2015 ኤፕሪል 23, ሐሙስ

ተዋሕዶ-በደም

ሚያዝያ 14ቀን 2007ዓ.ም
መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ
0000000000በደም ተመሥርተሽ
በደም ተገንብተሸ
በደም ተዋሕደሽ
በደም ተሰራጭተሸ
ደሙ ብርሃን ሆነን ከጨለማም ወጣን ፡፡
ተዋሕዶ
በደም አጥምቀሽን
በደም አጽንተሸን
ከጌታችን ጋራ አንድ አካል አረግሽን፡:
ተዋሕዶ
በደሙ አክብረሽን
በደሙ አስታርቀሽን
ደሙን ከካሰልን
የደሙን ማኅተም ኃይሉን ተጎናጸፍን፡፡

ተዋሕዶ
በደም ተገዝቼ
በደሙም ነጽቼ
በደሙ ጸንቼ
ኖርኩኝ ረክቼ ደሙን ጠጥቼ ፡፡

ተዋሕዶ
ለዓለም በፈሰሰው ደሙ
ምልክት ዓርማዬ ሲሆን ማኅተሙ
ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ እንዳይችል መልኩን
እንዴት በመከራ አላውቀውም ልበል?

ተዋሕዶ
ደሙ ይጠራኛል ጽና በርታ እያለ
ምልከት በልቤ ታትሞ ስላለ፡፡
እንዴት ልበጥሰው አላውቅም ልበለው?
መንፈሱ አጽንቶ መንፈሱ ካገዘኝ፡፡
የቀድሞ ማንነት በደሌን ሳያየው
በማተቤ አጸናኝ ለመንግሥቱ አበቃኝ፡፡

ለሰማእታቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተካሔደ፡፡


ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም.
001tselote fitat002tselote fitat004tselote fitat003tselote fitat
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሊቢያ ለተሰዉት ክርስቲያኖች ቀኖናው በሚፈቅደው መሠረት በቅርቡ የሰማእትነትን ክብር እንደምትሰጥ አሰታወቀች
ቅዱስ ጳትርያርኩ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የግብጽ አምባሰደር፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰማእታቱ ቤተሰቦችና ምእመናን በተገኙበት ጸሎተ ፍትሐቱ ተከናውኗል፡
በጸሎተ ፍትሐቱ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራን ሰማእታቱን አስመልከቶ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ያስተላለፉትን መልእክት ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን!
ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡነ ዘበሰማያት
በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ
የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 10*32
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት 
የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ 
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ወጣቶች
ምእመናንና ምእመናት
ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕትነት አብሯት የኖረ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ዘመናት ልጆቿ በግፍ ተገድለው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡

በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በናግራን፣ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት፣ በዐሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አሕመድ፣ በዐሥራ ዘጠነኛውና ሃያኛው ክፍለ ዘመን በውጭ ወራሪ ኃይሎች በርካታ የሰማዕትነት ታሪኮች አልፈዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሁሉም ዘመን የተነሡባት አሳዳዶችና ገዳዮች ከነታሪካቸው ሲጠሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአምላኳ ጥበቃና በልጆቿ ጽናት ሰማዕታቷን አክብራ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ሀብትን እያደለች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች፡፡

ዛሬ እነዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጠባቡ በር ተጉዘው በደማቸው ማሕተም ወደ መንግሥተ ሰማያት የገቡ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት ጽኑ ምስክሮች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ለእነዚህ ልጆቻችን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት የሚገባውን የሰማዕትነት ቀኖና ሥነ ሥርዓት በቅርቡ በማከናወን ለመላው ዓለም ያሳውቃል፡፡

ስለዚህ የክርስቶስ ቤተሰቦች የሆናችሁ ክርስቲያኖች ሁሉ በዚህ አረመኔያዊ ወንጀል ሳትደናገጡ አሸባሪነትን በአንድነት ሆናችሁ በማውገዝና በመከላከል የተጀመረውን ተቃውሞ ትርጉም ባለውና አፋጣኝ በሆነ መንገድ ልንፈጽመው እንደሚገባ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

