ ብሎ ማድረግ አይገባም፡፡ ይህ እንመለሳለን ለሚሉትም ሰዎች፣ ለማኅበረ ምእመናኑም ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፡፡ ያን ኑፋቄ ዳግመኛ ሲያስተምሩ ቢገኙ ማንነታቸውን በግልጽ ለመለየት ይጠቅማል፡፡
    Yared Ademe
    በዘማሪት ወ/ሮ ፋንቱ ወልዴ አቅራቢነት መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን በመኖርያ ቤቶቻቸው ተገኝቶ ይቅርታ የጠየቀውና ይቅርታ በመጠየቁ ይዞት ከወጣው ጠርዘኛ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኝ ቡድን በተነሣበት ተቃውሞ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ዲ/ን ያሬድ አደመ
  • መናፍቃን ሲመለሱ በጓዳና ለሌሎች በማይታወቅ ኹኔታ ሳይኾን በግልጽ፣ ምእመናን ሁሉ በሚሰሙበትና በሚያውቁበት መድረክ በይፋ መኾን አለበት፡፡ በፊት የካዱት፣ ቤተ ክርስቲያንን ያሳጡትና የነቀፉት በይፋ እንደነበር ሁሉ ሲመለሱም በይፋ መኾን ይኖርበታል፡፡ መመለሳቸው በይፋ ከተደረገ፣ የቀድሞ ኑፋቄያቸውን እናስተምራለን ቢሉ እንኳ ‹‹ተመልሰናል ብላችሁ አልነበረምን? የቀድሞ ስሕተታችንን ትተናል ብላችሁ አልነበረምን?›› ብሎ ለመጠየቅና በቶሎ ማንነታቸውን ለማወቅ ይረዳል፡፡
  • የሚመለሱ መናፍቃን በእውነት ከመናፍቃን የተለዩና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጋራ የተዋሐዱ ስለመኾናቸው አንዱ ምስክር የሚኾነው ከቀድሞ  ጀምሮ  የተነሡ  ዋና  ዋና  የኑፋቄ አመንጪዎችን  በይፋ  በማውገዛቸው  ነው፡፡ ስለኾነም በጥንቃቄ በተዘጋጀ የመናፍቃን ዝርዝር ላይ እነዚያን መናፍቃን ማውገዝና ለዚህም መፈረም ይኖርባቸዋል፡፡ 
  • የሚመለሱ መናፍቃን እስከ ዛሬ ድረስ በስብከቶቻቸውና በመጻሕፍት ያስተማሯቸውንና የጻፏቸውን የኑፋቄ ትምህርቶች ሁሉ ቀድሞ ኑፋቄው ከተላለፈበት ልሳን (ሚዲያ) እና የሚዲያ ውጤቶች ዐይነትና ተደራሽነት ጋራ ተመጣጣኝ በኾነ መንገድ እንዲያወግዙና ስሕተት መፈጸማቸውን ተቀብለው ከአሁን በኋላ እንደዚያ ዐይነት የስሕተት ትምህርት እንደማያስተምሩ በጽሑፍ ቃል መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም በተለያየ ጊዜና ቦታ በኑፋያሳሳቷቸው ሁሉ ስሕተታቸውን አምነው መመለሳቸውን እንዲረዱ፣ ወደ ስሕተታቸው ዳግመኛ በማይመለሱበትና በአስተማማኝ መልኩ ለመጥቀስና ምስክር ይኾንባቸ ዘንድ ነው፡፡
  • መናፍቃን ሲመለሱ በስሑት ትምህርታቸው የተነሣ ከእናት ቤተ ክርስቲያን ለመውጣታቸውና ለነፍሳቸው ጥፋት ምክንያት የኾኑባቸው ሰዎች እንዲመለሱ ጥረት ማድረግና መመለስ አለባቸው፡፡
  • የሚመለሱ መናፍቃን ከቀድሞ ጀምሮ የተነሡ ዋና ዋና የኑፋቄ አመንጪዎችን በይፋ እንዳወገዙ ሁሉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ የሚቀበሉ ስለመኾናቸውም ግልጽና ጠንቃቃ ቃለ ጉባኤ አዘጋጅቶ እንዲፈርሙ ማድረግ ይገባል፡፡
  • ፍትሐ ነገሥታችን ለሌላው ሰው ክሕደት ምክንያት የሚኾን ሰው ሲመለስ ቀኖናው ከበድ ያለ እንዲኾን ያዝዛል፡፡ ስለዚህ ተመላሾቹ ከበድ ያለ ቀኖና ተሰጥቷቸውና በነገረ ሃይማኖት የበሰሉ ሊቃውንት ተመድበውላቸው ከእነርሱ መማራቸው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ተመልሰናል የሚሉት ሰዎች መመለሳቸውና ንስሐቸው የእውነት መኾን አለመኾኑ የሚገለጥበትና የሚፈተንበት አንዱ መንገድም ይኽ ነው፤ የተመለሱት በእውነት ከኾነ ግድ እናስተምር፤ በመድረክ እንቀጥል አይሉም፤ ነገር ግን የተንኮልና የስልት ከኾነ መድረኩ ላይ ካልቀጠልን ብለው የሙጥኝ ይላሉ፡፡ እንመለስ የሚሉ ሰዎች ጭንቀታቸው መድረክ ላይ ስለ መዘመራቸውና ስለ መስበካቸው ከኾነ ጉዳዩ ዓላማን በውጭ ኾኖ ማስፈጸም ስለማይመች ወደ ውስጥ ገብቶ ተሐድሷዊውን ዓላማ ለማስፈጸም የአስገቡኝ ጥያቄ እንጂ የመመለስና የንስሐ ጥያቄ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይኼ የድርድር እንጂ የንስሓ መንገድ አይደለም፡፡
    Begashaw Dessalegn
