2016 ጃንዋሪ 16, ቅዳሜ

ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ .ሕዝ.36› 25 -33

                                                                         

                                  
ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ  ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ ጥሩ ውሃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ ከርኩሰታችሁ ሁሉ ከጣዖቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለሁ  አዲስ ልብ እስጣችኋለሁ አዲሰ መንፈስ በወስጣችሁ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ  መንፈሴን በወስጣችሁ አኖራልሁ .......
ነቢያት በተሰጣቸው ፀጋ  መሠረት ያለፈውንና   የሚመጣውን   ትንቢት የመናገር  ኃብት ተሰጥቶአቸዋል
ነቢዩ  ሕዝቅኤልም ከላይ እንደተጠቀሰው   ስለ ጥምቀት ተናግሮአ ፤  እስቲ !ኃይለ ቃሉን  በዝርዝር እንየው
        1 . ጥሩ ውሃ ምንድነው?
ውሃን  እግዚአብሔር  ሲፈጥረው  ለበጎ ነገር የሰው ልጅ  እንዲጠቀምበት አድርጎ ፈጥሮታል ። ለመጀመሪያ ጊዜ የእግዚአብሔርም  መንፈስ ያደረው በውኃ ላይ ነው ። የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር ። ዘፍ .1  ፤ 2   ይሁን እንጂ  የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን እየጣሰ ሲመጣ ለሰው ልጅ መጠቀሚያ  የነበርው ሁሉ  መጥፊያም መሆን ጀመረ ።  በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ  በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል ። ዘፍ .6  ፣ 18  ተብሎ ተጽፎአል
ታዲያ ውኃ ከምሥጢረ ጥምቀት ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት  ለምሥጢረ ጥምቀት በሚገባ  ቋንቋ  ነቢዩ ሕዝኤል ገልፆታ።
  ጥሩ ውኃ  ሲል የጠራ፣ ንጹህ የሆነ ውኃን  እረጭባችኋለሁ ማለቱ ጌታ በወንጌል  ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› ብሎ እንደተናገረው ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር መሆኑን ተገልፆለት ተናግሮታል ፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ይህውም ተግባራዊ የሚሆነው በውኃ ነው።ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የምስጢረ  ጥምቀት አመጣጥ  የተገለጸው በውኃ ነው። አማናዊውን ጥምቀት በሐዲስ ኪዳን የጀመረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ግልጽ መሆኑ ቢታወቅም ከዚያ በፊት ግን በብዙ ምሳሌ ይታወቅ ነበረ።አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 1417/
v  ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡
v  ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ 2ነገ. 514 ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡
v   የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 613 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችንኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ፡፡›› /1ጴጥ. 320/
v   እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ /ዘፀ. 1415/ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው›› /1ቆሮ. 101/
v   ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 179/ ‹‹በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል፡፡›› /ቈላ. 211/
                                             ጥምቀት ለምን?
                 1.የእግዚአብሔርን ልጅነት ለማግኘት
ከላይ በመነሻ ላይ እንደተገለጸው  “ ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ” የሚለው ኃይለ ቃል  የሚገልጸው ከሌሎች በጥምቀት ኃብተ ወልድና ሥመ ክርስትና ከሌላቸው ሰዎች መለየትን ነው  ። ”ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን “ ሮሜ .8 ፤ 17  ስለዚህ የመጠመቃቸን አንዱ ምክንያትም ሆነ ጥቅም የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን  ከሌሎች መለየት ነው ። ልጆች ደግሞ ስለሆን ገድልን  ከነቅድስናው  በረከተ ሥጋ ወነፍስን  ለመውረስ  ያስችላል።
              2. አገረ ሕይወት መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ
ከየአገሩም  ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ” የሰው ልጅ ከፈጣሪው በኃጢያት ምክንያት  ከተለየ በኋላ ያልተስተካከል የተዘበራረቀ ያልተረጋጋ  ጭንቀት የበዛበት እና የተበታተነ ሕይወት በመኖር 5500 ዘመናትን አሳልፎአል  ወተትና ማር የምታፈስ ገነትን ያህል  ቦታ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ አጥቷል ። ይሁን እንጂ ወደ ቀደመው ቦታችን ለመመለስ  ያቺን የሕይወት አገር ለመውረስ እንችል ዘንድ የተሰጠን ልዩ ስጦታ ጥምቀት ነው ። በጥምቀት የተበታተን ሕይyanወታችን ይሰበሰባል ወደቀደመ አገራችን እንመለሳለንና ነቢዩ ከየአገሩም  ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ” በማለት ተናገረ። ጥምቀት የምናገኘውን ፀጋ  ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “ በጥምቀት ከርሱ ጋር ተቀብራችሁ ፤ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ” ቆላ. 2 ፤ 12 ትንሣኤ ዘለክብርን አግኝቶ መንግስተ ሰማያትን መውረስ የሚቻለው በጥምቀት ነው። ‘’ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።እንዲል.  ሕዝ. 36 ፤ 28
                                                     3. አዲስ ሕይወት ለማግኘት
ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ  በቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ላይ እንደገለጠው “ ሰው እንደ አዲስ ጨርቅ ነው አዲስ ጨርቅ አዲስ እንደሆነ ሁሉ  አሮጌ ደግሞ ይሆናል ። ሁለቱ ነገሮች በሰው ሕይወት ላይ ይፈራረቃል ። ክፋትና በጎነት ፤ ኃጢአትና ጽድቅ ፤ ቂመኛነት እና ይቅርባይነት ፤ ለጋስነት እና ንፉግነት  በአጠቃላይ የሥጋና የመንፈስ  ፈቃዳት በሰው  ልጆች ሕይወት ላይ ይሟገታሉ ። በአንጻሩ የመንፈስ ፈቃዳትን ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ እና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ለመሆን አዲስ ሕይወት ያስፈልጋል ። ይህውም በጥምቀት  የሚገኘው በጥምቀት ነው። “ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአበሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?........... የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፡ ያውም እናንተ ናችሁ። 
1.ቆሮ .3፤16
አዲስ ሕይወት ያልው ሰው አዲስ መንፈስ፤ አዲስ ልብም ይኖረዋል ። ለበጎ ሥራ የሚነሳሳ የይቅርታ ፤’ የሰላም’፤ የፍቅር ልብ የሚኖረው አዲስ ሕይወት ሲኖረን ነው ። ያን ጊዜ “ የድንጋዩንም ልብ  ከሥጋችሁ አወጣለሁ »  ተብሎ እንደተጻፈው  ክፉ ሐሳብ እና ተግባር ሁሉ ከሰው ይወገዳል ። የድንጋይ ልብ ያለው ሰው ጨካኝ  የማይጸጸት ለሰው የማይራራ ይሆናል። አሁን በዘመናችን የምናየውና የምንሰማው ይህንኑ ነው። ‘’ የሥጋንም  ልብ እሰጣችኋለሁ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ ......... መልካም ያይደለውን ሥራችሁን  ታስባላችሁ ስለ በደላችሁና ስለ ርኩሰታችሁም ራሳችሁንም ትጸየፋላችሁ። ሕዝ.36 ፤ 32  በምድር ላይ ያለው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔ ፍጥረት እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም ። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የሚቻለው በጥምቀት ነው ።” አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነትን መንፍስ  ተቀበላችሁ እንጂ  እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና  የእግዚአብሔር ልጆች  መሆናችንን  ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ .8 ፤ 15  ልጆች ሲያጠፉ  ወይኔ! አባቴ ፤ እናቴ ይቆጡኛል  ይፈራል እንጂ ሌላ ሰው አይፈራም  አባትም ከሌሎቹ ልጆች ለይቶ ልጁን ይቆጣጠራል  የሚያስፈልገውን ሁሉ ያሟላለታል።  እግዚአብሔርም ለኛ ለልጆችሁ እንዲሁ ነው ።  አሁን እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎችም ሆይ ! በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል  እስኪ ፍረዱ ፡ ለወይኔ ያላደረኩለት ከዚኦህ ሌላ አደረግለት ዘንድ የሚገባኝ መንድንው?   ኢሳ፤ 5 ፤ 3  የሚሰጠንም ፀጋ ከልጅነታችን አንፃር ነው ብዙ ነገር ስለተደረገልን ብዙ ነገር ደግሞ ይጠበቅብናል ።
በአጠቃላይ  ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች የጥምቀት በዓል ሲከበር ብቻ የሚታወሱ አይደሉም ነገር ግን በየዓመቱ በዓልትን ስናከብር መሠረታዊ የሆኑ የድኅንት መንገዶችን ማክበር  ትኩረት ሰጥቶ ማስታወስ  ይገባል ። ይልቁንም በዓላትን በስደት ሀገር ሆኖ ሲከበር ደግሞ ሥርዓተ ሃይማኖቱን ጠብቆ በጎ የሆነውን ባህላችንንና አለባበሳችን ሳይቀር ሳንተው ያለንበትን ሀገር ሀገራችን አድርገን ማክበር ይገባል።
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን !
                              
                                       ከሰሜን አውሮፓ  ፊንላንድ
            

ገድለ ቅዱስ ጳውሎስ ወገድለ ቅዱስ ሰራባሞን: ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የተመለሰበት “የስጦታ ውል” እያወዛገበ ነው



  • ዩኒቨርስቲው ያዘጋጀው ውል የደብረ ሊባኖስ ገዳምን የባለቤትነት መብት ይነፍጋል
  • ኢጣልያ የአኵስም ሐውልትን የባለቤትነት ድርሻ ለመውሰድ የጠየቀችውን ይመስላል
  • ከዩኒቨርስቲ ጋር የተፈራረሙት የገዳሙ ፀባቴ(አስተዳዳሪ) ከሥራቸው ታግደው ነበር
  • ፓትርያርኩ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትቀበለው ውል እንዲዘጋጅ መመሪያ ሰጥተዋል
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፴፭፤ ቅዳሜ ጥር ፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)
Publication1
“እውነት እና አገልግሎት”
 (Truth and Service) ተቋማዊ ብሂሉ እና መፈክሩ ነው፡፡ በተለይ፣ ለጥቁሮች በሚሰጠው የከፍተኛ ትምህርት ዕድል እና አስተምሮ በሚያወጣቸው ጥቁር ምሁራን ብዛት ይታወቃል – መቀመጫውን በሰሜን ምዕራብ ዋሽንግተን 
ያደረገውና የ150 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው የአሜሪካው ሐዋርድ ዩኒቨርስቲ፡፡
የዘር እና የቀለም ልዩነቶች፣ ፖሊቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ በደሎች ያስከተሏቸውን መድልዎች፤ ለማኅበራዊ ፍትሕ በቆሙ እና ለሰብአዊ ነፃነት በሚሟገቱ ምሁራን ማስወገድ ዓላማው ያደረገው ዩኒቨርስቲው፤ በአፍሪካ፣ በአሜሪካ እና በሌላውም ዓለም የተበተኑ ጥቁሮችን የታሪክ እና የባህል ቅርሶች ያካበተበት የምርምር ማዕከሉም ከዓለም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ያደርገዋል፡፡
በየአጋጣሚው ያሰባሰባቸውን ቅርሶች እና ውርሶች፣ ወደ ጥንት ቦታቸው እና ለትክክለኛ ባለቤቶቻቸው በሕጋዊ መንገድ መመለስ፣“ታሪካዊ እና ባህላዊ ሀብቶቹን ማክበር ነው፤” ይላሉ፣ የዩኒቨርስቲው የሥነ መለኰት ት/ቤት የአካዳሚያዊ ጉዳዮች ተባባሪ ዲን ዶ/ር ጋይ ባይረን፡፡ በተለይም ኢትዮጵያዊ ቅርሶችን ለኢትዮጵያ የመመለስ ጉዳይ፣ የት/ቤቱ የቆየ ተምኔት እንደነበርና ይህም በአሜሪካም ሆነ በሌላው ዓለም ቅርሶቹን በግልና በተቋም ለያዙ ግለሰቦች፣ ሙዝየሞች እና ተቋማት አርያኣነት እንዳለውና ተነሣሽነትንም እንደሚፈጥር ዶ/ር ባይረን አስረድተዋል፡፡
Gädlä Särabamon
ገድለ ቅዱስ ጳውሎስ ወገድለ ቅዱስ ሰራባሞን
በት/ቤቱ ማኅደረ ቅርስ ከተከማቹት ኢትዮጵያዊ የብራና ሥነ ጽሑፍ ሀብቶች መካከል፣ ገድለ ቅዱስ ጳውሎስ እና ገድለ ቅዱስ ሰራባሞን አንዱ ነው፡፡ በመለዮ ቁጥር Tweed MS150 የተመዘገበው የብራና መጽሐፉ፣ በ1993 ዓ.ም. ዶ/ር አንድሬ ቲውድ ከተባሉ የዩኒቨርስቲው የቀድሞው ተማሪ በስጦታ የተበረከተ ሲኾን የ4ኛው መ/ክ/ዘመኑን ሰማዕት ቅዱስ ሰራባሞንና የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ገድል በ240 ቅጠሎች አካትቶ የያዘ ወጥ ጥራዝ ነው፡፡ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ ከብዙ መጻሕፍት ጋር በ15ኛው መ/ክ/ዘ መጥቶ ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመውም፤ በዘጠነኛው የደብረ ሊባኖስ ዕጨጌ አባ መርሐ ክርስቶስ አስተዳደር(ከ1456-1490 ዓ.ም.) ነበር፡፡
Dr. Amsalu Tefera
ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ
