2015 ኤፕሪል 7, ማክሰኞ

ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች በሰሙነ ሕማማት


አትምኢሜይል
መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም.
በዓቢይ ጾም ከሰርከ ሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፤ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ አለመሳሳም፤ አክፍሎት፤ ቄጤማ ማሰር፤ ጥብጣብ፤ ጉልባን እና ሕጽበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለ እነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈጻጸም መዛግብት አገላብጠን፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

አለመሳሳም፡-
በሰሙነ ሕማማት ምእመናን መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፤ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡

ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ €œእንስቀለው . . . እንግደለው€ ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያንን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፤ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሰላምታ የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡

ይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ €œእኔ የምስመው እርሱ ነው ያዙት ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው፤ ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት /የተቀደሰ ስጦታ/ አይደለም፤ ተንኮል የተሞላበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሄዋንን €œሰላም ለኪ€ ብሎ ነው ያታለላት፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት የሰላምታ ልውውጥ አይደረግም፡፡

ሕጽበተ እግር፡-
የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበት፤ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው፡፡

ሕጽበተ እግር ጌታችን €œእናንተ ለወንድማችሁ እንዲህ አድርጉ€ በማለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው €œእኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ€ /ዮሐ.13፡16-17/ በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡

ጌታ በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር ሲያጥብ €œእኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአያን ሰጥቻችኋለሁ፤ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል€ አለ፡፡ ደቀመዛሙርቱም €œማን ይሆን?€ አሉ፡፡ ጌታም ኅብስት ቆርሼ፤ ከወጡም አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው€ አላቸው፡፡ ደቀመዛሙርቱም ደነገጡ፡፡ ይሁዳን ማመልከቱ ነበር፤ ለጊዜው ግን አልገባቸውም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማራቸው በኋላ፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመስጠት የኦሪትን መስዋዕት የሻረው እና መስዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ ዕለት ነው፡፡

በዚህ ሃይማኖታዊ መነሻነትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በወሎና በጎንደር ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ብቻ የሚጋገር የተለየ ዳቦ አለ፡፡ ይህ ልዩ ዳቦ በወሎ €œትኩሴ€፤ በጎንደር ደግሞ €œሙገራ€ ይባላል፡፡ ይህ ዳቦ ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸውን ኅብስት አምሳያ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከዚህ ቀን ውጪ በሌላ ጊዜ አይጋገርም፡፡ በመሆኑም ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚከበርባቸው እንደ ማኅበርና ሰንበቴ በመሳሰሉት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች የሚቀርብበት ጊዜ አለ፡፡

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስበከት በቅዱስ ላሊበላ አጠገብ በሚገኘው የይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጣርያ ላይ ካህኑ €œትኩሴ€ ዳቦ ሲባርክ የሚያሳይ ሥዕል አለ፡፡

በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዕለቱ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ጸጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ያን ቀን ያልተላጨ ልጅ €œኃጢአት ይሆንበታል€ ስለሚባል ሳይላጭ የሚውል የለም፡፡ ልጃገረዶች በበኩላቸው በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን እንግልትና መስቀል ለማዘከር ነው ተብሎ ይነገራል፡፡

እነሆ ይህንን ዕለት በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ቀሳውስት ያሉት አባቶች በያሉበት አጥቢያ /ደብር/ በመገኘት በመዓርግ የሚያንሷቸውን የካህናት፤ የዲያቆናት እና የምእመናንን እግር ያጥባሉ፤ የሚያጥቡትም የወይራና የወይን ቅጠል በውኃ በመዘፍዘፍ ነው፡፡

አክፍሎት፡-
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ ሰዓት/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከአርብ እስከ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ብዙዎች ያከፍላሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን፤ ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡

ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬኔዎስ፤ አውሳብዮስ የተባሉ ጸሐፍት፤ ሐዋርያት በሰሙነ ሕማማት ከደረቅ ዳቦ እና ከትንሽ ውኃ በቀር እንደማይመገቡ፤ ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉም ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኸው ነው፡፡

ጉልባን
ጉልባን ከባቄላ ክክ፤ ከስንዴ ወይም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲሁም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም አብዛኞቹን የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይታሰባል፡፡

ጥብጣብ፡-
በሰሙነ ሕማማት ዕለት ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው በሕማማት ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ፤ ሲጸልይ፤ ሲያነብ ከዋለ በኋላ ሰርሆተ ሕዝብ /የሕዝብ መሰነባበቻ/ ከመሆኑ በፊት በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምእመን ጀርባ ቸብቸብ መደረጉ የጌታን ግርፋት ለማሰብ ነው፡፡ ማቴ.27፡26፤ 19፤1-3/

ቄጤማ፡-
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ€ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላም እንደሰጠን እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ገጸ በረከት ያቀርባሉ፤ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡

በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው፤ ቃጭል ሲያቃጭሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቁ ምእመናን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፤ ከሚያዝያ 1-5 ቀን 2004 ዓ.ም.

2015 ኤፕሪል 2, ሐሙስ

ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት ወምስጢራት


አትምኢሜይል
በዲ.ቸሬ አበበ 

ከአባታችን አዳም በደል ወይንም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሰፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የሆነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የሆነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ የሌለውን ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጡአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ሆነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ሆነን፡፡
 
ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው? 

ሰመነ ስምንት /ሳምንት/ አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልእት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡

መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት

ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/

ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ /የቤተ መቅደስ መንጻት/ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ /ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ አጸደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ ...»፤ ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡

ዕለተ ሠሉስ /ማክሰኞ/

ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡ /ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ «ወይቤሎሙ ኢየሱስ አማን እብለክሙ ከመ መጸብሓውያን ወዘማውያት ይቀድሙክሙ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር»፤ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/

ዕለተ ረቡዕ

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ የምክር ቀን በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሶበ ኀፀቦሙ እገሪሆሙ ነሥአ አልባሲሁ ወረፈቀ ካዕበ ወይቤሎሙ አእመርክሙኑ ዘገበርኩ ለክሙ ... ወሶበ አነ እንከ ሊቅክሙ ወእግዚእክሙ ኀፀብኩክሙ እገሪክሙ ከማሁኬ አንትሙኒ ይደልወክሙ ትኅፅቡ እግረ ቢጽክሙ፡፡»፤ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?... እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡

ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡

አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን?  አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/

የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡

ቀዳሜ ስዑር

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈበት ዕለት ነች፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈበት ሰንበት ዐባይ /ታላቋ ሰንበት/ ትባላለች ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዘፍ.1፡3፡፡

ዕለተ ቀዳሚት /ሰንበት ዐባይ/ በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ሁሉ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል፡፡ ማቴ.27፡61፡፡

በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡ ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡

በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፡-በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» የምሥራች እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ይታደላል ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡

«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡

የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡ 
 
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡አሜን፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

2015 ማርች 19, ሐሙስ

በተመሳሳይ ኃጢአት እየወደቅኩ ተቸገርኩኝ፡፡ ምን ላድርግ?


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሑደ አምላክ አሜን!!!
        ውድ መቅረዛውያን እንዴት አላችኁ? በዛሬው ጽሑፋን ከአንባብያን ከተላኩልን ጥያቄዎች አንዱን ካህናትን ጠይቀን መልስ ይዘን መጥተናል፡፡ መልሱን የሚሰጡን በቀበና መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ እንዲኹም በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም የመጻሕፍተ ሐዲሳት የ5ኛ ዓመት ደቀ መዝሙር የኾኑት ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ናቸው፡፡ ለርሳቸው ተናጋሪ አንደበት ለእኛም ሰሚ እዝነ ልቡና ያድለን፡፡ አሜን!!!
ጥያቄ፡- “እንደምን አላችኁ መቅረዞች? እባካችሁ አንድ ኃጢአት በተደጋጋሚ እሠራለሁ፡፡ ንስሐ አባቴ ጋር በተደጋጋሚ ብሔድም ኃጢአቴን መተው አልቻልኩም፡፡ ምን ላድርግ? እባካችሁ ጉልበት የሚኾነኝ ምክር ስጡኝ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡”
 
