2015 ኤፕሪል 22, ረቡዕ

እስመ በእንቲኣሁ ይቀትሉነ ኲሎ አሚረ፡፡ ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሑ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፤እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን:: መዝ.43፡22

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት የተሰጠ የሐዘን መግለጫአትምኢሜይል
              
                                                                                ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም.
         

ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ ነው፡፡ ይህንንም ስንል ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ምንም በደል ሳይገኝበት በአይሁድ ተከስሶ በግፍ የሞት ፍርድም ተፈርዶበት በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ደሙን አፍስሶ የሰው ልጆችን ዕዳ በደል ደምስሶ ነጻ እንዳወጣንና ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንዳደለን በማመን እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ በማለት በሰጠው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት ትመራለች ማለታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንም ይህንኑ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አምነው በሥራ ሲገልጡ ኑረዋል፤ ዛሬም በዚሁ እውነታ ይገኛሉ፡፡

ስለእውነት መሥዋዕትነት መክፈል ለቤተ ክርስቲያን እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በየዘመናቱ እግዚአብሔር ለዚህ ክብር ያደላቸው ቅዱሳን ሰዎች የጌታን ፈለግ ተከትለው ስለክርስትናቸው ወይም በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በማመናቸውና ይህንንም በይፋ በመመስከራቸው ብቻ በክፉዎች ሰዎች እጅ በሥጋቸው መከራ እየደረሰባቸው ለሞት በመብቃታቸው ሰማዕት እየሆኑ አልፈዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችንም እነዚህን ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር እሰከ ሞት ድረስ በመታመን የገለጹትን ልጆቿን በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ታዘክራቸዋለች፤ ምእመናንም በእነርሱ የሕይወት ጎዳና እንዲማሩና በኑሮአቸውም እንዲጽናኑ እያደረገች ትገኛለች፡፡ በዚህ ሂደትም የክርስቲያኖችን ሕይወት የቀጠፉትን ዓላውያንን ድርጊታቸውን እያወገዘች አድራጊዎቹ ግን በክፉ መንፈስ የተመሩ ሰዎች በመሆናቸው ለእነርሱም ልቡና እንዲሰጣቸውና ምህረትን እንዲያገኙ ከእግዚአብሔር መለመንን አላቋረጠችም፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በመሰቀል ላይ ሳለ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ቅር በላቸው በማለት የበደሉንን እንኳ ይቅርታ እንድናደርግላቸው ባስተማረን ትምህርት መሠረት ነው፡፡

የክርስትና ተግባር እንደየዘመኑ ሁኔታ የሚቀያየር ሳይሆን ከእግዚአብሔር አንድ ጊዜ የተሰጠና የጸና ዘላለማዊ እውነታ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ዛሬም በምእመናን ሁሉ ዘንድ ህልው ሆኖ ይኖራል፤ በሥራም ይገለጣል፡፡

በሰሞኑ ራሱን እስላማዊ መንግሥት (IS) እያለ በሚጠራው ዓለም አቀፋዊው አሸባሪ ድርጅት በተለያየ ምክንያት ወደ ሊቢያ የገቡ ክርስቲያን ወንድሞቻችንን እና እኅቶቻችንን ይዞ በማሰር በውስጣቸውም 30 የሚያህሉትን ወንድሞቻችንን በሁለት የተለያዩ ቦታዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደላቸው በይፋ በኢንተርኔት ባሰራጨው የቪዲዮ መረጃ አሳውቋል፡፡ በዚሁ መረጃው ላይም የተገደሉት ወንድሞቻችን የተገኘባቸው አበሳ ወይም ወንጀል ክርስቲያን ሁነው መገኘታቸው (በተለይም እነርሱ ጠላታችን ያሏት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆናቸው) እና ሃማኖታቸውንም አንቀይርም ማለታቸው እንደሆነ በግልጽ አሳውቋል፡፡ ይህም ሳይበቃው የገደለበትን አሰቃቂ መንገድ በቪዲዮ ቀርጾ በማስፈራሪያ ቃላት በማጀብ ለዓለም ሁሉ አስራጭቶታል፡፡ ይህ ሁኔታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ዋጋ የከፈለለትን የሰው ልጅ አንገቱን በካራ ቀልቶ ደሙን ማፍሰስ እና ሕይወቱን ማጥፋት እጅግ የሚዘገንን ሰይጣናዊ ተግባር ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህ አሳዛኝ ዜና እንደተሰማ ድርጊቱን አውግዞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ደረጃ የጸሎት ጊዜ ማወጁና ምእመናን ሁሉ በየአሉበት አካባቢ ሁነው እንዲሳተፉ ጥሪ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ምእመናን ሁላችንም በዚህ የአንድነት መገለጫ በሆነው መንፈሳዊ ተግባር ላይ ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ በበረኻው ላይ ደማቸው የፈሰሰው ወንድሞቻችን ለሃይማኖታቸው ያሳዩት ጥብዓት ለሁላችንም ትልቅ ትምህርት የሚሆንና አክብሮት የሚገባው ተግባር ነው፡፡ እነርሱ ወደጠራቸው ወደ እግዚአብሔር በክብር ተጉዘዋል፡፡ በወንጌል ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩâ€Ãƒ‚ºÃƒÃ‚¢€Ãƒ‚º በማለት የተጻፈውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በሥራ በመተርጎም ምስክር ሁነዋል፡፡ ሉቃ.12.4 የተማሩትን የክርስትና ትምህርት በትክክል በሥራ በማሳየታቸው እጅግ የሚያኮራ ተግባር ፈጽመዋልና ሁላችንም እንኰራባቸዋለን፡፡