በጀርመን – ሙኒክ ዩኒቨርስቲ የጥንታዊ ድርሳናት ተመራማሪው ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ፥ የቅዱሱ ገድል ከነተኣምራቱ በሙሉ ይዘቱ የሚገኘው ከዐረብኛው ይልቅ በግእዙ ትርጉም እንደኾነ፣ ከሦስት ዓመት በፊት በሜኒሶታ ቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርስቲ ጋባዥነት ባደረጉት ጥናት አረጋግጠዋል፡፡ ከ10ሺሕ በላይ የብራና መጻሕፍት ቅጂዎችን በመያዝ ከዓለም ቀዳሚ በኾነው በዩኒቨርሲቲው ተዘጋጅቶ በነበረ ወርክሾፕ ላይ፣ “Gädlä Särabamon: The Case of the Ethiopic Version”በሚል ርእስ በሐምሌ 2006 ዓ.ም. ባቀረቡት ጥናታቸው፥ ገድለ ሰራባሞን ወጳውሎስ በተለይ እስከ 4ኛው መ/ክ/ዘ በነበረን አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዕውቀት ላይ ብዙ ነገሮችን ግልጽ ያደርግልናል፤ የቅብጥ፣ የጽርዕ፣ የዐረብኛ ቃላትና ስያሜዎችም በብዛት ስለሚገኙበት ለጥናት እና ለምርምር ሥራ በእጅጉ ይረዳል፤ በማለት ፋይዳውን አስረድተዋል – የሥነ ድርሳን ተመራማሪው ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ፡፡
በሐዋርድ ዩኒቨርስቲ የጥንተ ክርስትና እና የሐዲስ ኪዳን ምሁሩ ዶ/ር ባይረን፣ የብራና መጽሐፉን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች በመሰነድ(digitization) የትመጣውን ለማወቅ ጥናት ካደረጉት የሥነ መለኰት ት/ቤቱ ምሁራን አንዱ እንደነበሩ፣ የዩኒቨርስቲው ድረ ገጽ ዘግቧል፤ የገድሉ ጥንተ ባለቤት የደብረ ሊባኖስ ገዳም መሆኑ የታወቀውና ወደ ጥንት ቦታው ለመመለስ የተወሰነውም የገድሉ ይዘት እና መዘርዝር ሲጠና በነበረበት ሒደት (cataloguing) እንደነበር በዘገባው ተገልጧል፡፡ ከገድሉ ይዞታ ጋር በተያያዘ አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ አካሔዶችን ጨምሮ የተለያዩ ዕንቅፋቶች ዩኒቨርስቲውን ሲያጋጥሙት፣ ድረ ገጹ በጥናቱ የተሳተፉ ምሁራንን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ዩኒቨርስቲው ገድሉን ወደ ጥንት ቦታው በሕጋዊ መንገድ ለመመለስ በማሰብ፣ በሕግ አማካሪው አርቃቂነት “የስጦታ ውል”(Deed of Gift) የተሰኘ እና በስምንት ነጥቦች የተዘረዘረ የስምምነት ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ ውሉ በሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ እና በደብረ ሊባኖስ ገዳም መካከል የተፈጸመ መኾኑን የሚገልጸው ሰነዱ፤ በሥነ መለኰት ት/ቤቱ ዋና ዲን ዶ/ር አልተን ፖላርድ ሣልሳዊ እና በገዳሙ ፀባቴ (አስተዳዳሪ) አባ ወልደ ማርያም አድማሱ እንደተፈረመበት ተጠቁሟል፡፡ ይኹንና የውሉ ይዘት እና አፈጻጸሙ ከባለቤትነት መብት እና ከቅርሱ አመላለስ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሣ ኾኖ ተገኝቷል፤ ይላሉ የዜናው ምንጮች፡፡
ዩኒቨርስቲው÷ “ከማናቸውም ግዴታ ነፃ የሆነ የባለቤትነት መብት በብራና መጽሐፉ ላይ አለው” የሚለው የውሉ መግቢያ፣ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚመልሰውም “በስጦታ ለመስጠት በመፈለጉ” እንደኾነ ይገልጻል፤ የብራና መጽሐፉን ለገዳሙ በስጦታ የሚሰጥበት የባለቤትነት መብት እንዳለውም ገዳሙ መስማማቱን የሚጠቅሰው ውሉ፣ ገዳሙም የብራና መጽሐፉን ሲቀበል፣ ዩኒቨርስቲው ሙሉ በሙሉ የሚያስተላልፈው፣ “አካላዊ የባለቤትነት መብት”ን እንደሆነ አስፍሯል፡፡ ገዳሙን በመወከል በሓላፊነት የፈረሙትም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውል ስምምነቱን እንድታከብር የሚያደርግ ዋስትና የመስጠት ሥልጣን እንዳላቸው በውል ሰነዱ ላይ አመልክቷል፡፡
HOWARD Univ delegates
የብራና መጽሐፉን ያስረከቡት የሥነ መለኰት ት/ቤቱ ልኡካን