        ቀሲስ ፋሲል ታደሰ፡- አንድ ሰው “ምን ላድርግ?” ብሎ ሲጠይቅ መንፈሳዊ ሕይወትን መፈለጉ ማሳያ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን “ምን ማድረግ ይገባኛል?” የሚል ጥያቄ ካነሣ ለማደግ መፈለጉን፣ መንፈሳዊ መፍትሔ መሻቱን፣ እግዚአብሔር እንደሚረዳው በማያጠያይቅ መንገድ ማመኑን ያመለክታል፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሚያስተምርበት ጊዜ ሕዝቡ፣ ቀራጮች እንዲኹም ጭፍሮች እየመጡ፡- “ምን እናድርግ?” ይሉት ነበር /ሉቃ.3፡10-14/፡፡ ስለጠየቁም “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ብሏቸዋል /ማቴ.3፡8/፡፡ ሐዋርያት ሲያስተምሩ፡- “ወንድሞች ሆይ! ምን እናድርግ?” ያሉት የገባቸው ናቸው /ሐዋ.2፡37/፡፡ ስለዚኽ ምንም ደካሞች ብንኾንም ድካማችንን ከእኛ የሚያርቀው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር “በርሱ ቃል እታነፃለኁ፤ እመከራለኁ” ብሎ “ምን ላድርግ?” ብሎ መጠየቅ ታላቅነት፣ አንድም ትሕትና፣ አንድም የመንፈሳዊ ሕይወት ፍላጎትን የሚያሳይ ነውና ኹል ጊዜ ጠያቂዎች ለካህናት፣ ለቤተ ክርስቲያን መምህራን “ምን ማድረግ ይገባኛል?” ብለው ሲጠይቁ ሊበረታቱ ይገባቸዋል፡፡ በመኾኑም ውድ ጠያቂያችን ምሥጢራቸውን በማካፈል የኃጢአት ልምምድ ድል መንሻ ጥበባትን እንድንማማር ምክንያት ስለኾኑን በልዑል እግዚአብሔር ስም ላመሰግናቸው እወዳለኁ፡፡
ጥያቄው የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ አበው ሲናገሩ፡- “ሰው ኾኖ የማይበድል እንጨት ኾኖ የማይጤስ” እንዲሉ እንደየኑሮአችን ደረጃ፣ እንደየሥራችን ዓይነት ይለያይ እንደኾነ እንጂ ክርስትና ሕይወታችን ስንመላለስ አንድ ከሚያደርጉን ነገሮች ውስጥ ኃጢአት የሚስማማን መኾኑ ነው፡፡ ጥያቄአችንም ጠያቄአችን እንዳነሡት “ምን እናድርግ?” ነው፡፡ በርግጥም “ምን እናድርግ?”፡-
1.     የኃጢአቱን ምንነትና መነሻውን ማወቅ፡- አንድ ሰው የሚወድቅበት ሌላኛው የማይወድቅበትና ትኩረት የማይሰጠው ሊኾን ይችላል፡፡ ከዚኽ አንጻር ጠያቂው “በተመሳሳይ ኃጢአት ደጋግሜ እወድቃለኁ” ያሉት ኃጢአት ምንድነው? እየተደጋገመ ያስቸገራቸው ምንድነው? ከምንም በፊት የኃጢአቱን ምንነትና መነሻውን ያጢኑት፡፡ መፍትሔው የሚዠምረው ከዚኽ ነው፤ የኃጢአቱን ምንነትና መነሻውን ከማወቅ፡፡
2.    የኃጢአቱን ምንነትና መነሻውን ከለዩ በኋላ ለዚያ ከሚዳርጉን ቦታዎች፣ ወይም ጓደኞች፣ ወይም ኹኔታዎች መሸሽ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ወደምንወድቅበት ኃጢአት የሚገፋፉ ኹኔታዎችን፣ ቦታዎችን ወይም ጓደኛን በአጠቃላይ እንደየኃጢአቱ መነሻነት መራቅ ያስፈልጋል፡፡ “ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ኾነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ኾነህ ትገኛለህ” ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት /መዝ.18፡26/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም፡- “አትሳቱ፤ ክፉ ባለንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ይላል /1ኛ ቆሮ.15፡33/፡፡ በዚኽ መሠረት ጠያቂያችን ብቻ ሳይኾኑ ኹላችንም ኃጢአትን ደጋግመን የምንሠራው በኹኔታዎች ተጽዕኖ ነው? ወይስ በጓደኞች ግፊት? ወይስ በምንሰማው፣ በምናየው፣ በምንዳስሰው ተጽዕኖ? ይኽን በአግባቡ ከለየን በኋላ ከምንጩ ለማድረቅ ለዚያ ከሚዳርጉ ኹኔታዎች መሸሽ ነው፡፡ ይኽን ስናደርግም ከምንም በፊት ኅሊናን ማሳመን ይጠይቃል፡፡ በመቀጠልም አካላዊ ውሳኔ መስጠትን ነው፡፡ ለኃጢአት በሚዳርግ ቦታ ተቀምጠን “በፍጹም አይነካኝም፤ አይደርስብኝም” ማለት መመጻደቅ ነው፡፡ ሰይጣንም እኛን ለመጣል አያርፍምና የምንወድቅበትንም መንገድ ያዘጋጃልና በኅሊናም በአካልም ከዚያ መሸሽ ያስፈልጋል፡፡ የጴጢፋራ ሚስት ዮሴፍን ለክፉ ሥራ ስትከጅለው ቆሞ አልተሟገተም፤ ጥሏት ሸሸ እንጂ /ዘፍ.39/፡፡ ስለዚኽ ለተደጋጋሚ ኃጢአት ከሚዳርጉንና ከሚገፋፉን ነገሮች “እችለዋለኁ፤ እቋቋሟዋለኁ” ብሎ መመጻደቅ ሳይኾን መሸሽ ካለብን መሸሽ ያስፈልጋል፡፡ እንደየኹኔታው በይበልጥም ከክፉ ቦታዎች፣ እንደየኃጢአቱ መነሻነት መሸሽ ያስፈልጋል፡፡
3.    ኃጢአቱ በሥጋም በነፍስም ጎጂ እንደኾነ ማስተዋል፡፡ ይኽ በተመሳሳይ እየወደቅንበት ያለው ኃጢአት በሥጋም ጭምር የሚጎዳን ይኾናል፡፡ ከክርስትና ሕይወት ባሻገር ስብእናን የሚያጎድፍ፣ ጤናን የሚያውክ ሊኾን ይችላል፡፡ ከዚኽ አንጻር የዚኽ ጉዳት በጥልቀት ማስተዋል ያስፈልጋል፤ ጉዳት ማሰብ ለመጠንቀቅ ይረዳልና፡፡
4.    ከመምህረ ንስሐ፣ ከመምህራን እንዲኹም ከመጻሕፍት ትምህርት ማግኘት፡፡እድገት በደረጃ ነው፡፡ በአንድ ጀምበርም ለውጥ ላይመጣ ይችላል፡፡ በመኾኑም በሒደት ያንን የመተው መስመር ውስጥ እንድንጠነክር ከዚኽ ኹኔታም ፈጽመን ለመራቅ በራሳችን ጉልበት ብቻ አንችልም፡፡ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ብሎናልና /ዮሐ.15፡5/፡፡ በዚኽም መሠረት ከመምህራን የምንሰማው የእግዚአብሔር ቃል፣ ከመጻሕፍት የምናገኘው፣ ከመምህረ ንስሐም በጸሎትና በምክር የምናገኘው ሐሳብ ያ እያጠቃንና እየጣለን ያለውን እንዲኹም የምንደጋግመውን ኃጢአት ለማስወገድ ኃይል ይኾነናል፡፡
5.    መንፈሳዊ ተግባራትን ማዘውተር፡፡ እንግዲኽ እንደየ ክስተቱ ለየትኛውም የኃጢአት ተግባር መንፈሳዊ ሕይወት፣ መንፈሳዊ ተግባር ድል መንሻው ነው፡፡ ይኽም “እንዲኽ ያለውን ክፉ መንፈስ ያለ ጾም ያለ ጸሎት ከእናንተ አይወጣም” እንዳለ /ማር.9፡29/ ጾምን፣ ጸሎትን፣ ንስሐን የሕይወታችን መሠረት ማድረግ ነው፡፡
6.    መተውን መለማመድ፡፡ ይኽም ማለት ጠቢቡ “ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር” እንዳለ /ምሳ.23፡17/ “እስኪ ዛሬ ተቆጥቤ ልዋል” ብሎ መወሰን ማለት ነው፡፡ ከዚያ ከምንጠላው ግን ደግሞ እየወደቅንበት ካለው ስሕተት ተቆጥበን ከዋልን ማታ ላይ ተመስገን ብሎ ጸልዮ ማደር ነው፡፡ ነገም ሲነጋ “ዛሬም እንዲኹ እንደ ትናንትናው መንፈሳዊ መንገድና ሒደት ልዋል፡፡ ዛሬም እንዲኽ ካለው ተግባር ፍጹም ተቆጥቤ መዋል አለብኝ፡፡ ደግሞም እችላለኁ፡፡ እግዚአብሔር ያስችለኛል፡፡ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ኹሉን እችላለኁ፡፡ እግዚአብሔር ያበራታኛል” ስንልና ዕለት ዕለት ኹኔታውን እየኰነንነው፣ እያወገዝነው፣ “በዚያ መንፈስ ዛሬ አልውልም፡፡ ይልቁንም በመንፈሳዊ መንገድና በጥንካሬ እውላለኁ” ብለን ስንወስን ያን ውሳኔአችንን እያደነቅን ስለተደረገልን ጥንካሬም ተመስገን እያልን ልምምድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ደጋግመን የምንሠራው ኃጢአት እጅግ ብዙ ዘመናት ከእኛ ጋር የቆየ ሊኾን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ኃይል በላይ የኾነ ኃጢአት የለም፡፡ ዋናው የእኛ ውሳኔ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የምንታለለው እዚኽ ጋር ነው፡፡ ለመተው እንፈልጋለን፤ ለመተው ግን በተግባር አንወስንም፡፡ ንስሐ መግባት የማይፈልግ ሰው የለም፤ በተግባር ወስኖ የሚገባ ግን ጥቂት ነው፡፡ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ መኖር የማይፈልግ ክርስቲያን አይኖርም፡፡ ብዙዎች መቁረብ ይፈልጋሉ፤ ወስነው የሚቆርቡት ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ከዝሙት ኃጢአት መራቅ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ዝሙትን የሚያበረታቱ ማስታወቂያዎችን፣ ዝሙትን የሚያበረታቱ ምስሎችን እንዲኹም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ ዝሙትን የሚያበረታቱ ዘፈኖችን እንዲኹም ጽሑፎችን፣ ዝሙትን የሚያበረታቱ ንግግሮችን ሲያደርጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚኽን ሰዎች ስናያቸው በውስጣቸው ከዚያ ኃጢአት የመራቅ ፍላጎት አለ፤ ተግባሩ ላይ ግን ከዚያ የሚያሸሻቸው አይደለም፡፡ ለዚኽም ነው ጌታ፡- “ብዙዎች ይፈልጋሉ፤ አይችሉምም” ያለው /ሉቃ.13፡24/፡፡ ስለዚኽ ከኃጢአት መራቅ የሚፈልግ ሰው የመተው ልምምድን አኹንኑ መዠመር አለበት፡፡ “ዛሬ ዘፈን አላዳምጥም፡፡ ዛሬን በዚኽ ምትክ መዝሙር አዳምጣለኁ” ብሎ መለማመድ አለበት፡፡ በዚኽ ውሳኔው ጸንቶም ዛሬን ይውላል፤ ያድራልም፡፡ ሌሎች ነገሮችም እንደዚኽ ናቸው፡፡ የመጠጥ ልምድ ያለው ሰው “ዛሬ አልጠጣም፤ ዛሬ በምጠጣበት ሰዓት እዚኽ ቦታ እሔዳለኁ፡፡ እዚያ ሒጄ እውላለኁ፡፡ በበጎ ነገር አሳልፈዋለኁ” ሲል ዛሬን ይውላል፡፡ ማታ ላይ ሲመሽ “ለካ ይቻላል፡፡ ለካስ እኔ ከበረታኁ እግዚአብሔር ያስችለኛል” የሚለውን በኅሊናው ያሳምናል፡፡ ነገሮችን የመተው ልምምድ በተግባር ማሳየት ማለት ይኸው ነው፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያ ያስቸግረን የነበረው ተደጋጋሚ ኃጢአት ታሪክ ይኾናል፤ ለሌላ ሰው መካሪ ኾነን ራሳችንን በለውጥ ቦታ ላይ እናገኟለን፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡         

