2015 ጁላይ 9, ሐሙስ

ሕጻናት በስደት ሀገር .............



GA 15 5


የሰው ልጅ በተለያየ ምክንያት ከአንዱ ሀገር ወደ  አንዱ ሀገር ይዘዋወራል፡ ለትምህርት ፡ለኑሮ ለመሳሰሉት  ሁሉ ይሰደዳል ከዚሁ ጋር ትዳር መያዝ ልጅ መውለድ እይቀሬ ነው ይልቁንም ለሕጻናት መብት ፡ለልጆች ትምህርት ወዘተ የተሻለ ነውና / ተብሎ ስለሚታሰብ ቤተሰብእ፡ያለሐሳብ ልጅ ወልዶ ለመኖር ይወስናል፡፡ እንደ የሀገሩም ሕግ በተለይ የሕጻናት እንክብካቤ ቁጥጥርም በሉት ከባድ ነው ፡፡በየጊዜው ቁመታቸው፡ ክብደታቸው፡ የጭንቅላታቸሀው እድገት ፡ ጸጉራቸው ፡ጥርሳቸው ሁሉ ሳይቀር ሁል ጊዜ በህክምና ባለሙያ ይታያል ፡ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንት ቁጥጥሩ  የሀገሪቱ መንግስት ነው ወላጆች ስለ ልጆቻቸው መናግርና ውሳኔ ማሳለፍ አይችሉም በዚህ ምክንያት  ባህላቸው ሃይማኖታቸው ሥርዓተ ቤተክርስቲያናቸው ቛንቛቸው ሁሉ እየጠፋ ነው  ስለዚህ በስደት ሀገር ስለሕጻናት ጠበቅ ጠለቅ ያለ ሀሳብ ማሰብ ማቀድ ያስፈልጋል  በውጪ ሀገር ያለች ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን በዋጀ መልኩ የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት በመሰለ መልኩ መንፈሳዊ ሥርዓተ ትምህርት በፍጥነት ማዘጋጀት ያስፈልጋል ይህ ካልሆነ በስደት ያሉት ሕጻናት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሀገራቸውን ሃይማኖታቸውን….. ያጣሉ ለዚሁ ጥሩ ጅምር ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካው ማዕከል የጀመረው አመርቂ ጅምር ይበል የሚያሰኝ ነው ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓው ማዕከልም በፍራንክፈርት ከተማ ጀርመን የ፲፭ኛው ዓመት ጠቅላላ ጉባዔውን ባደረገበት ውቅት በቀጣዩ ዓመት ከአጸደቀው እቅዶች መካከል አንዱ «በውጭው ዓለም የሚገኙ ሕጻናትን በቤተ ክርስቲያን በተቀናጀ መልኩ እንዴት እናስተምር?  በሚል ያቀደው እቅድ ሊበረታታና ሁሉም ሰው ሊረባረብበት ይገባል በተለይ በውጭ ሀገር ያሉ ነዋሪዎች ልጆቻቸው ራሳቸው ልጆች  ኢትዮጵያውያን ሆነው ሃይማኖታቸውን  በጎ ባህላቸውን ጠብቀው ይቀጥሉ ዘንድ መረባረብ ይገባል ያለበለዚያ ሕጻናት ከሃይማኖታቸው፡ ከመልካም ባህላቸው፡ ከሥርዓተ ቤተክርስቲያናቸው እንዳይሰደዱ ሊታሰብበት ይገባል።

የአውሮፓ ማዕከል ፲፭ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በፍራንክፈርት ፥ ጀርመን አካሄደ