ባለፈው ሰኞ፣ የሥነ መለኰት ት/ቤቱን ዲን ጨምሮ ስድስት ልኡካንን የያዘው የዩኒቨርስቲው ሓላፊዎች እና ምሁራን በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ተገኝተው ገድለ ቅዱስ ጳውሎስ ወገድለ ቅዱስ ሰራባሞን ለገዳሙ ባስረከቡበት ወቅት፣ በግልጽ የተነሡት ተቃውሞዎች እና ስጋቶች፣ ፀባቴው(አስተዳዳሪው) ከዩኒቨርስቲው ጋር የተፈራረሙት ሰነድ፣ የገድሉን ባለቤትነት ለገዳሙ ሳይኾን ለዩኒቨርስቲው አሳልፎ መስጠቱን አረጋግጠዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው ገድሉን ወደ ጥንት ቦታው መመለሱን ቤተ ክርስቲያኒቱ በከፍተኛ አድናቆት እንደምትመለከተውና እንደሚያስደስታት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተናግረዋል፡፡ “ጥንታዊው ብራና ቅርሳችን በመሆኑ ብንቀበለውም ስምምነቱ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ የባለቤትነት መብት የሚጎዳ፣ በትውልዱም ዘንድ የሚያስነቅፍ በመኾኑ ተቀባይነት የለውም፤” ሲሉ ይዘቱን ተቃውመዋል፡፡ የውል ሰነዱም፣ በልዩ ጽ/ቤታቸው፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የውጭ ግንኙነት መምሪያ፣ በሕግ አገልግሎቱ እና በቅርሳቅርስ ጥበቃ መምሪያ በጋራ ታይቶ ዳግመኛ እንዲዘጋጅም ፓትርያርኩ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኝበትን የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት በሊቀ ጳጳስነት የሚመሩት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በበኩላቸው፣ የቅርሱ መመለስ የኹላችን ደስታ ቢኾንም የተመሰለበት ሒደት ግን የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓትና መዋቅር እንዲኹም የገዳሙን ክብር እንዳልጠበቀ ገልጸዋል፡፡ ሦስተኛ ወገን በማስገባት በአስተዳዳሪው እና በዩኒቨርስቲው የተፈረመውን ስምምነት÷ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ሊቀ ጳጳሱ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ቅዱስ ሲኖዶሱ ሳያውቁትና ሳይመረምሩት ሕጋዊ የባለቤትነት መብትን በሚያሳጣ መልኩ መፈጸሙን ብፁዕነታቸው አስረድተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና እና መዋቅር በመጣስ “ለመታየት እና ለመግነን” ሲባልየተፈጸመው ድርጊት አግባብ ያለመኾኑን በርክክቡ ወቅት በመናገራቸውም፣ “እዚያች ገዳም ትኖራታለኽ፤ እንተያያለን፤ የፈለከውን ሹምበት”በሚል በገዳሙ አስተዳዳሪ መዘለፋቸው ተጠቅሷል፡፡
ከዚኹ ጋር በተያያዘ የገዳሙ አስተዳዳሪ፣ ባለፈው ረቡዕ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ÷ ከሥራ፣ ከደመወዝ እና ከአገልግሎት ታግደው እንደነበር ታውቋል፡፡ ከትላንት በስቲያ 15 ያኽል የገዳሙን ማኅበረ መነኰሳት አስከትለው በመምጣት በፓትርያርኩ ፊት በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ እግር ላይ በመውደቅ ይቅርታ በመጠየቃቸው ዕርቀ ሰላም አውርደዋል፡፡ ይኹንና “ተጠሪነቴ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ነው” በሚል ያለሥልጣናቸው ከዩኒቨርስቲው ጋር ፈጽመውታል የተባለው ስምምነት፣ በገድለ ጳውሎስ ሰራባሞን የባለቤትነት ድርሻ ላይ ያስነሣቸው ስጋቶች እና ተቃውሞዎች ግን መቋጫ ሳይገኙ በእንጥልጥል ላይ ይገኛሉ፡፡
በማይክሮፊልም በተነሣው የሜኒሶታው ቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ የግእዙ ቅጂ ላይ ጥናት ያካሔዱት ዶ/ር አምሳሉ፣ በገድለ ሰራባሞን ወጳውሎስ ላይ ምርምሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፣ አመላለሱን መነሻ በማድረግ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ማስታወሻ ያሳስባሉ – “ታሪኩ በጣም የሚመስጥ ተጋድሎውም የሚደነቅ ነው፤ ለጥንት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አጥኚዎች ትልቅ ትምህርት እናገኝበታለን፤ በውጭ አገሮች በኮፕቲክ፣ በዐረብኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዝኛ ጥናቶች አሉ፤ በኢትዮጵያውያን ግን እምብዛም አይታወቅም፤” ይላሉ የምርምሩን አስፈላጊነት ሲያስረዱ፡፡
