2014 ኤፕሪል 19, ቅዳሜ

ትንሣኤ ዘክርስቶስ - የክርስቶስ ትንሳኤ

                                                          

Nahti Kumsa's photo.



  • ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
  • ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤
  • እንዴት ተነሣ?
  • ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
  • እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?
  • መቃብሩን ማን ከፈተው?


(መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው/ PDF):- ጌታችን  አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ÷ ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስቀርልን ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ÷ ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ይሰብክላቸው ዘንድ ነው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ ለዚህ ነው፥ መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው፤ ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለውም፡፡
ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለው ይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡ መዝ ፲፭÷፲፡፡ ሐዋርያው  ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) እንዲያቀርበን፥ እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት (ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎ በመሰጠት) ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየበመንፈስ ግን ሕያው ሆነ÷ (ያን ሥጋ ነፍስ እንድተለየችው መለኰት አልተለየውምበእርሱም ደግሞ (መለኰት በተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው፤» ብሏል።

 ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
ጌታችን በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ «ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤» የሚለው ቃለ ትንቢት የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ መዝ ፲፭፥፱፡፡ ምሥጢራዊ ትርጉሙም «ወደ መቃብር የወረደ ሥጋዬ በተስፋ ትንሣኤ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር አደረ፤» ማለት ነው፡፡ ተስፋ ትንሣኤውም በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር ወደ መቃብር የወረደ መለኰት ነው፡፡ ነቢዩ ሆሴዕም፡- «÷ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና÷ (በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን ጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነውእርሱም ይፈውሰናል፤ (መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አስወግዶ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋግረናል) እርሱ መትቶናል÷ እርሱም ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፡፡» በማለት ትንሣኤ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሆሴ ÷፲፪፡፡ ይልቁንም ጌታችን ራሱ በመዋዕለ ሥጋዌው፡- ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል፡፡ ማቴ ፲፮÷፳፩፡፡ በገሊላም ሲመላለሱ፡- «ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው÷ ይገድሉትማል÷ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፯÷፳፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ምልክት በጠየቁት ጊዜ፡- «ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ፥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፪፥፴፰-፵።
ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤
ጌታ በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ ይኽንንም ለመረዳት ዕብራውያን ዕለታትን እንዴት እንደሚቆጥሩ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ በሀገራችን የሌሊቱን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ከዋዜማው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ነው÷ የቀኑን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ደግሞ ከማለዳው አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ የሌሊቱ ሰዓት የሚያ ልቀው ከማለዳው አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን፥ የቀኑ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ነው፡፡ የቀኑም የሌሊቱም ዓት ተደምሮ ሃያ አራት ሰዓት ይሆናል፡፡ ሁሉም ሰዓት ዕለቱን ይወክላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እሑድ ዕለት ከሃያ አራቱ ሰዓ በአንዱ ቢወለድ እሑድ ተወለደ ይባላል÷ ቢሞትም እሑድ ሞተ ይባላል፡፡ ዕለቱ በሚጀምርበትም ሰዓት ሆነ፥ በሚያልቅ በት ሰዓት፥ ድርጊቱ ቢፈጸም ሰዓት እንደ አንድ መዓልትና እንደ አንድ ሌሊት ይቆጠራል፡፡ አውሮፓውያን አንድ ብለው ሰዓት መቁጠር የሚጀምሩት በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ነው፡፡ እስከ ሃያ አራት ይቆጥሩና በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን ይጨርሳሉ፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ሲሆን ዜሮ ይሉና እንደገና አንድ ብለው መቁጠር ይጀምራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ከሌሊት እስከ ሌሊት ይቆጥራሉ፡፡ አሜሪካውያን ደግሞ በእኛ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡ ከዚያም በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ ሰባት ሰዓት እንደገና አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡
 ዕብራውያን ግን ዕለትን መቁጠር የሚጀምሩት ከዋዜማው ማለትም በአውሮፓውያን ከአሥራ ሰባት ሰዓት÷ በአሜሪካውያን ከአምስት ሰዓት (P.M.) ÷ በእኛ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ሃያ አራት ሰዓት ቆጥረው አንድ ቀን ይላሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጠው እያንዳንዱ ሰዓት የዕለቱን መዓልትና ሌሊት ይወክላል፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ከመስቀል ወርዶ የተቀበረው ዓርብ ቅዳሜ ከመግባቱ በፊት ነው፡፡ ዓርብ ዕለቱ የሚጀምረው ከዋዜማው ሐሙስ በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ የተቀበረው በዓርብ ሃያ አራት ሰዓት ክልል ውስጥ በመሆኑ እንደ አንድ መዓልትና ሌሊት ይቆጠራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዓርብ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ቅዳሜ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ እሑድ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሰኞ ምሽት ይገባል፡፡ ጌታ የተነሣው በሦስተኛው ቀን እሑድ መንፈቀ ሌሊት ነው።
እንዴት ተነሣ?