አትም
በብዙኀን መገናኛ እና ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል
ሐምሌ 02 ቀን 2007 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል አስራ አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በጀርመን ሀገር በፍራንክፈርት ከተማ በምትገኘው በደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከሰኔ ፳፮ እስከ ፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. አካሄደ።
GA 15 1
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ሙሴ የደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አኅጉረ ስብከት ዋና ጸሐፊ፣ የዋናው ማዕከል እና የአሜሪካ ማዕከል ተወካዮች እንዲሁም በጀርመን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የደብር አስተዳዳሪዎች እና ከመላው አውሮፓ የተሰባሰቡ ከ፺ በላይ የሚሆኑ የማኅበሩ አባላት ተገኝተዋል።
ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ቀትር ጀምሮ እንግዶች ወደ ጉባኤው ቦታ ፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የደረሱ ሲሆን ጉባኤው ሠርክ ላይ በአባቶች መሪነት በጸሎተ ኪዳን ተጀምሮ በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል። በመቀጠልም የእራት መስተንግዶ በጀርመን ቀጣና ማዕከል ከተደረገ በኋላ በጠቅላላ ጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ደረጀ ወርቁ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ተላልፎ በመጨረሻም የአባላት የእርስ በርስ የትውውቅ መርሐ ግብር ከተከናወነ በኋላ የእለቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል።
ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጠዋት ጸሎተ ወንጌል (ማቴ.፯ ፥ ፳፬) በብጹዕ አቡነ ሙሴ መሪነት ደርሶ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ «እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጅ የቱ ነው?» (ሉቃ.፲፭ ፥ ፲፩ - ፴፪) በሚል ርዕስ ትምህርት ሰጥተዋል። ቀጥሎም የማዕከሉ ሰብሳቢ ዲ/ን ሰሎሞን አስረስ ለተጋባዥ እንግዶች እና ለማዕከሉ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። የ፳፻፯ ዓ.ም. የማዕከሉ የአገልግሎት ክፍሎች እና የማዕከላት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማዕከሉ ሰብሳቢ የቀረበ ሲሆን ጉባኤው የሂሳብ፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽንን ዕቅድ ክንውን ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ በሪፖርቱ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል። ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ማብራሪያ እና ምላሽ ከሰጡ በኋላ አጠቃላይ ኃሳቦች በብጹዕ አቡነ ሙሴ እና በተጋበዙ እንግዶች ተሰጥተው ሪፖርቱን ጉባኤው አጽድቆታል።
GA 15 2
የደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከትን መልእክት ያስተላለፉት ዋና ጸሐፊው መጋቤ ኅሩይ ኤርምያስ ማዕከሉ ለሀገረ ስብከቱ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው ወደፊትም ከማዕከሉ ጋር አብሮ ለመሥራት ሀገረ ስብከቱ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል። «በማዕከሉ የተሠሩ ሥራዎችን በማየቴ ተደስቻለሁ፤ እኛ ያላየናቸውን የአገልግሎት ክፍተቶች በማየታችሁ ፣ በመሥራታችሁ እግዚአብሔር ይስጣችሁ » በማለት ዋና ጸሐፊው መልእክታቸውን ቋጭተዋል። ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሐ በበኩላቸው «ከዋክብት ሰማይን ፣ አበቦች ምድርን እንደሚያስጌጡ ሁሉ ፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ጌጦች ናቸው፤ እናንተም ለቤተ ክርስቲያን ጌጦች ናችሁ» በማለት ማኅበሩ በአገልግሎት እንዲተጋ አበረታትተዋል።
GA 15 4በመጨረሻም ብጹዕ አቡነ ሙሴ ባስተላለፉት መልእክት ማኅበሩ በተለይም ግቢ ጉባኤያትን በማስተማር እና የተዘጉ ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማስከፈት በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ብዙ ክፍተቶች ሸፍኗል። አሁንም ማኅበሩ ይህንን መልካም ሥራውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ሲሉ ብፁዕነታችው መልእክታቸውን ለጉባኤው አስተላልፈዋል። ወደፊትም ማዕከሉ ከሀገረ ስብከቱ እና ከአባቶች ጋር ከዚህ የበለጠ ተቀራርቦ እንዲሠራ በማለት መመሪያ ካስተላለፉ በኋላ የጠዋቱን መርሐ ግብር በጸሎት ዘግተዋል።
በእለቱ ከምሣ መስተንግዶ መልስ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ በጀርመን የካርልስሩኸ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ወረብና መዝሙር፣ በማዕከሉ አባላት ወረብ እንዲሁም በጀርመን የሙኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በሆኑት በሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሐ መዝሙር ቀርቧል። በዚሁ እለት ከሰዓት በኋላ ጉባኤው ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ የተወያየበት አንዱ ርዕሰ ጉዳይ «በውጭው ዓለም የሚገኙ ሕፃናትን በቤተ ክርስቲያን በተቀናጀ መልኩ እንዴት እናተምር?» የሚል ነው። በዚህም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ችግሮችን ፣ መፍትሔዎችን እና ተሞክሮዎችን የዳሰሰ ጥናት ለጉባኤው ቀርቧል። በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ዙርያ በተደረገው ውይይት ማኅበሩ ከዚህ በፊት የቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት መኖሩ ተወስቶ ወደፊት ግን በአዲሱ የውጭ ማዕከላት መዋቅር መሰረት ሕፃናት እና አዳጊ ወጣቶችን የማስተማር ሥራ እራሱን በቻለ «የተተኪ ትውልድ ሥልጠና» በሚባል ክፍል ተመስርቶ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት አፅንኦት ተሰጥቶበታል።
GA 15 3
ከዚህ በመቀጠልም «ሚዲያ ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት» በሚል ርዕስ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በርካታ ገንቢ ኃሳቦች ተሰጥተዋል።
በዚሁ እለት ምሽት ከእራት በኋላ ከዋናው ማዕከል ተወክለው በመጡት አቶ ፋንታሁን ዋቄ « የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እና ተግዳሮቶች » በሚል ርዕስ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ማብራሪያ በጽሑፉ አቅራቢ ተሰጥቶባቸዋል። የዕለቱ መርሐ ግብርም መንፈቀ ሌሊት ሲሆን ተፈጽሟል።
ጉባኤው እሑድ ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቅዳሴ በኋላ እኩለ ቀን ላይ ቀጥሎ የተሻሻለውን የውጭ ማዕከላት መመሪያና መዋቅር አተገባበርን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል። የማዕከሉ የአገልግሎት ክፍሎች እና የኦዲት እና ኢንስፔክሽን የመጪው ዘመን የ፳፻፰ ዓ.ም. ዕቅድ ቀርቧል። በእቅዱ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላቱ ማብራሪያ እና ምላሽ ከሰጡ በኋላ እቅዱ በጠቅላላ ጉባኤው ጸድቋል።
GA 15 5
በመቀጠልም ሕጻናት መዝሙር አቅርበው ፣ የሰሜን አሜሪካ ማዕከል ተወካይ ዲ/ን ብዙአየሁ ልመንህ የማዕከሉን መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የማዕከላቸውን ልምድ ለጉባኤው አካፍለዋል። እንዲሁም ሁለቱ ማዕከላት በጋራ ሊያገለግሉባቸው የሚችሉባቸውን የአገልግሎት ዘርፎች ለጉባኤው አቅርበዋል። የዋናው ማዕከል መልእክትም በተወካዩ በአቶ ፋንታሁን ዋቄ ለጉባኤው ቀርቧል።
በመጨረሻም የማዕከሉ ሰብሳቢ ዲ/ን ሰሎሞን አስረስ ለዚህ ጉባኤ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሲራክ ተድላ የፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ፣ ለቤተ ክርስቲያኗ ሰብካ ጉባኤ፣ አባታዊ ምክርና ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት ለጉባኤው ሞገስ ለሆኑት አባቶች ፣ ተወካይ በመላክ ልምዳቸውን እንድናገኝ ላደረገው የሰሜን አሜሪካ ማዕከል እንዲሁም ፲፭ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ላዘጋጁት የጀርመን ቀጣና ማዕከል አባላት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው፣ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተነሱና ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችን ለመተግበር ሁሉም አባላት እንዲተባበሩ ጥሪ በማስተላለፍ ፲፭ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ተጠናቋል። ቀጣዩን የማዕከሉን ፲፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለማዘጋጀት የዩኬና የኔዘርላንድ ማዕከላት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን የማዕከሉ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ወስኖ ለአባላት እንደሚገልጽ አሳውቋል።
በጉባኤው ማግስት ሰኞ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የተወሰኑት አባላት ከፍራንክፈርት የአንድ ሰዓት ገደማ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ እንጦስ ገዳም በመሄድ ጉብኝት አድርገዋል።

2015 ጁላይ 3, ዓርብ

ንዋዬ ቅዱሳቱ በባህር ማዶ





ፍራንክፈርት መሃል ከተማ አንድ ትልቅ ሙዚዬም አለ ቱሪስቶች ሁሉ ይጎበኙታልና እኛም ለመጎብነት ወደዛው አመራንና መጉብኘት ጀመርን አስተናጋጆቹ የጎብኞችን አያያዝ ተዉኝ  መጡብን ሳይሆን መጡልን እያሉ መሆኑን ከፊታቸው በትልልቅ የቁም ጽሁፍ ይነበባል መጎብኘት ስንጀምር ለብቻው አንድ ክፍል ውስጥ ትልልቅ የብራና መጻሕፍት፡ ጥንታውያን መስቀሎች፡ ጥንታውያን ቅዱሳት ሥዕላት በክብር ተይዘው አገኘናቸው  በልባችን .መቼ መጣችሁ? እንዴት መተጣችሁ? ማን አመጣችሁ?  ለምን መጣችሁ? ከመጣችሁ ስንት ዘመን ሆናችሁ? ሌሎች ጘደኞቻችሁስ ይመጡ ይሆን? ለመሆኑ እናተስ ወደ ሀገራችሁ ለመመለስ አስባችኋል? የሚለውን ጥያቄ ጠይቀን  መልስ ሳናገኝ ወጣን እላችኋለሁ እስቲ አናነተም በዚህ ጉዳይ ተነጋገሩና ከላይ የተጠየቁትን ጥያቄዎች መልስ ፈልጉ
ከፍራንክፈርት ጀርመን

2015 ጁን 29, ሰኞ

ክርስትናው እኛጋ ተግባሩ ግን…………………….


