2015 ፌብሩዋሪ 17, ማክሰኞ

የዘወረደ ምንባብ (ዕብ.13÷7-17)


አትምኢሜይል
የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም የሚኖር እርሱ ነውና፡፡

 ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያአልተጠቀሙምና፡፡ ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤ ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር፡፡

ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ፡፡ አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን÷ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ፡፡ በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም የምትመጣውን እንሻለን እንጂ፡፡ በውኑ እንግዲህ በሰሙ አናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡


 (ያዕ.4÷6 )
ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡


 (ሐዋ.25÷13- ) 
ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡ በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው÷ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ፡፡ በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ፡፡ አኔም፡- ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም÷ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው፡፡

ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ÷ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ፡፡ የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ÷ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው÷ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤ ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት፡፡” አግሪጳም ፊስጦስን÷ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወደለሁ” አለው፤ ፊስጦስም÷ “እንግደያስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው፡፡


በማግሥቱም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጡ፤ ከመሳፍንቱና ከከተማው ታላላቅ ሰዎች ጋርም ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ፊስጦስም እንዲህ አለ÷ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ÷ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ወንድሞቻችን ሁላችሁ÷ ስሙ፤ አይሁድ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው በኢየሩሳሌምም ሆነ በዚህ እየጮሁ የለመኑኝ ይህ የምታዩት ሰው እነሆ፡፡ እኔ ግን ለሞት የሚያደርሰው በደል እንዳልሠራ እጅግ መርምሬ÷ እርሱም ራሱ ወደ ቄሣር ይግባኝ ማለትን ስለወደደ እንግዲህ ልልከው ቈርጫለሁ፡፡ ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የታወቀ ነገር የለኝም፡፡ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን አገኝ ዘንድ ወደ እናንተ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ ወደ አንተ አመጣሁት፡፡ የበደሉ ደብዳበቤ ሳይኖር እስረኛን ወደ ንጉሥ መላክ አይገባምና፤ ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል፡፡”



ነፍስና ሥጋ የውል ስምምነት ተፈራረሙ

አትምኢሜይል


የካቲት 10ቀን 2007ዓ.ም. 
በመ/ርት ጸደቀወርቅ አሥራት
ነፍስና ሥጋ እንደከዚህ በፊቱ ለሚጠብቃቸው ከባድ የሥራ ኃላፊነትና አለመግባባት የውል ስምምነት ተፈራረሙ። የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት በዚህ ሣምንት የገባውን የዐቢይ ፆም ምክንያት በማድረግ ነው።

በውሉ ሥነ ሥርዐት ላይ ነፍስ እንደገለጸችው ከዚህ በፊት በአጽዋማት ጊዜ በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ውሉ ጠቃሚነቱ የጎላ ነው። ባለፉት ዓመታት ሥጋ የአጽዋማትን ወቅት ጠብቆ ነፍስ ተገቢውን ድርሻ እንዳትወጣ እንቅፋት እየሆነ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸው ስምምነቱ በመካከላችው ሰላም እንዲሰፍን ምክንያት ይሆናል ያሉን በስምምነቱ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት የነፍስ አባት ናቸው።
ከፊርማው ሥነ ሥርዐት በኋላ ባነጋገርነው ወቅት ስምምነቱን ተቀብሎ የነፍስን ሥራ ሳይቃወም ሊገዛላት መዘጋጀቱን ሥጋም ቢሆን አልሸሸገም። በሥነ ሥርዐቱ ላይ የተገኙት ሌሎች ምዕመናንም ሥጋን በቃልህ ያጽናህ እያሉ ከስብሰባው አዳራሽ ሲወጡ እንደተሰሙ “ሪፖርተራችን” ዘግቦልናል።

