2014 ማርች 26, ረቡዕ

ደብረዘይት ዘሰንበተ ክርስቲያን



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 12 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 እኛ ክርስቲያን እንባል ዘንድ፣ ከክርስቲያኖችም ጋር እንኖር ዘንድ፣ በዘመናችንም ሁሉ እንደኖሩት ሐዋርያት ትምህርት እንኖር ዘንድ፣ እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት ክርስቲያን ሆነን በመቃብር ውስጥ ባንቀላፋንም በዚያ በደብረዘይት በምንነሳም ጊዜ ከእነርሱ ጋር በእነርሱ እቅፍ እንቀመጥ ዘንድ በአንተ ፍቅር ልንኖር ግድ ይለናል:: በማይለወጥ ፍቅሩ ሰላም ለእናንተ ይሁን::

 የወጉትም ያዩታል” እንዲል መጽሐፍ ዛሬ አክብረነው የምንውለው በዓል ደብረዘይት ይባላል:: ጌታችን የዚህችን ዓለም ፍጻሜ ዘመን ያስተማረባት ተራራ ነች:: በዛሬዋ ሰንበትም ሁሉን እንደ ስራው ሊከፍለው የሚመጣው ተቆጣጣሪ የሥራውን ሁሉ የክፍያ መጠን ዛሬ አስታውቋል:: ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በጾሙ ወቅት እንዳየነው ሰው የመጀመሪያ ፍጻሜውን የሥጋውን ሞት እንዲያስብ በዜማ ይነግረን ነበር:: ከቀናት ሁሉ የምትጨንቀውን አስፈሪዋን ደግሞ ዛሬ በማሰብ እንድንውል እጁን ወደ ላይ ልቡን ወደ አርያም አድርጎ አብረነው እንድናዜም ያዘናል::
  የዚህ ሳምንት ድርሰቱ ደብረዘይትን አስቀድሞ እንዲህ ብሎ ስለሚጀምር የደብረዘይት ሳምንት ተብሏል:: “እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ፣ በሰንበት ኢይኩን ጉያክሙጌታችን በደብረዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱን እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ፤ ሽሽታችሁ በሰንበት አይሁን አላቸው፡፡ካዕበ ይቤሎሙዳግመኛም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የመከሩ ጊዜ እንደደረሰ ምሳሌውን ከበለስ እወቁ አላቸው::” አሁን የእግዚአብሔር መንግስት በመካከላችሁ ናት:: በሕይወት የማታውቁትን እግዚአብሔርን ተሰብካችኋል፤ ተጽፎላችኋል፤ ተዘምሮላችኋል:: ነገር ግን አብልጬ ስነግራችሁ አብልጣችሁ ራቃችሁኝ፡፡ ዛሬ የመጨረሻው ቀን ከበር ላይ ነው:: ሁሉ በስሜ መጥተዋል፤ በስሜ አጋንንት አወጡ፤ ወገንና ደጋፊ አበጁ፤ ግን አላውቃቸውም፤ ከእኔ አይደሉም:: በሚታረፍባት ቀን ስደት እንዳይሆንባችሁ ለጉዞ የሚሆናችሁን ስንቅ አስቀድማችሁ ያዙ::
 አሜሃ ይበክዩ ኵሎሙ ኃጥአነ ምድር ሶበ ይሬእይዎየሰውን ልጅ በሰማይ ደመና በኃይል ሆኖ ባዩት ጊዜ የምድር ኃጢአተኞች ያን ጊዜ ያለቅሳሉ::” የሰው ልጅ ዛሬ በእኛ መካከል በቸርነቱ ታውቋል፤ በአቅማችን ተገልጧል:: ይህን ጊዜ ምሕረቱን እያሰብን ስለ ኃጢአታችን አልቅሰን ኃጢአተኛ ከመባል እንውጣ እንጂ ያን ጊዜ በኃይል በግርማ ሲመጣ ስለ ኃጢአታችን ሳይሆን የኃጢአተኝነታችን ነገር፣ ጉዳችን ግልጥ በሚሆን ጊዜ የማይጠቅመውን ልቅሶ አናልቅስ::