……….
ቦታው ሰሜን መዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት  ፊንላንድ ነው ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን  ሄልሲንኪ ከተማ   እሁድ ቅዳሜ ጉባኤ ነበረ የከተማዋን ፣ የሀገሩን ሁኔታ ስጠይቅ
1.      የሀገሩ ሕዝብ ሐሰት መናገር ጨርሶ አያውቅም አይሆንለትም
2.     ዕቃ ወድቆ ቢያገኝ በሚታይ ቦታ ያስቀምጣል እንጂ አይወስድም
3.     እናቶች ልጅ ይዘው ሲሄዱ የከተማው ባሶች፣ ቀላል ባቡሮቸ፣  ወዘተ …እንዲሁ ያለክፍያ ይወስዳሉ
4.     እናቶች ሲወልዱ እስከ ለሦስት ዓመት ያህል እንክብካቤ ይደረግላታል  ሌሎችም ምግባራትን እዚያ አገኘሁዋቸው  ምናለበት  ይህ ተግባር   ሃይማኖቱ ፣ሥርዓቱ፣ ሊቃውንቱ፣ ገዳማቱ፣ ካህናቱ፣ መነኮሳቱ፣ ቅዳሴው፣ ሳህታቱ፣ ማኅሌቱ፣ ባለበት በእኛው  ሀገር ቢተገበር ቀድሞ አበዊነ ሐዋርያት ያስተማሩት ከሃይማኖት በስተቀር ሁሉም አለ  ከእኛ ተገባሩ ተሰዶብናልና ወደ ሀገሩ ቢመለስልን ብዬ ተመኘቼ ነው፣

                         ከሄልሲንኪ ፊንላንድ



































2015 ጁን 28, እሑድ

እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለይ› የሚለውን በስዕል፣


ነገሩ እንዲህ ነው ሰኔ 17 2007 ዓ.ም ከምሽቱ 5 ሰዓት ተነስቼ በእኛው አውሮፕላን ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት ለአገልግሎት ተጉዤ ነበር እንደደረስኩም  ቀሲስ አብርሃምና ዶ/ር አንኬ ተቀበሉኝ ክብር ያድልልኝ እላለሁ ከትንሽ እረፍት ቀጥሎ ከ አንኬ ጋር  ከተማዋን ለማየት በወጣሁ ጊዜ ያየሁትን  ትልቅ ወንዝ ከተማዋን ሰንጥትቆ ያልፋል ይልልቅ መርከቦች ፣ ጅልባዎች  ይሄዱበታል መሸጋገሪያ ድልድዮቹ ላይ የሀገር ቁልፎች ተቆልፎበታል  ምሥጢሩ ምንድነው › ጠየቅሁ እጮኛሞች፣ የልብ ጉዋደኞች፣ ናቸው የሚቆልፉት መክፈቻውን ወሃው ውስጥ ይጥሉታ  ፣መክፈቻውን ሰዎች ስለማያገኙት አይከፍቱትምና አይለየን ፣ማለታቸው ነው አሉኝ  ተቆልፎአልና. እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለይ ያለውን በስዕል ፣ ተስሎ ተመለከትነው

                                ከፍራንክፈርት ጀርመን

2015 ጁን 24, ረቡዕ

ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም (ክፍል ኹለት)


በዲ/ን ዳንኤል ክብረት
(መዝረቅ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 16 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡             - በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ኹለተኛው በይሁዳ ነው!
ይሁዳ የኢየሩሳሌም አውራጃው ነው፡፡ የይሁዳ አውራጃ ዋና ከተማም ኢየሩሳሌም ነች፡፡ ከኢየሩሳሌም ይሁዳ ይከፋል፤ ከሰማርያ ግን ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ኢየሩሳሌም ዋና ከተማዋ ነች፣ ጌታም የተወለደው በይሁዳ አውራጃ በቤተ ልሔም ነው፡፡ የተሰቀለው፣ የሞተው፣ የተቀበረው፣ ያረገው፣ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከው በኢየሩሳሌም ከተማ ነው፡፡ ስለዚህ የኢየሩሳሌም ነገር በይሁዳ አውራጃ የተሻለ ይወራል፤ ይነገራል፡፡ የሚያውቁት ዘመድ ይኖራል፡፡ የሐዋርያትና የይሁዳ ቋንቋ ተመሳሳይ ነው፡፡ የይሁዳ ባሕልና የኢየሩሳሌም ባሕል ተመሳሳይ ነው፡፡ ከሰማርያ ቢሻልም ከኢየሩሳሌም ግን ይከፋል፡፡