005tselote fitat006tselote fitat007tselote fitat10tselote fitat
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
አሸባሪነት ሃይማናት የለውም፣ በዕውቀትና በበሳል አእምሮ የሚከናወን ተግባርም አይደለም፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎችም የተረጋጋ ሥነ ልቦና ያላቸው ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ብሶት ያለባቸው ሰዎች እንደሚያደርጉት ያለ የነፃነት ትግልም አይደለም፡፡

ነገር ግን በፍጹም ራስ ወዳድነትና ጭካኔ ላይ የተመሠረተ አስነዋሪ ወንጀል ነው፡፡ የአይ ኤስ አሸባሪዎች የፈጸሙት ወንጀል የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ አስተሳሰብን የማይወክልና የሰውን ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህርይ የጣሰ ተግባር ነው፡፡

ይህንን አስነዋሪ ግፍ ክርስቲያኖችና የሌላ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘውና ሊጸየፈው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የፈጸሙት ተግባር በራሳቸው ላይ ቢፈጸምና በጤናማ ሥነ ልቦና ቢያዩት ኖሮ በወጣቶቻችን ላይ በፈጸሙት ተግባር ልክ እንኳ ቢከፈላቸው እንደማይበቃ አድርገው በራሳቸው ላይ ይፈርዱ ነበር፡፡

ዛሬ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ለሚመስሉት ወገኖቹ ሕይወት፣ ምቾትና ሰላም ደፋ ቀና በሚልበት ዓለም ከሰው የተፈጠሩ የማይመስሉ አረመኔዎች ክቡር የሆነ የሰውን ልጅ ነፍስ ኢሰብኣዊ በሆነ መንገድ ሲቀጥፉ መታየት ምን የሚሉት እምነት ነው?

ይህን አስነዋሪና ከሰው ተራ የሚያወጣቸውን ተግባርስ የወጣቶቹ ወላጆች ሳይቀሩ ዓለም ሁሉ በሚመለከተው ሚዲያ ማሳየት ምን የሚሉት ጭካኔ ነው?

የሰውን ልጅ የቀድሞ ታሪክ አጥፈቶ አዲስ የግፍና የኢሰብኣዊነት ታሪክ ለመሥራት መጣጣርስ ምን የሚሉት አስተሳሰብ ነው?

ስለዚህ አይ ኤስን ጨምሮ በሰብአዊ ፍጡር ሉዓላዊ ክብር ላይ የተቃጣ የአሸባሪነት ወንጀል ያልምንም ቅድመ ሁኔታ ከምድራችን ሊወገድ የሚገባው እኩይ ግብር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ራሳቸውን አይ ኤስ ብለው የሚጠሩት አሸባሪዎች ከዕውቀትና ከሃይማናት የወጡ፣ የልማትና የሰው ልጅ ሰላማዊ ሕይወት ሥጋቶች የሆኑ ቡድኖች በመሆናቸው ዓለም በአንድነት ተባብሮ ሊያቆማቸው ይገባል፣

ምናልባት ቡድኑን በገንዘብና በልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት ካሉም የጥፋት ተባባሪ ከመሆን ሊታቀቡ ይገባል፣

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ለፈጸሙት ወንጀል በነፍሳቸውና በኅሊናቸው ከሚመጣባቸው ዘለዓለማዊ ፍርድ ይድኑ ዘንድ ንሥሓ እንዲገቡ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ቀደም ሲል እንደገለጽነው በመንፈሳዊ ሕይወት ከምናገኘው ዋጋ ሁሉ የሰማዕትነት ዋጋ ተወዳዳሪ የለውም፣

በፍትሕ መንፈሳዊ ወሰማእታትሰ እሉ እሙንቱ ዘይቤ ክርስቶስ በእንቲሆሙ ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አእምኖ በቅድመ አቡነ ዘበሰማያት፣ ወለእመተሳተፍክምዎሙ በጊዜ ኅዘናቲሆሙ ይከውን ለክሙ ስምዕ በእንተ ጻሕቀ ኅሊናክሙ፡፡

ሰማዕታት ማለት እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏቸው ስለ ቁርጥ ሓሳባችሁ ሰማዕትነት ይቆጠርላችኋል፡፡ የተባለላቸው ናቸው፤

ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው ታማኞች ለመድኅኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደማቅ ምስክሮች ናቸው፤