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ ይህ ኃይልና ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይኽንንም፡- «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ (ሰውነቴን ከሞት አነሣት ዘንድ) አኖራለሁና (በፈቃዴ እሞታለሁና) ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ ለይቼ በገነት÷ ሥጋዬንም በመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ) ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ (ያለ እኔ ፈቃድ የሚፈጸም ምንም ነገር የለም)፡፡ ላኖራት (ነፍሴን በገነት÷ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው) ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ ላነሣት) ሥልጣን አለኝ፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡ ዮሐ ÷፲፯-፲፰፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት÷ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈ ተም፡፡» በማለት መናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ ትንቢት ነበር፡፡ ኢሳ ፶፫፥፯፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ከዚህ የሚመሳሰል ቃል ተናግሯል፡፡ ፩ኛጴጥ ÷፳፴፡፡ በዚህ ዓይነት ነቢያትም ሐዋርያትም የተናገሩለት ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጐ÷ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሥቷል፡፡ እርሱ የትንሣኤና የሕይወት ባለቤት ነውና፡፡ ዮሐ ፲፩÷፳፭፡፡
ይህ እንዲህ ከሆነ÷ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፤» በማለት አይሁድን ከወቀሳቸው በኋላ፡- «እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤» ለምን አለ? የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ ይኽንን ኃይለ ቃል በመያዝ «አብ አስነሣው እንጂ በራሱ አልተነሣም፤» የሚሉ አሉና፡፡ እነዚህም ትርጓሜውን ያልተረዱ ምሥጢሩን ያላስተዋሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያው «እግዚአብሔር አስነሣው፤» ያለው «እግዚአብሔር» የሚለው ስም የሦስቱም መጠሪያ እንጂ የአብ ብቻ አለመሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም፦ ወልድም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ÷ የሐዋ ÷፳፰፡፡ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ÷፪፡፡ ስለዚህ፦ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው፥ «አንዲት በሆነች በአብ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ተነሣ፤ አንድም፦ ወደ መቃብር የወረደ ሥጋ፥ መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ተነሣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሣ፤» ተብሎ ይተረጐማል፥ ይታመናል፡፡ ትንቢተ ነቢያትም የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ÷ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤» ይላል። መዝ ፸፯፥፷፭።
ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
በእስራኤል ባሕል፥ የአባቶቻቸው አፅም ካረፈበት መቃብር፥ የመቀበር ልማድ አላቸው፡፡ ዮሴፍ በግብፅ የእስራ ኤልን ልጆች፡- «እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤» ብሎ ያማላቸው፥ የአባቶቹ የአብርሃም እና የይስሐቅ የያዕቆብም አፅም ካረፈበት ለመቀበር ፈልጐ ነው፡፡ ዘፍ. ÷፳፭፡፡ በቤቴል የነበረውም ሽማግሌ ነቢ ይ፡- «በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤» ብሏል ፡፡  ፩ኛነገ ፲፫÷፴፩፡፡ ጌታችን የተቀበረው እንደ እስራኤል ባሕል የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበት ከአዲስ መቃብር ነው፡፡ ይኸውም ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው፡፡ «ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው÷ ከዓለት በወቀረ በአዲሱ መቃብርም አኖረው÷ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ፤» ይላል ማቴ ፳፯÷፶፱፡፡ ይህም የሆነው እርሱ ባወቀ በርሱ ጥበብ ነው፡፡ እንዲህም በማድረጉ አይሁድ ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው፥ ከነቢዩ ከኤልሳዕ መቃብር ተቀብሮ የነበረው ሰው፥ የነቢዩ አጥንት በነካው ጊዜ፥ በተአምር ተነሥቷል። ፪ኛነገ ፲፫÷፳፡፡ እንግዲህ ጌታችንም፥ ከአንዱ ቅዱስ መቃብር ተቀብሮ ቢሆን ኖሮ፥ ሞትን ድል አድርጐ በሚነሣበት ጊዜ «በራሱ አልተነሣም፥ የቅዱሱ አፅም ነው ያስነሣው፤» ባሉት ነበር፡፡ ይኸንን ምክንያት ለማጥፋት ነው፥ በአዲስ መቃብር የተቀበረው።
እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?
ጌታችንን ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩት በኋላ፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተመልሰው፡- « ጌታ ሆይ÷ ሰው (ክርስቶስ) ገና በሕይወቱ ሳለ፥ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ፥ እንዳለ ትዝ አለን፡፡ እንግዲህ ደቀመዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም  ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ÷ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት፡፡ ጲላጦስም፡- ጠባቆች አሉአችሁ፥ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ፤» አላቸው፡፡ እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ፡፡» ማቴ ፳፯፥ ፷፫÷፷፮፡፡ በታላቅ ድንጋይ የተገጠመው መቃብር፥ ድንጋዩ እንደታተመ፥ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ተነሥቷል፡፡ ይኸውም፦ ምንም የማያግደው መለኰት በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር በመቃብር ስለነበረ ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው፥ በተዋሕዶ፥ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፥ የሥጋም ገንዘብ ለቃል በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ አይሁድ ብዙ ጊዜ በድንጋይ ቀጥቅጠው ሊገድሉት ሲፈልጉ፥ እያዩት ይሰወርባቸው ከእጃቸውም ይወጣ ነበር፡፡ በመካከላቸው አልፎ ሲወጣ አያዩትም ነበር፡፡ ዮሐ ÷፶፱፤ ፲፥፴፱፡፡ ይህም የሆነው፥ እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ፥ መለኰት ሥጋን በመዋሐዱ ነው፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከተዘጋ ቤት በሩ ሳይከፈት የገባው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ ÷፲፱፤ ፳፮፡፡ በልደቱም ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና እንደታተመች የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ÷፲፬፡፡ ማቴ ÷ -፳፫ ሉቃ ÷-፯፡
መቃብሩን ማን ከፈተው?
         ጌታችን የተነሣው መግነዝ ፍቱልኝ፥ መቃብሩን ክፈቱልኝ ሳይል ከሆነ፥ «መቃብሩን ማን ከፈተው? ለምንስ ተከ ፈተ  የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፤ በወንጌል እንደተጻፈው፥ የአይሁድ ሰንበት ቅዳሜ ካለፈ በኋላ፥ እሑድ በማለዳ፥ ፀሐይ ሲወጣ፥ መግደላዊት ማርያም÷ የያዕቆብም እናት ማርያም ሶሎሜም ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ መጥተው ነበር፡፡ ትልቁ ጭንቀታቸው «ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናልየሚል ነበር÷ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደነበር ተመለከቱ፡፡ ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ፡፡ በጐልማሳ አምሳል የተገለጠላቸው የጌታ መልአክ ነው፡፡ እርሱ ግን፡- «አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ፤ ተንሥቷል በዚህ የለም፡፡» አላቸው፡፡ ማር ፲፮÷-፮፡፡ ጌታችን በዝግ መቃብር ከተነሣ በኋላ ባዶ የነበረውን መቃብር የከፈተው ይህ የጌታ መልአክ ነው፡፡ የከፈተበትም ምክንያት በእምነት የመጡ እነዚህ ሴቶች ያልተነሣ መስሏቸው ዘወትር በመመላለስ እንዳይቸገሩ ነው፡፡ አንድም ትንሣኤውን እንዳይጠራጠሩ ነው፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልም «በሰንበትም መጨረሻ የመጀመሪያው ቀን ሲነጋ፥ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ፡፡ መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፡፡ ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ፡፡ እንደ ሞቱም ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፥ እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤» የሚል ተጽፏል፡፡ ማቴ ፳፰÷-፮፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በእርግጠኝነት ትንሣኤውን ያመኑት መልአኩ ወደ ከፈተው መቃብር ገብተው መግነዙን ካዩ በኋላ ነው። ዮሐ ፳፥፯።