በርግጥ በሥጋ ስለተለዩን እንደ ሰውነታችን ልናዝንና ልናለቅስ እንችላለን፡፡ በተለይም ቤተሰዎቻቸው እና የቅርብ ወዳጆቻቸው የደረሰባቸው ኀዘንና ጉዳት ከፍትኛ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ስለዚህም የልብ ስብራትን የሚጠግነው እግዚአብሔር አምላካችን መጽናናትን እንዲሰጣቸው እንጸልያለን፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ወንድሞቻችን የተጓዙት ሁላችን ወደምንናፍቀው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመሆኑ ልናዝን አይገባም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ምስክር ያገኙ በመሆናቸው ደስ ሊለን እንጂ፡፡ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት በክፉዎች ሰዎች ፊት ያለፍርሃትና ያለኀፍረት ስለርሱ መስክረው በዐደባባይ መከራ ተቀብለዋል፡፡ ማቴ.10.32፡፡ እንዲሁም ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጎናጸፋል፣ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፤ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ በማለት እንደተናገረው ቃሉ የታመነ የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋጋቸውን እንደሚከፍላቸው ፍጹም እምነታችን ነውና በዚህ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ራእ.ዮሐ.3.5፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጸጋና ክብር አግኝተው ወደ አምላካቸው ለሔዱት የሃይማኖት ጀግኖች የክብር አሸኛኘት ማድረግና አኩሪ ተግባራቸውን ማዘከር ግን ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ዘመን ላለነው ክርስቲያኖች ሁሉ ለሃይማኖታቸው ሕይወታቸውን አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ መሥዋዕት በመሆን አብነት ሁነውናልና፡፡

ይህ ጭካኔና ክፉ ድርጊት የፈጸሙት ፉከራቸውን በዐደባባይ የገለጹት ሰዎች ምናልባት ክርስቲያኖች በዚህ ፈርተውና ተሰቅቀው ከሃይማኖታቸው ፈቀቅ የሚሉ፣ ቤተ ክርስቲያንም የምትሸማቅቅ አድርገው ገምተው ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ሰማዕትነት ክርስትናን የሚያለመልምና የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ከታሪክ ሊማሩት ይገባል፡፡ የመጀመሪያውን ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ለመበተንና ክርስትናን በእንጭጩ ለማጥፋት አስበው አይሁድ ቅዱስ እስጢፋኖስን በዐደባባይ በድንጋይ ይወግረው ማስፈራሪያ እንዲሆን ገድለውት ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ይህ ድርጊት ክርስቲያኖችን ከኢየሩሳሌም ከተማ ወጥተው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንዲሔዱና ክርስትናን የበለጠ እንዲያስፋፉት አደረጋቸው እንጂ ቤተክርስቲያንን ማሸማቀቅ አልቻለም፡፡

በሮማውያን የኃያልነት ዘመንም እንዲሁ ነገሥታቱ ክርስትናን ለማጥፋት ብዙ ደክመዋል፡፡ ቢሆንም የነርሱ የጭካኔ ተግባር ክርስትና የበለጠ በቤተ መንግሥታቸው ጭምር እንዲሰበክና እንዲስፋፋ፣ የቤተ መንግሥቱ አባላት የነበሩ ሰዎችም ክርስትናን እየተቀበሉ ሰማዕታት እንዲሆኑ አደረጋቸው እንጂ ክርስትናን አላጠፋውም፡፡ በርግጥ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ክርስቲያኖች ኑሮአቸውንም ሆነ መንፈሳዊ ተግባራቸውን በካታኮምብ ውስጥ እንዲያደርጉ አስገድዶ እንደነበር ግን አንዘነጋውም፡፡ አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች በክፉ አሳብ በሚመሩ ሰዎች ምክንያት እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ቢያጋጥም ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተምረንና በእግዚአብሔር ኃይል ታምነን ፍጹም ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድና ልናሳልፈው፣ ድል ልንነሣውም ይገባል፡፡