ሰማዕታት በቅዱሳት መጻሕፍት ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፤(ማቴ 10*28) የሚለውን ቃል ተቀብለው ምርጫቸው እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ ያሳዩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡

ሰማዕታት የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው በተባለው መሠረት የመንግሥተ ሰማያትን የክብር አክሊል በጥበብ ጀምረው በደማቸው ምስክርነት የተቀዳጁ ናቸው፡፡

ክብራቸውም አቡቀለምሲስ ዮሐንስ በራእዩ ምዕ 20 ቁጥር 4 ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእርሱ ላይ ለተቀመጡትም ዳኝነት ተሰጣቸው፣ ስለኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቆረጡባቸውን ሰዎችአየሁ ብሎ እንደተናገረው በእግዚአብሔር መንግሥት የማያልፍ አክሊልና የፍርድ ዙፋን የተዘጋጀላቸው ናቸው፡፡

ስለዚህ የእነዚህ ወጣቶች ልጆቻችን ቤተሰቦች የሰማዕታት ቤተሰቦች በመሆናችሁ ልትጽናኑ ይገባል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በደሙ የመሠረታት ወልደ እግዚአብሔር የልጆቿን ነፍስ በክብር እንዲቀበል ትጸልያለች፡፡
ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻችንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች መጽናናትና ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻችንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምንና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች መጽናናትና ብርታትን ይስጥልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ 
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

‹‹ልጆቻችን፣ ማዕተቤን አልበጥስም፤ ወደ ሌላ አንለወጥም አሉ፤ በሰማዕትነታቸው ልንጽናናባቸው ልንማርባቸው እና ልናወድሳቸው ይገባል›› – የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የማጽናኛ ቃለ ምዕዳን



