2015 ጁን 1, ሰኞ

፬ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የጋራ አቋም መግለጫ


eotc ssd pouring out to patriarch palace00
በሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት እና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና እና ዕድገት ፊት ከተጋረጡትና አፋጣኝ እልባት ከሚሹት የዘመናችን የውስጥ ችግሮች እና የውጭ ተግዳሮቶች ውስጥ ሙስና እና ኑፋቄ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አንዱ የሌላው መተላለፊያ፣ መንሥኤ እና
ውጤት እየኾኑ ለቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ለውጥ የተደረጉ ጥረቶችን ሲያመክኑ፤ የመዋቅር እና የአደረጃጀት አቅሟን ሲያዳክሙ ቆይተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. መግለጫ እንደተመለከተው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው ከተለዩ በኋላ በቅጥር ወደ አስተዳደራዊ እና የአገልግሎት መዋቅሯ የገቡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን መኖራቸው ሙስና እና ኑፋቄ የተሳሰሩ እና የሚመጋገቡ ለመኾናቸው ግልጽ አስረጅ ነው፡፡
ከግንቦት ፳፩ – ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሔድ ቆይቶ ለጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ አርዕድ አንቀጥቅጥ በኾኑ፤ መልካም አስተዳደር እና ፍትሐዊ ፍርድ በሚጠይቁ መዝሙሮች ትላንት ማምሻውን የተጠናቀቀው ፬ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ፣ በጋራ አቋም መግለጫዎቹ በቀጥታ ይኹን በአማራጭ ያረጋገጠውም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡
*       *       *
eotc ssd 4th gen assembly participants
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የወላይታ ኮንታ እና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ፣ የጉራጌ ስልጤ ከምባታ እና ሐዲያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች
ከተለያዩ አካላት ጥሪ የተደረገላችኹ የክብር እንግዶች፤
እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤያትን ወክለን በ፬ኛው የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የተሳተፍን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ከግንቦት ፳፩ – ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ላለፉት ሦስት ቀናት÷ የማደራጃ መምሪያው ዓመታዊ የአገልግሎት ዘገባ፤ ከ37 አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የሰንበት ት/ቤቶች ዋና ክፍሎች ሪፖርቶች፤ የሰንበት ት/ቤቶች አባላት በኾኑ ባለሞያዎች በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡
በመምሪያው ዘገባም ኾነ ከ37 አህጉረ ስብከት የመጡ ተወካዮች ያቀረቡት ሪፖርት ሰንበት ት/ቤቶች እጅግ በርካታ ተግባራት እያከናወኑና የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማፋጠን እየተጉ መኾኑን አስገንዝቧል፡፡ ኾኖም ግን በየአህጉረ ስብከቱ የሚታዩ፡-
  • የመናፍቃን እና የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ
  • በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እየደረሱ ያሉ የአስተዳደር በደሎች
  • የበጀት እና የመምህራን እጥረት፣ የአዳራሽ እጥረት፤
  • የአንዳንድ አህጉረ ስብከት ስፋት ለትራንስፖርት አመቺ አለመኾን፤
አገልግሎቱን እየተገዳደሩ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ኾነው ተዘግበዋል፡፡
‹‹የሰው ኃይል አያያዝ በሰንበት ት/ቤት›› በሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ መነሻነት በተደረገው ውይይትም ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ የኾነው የሰው ኃይል መኾኑን በማመን የቤተ ክርስቲያን አካላት በሙሉ በተለይም ሰንበት ት/ቤቶች ትኩረት ሰጥተን ልንሠራበት እንደሚገባ ተገንዝበናል፡፡ በማያያዝም ‹‹የኢኮኖሚ ግንባታ ለቤተ ክርስቲያን›› በሚለውም ጥናት፣ የኢኮኖሚ አቅም ማነስ÷ የመጠቀምን፣ የመደመጥን፣ የመወሰንን፣ የመተግበርን አቅም ያሳጣል፤ በሌላ በኩል እምነትን ይፈትናል፤ ሥጋዊውን ጥቅም ለማሳካት ሲባል ከቤተ ክርስቲያን መለየትን ያመጣል፤ ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሏት ያለውን የእግዚአብሔር ቃል ያስጥሳል፤ ወጣቱንም ለስደት እና ለመከራ እየዳረገ ይገኛል፤ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮም እንዳይፋጠን ያደርጋል፡፡
ስለዚኽ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ አቅሟን ልታጠናክር፤ ተሰሚነቷን ልታስከበር ይገባታል፤ ሰንበት ት/ቤቶችም የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት ሊሠሩ፤ የቤተ ክርስቲያን መምሪያዎችም ሊያግዟቸው እንደሚገባ ውይይቱ ትኩረት ሰጥቶበታል፡፡
በመጨረሻም በሪፖርቱም ኾነ በጥናታዊ ጽሑፎች የተጠቀሱትን ዋና ዋና ችግሮች በመለየት በተደረገ የቡድን ውይይት ሰንበት ት/ቤት በቀጣይነት በጋራ የምንሠራቸውን እና የምንስማማባቸውን የአቋም መግለጫዎች አውጥተናል፡፡
  1. የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከ2006 – 2010 ዓ.ም. የታቀደውን የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ በቀሩት ጊዜያት ለመፈጸም እና ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፤
  2. የሰንበት ት/ቤቶች አጠቃላይ መሪ ዕቅድ የኹሉም የአጥቢያ ሰበካ መንፈሳውን ጉባኤያት ዕቅድ አካል እንዲኾን እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችም ኹሉ መሪ ዕቅዱን ከዕቅዳቸው ጋራ በማገናዘብ እንዲያካትቱ ይደረግ ዘንድ እንጠይቃለን፤
  3. መልክአ ምድርን መሠረት ያደረገ የሰንበት ት/ቤቶች ትስስር በማጠናከር ሰንበት ት/ቤቶች ባልተቋቋሙባቸው አጥቢያዎች እንዲቋቋሙ፣ በተቋቋሙባቸው ደግሞ የተጠናከረ አገልግሎት እንዲሰጥባቸው ለማድረግ እንሠራለን፤
  4. የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ችግሮችን ለማጋለጥ ያስችል ዘንድ ከሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት የሚደርስ መረጃ የማሰባሰብ ሥርዐት በመዘርጋት የመረጃ ማሰባሰቡን አጠናክረን እንሠራለን፤
  5. በአኹኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያን ተልእኮ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንን እንቅሰቃሴ ለማስቆም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፤
  6. ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ስለ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን የቀረበው ማስረጃ ውሳኔ እንዲሰጠው፤ ውሳኔውም ተግባራዊ ይኾን ዘንድ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፤
  7. በአኹኑ ጊዜ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አባላት ላይ በተሳሳተ አመክንዮ እያደረሱት ያለው እስር፣ እንግልት እና ወከባ እንዲቆምልን በአጽንዖት እንጠይቃለን፤
  8. ከዚኽ ጋር ተያይዞ የመንግሥት የፍትሕ አካላትም ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር የሰንበት ት/ቤት አባላትን ከማሰር እና ከማንገላታት እንዲታቀቡ ይደረግ ዘንድ እንጠይቃለን፤
  9. በቃለ ዐዋዲው እና በ1986 ዓ.ም. ሕገ ደንቡ ላይ የተጠቀሰው የሰንበት ት/ቤቶች የዕድሜ ገደብ እንዲነሣልን በድጋሜ እንጠይቃለን፤
  10. ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንሥቶ እስከ አጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች የሚደርስ የፋይናንስ ትስስር እና አያያዝ ሥርዐት በመምሪያው በኩል ተጠንቶ እንዲጸድቅልን እንጠይቃለን፤
  11. የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እና ንብረት ለግል ጥቅማቸው በማዋል የቤተ ክርስቲያንን አቅም የሚያዳክሙ አማሳኞች ማስረጃ ተጠናቅሮ በአገሪቱ ሕግ መሠረት እንዲጠየቁልን እንጠይቃለን፤
  12. የቤተ ክርስቲያን የፋይናንስ አሠራር ማእከላዊ እንዲኾን እና በባለሞያዎች የሚታገዝ የክትትል እና የቁጥጥር ሥርዐት እንዲኖረው እንጠይቃለን፤
  13. በዘመናችን ሚዲያ በወጣቱ እና በሕፃናት አስተዳደግ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ስለሚገኝ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በስፋት ለምእመናን ለማዳረስ እንዲቻል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚመራ እና የሚተዳደር፤ ቤተ ክርስቲያኒቷንም የሚወክል የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እንዲጀመር በአጽንዖት እንጠይቃለን፤
  14. በአኹኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያንን የማይወክል ትምህርት እና መልእክት የሚያስተላልፉ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች በተቻለ ፍጥነት እንዲዘጉ አልያም በቤተ ክርስቲያን ስም ከመጠራት እና ከመጠቀም እንዲከለከሉ እንጠይቃለን፤
  15. ለጠቅላላ ጉባኤው ተወካዮቻቸውን ያልላኩ አህጉረ ስብከት ተለይተው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን፤
  16. በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እና ልማታዊ ጉዳዮች ከአባቶቻችን ጋር በመኾን ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እና ልዕልና የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፤
  17. የቤተ ክርስቲያናችንን ኹለንተናዊ ችግር ለመፍታት ከመንፈሳዊ ኰሌጅ ምሩቃን(ቴዎሎጅያን) ጋር ተባብረን የምንሠራ መኾናችንን እንገልጻለን፤
  18. የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ያቀረበው ጥያቄ የኹላችንም አቋም ስለኾነ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡
 ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.