በኲረ ትንሣኤ፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለባሕርይ አባቱ፥ ለአብ ለእናቱ ለድንግል ማርያምም የበኵር ልጅ ነው፡፡ ዕብ ÷፮፣ ሉቃ ÷፯፡፡ ለበጎ ነገርም ሁሉ በኵር በመሆኑ የትንሣኤያችንም በኵር እርሱ ነው፡፡ «አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት በሰው (በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ፥ ትንሣኤ ሙታን በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳም በተባለ በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው፤» ይላል፡፡ ፩ኛቆሮ ፲፭÷-፳፫፡፡ በተጨማሪም፡- «በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯልና፥ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፡፡ (ከፍጥረታት በፊት የነበረ÷ የፍጥረታት አለቃ÷ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ ነው) ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በህልውና የነበረ ነው) ሁሉም በእርሱ ተጋጥሟል፡፡ እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርሰቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው፡፡» የሚል አለ፡፡ ቈላ ÷፲፮-፲፰፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም፡- «ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም÷ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት÷ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤» ብሏል። ራእ ፩፥፭።
 በብሉይ ኪዳን እነ ኤልያስ÷ እነ ኤልሳዕ ሙት አስነሥተዋል፡፡ ፩ኛነገ ፲፯፥፳፪ ፪ኛነገ ÷፴፪-፴፰፡፡ በአዲስ ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ የመኰንኑን ልጅ ÷ የመበለቲቱን ልጅ÷ አልዓዛርንም ከሞት አንሥቷቸዋል፡፡ ማቴ ÷፳፭፣ ሉቃ ÷፲፭ ዮሐ ፲፩÷፵፬፡፡ ነፍሱን በመስቀል ላይ በፈቃዱ አሳልፎ በሰጠም ጊዜ አያሌ ሙታን ከእግረ መስቀሉ ተነሥተዋል፡፡ ማቴ ፳፯÷፶፫፡፡ እነዚህ ሁሉ በኵረ ትንሣኤ አልተባሉም፡፡ ምክንያቱም፦ አንደኛ፥ በራሳቸው ኃይል የተነሡ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜ ከኖሩ በኋላ ተመልሰው ሞተው ትንሣኤ ዘጉባኤን የሚጠብቁ ሆነዋል፡፡ ሦስተኛ፥ ፍጡራን ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባሕርይ አምላክ በመሆኑ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ተነሥቷል፡፡ ዳግመኛም አይሞትም፡፡ ይኽንንም፡- «ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደፊት እንዳይሞት፥ ሞትም ወደፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና ÷ መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቷልና፡፡» በማለት ሐዋርያው ገልጦታል፡፡ ሮሜ ÷፱፡፡ ጌታችንም፡- «ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤» ብሏል። ራእ ፩፥፲፰።
ከትንሣኤው በኋላ ለምን ተመገበ?
ጌታችን በተዘጋ ቤት ገብቶ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠ ጊዜ፥ መንፈስ የሚያዩ መስሏቸው ኅሊናቸው ደንግጦ÷ ልባቸውም ፈርቶ ነበር፡፡ እርሱም፡- «ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት÷ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና፥ እኔን ዳስሳችሁ እዩ፤» ካላቸው በኋላ እጆቹንና እግሮቹን አሳይቷቸዋል። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፡- «በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁንአላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ፥ ይላል። ሉቃ ፳፬÷፴፮ -፵፫። ለሦስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ በተገለጠላቸውም ጊዜ አብሯቸው ተመግቧል፡፡ ዮሐ ፳፩÷-፲፬። ይኽንንም ያደረገው ከትንሣኤ በኋላ መብላት መጠጣት ኖሮ አይደለም፡፡ አለማመናቸውን ለመርዳት ነው፡፡ ደቀመዛሙርቱ በተዋሐደው ሥጋ ለመነሣቱ እርግጠኞች እንዲሆኑ ነው፡፡ ከወንጌሉ እንደምንረዳው ደቀመዛሙርቱ ይበልጥ እርግጠኞች የሆኑት ስላዩት ሳይሆን፥ ያቀረቡለትን በመብላቱና በመጠጣቱ ነውና፡፡
ለምን አትንኪኝ አላት?
መግደላዊት ማርያም ገና ሰማይና ምድሩ ሳይላቀቅ፥ በማለዳ፥ ሽቱ ልትቀባው ከመቃብሩ አጠገብ ተገኝታ ነበር። እንደደረሰችም ድንጋዩ ከመቃብሩ አፍ ተፈንቅሎ አየች። ይህች ሴት በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ከባለቤቱ ብትሰማም፥ « እንደተናገረ ተነሥቶ ነው፤» ብላ አላመነችም። ላለማመኗም ምክንያት የሆነው፥ «እኛ ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት ሰረቁት፤» የሚለው የጭፍሮች ወሬ ነው። ጭፍሮቹ እውነትን በሐሰት ለውጠው ይኽንን ያወሩት፥ በገንዘብ ተደልለው ነው፡፡ ማቴ ፳፰÷፲፩-፲፭፡፡ ለዚህ ነው ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ፡- «ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤» ያለቻቸው፡፡ ዮሐ ÷፪፡፡ ከመቃብሩ ራስጌና ግርጌ ሁለት መላእክት ተገልጠውላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽባሏት ጊዜም፥ «ጌታዬን ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤» ብላቸዋለች፡፡ ዮሐ ÷፲፫፡፡ በመጨረሻም ጌታ ራሱ ተገልጦላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽሲላት አላወቀችውም፡፡ ለዚህ ነው፥ አትክልት ጠባቂ መስሏት፡- «ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ፥ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፥ እኔም ወስጄ ሽቱ እንድቀባው፤» ያለችው፡፡ ዮሐ. ÷፲፭፡፡ በዚህን ጊዜ፥ «ማርያም» ብሎ በስሟ ቢጠራት በድምፁ አወቀችውና «ረቡኒ ( መምሕር ሆይአለችው፡፡ መልኩን አይታ፥ ድምፁን ሰምታ÷ ትንሣኤውን አረጋግጣ፥ «አምላኬ» አላላችውም፡፡ ስለዚህ «ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ አትንኪኝ፥ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ (ወደ ደቀመዛሙርቴ) ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ÷ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብሏል፥ ብለሽ ንገሪያቸው፤» አላት፡፡ እንዲህም ማለቱ የእርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መባልና የእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች መባል ፍጹም የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡ እርሱ፥ «አባቴ» ቢል የባሕርይ ልጅ በመሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ግን የጸጋ ልጆች ናቸው፡፡ እርሱ፥ «አምላኬ» ቢል ስለተዋሐደው ሥጋ ነው፡፡ የተዋሐደው የፈጠረውን ሥጋ ነውና ፡፡ እነርሱ ግን «አምላካችሁ» ቢባሉ ፍጡራን ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም እርሱ ፈጣሪ እነርሱ ፍጡራን መሆናቸውን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ቶማስን ግን፡- «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን፤» ብሎታል፡፡ ዮሐ ፳፥፳፯ ፡፡ ምክንያቱም አይቶ፥ ዳስሶ፥ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ የሚያምን ነውና፡፡ አንድም ሥጋውንና ደሙን ለመዳሰስ÷ ለመፈተት፥ የተጠራ የተመረጠም ካህን ነውና፡፡
ተስፋ ትንሣኤ፤
በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እየተኰነኑ በሞተ ነፍስ ተይዘው ወደ ሲኦል ይወርዱ ነበር ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ÷፳፪፡፡ «ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ( እስከ ክርስቶስ) ድረስ ሞት ነገሠ፤» የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ሮሜ ÷፲፬፡፡ ከዚህ የተነሣ እነ አብርሃም እንኳ ሳይቀሩ የወረዱት ወደ ሲኦል ነው፡፡ እነ ኢሳይያስ፡- «ጽድቃችንም ሁሉ እንደመርገም ጨርቅ ነው፤» ያሉት ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ፷፬ ÷፮፡፡ እነ ኤርምያስም፡- «ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም፥ ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፡፡» ብለዋል፡፡ ኤር ፲፪÷፲፫። በዚህ ምክንያት የብሉይ ኪዳን፥ ዘመን ዘመነ ፍዳ÷ ዘመነ ኵነ ÷ ዘመነ ጽልመት ተብሏል፡፡ በዚህ ዘመን እነ ቅዱስ ዳዊት፡- «አንሥእ ኃይለከ÷ ወነዓ አድኅነነ፤ ኃይልህን አንሣ÷ እኛንም ለማዳን (በሥጋ ተገልጸህ÷ ሰው ሁነህ አድነን)» እያሉ ወልድን ተማጽነዋል፡፡ መዝ 79÷ 2 ፡፡ «ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፤ ብርሃንህንና እውነትህን ላክልን፤ (ብርሃን ወልድን÷ እውነት መንፈስ ቅዱስን ላክልን) እነርሱ ይምሩን÷ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ÷ (ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት) ይውሰዱን  » እያሉም አብን ተማጽነዋል፡፡ መዝ ÷፫፡፡ ይህም የሚያመለክተው በዚያ በጨለማ ዘመን ሆነው ተስፋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ እንደነበረ ነው፡፡ በሞት አጠገብ ሕይወት÷ በመቃብር አጠገብ ትንሣኤ እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያደርጋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነውና፡፡ ያንጊዜ ከሲኦል እንደሚወጡ፥ የተዘጋች ገነትም እንደምትከፈትላቸው ያውቃሉና፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ የአዳም ልጆች በጠቅላላ ትንሣኤ ዘጉባኤን በተስፋ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ተስፋ ሃይማኖት እንዲይዙ÷ ምግባር እንዲሠሩ አጽንቷቸዋል፡፡ ምድራዊውን እንዲንቁ፥ ሰማያዊውን እንዲናፍቁ አድርጓቸዋል፡፡ « ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛ ጴጥ ÷፲፫፡፡ ቅዱሳን በሃይማኖት አይተዋታል፡፡ «አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ÷ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና÷ ባሕርም ወደፊት የለም፡፡ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፡፡» ይላል፡፡ ራእ ፳፩÷፫፡፡ እግዚአብሔርም፡- «እነሆ÷ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፥ የቀደሙትም አይታሰቡም÷ ወደ ልብም አይገቡም፡፡ ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ፥ ለዘላለምም ሐሴት አድርጉ፤ እነሆ÷ ኢየሩሳሌምን ለሐሴት÷ ሕዝቧንም ለደስታ እፈጥራለሁና፡፡» ብሏል፡፡ ኢሳ ፷፭፥፲፯።
ሙታን እንዴት ይነሣሉ?
እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና የሚነቃ አድርጐ ፈጥሮታል፡፡ ማንቀላፋቱ የሞት፥ መንቃቱ ደግሞ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩም የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ÷፲፡፡ የሄኖክም ከዓይነ ሞት ተሰውሮ በእግዚአብሔር መወሰድ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ÷፳፬፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላም ትንሣኤን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ የፀሐይ መውጣት የመወለድ÷ የፀሐይ መጥለቅ የመሞት÷ ከጠለቀች በኋላም እንደገና መውጣት የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን እንደሚነሡ በቃልም በተግባርም አስተምሯል፡፡ በቃል - «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ÷ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፡፡» ሲል አስተምሯል፡፡ ዮሐ ÷፳፱፡፡ በተግባርም የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነሥቷል፡፡ ዮሐ ፲፩÷፵፫፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፡- እነ ኢሳይያስ «ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ፡፡» ብለዋል። ኢሳ ፳፮÷፲፱፡፡ እነ ዳንኤልም፡- «በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች (ሁሉም) ይነቃሉ፤ እኵሌቶችም ወደ ዘላለም ሕይወት÷ እኵሌቶችም ወደ እፍረትና ዘላለም ጉስቊልና፡፡» ብለዋል፡፡ ዳን ፲፪÷፪፡፡ በተለይም ለነቢዩ ለሕዝቅኤል፥ እግዚ አብሔር፦ በአፅም የተሞላ ታላቅ ሸለቆ ካሳየው በኋላ፥ «እነዚህ የደረቁ አጥንቶች ተመልሰው በሕይወት የሚኖሩ ይመስ ልሃልንሲል ጠይቆታል፡፡ ሕዝቅኤልም፡- «እግዚአብሔር ሆይ÷ አንተ ታውቃለህ፤» የሚል መልስ ሰጥቶቷል፡፡ በመጨ ረሻም እነዚህ ሁሉ ሕይወት ዘርተው ሲነሡ አይቷል፡፡ ይኸንንም፡- «እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ÷ ትንፋሽም ገባባቸው፥ ሕያዋንም ሆኑ÷ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ፡፡» በማለት ገልጦታል፡፡ ሕዝ ፴፯፥፩-፲፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር «ነገር ግን ሰው፥ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል፡፡» ብሎ ከጠየቀ በኋላ፥ «አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፡፡» ብሏል፡፡ ከዚህም አያይዞ «የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል÷ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም (ክርስቶስ) ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው። ሁለተኛው ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊው እንደሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው ፡፡ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን፡፡» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፲፭÷፴፭-፵፱፡፡ በፊልጵስዩስ መልእክቱም፡- «ክቡር ሥጋውን እንደሚስል የተዋረ ደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» ብሏል፡፡ ፊል ÷፳፩። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም፡- «እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፤» ብሏል፡፡ ፩ኛ ዮሐ ÷፪።
የትንሣኤ ጸጋ፤
         በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል÷ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል ሙታን የነበርን ሕያዋን÷ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን÷ ሥጋውያን የነበርን መንፈሳውያን ሆነናል፡፡ «ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ÷ ድል መንሣትህ የት አለየምንል ሆነናል፡፡ ሆሴ ፲፫÷፲፬ ፩ኛቆሮ ÷፶፭፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና÷ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠ ባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋች ንን ይለውጣል፡፡» የምንል ሆነናል፤ ፊል ፫፥ -፳፩፡፡ ናፍቆታችን ሁሉ በትንሣኤ ያገኘነውን ጸጋ እውን ማድረግ ነው፡፡ «ድንኳን የሚሆነው ምድራዊው መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና÷ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድን ለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛቆሮ ፭፥፩-፪፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ÷ እድፈትም ለሌለበት÷ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ» ብሏል፡፡ ፩ኛጴጥ ÷፫፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም፡- «በሚመጡ ዘመ ናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳ የን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነ ሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።» ብሏል። ኤፌ፪÷-፯።
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡                             
Like · ·