2015 ጃንዋሪ 27, ማክሰኞ

እመቤቴ ማርያም ሆይ፤ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል፡፡ መልክአ ማርያም





በዲያቆን ንጋቱ አበበ

 ቅዱሳን ሐዋርያት፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእነርሱ በመለየቷ ፈጽመው ያዝኑ ነበር። ከእለታት በአንዱ ቀን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ተገለጠላቸውና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሚያዩ ተስፋ ሰጣቸው። በዚያን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን እየሰበከ፤ እያስተማረ፤ ሕዝበ ክርስቲያንን እያጽናና እስያ በምትባል ሃገር ነበር። ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ተነጥቆ፤ ተድላና ደስታ ከሰፈነባት ቦታ ወደ ገነት ሄደ። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት አናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሯት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው። ቅድሳን መላእክቱም
እንደታዘዙት አደረጉ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ወጣ። ጌታችንም

እንዲህ እያለ አረጋጋት። የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘለዓለማዊ ወደ ሆነ መንግስተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነይ። ያን ጊዜ በገነት ያሉ ዕፅዋት በሙሉ አዘነበሉ ሰገዱ። ቅዱሳን መላእክትም፤ ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ አያመሰገኗት እያወደሷት በእልልታ ወደ ሰማይ አሳረጓት። ቅዱስ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ። ቅዱሳን ሐዋርያትም ተሰብስበው ሳለ፤ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እረፍት ፈጽመው እያዘኑ እየተከዙ ሳለ አገኛቸው። እርሱም እንዳየና እንደሰማ፤ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው። ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስም አንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ። ፈጽመው እያዘኑ ሳሉ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ሥለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን አብዝታችሁ ታዝናላችሁ? እነሆ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባል አላቸው። ይህንንም ብሎ ከእርሳቸው ዘንድ ወደ ሰማያት አረገ። ቅዱሳን ሐዋርያትም አመት ሙሉ ቆዩ። የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት፤ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አላቸው። አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሳየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባኤ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው። በልጇ በወዳጇ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በሷ ደስ እንዲለን። በዚያን ጊዜም ቅዱስ ዮሐንስ እንዳላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ ወር መጀመሪያ እስከ 16ተኛው ቀን ድረስ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ። ሱባኤ በያዙ በአስራ ስድስተኛው ቀንም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጇ ተቀምጣ፤ ከሥጋዋ ተዋሕዳ፤ ተነስታ እመቤታችንን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ ቅዱሳን ሐዋርያትን ባረከቻቸው። እነርሱም ፈጽመው ተደሰቱ። ጌታችንም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ሆነ። ቅዱስ እስጢፋኖስም አዘጋጀ። ቅዱስ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ። ሁሉም ቅዱሳን ሐዋርያት በመሰዊያው ዙርያ ቆሙ። በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ። ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። ከዚያም በሱራፌልና በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት። በዚህች ቀን የሆነ የእርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችስ ቅዱሳን ሐዋርያትን እዘዣቸው። መታሰቢያሽን የሚያደርግ ሁሉ ተጠብቆም በዚህች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም። መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ፤ በዚህች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት በቸርነቴ እጎበኘዋለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇን ወዳጇን ጌታችንን እንዲህ አለችው። ልጄ ሆይ እነሆ በአይኖቻቸው አዩ፤ በጀሮቻቸውም ሰሙ፤ በእጆቻቸውም ዳሰሱ ሌሎች ታላላቅ ድንቅ ተአምራትንና ሥራዎችን አዩ ብላ ከነገረችው በኋላ ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ።
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ምዕመናን ሆይ የፈጣሪን እናት የ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በፍጹም ደስታና በመልካም ምግባር መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለ እኛ ወደ ተወደደ ልጇ ሁልጊዜ ትማልዳለችና።
ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን
በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን። በረከቷ፤ ፍቅሯ፤ ጣዕሟ በእኛ በልጆቿ ላይ አድሮ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመሞቷ በፊት በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበር። መንፈስ ቅዱስም ለእመቤታችን ከዚህ ዓለም እንደምትለይ ነገራት። ጌታችንም በደብረ ዘይት ላሉ ደናግላን ነግሯቸዋልና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጥነት መጡ። እርሷን መንፈስ ቅዱስ የነገራትን ነገረቻቸው።