ፈቃደ እግዚአብሔር ኾኖ ገድሉ ወደ አማርኛ መተርጎሙን ተመራማሪው በማስታወሻቸው ጠቅሰዋል፡፡ ከሰማዕቱ ዜና ሕይወት እና ዜና ተጋድሎ ባሻገር ነገረ ክርስቶስን የሚከበውንና በዘመኑ ለተነሡት እንደ አርዮስ ላሉ መናፍቃን ምላሽ የሚሰጠውን ገድል ኹላችንም ብናነበው እንባረክበታለን፤ በሰማዕቱ የገድል ጽናት እንበረታበታለንም፤ ብለዋል፡፡ ዶ/ር አምሳሉ አያይዘውም፣ የሐዋርድ ሰዎችም በነካ እጃቸው የቀሩትን የብራና መጻሕፍት ቢመልሷቸው የሚል ማሳሰቢያ ማቅረብ ቀጣዩ ሥራ መኾን እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በዩኒቨርስቲውና በገዳሙ ፀባቴ ተፈርሟል በተባለው ስምምነት፣ የባለቤትነት መብቷን አሳልፋ ሰጥታ መልሳ በስጦታ መልክ የምትቀበልበት አንዳችም ምክንያት እንደለሌና ዩኒቨርሲቲውም ፍላጎት እንዳልኾነ የመስኩ ባለሞያዎች ጠቁመዋል፡፡ በዚኽ ዓይነቱ ስምምነት የባለቤትነት ድርሻን አሳልፎ መስጠት፤ ፋሽስት ኢጣልያ በጦርነት የዘረፈችውንና በሮም ዐደባባይ አቁማው የነበረውን ታሪካዊውን የአኵስም ሐውልት ለኢትዮጵያ በመለሰች ጊዜ፣ “የባለቤትነቱን ድርሻ ልውሰድ” በማለት በቅድመ ኹኔታ ካቀረበችው ጥያቄ ጋር አመሳስለውታል፤ ኾኖም ግን ጥያቄው እውነታን መሠረት ያላደረገ በመኾኑ፣ ኢትዮጵያ የባለቤትነት መብቷ ተረጋግጦ ታሪካዊው ሐውልታችን ወደ ጥንተ ሀገሩ ተመልሶ በቀደመ ቦታው መተከሉን ተሟጋቾቹ ባለሞያዎች አስታውሰዋል፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ቅርሱን ለሕጋዊ ባለቤቱ ያስረከበው፣ የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የሥነ መለኰት ት/ቤቱን ዲን ጨምሮ ስድስት አባላት ያሉት ልኡክ ለኹለት ሳምንታት ቆይታ በኢትዮጵያ ይገኛል፡፡ ዲኑ ዶ/ር ፖላርድ፣ ጉዟቸውን ታሪካዊ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊም እንደኾነ ያስረዳሉ – “መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤”(መዝ. 68÷31) የሚለውን በስፋት የሚታወቅ የመዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ኃይለ ቃል መሠረት በማድረግ፡፡
“እኛም እጆቻችን ወደ እግዚአብሔር መዘርጋታችንን አናቋርጥም፤ ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን እጆቻችንን መዘርጋታችን በእጅጉ አስደስቶናል፤” ብለዋል፤ ገድለ ሰራባሞን ወገድለ ጳውሎስን ወደ ጥንት ቦታውና ለትክክለኛው ባለቤቱ መመለሳቸው (the restitution of Debre Libanos Monastery’s manuscript) ሐሤት እንዳሳደረባቸው ሲገልጹ፡፡ ሒደቱን በቅርበት የሚከታተሉት ባለሞያዎች እንዲያውም፣ “የስጦታ ውሉ” የቀሰቀሰውን ቁጣና ያስነሣውን ውዝግብ የተረዱት የዩኒቨርሲቲው ዋና ዲን፣ የአካዳሚ ጉዳዮች ተባባሪ ዲንና ሌላ ምሁር ውሉን እንደተቃወሙትና በዚኹም ሳቢያ ዩኒቨርሲቲው የሕግ አማካሪውን ሳያሰናብት እንዳልቀረ ይናገራሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በበኩሏ፣ “የስጦታ ውል” ሰነዱን እንደምትቃወመው ለዩኒቨርሲቲው በይፋ በማሳወቅ፣ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ ሕጋዊ ባለቤትነቷን (the rightful owner of the manuscript)፣ የሚያረጋግጥ ተቀባይነት ያለው ስምምነት እንዲዘጋጅ ጥያቄ ማቅረብ እንዳለባት በአጽንዖት መክረዋል፡፡ ይህን ማድረጓም የአሜሪካንና የአውሮፓን ዩኒቨርሲቲዎች ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት ባጣበቡትና ባደመቁት እልፍ ቅርሶቿ ቀጣይ አመላለስ ላይ የራሱ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ ብለዋል፡፡
*               *               *
ጥቂት ስለ ቅዱስ ሰራባሞን እና የሰማዕትነት ገድሉ
ቅዱስ ሰራባሞን ማን ነው?
