2014 ኤፕሪል 25, ዓርብ

ፕሬዝዳንት ሙላቱና ቤተሰቦቻቸው ‹‹በየሰንበቱ ያስቀደሳሉ፤ ይቆርባሉ››


  • ቅዳሴው በቤተ መንግሥት ደብረ ገነት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ይከናወናል
  • ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ‹‹ከኹለት ጊዜ በላይ›› በጸሎተ ቅዳሴ አገልግለውበታል
  • የግብጽ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች በትንሣኤ ሌሊት ጸሎተ ቅዳሴ ላይ ተሳተፉ
AFRO TIMES ON PRESIDENT MULATUS CHRISTIANITY(ቅጽ ፩ ቁጥር ፯፤ ማክሰኞ እና ረቡዕ፤ ሚያዝያ ፲፬ – ፲፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
ከዕለተ ሢመታቸው አንሥቶ ኢአማኒ (non-believer) እንደኾኑ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲነገርባቸው የቆዩት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና ቤተ ሰዎቻቸው፣ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ቅጽር ውስጥ በምትገኘውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ባለችው የደብረ ገነት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በየእሑድ ሰንበቱ የሚከናወነውን ጸሎተ ቅዳሴ እየተሳተፉ ቅዱስ ቁርባን እንደሚቀበሉ ተገለጸ፡፡
Patriarch Mathias welcoming the newly elected FDRE president Dr Mulatu Teshome
ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በፕሬዝዳንት ሙላቱ ሹመት ሰሞን በብሔራዊ ቤተ መንግሥት
ደብሯን በእልቅና በማስተዳደር ላይ በሚገኙት መልአከ ገነት አባ መዓዛ ኃይለ ሚካኤል ስም ተፈርሞና የደብሩን ማኅተም ይዞ በቁጥር ደ/ገ/ቅ/ል/ማ/36 በቀን 6/03/2006 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከተላከው ደብዳቤ ለመረዳት እንደተቻለው÷ ከ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. ጀምሮ ሀገረ ስብከቱ በቋሚነት በሚመድባቸው አምስት መነኰሳት ካህናትና በአንድ ዲያቆን ልኡክነት ጸሎተ ኪዳንና ሥርዓተ ቅዳሴ በቤተ ክርስቲያኒቱ ይፈጸማል፤ በዚኹ ሳምንታዊ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓተ አምልኮ ላይም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ከነቤተሰቦቻቸው፣ የቤተ መንግሥቱ ሠራተኞችና የግቢ ጥበቃ አባላት እንዲሁም ሕፃናትንና እናቶችን ጨምሮ በርካታ ምእመናን ይገኙበታል፡፡
ደብዳቤው እንደሚያመለክተው፣ ጸሎተ ኪዳኑን የሚያደርሱትና ሥርዓተ ቅዳሴውን የሚፈጽሙት ስድስቱ ካህናት ከአምስት የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት የተውጣጡ ሲኾኑ እነርሱም ከመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ ከታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም፣ ከመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና ከደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን እንደኾኑ ዘረዝሯል፡፡
ለአገልግሎት ከተመደቡት ካህናት መካከል በዕድሜ መግፋትና በደረጃ ዕድገት ወደ ሌላ ደብር በተካሔደ ምደባ ምክንያት ኹለት ልኡካን መጓደላቸውን መነሻ በማድረግ የተጻፈው ይኸው የደብሯ አስተዳደሪ ደብዳቤ፣ ዘውዳዊ ሥርዓተ መንግሥት መለወጡን ተከትሎ ለረጅም ጊዜ ተዘግታ ቆይታ በከፍተኛ ጥረት ዳግመኛ በተከፈተችው ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱን ለግቢው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በአግባቡ ለማበርከት ይቻል ዘንድ በተጓደሉት ካህናት ምትክ ለቦታው ተስማሚ የኾኑ አባቶች እንዲመደቡለት ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጥያቄ የቀረበበት ሲኾን ሀገረ ስብከቱም በጥያቄው መሠረት ምላሽ መስጠቱ ተገልጦአል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተሠርታ የተደራጀችው በዐፄ ኃይለ ሥላሴ እንደኾነና በደርግ ሥርዓተ መንግሥት ተዘግታ የተለያዩ ዕቃዎች ማስቀመጫ ኾና እንደነበር ያስታወሰው ደብዳቤው÷ ዳግመኛ ተከፍታ፣ ተጠግናና ተስተካክላ አገልግሎቷን እንድትቀጥል የተደረገው ከዐሥር ዓመት