           በዲያቆን ንጋቱ አበበ


እነሱም እንደመጡ ባየች ጊዜ እንዲህ ብላ ጸለየች። ልጄ ውዳጄ፤ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናየን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚህች ሰዓት አምጣው፤ እንዲሁም በሕይወት ያሉትንና በሕይወት የተለዩንን ቅዱሳን በሙሉ ወደ እኔም አምጣቸው። አንተ የሕያዋን አምላክ ነህና፤ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን አለች። በዚያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ቅዱስ ዮሐንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደረሰችው። ቅዱስ ዮሐንስም እንደደረሰ ሰገደላትና በፊቷ ቆሞ እንዲህ አላት፤ ሰላምታ ይገባሻል ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልደሽልናልና፤ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። አንቺ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ትሄጃለሽና። እመቤታችንም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እንዲህ ብላ አምላኳንም አመሰገነችው። ጌታዬ አምላኬ ፈጣሪዬ ሆይ፤ ላንተ ክብር ምስጋና ይገባል። የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና። አሁንም ነብሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊይሳርጓት ከሚመጡ መላእክቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ። በዚህን ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ድምጽ መጣ፤ እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ። ቅዱሳን ሐዋርያትም ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ይደርሳሉ። ቅዱሳን ሐዋርያት ከዚህ ዓለም የተለዩትም፤ በሕይወት ያሉትም ሁሉ በአንድነት መጥተው ለእመቤታችን ሰገዱላት። እነርሱም አመሰገኗት እንዲህም አሏት። ጸጋን የተመላሽ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይብልሽ ፈጣሪያችን ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከእርሱ ጋር ያሳርግሻልና አሏት። በዚህን ጊዜ እመቤታችን በአልጋዋ ላይ ተቀመጠች። ቅዱሳን ሐዋርያትንም እንዲህ አለቻቸው። ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እኔ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን አወኩ። ከዚህ ከሥጋዬ ወጥቼ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እሔዳለሁ። ነገር ግን እናንተ እኔ ከዚህ ዓለም እንደምለይ ማን ነገራችሁ? አወቃችሁ? ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱሳን ሐዋርያት በሙሉ ወደ አንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን፤ መጣን አሏት። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ይን ነገር ከቅዱሳን ሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ አምላኳን አመሰገነች። እንዲህም አለች ከ እንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል። ይህን ብላ እንደጨረሰች እጣን አምጥታችሁ በማጠን የፈጣሪዬን ስም ጥሩት አለቻቸው። እነሱም እንደታዘዙት አደረጉ። በዚህን ጊዜ ጌታችን ተገልጾ ብዙ ድንቅ ተአምራትን አደረገ። በሽተኞች ወደ እመቤታችን ወደ አለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌአቸው ይፈወሱ ነበር። እመቤታችን ከሥጋዋ የምትለይበት ሰዓት ሲደርስ ቅዱሳን ሐዋርያትንና ደናግልን ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት። እመቤታችንም እጇን ዘርግታ ባረከቻቸው። በዚህን ጊዜ ፈጣሪያችን ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጎናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከ እርሱ ጋር አሳረጋት። ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው፤ ወደ ጌቴ ሰማኒ ተሸክመው እንዲወስዷ ሐዋርያትን አዘዛቸው። ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃን እያየች ነበር። እመቤታችንም ፈጣሪዋን ልጇን ወዳጇን እንዲህ ብላ ጠየቀችው። ልመናየን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ። በስሜ ወደ አንተ የሚለምነውን ሁሉ፤ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወደ አንተ የሚለምነውን ከመከራም ሁሉ አድነው፤ በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሃሊ ነህና መታሰቢያየን በውስጧ የሚያደርጉባትን የሁሉንም መስዋእታቸውን ተቀበል። ፈጣሪም እንዲህ ብሎ መለሰላት። የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ። እመቤታችንም ከአረፈች በኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴ ሰማኒ ሊወስዷት ሐዋርይት ገንዘው ተሸከሟት። አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊይቃጥሉ መጡ። ከ እነርሱም አንዱ ከምድር ይጥላት ዘንድ ይእመቤታችንን አልጋዋን ያዘ። ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በአልጋው ላይ ጠንጠለጠሉ። ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ እያለ ለመነ። የ እውነተኛ አምላክ ይጌታ ኢይሱስ ክርስቶስ እናት አንቺ በ እውነት ድንግል ይሆንሽ በ እኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ አለምንሻለሁ። በሐዋርይትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደህና ሆኑ። እመቤታችን በቀብሯት ጊዜ ከዚያ ሶስት ቀን ኖሩ እረፍቷም የነበረው እሁድ ቀን ጥር 21 ነብር። ጌታችንም ብርሃናውይን መላእክትን ልኮ ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሯት። ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲያሳርጓት እመቤታችንን አገኟት ። መላእክትም ለአምላክ እናት ለ እመቤታችን ድንግል ማርይም ና እጅ ንሳ አሉት እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከ እርሷም ተባረከ ከዚህም በኋላ ወደ ሐዋርያት ደረሰ። እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንደ አረፈችና እንደ ቀበሯትም ነገሩት። ቅዱስ ቶማስም ሥጋዋን እስከ ማይ አላምንም አላቸው። ሥጋውንም ይሳዩት ዘንድ ወደ መቃብሯት በአደረሱት ጊዜ ከመቃብሩ ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችን እንዳገኛት ነገራቸው። ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የ እመቤታችንን ዕርገቷን ኡ ስላላዩ እጅግ አዘኑ ሥጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው። ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ሰጣቸው። እነርሱም በተስፋ እስከ ነሐሴ 16 ቀን በተስፋ ኖሩ። የ እመቤታችንም የእድሜዋ ዘመን 64 ዓመት ነው። በአባትና በእናቷ ቤት 3 ዓመት፤ በመቅደስም 12 ዓመት፤ በዮሴፍም ቤት 34 ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ ዕርገት በኋላ በወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ቤት 14 ዓመት ነው። 