the martyr daniel hadush
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን
፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይችላልን? ልጆቻችን የምንኮራባቸው መጻሕፍቶቻችን፣ የምንማርባቸው ዩኒቨርስቲዎቻችን ናቸው፤ አስተምረውናል፤ አኩርተውናል፤ አስከብረውናል››
(ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)His Grace Abune Lukas
የልጆቻን የኃይለ ሚካኤል(ኢያሱ ይኵኖ አምላክ) እና የኃይለ ኢየሱስን(ባልቻ በለጠ) ነፍስ ይማርልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የሐዘን ዳርቻ ያድርግልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የቤተሰቡን ሕይወት፣ የቤተሰቡን ሐዘን በመልካም ነገር፣ በፍቅር ነገር ይለውጥልን፡፡ ቤተሰቡን ያለምልምልን፡፡ ቤተሰቡን ያጽናልን፡፡ ደግ ያልኾኑ ሰዎችን ወደ ደግነት፣ ወደ ምሕረት፣ ወደ ቸርነት ይመልስልን፡፡ ለዓለሙ ኹሉ ሰላም መረጋጋትን ያድልልን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያን በክብር በረድኤት ይጠብቅልን፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
የውድ ልጆቻችን የሰማዕታቱ፣ የታማኝ ልጆቻችን፣ የጀግኖች ልጆቻችን፣ በኢትዮጵያዊ ባህላቸው፣ በኢትዮጵያዊ ትውፊታቸው፣ በእምነታቸው፣ በሥርዐታቸው፣ በወጋቸው ጸንተው፣ ለማንም ሳይበገሩ እና ለማንም ሳይደለሉ፣ ለሌላ እጃቸውን ሳይሰጡ፣ ሳይቀለበሱ ጀግንነትን ያስተማሩ ልጆቻችን፣ መጻሕፍት የኾኑ ልጆቻችን ወላጆች እና እዚኽ የተሰበሰባችኹ ውድ ወገኖቼ፤
ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰባት መቶ ዓመታት ቀድሞ የነበረው ነቢዩ ኤርሚያስ፣ በዚያን ጊዜዋ ባቢሎን በዛሬዋ ኢራቅ፤ በዚያን ጊዜዋ ፋርስ በዛሬዋ ኢራን እየዘዋወረ ባስተማረበት ዘመን ስለ ኢትዮጵያውን አድናቆት፣ ክብር፣ ጀግንነት፣ አይበገሬነት በትንቢቱ ምዕራፍ 13 ቁጥር 23 ላይ እንዲኽ ብሏል፡- ‹‹ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይችላልን?››
ኢትዮጵያዊ ባህሉን፣ ኢትዮጵያዊ እምነቱን፣ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ጀግንነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ትውፊቱን በሌላ ሊቀይር ይችላልን? አይቀየርም፡፡ ነቢዩ ሠቆቃው ኤርሚያስ በተባለ መጽሐፉም ይህን በስፋት እየገለጸ ይናገራል፡፡
libyan martyrs compiledውድ ወገኖቼ፤ ልጆቻችን እኮ ጀግኖች ናቸው፤ ልጆቻችን እኮ እጃቸውን አልሰጡም፤ ልጆቻችን እኮ አልተንበረከኩም፤ ልጆቻችን እኮ መጻሕፍቶቻችን ናቸው፤ ልጆቻችን እኮ አርበኞቻችን ናቸው፤ አልተማረኩም፤ የጀግና እናት አታለቅስም እንደተባለው ኹሉ፣ እናንተም የጀግኖች እናቶች ናችኹ፤ ልትኮሩ ይገባችኋል፤ ስማቸውን ለውጠው፣ ሃይማኖታቸውን ለውጠው፣ ሥርዐታቸውን ለውጠው፣ ተማርከው ቢኾን ኖሮ ነበር ማልቀስ የሚገባን፡፡
ውድ ወገኖቼ፤ የጀግኖች ወላጆች ናችኹና ልትኮሩ፣ ልትጽናኑ ይገባችኋል፡፡ እሰይ ልጄ፤ ተባረክ ልጄ፤ ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃኽ ብላችኹ ልትመርቁ፣ ልትጸልዩ፣ ልትጽናኑ ይገባል፡፡ የመጽናኛ ዕለት ነው፤ ልጆቻችን አስተምረውናል፤ ልጆቻችን አኩርተውናል፤ ልጆቻችን አስከብረውናል፤ አስወድደውናል፤ በዓለም ደረጃ አገራችንን አስተዋውቀዋል፡፡
ውድ ወገኖቼ፤ እንዲኽ ላሉት ነው እንዴ የሚለቀሰው? አገር አጥፍቶ ለሔደ፣ በሙስና ተዘፍቆ ለሔደ፣ ሰክሮ ለሔደ፣ አመንዝሮ ለሔደ፣ ቀምቶ ለሔደ÷ ‹‹በምድር ኑሮው ተበላሽቶ፣ በሰማይ እንዴት ይኾን ከቶ›› ተብሎ የሚለቀስለት ለዚኽ ነው፡፡ ብዙ ልጆቻችን በየመልኩ ኸሉም አርበኛ ነው፡፡ አካሉን፣ ሕይወቱን፣ ወላጁን፣ ልጁን፣ ዘመኑን፣ ንብረቱን የሰጠ ስንት አለውድ ወገኖቼ፤ እንዴ፣ እነዚኽማ ልጆቻችን የምንኮራባቸው መጻሕፍቶቻችን ናቸው!! የምንማርባቸው ዩኒቨርስቲዎቻችን ናቸው ልጆቻችን!! ብርሃናችን ናቸው ልጆቻችን!! ማዕተቤን አልበጥስም፤ ወደ ሌላ አንለወጥም፤ አንበገርም አሉ፤ ይኼ ነው ወይ የሚያስለቅሰው? የሚለቀስበትን ነገር እንወቅ እንጂ!