ይሁዳ ምንድነው ይሁዳ? ይሁዳ አከባቢያችን ነው፡፡ ይሁዳ መንደራችን ነው፡፡ ይሁዳ ጓደኞቻችን፣ የምንሠራበት አከባቢ፣ የምንማርበት አከባቢ ነው፡፡ በየመንደሩ የሚሰበሰቡ ሰዎች ለወንጌል እንዲሰበሰቡ ማድረግ ይቻላል፡፡ አባቶቻችን ጽዋን፣ ሰንበቴን የመሠረቱት አንዱ ትልቁ ጥቅም በቅዱሳን ስም ተሰብስበን እንድንማር፣ እንድናውቅ፣ በይሁዳ ወንጌል እንዲሰበክ ነው፡፡
ታላቁ ሐዋርያ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ማኅበረ ጽዮን የተሰኘችውን የመጀመሪያዋን የጽዋ ማኅበር በአክሱም ጽዮን ሲመሠርት ሦስት ዓላማ ነው የነበረው፡፡ የመጀመሪያው ዓላማ ከዚያ ከቅዱሱ ረድኤት በረከት ማግኘት፤ ኹለተኛው ዓላማ ወንጌልን መማር፤ ሦስተኛው ዓላማ ድኾችን መርዳት፡፡ ዛሬ ጽዋዎቻችን እነዚህን ዓላማዎች ይተግብራሉ? ትምህርት አለ? ድኾች ይረዳሉ? ወይስ ከተለያየ ቦታ ተሰብስበን በቤታችን የሰለቸነውን ምግብ እንደገና አምጥተን በልተን ነው የምንለያየው? አብያተ ክርስቲያናት ይረዳሉ? የሐዊረ ሕይወትንና የመሳሰለውን ጉባኤ’ኮ ማዘጋጀት ያለባቸው በየከተማው ያሉ ሰንበቴዎች፣ ጽዋ ማኅበራት፣ የጉዞ ማኅበራት አንድ ላይ ኾነው ነው፡፡ ይኼ ነዋ ዓላማቸው! ወንጌል እንዲሰበክ ማድረግ ነዋ ዓላማቸው! አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የሾማቸው የመጀሪያዎቹን ሰባት ኢትዮጵያውያን ሐዋርያት የሚያስፈልጋቸውን አሟልታ “ሒዱ፤ አስተምሩ” ብላ የላከችው’ኮ ያቺ ማኅበረ ጽዮን የተባለችው የጽዋ ማኅበር ናት፡፡ ዛሬ ጽዋዎቻችን ሐዋሪያዊነት አላቸው? ስብከተ ወንጌል ላይ ይሠራሉ? የጽዋ ማኅበርተኞች ይማራሉ? በየመንደራችንስ ትምህርት አለ?
በይሁዳ ማለት ይኼ ነው፡፡ ኹለተኛው ስምሪት ይኼ ነው፡፡ ጥቂት የሚያውቁ፣ ጥቂት የተማሩ፣ ጥቂት የገባቸው፣ መንደሩን የሚያውቁ ምእመናን አከባቢያቸውን ሰብስበው የሚያስተምሩበት ነው፤ ይሁዳ፡፡ ነጋዴዎች በንግድ አከባቢ ያሉትን ሰብስበው፣ ሾፌሮቹ በዚያ በሙያቸው ያሉትን ሰብስበው፣ ፓይለቶቹ በዚያ አከባቢ ያሉትን ሰብስበው፣ ሊስትሮዎቹ በሙያ የሚቀርባቸውን ሰብስበው፣ የመንግሥት ሠራተኞቹ በዚያ የሚቀርቧቸውን አሰባስበው፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም እንደዚሁ፤ ሌሎችም የሚቀርቧቸውን ሰብስበው የሚያስተምሩበት ነው፡፡ “ኑ እንወቅ፤ ኑ እንማር፡፡ እኛ መጀመሪያ እንወቅ፤ ከዚያም እንሒድ፤ ሌላ ቦታ እንድረስ” የሚሉበት ነው፤ ይሁዳ፡፡
ምናልባት ሔደን ቆመን ላናስተምር እንችል ይኾናል፡፡ ነገር ግን ሞራል መኾን እንችላለን፡፡ የሐዊረ ሕይወትና የበእንተ ወንጌል ጉባኤ ተዘጋጅቶ ወደ ሌላ አከባቢ ስንሔድ እኛን ያዩ የዚያ አከባቢ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ በአጠቃላይ ምእመናን ምን እንደሚሰማቸው እስኪ አስቡት? ሰው’ኮ ከዕውቀት ከትምህረት እጥረት በላይ የሞራል እጥረት ይጎዷል፡፡ በተደጋጋሚ እርሱ ከሚያምነው የተለዩ ሰዎች የሞራል ጫና ሲያሳድሩበትና “አንተ’ኮ የለህም፤ የሚጠይቅህም የለም” ሲሉት በጣም ነው የሚጎዳው፡፡ እስረኛና በሽተኛ ትልቁ የሚርበው ጠያቂ ነው፡፡ አንድ በሽተኛ ተኝቶ፣ አንድ እስረኛም ታስሮ ሔዶ የሚጠይቀው ሰው ነው የሚርበው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን በማቴዎስ 25 ከጠየቃቸው ጥያቄዎች አንዱ፡- “ታስሬ አልጠየቃችሁኝም፤ ታምሜ አልጎበኛችሁኝም” የሚለው፡፡ ምክንያቱም አንድ የታመመና የታሰረ ሰው መጀመሪያ የሚፈልገው ምግብ ወይም ገንዘብ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ሔዶ “እግዚአብሔር ያበርታህ፤ ደኅና ነህ ወይ?” የሚለውን ነው የሚሻው፡፡ የታመም ሰው “አይዞህ፤ በርታ! እግዚአብሔር ያጽናህ፤ እግዚአብሔር መድኃኒቱን ይላክልህ” የሚለው ሰውን ነው የሚፈልገው፡፡ ስለዚህ ምንም ባናደርግም መምጣት በራሱ ትልቅ ሐዋርያነት ነው፡፡ መጥቶ “እኛ የእናንተ አካል ነን፤ አብረናችሁ ነን፤ ከእኛ ጋር ናችሁ፤ ወገኖቻችን ናችሁ፤ ወገኖቻችሁ ነን” ማለት በራሱ ትልቅ ሐዋርያነት ነው፡፡
አሁን ትንሽ ተስፋ የምናየው በይሁዳ ያለው አገልግሎት ነው፡፡ ሰዎች ይሰበሰባሉ፤ የሚቀር ግን አንድ ነገር አለ፡፡ ብዙዎቻችን ለእንዲህ ዓይነቱ የመሔድ አገልግሎት የበረታን አይደለንም፡፡    
ሦስተኛው በሰማርያ ነው!
ለምንድነው ሰማርያ ያለው? ሰማርያ ከአይሁድ በብዙ ይለያል፡፡ በቋንቋ ይለያሉ፤ በባሕል ይለያሉ፡፡ በእምነት ይለያሉ፤ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ ነውና የሚቀበሉት /ዮሐ.4/፡፡ ስለዚህ ወደ ሰማርያ መሔድ ማለት በባሕል፣ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በአስተሳሰብ፣ በአለባበስ፣ በአመጋገብ ወደሚለዩ ሰዎች መሔድ ነው፡፡ ጣዖት የሚያመልኩ ሊኾኑ ይችላሉ፤ ባሕላዊ እምነት የሚያመልኩ ሊኾኑ ይችላሉ፤ ሌላም ነገር የሚያመልኩ ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ ወደነዚያስ መቼ ነው የምንሔደው? “በይሁዳ እንዳትቀሩ፤ ወደ ሰማርያ ሒዱ” ነዋ የተባልነው፡፡