ይቆየን…………….

የሕይወት የድህነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
 
የእመቤታችን በረከቷ ረድ ኤቷ ይደርብን አሜን!!!

2015 ጃንዋሪ 10, ቅዳሜ

የታክሲ ሾፌሮች፤ ረዳቶችና ተራ አስከባሪዎች ጉባኤ 8ኛ ዓመት ተከበረ


አትም ኢሜይል
ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም.
በደመላሽ ኃይለ ማርያም
የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ለታክሲ ሹፌሮች፣ ተራ አስከባሪዎችና ረዳቶቻቸው አገልግሎት እንዲሰጥ የመሠረተውን ጉባኤ 8ኛ ዓመት አስመልክቶ ታኅሣሥ 25 እና 26 ቀን 2007 ዓ.ም. “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ” በሚል የመጽሐፍ ቅዱስ መሪ ቃል በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ አባላቱና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ተከበረ፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብሩ አስተዳዳሪ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ ሲሆን፤ የታክሲ አገልግሎት ሥራን በሚመለከት ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር አያይዘው “ኖላዊ” በሚል ርዕስ በተጋባዥ መምህራን ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡

የታክሲ ሹፌሮች፣ ረዳቶቻቸው እና ተራ አስከባሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን በጎ ያልሆነ ግንኙነት ለማሻሻል እና በክርስትና ሕይወታቸው ምሳሌ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍራት እንዲቻል፤ እንዲሁም በእነሱ ቸልተኝነት እና ጥድፊያ በመኪና አደጋ እየጠፋ ያለውን የሰውን ሕይወት ለመቀነስ ታስቦ ጉባኤው መመስረቱን የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ ዲያቆን ያሬድ ያስረዳል፡፡