2015 ሜይ 30, ቅዳሜ

4ኛው ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ተጀመረ


አትም ኢሜይል
ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስ002sundayቲያን መንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተጀመረ፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት፤ የከንባታ ሀዲያ የስልጤ ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ጉባኤውን በጸሎት ከፍተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት ከዚህ በፊት ሰንበት ት/ቤቶች ተጣምረው የጋራ ሥራ መሥራት ባለመቻላቸው በተናጠል ዕቅዶችን በማውጣትና የአፈጻጸም ስልቶች በመንደፍ ይጓዙ እንደነበር ገልጸው፤ የተናጠል ጉዞውም ውጤታማ ባለመሆኑ ከሰ/ት/ቤቶች ወጣት ምሁራን ጋር በመነጋገርና በመገምገም የአገር አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት በማቋቋም ለቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ፤ ቅዱስ ሲኖዶስም የቀረበው ጥያቄ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ጥቅም በማረጋገጥ ደንብ ወጥቶ መጽደቁን ጠቅሰዋል፡፡

የሰ/ት/ቤትን ጥቅም ባልተረዱ በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ የሰ/ት/ቤት ተማሪዎች መባል እንደ ነቀፋ ይቆጠር የነበረውን ስም ማስቀረት የሚቻለው በሥራ መሆኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው የወጣቱን አእምሮ ለሃይማኖታዊ ልማት በማነሳሳት ረገድ የአንድነቱ መቋቋም ጉልህ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ አባላቱም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጥቅም በማስቀደም ከቡድናዊና ጐሣዊ አስተሳሰብ በመራቅ የቤተ ክርስቲያንን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

001sunday003sunday
የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ መምህር ዕንቁባሕርይ ተከስተ ባቀረቡት ሪፖርትም በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ 37,332 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከ20,000,000 በላይ ወጣቶች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን፤ እሰካሁን በ8,610 አብያተ ክርስቲያናት በሥርዓት ተመዝግበው አገልግሎት በማግኘት ላይ ያሉ ወጣቶች 2,701,253 ብቻ መሆናቸውን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ገልጸው ይህንንም መሠረት በማድረግ ገና ብዙ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችንም በተመለከተ መምህር እንቁባሕርይ ለጉባኤው አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሀገር አቀፍ አደረጃጀት በመላው ሀገሪቱ አደራጅቷል፤ ያልተቋቋመባቸውም ቦታዎች ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ፤ የ2007 ዓ.ም. እና የ2008 ዓ.ም. ዝርዝር የአፈጻጸም መርሐ ግብር በማውጣት በመላው ሀገሪቱ ተግባራዊ መደረጉ፤ ከ2005 እስከ 2010 የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ፤ በማደራጃ መምሪያው ድረ ገጽ በመላው ዓለም ለሚገኙ ምእመናን እያሰተማረ መሆኑ፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀትን እስከ ወረዳ ድረስ በማውረድ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ፤ የተለያዩ ስልጠናዎችንና ጉባኤያትን እንዲሁም ስብሰባዎች ማድረጉ፤ የፋይናንስ አሠራር ረቂቅ ተዘጋጅቶ በውይይጥ ላይ እንደሚገኝ በሪፖርታቸው ውስጥ ተካትተዋል፡፡