እኛ በክርስቶስ የደም ዋጋ የተገዛንና ዋጋም የተከፈለልን መሆኑን ሳንዘነጋ በክርስትናችን ምክንያት ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ሲመጣ እንደነዚህ ወንድሞቻችን በጥብዐት ልንቆም ያስፈልጋል፡፡ እነርሱ ሕይወታቸውን ሰጥተው ለሃይማኖታቸው እንደተጋደሉ መደለያ የሆነው ጊዜያዊ ኑሮም እንዳላታለላቸው ሁሉ እኛም ሃይማኖታችንን ከሥጋዊ ፍላጎታችን በላይ ልናስቀድም እንደሚገባን የተማርንበት ክስተት በመሆኑ ሁላችንም እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥመን ልንከተለው የሚገባንን የክርስትና አቅጣጫ ግልጽ በሆነ መንገድ በማሳየት ረገድ ለዚህ ዘመን ትውልድ መልካም አርአያ ሆነውናልና በዚህም ዘወትር ልናዘክራቸውና ልናመሰግናቸው ይገባናል፡፡

ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ብንኖርም ከእግዚአብሔር ጋር በደስታ እንኖራለን በሥጋ ብንሞትም ወደ እግዚአብሔር እንሔዳለንና ሁሌም የእግዚአብሔር ነን፡፡ በመጽሐፍ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፣ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፡፡ እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን እንደተባለው በማንኛውም ሁኔታ በእግዚአብሔር ደስ ይለናል እንጂ በምንከፍለው ዋጋ ልንሳቀቅ አይገባንም፡፡ ሮሜ.14.8፡፡

ክርስትና ራስን ለሌላው አሳልፎ መስጠት ነውና አንዱ ወገናችን ሲያዝን በሐዘኑ ልንካፈል ጭንቀቱንም ተጋርተን ብንችል ልናቃልልለት ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፣ ከሚያለቅሱት ጋር አልቅሱ ሮሜ.12.15፤ በማለት እንዳስተማረው በማኅበራዊ ሕይወታችን በፍቅር መንፈስ ልንረዳዳ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በዚህ በመከራ ጊዜ ሐዘንተኞችን ማጽናናት፣ እንዲሁም ደግሞ ገና በየእስር ቤቱ በችግርና በሰቆቃ ያሉትን ወገኖቻችንን በምትለው ዐቅም ሁሉ ልንረዳቸውና ከጎናቸው ልንቆም ያስፈልገናል፡፡

ከዚህ አንጻር ካህናት አባቶቻችንም ሆኑ መምህራነ ወንጌል ድርሻቸው የጎላ ነውና የተለመደ መንፈሳዊ አገልገሎታቸውን ፍጹም በሆነ ሓላፊነት እንደሚወጡ አንጠራጠርም፡፡ በተለይ የችግሩ ሰለባ የሆኑትን በመርዳቱ ረገድ ሁሉም ሰው በአፋጣኝ የድርሻውን እንደሚወጣ እምነታችን ነው፡፡ እዚህ ላይ በተለያየ ምክንያት ከሀገራቸው የወጡ፣ በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉና ያለፉ ሁሉ አንዳቸው ሌላውን ወገናቸውን በመርዳት መንፈሳዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ ማሳሰቡ አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህ ክስተት የምንማረው ሰው በመልካም ትምህርት ከተቀረጸ ነፍሱን ለሌላው አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ እንደሚታገስ ለሃይማኖቱም ፍጹም ዋጋ ሊከፍል የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ምእመናኗን በትምህርተ ሃይማኖትና በሥነ ምግባር በመቅረጹ ረገድ የበለጠ በርትታ እንድትሠራበት የሚያመላክት ነው፡፡ እውነተኛው የክርስትና ትምህርት ሌላውን ወደማጥፋት ሳይሆን ወደ ርኅራኄና የራስን ሕይወት ወደመስጠት፣ በአጠቃላይም እንዲህ ወደ መልካም ጎዳና ይመራልና፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ክፉ ትምህርት ሰውን ወደ አውሬነት ሊቀይር የሚችል መሆኑን ይህን ኢሰብአዊ ተግባር ያለምንም ርኅራኄ ሲፈጽሙ ከምናያቸው ሰዎች እንገነዘባለን፡፡ ስለዚህ ሰዎችን ከልጅነታቸው ጀምሮ በጥሩ መንገድ መምራት፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን መስበክ፣ በአጠቃላይም መልካም የሆነውን ትምህርት ማስተማር ለሀገርም ሆነ ለዓለም የሚበጅ መሆኑን ተረድተን ሁላችንም የበኩላችንን እና የሚመለከተንን መወጣት እንደሚያስፈልገን ትምህርት ወስደንበታል ብለን እናምናለን፡፡

ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ከተሰማ ጀምሮ የተለያዩ አካላት ድርጊቱን በማውገዝ ኃዘናቸውን በመግለጽ ረገድ የየራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ ይህ በራሱ የጋራ አንድነትንና መረዳዳትን የሚያመለክት በመሆኑ በእጅጉ የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ የጭካኔ ሥራ በአጭር ጊዜ የተቀነባበረና የአንድ ወቅት ክስተት ሳይሆን በተደጋጋሚ እየተፈጸመ የብዙ ንጹሐን ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከማውገዝ ባለፈ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጣና ችግሩን ሊፈታ የሚችል ሥራ በመተባበር ሊሠራ ይገባዋል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም የተለያዩ የእምነት ድርጅቶችና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ግንባር ቀደም ድርሻ ሊኖራቸው ስለሚገባ ልዩነትን ከማጉላት ይልቅ ለሰው ልጅ ሕይወት የሚጠቅም ነገር በመሥራት ሓላፊነታቸውን ሊወጡ፤ መንግሥታትንም ሊያሳስቡ ይገባል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆንን ሁላችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በሆነው ትምህርቱ እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና፡፡ ማቴ.5.44-45፡፡ በማለት እንዳስገነዘበን ክፉ አድራጊዎቹ ድርጊታቸው የሚወገዝና ማንም ሰው ቢሆን ሊጸየፈው የሚገባ ቢሆንም ይህን የፈጸሙት ሰዎችና የአስተሳሰባቸው ደጋፊዎች የሆኑ አካላት ግን ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ እንደ ክርስትናችን ትልቅ ሓላፊነት አለብን፡፡ በክርስትና ጎዳና የተጓዙ አባቶቻችንና እናቶቻችን የጭካኔ ተግባር እየፈጸሙባቸው ያሉትን ሰዎች ሳይቀር ምሕረት እንዲያገኙ ወደ እግዚአብሔር ያመለክቱላቸው እንደነበር ከታሪካቸውና ከገድላቸው እንማራለን፡፡ ስለዚህ እኛም ለእነዚህ ክፉ አድራጊዎቹ ሰዎች ልንጸልይላቸው፣ እግዚአብሔር እንዲምራቸው ልቡናን እንዲሰጣቸው ልንለምንላቸው ይገባል፡፡ በውስጣቸው ያለው መንፈስ እጅግ ክፉ ነውና ጌታም በወንጌል ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም ማር.9.29፡፡ በማለት እንዳስተማረው እንዲህ ዓይነቱ ክፉ መንፈስ ከሰዎች እንዲርቅ በጾምና በጸሎት ልንተጋ ይገባናል፡፡

በመጨረሻም ስለሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን የተቀበሉትን ወንድሞቻችንን አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱሳንን ባከበረበት ክብር እንዲያከብራቸው፣ ለቅዱሳን ሰማዕታት ያቀዳጃቸውን የክብር አክሊል እንዲያቀዳጃቸው በፍጹም እምነት እየጸለይን ቤተሰዎቻቸውንና ወዳጆቻቸውንም ቸሩ ፈጣሪያችን መጽናናትን እንዲያድላቸው እንመኛለን፡፡

2015 ኤፕሪል 21, ማክሰኞ

ሰበር ዜና – ቅ/ሲኖዶስ ከነገ ሚያዝያ ፲፬ ቀን ጀምሮ የሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ ዐወጀ፤ ቤተሰቦች የተሠው ክርስቲያኖችን ፎቶ፣ ስመ ክርስትና እና ሙሉ አድራሻ እንዲያቀርቡ አዘዘ – ‹‹ልጆቻችን የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን ናቸው››


pat mat
  • ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቢያ በግፍ የተሠው ክርስቲያኖች፣ ሃይማኖታችንን አንክድም በማለት የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉየሃይማኖት መስተጋድላን መኾናቸውን አረጋገጠ፤ ‹‹የልጆቻችን ሰማዕትነት በእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅ ዋጋ ስላላቸው በዚኽ ከሐዘናችኹ እንድትጽናኑ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች፡፡››
  • ነገ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መላው የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ ካህናት የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች እንዲኹም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ሓላፊዎች እና ልዩ ልዩ ሠራተኞች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ወንጌል ይከናወናል 
  • ሥነ ሥርዐቱ በደቡብ አፍሪቃ በግፍ የተገደሉ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንንም ይጨምራል