 አመ ይመጽዕ ወልድ በስብሐት ይትከወስ ኵሉ ኃየለ ሰማያትወልድ በምሥጋና በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ኃይል ሁሉ ይናወጣል…” ወዮ ያን ጊዜ ማን ይቆማል?
 ቅዱስ ያሬድ ያዜማል! ስለዚያች ቀን በሚያሳዝን ዜማው ልባችንን እየነካ ያች ቀን እየታየችው ይናገራል:: “ከመ እንተ መብረቅ ዘይወጽዕ እምጽባሕመብረቅ ከምስራቅ ወጥቶ እስከ ፀሐይ መግቢያ ብልጭ ብሎ እንደሚታይ ከሰማይ ኃይል ጋር ከመብረቆች ብልጭታ ከአእላፍ መላእክት ጋር የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ነው:: የአክሊሎች አክሊል በካሕናት ራስ ነው::” ከቃሉ ትዕዛዝ መላእክት መለከትን ይነፋሉ:: ያን ጊዜ የትዕግስታችን ልክ ርዝመቱ ይታወቃል፤ ያን ጊዜ የሰው ንጽሕና ስፋቱ ይለካል፤ ያን ጊዜ ካሕን ወይ ሌላ፣ ያን ጊዜ ባዕለ ጸጋ ድሃ የለም፤ የሁሉም ስራው ይሰፈራል::
  አመ ዕለተ ፍዳ አመ ዕለተ እግዚአብሔር ምንተ ንብላ ለነፍስ አመ ኢታድኅን እም ውሉዳበመከራና በፍዳ ቀን ነፍስን ምን እንላታለን? እናት ልጇን ማዳን በማትችልበት ጊዜ፣ ምድርም አደራዋን በምትመልስበት ጊዜ፣ አባት የበደል ዋጋ ልብስን በለበሰ የበቀልን ግምጃ በለበሰ ጊዜ፣ በምታስፈራ አደባባይ በወቀሰን ጊዜ፣ ያን ጊዜ ሥራችን ሁሉ ይገለጣል፤ የሰራነው ሁሉ ይነበባል:: ጌታችን በደብረዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ለሰው ችግረኛን ቢያስብ በጎ ነገርን ቢሰራ በተሻለው ነበር::” መብራቱ ሳይጠፋ ዘይትን ማዘጋጀት ይበጃል::
 አመ ይመጽዕ ንጉሥ በንጥረ መባርቅትንጉሥ በንጥረ መባርቅት በሚመጣበት ጊዜ የዕለታት አውራ ሰንበት ትገዛለች:: ያን ጊዜ ጨረቃ፣ ፀሐይ፣ ክረምትና በጋ የለም:: የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ኃይል ይናወጣል፤ ኃጥአን በሕይወት ዘመናቸው ያላሰቡትን ያለቅሳሉ፤ የእሳት ጎርፍ በፊቱ ይፈሳል፤ የእሳት ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እንደ ክረምት ውሀ እንባ ይፈሳል፤ ኃጥአን ከጻድቃን መካከል ይለያሉ ሕይወትን የፈጠረ ነውና:: ሰነበትን ለእረፍት ሰራ::” ሽባን የሚያድኑ፣ አንካሳን የሚያቀኑ፣ እውርን የሚያበሩ፣ ዓለምን የፈጠረበት ቃሉ የምህረት ምንጭ ነው:: በዚያን ጊዜ ግን ለኃጥአን ከሰይፍ የከፋ ይሆናል:: ከእኔ ሂዱ ይላቸዋልና:: ከእርሱ የሄደ ምንድነው? ምንስ አለው? ስለዚህስምዑ ቃልየቃሌን ስሙ ህጌንም ጠብቁ::…” ይለናል:: “ንጉሥ ሁሉን ጠራ” ይላል ዜመኛው፤ንጉሥ ሁሉን ጠራ፤ የመረጣቸውን ግን በመለከት ድምጽ ሰበሰባቸው:: የእርሱን ትንሣኤ ወራሾች የአባቴ ቡሩካን ይላቸዋል::” አቤቱ እኛን ባሪያዎችህን ታድነን ትምረንም ዘንድ የሕያዋን ጌታ ማረን::
  ፀሐይ ሠረቀ ቀርን ፀርሐፀሐይ ወጣ፤ ነጋሪት ተመታ፡፡ ዓዋጅ ነጋሪ ደረሰ፡፡ እውነተኛ ፍርድን ለመፍረድ ትጉሃን ይሮጣሉ፤ የደከሙ ይደሰታሉ፤ ሰነፎች ይደነግጣሉ፤ በቀኙ ያሉ የተገዙለት በሕይወታቸው የተገዙለት ፊቱን ባዩ ጊዜ ይደሰታሉ:: እስራኤል ሕዝብህን አቤቱ አስበን::
 መሐረነ እግዚኦ ወተሠሃለነአቤቱ ማረን ይቅር በለን፡፡ ከእኛ ምሕረትህን አታርቅ፡፡ አቤቱ ሰላምን ምሕረትን ስጠን::” አሜን!