ያጋጠሙ ችግሮችን በመተመለከተም የበጀት እጥረት፤ ብቁ የሰው ኃይል አለመመደብ፤ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ እጦት የፈጠረው ችግር፤ ወጣቶች በየቦታው እየተንገላቱና እየታሰሩ መሆናቸው፤ ሕጋዊ የወጣት ሰንበት ትምህርት ቤት እያለ ከመዋቅር ውጭ የደብር አለቃና ጸሐፊ በተጓዳኝ የጽዋ ማኅበራትን እያደራጁባቸው እንደሚገኙ፤ የማኅበራት ወሰን የለሽ እንቅስቃሴና ጣልቃ ገብነት ሓላፊው እንደ ችግር ካነሷቸው መካከል ይገኙባቸዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች በተመለከተም ግልጽ የሆነ የወጣቶች ራዕይና ስትራቴጂ ማስቀመጥ፤ከሀገር አቀፍ ጠቅላላ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት እስከ አጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ድረስ ማጠናከር፤ የሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች አሠራር እንቅስቃሴ በማእከል ደረጃ መቆጣጠርና መከታተል እንዲቻል የሀሳብ ልውውጥና ስልት መንደፍ፤ የትምህርትና የመዝሙርን ወጥነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ እንደመፍትሔ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ምክትል ሓላፊ ወ/ሮ ማርታ ኃ/ማርያም ባቀረቡት ሪፖርት የአንድነቱ ሥራ አመራር ኮሚቴ ከተመረጠ ሁለት ዓመታት ቢያስቆጥርም የአመራር አባላቱ ከተለያዩ አህጉረ ስብከት የተመረጡ በመሆናቸው ተሰባስቦ ወጥ የሆነ አገልግሎት ለመፈጸም እንደተቸገሩ ገልጸው፤ በዚህ ዓመት ግን የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች እያጋጠሟቸው ከሚገኙ ችግሮች መካከል ሲገልጹ የተዘጋጀ ሥርዓተ ትምህርት በየደረጃው ያለመኖር፤ የመመህራን ችግር፤ የፋይናንስ እጥረት፤ ከውስጥ ሆነው ቤተ ክርስቲንን የሚያጠቁ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ እንዲሁም የአስተዳደር ችግሮች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በተነሱትና ሌሎችም ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ጠቅላላ ጉባኤው ተወያይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡

ቀጥሎም የሀገረ ስብከታቸውን ሰንበት ትምህርት ቤቶች  አንድነት ወክለው በመጡ የሰንበት ትምህርት ቤት አመራር አባላት የ2007 ዓ.ም. ሪፖርታቸውን በቅደም ተከተል አቅርበዋል፡፡

መምህር በለጠ ብርሃኑ የሰው ኃል አያያዝ በሰንበት ትምህርት ቤት በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ተከታታ ቀናት ሲካሔድ ይቆያል፡፡

2015 ሜይ 26, ማክሰኞ

ሰበር-ዜና የታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም የድጓው ሊቅ አለቃ መርዓዊ /የኔታ መኮንን አረፉ