ብዙ ሐዋርያት ከሰማርያም አልፈው ነው የሔዱት፡፡ እነ ቅዱስ ቶማስ ሕንድ ሔደዋል፡፡ እነ ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሮም እስከ ስፔን ድረስ ሔደዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሐዋርያትም እንደዚሁ ከሰማርያ አልፈው ሔደዋል፡፡ ዛሬ የተነሡ አንዳንድ ሰዎች ሰማርያ አልፋ የሔደች አይመስላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ማይክራፎን ከመጣ ወዲህ ማስተማር የጀመረች ነው የሚመስላቸው፡፡ ከሞንታርቦ ዘመን ወዲህ ነው ታሪኳን የሚጀምሩት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን የሞንታርቦ ዘመን ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡፡ ብዙዎች ሐዋርያት ተሰማርተዋል፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ወደማይታወቅ ቦታ ስምሪት ነበረ፡፡ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ሰባት ሐዋርያትን እስከ ሱዳን ድረስ ልኳል፡፡ ከዚያ በኋላ የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳንም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ እንኳን በአክሱም ከተማ የተቀመጡት ኹለቱ ብቻ ናቸው፤ አባ ሊቃኖስና አባ ጰንጤልዮን፡፡ እርሱም ንጉሡ፡- “እኔንማ ትታችሁኝ ከሔዳችሁ ማን ይባርከኛል? ማን ይጸልይልኛል? እኔ ክፉ ከኾንኩ የእናንተ የወንጌል አገልግሎትም ክፉ መኾኑ አይደለም ወይ? እኔንምኮ ማስተማር አለባችሁ፤ እኛ መኳንንቱ እኛ ነገሥታቱ ሐላፊዎቹ ከከፋን አገር ትከፋለች፡፡ ስለዚህም እኔንም ማስተማር ሐዋርያዊ አገልግሎት ነው” ብሏቸው ነው፡፡ የቀሩት ሰባት ግን አክሱም መቀመጥ እንኳን እንደ ቅንጦት እንደ ምቾት ቈጥረዉት ወጥተው ነው የሔዱት፤ ከሔዱ ደግሞ አልተመለሱም፡፡ 
ከእነርሱም በኋላ የመጡት ሐዋርያት ወደማያውቁት አገር ነው የሔዱት፡፡ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መጀመሪያ 17፣ በኋላ (በአቡነ ፊልጶስ ዘመን) ያፈሯቸው 12ቱን ሐዋርያት ሀገረ ስብከት አካፍለው ነው የላክዋቸው፡፡ ማንም ወደተወለደበት አከባቢ አልሔደም፡፡ ተመልሶ በሰላም የመጣም የለም፡፡ በክፍል አንድ ትምህርታችን ያነሣነው አቡነ አኖሬዎስ ባሌን ተሻግሮ በዚያው ዐርፎ፡ ዐፅሙ ነው በደቀመዛሙርቱ የተመለሰው፡፡ አባ በጸሎተ ሚካኤል ዐፅሙ ነው ወደ ገዳሙ የተመለሰው፡፡ አቡነ ፊልጶስ ዐፅሙ ነው ወደ ገዳሙ የተመለሰው፡፡ ማንም የላመ የጣመ ያለበት የተመቸ ቦታ ላይ ልቀመጥ ያለ የለም፡፡ እንደሔዱ ነው የቀሩት፡፡ እንደተጓዙ ነው የቀሩት፡፡ ይኼ ነው ወደ ሰማርያ መሔድ፡፡
አሁን የሚቀረንና የምንወቀስበት ትልቁ አገልግሎት ይኼ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኹለት ሺሕ ዓመት ታሪክ አፍሪካ በሙሉ ክርስቲያን መኾን ነበረበት፡፡ መሔድ ማስተማር ነበረብን!
ዛሬ በጠረፉ አከባቢ ያለው መልክ ትክክለኛ መልክ አይደለም፡፡ የሠሩ ሰዎች ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም፤ ሠርተዋል፡፡ እነ ዕጨጌ ዕንባቆም ከየመን ተነሥቶ፣ ሃይማኖቱን ቀይሮ፣ ክርስቲያን ኾኖ፣ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ፣ መንኩሶ፣ መንኖ፣ ከዛ ደግሞ 12ኛው የደብረ ሊባኖስ ዕጨጌ ኾኖ፣ እንደገና ተሰማርቶ በዐባይ በረኻ በወለጋ ያስተማረው ትምህርት የሚደግመው ጠፋ፡፡ እስከ አሶሳ ድንበር ድረስ አስተምሮ ነበር፤ ነገር ግን የሚደግመው ጠፋ፡፡ እነ አቡነ አኖሬዎስ እስከ ባሌ ድረስ ሔደው አስተምረው ነበር፡፡ በመተሐራና በወንጂ እነ አቡነ ኢዮስያስ ሔደው አስተምረው ነበር፡፡ በዳሞት፣ በከንባታ፣ በሀድያ እስከ ጋሞጎፋ ድረስ እነ አቡነ ታዴዎስ ተሰማርተው አስተምረው ነበር፡፡ በምሥራቅ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ የሶማልያ ሀገረ ስብከት እስከምንለው ድረስ እነ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ሔደው አስተምረው ነበር፡፡ (የአቡነ ሳሙኤል ዋናው ገዳማቸውኮ ደብረ ወገግ አይደለም፡፡ ደብረ ኪሩብ የሚባል ነው፡፡ ዛሬ ምንም ነገር የለውም፡፡ አሰቦት ላይ ቆማችሁ ደብረ ኪሩብ ይታያችኋል፡፡ እርሳቸውም ሲያስተምሩ ያረፉት እዚሁ ደብረ ኪሩብ ላይ ነው፡፡ ዐፅማቸው በኋላ ነው የተመለሰው፡፡) ዛሬ ዓፋር የምንለው አከባቢ የእነ አባ አንበስ ዘደብረ ዓዘቦ ሀገረ ስብከት ነበር፡፡ (ደብረ ዓዘቦ ዛሬም ፍርስራሹ አለ፡፡ በረዶ የሚያፈላበት ትልቁ ተራራ ጫፍ ላይ ነው ገዳማቸው የነበረው፡፡ እዛ ላይ ኾነው ነው አከባቢውን ሲያስተምሩ የነበሩት፡፡) ማን ይተካቸው? ማን ይውረሳቸው? የለም! ኹላችንም የተመቸ ቦታ ላይ ተቀምጠን ያለነው፡፡ ከላይ እስከ ታች ያለነው ሰዎች ከኢየሩሳሌም ከከፋም ከይሁዳ ላለመውጣት ወስነናል፡፡