2015 ማርች 14, ቅዳሜ

ደብረ ዘይት




መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም.
በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድ ነው?/ማቴ. 24፣3/

በዓቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት 5ኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ ተራራ ማለት ሲሆን፣ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት” የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?”/ማቴ. 24፣3/ ብለው ጠይቀውት እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ ለምእመናኑም ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር በመጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶቹን ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን አስመልክቶ የሚነገሩ ምስጢራት እጅግ ሰፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ የምናየው ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር በዓለም እየተከሰቱ ካሉ ወቅታዊ ምልክቶች ጋር በማገናዘብ ይሆናል፡፡

የሰው ልጅ ከሥነ ፍጥረት መነሻ ጀምሮ ስለ ራሱ መጨረሻና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምንነት ማወቅን እንደሚሻ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ከነዚህም በተለይ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ዘይት እለት የምታስተምረው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት’ የዓለሙ ፍሳሜስ ምልክቱ ምንድነው?/ማቴ. 24፥3/’ በማለት የጠየቁት ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ከመለሰላቸው ዋናውና ቀዳሚው የምጽአቱ ምልክት የሐሳዊ መሲህ መምጣት ነው፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ማለት በቀጥታ ትርጉሙ ሐሰተኛ የሆነ በስሙ ማለትም በኢየሱስ፣ በክርስቶስ፣ በአምላክ ስም የሚመጣ የክርስቶስ ተቃዋሚ ማለት ነው፡፡ ትርጉሙን አስፍተን ስናየው፣ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያያዥ የሆኑና ያልሆኑ በዓለም እየተካሄዱ ያሉ ሐሰተኛ ጉዳዮችንና የጥፋት መንገዶችን ያጠቃልላል፡፡ የሐሳዊ መሲሕ የጥፋት ሥራዎች ሳያውቁም ሆነ በተለይ ሆን ብለው በዓለማውያንና በክፉ መናፍስት ተከታዮች እየተፈለሰፉ በሚከሰቱ ሁኔታዎች የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኙ የሃይማኖት የሥነ ተፈጥሮ የጋብቻና የመሳሰሉ ድንበሮች ማፍለስን ዓላማ ያደረጉ፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ባህል፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ሁሉ ከሐሳዊ መሲሕ መደብና ከዓለም ፍጻሜ ምልክትአንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ በዝርዝር ለማየት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፣

1. የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ፡- ”አባቶችህ ያኖሩትን /የሠሩትን/ የቀድሞውን የድንበር ምልክት አትፍልስ” ምሳ.22፥28፣ 23፥10 አፈጻጸሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት እንዳያውቁ ከማድረግ ይጀምራል፡፡ከዚህም አንዱ ሐሳዊ መሲሕ በእግዚአብሔር ስም በተለያየ ሁኔታና መንገድ መገለጥ ነው፡፡ ”እስመ ብዙሃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ፤ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙ ሰዎች በኔ ስም ይነሣሉና” /ማቴ. 24፣5/፡፡ ይህም እንደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና የቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት መሠረት፣ ከክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ በኋላ የሚመጣ፣ ክርስቶስን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ነው ብሎ የማይሰብክ ሁሉ፤ ሌላ አምላክን የሚሰብክ ሁሉ መደቡ ከሐሳዊ መሲሕ ትምህርት ይመደባል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት ያለፉ፣ አምላክ ነን ብለው የተነሡ እንደ ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ /ሐዋ. ሥራ. 5፣36-37/ የመሰሉ ሁሉ ከዚያም በኋላ በየጊዜው የተነሡና በዚህም ወቅት የዋሁን ሕዝብ ”ኢየሱስ ነኝ፣ ኢየሱስ በኛ ዘንድ አለ” እያሉ የሚያጭበረብሩ ሁሉ ሐሳውያነ መሲሖች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ክርስቶስን ከአብ የሚያሳንሱ፣ ”ሎቱ ስብሐት” ነቢይ ነው ብለው የሚያምኑ፣ በመናፍስት አሠራር የሚጠነቁሉ፣ በማቴሪያሊስት /ቁሳውያን/ ወይም በኢቮሉሽን /በዝግመተ ለውጥ/ ትምህርት አምነው አምላክ የለም የሚሉ ሁሉ፣ ወዘተ የሐሳዊው መሲሕ አካላት ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ”ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንደማመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።” /1ዮሐ. 4፣3/ በማለት ይመሰክርባቸዋል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም በመልእክቱ ”ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።” /1ዮሐ. 2፥18/ ይለናል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የክርስቶስ ተቃዋሚ መምጣት የምጽአት ጊዜው መቃረብ ምልክት መሆኑን የማያሻማ ሀሳብ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም የምጽአትን መቅረብ የሚያመለክቱ፣ ስለ ሐሳዊው መሲሕ እና ከርሱ ጋር ተያያዥ ስለሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ተዛማጅ የሆኑትን የሚከተሉትን ትንቢቶች እንመልከት፣

ሀ. ”የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።” /ራእ. ዮሐ. 13፥16-18/ የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ራእይን ሊፈታ ከሚችልበት ትርጉም አንዲት ቅንጣት ብቻ ከዘመኑ አንጻር ብናይ ’የሚናገር የአውሬው ምስል’ ማለትም ለሱ ያልተገዙትን ወይም ቁጥሩን ያልያዙትን የሚናገርባቸው፤ ምልክቱን ያልተቀበሉትን ሊገዙና ሊሸጡ እንዳይችሉ ያደርግል ማለት መኖር፣ መሥራት፣ መሸጥ፣ መለወጥ ወዘተ የሚያግዳቸው ሲል አሁን ባለን ወቅታዊ የዚህ ዓለም አኗኗር አንጻር ሲታይ ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ መታወቂያ ወረቀት፣ ፓስፖርት፣ ቪዛ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወዘተ በዓለም አጠቃላይ አሠራር እና ባንድ ሰው የመኖር ማንነት ሚና ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መታወቂያ ወረቀቶች የሌሉት ሰው ካለበት የትም መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ ጉዳዩን ስናሰፋው በሰለጠኑት ዓለማት አሠራር የእያንዳንዱ ሰው የጣት አሻራ ኮምፒውተራይዝድ በሆነ መንገድ የተደራጀ በመሆኑ፣ እዚያ አደረጃጀት ውስጥ ካልተካተተ በቀር እዚያ ሀገር ሊኖር፣ ሊዘዋወር፣ ሊሠራ፣ ሊነግድ ወዘተ አይችልም፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ እዚህ የኮምፒውተር ድር አደረጃጀት ውስጥ ያለ ሰው የትም ዓለም ቢሄድ በጣቱ አሻራ ይታውቃል፡፡ በትንቢቱ” አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።”  የሚለው ይህን የሚያደራጀው ጉዳዩን የሚያስተሳስረው ሌላ አካል ሳይሆን ሰው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት የሚለው ቁጥር የሰው ልጅ የጅማት ቁጥር ነውና፡፡

ለ. ሌላው የምጽአት መቃረብ ምልክት የሐሳዊው መሲሕ ዘመቻን አውቀው በድፍረት፣ ላላወቁት በረቀቀ መንገድ እግዚአብሔርን ያመለኩ አስመስሎ የእግዚአብሔርን ስም፣ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን፣ ባጠቃላይ በሰማይ የሚያድሩትን መስደብ ነው፡፡ እነዚህም ተግባራት በተለያዩ ዘመናት ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው ዛሬም ተጠናክረው እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሩቅ ሳንሔድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተነ ያለው የተሐድሶ ሤራ ዋናው ተቃውሞው የወልድን አምላክነት፣ የድንግል ማርያምን ክብርና አማላጅነት፣ የታቦትንና የመስቀልን ክብር፣ የቅዱሳንን ክብርና አማላጅነት ነው፡፡ በመሆኑም ተሐድሶ በሥራው የአውሬው መንፈስ አራማጅና መንገድ ጠራጊ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ ”ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፡- አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።” /ራእ. ዮሐ. 13፣4.8/ እንዲል፡፡