                                                                                                         ዜና ዕረፍቱ ለአለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል ማኅቶታ ለደብረ ሊባኖስ ፈረየ ዓምአተ ወአመከአበ ቦ ዘ፷ ወቦ ዘ፴ ዘራዒሁሰ እንድርያስ ውእቱ ወፍሬሁኒ ጳጳሳት ወሊቃውንት እሙንቱ ::
   ታላቁ ሊቅ አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል የቤተ መንግሥት ቁም ጸሐፊና የደብረ ሊባኖስ ገዳም የሃይማኖተ አበው ትክለኛ ከሆኑት አባታቸው አለቃ ሣህለ ሚካኤልና ከእናታቸው ወ/ሮ እቱነሽ ጌታሁን በደብረ ሊባኖስ አካባቢ ልዩ ስሙ ፍኖተ ጽድቅ /ዋሻ ገደል/ ታሕሳስ 13ቀን 1915 ዓ.ም ተወለዱ
  እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የአባታቸው ርስት ከሚገኝበት ልዩ ስ ጠሬ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከአባ ወልደ ማርያም ንባብና የቅዳሴ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጲያን በወረረበት ወቅት ከተክለ ሃይማኖት ልጆች ጋር በመሆን ገና በልጅነት ዕድሜያቸው በግዳጅ ታስረው ወደ ሞቃዲሾ ተግዘዋል ከዚያም ፋሺሽት ጣሊያን ድል ተነሥቶ ኢትዮጲያን ለቆ ከወጣ በኋላ በ1933 ዓ.ም  ከሞቃዲሾ ወደ ትውልድ ቦታቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ተመልሰው በጠላት ምክንያት ለተቋረጠው ትምህርታቸው መንፈሳዊ ቅንዓትና ልዩ ፍላጎት ስለነበራቸው
 አንደኛ ከሁለቱ መምህራኖች ከአለቃ ተገኝና ከየኔታ ንጉሤ የዜማ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል::
   ሁለተኛ በ1936 ዓ.ም በሥሬ መድሐኔዓለም ዝነኛና ታዋቂ ከሆኑት ከታላቁ ሊቅ አለቃ ጥበቡ ገሜ ዘንድ ቅኔን ከነ አገባቡ ቀጽለዋል
   ሶስተኛ በ1937 ዓ.ም ወደ ጎንደር በመሄድ በእስቴ ወረዳ ልዩ ስሙ መካነ ኢየሱስ ከሚባለው ደብር ከመምህር ጥበቡ ድጓና ጾመ ድጓን ለሁለተኛ ጊዜ ተምረዋል እንዲሁም በዚሁ ደብር ከላይ በተጠቀሱት መምህር ዝማሬና መዋስዕትን በሚገባ ተምረዋል ::
አራተኛ በ1940 ዓ.ም በዚያው በጎንደር ቆላማ አካባቢ ወደ ሆነው ወደ መልዛ በመውረድ የተማሩትን እያስተማሩ ለድጓና ጾመ ድጓ ጽሑፍ የሚሆናቸውን ብርሃና በማውጣት ቆይተዋል::
  አምስተኛ በ1945 ዓ.ም የድጓ ማስመስከሪያ ወደ ሆነው ወደ ቤተልሔም ገብተው ለሶስት ዓመታት ድጓና ጾመ ድጓውን ጽፈውና አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀዋል
 ስድስተኛ ወደ ጎንደር ከተማ በመሄድ ደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በዓታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ከሆኑት ከአለቃ ክፍሌ ዘንድ አቋቋም በሚገባ ተምረዋል የአቋቋም ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የትምህርት ቤት ጓደኛቸውና የመንፈስ ቅዱስ ወንድማቸው ከሆኑት ከርዕሰ ደብር መዝገቡ ኃብተ ገብርኤል ጋር በመሆን ለትምህርት ከሄዱበት ከጎንደር ክፍለ ሀገር ለቀው በአውሮፕላን የኢትዮጲያ መናገሻ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥተው በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በድጓ መምህርነት እያስተማሩ ሳለ በወቅቱ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፖትርያርክ በሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መልካም ፈቃድ ለድጓ መምህርነት ተመርጠው የትውልድ ቦታቸው ወደ ሆነው ወደ ታላቁ ገዳም ወደ ደብረ ሊባኖስ በ1949 ዓ.ም ተመድበው የማስተማር ሥራቸውን ጀምረዋል::
    አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል ከመምህርነት ሥራቸው በተጨማሪ ባላቸው ጊዜ የሐዲስ መምህር ከሆኑት ከመምህር ፍስሐ ኪዳንና ትምህርተ ኅቡዓት አንድምታ ትርጓሜን ቀጽለዋል በመቀጠልም ከየኔታ አንድርጌ ውዳሴ ምርያምና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜን አሂደዋል::
         አለቃ መርዓ ሣህለ ሚካኤል ዘነሣዕክሙ በፀጋ  በፀጋ ሀቡ የሚለውን አምላካዊ ቃል አብነት በማድረግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያለዋጋ ከመላው ኢትዮጲያ የሚመጡ ደቀ መዛሙርትን በዕውቀት በመቅረጽ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን አያሌ ሊቃውንትን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አፍርተዋል::
   አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤልን ከመምህራን ልዩ የሚያደርጋቸው ለተማሪዎቻቸው ከዜማ ትምህርት በተጨማሪ ፍትሐ ነገሥት መጽሐ መነኮሳት የዓለም ታሪክን በማገናዘብ የዓለም ታሪክን በማስነበብ አዕምሮአቸው እንዲበለጽግ በማድረግ እጅግ የላቀ ተሰጥኦ ነበራቸው
  እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ወንዶችና ሴቶች ህፃናትን ወደ ገዳሙ የሚመጡ መናንያንን ሴት መነኮሳትን የግዕዝ ንባብና ሥነ ጽሑፍ እንዲያውቁ በማድረግ ትውልድ የሚያኮራ ታላቅ ሥራ ሠርተዋል::
ታላቁ ሊቅ አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል በልዩነት ከተሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ሐብት የሚያስደንቀወ የዜማ ትምህርት ለመማር ከሳቸው ዘንድ የሚመጡ ደቀ መዛሙርት ሁሉ በአዕምሮ የበለፀጉ ማስተዋልና በዕውቀት እጅግ የተካኑ መሆናቸው የእሳቸውን የመንፈስ ቅዱስ ልዩ ስጦታ መሆኑን ይገልጻል
     ሥልጣነ ክህነትን በተመለከተ አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል የዲቁና ማዕረግን ከብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ግብጻዊ የቅድስና ማዕረግን ከብፁዕ አቡነ ሣዊሮስ ኢትዮጲያዊ ተቀብለዋል::ሥርዓተ ምንኩስናም በዚሁ ታላቅ ገዳም ፈጽመዋል::
      አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ በዕልቅና ከ1977 ዓ.ም እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ሊቃውንቱን በቅንነትና በመንፈሳዊነት ሲመሩ ቆይተዋል::
   አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል በክብር ላይ ክብር በትሩፋት ላይ ትሩፋት ለመጨመር ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በመሄድ ታሪካዊ ቦታዎችን ጎብኝተዋል::
አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል እንደ ኢዮብ በትዕግሥት እንደ አብርሃም በልግስና እንደ አባታቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተጋድሎና በትሩፋት በንጽሕና በቅድስና ምትክ የሌላቸውና አባታቸው ቅዱስ ያሬድ ዘኮኖ ልቡ ሠረገላ ለጸሎት ብፁዕ ውእቱ ያለው ቃል የተፈጸመላቸው የምንመካባቸው አባታችን ነበሩ ምንም እንኳን ለደቀ መዛሙርቶቻቸው ብርሃን ለዚህ ታላቅ ገዳም ዓምድ ቢሆኑም ለሰው ልጆች ሁሉ የማይቀር የሞት ፅዋ ለሳቸውም የማይቀር በመሆኑ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አንሰ በድርየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ ሰለጥኩ እንከሰ ጽኑሕ ሊተ አክሊል ዘየአስየኒ መኮንነ ጽድቅ ብለው ለ60 ዘመናት እስትንፋሳቸው እስከ ተቋረጠችበት ዕለት ድረስ ከደቀ መዛርቶቻቸውና ከወንበራቸው ሳይለዩ ግንቦት7 ቀን 2007 ዓ.ም በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተው የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አበው መነኮሳት ሊቃውንት ደቀ መዛሙርቶቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም በታላቁ ደብረ ሊባኖስ በክብር ተፈጽሟል::
    ለደቀ መዛሙርቶቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እየተመኘን ለሁላችንም በረከታቸውና ረድኤታቸው አይለየን በማለት እንሰናበታቸዋለን::




2015 ሜይ 15, ዓርብ

ሰበር-ዜና የታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም የድጓው ሊቅ አለቃ መርዓዊ /የኔታ መኮንን አረፉ



ነገ ወደ መንገድ እሄዳለሁ ውዳሴ ማርያም እንዳታስታጉሉ፡፡

የኔታ መርዊ ሐሙስ ማታ ተማዎቻቸውን ካስተማሩ በኋላ  ከተናገሩት 

         
                                                                     
ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሲነሳ አብረው የሚታወሱ ለረጅም ዘመናት ድጓ በማስተማር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን የፈሩ በምናኔያቸው ፤በማስተማር ብቃታቸው፡ በመኅሌት ቁመት ድካም የማያውቃቸው አለቃ መርዓዊ ዛሬ ግንቦት 7 /2007 ዓ.ም ማረፋችው ተሰማ፡፤ ይህ ዜና እንደተሰማ በተለይ በ አዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት በማገልገል ላዪ የሚገኙ ሊቃውንት ልጆቻቸው ዛሬ ከሰዓት በኋላ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ኢየተመሙ ይገኛሉ፡፡አለቃ መርዓዊ ከገዳሙ ህልውና ቀጥሎ በስስት ዓይን የሚታዩ ትሁት ፤መናኝ፤ ፤ ማኅሌታዊ፤ መምህር ነበሩ ፡፡
ማሳሰቢ
ይህን አሳዛኘ ዜና የሰማሁት  ለአገልግሎት ኮቦልቻ  እንደደረስኩ ነውና  ሙሉ ዝርዝር መረጃዎችን አጠናክረን እናደርሳለን፡፡
የሊቁ አባታችንን ነፍስ ከቅዱሳን ሊቃውንት አጠገብ ያኑርልን፡፡

2015 ሜይ 6, ረቡዕ

ሰበር ዜና – ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቢያ ለተሠዉት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የሰማዕትነት ሥያሜ ሰጠ


ethiopian Orthodox martyrs
  • ዝርዝር መግለጫው በይፋ የሚወጣው በቀጣዩ የጥቅምት ምልዓተ ጉባኤ ነው
  • በስደት ያሉ የሚመለሱበትና በኑሯቸው የሚቋቋሙበት ጠንካራ ውሳኔ ተወስኗል
  • ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ጋራ የሚሠራ ኮሚቴ ይቋቋማል
በሊቢያ፣ ‹‹ሃይማኖታችን አንክድም፤ ማዕተባችንን አንበጥስም›› ብለው በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነታቸው በመጽናታቸው፣ ራሱንእስላማዊ መንግሥት(ISIS) ብሎ በሚጠራው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን በሰይፍ ተቀልተው እና በጥይት ተደብድበው የተገደሉት ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች የሰማዕትነት ሥያሜ እንዲሰጣቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወሰነ፡፡
የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአረመኔያዊ አኳኋን የተገደሉት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ሰማዕት እንዲባሉ የወሰነው፣ በዛሬው ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የመጀመሪያ ቀን የቀትር በኋላ ውሎው በጉዳዩ ላይ በስፋት ከመከረበት በኋላ ነው፡፡
በሊቢያ የሜዲትራንያን ባሕር ዳርቻ እና በረሓ በወሩ መጀመሪያ ስለ እምነታቸው መሠዋታቸው የታወቁት ኦርቶዶክሳውያን፣ ‹‹ወኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት = እስከ ሞት ድረስ የታመንኽ ኹን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለኹ›› /ራእይ ፪፥፲/ ያለውን የጌታችን ቃል ጠብቀው ሃይማኖታችንን አንክድም በማለት የሃይማኖት ሰማዕትነትን የተቀበሉ የሃይማኖት መስተጋድላን እንደኾኑ የግድያው ዜና በተሰማበት ማግሥት በቋሚ ሲኖዶስ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. መግለጫው በአይ.ኤስ አሸባሪ ቡድን በግፍ የተገደሉት ልጆቻችን ቤተ ሰዎች ኹሉ የሰማዕታቱን ስመ ክርስትና፣ ሥዕለ ገጽ(ፎቶ) እና ሙሉ አድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተቻለ ፍጥነት እንዲያቀርቡ አሳስቦ ነበር፡፡
በሃይማኖታቸው ምክንያት ለተሠዉት ክርስቲያኖች ሊሰጥ የሚገባው የሰማዕትነት ክብር(ማዕርግ) መኾኑን በውሳኔው ያመለከተው ምልዓተ ጉባኤው፣ ስለ ሥያሜው እንዲኹም እያንዳንዳቸው ስለተሠየሙበት የሰማዕትነት ማዕርግ እና ክብር ዝርዝር መግለጫ የሚሰጠው በመጪው ዓመት ጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንደሚኾን በውሳኔው ማመልከቱ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ምልዓተ ጉባኤው በዛሬው ውሎው፣ በስደት ያሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እና የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሊቢያን ጨምሮ ለጥቃት ከተጋለጡባቸው አካባቢዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ ግፊት ከማሳደር ጀምሮ ተመላሾችን በማቋቋም ረገድፋይናንሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቡናዊ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚኖርባት የሚገልጽ ጠንካራ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል፡፡
ውሳኔውን የሚያስፈጽም ራሱን የቻለ አካል የሚቋቋም ሲኾን፣ ይኸው አካል ተግባሩን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ጋራ በመተባበር እንደሚፈጽም ተጠቅሷል፡፡ የስደተኞች እና ተመላሾች ጉዳይን በመምሪያ ደረጃ አቋቁሞ በቀጥተኛ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠራው ኮሚሽኑ፣ ቀደም ሲል የገንዘብ አስተዋፅኦ የሚሰበሰብበት አካውንት በመክፈት ገባሬ ሠናይ አካላትን ማነጋገር መጀመሩ ተገልጧል፡፡

2015 ሜይ 2, ቅዳሜ

‹‹ምንም ብትሉ÷ ምንም ብትሉ የማይከፈል ሕዝብ ነው፤… መሸበር አያስፈልግም›› /የበዓለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ውርስ/