2014 ኤፕሪል 17, ሐሙስ

ዐርብ እና ሰዎቿ

                
                                                                                                                                                                    ዕለተ ዐርብ የፍጥረተ ዓለም መካተቻ፣ ከሳምንቱ ቀኖ
ች ውስጥ የመጨረሸዋ ቀን ናት፡፡ ዕለተ ዐርብ ጌታችን መድኀኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም መድኅን ሆኖ የተሰጠበት፣ ራሱን  መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት የመከራ ሞቱ ዕለት ናት፤ ዕለተ ዐርብ፡፡



ዕለተ ዐርብ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃደ ሥጋን ጋሻ ጦር አድርጎ ከሚቃወመን ከፈቃደ ሰይጣን ያድነን ዘንድ ስለ እኛ ኃጢአት ራሱን ለሕማም፣ ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ በቀራንዮ አደባባይ ቅዱስ ሥጋውን የቆረሰበት፤ ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት የመጨረሻዋ ዕለት ናት፤ ዕለተ ዐርብ፡፡



ዕለተ ዐርብ እብኖዲ፣ ታኦስ፣ ማስያስና ትሰቡጣ እየተባለ በሥጋዌው ስሞቹ የተጠራው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ዝቅ ከምድር ብቅ ብሎ በተተከለ መስቀል ተሰቅሎ በመስቀሉ 5500 ዘመን ተለያይተው፣ ተራርቀው ይኖሩ የነበሩ ሰውንና እግዚአብሔር፤ ሰውንና መላእክትን፣ ሕዝብንና አሕዛብን ማስታረቁን እና ይኽን የቤዛነት፣ የድኅነተ ዓለም ሥራውን በመስቀል ሞት መፈጸሙን ‹‹ተፈጸመ›› ብሎ ፍጻሜ የሌለውን የምስራች ያወጀበት መልካም ዐርብ /Good Friday/ ናት፤ ዕለተ ዐርብ፡፡



ይህች ዕለት በ5500፤ በ34 ዓመተ ዓለም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ተፈጽማ በአማናዊትነት እስክትከበር ድረስ በትንቢት ስትነገር፣ በምሳሌነት ሰትከበር ብዙ ዘመን አሳልፋለች፡፡



በትንቢት መነገሯ የተጀመረው አዳም ዕፅ በለስን በልቶ ከገነት ከወጣ በኋላ በሠዋሁት መሥዋዕት፤ ባቀረብኩት ጸሎት እድናለሁ በሚል መሪር እንባ አልቅሶ፤ ከገነት ፍሬ በደሙ ለውሶ መሥዋዕት ስላቀረበ ጌታ ‹‹አዳም አዳም›› ብሎ ጠርቶ ‹‹ይህ ዓለም በዕሩቅ ብእሲ ደም የሚድን አይምሰልህ፤ እኔ 5500 ሲፈጸም ወደ አንተ መጥቼ፣ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅዬ፣ ሥጋዬን ቆርሼ፣ ደሜን አፍስሼ አድንሃለሁ›› ብሎ ጽኑ ተስፋ በሰጠው ጊዜ ነው፡፡ የዚህም ጽኑ ተስፋ ፍጻሜ ዕለት፡- ዕለተ ዐርብ ናት፡፡



ከዚህም ጋር አያይዘው ነቢያት<< ስቅልተ ትሬእያ ለሕይወትከ እስራኤል ወኢትትአመና፤ ሕይወትህ ተሰቅላ ታያታለህ፤ አንተ ግን አታምንባትም:: >>ዘዳ. 28/66 እንዲሁም <<..ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ፤ እጄንና እግሬን ቸነከሩኝ::>>መዝ. 22.16 ብለው የተናገሩት እና<< ..ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልየ፣ ወአስተዩኒ ብኀኂዐ ለጽምዕየ፤ በምግቤ ሐሞት ጨመሩበት፤ ብጠማም መጣጣ አጠጡኝ::>> መዝ. 69.21፡፡ እንዲሁም ..ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፤ ደዌያችንን ወስዶ ሕማማችንን ተሸከመ.. ኢሳ. 53/4፣ ‹‹መጠውኩ ዘባንየ ለቅሥፈት፣ ወመልትሕቴየ ለጽፍዐት ወኢሜጥኩ ገጽየ እምኃፍረተ ምራቅ፤ ጀርባዬን ለግርፋት፣ ፊቴን በጥፊ ለመመታት አሳልፌ ሰጠሁ፡፡ አፍሬ ፊቴን አልመለስኩም››ኢሳ. 50/5 ተብለው የተነገሩት ትንቢቶችም በክርስቶስ ጸዋትወ መከራ የተፈጸሙት በዕለተ ዐርብ ነው፡፡



በዚህ መልኩ ስለ ዕለተ ዐርብ የተሰጠው አጭር ማብራሪያ የዕለቷን ታላቅነት ከመግለጹም ባሻገር የዕለቷን የመከራ፣ የጭንቅ፣ የምጥ ዕለት መሆኗን በሚገባ ያሰረዳል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በራሱ የቁርጥ ጊዜ እና አደርባዮች እንዲሁም የመከራ ዘመን እና የደስታ ዘመን ወዳጆች የተለዩባት ዕለት መሆኗን ያመለክታል፡፡



የሰዎች እውነተኛ ማንነት የሚገለጠው፣ ከገቡት ቃል ይልቅ እስከ ሞት መታመናቸው የሚገለጠው፣ ምንደኛው ከእውነተኛው አገልጋይ ተለይቶ የሚታየው፣ ሥርዐት አክባሪው ሥርዐት ከማያከብረው የሚለየው በዕለተ ዐርብ በመከራ ጊዜ እንጂ በዕለተ ሐሙስ፣ በፋሲካ በደስታ ጊዜ አይደለም፡፡ ደስታ፣ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዝና ባለበትም ሁሉም አለ፡፡እነዚህ ባሉበት የማያረጠርጥ፣ የማያለቀልቅ፣ እጅ የማይነሳና ደጅ የማይጠና የለም፡፡ ሰው ማግኘት የሚቸግረው በዕለተ ዐርብ በመከራ ጊዜ ነው፡፡ እስቲ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሁለት ወገን ማሳያ ልጥቀስ፡፡



1. ሕዝበ አይሁድ

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመስቀል ሞት ተላልፎ እስከ ሚሰጥባት ዕለተ ዐርብ ድረስ ብዙዎች ይከተሉት፤ ያደንቁት ነበር፡፡ የእነዚህ ሰዎች መከተልና አድናቆት ዕለተ ሐሙስን ተሻግሮ አርብን መዝለቅ አልቻለም፡፡ በዕለተ ዐርብ በመከራው ሰዓት ከጌታ ጋር አብረው ለመቆም አላስቻላቸውም፡፡