ምእመናንም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያለንን ሩጫ ያኽል ስብከተ ወንጌል ላይ የለንም፡፡ እስኪ ማን ነው ገንዘቡን፡- “እዚህ አከባቢ ያለው ሕዝብ ሊማር ይገቧል፡፡ ሐዋርያ ሊደርሰው ይገባል፡፡ የኛ ገንዘብ እዛ መዋል አለበት” የሚል? ያንን ስምሪት የሚተካ አልመጣም፡፡
ኹሌ የምንኮራበት፣ “እርሱም ለወገኖቹ ሐዋርያ ኾነ” ብሎ አውሳብዮስ የተናገረለት ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ’ኮ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም ብዙውን ያስተማረው፡፡ መጀመሪያ ኢትዮጵያ - አክሱም አከባቢ፣ ከዛ ኑብያ - የዛሬዋ ሰሜን ሱዳን፣ ከዚያ ቀጥሎ ናግራን - የዛሬዋ ደቡብ የመን፣ ከርሱ ቀጥሎ ፋርስ - የዛሬው ኢራንና ዒራቅ፣ ከዚያ ቀጥሎ ሕንድ፣ ከሕንድ ቀጥሎ ቻይና አጠገብ ሲኖል የምትባል ደሴት አስተምሮ ነው ተሰማርቶ ያረፈው፡፡ ይህን ዛሬ ማን ይተካው? ማን ነው የሚሰማራው? ይህ ስምሪት ስለጎደለ ነው ዛሬ ትልቅ አደጋ ውስጥ የገባነው፡፡
ሠርተው ነበር አባቶቻችን!!! ወንዶቹ ብቻ አይደሉም፤ ሴቶቹም ጭምር!!! ሴቶችን ለመቀበል በማይደፍረው ዘመን እንኳን ኦርኒና መክብዩ የሚባሉ የአቡነ ፊልጶስ ደቀ መዛሙርት ተሰማርተው ነበር፡፡ እነዚህ ኦርኒና መክብዩ እሳት የላሱ ወንጌላውያን ነበሩ፡፡ ጥቅምት 23 ነው የሰማዕትነትን ጽዋ የተቀበሉት፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው የንጉሥ ወታደር ተሰልፎ፣ አንዱ ባታሌውን ጠርቅሞ፡- “ማስተማር የለባችሁም” ሲላቸው “እኛኮ ተናገሩ እንጂ ዝም በሉ አልተባልንም፡፡ ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም፡፡ ታዲያ ለምን እንፈራለን? ጌታችን በጲላጦስ አደባባይ በንጉሡና በወታደሮቹ ፊት አልፈራም፤ እኛም ልጆቹ አንፈራም፡፡ እንዲያውም ቁሙ፤ እናንተንም እናስተምራችኋለን፡፡ ቁሙ! እኛን ለመግደል አይደል የመጣችሁ? ለማሰር አይደል የመጣችሁ? እንደዉም ባላችሁበት ቁሙ፤ ይኼን ትምህርትማ ሰምታችሁ መሔድ አለባችሁ” ነው ያሉት፡፡ በዚያ ዘመን ሴቶች እንዲህ የሚናገሩበት ዘመን ስላልነበረ “ምንድነው የመጣብን?” ብለው እጅግ ደንቋቸው ቆሙ፤ ሰሟቸው፡፡ ወደ 23 የፈጀ ትምህርት ነው ያስተማሯቸው፡፡ እናቶች ዛሬ ለ23 ቀን የሚኾን ትምህርት አላችሁ? ወይስ ለ23 ቀን የሚኾን የቡና …. አልጨርሰውም፡፡ አርኒና መክብዩ ግን ቆሙ፡፡ አስተምረዋል፡፡ እስከ ጠረፍ ድረስ ሔደው መስክረዋል፡፡
እነ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ሱስንዮስ “አገሪቱን ወደ ካቶሊክነት እቀይራታለሁ” ባለ ጊዜ፣ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖን ሲገደሉ፣ ታላላቆቹ ሊቃውንት ሲታሰሩ፣ መምህራኑ በየገዳማቱ ሲሰደዱ ዞራ አስተምራለች፡፡ ባሏ የሱስንዮስ የጦር አዛዥ ነበር፡፡ ሊቀ ጳጳሱን ገድሎ፣ አክሊላቸውን (አስኬማቸውን) እና ልብሳቸውን እንደ ግዳጅ ይዞት ሲመጣ፡- “ይኼውልሽ! ዛሬኮ በጦርነት ላይ ዋልኩ፡፡ ካቶሊክነትን አልቀበልም ያሉትን ጳጳስ ገደልኩ” ሲላት፡- “አባቴን ገድለህ ከእኔ ጋር መኖር አትችልም፡፡ የእኔና የአንተ ግንኙነት በዚህ ላይ አበቃ፡፡ ሃይማኖት ነው የመሠረተው፤ እዚህ ላይ አበቃ፡፡ የአንተን ሚስት ነኝ እላለሁ፤ ግን የማን ልጅ ነኝ እላለሁ?” ብላ ነው ወጥታ በመላ ትግራይ፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ጎንደር ዞራ ያስተማረችው፡፡ ንጉሡ የሚያደርገው እስኪጠፋው ድረስ ድረስ ነው ያስተማረችው፡፡ እንዳይገድላት ወንድሞቿ የንጉሡ የቀኝ ግራ አዛዦች ናቸው፡፡ እርሷን ገድሎ ከእነርሱ ጋር መኖር ፈራ፡፡ ዝም እንዳይላት “እንዴ! ሴቷ እንኳን እንደዚህ ስታስተምር” ብለው ሊቃውንቱ ሞራል እየኾነቻቸው ተነሡበት፡፡ ዙራ አስተምራለች፡፡ እርሷ እንድታስተምር ትልቁን እገዛ ያደረጉት በተለይ በጣና ሐይቅ ይሠሩ የነበሩ ባለ ጀልባዎች ናቸው፡፡ ከዕንጨት ጋር እየደበቁ፣ ከሌላ ነገር ጋር እየደበቁ አገር አገር እያሻገሯት እንድታስተምር ያደረጉት፡፡ ዛሬ ወደየገዳማቶቻችን አድርሰው እንደሚመልሱን ሹፌሮች ማለት ነው! ከተጠቀምንበትኮ ይህም ትልቅ ሐዋርያነት ነው፡፡