ነፍስህን ይማር በሉኝ


 ሁለት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በአንድ ላይ  ያገለግላሉ  ሰባክያነ ውንጌል ናቸው  አንደኛው ለአገልግሎት ውደ ክፍለ ሀገር ወጥተው  ሲመለሱ የመኪና አደጋ ደረሰና ወደ 35 ሰዎች ህይወታቸው  ሲያልፍ ሰባኬ ወንጌሉ ተረፉ  ይህንን የሰማ በልደረባቸው  የስራ አጋሮቹን ጠርቶ  ከፊታቸው ቁጭ ብሎ  ነፍስህን ይማረው  በሉኝ  እኔ እደሆን  ለአገልግሎት መንቀሳቀሴ አይቀርም  አደጋውም  አይቀርምና መሞቴ ሰለማይቀር  ከወዲሁ  አይኔ እያየ ጆሮየ እየሰማ  ነፍስህን  ይማረው በሉኝ  አለ ይባላል ፡፡
 በጆሮአችን ስንሰማ የነበረውን  በመጽሐፍ ስናነብ ነበረውን  ሰማእትነት  በዐይን አይተናል  ድሮውኑ ክርስቲያን መሆን ሰማእትነት የሚያጎናጽፍ ስለሆነ  ሁላችንም አንገታችንን እንደ ሰጠን ለጊዜው እየቆጠርን ተግባራዊ ለሚሆነው ሰማእትነት መታደል የሚጠይቅ ቢሆንም ሃይማኖታዊ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፤፤

ለነገሩ በቸልተኝነት አልፈነው ነው እንጂ  1999 ዓ.ም በጅማ  የነበረው ሰማእትነት  ትኩረት ስላልተሰጠው አሁን  ገና ዋጋ ያስከፍላል፡፡  በተለይ የሃይማኖት መሪዎችን፡ በነገራችን ላይ እስካሁን የግብጾችንም ጨምሮ  የሃይማኖት መሪዎች  ለሰማእትነት  አልተመረጡም  ምሥጢሩ ምን ይሆን ?

ታላቁ ሊቅ ሊቀ ጉባዔ ቀለመወርቅ ገብረ ዮሐንስ አረፉ



ሊቀ ጉባዔ ቀለመወርቅ   በ1927 ዓ.ም ነሐሴ 5 ቀን  በቀድሞው ጎንደር ከ/ሀገር  እስቴ ወረደ  ከአባተቸው  ገብረ ዮሐንስና ከእናታቸው ወ/ሮ ጠጅቱ  ተወለዱ ፡፡ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሱ በአካባቢያቸው  ከሚገኙ መምህራን  ዳዊት ፤ ውዳሴማርያም  አጠቃላይ ንባብ በሚገባ ተምረዋል ፡፡ በመቀጠልም ወደ ደብረ ታቦር ሄደው ዲቁናን  ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዘግሸን ተቀብለዋል ፡፡ ወደጎጃም በመጓዝ  ቅኔን ከነ አገባቡ በሚገባ ተምረዋል  በ1946 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሄደው  ጽርሐ አርያም ቅ. ሩፋኤል  ተመድበው አገልግለዋል  ፡፡በ1951 ዓ.ም መጋቤ ብሉይ ቶማስ ደብረ ጽጌ ቅ/ ማርያም ተመድበው ሲሄዱ አብረው በመሄድ  በዚሁ ገዳም እንደገና ቅኔ ፤ መጻሕፍተ ብሉያት ፤ባሕረ ሓሳብ  ከየኔታ አምሳሉ ክብረ በዓል የተማሩ ሲሆን የኔታ አምሳሉ ሲልቁ ከየኔታ ቀለመወርቅ አቋቋም፣ ክበረ በዓል እና መዝሙር በሚገባ ተምረዋል ፡፡ ከ1956 ዓ.ም ከሰዋስወ ብርሃን ቅ/ ጳውሎስ ማሰልጠኛ በመጡ በአባ ገ/ሚካኤልና በመምህር ገ/ወልድ(የአሁኑ አቡነ ኤርምያስ) የስብከት ዘዴ እና የመሳሰሉትን ስልጠናዎች ሰልጥነዋል(በቦታው)፤ አያይዘውም በ1978 ዓ.ም ወደ ዘዋይ ገዳም ገብተው ለ3 ወራት ያህል የስብከት ዘዴ እና የመሳሰሉትን ተጨማሪ ሥልጠናን ወስደዋል ::  
 ፡ በ1959 ዓ.ም ወደ ደብረ ጽጌ ገዳም ተመልሰው  በሊቀ  ጉባዔነት ፤ በንባብ መምህርነት ፡ የገዳሟ አስጎብኚ በመሆን ሃይማኖተ አበውን በማስነበብ ፤ በሰባኬ ወንጌልነት፤ አገልግለዋል ፡፡ በተለይ የጻድቁ አቡነ ሀብተማርያምን ገድል            ለ28  ዓመታት/ ለ4 ሱባኤያት) በመተርጎም  የጻድቁን ታሪክ ለህዝቡ በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በደብረ ጽጌ ገዳም ብቻ ለ56 ዓመታት ያህል ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል  ሊቀ ጉባዔ  ቀለመወርቅ ፤ቅን ፤ሰው ወዳጅ፤ ዘመኑን የዋጁ ሰባኬ ወንጌል የማንኛውን ጥያቄ መላሽና  የሚጠቀሱ መጽሐፍ ነበሩ፡፡ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 11  ቀን በ80 ዓመታቸው  አርፈው  ሥርዓተ ቀብራቸው  በተለያየ ቦታ የሚገኙ ሊቃውንት  ልጆቻቸው  ወዳጅ ዘመዶቻቸው  በተገኙበት  ሚያዝያ 12  /2007 ዓ.ም  በደብረ ሊባኖስ ገዳም  ተፈጽሟል ፡፡ሊቀ ጉባዔ ባለትዳርና  የሦስት ወንዶችና  ሦስት ሴቶች ልጆች አባት ናቸው ፡፡ የአባታችንን ነፍስ  ከቅዱሳን ዕቅፍ ያኑርልን፡፡