Historical+account+of+His+Grace+Abune+Gregory+II-p2-3በረከታቸው ይደረብንና የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ (1932 – 1982 ዓ.ም.) ሚያዝያ 23 ቀን 1982 ዓ.ም. በሻሸመኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሰጡት ትምህርት
ጀግና በጦር ሜዳ ይወለዳል፤ በክፉ ቀን ከብዙ ፈሪዎች ከብዙም ጀግኖች መካከል ቅ/ጊዮርጊስ ተገኘ
የተወደዳችኹ ምእመናን፤ በዚኽች በበዓለ ኀምሳ ውስጥ፣ ዛሬ ተጨማሪ በዓል የምናከብረው የታላቁን ሰማዕት የቅዱስ ጊዮርጊስን የምስክርነት በዓል ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው፡፡ በእርግጥ ያ ዘመን ለክርስቲያኖች ጥሩ ዘመን አልነበረም፤ ያ ጊዜ ለክርስቲያኖች ጥሩ ጊዜ አልነበረም፡፡ ክርስቲያኖች የሚፈተኑበት ጊዜ ስለነበር ይኼ ታላቅ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚያ ጊዜ ተገኘ፡፡ ጀግና በጦር ሜዳ ይወለዳል እንደሚባለው ኹሉ፤ ክፉ ቀን ያስተዛዝባል፤ ክፉ ቀን ደግሞ ብዙ ጀግኖች ይከሠቱበታል፤ ፈሪዎች የሚታወቁት ጀግኖችም የሚታወቁት በክፉ ጊዜ ነው፡፡ በደኅና ቀንማ ኹሉም ጀግና ነው፤ ኹሉም ልባም ነው፡፡ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚያ በክፉ ቀን ከብዙ ፈሪዎች መካከል ከብዙም ጀግኖች መካከል እርሱ ተገኘ፡፡
የሊቀ ሰማዕቱ የፈተና ንብርብር፣ የድል እና የጽድቅ አክሊል
St-George
ቅዱስ ጊዮርጊስን ይከራከሩት የነበሩት ሰዎች፣ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስቸግሩት የነበሩት ሰዎች ተራ ሰዎች አልነበሩም፡፡ የታናሽ እስያን በትረ መንግሥት የጨበጡ ንጉሣውያን ቤተ ሰዎች ነበሩ፤ የዳክዮስ ቤተ ሰዎች ነበሩ፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያ የተፈተነው፣ ከንጉሡ ልጆች አንዲቱን ልዕልት እንዲያገባ ነበር፡፡ መልከ ቀና ስለነበር፣ ዘረ ጥሩ ስለነበር ተመርጦ ሃይማኖቱን እንዲክድ እና ለጣዖት እንዲሰግድ ወዲያውም ደግሞ የንጉሡን የመጀመሪያ ልጅ ልዕልቲቱን እንዲያገባ ነበር፡፡ በፍትወት ነበር የተፈተነው ማለት ነው፡፡ እንግዲኽ በዚኽ ፈተና ውስጥ ብዙ ብዙ ነገሮች አሉ÷ ፍትወት አለ፤ ገንዘብ አለ፤ ሥልጣን አለ፤ የፈተና ንብርብር ነው የደረሰበት ጊዮርጊስ፡፡ ነገር ግን ጊዮርጊስ÷ እንዳልኋችኹ ጀግና ሰው ስለነበር ለዳክዮስ እና ለቤተ መንግሥቱ አልተንበረከከም፤ አሸነፈ! እና በእግዚአብሔር ዘንድ በ፳፫ ዓመቱ÷ ዛሬ ወጣቶች ኃጢአት ለመሥራት ልምምድ በሚያደርጉበት ጊዜ እርሱ አሸንፎ የድል እና የጽድቅ አክሊል ተሸለመ፡፡ ይኼን ነው እንግዲኽ ዛሬ ክርስቲያኖች የሚያከብሩት፡፡ ክፉውን ነገር ኹሉ ያሸነፈ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማት የሚያገኝበት ዕለት ነው፡፡ የሽልማት ቀን ማለት ነው ዛሬ፡፡
በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ አገሩ የት ነው? ቋንቋው ምንድን ነው? አይባልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታገናኝ ናት፤ ሕዝብን እና ሕዝብን የምታዋሕድ አንድ የምታደርግ ናት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ስለኾነች የትም ይወለድ የትም የእግዚአብሔር ሰው መኾኑን ተቀብላ ታከብራለች፤ ሌሎችም እንደዚኹ፡፡ ለምሳሌ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ ሲኾኑ በግብጽ ብትሔዱ ዛሬ በእስክንድርያ በካይሮ በሌሎችም ቦታዎች የተክለ ሃይማኖት መቅደስ የሌለበት፣ የተክለ ሃይማኖት ሥዕል የሌለበት አታገኙም፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ አገሩ የት ነው? ቋንቋው ምንድን ነው? አይባልም፡፡ የእግዚአብሔር ሰው መኾኑ ብቻ ነው የሚታየው፡፡ ይኼ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ኹሉ የተወረሰ ሐዋርያዊ ውርስ ነው፡፡
ሐዋርያትም መጀመሪያ ብዙ የታገሉት እስራኤልን እና አሕዛብን ለማገናኘት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታገናኝ ናት፤ ሕዝብን እና ሕዝብን የምታዋሕድ አንድ የምታደርግ ናት፡፡ ስለዚኽ ነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳንን ማክበር ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ ሕዝብ ያደረገችው፡፡ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብ ሳትለይ፤ አኹን በዛሬው ቀን ከቀይ ባሕር እስከ ጋምቤላ ከዚያም እስከ ዘይላ ድረስ ብትሔዱ÷ የጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ባለበት ኹሉ በዓሉ ይከበራል፡፡ አዎ! ጦርነትም ይኹን ረኀብም ይኹን ይከበራል፤ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡ ጸሎታችንም መሥዋዕታችንም÷ በዚኽም ያለነው በዚያም ያለነው አብሮ ወደ እግዚአብሔር ይሔዳል፡፡