ዲያቆን ያሬድ አክሎም “የአባላቱን ቁጥር ከዚህ የበለጠ በማሳደግና በጉባኤው ውስጥ በማካተት ትምህርተ ሃይማኖት እንዲማሩ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊት እንዲያውቁ፤ በሥነ ምግባር የታነጹና ሥርዓት አክባሪዎች ሆነው ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ ከፈጣሪ ጋር እንጥራለን” ብሏል፡፡

ከተጋባዥ እንግዶች መካከልም የአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ም/ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ድንገተኛ፤ ለንስሐ እና ለኑዛዜ የማያበቃውን በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት ለመከላከል ምእመናን እና የታክሲ ሹፌሮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጪው ዓመት ሃምሳኛ ዓመቱን የሚያከብረው ይህ የፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት እየሠራ ያለው ሥራ እጅግ በጣም ሊበረታታ የሚገባውና በሌሎችም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሊለመድና ሊሰራበት እንደሚገባ ጉባኤውን የተከታተሉ ምእመናን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

2015 ጃንዋሪ 9, ዓርብ

አባቶችና ምእመናን ‹‹ሸኚው ሸኚ ሲያጣ›› እስኪሉ ድረስ በመጣደፉ በእጅጉ ያዘኑበት የ106 ዓመት አረጋዊው የብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ



funeral of Abune Aregawi
ፎቶ: ማኅበረ ቅዱሳን

ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ አቡነ አረጋዊ

ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በ1901 ዓ.ም. ወልደው በፀለምት /ሰሜን ጎንደር/ ተወልደው ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት ቤት ገብተው ንባብና ዳዊት እንዲኹም እስከ ፀዋትወ ዜማ አጠናቅቀው ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ማዕርገ ዲቁናና ማዕርገ ቅስና ተቀብለዋል፡፡
በዋልድባ አብረንታንት ገዳም ገብተው ለዘጠኝ ዓመታት ያኽል (ከ1933 – 42 ዓ.ም.) ሥርዓተ ገዳሙን ከአጠኑና በግብዝና ከአገለገሉ በኋላ በዚኹ ገዳም መዓርገ ምንኵስናን ተቀብለዋል፡፡ ትምህርታቸውን በመቀጠል በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በሚገኘው በደብረ ዓባይ ገዳም የደብረ ዓባይ መዝገበ ቅዳሴ ዜማ ተምረው በመምህርነት በቅተዋል፡፡
በ1943 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ፈቃድና ትእዛዝ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትን እንዲያገለግሉ ተልከው ለአራት ዓመታት ያኽል አገልግለዋል፡፡ አኹንም በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ ወደ ግብጽ ሔደው ለ16 ዓመታት ያኽል ነገረ መለኰትን በዓረብኛ ቋንቋ አጥንተው ተመርቀዋል፡፡funeral of Aba Aregawi 
ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በሓላፊነት ለማገልገል ተልከው ለስድስት ዓመታት ያኽል በአስተዳዳሪነት ሠርተዋል፡፡ በዚኹ ሓላፊነት ሳሉም በ1968   ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ኹነው በተሾሙ ጊዜ በሱዳን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በመምጣት ለበዓሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
በ1972 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት በመኾን አገልግለዋል፡፡
በጥቅምት ወር 1983 ዓ.ም. በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ኾነው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ ተሾመዋል፡፡
ከመጋቢት 1985 ዓ.ም. ጀምሮ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ለአንድ ዓመት ያኽል ሠርተዋል፡፡
ከየካቲት 1986 ዓ.ም. ጀምሮ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳምና ት/ቤት የበላይ ሓላፊ ኾነው አገልግለዋል፡፡
ከሐምሌ 1968 ዓ.ም. ጀምሮ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው አገልግለዋል፡፡
ከግንቦት 1992 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ሓላፊ ኾነው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም በዚኹ ሥራ ላይ ሳሉ ባደረባቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በተወለዱ በ106 ዓመታቸው ከዚኽ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡
funeral of Aba Aregawi03
የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም በዚኹ ዕለት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበትና የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ሥርዓተ ጸሎተ ፍትሐቱ ከተፈጸመ በኋላ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ልዑል እግዚአብሔር የብፁዕ አቡነ አረጋዊን ነፍስ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ሰጥቶ በአብርሃም በይሥሐቅ በያዕቆብ አጠገብ ያኑርልን፤ በማለት እንሰናበታቸዋለን፡፡
About these ads