በፊት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መልካም ፈቃድና ትእዛዝ፣ በቀድሞው የቤተ መንግሥቱ ዋና አስተዳደር ብርጋዴር ጀነራል ፍሬ ሰንበት ዓምዴ ጥረት መኾኑን ገልጦአል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ጥገናና ማስተካከል ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በስፍራው ተገኝተው የቅድስት ልደታ ለማርያም ታቦተ ሕግ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም መጥቶ እንዲገባ፣ አገልጋይ ካህናትም እንዲሟሉለት በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ልኡካኑ ተሟልተው ተመድበው ሥርዓተ ቅዳሴውና ጸሎተ ኪዳኑ ኹሉ በአግባቡ እየተከናወነ ከመቆየቱም ባሻገር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ራሳቸው ከኹለት ጊዜ በላይ ጸሎተ ቅዳሴውን በመምራት አገልግሎት እንደሰጡበት በደብዳቤው ሰፍሯል፡፡
ሥዩመ እግዚአብሔር ተብለው በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚቀቡት የቀድሞዎች ነገሥታት በአብያተ መንግሥቶቻቸው ውስጥ የግል ጸሎታቸው የሚያደርሱባቸውን ቤቶች የሚያንፁ ሲኾን እኒኽም ሥዕል ቤት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በኾነው የምኒልክ ቤተ መንግሥት አጠገብ የምትገኘው ሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ የቀድሞው ቤተ መንግሥት የነበረውንና ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተበረከተውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትን የሚያዋስነው የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በማሳያነት ይጠቀሳሉ፡፡
በዚሁ ልማድ ታቦቷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽላት ቤት ተዘጋጅቶ የተመሠረተችውና እስከ ኻያ አምስት ሰዎችን የሚይዝ ስፋት ያላት የታላቁ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ደብረ ገነት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን÷ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ የግል ጸሎታቸውን የሚያደርሱባት ስትኾን በእሑድ ሰንበት ደግሞ ሌሎች ክብረ በዓላት ከሌሉ በቀር የሚያስቀድሱባት እንደነበረች ይነገራል፤ በቅርቡም ከኮንቴይነር የተበጀ ቤተ ልሔም እንደተበጀላትም ታውቋል፡፡
ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከተቋቋመ በኋላ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ እንደኾኑና መንግሥታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት እንደማይኖር የታወጀ ቢኾንም የመንግሥቱ መሪዎች በግል የያዙትን እምነት ከማራመድ ባለመከልከላቸው የደብሯ ታሪክ በታሪካዊነቱ ተጠብቆ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይና በወጣትነታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ በነበሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መልካም ፈቃድ በተሟሉ ልኡካን ደብሯ አገልግሎቷን ለቤተ መንግሥቱ ክርስቲያን ማኅበረሰብ እየሰጠች ትገኛለች፤ ከእርሳቸውም በኋላ ለተተኩት የፌዴራል ሥርዓቱ ሦስተኛ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመና ቤተ ሰዎቻቸው አገልግሎቷን ቀጥላለች፡፡
President Dr Mulatu's wife W.ro Meaza Abreham on the patriarch enthronment 1st anniv.
በፓትርያርኩ የአንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት አከባበር በክብር እንግድነት የተገኙት የፕሬዝዳንቱ ባለቤት ወ/ሮ መዓዛ ኣብርሃም
የፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተከበረበት ወቅት በክብር እንግድነት የታደሙት የፕሬዝዳንቱ ባለቤት ወ/ሮ መዓዛ አብርሃም እንደ ግቢ ገብርኤል ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በክብረ በዓላት ወቅት በዐደባባይ ከመታየት አልፎ ዝክርና ሌሎችንም ተራድኦዎች ሲያደርጉ መታየታቸው ባለቤታቸው በብዙዎች እንደሚባለው ቢያንስ ኢአማኒ እንዳልኾኑ ፍንጭ ሰጥቶ የነበረ ሲኾን ይህ የደብሯ አስተዳደር ደብዳቤ ደግሞ የፕሬዝዳንቱን አማኒነት(ሃይማኖተኛነት) ያሳየና ኢአማኒ ናቸው እየተባለ የሚነገረውም ቅቡልነት የሌለው መኾኑን እንደሚያመለክት ጠቁመዋል፡፡