ይህ የሰማይና ምድር ጌታ ምንም እንኳን የፈጸመው ቤዛነት እነርሱንም የዋጀ ቢሆንም ቅድመ ዐርብ ያላደረገላቸው ነገር እና ያልሆነላቸው ሁኔታ የለም፡፡ ሲራቡ ምግበ ሥጋን አበርክቶ አብልቷቸዋል፡፡ ሲታመሙ በተአምራት አድኗቸዋል፡፡ በትምህርቱ ምግበ ነፍስ ሆኗቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቤተሰብና ጎረቤት፤ ልጅና ዘመድ፣ እውነተኛ ወዳጅና ጠላት፤ ምንደኛና እውነተኛ አገልጋይ የሚለይባት ዕለተ ዐርብ የመከራ ቀን ስትደርስ ‹‹ስቀለው፣ ስቀለው›› ማለት ጀመሩ፡፡ ከጌታችን ይልቅ ልጆቻቸውን የሚገድልባቸውን፣ ንብረታቸውን የሚዘርፍባቸውን ልበ ጨካኝ የሆነውን ወንበዴ በርባንን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ /ማቴ. 27/15/



ከሞት ሊያድናቸው፤ ከመከራ ነፍስ ሊታደጋቸው የመጣውን ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንዲሰቀል በአንድነት ፈረዱበት፡፡ ለምን? እነርሱ ቀድሞም ቢሆን የሐሙስ የፋሲካ ሰዎች እንጂ የዕለተ ዐርብ ሰዎች አይደሉምና፡፡ እነርሱ ቀድሞም የድሎትና የምቾት ዘመን ሰዎች እንጂ የመከራ ዘመን ወዳጆች አይደሉምና፡፡ እነርሱ ቀድሞም ቢሆን የተከተሉት ከሥጋዊ ድካማቸው ስለሚታደጋቸው እንጂ የዓላማና የቁርጥ ዘመን ሰዎች አይደሉምና፡፡ ‹‹ክርስቶስን ስለመምሰል›› በሚል ርእስ የታተመው መጽሐፍ <<ዛሬ ለክርስቶስ የሰማያዊ መንግሥቱ ወዳጆች ብዙ አሉት፡፡ ነገር ግን የመስቀሉ ተሸካሚዎች ጥቂት ናቸው፡፡ የመጽናናት ወዳጆች ብዙ አሉት፤ የመከራ ወዳጆች ግን ጥቂት ናቸው>> ይላል፡፡



በዚህ በያዝነው ክፍለ ዘመንም ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት ቅድስት ቤተክርስቲያን ራሷ ክርስቶስ የገጠመውን ዓይነት መከራ እየገጠማት ነው፡፡ ዘመኑም ዕለተ ዐርብ፤ ሰዎቿም ሕዝበ አይሁድ የሆኑባት ይመስላል፡፡ ብዙዎች ዐውደ ምሕረቷንና ደጀ ሰላሟን ተጠቅመው ክብርን አግኝተዋል፤ ዝናውን አትርፈዋል፤ ሀብቱን አግበስብሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደሆነችላቸው ሲሆኑ አይታዩም፡፡ ከዚያ ይልቅ በሥርዐቷ፣ በቀኖናዋና በዶግማዋ ላይ ያልተገራ አንደበታቸው ሲያላቅቁ መመልከት ተለምዷል፡፡



ሁሉን ነገር ያደረገችላቸውንና ሁሉን ነገር የሆነችላቸውን እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዐቷን፣ ቀኖናዋን፣ ዶግማዋን እና የዝማሬ ለዘዋንና የስብከት ይትብሐሏን ለፕሮቴስታንት እና በፕሮቴስታንታዊነት ክህደት ለሚሰቅሏት ሰቃዮች አሳልፈው ሰጥተዋታለ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሐሣር ወደ ክብር፣ ከመርገመ ሥጋ ወደ በረከተ ሥጋ፣ ከመርገመ ነፍስ ወደ በረከተ ነፍስ ከሚያሸጋግረው መሠረተ እምነቷና ትምህርቷ ይልቅ ሕዝቡ ምርጫው የሞት መንገድ እንዲሆን የሚያስገድዱ ረበናተ አይሁድ ሆነውባታል፡፡

2. ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ

ካደረበት ፍርሃት የተነሣ የሐሙስ ሰው እንጂ የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን ከተሳናቸው መካከል ሌላኛው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፡፡



ምንም እንኳን በኋላ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ተጸጽቶ የንስሐ እንባን ቢያነባም አስቀድሞ ካደረበት ፍርሃት የተነሣ ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ዐርብ ሰው ሊሆንላት አልቻለም፡፡ ቅድመ ዐርብ የነበረው ጀግንነቱ በዕለተ ዐርብ ነጠፈ፡፡

ስምዖን ጴጥሮስ ጌታውን እወድኃለሁ፣ ከአንተ አልለይም፣ ሞትህን ሞቴ ያድርገው እያለ እንዳልማለ፣ እንደ አልተገዘተ ዕለተ ዐርብ የመከራ ሰዓት ስትደርስ መሐላውን አፈረሰ፤ የራሱን ግዛት ተላለፈ፡፡



በዚህ መልኩ ይምልለት፣ ይገዘትለት የነበረውን አምላኩን ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ሳለ  አንዲት አይሁድ ወደ እርሱ ቀርባ <<አንተም እኮ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርክ>>ስትለው እርሱ ግን <<የምትይውን ሰው አላውቀውምብሎ  በሁሉ ፊት ካደ፡፡ ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት ‹‹ይኽ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበር››  ስትል እርሱ ዳግመኛም ‹‹ይኽን የምትሉትን ሰው አላውቀውም፤ እንደ ማላውቀውም እውነት ነው››  ብሎ ማለ፡፡ ጥቂትም ቆይተው በዚያ ቆመው የነበሩ አይሁድ ቀርበው ጴጥሮስን ‹‹ከእርሱ ወገን እንደሆንክ አነጋገርህ ይገልጥኃል›› አሉት፡፡ በዚህን ጊዜም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ..ሰውየውን አላውቀውም.. ብሎ ይምል ጀመር፡፡ የያዘውን ጥሎ ..እንዲህ ይጣለኝ፤ የእርሱን ሞት ለእኔ ያድርገው፤ እንዲህ ያለውን ሰው አላውቅም.. በማለት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ካደው፡፡ /ማቴ. 26/69-75/



እንግዲህ ይህ ዘመን ለቤተክርስቲያን ዕለተ ዐርብ ሆኖባታል፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ፍርሃት የወለደው ክህደት ብዙዎቹን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መምህራነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ ምእመናንና የማኅበራት አመራር አካላት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ሓላፊዎችና የድርጅት ሥራ አስኪያጆችን ተጠናቷቸዋል፡፡ የቅዱሳ ጴጥሮስ የክህደት ሕይወት፤ ዛሬ እነዚሁ ሰዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የካዱበት ሕይወት ነው፡፡



