2015 ፌብሩዋሪ 20, ዓርብ

ቅድስት(የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም.


የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ 
ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኅበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ፡፡

ትርጉም:- ለእግዚአብሔር ተገዙ ስሙንም ጥሩ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው ለስሙም ምስጋናን ስጡ /አቅርቡ/ ሰንበትን አክብሩ እውነትንም አድርጉ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችኹም ተቀመጡ ክርስቶስ ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ፡፡

ምንባባት
መልዕክታት
1ኛ ተሰ.4÷1-12:- አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ÷ በእኛ ዘንድ እንደ ታዘዛችሁ በሚገባ ትሄዱ ዘንድ÷ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኙ ዘንድ÷ ደግሞ እንደ ሄዳችሁ ከፊት ይልቅ በዚሁ ታበዙና ትጨምሩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንነግራችኋለን፤ እንማልዳችኋለንም፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ያዘዝናችሁን ትእዛዝ ታውቃላችሁ፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነውና፤ እርሱም ከዝሙት ትርቁ ዘንድ መቀደሳችሁ ነው፡፡ ሁሉም እያንዳንዱ ገንዘቡን ይወቅ፤ በንጽሕናና በክብርም ይጠብቀው፡፡ እግዚአብሔርን እንደማያውቁት እንደ አረማውያንም በፍትወት ድል አትነሡ፡፡ ይህንም ለማድረግ አትደፋፈሩ፤ በሁሉም ወንድሞቻችሁን አትበድሉ፤ አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁና እንደ አዳኘሁባችሁ÷ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር የሚበቀል ነውና፡፡ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኲሰት አልጠራንምና፡፡ አሁንም የሚክድ÷ መንፈስ ቅዱስን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን የካደ አይደለም፡፡

ባልንጀሮቻችሁን ስለ መውደድ ግን ልንጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ራሳችሁ በእግዚአብሔር የተማራችሁ ናችሁና፡፡ በመቄዶንያ ሁሉ ካሉት ወንድሞቻችን ሁሉ ጋር እንዲሁ ታደርጋላችሁ፤ ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ትበዙና ትጨምሩ ዘንድ÷ ሥራችሁንም ታከናውኑ ዘንድ እንደ አዘዝናችሁም በእጃችሁ ትሠሩ ዘንድ÷ በውጭ ባሉት ሰዎችም ዘንድ ከማንም አንዳች ሳትሹ በሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን፡፡

1ኛጴጥ.1÷13:- ፍጻ. ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ክፉ ምኞት አትከተሉ፡፡ ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” የሚል ተጽፎአልና፡፡ ለሰው ፊትም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርድ አብን የምትጠሩት ከሆነ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ በፍርሃት ኑሩ፡፡

ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ፡፡ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር የታወቀ÷ በኋላ ዘመን ስለ እናንተ የተገለጠ፡፡ ከሙታን ለይቶ በአስነሣው÷ ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ቃል ያመናችሁ÷ አሁንም እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሁን፡፡

ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ ወንድሞቻችሁን ትወድዱ ዘንድ÷ ለእውነት በመታዘዝ ሰውነታችሁን አንጹ፤ እርስ በእርሳችሁም ተፋቀሩ፡፡ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡

ግብረ ሐዋርያት
የሐዋ.10÷17-29፡- ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር፡፡

ተጣርተውም፡- ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ፡፡ ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው÷ “እነሆ÷ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፡፡ ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና፡፡” ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና÷ “እነሆ÷ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው፡፡

እነርሱም÷ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት፡፡ እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ፡፡ በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር፡፡

ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት፡፡ ጴጥሮስም÷ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው፡፡ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው÷”ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ፡፡ አሁንም ስለላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ፡፡”

ምስባክ
መዝ.95÷5 እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ

ትርጉም፦ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ ምስጋና ውበት በፊቱ ቅዱሰነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡

ወንጌል
ማቴ.6÷16-24፡- “በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ እንደ ጾሙ ለሰው ይታዩ ዘንድ መልካቸውን ይለውጣሉና÷ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ እናንተስ በምትጾሙበት ጊዜ ራሳችሁን ቅቡ፤ ፊታችሁንም ታጠቡ፡፡ በስውር ለሚያይ ለአባታችሁ እንጂ÷ ለሰዎች እንደ ጾማችሁ እንዳትታዩ፤ በስውር የሚያያችሁ አባታችሁም ዋጋችሁን በግልይ ይሰጣችኋል፡፡

“ብልና ነቀዝ በሚያበላሹት÷ ሌቦችም ቈፍረው በሚሰርቁበት በምድር ለእናንተ መዝገብ አትሰብስቡ፡፡ ነገር ግን ብልና ነቀዝ የማያበላሹት÷ ሌቦችም ዘፍረው በማይሰርቁት በሰማይ ለእናንተ መዝገብን ሰብስቡ፡፡ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይኖራልና፡፡

“የሰውነትህ መብራቱ ዐይንህ ነው፤ ዐይንህ ብሩህ ቢሆን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል፡፡ ዐይንህ ግን ታማሚ ቢሆን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል፤ በአንተ ላይ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማህ እንዴት ይበዛ! ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አገልጋይ የለም፤ ያለዚያ አንዱን ይወዳል፤ ሁለተኛውንም ይጠላል፤ ወይም ለአንዱ ይታዘዛል፤ለሁለተኛውም አይታዘዝም፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም፡፡

ቅዳሴ
ዘኤጲፋንዮስ
ዐቢይ ውእቱ እግዚአብሔር በዕበዩ ቅዱስ በቅዳሴሁ እኩት በአኮቴቱ ወስቡሕ ስብሐቲሁ . . .
ትርጉም፡- እግዚአብሔር በገናንነቱ ገናና ነው በቅድስናው የተቀደሰ ነው በምስጋናው የተመሰገነ ነው በክብሩም የከበረ ነው. . .

2015 ፌብሩዋሪ 18, ረቡዕ

21 የግብጽ ኮፕት ክርስቲያኖች ሰማእትነት ተቀበሉ


አትም ኢሜይል
የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
egypt copts21 የግብጽ ኮፕት ክርስቲያኖች ራሱን ኢስላሚክ ስቴት /ISIS/ እያለ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን በምሥራቃዊ ሊቢያ ሲርት ውስጥ የካቲት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰማእትነት ተቀበሉ፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በላከው የአምስት ደቂቃ የምሥል ወድምጽ መረጃ አጋቾቹ ሰውነታቸውን በጥቁር አልባሳት በመሸፈን፤ ታጋቾቹን ደግሞ ብርቱካናማ ልብስ በማልበስ ወደ የባሕር ዳርቻ በመውሰድና በጉልበታቸው በማንበርከክ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ አንገታቸውን ቀልተዋቸዋል፡፡

በእምነታቸው ምክንያት የታገቱት እነዚህ የኮፕት ክርስቲያኖች ለሥራ ፍለጋ ከግብጽ ወደ ሊቢያ የሔዱ ሲሆን፤ በታጣቂዎቹ መታገታቸውን ቢቢሲ እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች ዘግበዋል፡፡

የክርስቲያኖቹ መገደል ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፤ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት፤ የሀገራት መሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የመንግሥታት ሓላፊዎች ተቃውሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ “በክርስቲያኖቹ ግድያ ጊዜውን የጠበቀ አጸፋ ለመመለስና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ያሉንን አማራጮች ሁሉ እንድንጠቀም እንገደዳለን” ብለዋል፡፡
 

በተያያዘ ዜና የግብጽ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖቹን ሰማእትነት ለማዘከር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናቷ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ጾም፤ ጸሎትና ቅዳሴ እንዲደረግ አውጃለች፡፡

2015 ፌብሩዋሪ 17, ማክሰኞ

የዘወረደ ምንባብ (ዕብ.13÷7-17)


አትምኢሜይል
የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም የሚኖር እርሱ ነውና፡፡

 ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያአልተጠቀሙምና፡፡ ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤ ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር፡፡

ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ፡፡ አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን÷ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ፡፡ በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም የምትመጣውን እንሻለን እንጂ፡፡ በውኑ እንግዲህ በሰሙ አናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡


 (ያዕ.4÷6 )
ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡


 (ሐዋ.25÷13- ) 
ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡ በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው÷ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ፡፡ በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ፡፡ አኔም፡- ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም÷ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው፡፡

ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ÷ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ፡፡ የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ÷ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው÷ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤ ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት፡፡” አግሪጳም ፊስጦስን÷ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወደለሁ” አለው፤ ፊስጦስም÷ “እንግደያስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው፡፡


በማግሥቱም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጡ፤ ከመሳፍንቱና ከከተማው ታላላቅ ሰዎች ጋርም ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ፊስጦስም እንዲህ አለ÷ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ÷ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ወንድሞቻችን ሁላችሁ÷ ስሙ፤ አይሁድ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው በኢየሩሳሌምም ሆነ በዚህ እየጮሁ የለመኑኝ ይህ የምታዩት ሰው እነሆ፡፡ እኔ ግን ለሞት የሚያደርሰው በደል እንዳልሠራ እጅግ መርምሬ÷ እርሱም ራሱ ወደ ቄሣር ይግባኝ ማለትን ስለወደደ እንግዲህ ልልከው ቈርጫለሁ፡፡ ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የታወቀ ነገር የለኝም፡፡ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን አገኝ ዘንድ ወደ እናንተ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ ወደ አንተ አመጣሁት፡፡ የበደሉ ደብዳበቤ ሳይኖር እስረኛን ወደ ንጉሥ መላክ አይገባምና፤ ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል፡፡”



ነፍስና ሥጋ የውል ስምምነት ተፈራረሙ

አትምኢሜይል


የካቲት 10ቀን 2007ዓ.ም. 
በመ/ርት ጸደቀወርቅ አሥራት
ነፍስና ሥጋ እንደከዚህ በፊቱ ለሚጠብቃቸው ከባድ የሥራ ኃላፊነትና አለመግባባት የውል ስምምነት ተፈራረሙ። የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት በዚህ ሣምንት የገባውን የዐቢይ ፆም ምክንያት በማድረግ ነው።

በውሉ ሥነ ሥርዐት ላይ ነፍስ እንደገለጸችው ከዚህ በፊት በአጽዋማት ጊዜ በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ውሉ ጠቃሚነቱ የጎላ ነው። ባለፉት ዓመታት ሥጋ የአጽዋማትን ወቅት ጠብቆ ነፍስ ተገቢውን ድርሻ እንዳትወጣ እንቅፋት እየሆነ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸው ስምምነቱ በመካከላችው ሰላም እንዲሰፍን ምክንያት ይሆናል ያሉን በስምምነቱ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት የነፍስ አባት ናቸው።
ከፊርማው ሥነ ሥርዐት በኋላ ባነጋገርነው ወቅት ስምምነቱን ተቀብሎ የነፍስን ሥራ ሳይቃወም ሊገዛላት መዘጋጀቱን ሥጋም ቢሆን አልሸሸገም። በሥነ ሥርዐቱ ላይ የተገኙት ሌሎች ምዕመናንም ሥጋን በቃልህ ያጽናህ እያሉ ከስብሰባው አዳራሽ ሲወጡ እንደተሰሙ “ሪፖርተራችን” ዘግቦልናል።

2015 ጃንዋሪ 27, ማክሰኞ

እመቤቴ ማርያም ሆይ፤ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል፡፡ መልክአ ማርያም





በዲያቆን ንጋቱ አበበ

 ቅዱሳን ሐዋርያት፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእነርሱ በመለየቷ ፈጽመው ያዝኑ ነበር። ከእለታት በአንዱ ቀን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ተገለጠላቸውና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሚያዩ ተስፋ ሰጣቸው። በዚያን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን እየሰበከ፤ እያስተማረ፤ ሕዝበ ክርስቲያንን እያጽናና እስያ በምትባል ሃገር ነበር። ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ተነጥቆ፤ ተድላና ደስታ ከሰፈነባት ቦታ ወደ ገነት ሄደ። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት አናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሯት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው። ቅድሳን መላእክቱም
እንደታዘዙት አደረጉ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ወጣ። ጌታችንም