2014 ማርች 16, እሑድ

የተሃድሶ ፕሮቴስታንት የውስጥ አርበኞችን የማስወገድ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ወጣቶችና ጎልማሶች ማህበራት ህብረት ወጣቶችና ጎልማሶች አስገነዘቡ


                                                                                   

 ፡፡ ከ60 በላይ ማህበራት ተወካዮች የተገኑበት መንፈሳዊ ጉዞ  ወደ ርእሰ አድባራት ወገዳማት  አዲስ ዓለም ገዳም መጋቢት 7 ቀን 2006 ዓ.ም ያደረገው ህብረቱ በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አቅራቢነት ከቋሚ ሲኖዶስ  እውቅናን  አግኝቷል፡፡  ወጣቶቹ የሚታወቁት በተለይ በጥምቀት በዓል ለታቦታቱ ምንጣፍ በማንጠፍ አስፋልቱን በማጽዳት ቄጠማ በመጎዝጎዝ  ከመታወቃቸውም በተጨማሪ የተሃድሶን እንቅስቃሴን በመግታት ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ የተወጡ ናቸው፡፡ እነዚህን ወጣቶች ማንም ሳያነሳሳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት የተነሱ ስለሆነ መሰልቸትና ወደኋላ ማፈግፈግ የሚባል ነገር አይታይባቸውም፡፡ የወጣቱን ከፍተኛ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የተመለከተችዋ ቤተ ክርስቲያናችንም  ለወጣቶቹ  እውቅና  ሰጥታለች፡፡ መጋቢት 7 በተደረገው መንፈሳዊ ጉዞ ላይ በአሁን ሰዓት የተሃድሶ  ፕሮቴስታንትን  የውስጥ  አርበኞችን   በቤተክርስቲያን ላይ እያሴሩ ያለውን ድብቅና ግልጥ አጀንዳቸውን በተመለከተ  መረጃ የቀረበ ሲሆን ወጣቶቹም ከዚህ በፊት ለቅዱስ ሲኖዶስ የቀረበውና ጉዳያቸው በይደር የተያዘውን ጉዳይ ከፍጻሜ እንዲያደርስና አፋጣኝ መልስ ለህዝበ ክርስቲያኑ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ በተለይ በቅርቡ ጉዳያቸው በይደር የተያዘላቸው ግለሰቦች ሾልከው  ወደ ቤተክርስቲያን መግባታቸውን የገለጹት ወጣቶቹ   ቤተክርስቲያናችንን አናስደፍርም፤ ነቅተን እንጠብቃለን  ተሀድሶ አራማጆች  ግለሰቦችን ወደ ቤተክርስቲያን በማስገባት የሚሯሯጡትን አባቶችም  ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡ ቤተክርስቲያን የሁላችንም ናት ያሉት ወጣቶቹ ጥቂት አባቶች የቅዱስ ሲኖዶሱን /ምለዓተ ጉባኤ/  አጀንዳ ወደ ጎን በመተው የሚወሰነው ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን የገለጹት ወጣቶቹ   ወደፊትም በየደብራችን  ቤተክርስቲያናችንን ነቅተን  መጠበቅ አለብን በማለት ተስማምተዋል፡፡ ከ6000/ ከስድስት ሺህ በላይ አባላት  ያሉት ህብረቱ ወደፊትም  ከሰንበት ት/ቤቶች ከሰበካ ጉባኤ አባላት ከምእመናንና ከሌሎች ማህበራት ጋር በጋራ መበሆን የተሀድሶ  እንቅስቃሴ ከመሰረቱ ነቅሎ እንደሚጥልም አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን  ማንኛውም ተባባሪ አካላትም ከጎናችን እንዲቆም ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንኑ የወጣቱን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በመደገፍ ና ወጣቱን ሰብስቦ በማወያየት አባታዊ ምክርና ትምህርት  በመስጠት  ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ  የአባትነት ድርሻቸውን በሚገባ እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
       

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...