2014 ጁላይ 7, ሰኞ

ሰኔ 30 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ


 በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ  (ናታኒም ጡመራዊ መጽሔት ሰኔ 30 እንኳን ለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+" ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ "+

=>ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

+የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር:: ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::





+ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

+የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ በዚህች ቀን (ሰኔ 30) ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

=>መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
+የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
+በማሕጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት
+በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
+እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ
+የጌታችንን መንገድ የጠረገ
+ጌታውን ያጠመቀና
+ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው::

+ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን ነቢይ: ሐዋርያ: ሰማዕት: ጻድቅ: ገዳማዊ: መጥምቀ መለኮት: ጸያሔ ፍኖት: ቃለ ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች::

+" አባ ጌራን ሕንዳዊ "+

=>ዳግመኛ በዚህች ቀን ሕንድ ካፈራቻቸው ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት ጻድቁ አባ ጌራን ይታሰባሉ:: የእኒህ ቅዱስ ታሪክ አሳዛኝ ነው:: ቅዱሱ በሕንድ ተወልደው: በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድገው: ገና በወጣትነታቸው መንነው: ደሴት ውስጥ ወደሚገኝ አንድ በርሃ ገብተዋል:: ከገድላቸው ጽናት: ከቅድስናቸውም ብዛት የተነሳ በሃገረ ሕንድ ሰይጣን እንዳይገባ: ጠብ ክርክር እንዲጠፋ: ሰው ሁሉ በፍቅርና በሰላም እንዲኖር ማድረግ ችለው በጣም ተወዳጅ ነበሩ::

+በዚህ የተበሳጨ ሰይጣን ግን ባልጠረጠሩት መንገድ መጣባቸው:: አንዲት ሴት ወደ እርሳቸው መጥታ (የንጉሡ ልጅ ነኝ በሚል) አስጠግተዋት ነበር:: አንድ ሌሊት ላይ ግን አውሬ ያባረራት በመምሰል ሩጣ ወደ ቤታቸው ገብታ አቀፈቻቸው:: በዚያ ቅጽበት ፍጡር ደካማ ነውና ታላቁ አባ ጌራን ተሰነካከሉ:: ከአፍታ በሁዋላ የሆነውን ሲያውቁ ደም አለቀሱ::

+ልብሳቸውን ቀደው: እንባቸው እንደ ዥረት እየፈሰሰ አለቀሱ:: ራሳቸውን በትልቅ ድንጋይ እየቀጠቀጡት የጭንቅላታቸውና የደረታቸው አጥንቶች ተሰባበሩ:: እርሱ እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ይቅር ብሎ: የቅድስና ስም ሰጥቶ በዚሕች ቀን ወደ ገነት አሳርጉዋቸዋል:: ለዚህ ነው መጽሐፉ "ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና: ይነሣማል" ያለው:: (ምሳ. 24:16)

=>አምላካችን ከቅዱሱ ቤተሰብና ከጻድቁ አባ ጌራን በረከት ይክፈለን::

=>ሰኔ 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት (ልደቱ)
2.ቅዱሳን ዘካርያስና ኤልሳቤጥ (ወላጆቹ)
3.አባ ጌራን መስተጋድል (ሕንዳዊ)
4.ቅዱሳት ደናግል ማርያና ማርታ (ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት-የአልዓዛር እህቶች)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

=>+"+ ደግሞም አንተ ሕጻን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ:: መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና:: እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ:: ይሕም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው:: +"+ (ሉቃ. 1:76)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...