2014 ሴፕቴምበር 3, ረቡዕ

የ2006 ዓ.ም. የግቢ ጉባኤያት ፍሬዎች ዋንጫና ሜዳልያቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን አስረከቡ


አትም ኢሜይል
ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም
እንዳለ ደምስስ
  • ለኔ ይህ ዋንጫ ትልቁ ሀብቴ ነው፤ ሰው ሀብቱ ባለበት ልቡ ይኖራልና ዋንጫውን ሳስብ ማኅበሬን አስባለሁ፤ ተግቼም እንዳገለግል ያደርገኛል፡፡ የማልተካውን ሀብቴ ለማይተካው የማኅበሬ አገልግሎት መሥጠት ለኔ ታላቅ ደስታ ነው፡፡ /ዲያቆን ቶሎሳ ታዬ/

dn tolosa 2ማኅበረ ቅዱሳን በ2006 ዓ.ም. ከዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ግቢ ጉባኤያት በርካታ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ቆይታቸው ያስመዘገቡት ውጤት ከፍተኛ በመሆኑም በርካቶች የተሸለሙትን ዋንጫና ሜዳልያ በሥጦታ ለማኅበሩ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ተመራቂዎች መካከል በወሎ ዩኒቨርስቲ ደሴ ካምፓስ በእንስሳት ሳይንስ ትምህርት የተመረቀው ዲያቆን ቶሎሳ ታዬ አንዱ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው የግቢ ጉባኤው ሰብሳቢ የነበረ ሲሆን፤ በርካታ ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ 4 ነጥብ 18A+ በማምጣት የዩኒቨርስቲው አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ዋንጫና ሜዳልያ ለመሸለም በቅቷል፡፡

የተሸለመውን ዋንጫ በማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት ለማኅበሩ ሲያስረክብ፤ ሜዳልያውን ደግሞ ከሕፃንነት ጀምሮ ሲያገለግልበት ለነበረው ለምእራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት በለስ ወረዳ ዳቡስ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲሰጥለት በጉባኤው ላይ ለተገኘው የወረዳ ማእከሉ ተወካይ እንዲያደርስለት አስረክቧል፡፡dn tolosa 3

ዲያቆን ቶሎሳ ዋንጫና ሜዳልያውን ካበረከተ በኋላ ባስተላለፈው መልእክት “ወሎ ዩኒቨርስቲ ስገባ ማኅበሩ ባዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል መርሐ ግብር ላይ ተገኝቼ የጉባኤ ቃና ጋዜጣን ገዝቼ ዶክተር እንግዳ በጅማ ዩኒቨርስቲ ሲመረቁ ያገኙትን ሜዳልያ ለማኅበሩ እንደሰጡ አነበብኩ፡፡ ወዲያውኑ እኔም ለዚህ ክብር እግዚአብሔር ቢያበቃኝ ያገኘሁትን ሽልማት ለማኅበሩ ለመሥጠት ቃል ገባሁ፡፡ እግዚአብሔርም ምኞቴን አሳካልኝ፡፡ ለኔ ይህ ዋንጫ ትልቁ ሀብቴ ነው፤ ሰው ሀብቱ ባለበት ልቡ ይኖራልና ዋንጫውን ሳስብ ማኅበሬን አስባለሁ፤ ተግቼም እንዳገለግል ያደርገኛል፡፡ የማልተካውንና በሕይወቴ አንድ ጊዜ ብቻ የማገኘውን ሀብቴ ለማይተካው የማኅበሬ አገልግሎት መሥጠት ለኔ ታላቅ ደስታ ነው” ብሏል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ዋንጫውንና ሜዳልያውን ከዲያቆን ቶሎሳ በመረከብ ለማኅበሩ ሰብሳቢና ለወረዳ ማእከሉ ከሠጡ በኋላ የተሰማቸውንdn tolosa 4 ደስታ ሲገልጹ “ይህ ውጤት በሀገራችን በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ታሪክ በጥቂቶች ብቻ ሊመዘገብ የሚችል ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡ ካስመዘገበው ውጤት ይልቅ ደግሞ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ በሕይወቱ አንድ ጊዜ ብቻ ሊገጥመው የሚችለውን እድል ውድ ሥጦታ ለማኅበሩ መሥጠቱ አስደንቆኛል፡፡ ብዙዎቻችንንም ያስተማረ ነው፡፡ ወደፊትም በሕይወቱ የተሳካ ጊዜ አሳልፎ ለሌሎች አርአያ እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል፡፡

የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ሰሙ ሥጦታውን ከተቀበሉ በኋላ የተሰማቸውን ሲገልጹም “ይህ ሥጦታ ጠቅላላ ጉባኤውንና ማኅበራችንን ወክዬ ነው የተቀበልኩት፡፡ እኛም ይህንን ታሪክና ሀብት ለመጠበቅ፤ አገልግሎቱንም ለማገዝ አብሮንም በአገልግሎት እንዲዘልቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ አደራውንም ተቀብለናል” ብለዋል፡፡

የደሴ ማእከል የማኅበረ ቅዱሳን ጸሐፊ ዲያቆን ሰሎሞን ወልዴ በሠጠው ምሥክርነትም ዲያቆን ቶሎሳ የግቢ ጉባኤው ሰብሳቢ ሆኖ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መሠብሠቢያ አዳራሽ በማሠራት፤ በአቅራቢያው ቤተ ክርስቲያን በማሳነጽና በመምራት፤ የሥራ አስፈጻሚና በዩኒቨርስቲው የሚካሔዱ አገልግሎቶችን በማስተባበር ተጠምዶ ስለሚውል ለዚህ ክብር ይበቃል የሚል ግምት አልነበረንም፡፡ ሆኖም ለግቢ ጉባኤውና ማኅበሩ ለሚያከናወነው አገልግሎት አርአያ እንዲሆን ስናበረታታው ቆይተናል፡፡ እግዚአብሔር መልካም ነገር አደረገልን፡፡ በወረዳ ማእከላችን ከሚገኙ 8 ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውሰጥ ከተዘጋጁት ሜዳልያዎች ሰባቱን የወሰዱት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ናቸው ብሏል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በደሴ ካምፓስ በትምህርትና እቅድ አስተዳደር ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው አሰፋ አደፍርስ፤ በደብረ ታቦርdn tolosa 5 ማእከል የፈቃደ እግዚእ ኮሌጅ ተመራቂዎቹ ዘውዴ ደሴና ከፍያለው ስመኝ ለማኅበሩ ማእከላት ሜዳልያቸውን አስረክበዋል፡፡ እንዲሁም ከሐረር የሜንሽን አግሮ ቴክኒካል ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ሰብሳቢ የሆነው ቃል ኪዳን ዓለሙ ሜዳልያውን በማእከሉ በኩል ለኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን እንዲሰጥለት አበርክቷል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...