2016 ጃንዋሪ 16, ቅዳሜ

ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ .ሕዝ.36› 25 -33

                                                                         

                                  
ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ  ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ ጥሩ ውሃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ ከርኩሰታችሁ ሁሉ ከጣዖቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለሁ  አዲስ ልብ እስጣችኋለሁ አዲሰ መንፈስ በወስጣችሁ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ  መንፈሴን በወስጣችሁ አኖራልሁ .......
ነቢያት በተሰጣቸው ፀጋ  መሠረት ያለፈውንና   የሚመጣውን   ትንቢት የመናገር  ኃብት ተሰጥቶአቸዋል
ነቢዩ  ሕዝቅኤልም ከላይ እንደተጠቀሰው   ስለ ጥምቀት ተናግሮአ ፤  እስቲ !ኃይለ ቃሉን  በዝርዝር እንየው
        1 . ጥሩ ውሃ ምንድነው?
ውሃን  እግዚአብሔር  ሲፈጥረው  ለበጎ ነገር የሰው ልጅ  እንዲጠቀምበት አድርጎ ፈጥሮታል ። ለመጀመሪያ ጊዜ የእግዚአብሔርም  መንፈስ ያደረው በውኃ ላይ ነው ። የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር ። ዘፍ .1  ፤ 2   ይሁን እንጂ  የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን እየጣሰ ሲመጣ ለሰው ልጅ መጠቀሚያ  የነበርው ሁሉ  መጥፊያም መሆን ጀመረ ።  በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ  በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል ። ዘፍ .6  ፣ 18  ተብሎ ተጽፎአል
ታዲያ ውኃ ከምሥጢረ ጥምቀት ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት  ለምሥጢረ ጥምቀት በሚገባ  ቋንቋ  ነቢዩ ሕዝኤል ገልፆታ።
  ጥሩ ውኃ  ሲል የጠራ፣ ንጹህ የሆነ ውኃን  እረጭባችኋለሁ ማለቱ ጌታ በወንጌል  ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› ብሎ እንደተናገረው ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር መሆኑን ተገልፆለት ተናግሮታል ፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ይህውም ተግባራዊ የሚሆነው በውኃ ነው።ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የምስጢረ  ጥምቀት አመጣጥ  የተገለጸው በውኃ ነው። አማናዊውን ጥምቀት በሐዲስ ኪዳን የጀመረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ግልጽ መሆኑ ቢታወቅም ከዚያ በፊት ግን በብዙ ምሳሌ ይታወቅ ነበረ።አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 1417/
v  ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡
v  ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ 2ነገ. 514 ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡
v   የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 613 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችንኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ፡፡›› /1ጴጥ. 320/
v   እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ /ዘፀ. 1415/ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው›› /1ቆሮ. 101/
v   ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 179/ ‹‹በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል፡፡›› /ቈላ. 211/
                                             ጥምቀት ለምን?
                 1.የእግዚአብሔርን ልጅነት ለማግኘት
ከላይ በመነሻ ላይ እንደተገለጸው  “ ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ” የሚለው ኃይለ ቃል  የሚገልጸው ከሌሎች በጥምቀት ኃብተ ወልድና ሥመ ክርስትና ከሌላቸው ሰዎች መለየትን ነው  ። ”ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን “ ሮሜ .8 ፤ 17  ስለዚህ የመጠመቃቸን አንዱ ምክንያትም ሆነ ጥቅም የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን  ከሌሎች መለየት ነው ። ልጆች ደግሞ ስለሆን ገድልን  ከነቅድስናው  በረከተ ሥጋ ወነፍስን  ለመውረስ  ያስችላል።
              2. አገረ ሕይወት መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ
ከየአገሩም  ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ” የሰው ልጅ ከፈጣሪው በኃጢያት ምክንያት  ከተለየ በኋላ ያልተስተካከል የተዘበራረቀ ያልተረጋጋ  ጭንቀት የበዛበት እና የተበታተነ ሕይወት በመኖር 5500 ዘመናትን አሳልፎአል  ወተትና ማር የምታፈስ ገነትን ያህል  ቦታ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ አጥቷል ። ይሁን እንጂ ወደ ቀደመው ቦታችን ለመመለስ  ያቺን የሕይወት አገር ለመውረስ እንችል ዘንድ የተሰጠን ልዩ ስጦታ ጥምቀት ነው ። በጥምቀት የተበታተን ሕይyanወታችን ይሰበሰባል ወደቀደመ አገራችን እንመለሳለንና ነቢዩ ከየአገሩም  ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ” በማለት ተናገረ። ጥምቀት የምናገኘውን ፀጋ  ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “ በጥምቀት ከርሱ ጋር ተቀብራችሁ ፤ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ” ቆላ. 2 ፤ 12 ትንሣኤ ዘለክብርን አግኝቶ መንግስተ ሰማያትን መውረስ የሚቻለው በጥምቀት ነው። ‘’ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።እንዲል.  ሕዝ. 36 ፤ 28
                                                     3. አዲስ ሕይወት ለማግኘት
ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ  በቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ላይ እንደገለጠው “ ሰው እንደ አዲስ ጨርቅ ነው አዲስ ጨርቅ አዲስ እንደሆነ ሁሉ  አሮጌ ደግሞ ይሆናል ። ሁለቱ ነገሮች በሰው ሕይወት ላይ ይፈራረቃል ። ክፋትና በጎነት ፤ ኃጢአትና ጽድቅ ፤ ቂመኛነት እና ይቅርባይነት ፤ ለጋስነት እና ንፉግነት  በአጠቃላይ የሥጋና የመንፈስ  ፈቃዳት በሰው  ልጆች ሕይወት ላይ ይሟገታሉ ። በአንጻሩ የመንፈስ ፈቃዳትን ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ እና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ለመሆን አዲስ ሕይወት ያስፈልጋል ። ይህውም በጥምቀት  የሚገኘው በጥምቀት ነው። “ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአበሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?........... የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፡ ያውም እናንተ ናችሁ። 
1.ቆሮ .3፤16
አዲስ ሕይወት ያልው ሰው አዲስ መንፈስ፤ አዲስ ልብም ይኖረዋል ። ለበጎ ሥራ የሚነሳሳ የይቅርታ ፤’ የሰላም’፤ የፍቅር ልብ የሚኖረው አዲስ ሕይወት ሲኖረን ነው ። ያን ጊዜ “ የድንጋዩንም ልብ  ከሥጋችሁ አወጣለሁ »  ተብሎ እንደተጻፈው  ክፉ ሐሳብ እና ተግባር ሁሉ ከሰው ይወገዳል ። የድንጋይ ልብ ያለው ሰው ጨካኝ  የማይጸጸት ለሰው የማይራራ ይሆናል። አሁን በዘመናችን የምናየውና የምንሰማው ይህንኑ ነው። ‘’ የሥጋንም  ልብ እሰጣችኋለሁ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ ......... መልካም ያይደለውን ሥራችሁን  ታስባላችሁ ስለ በደላችሁና ስለ ርኩሰታችሁም ራሳችሁንም ትጸየፋላችሁ። ሕዝ.36 ፤ 32  በምድር ላይ ያለው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔ ፍጥረት እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም ። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የሚቻለው በጥምቀት ነው ።” አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነትን መንፍስ  ተቀበላችሁ እንጂ  እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና  የእግዚአብሔር ልጆች  መሆናችንን  ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ .8 ፤ 15  ልጆች ሲያጠፉ  ወይኔ! አባቴ ፤ እናቴ ይቆጡኛል  ይፈራል እንጂ ሌላ ሰው አይፈራም  አባትም ከሌሎቹ ልጆች ለይቶ ልጁን ይቆጣጠራል  የሚያስፈልገውን ሁሉ ያሟላለታል።  እግዚአብሔርም ለኛ ለልጆችሁ እንዲሁ ነው ።  አሁን እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎችም ሆይ ! በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል  እስኪ ፍረዱ ፡ ለወይኔ ያላደረኩለት ከዚኦህ ሌላ አደረግለት ዘንድ የሚገባኝ መንድንው?   ኢሳ፤ 5 ፤ 3  የሚሰጠንም ፀጋ ከልጅነታችን አንፃር ነው ብዙ ነገር ስለተደረገልን ብዙ ነገር ደግሞ ይጠበቅብናል ።
በአጠቃላይ  ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች የጥምቀት በዓል ሲከበር ብቻ የሚታወሱ አይደሉም ነገር ግን በየዓመቱ በዓልትን ስናከብር መሠረታዊ የሆኑ የድኅንት መንገዶችን ማክበር  ትኩረት ሰጥቶ ማስታወስ  ይገባል ። ይልቁንም በዓላትን በስደት ሀገር ሆኖ ሲከበር ደግሞ ሥርዓተ ሃይማኖቱን ጠብቆ በጎ የሆነውን ባህላችንንና አለባበሳችን ሳይቀር ሳንተው ያለንበትን ሀገር ሀገራችን አድርገን ማክበር ይገባል።
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን !
                              
                                       ከሰሜን አውሮፓ  ፊንላንድ
            

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...