ለሐዋርያት ትምህርት ምልክቱ መለያያ ምክንያት እየፈጠሩ ሰውን እንዲጠፋ አለማድረግ ነው
ዛሬ ግን የሚመጡ እምነቶች ሰውን እና ሰውን የሚለያዩ ናቸው፡፡ ዛሬ እምነቶች ነን ብለው የሚመጡት እናትን እና ልጅን፣ አባትን እና ልጅን÷ ጎጥን፣ ጎሳን፣ ጎራን የሚለዩ ናቸው፡፡ ስለዚኽ ነው እኛ፣ እነዚኽ እንደ ሰኔ ሰርዶ ራሳቸውን ብቅ ብቅ ያደረጉትን ኹሉ የማንቀበላቸው የሐዋርያትን ትምህርት ስለማያስተምሩ ነው፡፡ ለሐዋርያት ትምህርት ምልክቱ ምንድን ነው? ሕዝብን እና ሕዝብን አንድ ማድረግ ነው፤ የተለያዩትን አንድ ማድረግ ነው፤ መለያያ ምክንያት እየፈጠሩ ሰውን እንዲጠፋ አለማድረግ ነው፡፡
ምንም ብትሉ÷ ምንም ብትሉ የማይከፈል ሕዝብ ነው፤… መሸበር አያስፈልግም
አኹን የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም በምን ሳንለያይ ባለፈው የፋሲካን በዓል አክበረናል፡፡ የትም ቦታ ብትሔዱ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ቦታ፤ እዚኽ ቤተ ክርስቲያን ያሉ ሰዎች ዘራቸው ምንድን ነው? ቋንቋቸው ምንድን ነው? ሳይባል ከአሜሪካ ጀምሮ እስከዚኽ ድረስ ባለው በአንድ ቀን ይከበራል፡፡ በሎንዶን የሚኖሩ እንዲያውም የሎንዶን ዜጎች የኾኑ የእኛ እምነት ተከታዮች የስቅለት ዕለት እኛ ጋራ ሊሰግዱ መጡ፤ ከሎንዶን ድረስ፡፡ ከስቅለት ቀደም ብለው መጡ፤ መንበረ ፓትርያርኩ ማረፊያ ተሰጣቸው፤ እዚያ ቆይተው ከእኛ ጋራ ጾሙንም ስግደቱንም አክፍሎቱንም አይተው ተሳትፈው ትንሣኤውን አክብረው በሳምንቱ ወደ አገራቸው ሔዱ፡፡ እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ከኹሉ በፊት የምትጥረው አንድ ሕዝብ ለማድረግ ነው፡፡ አኹን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው፤ አንድ ሕዝብ ነው፤ ምንም ብትሉ÷ ምንም ብትሉ የማይከፈል ሕዝብ ነው፡፡ ደኅና አድርጋ መሥርታዋለች ቤተ ክርስቲያኒቱ፡፡ የአባቶቻችንን ነፍስ ይማርና ደኅና አድርገው መሥርተውት አንድ ኾኗል፡፡ ይኼን እንዳታፈርሱ ነው ቤተ ክርስቲያን አኹን የምታስተምረው፤ በየጊዜው የምትሰበሰበው ይኽን ለማስተማር ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ያደረገችውንና የምታደርገውን አስተዋፅኦ እንደ ቀላል በመቁጠር፣ በቤተ ክርስቲያን መሰብሰባችንንም እንደ ሥራ ፈትነት በመቁጠር ብዙ ተችተውናል፡፡ አዎ÷ እንደማያልፍ የለም ትችቱም አልፏል፤ ይቀጥልም ይኾናል፡፡ ታዲያ መሸበር አያስፈልግም፡፡ የምንሠራውን እንደማናውቅ ኹሉ መሸበር እና በምንሠራው ሥራ መፍራትም አያስፈልግም፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ብቻ ሳይኾን በየሔደችበት በውጭ አገርም የምታስተምረው ሕዝብ እና ሕዝብ እንዲገናኝ፣ እንዲተባበር፣ እንዲተዛዘን፣ አንድ እንዲኾን፣ መለያያ ምልክት እንዲጠፋ ነው፡፡ የጌታችንም ትምህርት ይኼ ነበር÷ ሕዝብን እና አሕዛብን አንድ ለማድረግ፤ ኹሉም የብርሃን ልጅ እንዲኾን ነበር የጌታችን ትምህርቱ፡፡ እም ዕቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ ብርሃናተ ዘኢትሐጽፍ ተንሥኣ ለነ = ከዚያ ከሚያቃጥለው ከነዳጁ እሳት ያወጣን የብርሃናት ጌታ ብርሃናትን የሚለብስ እርሱ ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ የተነሣልን እኛ አንድ እንድንኾን ነው፡፡ እርስ በርሳችን ብቻ ሳይኾን ደግሞ ከእርሱ ጋራም አንድ እንድንኾን ነው፡፡ ከመ ይኩኑ አሐደ ብነ ከማነ = እኛ እርስ በርሳችን ያለንን አንድነት እንድናጠናክር እና ከእግዚአብሔር ጋራ ደግሞ ያለንን ግንኙነት ደግሞ እንድናጠናክር ነው፡፡
ሰው ፍላጎቱን ካላሸነፈ የእግዚአብሔር ሰው ለመኾን አይችልም
ምናልባት እዚኽ መካከል ኢየሩሳሌም የሔዳችኹ ካላችኹ ልዳን አይታችኁት ይኾናል÷ የጊዮርጊስን መቃብር፤ እኔ ግን ሳይገባኝ ዕድል ገጥሞኝ እመቃብሩ ላይ ተንከባልዬበታለኹ፤ደስ ብሎኝ፤ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ ቅዱስ ነው፤ ቅድስናውም ደግሞ ለትውልድ ኹሉ ምሳሌ የሚኾን ነው፡፡ ማን ነው ወጣት ዛሬ ለክፉ ነገር የማይንበረከክ ማን ነው? ብዙ ሱሰኞች ነን እኛ÷ ብዙ ሱስ ያጠቃናል፡፡ ከጊዮርጊስ ጋራ እንደ ጊዮርጊስ የምናያቸው ብዙ ቅዱሳን አሉ÷ እነ ቂርቆስ አሉ፤ እነ ሠለስቱ ደቂቅ አሉ፤ ፍላጎታቸውን ያሸነፉ፡፡ ሰው ፍላጎቱን ካላሸነፈ የእግዚአብሔር ሰው ለመኾን አይችልም፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ለመኾን የሚችለው ፍላጎቱን ሲያሸንፍ ነው፡፡ ከወንድሙም ጋራ የሚያጣላው ከእግዚአብሔርም ጋራ የሚያጣላው የፍላጎቱ ክብደት ነው፡፡ ፍላጎቱ እየናረ ሲሔድ እየከበደ ሲሔድ የሰውን ያስመኘዋል፡፡ ያልተሰጠውን ይመኛል፡፡ ያ ነው እንግዲኽ ከጎረቤቱም ከእግዚአብሔርም የሚያጣላው፡፡
ትምህርት ሲባል…