2015 ኤፕሪል 20, ሰኞ

የምናዝነው ስንት ሰው ሲሞት ነው?

በየመን፣ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ስለሚሞቱት ዜጎቻችን የሚሰጡት መንግሥታዊ መግለጫዎች ሁለት ነገር የጎደላቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሰብአዊ ስሜት፡፡ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ስለሌላው ሰብአዊ ፍጡር መከራና ስቃይ ሲሰማ መጀመሪያ አንዳች የኀዘን ስሜት ይሰማዋል፡፡ ከዕውቀት ይልቅ ስሜት ለሰዎች ቅርብ ነውና፡፡ ባለሥልጣን ቢሆን፣ ፖሊስ ቢሆን፣ ዳኛ ቢሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሆን ሰው ነውና ስሜት አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ያዝናል፣ ይከፋዋል፣ ልቡ ይረበሻል፣ ሆዱ ይባባል፣ ኅሊናው ይደማበታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያው ሥራው ማዘን ቀጥሎም ኀዘኑን በወጉ መግለጥ ነው፡፡ 

ሰሞኑን የማያቸው መግለጫዎቻችን ግን የኀዘን ወግ በሀገራችን የሌለ የሚያስመስሉ ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ወደ አደባባይ ወጥተው ለሞቱት ወገኖቻችን እንደ ኢትዮጵያዊነት ኀዘናቸው የሚገልጡት፣ ጥቁር ልብስ ለብሰው የምናያቸው፣ ነጠላ የሚያዘቀዝቁት ስንት ሰው ሲሞትብን ነው? የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ኀዘንኮ ፖለቲካ አይደለም፣ ፓርቲ አይደለም፣ ርእዮተ ዓለም አይደለም፣ ሊብራልም አብዮታዊ ዲሞክራሲም አይደለም፡፡ ኀዘን ሰብአዊነት ነው፡፡ የሚመራቸው ዜጎቹ፣ የሚያሠማራቸው በጎቹ ሲታረዱና ሲሞቱ ኀዘኑን በይፋ የማይገልጥ መሪና እረኛ መቼ ነው ኀዘኑን የሚገልጠው?
ዜጎቹ በሕገ ወጥ መንገድም ይሂዱ በሕጋዊ፣ ድንበር ጥሰውም ይሂዱ በአውሮፕላን ተሳፍረው፤ መጀመሪያ ሰዎች፣ ቀጥሎም የዚህች ሀገር ዜጎች ናቸውና ኀዘን ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው አገኘዋለሁ ብሎ ከሚያስበው ክብር አንዱ በሞቱ ጊዜ የክብር ልቅሶና ኀዘን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአካባቢያቸው ላለመራቅ፣ ከራቁም ለመመለስ ከሚሰጧቸው ምክንያቶች አንዱ ‹በክብር ዐርፎ በክብር መቀበርን፣ የክብር የኀዘን ሥነ ሥርዓትን ማግኘትን› ነው፡፡
ካገሬ እንዳወጣህ አገሬ መልሰኝ
በሹም የታዘዘ አፈር አታልብሰኝ፤
እንኳን የሚቀብረው የሚያዝንለት አጣ
ምን ወግ ማረግ ያያል ካገሩ የወጣ፤
የሚሉት ለዚህ ነበረ፡፡
የመንግሥት አካላት ለምን ይኼንን ለመዘንጋት እንደፈለጉ አልገባኝም፡፡ የደቡብ አፍሪካው ቃጠሎና ግድያ ሲመጣ የሀገራችን ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ብቅ ብለው ‹‹በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ነገር ከልብ እናዝናለን፣ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር ተነጋግረን አስፈላጊውን እናደርጋለን፤ ተመሳሳይ ችግር ለወደፊቱ እንዳይከሰትም አንሠራለን› ዓይነት ሰውነት ያለበት መግለጫ ጠብቄ ነበር፡፡ የለም፡፡ ሲሆን በሀገራችን የልቅሶ ሥነ ሥርዓት መሠረት፡፡ አሁን ደግሞ ዓለም ያወቀው አሸባሪ ‹አይ ሲስ› ኢትዮጵያውያኑን በክርስትና እምነታቸው ብቻ ሲሠዋቸው የተሰጠው መግለጫ ስሜት የሌለበት፣ ማዘን መደሰታቸውን የማይገልጥ፣ እንኳን ሰው እንስሳ የሞተብን የማያስመስል ሆነ፡፡ ከማጣራቱም ከምኑም በፊትኮ ስሜቱ ይቀድማል፡፡፡ አዝናችኋል ወይ? ስትሰሙና ስታዩ ምን ተሰማችሁ? የአሜሪካ መንግሥት እንደዚያ ዓይነት መግለጫ ሲያወጣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ያንን ነው ወይ መስማት ያለብን? ለመሆኑ መሪዎቻችን ኀዘናቸውን የሚገልጡት ምን ስንሆን ነው? ለምንድን ነው ሁሉም ነገር ፖለቲካ የሚሆነው?