እንዲህ እያለ አረጋጋት። የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘለዓለማዊ ወደ ሆነ መንግስተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነይ። ያን ጊዜ በገነት ያሉ ዕፅዋት በሙሉ አዘነበሉ ሰገዱ። ቅዱሳን መላእክትም፤ ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ አያመሰገኗት እያወደሷት በእልልታ ወደ ሰማይ አሳረጓት። ቅዱስ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ። ቅዱሳን ሐዋርያትም ተሰብስበው ሳለ፤ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እረፍት ፈጽመው እያዘኑ እየተከዙ ሳለ አገኛቸው። እርሱም እንዳየና እንደሰማ፤ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው። ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስም አንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ። ፈጽመው እያዘኑ ሳሉ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ሥለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን አብዝታችሁ ታዝናላችሁ? እነሆ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባል አላቸው። ይህንንም ብሎ ከእርሳቸው ዘንድ ወደ ሰማያት አረገ። ቅዱሳን ሐዋርያትም አመት ሙሉ ቆዩ። የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት፤ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አላቸው። አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሳየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባኤ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው። በልጇ በወዳጇ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በሷ ደስ እንዲለን። በዚያን ጊዜም ቅዱስ ዮሐንስ እንዳላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ ወር መጀመሪያ እስከ 16ተኛው ቀን ድረስ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ። ሱባኤ በያዙ በአስራ ስድስተኛው ቀንም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጇ ተቀምጣ፤ ከሥጋዋ ተዋሕዳ፤ ተነስታ እመቤታችንን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ ቅዱሳን ሐዋርያትን ባረከቻቸው። እነርሱም ፈጽመው ተደሰቱ። ጌታችንም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ሆነ። ቅዱስ እስጢፋኖስም አዘጋጀ። ቅዱስ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ። ሁሉም ቅዱሳን ሐዋርያት በመሰዊያው ዙርያ ቆሙ። በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ። ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። ከዚያም በሱራፌልና በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት። በዚህች ቀን የሆነ የእርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችስ ቅዱሳን ሐዋርያትን እዘዣቸው። መታሰቢያሽን የሚያደርግ ሁሉ ተጠብቆም በዚህች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም። መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ፤ በዚህች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት በቸርነቴ እጎበኘዋለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇን ወዳጇን ጌታችንን እንዲህ አለችው። ልጄ ሆይ እነሆ በአይኖቻቸው አዩ፤ በጀሮቻቸውም ሰሙ፤ በእጆቻቸውም ዳሰሱ ሌሎች ታላላቅ ድንቅ ተአምራትንና ሥራዎችን አዩ ብላ ከነገረችው በኋላ ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ።
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ምዕመናን ሆይ የፈጣሪን እናት የ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በፍጹም ደስታና በመልካም ምግባር መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለ እኛ ወደ ተወደደ ልጇ ሁልጊዜ ትማልዳለችና።
ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን
በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን። በረከቷ፤ ፍቅሯ፤ ጣዕሟ በእኛ በልጆቿ ላይ አድሮ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመሞቷ በፊት በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበር። መንፈስ ቅዱስም ለእመቤታችን ከዚህ ዓለም እንደምትለይ ነገራት። ጌታችንም በደብረ ዘይት ላሉ ደናግላን ነግሯቸዋልና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጥነት መጡ። እርሷን መንፈስ ቅዱስ የነገራትን ነገረቻቸው።

