2014 ኦክቶበር 10, ዓርብ

ማኅሌተ ጽጌ (Part One

 
 
ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙ መልእክቱ 
           ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እያሰቡ የሚደረስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡
             በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ) የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ ስንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን) ምንስ እንለብሳለን) ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.5÷28-33/ በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡
                እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ወሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና» /መዝ.12÷14-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት የረገፈው ሣር እየተነሣ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡
                     በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 15 ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት «ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል»  /ኢሳ.11÷1/ ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡
                                                                                                                  
                     እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌን እንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌ በመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንም ለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡
1. ጸሎት
            በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡
1.1.  አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ ለሰማዕት በጽጌሁ ሕይወት፡፡
              ጠቢቡ ሰሎሞን «የምእመናንንና የክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ «እንደ ማኅተም በልብህ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ» /መኃ.9÷6/ ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ «አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት» ማለቱ እመቤታችንን እንደ


ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ «በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንኒ ንግሥት» ይላል፡፡ ይኸም ማለት አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢ አቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ በማለት እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ «መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ» እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡
ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረሰዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ አኀሊ፣
ሥረዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሎ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡
            አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ውኃው በተአምራት ኅብስት ይሆንላቸው ነበር፡፡ ይህን ተአምር ከአደነቀ በኋላ «ማርያም ሆይ ሁሉን ማድረግ ትችያለሽና ኃጢአቴን አስተስርይልኝ» ይላል፡፡ ጌታችን «እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም» /ማቴ.17÷1/ በማለት ላመነ የሚሣነው ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ «ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ ...» ብሎ ባበሠራት ጊዜ ይህ እንደምን ይሆንልኛልብላ ስትጠይቅ «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም» ሲላት በፍጹም እምነት ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ እንደቃልህ ይሁልኝ» በማለት የተቀበለች ናት፡፡ ይህንንም ቅድስት ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን ተመልታ «ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና የታመነች ብፅዕት ናት» /ሉቃ.1÷453 ብላ መስክራለች፡፡ ላመኑ ሁሉ የሚቻል ከሆነ እመቤታችን ግን ቅዱሳን ሁሉ የሚማጸኑትን አምላክ በሥጋ ወልዳ ያስገኘች ስለሆነች ለእርሷ የሚሳናት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ነው ላንቺ የሚሳንሽ ነገር የለምና ኃጢአቴን አስተስርዪልኝ፣ የከበደኝን ሁሉ አቅልይልኝ በማለት የለመነው፡፡

2014 ኦክቶበር 8, ረቡዕ

የጅማ ሀገረ ስብከት ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ ተመረቀ


አትም ኢሜይል
መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
jima 2007 3የጅማ ሀገረ ስብከት ያስገነባው ባለ 5 ፎቅ ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅዱስ ፓትርያርኩና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ተመረቀ፡፡

jima 2007ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎችና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ክፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን የጅማ ሀገረ ስብከት ከሃያ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ አራት ሺሕ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን ባለ አምስት ፎቅ ዘመናዊ ሁለገብ ሕንፃ ባርከው ሲመርቁ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ይህ ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ በጣም የሚያስደንቅና ለቤተ ክርስቲያናችን ተጨማሪ ሀብት መሆን የቻለ ነው፡፡ ለሌሎች ሀገረ ስብከቶችም ታላቅ ምሳሌና በአርአያነቱም ተጠቃሽ የሚሆን ነው” ብለዋል፡፡

የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ባቀረቡት ሪፖርትም በጅማ ሀገረ ስብከት 308 አብያተ ክርስቲያናት እንደሚገኙና፤ የዚህ ሕንፃ መገንባት ዋነኛ ዓላማ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አብያተ ክርስቲያናት በካህናትና በበጀት እጥረት jima 2007 2ምክንያት የተቸገሩ በመሆናቸው ሕንፃው ተከራይቶ በሚያስገኘው ገቢ እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት በመደገፍ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ለማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ዝርዝሩንእንደደረሰልን እናቀርባለን፡፡


አርሴማ

ዐጽሟ ያረፈበት አርመን የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን
ቅድስት አርሴማ በ290 ዓም በአርመን በሰማዕትነት ያረፈች ወጣት ክርስቲያን ሰማዕት ናት፡፡ ትውልዷ ሮም ሲሆን ሰማዕትነት የተቀበለችው አርመን ነው፡፡ እኛ አርሴማ ስንላት እነርሱ Saint Hripsime ይሏታል፡፡ ታሪኳን የፈለገ ሰው በዚህ ስሟ ጎጉል ላይ ቢፈልግ በቀላሉ ያገኘዋል፡፡ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መስከረም 29 ቀን ወይም ኦክቶበር 9 ሰማዕትነት የተቀበለችበትን ቀን ያከብራሉ፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን በስሟ የተሠራውም አርመን ኤችሚዚን ውስጥ በ395 ዓም ነው፡፡ ይህ የአርሴማ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ሳይፈርሱ ከኖሩት እጅግ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ ነው፡፡