St. Serabamon
በሥጋ ልደት ከሰማዕቱ እስጢፋኖስ ጋር ዝምድና አለው። ይህንም ራሱ ሰራባሞን በገድሉ ውስጥ ደጋግሞ ይናገራል – መልካም ዘር ከነአገዳው ቸር እንዲሉ። እርሱ የተነሣበት ዘመን ክርስቲያን መኾን እንደ ወንጀል የሚቆጠርበት ዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ነበር፡፡ እርሱ ግን ከይሁዲነት (ቤተሰቦቹ አይሁድ ነበሩ) ወደ ክርስትና በፍቅር የመጣ ነው።
የቅዱሱ የመጀመሪያ ስም ስምዖን ነበር። ሰራባሞን ብሎ የሰየመው የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቴዎናስ ነው። ሰራባሞን፡ ማለትም “ውሉድ፡ በሃይማኖተ፡ አበው፡ ንጹሐን።” ማለት ነው። የተወለደው በእስራኤል ሲኾን የተጠመቀውና በጵጵስና ተሾሞ ያገለገለው፣ በኋላም ሰማዕትነትን የተቀበለው በግብፅ አገር ነው። ሰራባሞን ወደ ኢትዮጵያ በአካል አልመጣም። ገድሉ ከግብፅ መጥቶ ወደ ግእዝ ተተርጉሟል።
ትምህርቱ እና ቅድስናው
ቅዱስ ሰራባሞን፣ ለእመቤታችን የተለየ ፍቅር ስለነበረው በጉዞው ኹሉ ትመራውና ተገልጻም ታናግረው ነበር። የኒቅዩስ ሊቀ ጳጳስ ኾኖ ከመሾሙም በፊት እንዲኹም በኋላ ስለ ነገረ መለኰት፣ ስለ ነገረ ትስብእት፣ ስለ ነገረ ማርያም ትምህርቶችን እጅግ ጠሊቅ ትምህርቶችን አስተምሯል። ርእሰ መናፍቃን በመባል የሚታወቀውን አርዮስን የተከራከረ እና በጉባኤ ኒቅያ ከመወገዙ በፊት (መሊጦስንም ጭምር) ቀድሞ ያወገዘ ነው።
በቅድስናው የተነሳ ሀብተ ትንቢት ያደረበት ጻድቅ ነበር። ቀድሞ ከተናገራቸው እና በኋላ ከተፈጸሙት መካከል ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው፤
፩ኛ) 17ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት እንደሚሞትና “ተፍጻሜተ ሰማዕት” እንደሚኾን እንዲህ ብሎ ተንብዮ ነበር፤“….ወበከመ፡ ኮነ፡ ጴጥሮስ፡ ቀዳማየ፡ እምሐዋርያት፡ ከማሁ፡ አንተኒ፡ ትከውን፡ ተፍጻሜተ፡ ሰማዕት፨ ናሁ፡ አቅደምኩ፡ ነጊሮተከ፡ ዘይከውን፡ በጊዜሁ።” በዚኽም መሠረት ፓትርያርኩ ተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ እ.ኤ.አ. በ313 ዓ.ም. የሰማዕትነትን ክብር ተቀዳጅቷል።
፪ኛው) በሰራባሞን ላይ ብዙ መከራ ያደረሰበትን የአንፀናው ሀገረ ገዢ አርያኖስን በወቅቱ የጠላውን ክርስቶስን በኋላ እንደሚያምነው፣ ክርስቲያንም ኾኖ በሰማዕትነት እንደሚሞት ትንቢት ተናግሮ ነበር። ቃሉም እንዲህ ይላል፤ “….ወእንዘ ይወፅእ፡ ቅዱስ፡ ሰራባሞን፡ እምኀበ፡ መኰንን ተነበየ፡ ላዕሌሁ፡ እንዘ፡ ይብል፡ አርያኖስ፡ አርያኖስ፡ ሀለወከ፡ ትትኰነን፡ በእንተ፡ ስሙ፡ ለክርስቶስ፨….”፤ እጅግ የሚገርም ነው። ይህ አርያኖስ በትንቢቱ መሠረት ከመሞቱ በፊት ክርስቲያን ኾኖ፣ ያረፈውም በሰማዕትነት ሲኾን ስለ ክብሩ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን እንዲኹም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪኩ በስንክሳር (መጋቢት 8) ይዘከራል።
ዕረፍቱ