    በዘማሪት ወ/ሮ ፋንቱ ወልዴ አቅራቢነት መስከረም ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን በመኖርያ ቤቶቻቸው ተገኝቶ በግል ስላደረገባቸው መደፋፈር ይቅርታ የጠየቀውና ይቅርታ በመጠየቁ ይዞት ከወጣው ቡድን ጋራ ውዝግብ ውስጥ የገባው የቅ/ሲኖዶስ ፍርደኛ በጋሻው ደሳለኝ
  • የጠፉትን መቀበል ተገቢና መልካም ቢኾንም በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሂደት የሚደረገው እያንዳንዱ ነገር ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አርቆ ማየት ያስፈልጋል፤ የተመላሾቹን ጭምብሎቻቸውን ገልጦ ትክክለኛ ማንነታቸውንና አደጋውን መረዳትና መለየት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ሰላም ሰላም›› በሚል ቃል ብቻ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያንን ውሳጣዊ ሰላም፣ እንዲሁም ጊዜያዊ ችግር የፈታንና ያቃለልን ሲመስለን ለወደፊቱ ችግር እያወሳሰብንና እያቆላለፍን እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርብ ጊዜ ከስድስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ በኾነችው በሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኾነውን አሳዛኝ ነገር ልንረሳው አይገባንም፡፡
  • ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደተማርነው፣ እንመለሳለን ባይ መናፍቃን የፖለቲካ ሰዎችንና ባለሥልጣናትን በመዘወርና ከጎናቸው በማሰለፍ በኩል ይዋጣላቸዋል፡፡ በኒቅያ ጉባኤ በቅዱሳን አባቶች ተወግዞ የተለየው አርዮስና የኑፋቄ ጓደኞቹ የተለያዩ ሰዎችን በመላክና በውስጥ ለውስጥ በሠሩት የፕሮፓጋንዳ ሥራ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አርዮስን ከፈረደበት ከግዞቱ እንዲወጣና ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲመጣ ካደረጉ በኋላ ቅዱስ አትናቴዎስን ጨምሮ ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳትንና ካህናትን ከየመናብርታቸውና አብያተ መቅደሳቸው እያሳደዱ ሲፈነጩባቸው ኖረዋል፡፡ ዛሬም እውነተኛ ዓላማቸው የተነቃባቸው እንመለሳለን ባይ መናፍቃን፣ ለቤተ ክርስቲያናቸው ቀናዒ የኾኑ አገልጋዮችንና ምእመናንን የመንግሥት የወቅቱ አጀንዳ በኾነው የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ ተሸፍነው በጽንፈኝነት ውንጀላ ማሸማቀቃቸው የባሕርያቸው ነው፡፡
  • እንመለሳለን ለሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በሽምግልና ይኹን በአጣሪነት ከሚሳተፉ ሰዎች አንዳንዶቹ፣ ‹‹ዕርቅን ማን ይጠላል? ይቅርታና ሰላም ምን ክፋት አለው›› በሚሉ መሸፈኛዎች ከመታለልና ከማታለል መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡ ይልቁንስ ይቅርታ ጠያቂዎቹና እንመለሳለን ባዮቹ ከጠየቁት ጉዳይ ጋራ በተያያዘ ምን እያደረጉ እንደነበርና ምን በማድረግ ላይ እንደኾኑ ለመመርመር ብስለቱና ቅንነቱ ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡
  • ራሳቸውን በአስታራቂነት ጎራ መድበው፣ እነርሱ ከሌሎቹ የተሻሉ አስተዋዮችና ያላከረሩ ብልሆች እንደኾኑ አድርገው ራሳቸውን የሚቆጥሩ ሰዎች÷ አስታረቁ ተብለው ስም ለማሰርና ጀብድ እንደሠሩ ለመቆጠር፣ በስሕተቱ ተለይቶ የወጣውን አካል በሽፍንፍን በመመለስ በሌሎች አጀንዳዎች ከተቀየሙት አካል በተፃራሪ በወደረኛነት በማሰለፍና ጎልቶ በመታየት እንበቀላለን ብለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ይኸው ፍላጎታቸው ሊጋለጥ ደረጃቸውን ዐውቀው አድበው እንዲቀመጡ ሊደረግ ይገባል!!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...