ሐ. ሌላው በዓለም ላይ የሚታየው በሰዎች ዘንድ ክብር፣ ዝናና ታዋቂነትን ለማግኘት ሲባል ራስን ከፍ ማድረግና እንደ አማልክት መቁጠር ከሐሳዊው መሲሕ ያስመድባል፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደገለጸው የሰናዖር ሰዎችን ኀጢአት ስናሰተውል የተነሡበት ዋናው ነጥብ ’ስማችንን እናስጠራ’ የሚለው ነበር፡፡” ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።” /ዘፍ. 11፥4/ ነው የሚለን፣ በዚህ እኩይ አሳብ ምክንያት እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ደባለቀባቸው፡፡ የሰናዖር ሰዎች ያሰቡትናየተመኙት ትውልዱ እግዚአብሔርን ማድነቅ ትቶ፣ ለዘለዓለም ስማቸውን ሲጠራቸው፣ ሲያደንቃቸው መኖርን ነበር፡፡ ዛሬም ብዙዎቹ ይህንን የሰናዖርን ኀጢአትና የጥፋት ጉዞ እንደ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
2. የሥነ ተፈጥሮ ሕግ ድንበር መጣስ አንዱ የጊዜው መቃረብ ምልክት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት ፍጹም በመሆኑ፣ ይህ ቀረህ፣ ይህ ይጨመርልህ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት፣ ሰው ለተለያየ ጥቅም በሚል ሰበብ ዝርያቸው የተለያዩ የሆኑትን ፍጥረታት ማዳቀልንና ማደበላለቅን ተያይዞታል፡፡እንስሳትና ተክሎችን ለማባዛት የማያደርገው ጥረትና  የማዳቀል ዘዴ የለም፡፡ በተቃራኒውም የሰውን ቁጥር ለመቀነስ የማያደርገው ሩጫ የለም፡፡ በመሆኑም ውጤቱ የሰውን ቁጥር ለመቀነስ ሲባል በሚደረጉ ሕክምናዎች ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል፡፡ በሚደረገውም ማበረታታት በሠለጠኑት ዓለም ብዙዎቹ የግብረ ሰዶም ፈጻሚና አስፈጻሚ ሆነዋል፡፡ ይህ አሠራር አምላክ የሠራውን የፍጥረት ሕግ በማጣጣል ሰው ላሻሽል ወደሚል ያዘነበለ በመሆኑ የሰውን ልጅ ቅጥ ያጣ ድፍረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሥነ ፍጥረቱን እንዲያደባልቁበት አይፈልግም፡፡እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ”ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ” /ዘሌ. 19፣ 19፤/ ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው።” /ዘሌ 20፣ 13/ በማለት ያሰተምረናል፡፡

3.    በጋብቻ ላይ የሚደረግ ርኩሰትን ስንመለከትም በየትኛውም ዓለም የፍርድ ቤቶች ትልቁ ሥራ ማፋታት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ተጋቢዎች ባንድ ላይ እንዳይኖሩ አውሬው /አስማንድዮስ/ የጋብቻ ጠላት በመሆን ስለነገሠ ፈተናውን መቋቋም አልቻሉምና ነው፡፡ ስለዚህ አስማንድዮስ ከዛ ይልቅ ግብረ ሰዶምን እያበረታታ በአንዳንድ ሀገሮች እንደሚታየው ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር እያቆራኘ በቤተ ክርስቲያኖቻቸው” ጋብቻ እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣” ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።” /ሮሜ.1፥24-ፍጻሜ

4.    መንፈሳዊ ባህል፣  የክህነት ክብር፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና  ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ፣ በሚለው ዙሪያ ስንመለከት በቀላሉ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ያለውን ማየት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ እነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።” / 2ጢሞ. 3፥1.7/ በማለት በመጨረሻው ዘመን የሚነሡ ሰዎችን ፀባይን ይነግረናል፡፡ ይህንን ትምህርተ ጥቅስ ለማገናዘብ  እግዚአብሔርን የማያምነውን ህዝብ ትተን፣ አሁን በዓለም ሁሉ ካለው የቤተ ክርስቲያንዋ አማኞች ብቻ አንጻር በመጠኑ እንይ ደግሞ፤

ሀ. መንፈሳዊ ባህል ማፍረስን ስንመለከት፣ የሁሉንም ባይሆን፣ የአንዳንዶቹ አማኞች ሰዎች ጸባይ ቅ. ጳውሎስ ”ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” የሚያሰኝ ሕይወት የያዙ እንደሆነ ያስረግጥልናል፡፡ እንደ አማኝ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ፣ ነገር ግን መንፈሳዊ አምልኮ የማይፈጽሙና የራሳቸውን አሳብ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉትን ነው ’የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል’ ያላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት መታዘዝ፣ መከባበርና ሰላም የነገሠበት መሆን ነው ያለበት፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታ እንደሚስተዋለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙዎቹ በመንፈሳዊው ባህል የጠነከሩ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶቹ ሥራ ፈቶች ሆነው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፖለቲካ፣ዘረኝነት፣አሉባልታ፣ ወዘተ በማምጣት ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩአት ይታያል፡፡ ቅ. ሉቃስ በተመሳሳይ አይሁድ ቀንተው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረጉትን ”አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ።  አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥” /የሐዋ. ሥራ 17፣ 5/ በማለት እንደገለጸው ያሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ”ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።” ይላቸዋል፡፡

ለ. የክህነት ክብርን ማፍረስ በተመለከተ፣ ቅ. ጳውሎስ ”ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።” እንዳለው ሁሉ ካህናት ነን ከሚሉት ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሰጥቷቸው በአንብሮተ እድ እየተሾሙ ሲወርድ መጥቶ ለኛ የደረሰውን ታላቁን የድኅነት መፈጸሚያ ክህነት እንደ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ዛሬ በብዙዎች ተንቆና ተዋርዶ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ከሚፈጸሙ ስህተቶች ጥቂቶቹን ቀጥለን እንመለከት፣

  • ቅዱስ ማቴዎስ ”በዚያን ዘመን ብዙዎች ይሰናከላሉ፣ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ” /ማቴ. 24፣10/ እንዳለው ሁሉ፤ለዘመናት በአንድነት የኖረችውን ቤተክርስቲያን ”ከዓመጻም ብዛት የተነሣ የብዙዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” እንዲል፣ በዚህ ዘመን በድፍረት አስተዳደሩዋን በመከፋፈል ”ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት” እንዲሁ አሳድጋ፣ አስተምራ፣ ክህነት የሰጠቻቸውን እናታቸውን ቤተ ክርስቲያን እስከ ማውገዝ የድፍረት ኀጢአት የተደረሰበት ዘመን ነው፡፡በመወጋገዙ ሂደት ያለው ጉዳትን ማን አስተዋለው? እግዚአብሔር ይማረን እንጂ እንደ ሰውኛው ከሆነ፣ በጭካኔ፣ ውስጥ ያለው ውጪውን፣ ውጭ ያለው ደጋግሞ ውስጥ ያለውን አውግዞትአንዲት ነፍስ ወደ እግዚአብሔር እንዳትደርስ ተቆላልፎ ቁጭ ብሏል፡፡ ነገር ግን ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን ቢቃወሙትም ሙሴ ክህነቱ ከእግዚአብሔር በመሆኑ የእግዚአብሔር ክብር በርሱ ላይ ተገልጦ እግዚአብሔርን የተቃወሙት በደላቸው እንደ ተገለጠ ሁሉ፣ ዘለዓለማዊዋ ቤተ ክርስቲያን ክህነታዊ ክብርዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ነው፡፡  ”ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል።  እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል።” / ቲቶ. 1፥15/ እንዳለ፡፡
  • ” ሰለስቱ ምእት በኒቂያ ጉባኤ ’ያለ ኢጲስ ቆጶስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተ ከክህነቱ ይሻር’ብለው ደንግገዋል፡፡ ነገር ግን በተለይ በውጭ አገር እየተለመደ የመጣው ጉዳይ የትኛውንም ኤጲስቆጶስ ሳያስፈቅድ አንድ ካህን፣ ከዚያም አልፎ በሚገርም ሁኔታ ዲያቆን ወይም ምእመን ከፈለገ ቦርድ አቋቋምኩ እያለ ቤተ ክርስቲያን አስተምራ አጥምቃ ያሳደገችውን ምእመን ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን በማውጣት እንደ ማንኛውም ድርጅት ቤተ ክርስቲያን ከፈትኩ የሚባልበት የድፍረት ኀጢአት በጠራራ ፀሐይ ከሚፈጸምበት ዘመን ደርሰናል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ዓይነት ለተቋቋሙ ሁሉ የሚገለገሉበት ታቦት ከየት መጣ? ሜሮን ከየት ተገኘ? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የላቸውም፡፡ ”ብዙዎች ይስታሉ” እንደተባለ በድፈረትና በስሕተት መሠረት ላይ የስሕተትና የድፍረትን ግድግዳ ማቆም፣ የስሕተትና የድፍረት ጣሪያንም ማዋቀር እንደ ሕጋዊ ሥራ ከተቆጠረ ሰነባበተ፡፡
  • የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል” /ማቴ 24፣15/ በየአጥቢያው የሚሰማውን ክፉ ወሬ ስናስተውል የዚህ ትንቢት ተፈጻሚነት እንዳገኘ ያረጋግጥልናል፡፡ የተሐድሶ ሴራ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠሩት ጭቅጭቆች፣ በመነኮሳትና በካህናት የሚነሱ ሐሜቶች፣ ሙሰኝነት፣ዘረኝነት ምን ይነግሩናል?በውጭ አገር በየቦታው አቋቋምን የሚሉት ሰበካ ጉባኤ ሳይሆን ራስ ገዝ የቦርዶቹ አስተዳደር ግፍ ደግሞ በሚገርም ሁኔታ የሚያገለግለው ካህንን የሚያዩት እንደ እግዚአብሔር ካህን ሳይሆን ከአንድ ቅጥር ሠራተኛቸው በታች ነው፡፡ ስለ አስተዳደሩ እንዲያውቅ አይፈልጉም፣ እነሱ ያዘዙትን ብቻ ይሰብካል/ ይናገራል፣ ካህኑም ሲፈልጉ የሚያኖሩት ሲፈልጉ የሚያባርሩት ሆኗል፡፡ ይህን አሠራር ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን ከኖረችበት አንጻር ስናየው እጅግ የራቀና አስጸያፊ የሚባል ነው፡፡ ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በሥልጣነ ክህነት እንድትተዳደር ሲሆን ይህኛው በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምእመኑን አስተምራ አጥምቃ አሳድጋ እንደገና በተንኮለኞች ሤራ ልጆቹዋን ቀስጠው በስዋ ላይ እንዲያምጹ ማድረግ የጥፋት ርኩሰት መሆኑን ስንቱ ተረድቶት ይሆን?፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ”ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ።” /1 ጢሞ.6፥3-5/ እንዳለ፡፡