እናት! የዚህች ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፣ሊቃውንት፣ ሰባክያን የቆሎ ትምህርት ቤት እያላቸው፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆች በትምህርት ገበታ ሳላችሁ ከአንዲቷ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደስታዋም በሐዘኗም ላለመለየት፣ መሠረተ እምነቷን፣ ሥርዐተ አምልኮዋንና ትውፊቷን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ እንዳልማላችሁ፣ እንዳልተገዘታችሁና ቃል ኪዳን እንዳልገባችሁ ሁሉ ዛሬ ዘመናዊነት፣ ማግኘት፣ ምንፍቅና፣ ራስ ወዳድነት፣ ጥቅመኝነትና ጎጠኝነት ዕለተ ዐርብ ሆኖባችሁ መሓላችሁን አፈረሳችሁ፣ ግዝታችሁን ተላለፋችሁ፣ ቃል ኪዳናችውን  ቆረጣችሁ፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱን፣ የወሮበሎችና የወንበዴዎች ዋሻ እንድትሆን ፈቀዳችሁ፡፡



እናት! የዚህች ታላቅ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዐት፣ ትውፊትና ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እናሸጋግራለን ብላችሁ ማኅበር የመሠረታችሁ እና በዚሁ ማኅበር አመራር የሆናችሁ በዕድሜያችሁም ሆነ በትምህርት ደረጃችሁ ለሰማይ ለምድሩ የከበዳችሁ ፍርሃት የወለደው አጉል አርቆ አሳቢነት ዕለተ ዐርብ ሆኖባችሁ፤ የገባችሁትን ቃልኪዳን አፍርሳችሁ፤ ቤተ ክርስቲያንን ለበላተኞች አሳልፋችሁ ሰጥታችሁ የተቀመጣችሁ xYmSLÆCh#ምን) ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ የአስተዳደር በሽታዎች መድኃኒት መሆን ቢያቅታችሁ ጉልኮስ መሆን ያቅታችሁን? በዚህ ሁኔታ አሟሟች እንዳትሆኑ ያሰጋል፡፡



እናት! የዚህች ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርቲያን ልጆች የሆናችሁ ምእመናን ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ሰቃዮች ጋራ እሳት እንደሞቀ ሁሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ትውፊቷንና ሥርዐተ አምልኮዋን በጥርጥር እና በክህደት ለሚሰቅሏት ሰቃልያን ቲፎዞ ሆነን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የመደፈር፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የመተላለፍ፣ መሠረተ እምነትን የመናድ እሳት ሞቅን፡፡ እኛ ለቤተ ክርስቲያን እንዲህ ከሆንን፤ አይሁድ ለክርስቶስ ከሆኑት በምን ይለያል?



ስምዖን ጴጥሮስ ከአይሁድ ጋር እሳት እንደሞቀ አልቀረም፡፡ ዘግይቶም ቢሆን የእሳቱ ሙቀት ምቾት ሆኖት የዕለተ ዐርብ ሰው ከመሆን አልገታውም፡፡ ወዲያው ዶሮ ሲጮኽ ..ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ.. ያለው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ትዝ አለው፡፡ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቀሶ አለቀሰ፡፡ ስለበደሉ ተጸጽቶ፣ የንስሐን እንባን አንብቶ በእንባው የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን ቻለ፡፡ በኋላም መንፈስ ቅዱስ ፍርሃትን ቀርፎ ስለጣለለት የማይፈራ ሆኖ ስለክርስቶስ ፍቅር ቁልቁል ተሰቅሎ የሚሞት ሆኗል፡፡



በየፈርጁ ከላይ የተጠቀሳችሁ ሊቃነ ጳጳሳት፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ የየመምሪያ ሓላፊዎች፤ የድርጅት ሥራ አስኪያጆች፣ የማኅበራት አመራር አባላትና ምእመናንን ትላንት የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን ካልቻለን ዛሬ መሆንን እንችላለን፡፡ ከሰዓታት በፊት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የዕለተ ዐርብ ሰው ካልሆንን ከሰዓታት በኋላ መሆን እንችላለን፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት የሚነግረን ይኽንኑ ነው፡፡ እርሱ ከሰዓታት በፊት ለጌታው የዕለተ አርብ ሰው መሆን አቅቶት ጌታውን ሦስት ጊዜ ካደው፡፡ ከሰዓታት በኋላ አምላኩ ክርስቶስ የተናገረው ቃል ትዝ ሲለው ግን የንስሓን እንባ አንብቶ መላ ሕይወቱን በእርሱ ዐለትነት ለተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን የዕለተ ዐርብ ሰው ሆኖ በኔሮን አደባበይ ሰማዕት ሆነ፡፡



ከእኛም የሚጠበቀው ይኽው ነው፡፡ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የመድፈር፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የመተላለፍና መሠረተ እምነትን የመናድ እሳት ከሚሞቁ ውሉደ አይሁድ ተለይቶ ቤተ ክርቲያን በየጊዜው ያለችንና የነገረችን ቃል እና ሰማያዊ እናትነቷን ማስተወስ ነው፡፡ ይኼኔ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የዕለተ ዐርብ ሰዎች እንሆንላታለን፡፡ ስለ እርሷ መሠረተ እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮ፣ ትውፊትና ታሪክ ቀጣይነት ሰማዕት ለመሆን እንዘጋጃለን፡፡



3. ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ

በቅዱስ መጽሐፍ በዚህ መልኩ የዕለተ ዐርብ ሰዎች መሆን አቅቷቸው በየሁኔታው የተገራገጩ ሰዎች የመኖራቸው ያህል መከራው ከጀመሩት ጉዞ ሳያገራግጫቸውና እየሆነ ባለው ሳይሸማቀቁ የዕለተ ዐርብ ሰዎች መሆን የቻሉም አሉ፡፡



ከእነዚህ ጥቂት የዕለተ ዐርብ ሰዎች መካከል አንዱ ፍቁረ እግዚእ፣ ወልደ ነጎድጓድ፣ ነባቤ መለኮት፣ አቡቀለምሲስ፣ ቁጽረ ገጽ በመባል የሚታወቀው እና በሕይወቱና በኑሮው ጌታን ለመምሰል ይጥር የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡



ቅዱስ ዮሐንስ የምሴተ ሐሙስ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ የዕለተ ፋሲካም ሰው ብቻም አልነበረም፡፡ እርሱ የዕለተ ዐርብ ሰውም እንጂ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሁሉም ጌታን ጥለው ሲሔዱ የአይሁድን ዛቻ ሳይፈራ፣ ክርስቶስን በመከተሉ ሊያደርሱበት የሚችሉትን መከራ ሥጋ ሳይሰቀቅ ከእናቱ ድንግል ማርያምና ከጥቂት ቆራጥ ሴቶች ጋራ በእግረ መስቀሉ ሥር በመገኘት የዕለተ ዐርብ ሰው የሆነ ብቸኛ ሐዋርያ ነው፡፡