ሁለተኛው የሚጎድለው ነገር ደግሞ ፍጥነት ነው፡፡ አትሌቶቻችን በኦሎምፒክ ሲያሸንፉ የባለሥልጣናቱ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ሯጮቹ ቆርጠውት ካለፉት ሪቫን ቀጥሎ የሚመጣ ዜና ነበር፡፡ አትሌቶቹ ደክሟቸው ከመሬት ሳይነሡ የባለሥልጣናቱ መልእክት ለሚዲያ ይደርስ ነበር፡፡ በዚህ የሁላችንም ኀዘን በሆነው ጉዳይ ግን ለምን መዘግየት እንደተመረጠ ግልጽ አይደለም፡፡ ማጣረቱ፣ መረጃ መሰብሰቡ፣ ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ሂደቶችን መሄዱ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ማዘን ግን ጊዜ አይወስድም፡፡ ቪዲዮው ተለቅቋል፡፡ ሲሞቱ እያየን ነው፡፡ መልካቸው የኛው ነው፡፡ አይሲስ የገደላቸው ‹ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች› ብሎ ነው፡፡ የዓለም ሚዲያዎች ያንኑ እያስተጋቡ ነው፡፡ ይኄ ለኀዘን ያንሳል? አፈፍ ብሎ ተነሥቶ ‹በሆነው ነገር እናዝናለን፤ ልባችን ተነክቷል፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፤ ዝርዝሩን በየጊዜው እንነግራችኋለን› ለማለት ስንት ሰዓት ይወስዳል? የደቡብ አፍሪካው ችግር ደረሰ እንደተባለ ሙጋቤን ለውግዘት የቀደማቸው የለም፡፡ የኛዎቹስ የት ሄዱ?
መንፈሳዊ መሪዎችስ የት ናቸው? አንዳንዶቹ ውጭ ሀገር መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡ ሲሆን ይህንን ሲሰሙ አቋርጦ መምጣት፤ ካልሆነም ባሉበት ሆኖ አባታዊ ኀዘንን መግለጥና በእምነቱ የሚገባውን ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ሲኖዶሱስ ምን እየሠራ ነው? አልሰማም ይሆን? ዛሬ ጠዋት ቢያንስ በአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎት መደረግ አልነበረበትም? ባፈው ካይሮ ሄዳችሁ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው ያያችሁት? በጎቹ እረኛ የላቸውም ማለት ነው? አባቶች የሚያዝኑት ምን ሲገጥማቸው ነው? እረኛው የሚያለቅሰው ስንት በጎች ሲታረዱ ነው?
ቤተ ክርስቲያኒቱ ነገሩን በዝምታ የምታልፈው ከሆነ እኛ እንደ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ቀኖና እነዚህን በክርስትናቸው  ምክንያት የተሠው ክርስቲያኖች ‹ሰማዕታተ ሊቢያ› ልንላቸው ይገባል፡፡ የሰማዕትነታቸውንም በዓል ማክበር አለብን፡፡ በስንክሳሩ ማስገባት ባንችል ታሪካቸው በኅዳጉ ማስፈር አለብን፡፡ ማንም ይሁኑ ማን፣ በሚገባ የተማሩም ይሁኑ ያልተማሩ፣ ከመካከላቸው የማያምኑም እንኳን ቢኖሩ የተገደሉበት ምክንያት ክርስትና ነውና ሰማዕታት ናቸው፡፡ ያውም ‹ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት›፡፡ በስንክሳሩ እንደምናነበው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን የክርስቲያኖች መንደርና ቤተ ክርስቲያን እየተወረረ ክርስቲያኖቹ ሲሠው ገና ያልተጠመቁት፣ ነገሩ ያልገባቸው፣ ክርስትናን ለመቀበል ያልወሰኑት ሁሉ አብረው ተሠውተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን የተሠውበት ምክንያት ክርስትና በመሆኑ ሁሉንም ሰማዕታት ብላቸዋለች፡፡ የእነዚህም ክብር እንዲሁ ነው፡፡
እነርሱ በሰማይ ዋጋ አላቸው፡፡ አክሊለ ሰማዕታትንም ተቀብለዋል፡፡ እኛ ግን ሰማዕታቱን ባለማክበራችን ክብር ይጎድልብናል፡፡ ‹በረከታቸው ይደርብን› እንጂ ‹ነፍስ ይማር› አንልም፡፡   

 


 
 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቢያ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ


አትም ኢሜይል
ሚያዝያ 12 ቀን 2007 ዓ.ም.

የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች አቅርበናል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ ሀገር በንጹሐን ወገኖች ላይ ስለተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም ከእኩለ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ የዜና ማሰራጫዎች በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ አካባቢ አይኤስ በተባለ አሸባሪ ቡድን በንጹሐን ወገኖች አሰቃቂ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ዘግበዋል፡፡

ዘገባው ከምንኑም ከምኑ የሌሉበት ንጹሐን ክርስቲያን ወጣቶች በታጠቁና ፍጹም ሰብኣዊነት በሌላቸው አሸባሪዎች ሲገደሉ የሚያሳየው ምስልም በመላው ዓለም እየታየ ይገኛል፡፡

አሰቃቂው ግድያ ስለተፈጸመባቸው ንጹሐን ወጣቶች ዜግነትና ማንነት ግልጽና አስተማማኝ የሆነ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በበርካታ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ሲነገር እንደሚሰማው የዚህ የግፍ ወንጀል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን የዜና ማሰራጫዎቹ አክለው እየገለጹ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈጣሪ የተሰጠች የማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ኃላፊነት በማይሰማቸውና በእነሱ ላይ በማይፈቅዱ ምንም ዓይነት ሰብአዊ ርኅራኄ በሌላቸው እንድትቀጠፍ ስለማትፈቅድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን አሰቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፣ አጥብቃም ታወግዛለች፡፡

ስለዚህ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ተገንዝበው ሁኔታውን በትዕግሥት እንዲጠብቁ፤

እንደዚሁም የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር መሆኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያን የሆኑ ሁሉ እንደቀድሞው በአንድነት በማውገዝ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ኪሣራ እንጂ ምንም ዓይነት ትርፍ የማያገኙ መሆናቸውን በተግባር እንዲያሳዩዋቸው እናሳስባለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ

በሊቢያ የሚኖሩ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ


አትም ኢሜይል

ሚያዝያ 12ቀን 2007ዓ.ም
martyrበሊቢያ የሚኖሩ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም አይ ኤስ አይ ኤስ በተባለው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ክርስቲያን በመሆናቸውና ሃይማኖታችንን አንቀይርም በማለታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ፡፡
አሸባሪ ቡድኑ ካሰሠራጨው ቪዲዮ ለመረዳት እንደተቻለው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖቹ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት በመታረድና ጭንቅለታቸው በጥይት ተፈርክሶ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አሸባሪ ቡድኑ ያሠራጨውን ቪዲዮ መነሻ በማድረግ ባሠራጩት ዘገባ የተገደሉት ክርስቲያኖች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዘመን በአሸባሪ ቡድኑ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት የሚወገዝ ሲሆን፤ ድርጊቱን ለፈጸሙት አካላት እግዚአብሔር ልቡና እንዲሰጣቸው እንጸልያለን፡፡ ክርስቲያን ወንድሞቻችንም ስለ ሃይማኖታቸው ሲሉ ያሳዩት ምስክርነት፣ ስላሳዩት ጥብዓት /ስለ ሃይማኖት መከራን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን/ የወንጌልን ቃል መፈጸም በመሆኑ በእግዚአብሔር መንግሥት የከበሩና በቅዱሳኑ ዘንድ የተመሰገኑ ናቸው፡፡

ይህ በመሆኑም ድርጊቱ በዚህ ዓለም ላለነው ሰዎች እጅግ አሰቃቂ ቢሆንም በክርስቲያን ወንድሞቻችን ክርስቲያናዊ ተግባር እንኮራባቸዋለን፡፡ ጌታችን በደሙ የመሠረታትን፣ ቅዱሳን በደማቸው ያጸኑዋትን ቤተ ክርስቲያን እነሱም በደማቸው መሥክረዋልና፡፡

በመጨረሻም በክርስቲያን ወንድሞቻችን አሰቃቂ ሞት ምክንያት ለገጠማችሁ መሪር ሐዘን ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም በድርጊቱ ላዘናችሁ በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን፡፡

ይህን ጉዳይ እየተከታተልን የምንዘግብ መሆኑንም እንገልጻለን፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...