ሐ. ሰብአዊ ክብርና የዕድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና  ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ለሚለው ሌላ ብዙ ከማለት ይልቅ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ”ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥  ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ” በማለት የዘረዘረው ለርእሰ ጉዳዩ ተስማሚና በቂ ነው፡፡/1ጢሞ.3፥1-3/

ባጠቃላይም የምጽአት ምልክቶች የሚያሳዩት ሁኔታዎች ከመንፈሳዊው እስከ ዓለማዊው፣ ከተማረው እስከ መሀይሙ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ፣ ያላገባው፣ ያገባው፣ መነኩሴው ሳይቀር ሁሉም ሁሉም ባንድ ላይ ከቅድስና ርቀት፣ ከጥፋት ርኩሰት፣ ከመከራ ሕይወት፣ ተቋደሽ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው እንደመሰከሩልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድንገት ይመጣል አይዘገይም፡፡ ቅዱስ ዳዊት ”ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል።  አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።” /መዝ.49፥2-3/ ብሎ እንደተናገረው፡፡ ከላይ እንደተዘረዘረው የሰው ልጆች ሁለ ጊዜ ከመንፈሳውያን እስከ ዓለማውያን ድረስ በተጠመዱበት የዓለማዊ ሥራ እንደ ተወጠሩ ነው ያሉት፡፡ ከዚህም በኋላ የበለጠ በሥጋ ሥራ እየተወጠሩ ይሄዳሉ እንጂ መንፈሳዊ ወደ ሆነው የተጋድሎ ሕይወት የሚያዘነብል ይኖራል ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንዲያውም በዐመጽ እየበረታ እስከ መቅደስ ድፍረቱን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይገልጸዋል፤”ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው።” /2ተሰ.2፥3-4/ ይለናል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች ነን የምንል ሁሉ የጥፋት ትንቢቱ እኛ ላይ እንዳይፈጸም አሁኑኑ ሳናመነታ ንስሐ መግባትና በትንቢት ከተገለጡት ርኩሰቶች ጨክነን መራቅ ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ማቴ 24፤44


አትምኢሜይል
መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም.
በዲ/ን ተመስገን ዘገየ
ይህ ቃል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ለደቀመዛሙርቱ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምልክቶች ሲጠይቁት የተናገረው ኃይለ ቃል ነው፡፡ “ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ ቀረቡና እንዲህ አሉት፤ ንግረነ ማእዜ ይከውን ዝንቱ ወምንትኑ ተአምሪሁ ለምጽአትከ፣ ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የዓለም ፍጻሜ ምልክቱስ ምንድን ነው?” አሉት፡፡


ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው፡፡ 800 ሜትር ያህል ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ አለው፡፡ ቤተፋጌና ቢታንያም ከግርጌው የሚገኙ መንደሮች ናቸው፡፡ ደብረ ዘይት ስያሜውም የተሰጠው በላዩ ከሚበቅሉት (ተራራውን ከሸፈኑት) የወይራ ዛፎች የተነሳ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ የመላበት (በብዛት የሚገኝበት) ተራራ ማለት ነውና፡፡
የደብረ ዘይት ተራራ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ተራራ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመንም ዳዊት ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት እንደወጣ በ2ኛ. ሳሙ. 15፤30 “ዳዊትም ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ” ይላል፡፡ ይህ ተራራ በሕዝቅኤል ትንቢት ስብሐተ እግዚአብሔር እንደሚያርፍበት ተነግሮአል፡፡ የእግዚአብሔር ክብርም ከከተማይቱ መካከል ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል በአለው ተራራ ላይ ቆመ፡፡ ት.ሕ11.23
ዘሩባቤል ከሠራው ቤተ መቅደስ ዐደባባይ ደብረ ዘይት 75 ሜትር ገደማ ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ቤተ ፋጌና ቢታንያም የሚበሉት ታሪካውያን ቦታዎች ከደብረ ዘይት ግርጌ ይገኛሉ፡፡ 
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሳዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11.1 ላይ “ወአልጺቆሙ ኢየሩሳሌም ኀበ ቤተ ፋጌ ወቢታንያ በኀበ በደብረ ዘይት ፈነወ ክልኤተ እምአርዳኢሁ ፤ወደ ኢየሩሳሌም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወደ አሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ ከደቀ መዘሙርቱ ሁለቱን ላከ” ይላል፡፡ አይሁድም ጌታን የያዙት በደብረ ዘይት ተራራ ግርጌ በምትገኘው ጌቴሴማኒ ነው፡፡
አንቢቦሙ ወሰቢሖሙ ወጽኡ ወሖሩ ውስተ ደብረ ዘይት ወእምዝ ይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ኵልክሙ ትክሕዱኒ በዛቲ ሌሊት፣ መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ” አላቸው፡፡ ማቴ. 26.30
ጌታችንም ሲያስተምር ውሎ ማታ ሔዶ የሚያድረው በደብረ ዘይት ተራራ ውስጥ ባለችው ኤሌዎን ዋሻ ውስጥ ነበር፡፡ በዕለተ ሆሳዕናም ከኢየሩሳሌም ሲወጡ የገባውም ወደ ደብረ ዘይት ነው፡፡ ማር 11.1 በዚህ ዓለም የፈጸመውን አገልግሎት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሰማይ ያረገውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ወደፊትም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ትንቢት ላይ መገለጫው ደብረ ዘይት እንደሆነች ተገልጿል፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ቀን ይመጣል ብዝበዛሽንም በውስጥ ይከፍላሉ፡፡ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምን ይወጉአት ዘንድ እሰበስባለሁ ከተማይቱም ትያዛለች ት. ዘካርያስ 14.1
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ምጽአቱ (ዳግም ምጽአቱ በደብረ ዘይት ተራራ) ላይ በሰፊው አስተምሯል፡፡ በቤተ መቅደስ ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስና እንድርያስም ለብቻ ጠየቁት፡፡ እንዲህም አሉት ንገረን ይህ መቼ ይሆናል (ማር 13.3፣ማቴ 24.1-51) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቡነ ዘበሰማያት የሚለውን ጸሎት ያስተማረውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ከ62 ሀገሮች በላይ ልሳን(ቋንቋ) በሞዛይክ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ግእዝ ነው፡፡ በመሆኑም 5ኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት የክርስቶስ ነገረ ምጽአት የሚዘመርበት፤ የሚሰበክበት ዕለት ስለሆነ በደብረ ዘይት ተሰይሟል፡፡ ሰያሚውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍልም ማቴ 24.1-36 ነው፡፡
 ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት በሄደበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ አጠገቡ ቀርበው ዘሩባቤል ያሳነፀውን የመቅደስ ግንቦች እያሳዩት ቀረቡ፡፡ “አማን እብለክሙ ኢይትኀደግ ዝየ እብን ዲበ እብን ዘኢይትነሠት፣ እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የኢየሩሳሌምን መፍረስና ዳግም መምጣትን አስፍቶ አምልቶ ከነምልክቱ ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው፡፡ ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆንባቸው በሰማያዊ ንጉሥ ፊት ያለ ምክንያት ለፍርድ እንዲቆሙ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ወንጌል በአሕዛብ ቤት ሳይቀር ለሁሉም ይሰበካል፡፡ በዚህ ጊዜ መጨረሻው እየቀረበ ይመጣል” (ማቴ.24.14) በማለት በስፋት አስተምሮአቸዋል፡፡ እምበለስ አእምሩ አምሳሊሁ፣ ነገሩን በበለስ እወቁ፡፡ የበለስ ቅጠል መለምለም ማለት የጠፋችው የእስራኤል መንግሥት መመሥረት የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት 11ኛ ምልክት ነው፡፡ ማቴ 24.32
ከዚህ በኋላ በማናውቀው ጊዜና ሰዓት እግዚአብሔር ወልድ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት (በአካላዊ መጠን) ከቅዱሳን መላእክት ጋር በደመና ይመጣል፡፡ “ናሁ ይመጽእ በደመና ሰማይ ወትሬእዮ ኩላ ዐይን ወእልክቱሂ እለ ወግእዎ ይበክዩ በእንቲአሁ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር እወ አማን፣ እነሆ በሰማይ ደመና ይመጣል ዐይን ሁሉ ታየዋለች የወጉትም ሁሉ ያለቅሳሉ የምድር ወገኖች ሁሉ የኀዘን ድምፅ ያሰማሉ፡፡ አሕዛብ ሁሉ ስለ እርሱ ያለቅሳሉ፡፡” (ራእይ 1.7)
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱ በተናገረበት አንቀጹ ቅዱሳን ሐዋርያትን ካስጠነቀቀበት ዐቢይ ኃይለ ቃል መካከል ስለ ሐሰተኞች መምህራን መምጣት ነበር፡፡ “እስመ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወያስሕትዎሙ ለብዙኃን” የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ በማለት (በማቴ 24.5) አስጠንቅቋል፡፡ ክርስቲያኖች አሁንም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ከሆኑት ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፡፡ ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማል? በማለት እውነተኛ የወንጌል መምህራንን በመምሰል ብዙዎችን እንደሚያሳስቱ ጌታችን አስተምሮናል (ማቴ 7.15 ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ 16.17 “ነገር ግን ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትና ማሰናከያ የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምንቹሃለሁ፡፡ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግር ተንኰል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉና” ይላል፡፡
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረ “እኛስ ያለማወላወል የደጋግ አባቶችን ሃይማኖት እንይዛለን” (ሃይማኖተ አበው ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያውን እምነታችን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተከፋዮች ሆነናልና፡፡ (ዕብ 3.14) ይላል፡፡ ስለዚህ በጊዜው ያለ ጊዜውም መጽናት ይገባል (2ኛ ጢሞ4.2)
የዓለም መጨረሻውና የኢየሱስ ክርስቶስ መምጫ ምልክቶች በማቴ 24.1 በስፋት ተዘርዝረዋል፡፡

ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ታላላቅ ምጽአቶች እንዳሉት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “….በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሥዋት ኃጢአት ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል… አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸውም ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታዩላቸዋል” (ዕብ 9.26-28 ) በማለት ተናግሮአል፡፡

የመጀመሪያው ምጽአቱ ሥጋ በመልበስ ለሰው መሥዋዕት ሁኖ ሊያድን ለካሳ በፍጹም ትህትና የእኛን ውርደት ተቀብሎ በበረት በመወለድ በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ በሚሞት በሚሰደድ በሚዳከም ፤በሚበረታ፤ በሚራብ፤ በሚጠማ ፤ በሚዝል በሚወድቅ በሕርየ ሰብእ (የሰው ባሕርይ) እንደ አንድ ኃጥእ ሞት፣ እስኪፈረድበት ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጐ መጣ፡፡

ወንጌለ መንግሥቱን ሊሰብክልን ከሞት ወደ ሕይወት ሊያሸጋግረን በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ ከአይሁድ ስድብን ታገሠ ኃጥአንን በሽተኞችን ሊያድን በምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ ስለ እኛ ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ያውም መራራ ለሆነ የመሰቀል ሞት ታዘዘ፡፡ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ተነሳ ወደ ሰማይም በዐርባኛው ቀን አረገ በየማነ አብ ተቀመጠ፡፡ ይህ ነው የመጀመሪያው ምጽአቱ መከራን ለመቀበል እኛን ለማዳንና ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ነው፡፡

ዳግማዊ ምጽአቱ፡- በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በፍጹም ጌትነት በኃጥአን (የመጀመሪያ ምጽአቱን) ባልተቀበሉት ላይ ሊፈርድ ዐይን ሁሉ እየተመለከተው በገሃድ ይመጣል፡፡ “እግዚአብሔርስ ገሀደ ይመጽእ ወአምላክነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፣ እግዚአብሔር ግልጥ ሁኖ ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል (መዝ 50.3)
መጥቶም ዝም አይልም (ኤሌ ለክሙ ጸሐፍት ወፈሪሳውያን መደልዋን፤ ግብዞች ጸሐፍት ፈሪሳውያን ወዮላቸሁ) እያለ ይወቅሳል ወንጌልንም ያስተምራል፡፡ ጻድቃንን “እናንተ የአባቴ ብሩካን ወደ እኔ ኑ ብሎ ይጠራል ኃጥአንንም እናንተ ርጉማን ሐሩ እምኔየ፤ ከእኔ ወግዱ” ብሎ ያሰናብታቸዋል፡፡ በፊቱ እሳት ይነዳል ማለት ጻድቃን የሚድኑበት ሕይወት ኃጥአን የሚጠፉበት መዓት በባሕርዩ አለ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሆይ! የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ መገለጥ ለእኛስ ለምን ይሆን? ለዘለዓለማዊ ሕይወት ወይስ ለዘለዓለም ሞት?
ጌታችን በደብረ ዘይት ያስተማራቸው ትምህርቶች በመሠረታዊነት በ3 ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡
1. ምልክት፡- በዚያ ዘመን እንዲህ ይሆናል እያለ በፍጻሜ ዘመን የሚከሰቱትን ድርጊቶች፡፡
2. ትእዛዝ፡- በዚያ ዘመን ከጥፋት እንድን ዘንድ የሰጠን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ እያለ ፡፡

3. ማስጠንቀቂያ በፍጻሜ ዘመን እንዲህ ሁናችሁ የተገኛችሁ “ወዬላችሁ” እያለ የተናገራቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ምሳሌ “ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው” የሚለው እርጉዝ ማለት የኃጢአት ዐሳብ የጸነሱት ሲሆኑ የሚያጠቡ ያላቸው ኃጢአትን ጸንሰው በንግግር የወለዱትን ነው” 
በይሁዳ ያሉት ወደ ተራሮች ይሽሹ (ማቴ 24.16) በዚህ ቃል መሠረት በይሁዳ በዓለም ያሉ ወደ ተራራ ይሽሹ ተብሏል፡፡ በሃይማኖት ጸንተው ምግባር ትሩፋት እየሠሩ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ወደ ተራራ ይሽሹ ነው፡፡ 
ለመሆኑ ተራራ ምንድን ነው?
1. ተራራ የተባለው ረድኤተ እግዚአብሔር ነው፡፡ “ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው “መዝ. 124.2 ይላል፡፡ በዚህ ቃል የእግዚአብሔር ረድኤት በተራራ ተመስሎ ቀርቧል፡፡ ምክንያቱም ተራራ እንደሚከልል እግዚአብሔርም በረድኤቱ ይከልላልና፡፡ ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ረድኤተ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጉ ማለት ነው፡፡

2. ተራራ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡
3. ድንግል ማርያም የጽዮን ተራራ ትባላለች “አንሰ ተሠየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ፣ በጽዮን በደብረ መቅደሱ ፤እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ በተቀደሰው ተራራ ላይ በጽዮን ላይ ” መዝ.2.6 ስለዚህ ትውልድ ድንግል ማርያምን ዓምባ መጠጊያ ያደርግ ማለት ነው፡፡
4. ተራራ የተባሉት ቅዱሳን አባቶቻችን ናቸው፡፡ መዝ.86.1 መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን ፤መሠረቶቿ በቅዱሱ ተራሮች ናቸው” ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ወደ ቅዱሳን አባቶቻችን ቅረቡ በአማላጅነት ሥልጣናቸው አምናችሁ ተማጸኗቸው ሲል ነው፡፡

በሰገነት ያለውም በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ ይላል (ማቴ 24.17) ሰገነት ከፍ ያለ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቃል በሠገነት የተመሠለ በምግባር በሃይማኖት የበረታ የወጣትነት ዘመን አልፎ ከማዕከላዊነት የደረሰ ማለት ሲሆን፤ በዝቅታ የተመሠለ ደግሞ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ የነፍስ ተዋርዶ ነው፡፡ 
ዴማስና ይሁዳ በሰገነት ነበሩ በኋላ ግን በዝቅታ ሥፍራ ተገኙ፡፡ መዋል በማይገባቸው ቦታ ውለው ተገኙ፡፡ በክርስትና ከፍ ከፍ ብለው በመንፈሳዊነት መጽናት አቃታቸው፡፡ እኛስ ከየትኛው ስፍራ እንሆን?
በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላ አይመለስ (ማቴ24.18) በእርሻ የተመሰለ የመነነ ወይም በምንኩስና ሕይወት ያለ ማለት ነው፡፡ በእርሻ ያለ አይመለስ ማለት በምነና በምንኩስና ያለ ይህንን ሕይወት የጀመረ አይመለስ፡፡ ስለዚህ ስደታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ተግታችሁ ጸልዩ አለ (ማቴ 24 .20) ክረምት የፍሬ የአጨዳ ሳይሆን የሥራ የመዝሪያ ወቅት ነው፡፡ ሰንበትም የዕረፍት ቀን ናት፤ በሠንበት ሥጋዊ ሥራ አይሠራም፡፡ አንድም በክረምት ቅጠል ካልሆነ ፍሬ አይገኝም እናንተም ሃይማኖት ይዛችሁ ምግባር ከሌላችሁ ዋጋ የላችሁም ማለቱ ነው፡፡
ሽሽት የተባለ ዕለተ ምጽአት ሲሆን በሽሽት የተመሰለው ሞት ድንገት እንደሚመጣ ዕለተ ምጽአትም በድንገት ስለሚሆን ነው፡፡ ትርጉሙ ንስሓችሁን ሳትጨርሱ የንስሐ ፍሬ ሳታፈሩ በድንገት ዕለተ ምጽአት እንዳይደርስባችሁ ጸልዩ የሚል ይሆናል፡፡ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ሲኖር “ድልዋኒክሙንበሩ፤ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” ማቴ 24:24 በተባለው አማናዊ ቃል መሠረት ራሱን በንስሓ አዘጋጅቶ የጌታውን መምጣት ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡ 

2015 ማርች 11, ረቡዕ

እረፍቱ ለአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ


Written By Hulubante Abebe 

 የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።” 
                                 