national_palace.jpgየታኅሣሥ ግርግር ተብሎ ከሚታወቀው የ፲፱፻፶፫ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ለንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አንደኛ ዓመት ኢዮቤልዩ (ኻያ አምስተኛ ዓመት) መታሰቢያ በ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. ተጠናቆ ከመሠራቱ ጋራ ተያይዞ በቀድሞ አጠራሩ ኢዮቤልዩ ይባል የነበረውን ቤተ መንግሥት፣ የደርግ/ኢሕዴሪ መንግሥት ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በሚል ሰይሞታል፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳናና በማዕዶተ ፊንፌኔ (በፊንፊኔ ወንዝ ማዶ) የሚገኘው ግርማዊው ቤተ መንግሥት፣ ከ፲፱፻፶፭ – ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. በነበሩት ዐሥራ ሦስት ዓመታት በንጉሠ ነገሥቱና በንጉሣውያን ቤተ ሰዎቻቸው መኖርያነቱ ይታወቃል፡፡
EthiopianPresidentialPalaceLionየንጉሠ ነገሥቱ ስዒረ መንግሥት በዐሥር የደርጉ መኰንኖች ንባብ የተሰማበትን ቤተ መጻሕፍት ጨምሮ የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ልዩ ልዩ ንጉሣዊ አልባሳት፣ ገጸ በረከቶችና የወግ ዕቃዎች የያዘ አነስተኛ ቤተ መዘክር፣ የዱር እንስሳት ዐጸድ የሚገኙበት ቤተ መንግሥቱ ከአብዮቱ በኋላ በደርግ/ኢሕዴሪ ሥርዓት ለመንግሥታት መሪዎች ክብር ግብዣዎች ሲደረግበት እንዲሁም በመስከረም ፪ የአብዮት በዓል ለሠራዊቱ ግብር ሲገባበት ቆይቷል፤ ከሥርዓቱ ለውጥ በኋላም ፕሬዝዳንታዊ መኖሪያና ርእሰ ብሔሩ ኦፌሴልያዊ ሥራውን የሚያከናውንበት ኾኖ ይገኛል፡፡
ሃይማኖትና ሃይማኖተኝነት እንደኋላ ቀርነት የሚታይበትን ዘመን ተሻግረንና ርእዮቱን ሽረን በበለጸጉት አገሮች ዘንድ ሳይቀር መሪዎች በአማኙ መካከል እየተገኙ ሥርዓተ እምነታቸው ሰፈጽሙና አንዳንዶቹም የብሔራዊ ማንነታቸው መለያ አድርገው መታየታቸው ዛሬ ዛሬ ብዙም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የሩስያውን ኦርቶዶክሳዊ መሪ ቭላድሚር ፑቲንን፣ የእንግሊዙን አንግሊካን ፕሮቴስታንት ዴቪድ ካሜሮንን መጥቀሱ ይበቃል፡፡
ኹኔታው የፖሊቲካ መሪዎች በግል ያላቸውን የእምነት ቀናዒነት የሚያሳዩበት ከዚያም አልፎ በግል እምነታቸው በማይመስሉት አማኒም መካከል ተገኝተው የሕዝቡን ፖሊቲካዊ ድጋፍ የሚያሰባስቡበት ስልት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የሚገልጹ የፖሊቲካ ተንታኞችና አስተያየት ሰጭዎች፣ ይህ ዓይነቱ የፖሊቲካ መሪዎች ዝንባሌ በተለይ በምርጫ ሰሞን በርክቶ እንደሚታይ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ረገድ ከሠራዊቱ በቅርቡ ተሰናብተው በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውድድር ውስጥ የገቡት የግብፁ አብደል ፈታሕ አልሲሲና ሌላው ዕጩ ሃምዳን ሳባሂ ጥብቅ የእስልምና እምነት ተከታይ መኾናቸው ቢታወቅም ባለፈው እሑድ የምሥራቁም የምዕራቡም የክርስትና እምነት ተከታዮች ባከበሩት የጸሎተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታቸው በሀገሪቱ ጋዜጦች ተዘግቧል፡፡
የግብጹ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ታዎድሮስ የሚመሩትና ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎቹ የሚገኙበት የትንሣኤ ሌሊቱ ጸሎተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓቱ ከሚፈጽበት የአባሲያ ቤተ ክርስቲያን ወጣት አገልጋዮች ጋራ በመተባበር ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥርና የደኅንነት ጥበቃ የሚደረግበት እንደኾነ ተዘግቧል፡፡
ሃይማኖት ለልማት ከሚኖረው አስተዋፅኦ አንፃር ከፍተኛ አጽንዖት ተሰጥቶ በሚነገርበት ልማታዊ መንግሥት የፖሊቲካ መሪዎቻችን እንደየእምነታቸው በአማኒው የሥርዓተ አምልኮ አፈጻጸም ወቅት በመካከሉ መታየት የተለመደና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ኾኖ የሚታይበት ዘመን እናይ ይኾን?
ከብሔራዊ ቤተ መንግሥት ደብረ ገነት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተጻፈው ደብዳቤPalace letter to the dioseces0Palace letter to the dioseces01

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...