ውድ ወገኖቼ፤ ስለዚኽ ልጆቻችንን በሰማዕትነታቸው፣ በጀግንነታቸው ልናከብራቸው፣ ልንማርባቸው፣ ምሳሌአቸውን ልንወስድ፣ ልናወድሳቸው ይገባል፡፡ ስለዚኽ ይኼ የመረጋጋት፣ የሰላም‹ የፍቅር ቦታ ነው፡፡ ልጆቻችን የአገር ፍቅር፣ የአገር ሰላም፣ የአገር አንድነት አስተምረውናል፡፡ በልጆቻችን ተምረናል፤ ጠግበናል፤ ረክተናል፤ ኮርተናል፡፡
የልጆቻችንን ነፍስ በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያሳርፍልን፤ ይማርልን፤ ወላጆቻቸውን ይጠብቅልን፤ ከክፉ ነገር ይሰውረን፤ መልካሙን ነገር ያምጣልን፤ ልጆቻችንና ወገኖቻችንን በሰላም ወደ ቤታቸው ይመልስልን፡፡   ኹላችንም ተጽናንተን የሚያኮራ ሥራ እንድንሠራ ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡ ነፍሰ ገብሩ ኃይለ ኢየሱስ፣ ኃይለ ሚካኤል ሀገረ ሕይወትን መንግሥተ ሰማያትን ያውርስልን፡፡
*       *       *
‹‹ወገኖቻችን ሰማዕታት፣ ታሪክ አትርፈው ስለሔዱ ለዘላለም ስማቸውና ሥራቸው ሲወሳ ይኖራል››
(ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፤ የወላይታ ኮንታ እና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)
His Grace Abune Mathewosአኹን ያለንበት አካባቢ ቤተ መቅደሱ [ደብረ ፍሥሓ መካነ ሰማዕት]ቂርቆስ ነው፡፡ እንደምታውቁት ቂርቆስ ሕፃን ነው፡፡ በምን መልክ እንደ ዐረፈ ታውቃላችኹ፡፡ ሕፃኑ ቂርቆስ፣ ዓላውያን ነገሥታት በእኛ እምነት እመን፤ እኛ የምናዝዝኽን ፈጽም ባሉት ሰዓት አልተቀበላቸውም፡፡ እሳት ነደደ፤ በበርሜል ውስጥ ውኃ ፈላ፡፡ በዚኽ ሰዓት እናቱ ደንግጣ ወደ ፈላው ውኃ ለመግባት ስትፈራ ሕፃኑ ቂርቆስ፣ ‹‹እናቴ ጨክኚ፤ ዛሬ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ቀን ነው፡፡ አባቶቻችን በሰጡን፣ ባወረሱን፣ ባስተማሩን እምነት ጸንተን ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ነውና ከዓላዊው ንጉሥ አትፍሪ›› ብሎ እናቱን ወደ እሳት የጋበዘ ነው፡፡ እስከ መጨረሻው እስከ ዘላለሙ ሰማዕቱ ቂርቆስ ሲባል ይኖራል፤ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል፤ ታሪክ አይደመሰስም፡፡
አኹንም እነዚኽ ወንድሞቻችን፣ ወገኖቻችን ሰማዕታት የታሪክ ባለቤቶች ስለኾኑ፣ ታሪክ አትርፈው ስለሔዱ ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት ኹሉ ለዘላለም ስማቸው፣ ሥራቸው ሲወሳ ይኖራል፡፡ ሐዘን ኹልጊዜ ሲያነሡት ልብ ይሠቀጥጣል፡፡ ይኼን እያነሡ መናገር በጣም ይከብዳል፡፡ ጭንቅላት ሊሸከመው አይችልም፡፡ እናም እዚኽ ያሉትን እያጽናናችኹ፣ እዚያ የቀሩት ደግሞ በሰላም እንዲወጡ ምሕላ እያደረግን ልንጸልይ ይገባል፡፡ እኛ እዚኽ ፀሐይ እየሞቅን፣ እየተነጋገርን እናዝለን፤ እዚያ እነርሱ ከወጡበት ሰውነታቸው አልቆ ነፍሳቸው የምትጨነቅ አለችና በሰላም እንዲያወጣቸው ላለፉት ብቻ ሳይኾን ለቀሩትም ጸሎት እያደረጋችኹ በዚኽ እንድትጽናኑ ነው አደራ የምንለው፡፡
ወላጆች ወለዱ እንጂ የኹላችን ልጆች ናቸው፤ ሐዘኑ የኢትዮጵያ ነው፤ እግዚአብሔር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጽናቱን ይስጥልን፡፡ እዚያ የቀሩትንም በሰላም ያውጣልን፡፡
their graces the archbishops condoling the mournersስድስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዘካናዳ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፤ ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በደብረ ፍሥሓ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ሰበካ ተገኝተው የመስተጋድላን ሰማዕታትን ኢያሱ ይኵኖ አምላክ እና ባልቻ በለጠ ቤተ ሰዎች እና ወዳጆች ያጽናኑበት ቃለ ምዕዳን

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...