ziway-abune-gorgorios1

እንግዲኽ በዚኽች ዕለት በእውነቱ ከእኔ ይልቅ ቀደም ብሎ ትምህርት ሰምታችኋል፤ መዝሙሮችንም ሰምታችኋል፡፡ አኹን እነዚኽ ልጆች እንዲኹ በቀላሉ የተገኙ አይደሉም፡፡ ታዲያ ከመዝሙሩ ጋራ ደግሞ ሃይማኖታቸውን ሥነ ምግባራቸውን እንዲማሩ ያስፈልጋል፡፡ ልጆቻችኹን ይዛችኹ ወደ ቤተ ክርስቲያን ኑ÷ ብቻችኹን አትምጡ፡፡ ብቻችኹን ከመጣችኹ ልጆቻችኹ ወደ ሌላ ይሔዳሉ፡፡ እናንተ እዚኽ መጥታችኹ የምትሠሩትን አያውቁም፤ ወራሾቻችኹም አይኾኑም፡፡ ስለዚኽ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችኹን ይዛችኹ ኑ፡፡ አሳዩአቸው÷ ሥዕሉን ይሳሙ፤ ቅዳሴ ጠበል ይጠጡ፤ በእምነቱ አሻሹአቸው፤ መስቀል እንዲስሙ አስተምሯቸው፤ ዕጣኑን ያሽትቱ የሚታጠነውን፤ ሥጋ ወደሙን ይቀበሉ፤ ቃጭሉን ይስሙ፤ ደወሉ ሲደወል ይስሙ፤ ቄሳቸው ማን እንደ ኾነ፣ ቤተ ክርስቲያናቸው ምን እንደ ኾነች፣ በውስጥዋ ምን ምን እንደሚሠራ ያጥኑ፤ ይማሩ፤ ወደ ሰንበቴውም ስትገቡ ይዛችኋቸው ግቡ ወደ ሰንበቴው፤ ብርሌአችኹን ይዘው ይከተሉ፤ ወደ ማኅበርም ስትሔዱ ይዛችኋቸው ሒዱ፤ ቆሎውን ተሸክመው ይምጡ፤ ይማሩ፤ እነርሱም ነገ ይኼን እንዲወርሱ÷ የነገ ባለአደራዎች መኾናቸውን እንዲያውቁ፡፡ እንዲያው ዝም ብለን ብቻ ትምህርት ሲባል ሌላ ነገር እየመሰለን ነው እንጂ ትምህርቱን እኮ እናቶቻችን አባቶቻችን አስቀምጠውልናል፡፡ ያን መውረስ ነው ያቃተን እንጂ እነርሱ አዘጋጅተው አስቀምጠውልናል፡፡ ሰንበቴው፣ ዝክሩ፣ ማኅበሩ፣ በቅዱሳን ስም በበዓል መሰብሰቡ፣ ማስቀደሱ፣ መቁረቡ፣ ቅዳሴ ጠበል መጠጣቱ፣ መስቀል መሳለሙ፣ ሥዕል መሳለሙ ይኽን ኹሉ አስቀምጠውልናል፡፡ ሌላ ምንም አዲስ ትምህርት እኮ አያስፈልገንም ነበር፡፡
የትውልድ አደራ
መመካት የሚገባን ቢኾን ኖሮ መመካት የሚገባን ሰዎች ነን እኮ እኛ፡፡ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር መመካት እንጂ በራስ መመካት አይገባም፡፡ የሚገባ ቢኾን እኛ ከዓለም ኹሉ በበለጠ መመካት ይገባን ነበር፤ ምክንያቱም አባቶቻችን እናቶቻችን ሥርዐታችንን እምነታችንን ኹሉ ሰፍረው ቆጥረው ያስረከቡን ስለኾነ ነው፡፡
እና ይኽ ትውልድ ይህን እንዳያጣ ነው አደራ የምንለው፤ ይኽ ትውልድ ይህን ከቀበረ በኋላ ይህን ካጠፋ በኋላ እንደገና ወደ ቤተ መዘክር እንዳይሔድ ነው አደራ የምንለው÷ ሃይማኖቱን ፍለጋ ታሪኩን ፍለጋ፡፡
አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይጠብቃችኹ፤
አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያበርክታችኹ፤
አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያክብራችኹ፤
በአገልግሎቱ የተሳተፋችኹትን፣ ቁማችኹ ያስቀደሳችኹትን፣ ትምህርቱን የሰማችኹትን፣ ልቡናችኹን ለእግዚአብሔር የሰጣችኹትን ኹሉ እግዚአብሔር በበረከት ያትረፍርፋችኹ፡፡ አቡነ ዘበሰማያት፡፡

2015 ኤፕሪል 25, ቅዳሜ

ቀጣይ ሥራዎች ምን ሊሆን እንደሚገባ ብንወያይ


   
30 ኢትዮጵያውያን በሊብያ  ሰማእትነትን  ተቀበሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አዘነ . አለቀሰ ዓለም በሙሉ የሃዘን መግለጫ ሰጠ በጣም ግሩም ነው ፡፡ ነገር ግን ቀጣዩ ሥራችን የሚሆነው ምንድነው ?
ቅዱስ  ሲኖዶስ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን  በሚፈቅደው  መልኩ የሚወሰነውን  ውሳኔ ለዓለም እንደሚያሳውቁ ቅዱስ ፓትርያርኩ ባለፈው ገልጠዋል  ይሁን እንጂ
v  .     የተሰውትን 30 ኢትዮጵያውያንን  ሙሉ መረጃ  አሰባስቦ  ለቅዱስ  ሲኖዶስ ማቅረብ  የሚችል ጊዜያዊ  ኮሚት  ቤተክርስቲያናችን ማቋቋም ብትችልና ኮሚቴው መረጃዎችን አጠናክሮ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው  ቢያቀርብየሰማእታቱ  ፎቶ ሌሎችም መረጃዎች  በዚያ መቀመጥ ቢችል ደብሩ ወደፊትም በተመሳሳይ መልኩ ሰማእትነት ለተቀበሉት ኢትዮጵያን ብቻ ቢሆን /አውደ ሰማእታት ቢሆን/
v  አሁን በሊብያ በሕይወት ያሉትን በመርዳት ያሉበትን ሁኔታ በመከታተል የሚያስፈልገውን ሁሉ ከሚመለከተው ጋር ሆኖ የመርዳቱንም ነገር ቢታሰብበት
በአጠቃላይ ቤተክርስቲያቲ ለምትወስነው ቀጣይ ሥራዎች ግብአት ይሆን ዘንድ   ሀሳብ ቢሰጥ!!



















                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...