የዚህች ወጣት ሰማዕት ታሪክ በስንክሳር በመስከረም 29 ቀን ተጽፏል፡፡ በሀገራችን ገድላቸው ከተተረጎመላቸው የውጭ ቅዱሳን አንዷ አርሴማ ናት፡፡ የዚህ ምክንያቱ የታወቀ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ አርመን ከአርመንም ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱና የሚመጡ ቅዱሳን ነበሩ፡፡ በ10ኛው መክዘ አካባቢ በአርመን የደረሰውን የፋርሶችን ወረራ በመሸሽ አያሌ አርመናውያን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና ዛሬ ሐይቅ እስጢፋኖስ በተባለው ቦታ መሥፈራቸውን የአርመን ታሪክ ይነግረናል፡፡ በአርመንኛ ‹ሐይቅ› ማለትም ገዳም ማለት ነው ይላሉ፡፡
                        በአርመን ቤተ ክርስቲያንዋ የሚታወቀው ሥዕል ይህ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በ13ኛው መክዘ ኢትዮጵያዊው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ መጀመሪያ ወደ ግብጽ (1330-32 ዓም)፣ ከዚያም ወደ እሥራኤል በመጨረሻም ወደ አርመን ተጉዘው በዚያ ለአሥራ አራት ዓመታት ከቆዩ በኋላ በ1352 ዓም ዐርፈዋል፡፡ ከእርሳቸው ዕረፍት በኋላም ደቀ መዝሙሮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ እነዚህ የተመለሱ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ደቀ መዛሙርት ብዙ የውጭ ሀገር ቅዱሳት መጻሕፍትን ይዘው በመምጣትና ወደ ግእዝ በመበተርጎም ታላቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ (ዝርዝር ታሪኩን የፈለገ ‹አራቱ ኃያላንን› መመልከት ነው)፡፡ በጎንደር መንግሥት ጊዜም አቡነ ዮሐንስ የተባሉ ቆሞስ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስን ተረፈ ዐጽም ይዘው በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን መጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ከወዲህና ከወዲያ የነበሩ ግንኙነቶች ቅድስት አርሴማን በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንድትታወቅ አድርጓታል፡፡ ገድሏም ወደ ግእዝ ሊተረጎም ችሏል፡፡
በአሁኑ ዘመን አርሴማ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዘንድ ይበልጥ እየታወቀችና እየተከበረች መጥታለች፡፡ ወጣቱ የወጣቷን ሰማዕት አርአያ ማንሣቱ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስለ ክርስቶስ ስትል የከፈለችውን ሰማዕትነት፣ ድንግልናን በብጽዐት ለመጠበቅ ስትል የተቀበለችውን መከራ፣ ወጣትነቷ ሳያጓጓት ለእምነት የከፈለችውን ዋጋ፣ በሕይወቷ ሳለች ከሠራችውም በላይ በሰማዕትነቷ ያፈራችውን ፍሬ በማሰብና ከእርሱም በመማር ዘመኑን ከመዋጀት ይልቅ የሰማዕቷን ዝክር ከትዳርና ከፍቅረኞች፣ ከጥራጥሬና ከታሪኳ ጋር ከማይሄዱ ነገሮች ጋር ማገናኘቱ መልካም አይደለም፡፡
                                                    ቅድስት ባርባር
ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ የቅድስት አርሴማ ሥዕል ነው ተብሎ በስፋት የሚታወቀው ሥዕል በኦርቶዶክስ ሥነ ሥዕል (አይኮኖግራፊ) የቅድስት ባርባራ ሥዕል ነው፡፡ አርመን ኤችሚዚን በሚገኘው መቃብሯ ላይ የሚገኘው ሥዕሏ ከታች የተገለጠው ነው፡፡ ጣና ደሴት ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያንዋም ኢትዮጵያዊውን ሥዕል ማግኘት ይቻላል፡፡
                በመቃብሯ ላይ የሚገኘው ሥዕል
በአጠቃላይ ቅድስት አርሴማ ታሪኳ በመላው ዓለም ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ፣ ከንጽሕናና ቅድስና ጋር በእጅጉ የተገናኘ፣ ለወጣት ሰማዕታት ታላቅ አርአያ የሚሆን፣ ንጽሕናን ለመጠበቅ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ዘመን ምሳሌ የሚሆን፣ ቀደምት እናቶቻችንና እኅቶቻችን ስለ ክርስቶስ ሲሉ የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ በመሆኑ በዓሏም በዚህ መንፈስ መከበር ይኖርበታል፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...