 መዝ ፴፫፡፲፭-፲፯ 
መጋቢት 5 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማኞች ዘንድ የፃድቁ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል 
በዚህ እለት እምናከብረው የእረፍት መታሰቢያቸውን ሲሆን ከገድላቸውም እንዲህ ተፅፎ እናገኘዋለን 
ፃድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተወለዱት ግብፅ ንሂሳ በምትባል ቦታ ከአባታቸው ስምዖን ከእናታው አቅሌስያ ነው። በአጠቃላይ የኖሩበት ዕድሜ 562 አመት ሲሆን 300 ዓመቱን በግብጽ 262 ቱን በኢትዮጵያ 100 ዓመት በዝቋላ በተጋድሎ ያሳለፉ ታላቅ አባት ናቸውኢትዮጵም የአስራት ሐገራቸው ሆና በቃልኪዳን ተሰጣቸዋለች  እናታቸው ሳትታቀፋቸው ወተት ሳይጠጡ በመንፈስ ቅዱስ አድገው በ፫ ዓመታቸው ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ እስከ ሰባቱ ሰማያት አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር አቀረበው፤ ባረከውም፤ ድንግል ማርያም ጻድቃን ሰማዕታት ወዳሉበት ተወስዶ ተባርኮ በጌታችን ቃል ተቀብሎ ወደ አባ ዘመደ ብርሃን ወዳሉበት አውርዶ በዚያም አድጎ መንፈሳዊ ሥራን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ተጋድሎውን ጀምሯል። በበረሃ ሲኖሩ 60 አንበሳና ነብር የተሰጣቸው ሲሆን አንበሳ እና ነምሮቹም የሚበሉትም የቅዱሱን እግር ያረፈበትን ቦታ በመላስ ነው። የአባታችን ገድል እንደሚያስረዳው እንደ ሰው ልብስ ለብሰው ሳይሆን ልብሳቸው በጸጋ የተሰጣቸው ጠጉር ነበር እሱም ልክ እንደ ልብስ ያገለግላቸው ነበር
 ከሚያስገርመው ገድላቸው ውስጥ አባታችንን ለመጠየቅ የመጡት አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር መጥተው እንግዶቹን አንበሶቹ በልተው አባታችን አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስም በመንፈስ መምጣታቸውን አውቆ ሲነግሯቸው ለምን ያልተፈቀደላችሁን በላችሁ ብለው የበሉትን አንበሶች የበላችሁትን አንድም ሳታስቀሩ ትፉ ብሏቸው ወደ እግዚአብሔር ጸልየው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሱ ባሉ ጊዜ የተበሉት ነፍስ ዘርተው እነ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባም በሰላም ወደ ባእታቸው በአባታችን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸሎት በሠላም ገብተዋል።
መጋቢት 5 በገድለ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ
ዕለቱ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኗል፤ አሁንም ህማሙን እየታገለ እያላበው በድካም ለፍጥረቱ ሁሉ ይለምናል፤ “አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህን ኢትዮጰያንም ባርክ” ይላል። ህመም የጀመረው መጋቢት 3 ዓርብ ቀን ነው፤መታመሙን የሰሙ እንደርሱ ቅዱሳን የሆኑት ዘርአ ቡሩክ፤ ፍሬ ቅዱስ፤ያዕቆብ፤ብንያምና ዮሴፍ እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጰያ ንጉስ የነበረው እንድርያስ ሊጠይቁት ተሰብስበዋል ወደ አጠገቡ መድረስ ግን አልተቻላቸውም አባታችን ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚጋርደው እንጨት ዛፍ በሌለበት በርሃ እንደ አንበሳ ተኝቶ አዩት በላዩ ያረፈው የእግዚያብሔር ጸጋ ከፊቱ የሚወጣው ብርሃን ቀይ መልኩ ረዥም የራስ ጠጉሩ እንደ ነጭ ሐር የሚሆን ጽሕሙ አስደነቃቸው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ጸሐይና እንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጪፍ ድንጋይ ይወረወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩኸት
ንውጽውጽታ ሆነ። “ወዳጄ ገብረመንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን” እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አለው፤ አባታችንም “አቤቱ ጌታ ሆይ የኢትዮጰያን ህዝብ ማርልኝ” አለው፤ እነሆ ምሬልኃለው አስራት በኩራት አድርጌም ሰጥቼሃለው፤ ከመጋቢት አምስት ቀን ጀምሮ ዝክርህን ያድርጉ በአማላጅነትህም ይማጸኑ አለው። ከዚህ በኃላ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት የአባታችንን ነፍስ ሊቀበሉ ወረዱ በታላቅ ምስጋናም ወደ ሰማይ አሳረጉት ስጋውንም ይዘውት ሄዱ የት እንደተቀበረ ግን እስካሁን አይታወቅም አንዳንዱ በእየሩሳሌም ነው ይላሉ፤ ሌላው በምድረ ከብድ ነው ይላል ግን እስካሁን ልክ እንደ ሊቀ ነብያት ሙሴ ስጋ የት እንደተቀበረ አይታወቅም። ገድሉ ትሩፋቱ ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ ይበዛል ኢትዮጰያን አብዝቶ ይወዳታል፤ ምድራዊ ምግብ አልተመገበም የእናቱን ጡት እንኳን አልጠባም፤ ልብስ፤ መጠለያ አልፈለገም፤ የክረምት ቁር የበጋ ሐሩር እየተፈራረቀበት በተጋድሎ 562 ዓመት ኖረ፤ በዛሬዋ ቀን ሩጫውን ጨረሰ። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባታችን በረከት ያሳትፈን።
የአባቶችን የቅዱሳንን ታሪክ እንድናውቅ ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ከነርሱ ገድል ተምረን እኛም ወደአምላክ መንገድ እንድንቀርብብበት ነውና አምላከ ገ/መንፈስ ቅዱስ መንገዱን ያብራልን ። ገድሉንም ሰሚወች ብቻ ሳንሆን እምንማርበት ያድርግልን ።
መጋቢት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ /አባ ገብረ ሕይወት/                                     2.ቅዱስ አባ ሰረባሞን /በምድረ ግብፅ ምንኩስናን ካስፋፉ ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ/                 3.አባ ግርማኖስ ጻድቅ /ሶርያዊ/                                                         4.ቅድስት አውዶክስያ ሰማዕት /ከከፋ የኃጢአት ሕይወት ተመልሳ ለቅድስና የበቃች እናት/ 
5.ቅዱሳን ስምዖንና ሚስቱ አቅሌስያ /የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወላጆች/

                       ወስብሐት ለእግዚአብሔር

2015 ማርች 10, ማክሰኞ

እየደመሰሱ መቅዳት

ለረዥም ዓመታት በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ የሠራ ጋዜጠኛ ለአንድ ጥናት ወደ ጣቢያው ይሄዳል፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት እርሱ ራሱ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ነበር፡፡ ቃለ መጠይቁ የተደረገላት ሴት አሁን በሕይወት የለቺም፡፡ ለዚህ ነበር እርሷ የሰጠቺውን ቃል ፍለጋ ወደ ሬዲዮ ጣቢያው የሄደው፡፡ ያገኘው ግን የጠበቀውን አልነበረም፡፡ የተቀዳው ቃለ መጠይቅ የለም፡፡ ምነው? አለ ጋዜጠኛው፡፡ ‹‹ብዙ ካሴቶችን እየደመሰስን ቀድተንባቸዋል፡፡ በዚያ ምክንያት ያንን ቃለ መጠይቅ አሁን አታገኘውም›› አሉት፡፡ እርሱም በዚህ አዝኖ ወጣ፡፡
ለነገሩ እርሱ በካሴቱ አዘነ እንጂ ከኢትዮጵያ ታሪክ መገለጫዎች አንዱ እየደመሰሱ መቅዳት ነው፡፡ የሚመጣ መንግሥት ወይም ባለሥልጣን፣ ዐዋቂ ወይም ታዋቂ፣ ታሪክ ጸሐፊ ወይም ዐቅድ ነዳፊ ከእርሱ በፊት ለነበረው ነገር ዋጋ ሰጥቶ፣ የየራሱን ሥራ ከመሥራትና የዘመኑን አሻራ ከማኖር ይልቅ ያለፈውን መደምሰስ ይቀናዋል፡፡ 