ሰበር ዜና – ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዐረፉ



  • ሥርዐተ ቀብሩ ዛሬ በ9፡00 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል
His Grace Abune Aregawi
በተባሕትዎአቸውና በተመሰገነው ምንኵስናቸው የሚታወቁት የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ዐረፉ፡፡ ብፁዕነታቸው ዛሬ፣ ዓርብ ጥር ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጠዋት ያረፉት ለተሻለ ሕክምና በገቡበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡
ብፁዕነታቸውን ለኅልፈት ያደረሳቸው፣ ከአንድ ወር በፊት ለሐዋርያዊ ተልእኮ ወደ ደቡብ ሱዳን በሔዱበት ወቅት ያጋጠማቸው ቢጫ ወባ በኩላሊታቸውና በሳምባቸው ላይ ያስከተለው ጉዳት ነው፡፡
ከጉዟቸው መልስ ‹‹እኔ ንግግሬ ከእግዚአብሔር ጋራ ነው›› በማለት ያለሕክምና ርዳታ ለኹለት ሳምንት ያኽል በተዘጋ ማረፊያቸው የቆዩት ብፁዕነታቸው፣ በብፁዓን አባቶችና በቅርብ ወዳጆቻቸው ተማኅፅኖ በዘውዲቱ ሆስፒታል እና በሳንቴ የጤና ማእከል በተደረገላቸው ከፍተኛ ክትትል የተጎዳው ኩላሊታቸው አገግሞ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ በተሻለ ኹኔታ ላይ ይገኙ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ይኹንና ከዕድሜ አንጋፋነታቸው ጋራ ሕመሙ በሳምባቸው ላይ ባደረሰው ጉዳት የተፈጠረው ኢንፌክሽን ለኅልፈት እንደዳረጋቸው ተመልክቷል፡፡
በቅርበት የሚያውቋቸው ወገኖች÷ የዋልድባው መነኰስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሀብት ምክር ያላቸው፣ ታሪክ ዐዋቂና የታያቸውን በግልጽ የሚናገሩ መምህር ወመገሥጽ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
www-st-takla-org-abune-paulos-in-alex-15-july-2007-017
አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በግብጽ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ሐምሌ ወር ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.፣ ሐምሌ ፰ ቀን በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም በተሠራው ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት ወቅት፣ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የቅዱስነታቸውን ንግግር በልሳነ ዓረቢ እየመለሱ አሰምተው ነበር፡፡
የቀደምት ቅዱሳን አበውን ትውፊት በመከተል በግብጽ ገዳማት ለዐሥራ አምስት ዓመታት ያኽል በመቀመጥ ከአኃው መነኰሳት ጋራ መንፈሳቸውን ያስተባበሩት ብፁዕነታቸው፣ ልሳነ ዓረቢን አቀላጥፈው በመናገርም ይታወቃሉ፡፡ የቅድስት ሀገር ተሳላሚ ለመኾን የበቁትም በወጣትነታቸው ማለዳ ሳሉ ነበር፡፡
በፊት ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ ይባሉ የነበሩት ብፁዕነታቸው፣ አቡነ አረጋዊ ተብለው ጥቅምት ፲፰ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት በአራተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ ነው፡፡
ብፁዕነታቸው ቀድሞ ሊቀ ሥልጣናት በተባሉበት የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በበላይ ጠባቂነት ከመወሰናቸው በፊት፣ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲኹም የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን አገልግለዋል፡፡
የብፁዕነታቸው ሥርዐተ ቀብር ዛሬ፣ ጥር ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ለረጅም ዓመታት በአገለገሉበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በ9፡00 እንደሚፈጸም ተገልጧል፡፡
አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ለብፁዕ አባታችን ዕረፍተ ነፍስን ይስጥልን፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...