የክርስትና ሕይወት የመስቀል ጉዞ ነው፡፡ የመስቀለ ጉዞ ደግሞ የሐሙስ ሰው እና የፋሲካ ሰው መሆንን ብቻ ሳይሆን እንደ ቅዱስ ዮሐንስ በጥብዓት የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን የሚጠይቅ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ የአይሁድን ዛቻ ሳይፈራ እና መከራ ሳይሰቀቅ ከጌታው ጋራ እንደቆመ ሁሉ የዚህች ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፤ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ዘማርያን እና ምእመናን ነን የምንል ሁሉ ..ለቤተ ክህነቱ ገዥ.. መደቦች ዛቻና ማስፈራሪያ፤ ለተሐድሶ መናፍቃን ቀረርቶ ሳንበገር በቆራጥነት ለቤተ ክርስቲያን በመከራዋ ዕለት የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን ይጠበቅብናል፡፡



ቅዱስ የሐንስ የዕለተ ዐርብ ሰው በመሆኑ የተገኘው ቀራንዮ እንጂ የክርስቶስ ከሳሾች በሆኑት በአይሁድ ሸንጎ፣ በጲላጦስ ጓዳ አይደለም፡፡ የዕለተ ዐርብ ሰው ቀራንዮ በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለቅዳሴ፣ ለማኅሌት፣ ለሰዓታት ጉባኤ ዘርግቶ ለማስተማርና ለመማር  እና ስለ ሰላሟ፣ ስለ ዶግማዋ፣ ቀኖናዋና ትውፊቷ መጠበቅ ለመወያየት ይገኛል እንጂ እርሷነቷን ለማጥፋት በሚጎነጉኑ የአድማና የሴራ ሸንጎ አይገኝም፡፡ በውሉዳነ ጲላጦስ ጓዳም አይርመጠመጥም፡፡ የእርሷ ጲላጦስ እና ውሉደ ጲላጦስ ማንና ምን እንደሆነ እናውቃለንና፡፡



የዕለተ ዐርብ ሰው የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ የጌታን መከራ ሞት የራሱ መከራ ሞት፤ የጌታን ሕማም የራሱ ሕማም፤ የጌታን በዘንግ መመታትና በጥፊ ፊቱን መጸፋቱን የራሱ መመታትና መጸፋት፤ የጌታን 6666 ጊዜ መገረፍ የራሱ መገረፍ፤ የጌታን በጎዳና መውደቅ መነሣት የራሱ መውደቅ መነሣት፤ የጌታን የእጆቹ መጋፊያና መጋፊያ እስኪጋጠም ወደ ኋላ መታሰር የራሱ መታሰር፤ ከምሰሶ ወደ ምሰሶ መንገላታቱን የራሱ መንገላታት፣ በቅንዋተ መስቀል መቸንከሩን የራሱ መቸንከር አድርጎ በመውሰዱ ከጌታው ከመከራ ሞቱ አልተለየም፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያንም መከራዋን መከራው፤ ስደቷን ስደቱ፤ ውድቀቷን ውድቀቱ፤ ውድመቷን ውድመቱ፤ ውርደቷን ውርደቱ ፤ ጭንቀቷን ጭንቀቱ አድርጎ የሚያስብላት የዕለተ አርብ የመከራ ዘመን ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ ሰንበት ተማሪና ምእመን ዛሬ ያስፈልጓታል፡፡ እርሷ ያጣችው ይኽንን ነውና፡፡ መከራም እየተቀበለች ያለችው በእነዚሁ ነውና፡፡

እኛ ለዚህች ታላቅ ቤተክርስቲያን  የደስታ ዘመን፣ የፍስሐ ዘመን እና የደመወዝና የአበል ሰዎች ብቻ ከሆንላት ከአሕዛብ ከመናፈቃን በምን ተለየንላት? እነዚህ ሰዎች ከሰሙነ ሕማማቱ፣ ከጾሙና ከስግደቱ የሉበትም ከፋሲካው፣ ከደስታው ግን አሉበት፡፡ እኛ የዚህች ቤተ ክርስቲያን የደስታዋ፣ የፋሲካው ተካፋይ ብቻ ከሆንን ልጆች መሆናችን እምኑ ላይ ነው? የደስታዋ ተካፋይ መሆን የምንችለው በሕማሟም ተካፋይ ስንሆን ብቻ ነው፡፡ እኛን ከእነርሱ የሚለየንም ይኸው የዕለተ ዐርብ ሰዎች መሆናችን ነው፡፡



የዕለተ ዐርብ ሰው ቀራንዮ ወጥቶ ባዶ እጁን አይመለስም፡፡ የዕለተ ዐረብ ሰው የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ የድርሻውን ለመወጣት ቀራንዮ ወጥቶ ባዶ እጁን ያለዋጋ አልተመለሰም፡፡ ከስጦታ በላይ ስጦታ፤ ከዋጋ በላይ ዋጋ የሆነች ድንግል ማርያምን ይዞ ተመልሷል፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዕለተ ዐርብ ሰዎች ከሆንላት ዋጋችንን የማናገኝበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ቁም ነገሩ የድርሻን ለመወጣት ቀራንዮ በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘወትር መገኘት ብቻ ነው፡፡



ቁም ነገሩ ቢያንስ እንደቀሬናው ሰምዖን ከአይሁድ ምክር፣ ክፋት ላለመግባት መሰወር ዋጋ አለው፡፡ እርሱ ነገር ሁሉ ተፈጽሞ ሰላም ይሆናል ብሎ ከተሰወረበት ሲወጣ አይሁድ አገኙት፡፡ በክፋታቸው እና በተንኮላቸው ስላልተባበረ <<አንተም የእርሱ ወገን ነህ ››በማለት ይቀጡት ዘንድ መስቀሉን አሸከሙት፡፡ እነርሱ የቀጡት መሰላቸው እንጂ ንጹሕ ልቦናን ገንዘብ በማድረጉ የሰውን ዋጋ የማያስቀር እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ እንዲሳተፍ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ ፈቀደለት፡፡ /ማቴ. 27/32/



እግዚአብሔር በዚህ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን የዕለተ አርብ ሰው ለሚሆኑላት ዋጋቸውን እንደ ሰምዖን ቀሬና አያስቀርም፡፡ ሲሰጥም ልክ እንደ ሰምዖን ቀሬና በረቂቅ ጥበብ ለጊዜው ማንም በማያስተውለው መንገድ ነው፡፡ መመለስ የሚገባው ጥያቄ ግን ስንቶቻችን ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እና ከቅጥረኞቻቸው ምክር፣ ክፋት ላለመግባት ተሰወርን?



እንዲህም ተባለ እንዲያ ለእኔ ግን ዕለተ ዐርብ ይች ናት፡፡ ሰዎቿም ይኽን ይመሰላሉ፡፡ ለእኔ የአሁኗ ቤተ ክርስቲያንም ይህች ናት፡፡ የሰዎቿም ስብጥር እንዲሁ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ወዴት ታመራ ይሆን?

                                                                                                                                             መልካም በዓል፡፡ (2004ዓ.ም )

Like · ·

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...