ሀገር የማታልቅ ሕንጻ ናት፡፡ መሠረቷ ዛሬ አልተጣለም፡፡ መሠረቷ ከተጣለ ቆየ፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱን ድርሻ እየገነባ ይቀጥላል፡፡ የመጣው ሁሉ ባለው ላይ አዳብሮ፣ አሻሽሎ ወይም አሣምሮ የሚጨምር ከሆነ ሀገር እያደገች፣ እየበለጸገችም ትሄዳለች፡፡ የመጣው ትውልድ ሁሌም ከሥር ከመሠረቱ የሚያፈርሳት ከሆነ ግን ሀገር ባቢሎን ትሆናለች፡፡ ቅርስ እንጂ ሕይወት፣ ታሪክ እንጂ ዕድገት፣ ስም እንጂ ክብር አይኖራትም፡፡ ለጉብኝት እንጂ ለኑሮ አትሆንም፡፡ 
 ባቢሎን በታሪክ ቀድመው ከሠለጠኑ ሀገሮች ተርታ ነበረቺ፡፡ ነገር ግን የገዛት ሁሉ ከመሠረቷ እያፈረሰ እንደገና ሲሠራት፣ የመጣዉ ሁሉ እየደመሰሰ ሲቀዳባት ይሄው ዛሬም አላልፍላት ብሎ የጦር አውድማ ሆናለቺ፡፡ ስለ ኢራቅ ጥንታዊ ታሪክ የሚተረከውና የዛሬዋ ኢራቅ አይጣጣሙም፡፡ የመጡት ሁሉ በባቢሎን ካሴት ላይ እየደመሰሱ ሲቀዱ፣ መሠረት አልባ ጣራ ሊያቆመ ሲደክሙ፣ አሁን የመጡባት አሸባሪዎች ደግሞ ጨርሰው ታሪካዊ ቅርሶቿን በድጅኖ መናድ ጀመሩ፡፡ እየደመሰሱ መቅዳት ካንሰር መሆን ሲጀምር ይሄው ነው፡፡
ይኼ እፉኝታዊ ጠባይ ነው፡፡ እፉኝት የምትባል የእባብ ዘር አለች አሉ፡፡ አፈ ማኅፀኗ ጠባብ ነው፡፡ ከወንዱ ጋር ስትገናኝ የወንዱን አባለ ዘር ትቆርጠውና ወንዱ ይሞታል፡፡ ልጆቿን በማኅፀኗ ፈልፍላ ስትወልዳቸው ደግሞ ለመውጣት ስለማይችሉ ሆዷን እየቀደዱ እናታቸውን ገድለዋት ይወጣሉ፡፡ ልጆቹ ልጅ የሚሆኑት አባትና እናታቸውን ገድለው ነው፡፡ ያለፈውን ካልደመሰሱ መኖር አይችሉም፡፡
የመጣንበትንና የነበርንበትን ማንጠር ጠቢብነት ነው፡፡ መደምሰስ ግን እፉኝትነት፡፡ ማንጠር ማለት ደግሞ እንደ ቅቤ ነው፡፡ እናቶቻችን ቅቤ የሚያነጥሩት ለሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ቅቤው ሲነጠር አንጉላው ተለይቶ ይቀራል፡፡ ቅቤውም ኮለል ብሎ ይወርዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅመማ ቅመም በመጨመር በቅቤው ላይ ጣዕም ያክሉበታል፡፡ ወይም ቅቤውን ላቅ ወዳለ ሌላ የጣዕም ደረጃ ያሸጋግሩታል፡፡ ማንጠር ሲባል እንደዚሁ ነው፡፡ በታሪካችን፣ በባሕላችን፣ ወይም በልማዳችን ውስጥ እንደ አንጉላ ያሉ ነገሮች ተጨምረው ከሆነ በዕውቀትና ምርምር፣ በግልጽ ወይይትና ክርክር እሳት ላይ ጥዶ ማንጠር ነው፡፡ አንጉላውን ከለየን በኋላ ደግሞ በነበረው እሴታችን ላይ ሌላ እሴት መጨመር፡፡ 
ቅቤን ማንም አያነጥረውም፤ ባለሞያ ይጠይቃል፡፡ አንጉላውን የማስወገጃ መንገዱ ራሱ ልዩ ሞያ ጠያቂ ነው፡፡አንጉላ መስሎን ቅቤዉን ጭምር እንዳያስወግደው እንደ ዶሮ ላባ ባለ ስስ ነገር እየለዩ ማንጠርን ይጠይቃል፡፡
ታሪካችንንና ባሕላችንን፣ ወጋችንንና ልማዳችንን ስንመረምርና አንጉላውን ስንለይ፣ እንደ ቅቤ አንጣሪው በሞያ መሆን አለበት፡፡ ስሜት ቦታ ሊያገኝ አይገባም፡፡ ቅቤ አንጣሪ ስሜት ውስጥ ከገባ ምች ይመታዋልና፡፡ አረሙን እንነቅላለን ብለን ስንዴውን ጨምረን እንዳንነቅለው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ብለን የምንሠራቸው ሥራዎች አዙሪት ውስጥ እንዳይጥሉን ጉዳዩን የሞያና የዕውቀት ጉዳይ ማድረግ ይገባናል፡፡ ‹ዕውቀት አጠር፣ ስሜት መር› ከሆነው ጉዟችን ይልቅ ‹ዕውቀት መር፣ ስሜት አጠር› ወደሆነው ሥልጣኔ ካልወጣን በስተቀር እዚያው ጨለማው ውስጥ ስንኳትን እንኖራለን፡፡ 
ቅቤ አንጣሪ ሰው ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ያስፈልገዋል፡፡ ምች እንዳይመታው፡፡ የቅቤ ምች ያጠናግራል ይባላል፡፡ ቅቤውን በጥንቃቄ ያነጠረቺ ባለሞያ ናት ‹‹ቅቤ አንጣሪዋ እያለቺ ጎመን ቀንጣሿን ምች መታት› ብላ የተሳለቀቺው፡፡ ነባሩን ነገራችንን ስናነጥር ሞያ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄም ወሳኝ ነው፡፡ የዘመን ምች መትቶ እንዳያጠናግረን፡፡ ጎጠኛነት፣ የፖለቲካ ፍጆታ፣ የሥልጣን ፍቅርና ጊዜያዊ ጥቅም የሚባሉ ምቾች አደገኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ምቾች የመቱት ሰው ቅቤውን በሚገባ ማንጠር ቀርቶ ሌላ በሽታ በራሱ ላይ ይጨምራል፡፡ ጤነኛ የነበረው አንጣሪ ተጣሞ፣ ዓይኑ ጠፍቶ፣ ፊቱ ቆሳስሎ ይወጣል፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱ ያለፈው ታሪኩን ሁሉ የሚያየው በማንጠሪያ ዓይኑ ሳይሆን በተጠናገረ ዓይኑ ነው፡፡ 
አሁን በደምስሶ መቅዳት ሥራ ላይ የተሠማሩት ብዙዎቹ ወገኖቻችን ምች የመታቸው ናቸው፡፡ ዓይነ ልቡናቸውን ምች ስለ መታው ቅቤውንና አንጉላውን መለየት አልቻሉም፡፡ አንጉላ መስሏቸው ሁሉንም ነባር ቅቤ ሊያስወግዱ የቋመጡ ናቸው፡፡ የዛሬውን መንግሥተ ሰማያት ለማሰኘት የትናንቱን ሲዖል ማድረግ፣ የእነርሱን ዘመን የተድላ ዘመን ለማድረግ አላፊውን ዘመን የመከራ ዘመን ማድረግ፣ የአሁኑን አስተሳሰባቸውን ዘመናዊ ለማድረግ ያለፈውን ሁሉ ኋላ ቀር ማሰኘት የግድ ይመስላቸዋል፡፡ ያለፈው የተቀዳበትን ካሴት አዳምጠው ቀጥሎ የራሳቸውን ከመቅዳት ወይም አዲስ ካሴት ከመጠቀም ይልቅ ደምስሰው ካልቀዱ አይረኩም፡፡ አዲስ ሲሠሩ ከሚደሰቱት በላይ ነባሩን ሲያጠፉ የሠለጠኑ ይመስላቸዋል፡፡
ሰው በአንድ ቦታ ስለተሰበሰበ ብቻ ሀገር አይሆንም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ እሥራኤላውያን አሜሪካና ፖላንድ መኖር ይበቃቸው ነበር፤ ለፍልስጤማውያንም ዮርዳኖስና ሊባኖስ የሚኖሩት የካምፕ ኑሮ በቂ ነበር፡፡  ሰፊ መሬት ብቻውንም ሀገርን አይመሠርትም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ ሀገር ይሆን ነበር፡፡ ሀገር ግን ከሰውም ከመሬትም በላይ ናት፡፡ ሰው በመሬቱ ላይ ሲኖር የሠራው ታሪክ፣ ያካበተው ባሕል፣ የደነገገው ወግና ሥርዓት፣ ያዳበረው ቋንቋ፣ ያመጣው ለውጥ፣ የፈጠረው ዘዴ፣ የገነባው ሥነ ልቡና፣ የተከተለው እምነት፣ የእርስ በርሱ መስተጋብር፣ ዓለምን የሚያይበት ርእዮተ ዓለም፣ ሥነ ቃሉ፣ ሌላም፣ ሌላም፣ ሌላም ተዋሕደው የሚፈጥሩት ነገር ነው - ሀገር፡፡ 
 
እነዚህን የተሠራንባቸውን ነገሮች ነው ማንጠር የሚያስፈልገው፡፡ መጀመሪያ እንሰብስባቸው፣ እንመዝግባቸው፣ እንለያቸው፣እንዘግባቸው፣ እንቀርሳቸው፣ እንወቃቸው፡፡ ከዚያ እናጥናቸው፣ እንመርምራቸው፡፡ በመጨረሻም እናንጥራቸው፡፡ ገመዱ ውስብስብ ነው፡፡ ለዘመናት የተፈተለና የተገመደ፡፡ ርጋታ፣ ትዕግሥትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ወስነን አይደለም ማወቅ ያለብን ዐውቀን ነው መወሰን እንጂ፡፡ አንዳንዴ መጀመሪያ እንወስናለን፣ ከዚያ እንሰይማለን፣ ቀጥለንም እንፈርጃለን፣ በመጨረሻም እንመታለን፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ዕውቀት፣ ጥናትና ማንጠር ቦታ አይሰጣቸውም፡፡ እንዴው ዝም ብሎ ‹ስቅሎ ስቅሎ› ነው፡፡ ‹ትዕዛዝ ከበላይ፣ እግር ወደላይ› ይሆናል መመሪያው፡፡
 
በዚህ መንገድ ስንቱን እየደመሰስን ቀዳን፡፡ ስንቱን ነባር ዕውቀት ሳንጠቀምበት እንደ ገናሌ ወንዝ ፈስሶ ፈስሶ ቀረ፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል የተባለው በራሳችን ላይ ደርሶ ብልሆቹ አውሮፓውያን የራሳችንን መጻሕፍት ሰብስበው፣ ባሕላችንን አጥንተው፣ ታሪካችንን ፈትሸው፣ ነባር ዕውቀቶችን መርምረው - በውስጣቸው ያገኙትን ጥበብ ለዘመናዊ ሥልጣኔያቸው ተጠቀሙባቸው፡፡ እኛ ግን እየደመሰስን ስንቀዳ፣ አንድም ትናንት ሳይኖረን ዛሬን እናቆማለን ብለን መከራ እናያለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን እኛ የትናንቱን ደምስሰን እየቀዳን፣ የነገዎቹ የኛን አይደመስሱም ብለን ማመናችን ነው፡፡ ይኼንኑ አሠራር አይደል እንዴ የምናቆያቸው፡፡   

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...