ቢጨንቀው ንጉሡ “እስኪ አስተምራት” ብሎ ወደ አልፎንስሜንዴዝ ወሰዳት፡፡ እጅና እግሯን ታስራ ኹልጊዜ የኑፋቄ ትምህርት እንዲነበብላት ተደረገች፡፡ “ቀይራት፤ ባትሰማህም ንገራት” ተባለ፡፡ ደከመ፤ ነገር ግን ምንም ሊቀይራት አልቻለም፡፡ እንደዉም መጨረሻ ላይ እዚያ ቦታ መታሰሯን ያወቁ ሌሎች ጀግኖች መጡና እርሱ በሌለበት በሩን ሰብረው ገመዷን በጥሰው ይዘዋት ጠፉ፡፡ “ቀየርካት?” አለው፡፡ “የምትቀየር አይደለችም” አለው፡፡ ይዘዋት ከሔዱ በኋላ ደቀ መዛሙርቷ ጠየቋት፡፡ “ይኼን ያህል ጊዜ እርሱ የኑፋቄ ትምህርት ሲያስተምርሽ ከልብሽ ውስጥ አልገባም” ሲሏት “እርሱ የኑፋቄውን ሲያነብ እኔ ጸሎቴን አደርጋለሁ፤ ሰምቼው አላውቅም፡፡” እስኪ በየመሥሪያ ቤታችን፣ በየንግድ ቦታችን የሚጮኽ ነገር የለም ወይ? የሚወራ ነገር የለም ወይ? ታዲያ ያን ጊዜ ስንቶቻችን ነን ያቺን ሰዓት ለጸሎት የምንጠቀምባት? ነገር ግን ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ወደ ካቶሊክነት ከመለወጥ የታደጋት የእነ እምነ ወለተ ጴጥሮስ ሐዋርያነት ነው፡፡  
ምእመናን ሆይ! ይኼን ነው በሰማርያ ማምጣት ያለብን! ጉሙዝ ሕዝብ ሔዳ አስተምራለች፡፡ ታስራ ወደ ጉሙዝ ሔዳለች፡፡ የሚያስራት ሰውዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ስላላወቀ አሰራት፡፡ በኋላ ግን ሃይማኖቷን፣ ምግባሯን ቢያይ “ምን አድርገሽ ነው? ለምንድነው እኔ ጋር እሰራት ብለው የላኩሽ?” አላት፡፡ “እኔ ሃይማኖቴን ስለጠበቅኩ ነው፡፡ የአባቶቼን ሃይማኖት ስላከበርኩ ነው የታሰርኩት” ስትለው “እስኪ ይኼ ሃይማኖቴ የምትዪውን ንገሪኝ” አላት፡፡ መጀመሪያ ያስተማረችው እርሱን ነው፡፡ የለወጠችው እርሱን ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እርሷ ሦስት ዓመት እዚያ ስትታሰር እርሱ የእርሷ ደቀ መዝሙር ነው የኾነው፡፡ እስር ቤት ልንገባ እንችላለን፤ ግን ስንት ደቀ መዛሙርትን እናፈራለን?
ሰማርያ ማለትኮ ይኼ ነው፡፡ እስርቤቶቹ፣ ሆስፒታሎቹ፣ የተለያዩ ቦታዎች፣ ከሀገር ወጥተን የምንሔድባቸው ቦታዎች ሰማርያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን በብዙ ዓለማት ተሰማርተዋል፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ በየአጥቢያው ስትሔዱ እኛው ብቻ ነን፡፡ አንድ ቻይናዊ አምጥተናል? አንድ ሕንዳዊ አምጥተናል? አንድ ሜክሲኮአዊ አምጥተናል? እኛ ብቻ ነን፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በውጪው ዓለም መባላትና መናከስ ያለው፤ እኛው ብቻ ነና! ትንሽ ብንቀላቀል ኖሮኮ ያም ቋንቋው ስለማይችል መሰዳደባችንን እንኳን ስለማይገባው ተስማምተን እንኖር ነበር፡፡ አላመጣንም፡፡ በሰማርያ ግን አስተምሩ ተብለናል፡፡ ለእነርሱ የሚኾን መዝሙር አለን? አዲስ ሰው ቢመጣ ለእርሱ የሚኾን መጽሐፍ አለን? ለእነርሱ የሚኾን ትምህርት አለን? ለእነርሱ የሚኾን ዝግጅት አለን?
ሰሜን ኬንያ የነበሩ ሕዝቦ በስደተኞቹ ካምፕ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ሲያዩ ከጎሳው መሪ ጀምረው ተጠመቁ፡፡ “አሁን እኛ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. አማኞች ነን” አሉ፡፡ እምነታቸውን ትተው መምጣት፤ መጠመቁ አልቸገራቸውም፡፡ ነገር ግን የሚቀበላቸው ዝግጅት አልነበረም፡፡ ለእነርሱ የሚኾን ሰው አልነበረም፡፡ የሚበሉትን በልቶ፣ የሚጠጡትን ጠጥቶ፣ የሚኾኑትን ኾኖ የሚያስተምራቸው ሰው አልነበረም፡፡ አባቶቻችንኮ ወደ ባዕድ አገር ስትሔዱ “እንደነርሱ ኹኑ” ነበር ያሉን፡፡ “የሚበሉትን ብሉ፤ የሚጠጡትን ጠጡ፤ የሚለብሱትን ለብሳችሁ በቋንቋቸው ተናገሩና መልሷቸው” ነበር ያሉን፡፡ እንደዛ የሚኾን ሰው ግን አላተረፍንም፡፡ ብዙ ደቡብ አፍሪካውያን መጥተዋል፡፡ ነገር ግን ለእነርሱ የሚኾን አላዘጋጀንም፡፡ ይኼ ነው ሰማርያ ማለት፡፡ ነገ ትልቁ ሥራችንም ይኼ ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ የምናነብ ሰዎች እንዲሁ አንብበን “በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ጥሩ ጽሑፍ ነው” ብለን አይደለም መሔድ ያለብን፡፡ የቤት ሥራ ነው ይዘን የምንሔደው፡፡ ኹላችንም ይህን ጽሑፍ አንብበን በየመስካችን ካልተሰማራን ዝም ብለን ነው ከንፈር የምንመጠው፡፡ “እዚ ቦታ ላይ መናፍቃን እንዲህ አደረጉ፤ እዚህ ቦታ ላይ ከሐዲያን እንዲህ አደረጉ” ብንል ምን ያደርጋል? እንደ ሽሮ ወጥ ለጊዜው ከመቆጣት አልፈን ይኼ ነገር ነገ እንዳይደገም ምን እናድርግ ማለት አለብን፡፡ ይኼ ነው የሰማርያ ስምሪት፡፡ በሰማርያ ሒዱ የተባለው ይኼ ነው፡፡
አራተኛው ደረጃ በዓለም ዳርቻ ነው!
እስከ አሁን ያየናቸው ሦስቱም ይታወቃሉ፡፡ ኢየሩሳሌም ትታወቃለች፡፡ ይሁዳ ትታወቃለች፡፡ ሰማርያም ትታወቃለች፡፡ የዓለም ዳርቻ ግን የት ነው? አይታወቅም፤ ሰፊ ነው፡፡ እስከ ዓለም ዳርቻ ማለት እስከማትመለሱበት ቦታ ድረስ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያት ከሔዱበት አልተመለሱም፡፡ የሐዋርያት ልጆችም አልተመለሱም፡፡ በኪደተ እግራቸው የባረኩት አገራቸው ኾኖ በዚያ አስተምረው ነው የቀሩት፡፡ የአንዳንዶቹ ዐፅማቸው፣ የአንዳንዶቹ ተረፈ ዐፅማቸው ነው የተመለሰው፡፡ የዓለም ዳርቻ ማለት ይኼ ነው!