በገድሉ እንደምናነበው፣ የቅዱስ ሰራባሞን ሕይወት ያለፈው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰይፍ ተቀልቶ ነው። በሰማዕትነት ያረፈውም ኅዳር 28 ቀን ነው (በቅብጢ በሐቱር 28) ነው። በረከቱ ይድረሰን።
ገድለ ሰራባሞን
ደጋግመን እየተናገርንለት ያለው ገድለ ሰራባሞን፣ በመጀመሪያ የተጻፈው በቅብጢ (Coptic) ቋንቋ ሲኾን የጻፈውም በዘመኑ የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ረድእ የነበረውና በኋላ ግን የእስክንድርያ ፓትርያርክ በነበረው እለእስክንድሮስ (እ.ኤ.አ. ከ313-326 ዓ.ም.) ነው። የቅብጢ ቋንቋ እየተዳከመ ሲመጣና በዐረብኛ ሲተካ እንደ አብዛኞቹ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ይኸው ገድለ ሰራባሞንም ወደ ልሳነ ዐረቢ ተመለሰ።
መጽሐፉ (ብራናው) ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ወደ ግእዝ ቋንቋ የተተረጎመው፣ የደብረ ሊባኖስ ዘጠነኛ ዕጨጌ በነበሩትና ከ1456-1490 ዓ.ም. ገዳሙን ባስተዳደሩት በብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ዘመን (1401-1490 ዓ.ም.) ነው፡፡
መጽሐፉ ከያዛቸው ገድላት መካከል የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ገድል በስፋት የሚታወቅ ሲኾን ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ከገድለ ሐዋርያት ጋር አብሮ ተጠንቶ ወደ እንግሊዝኛም ተተርጉሟል። ገድለ ሰራባሞን ግን እንኳንስ በሕዝቡ ዘንድ በካህናቱም ዘንድ እምብዛም አይታወቅም።
የገድሉ ይዘት
የሰማዕቱን ዜና ሕይወት እና ዜና ተጋድሎ በኹለት ክፍሎች ይዘረዝራል። በዘመኑ ለነበሩ መናፍቃን የተሰጠ ምላሽን ይዟል፤ ነገረ ክርስቶስ ዋናው ማእከሉ ነው። በቅዱስ ሰራባሞን የተፈጸሙ ተኣምራትን ይዘረዝራል።
ገድሉ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። የመጀመሪያው፣ የቤተ ክርስቲያናችን ዕድሜ ጠገብ ሀብት ስለኾነ ቅርሳችን ነው። ሌላውና የሚገርመው በአሁኑ ሰዓት በግብጽ ሙሉው ገድሉ ተሟልቶ አይገኝም። የተወሰነ ክፍል በቅብጢ፣ የተወሰነው ደግሞ በዐረብኛ ነው። ሙሉው ገድሉ ከነተኣምራቱ የሚገኘው በግእዙ ነው። ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ይህን ጠብቀው ማቆየታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ በእኛም ዘመን አጥተነው ታሪክ ሊወቅሰን ነበር፤ በመጨረሻ የጻድቁ ፈቃድ ኾኖ ከወቀሳ ተረፍን፣ ቅርሱም ተመለሰ።
እስከ አኹን በነበረን የአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ (በተለይ የጥንቱ እስከ 4ኛው መ/ክ/ዘ) ዕውቀታችን ላይ ብዙ ነጥብ ይጨምርልናል፤ ብዙ ነጥቦችንም ግልጥ ያደርግልናል።
ለጥናትና ለምርምር ሥራ በእጅጉ ይረዳል። በግእዙ ገድለ ሰራባሞን ላይ የሚገኙ የቅብጥ፣ የጽርዕ፣ የዐረብኛ ቃላትና ስያሜዎች በብዛት ስለሚገኙበት ለጥናት ይጋብዛል።
ምንጭ ከዶ/ር አምሳሉ ተፈራ የፌስቡክ ገጽ የተገኘ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...