           በዲያቆን ንጋቱ አበበ


እነሱም እንደመጡ ባየች ጊዜ እንዲህ ብላ ጸለየች። ልጄ ውዳጄ፤ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናየን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚህች ሰዓት አምጣው፤ እንዲሁም በሕይወት ያሉትንና በሕይወት የተለዩንን ቅዱሳን በሙሉ ወደ እኔም አምጣቸው። አንተ የሕያዋን አምላክ ነህና፤ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን አለች። በዚያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ቅዱስ ዮሐንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደረሰችው። ቅዱስ ዮሐንስም እንደደረሰ ሰገደላትና በፊቷ ቆሞ እንዲህ አላት፤ ሰላምታ ይገባሻል ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልደሽልናልና፤ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። አንቺ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ትሄጃለሽና። እመቤታችንም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እንዲህ ብላ አምላኳንም አመሰገነችው። ጌታዬ አምላኬ ፈጣሪዬ ሆይ፤ ላንተ ክብር ምስጋና ይገባል። የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና። አሁንም ነብሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊይሳርጓት ከሚመጡ መላእክቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ። በዚህን ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ድምጽ መጣ፤ እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ። ቅዱሳን ሐዋርያትም ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ይደርሳሉ። ቅዱሳን ሐዋርያት ከዚህ ዓለም የተለዩትም፤ በሕይወት ያሉትም ሁሉ በአንድነት መጥተው ለእመቤታችን ሰገዱላት። እነርሱም አመሰገኗት እንዲህም አሏት። ጸጋን የተመላሽ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይብልሽ ፈጣሪያችን ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከእርሱ ጋር ያሳርግሻልና አሏት። በዚህን ጊዜ እመቤታችን በአልጋዋ ላይ ተቀመጠች። ቅዱሳን ሐዋርያትንም እንዲህ አለቻቸው። ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እኔ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን አወኩ። ከዚህ ከሥጋዬ ወጥቼ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እሔዳለሁ። ነገር ግን እናንተ እኔ ከዚህ ዓለም እንደምለይ ማን ነገራችሁ? አወቃችሁ? ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱሳን ሐዋርያት በሙሉ ወደ አንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን፤ መጣን አሏት። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ይን ነገር ከቅዱሳን ሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ አምላኳን አመሰገነች። እንዲህም አለች ከ እንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል። ይህን ብላ እንደጨረሰች እጣን አምጥታችሁ በማጠን የፈጣሪዬን ስም ጥሩት አለቻቸው። እነሱም እንደታዘዙት አደረጉ። በዚህን ጊዜ ጌታችን ተገልጾ ብዙ ድንቅ ተአምራትን አደረገ። በሽተኞች ወደ እመቤታችን ወደ አለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌአቸው ይፈወሱ ነበር። እመቤታችን ከሥጋዋ የምትለይበት ሰዓት ሲደርስ ቅዱሳን ሐዋርያትንና ደናግልን ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት። እመቤታችንም እጇን ዘርግታ ባረከቻቸው። በዚህን ጊዜ ፈጣሪያችን ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጎናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከ እርሱ ጋር አሳረጋት። ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው፤ ወደ ጌቴ ሰማኒ ተሸክመው እንዲወስዷ ሐዋርያትን አዘዛቸው። ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃን እያየች ነበር። እመቤታችንም ፈጣሪዋን ልጇን ወዳጇን እንዲህ ብላ ጠየቀችው። ልመናየን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ። በስሜ ወደ አንተ የሚለምነውን ሁሉ፤ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወደ አንተ የሚለምነውን ከመከራም ሁሉ አድነው፤ በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሃሊ ነህና መታሰቢያየን በውስጧ የሚያደርጉባትን የሁሉንም መስዋእታቸውን ተቀበል። ፈጣሪም እንዲህ ብሎ መለሰላት። የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ። እመቤታችንም ከአረፈች በኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴ ሰማኒ ሊወስዷት ሐዋርይት ገንዘው ተሸከሟት። አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊይቃጥሉ መጡ። ከ እነርሱም አንዱ ከምድር ይጥላት ዘንድ ይእመቤታችንን አልጋዋን ያዘ። ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በአልጋው ላይ ጠንጠለጠሉ። ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ እያለ ለመነ። የ እውነተኛ አምላክ ይጌታ ኢይሱስ ክርስቶስ እናት አንቺ በ እውነት ድንግል ይሆንሽ በ እኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ አለምንሻለሁ። በሐዋርይትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደህና ሆኑ። እመቤታችን በቀብሯት ጊዜ ከዚያ ሶስት ቀን ኖሩ እረፍቷም የነበረው እሁድ ቀን ጥር 21 ነብር። ጌታችንም ብርሃናውይን መላእክትን ልኮ ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሯት። ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲያሳርጓት እመቤታችንን አገኟት ። መላእክትም ለአምላክ እናት ለ እመቤታችን ድንግል ማርይም ና እጅ ንሳ አሉት እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከ እርሷም ተባረከ ከዚህም በኋላ ወደ ሐዋርያት ደረሰ። እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንደ አረፈችና እንደ ቀበሯትም ነገሩት። ቅዱስ ቶማስም ሥጋዋን እስከ ማይ አላምንም አላቸው። ሥጋውንም ይሳዩት ዘንድ ወደ መቃብሯት በአደረሱት ጊዜ ከመቃብሩ ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችን እንዳገኛት ነገራቸው። ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የ እመቤታችንን ዕርገቷን ኡ ስላላዩ እጅግ አዘኑ ሥጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው። ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ሰጣቸው። እነርሱም በተስፋ እስከ ነሐሴ 16 ቀን በተስፋ ኖሩ። የ እመቤታችንም የእድሜዋ ዘመን 64 ዓመት ነው። በአባትና በእናቷ ቤት 3 ዓመት፤ በመቅደስም 12 ዓመት፤ በዮሴፍም ቤት 34 ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ ዕርገት በኋላ በወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ቤት 14 ዓመት ነው። 

ይቆየን…………….

የሕይወት የድህነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
 
የእመቤታችን በረከቷ ረድ ኤቷ ይደርብን አሜን!!!

2015 ጃንዋሪ 10, ቅዳሜ

የታክሲ ሾፌሮች፤ ረዳቶችና ተራ አስከባሪዎች ጉባኤ 8ኛ ዓመት ተከበረ


አትም ኢሜይል
ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም.
በደመላሽ ኃይለ ማርያም
የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ለታክሲ ሹፌሮች፣ ተራ አስከባሪዎችና ረዳቶቻቸው አገልግሎት እንዲሰጥ የመሠረተውን ጉባኤ 8ኛ ዓመት አስመልክቶ ታኅሣሥ 25 እና 26 ቀን 2007 ዓ.ም. “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ” በሚል የመጽሐፍ ቅዱስ መሪ ቃል በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ አባላቱና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ተከበረ፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብሩ አስተዳዳሪ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ ሲሆን፤ የታክሲ አገልግሎት ሥራን በሚመለከት ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር አያይዘው “ኖላዊ” በሚል ርዕስ በተጋባዥ መምህራን ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡

የታክሲ ሹፌሮች፣ ረዳቶቻቸው እና ተራ አስከባሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን በጎ ያልሆነ ግንኙነት ለማሻሻል እና በክርስትና ሕይወታቸው ምሳሌ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍራት እንዲቻል፤ እንዲሁም በእነሱ ቸልተኝነት እና ጥድፊያ በመኪና አደጋ እየጠፋ ያለውን የሰውን ሕይወት ለመቀነስ ታስቦ ጉባኤው መመስረቱን የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ ዲያቆን ያሬድ ያስረዳል፡፡

ዲያቆን ያሬድ አክሎም “የአባላቱን ቁጥር ከዚህ የበለጠ በማሳደግና በጉባኤው ውስጥ በማካተት ትምህርተ ሃይማኖት እንዲማሩ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊት እንዲያውቁ፤ በሥነ ምግባር የታነጹና ሥርዓት አክባሪዎች ሆነው ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ ከፈጣሪ ጋር እንጥራለን” ብሏል፡፡

ከተጋባዥ እንግዶች መካከልም የአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ም/ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ድንገተኛ፤ ለንስሐ እና ለኑዛዜ የማያበቃውን በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት ለመከላከል ምእመናን እና የታክሲ ሹፌሮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጪው ዓመት ሃምሳኛ ዓመቱን የሚያከብረው ይህ የፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት እየሠራ ያለው ሥራ እጅግ በጣም ሊበረታታ የሚገባውና በሌሎችም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሊለመድና ሊሰራበት እንደሚገባ ጉባኤውን የተከታተሉ ምእመናን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...