በጠረፉ አከባቢ ትልልቅ ጉባኤዎች እጅግ የበዛ ዋጋ አላቸው፡፡ ስለዚህ ወደ ዓፋር፣ ወደ አሶሳ፣ ወደ ቦረና፣ ወደ ሶማሌ፣ ክርስቲያኖች ወደሚያንሱበት፣ አምስት ስድስት ኾነው ወደሚያስቀድሱበት መሔድ አለብን፡፡ ዕጣንና ጧፍ አንሷቸው “በቃ ማለቃችን ነው” ወደሚሉት መሔድ አለብን፡፡ “አይዟችሁ አለን፤ ብቻችሁ አይደላችሁም፡፡ ቦታ አራራቀን እንጂ ሃይማኖት አልለያየንም፡፡ ቦታ አራራቀን እንጂ ሥርዓት አንድ ነው፡፡ የእናንተ አገልግሎት የእኛ አገልግሎት ነው፤ የእናንተ ማስቀደስ የእኛም ማስቀደስ ነው” ብለን መሔድ አለብን፡፡ ሲኾን ከዛ አልፈን ወደ አፍሪካ አገራት፤ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን አይቷት ሰምቷት ወደማያውቁት መሔድ አለብን!
ዛሬ በንግድ የሚሔደው ቻይና፣ ጃፓን፣ ዱባይ፣ ሕንድ፣ ወደ ሌሎችም እንሔዳለን፡፡ ታዲያ ስንት አስተማርን? ስንት አጠመቅን? ወይስ ዕቃ ብቻ ይዘን ነው የምንመጣው? የኦሪትን እምነት እንድናገኝ ያደረገንኮ ታምሪን የተባለ ነጋዴ ነበር፡፡ ዛሬም ታምሪን የኾኑ ነጋዴዎች ያስፈልጉናል፡፡ ቶማስን ሕንድ ድረስ የወሰደው ነጋዴ ነው፡፡ ስለዚህ የነጋዴ ሐዋርያት፣ የሹፌር ሐዋርያት፣ የምሁር ሐዋርያት፣ የባለሙያ ሐዋርያት ያስፈልጉናል፡፡ ሱቅ ከፍታችሁ የምትሸጡ፣ ሻይ ቤት ከፍታችሁ የምትሸጡ፣ ምግብ ሠርታችሁ የምትሸጡ ሑሉ ሐዋርያ ለመኾን መዘጋጀት አለባችሁ፡፡ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ! እኛ ወደማናውቀው ድረስ መሔድ አለብን፡፡ ብዙ ይቀረናል፡፡ ጀመርነው እንጂ ገና ነን፡፡ ያለቀ እንዳይመስላችሁ! ዛሬ በጉባኤ ስለተሰባሰብን በዝተን ስንታይ የጨረስነው እንዳይመስላችሁ! ገና ብዙ አለ፡፡ ይኼን ተስፋ የሚያደርጉ በጣም ብዙ ሕዝቦች አሉ፡፡ ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም፡፡
እንዴት እንሒድ?
አባቶቻችንን ሒደታቸውን በአራት መንገድ ነው የሔዱት፡፡
v  የመጀመሪያው በአካል መሔድ ነው፡፡  
v  ኹለተኛ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጽፈው አስተምረዋል፡፡የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ተቃጥሎ፣ ተሰርቆ፣ አይጥ በልቶት፣ ምድር ቀብሮት እንኳን ሊያልቅ ያልቻለውን መጻሕፍት ጽፈዋል፡፡ ለዚህ ሐዋርያዊ ተልእኮ ሦስት አካላት ነበሩ፡፡ አንድ ሊቃውንቱ፤ ኹለት ጸሐፍቱ (የሚጽፉት)፤ ሦስት ደግሞ የሚያስጽፉት፡፡ ገድሉ መጨረሻ ላይ አይታችሁ ከኾነ “የጻፈ፣ ያስጻፈ” ይላል፡፡ ዛሬ እንደነዚህ ዓይነት ሐዋርያት ያስፈልጉናል፡፡ ለምንድነው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በየቋንቋው የማይተረጐመው? ሲቻል ሳይሸጥ (በተለይ ለዕጣንና ለጧፍ እንኳን መግዣ ለሌላቸው ምእመናን) ለምን አይሰጥም? ምን አለበት እኔና እናንተ ዐሥር ኾነን አንዳችን የአንድን መጽሐፍ፣ አንዳችን ሌላውን መጽሐፍ ማሰተሚያ በተለያየ ቋንቋ በኦሮምኛ፣ በሀዲያኛ፣ በከንባትኛ፣ በጉራጊኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በጀርመንኛ፣ በየቋንቋ ለምን አናስጽፍም? እዛ ሔደን ማስተማር ባንችል ለምን እንዲህ አድርገን የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ወደየ አገራቱ እንዲደርስ አናደርግም? ለምን የካሴት ሐዋርያት አንኾንም? ለምን ትምህርቱ በካሴት ተባዝቶ በነጻ እንዲሔድ አናደርግም? ዛሬ እንደዉም የዲሽ ዘመን ነው፡፡ በዲሾቻችን ምን እየመጣ እንደኾነ እናውቃለን፤ ወረራው ቀላል አይደለም፡፡ ይኼም ዓይነት ሐዋርያ መምጣት አለበት፡፡ በቀላሉ የሚሔድ ሐዋርያ! አንድ ሰው ወደ እኛ እንዲመጣ አስተርጓሚ መጠበቅ የለበትም፡፡ እኛ ቶሎ ደርሰንለት ቶሎ አምኖ ቶሎ መጽደቅ አለበት፡፡ ጊዜ የለም አሁን፡፡ እርሱን መቼ ነው የምንሠራው?     
v  ሦስተኛው ማእከል የመመሥረት ሐዋርያነት፡፡ አባቶቻችን ለምን ይመስላችኋል ከሰሜን እስከ ደበቡ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፡ በየቦታው ገዳማትን የተከሉት? ዛሬ ካሉት ገዳማትኮ በተለያዩ ጦርነቶች ምክንያት የጠፉ ገዳማቶቻችን ይበልጣሉ፡፡ በታሪክ የምናውቃቸው ዛሬ ግን በአካል ያላገኘናቸው በጣም ብዙ ሺሕ ገዳማት ነበሩ፡፡ አባቶቻችን እነዚህን ገዳማት የተከሉበት አንዱ ዓላማ ለስብከተ ወንጌል ስምሪት ማእከል እንዲኾኑ ነው፡፡ እዛ ያስተምራሉ፤ እዛ ይጸልያሉ፤ እዛው የምንኩስናው አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከዚያ የወጡ ደቀ መዛሙርትም ይሔዳሉ፤ ያስተምራሉ፤ ይሔዳሉ፤ በተራቸውም ገዳም ይተክላሉ፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሸዋ ነው የሔዱት፡፡ መጀመሪያ አባ በጸሎተ ሚካኤል አምሐራ፣ ከዚያ ሐይቅ፣ ከዛ ደብረ ዳሞ፣ ከዛ ኢየሩሳሌም፣ ከዚያ ግብጽ ሔደዋል፡፡ ተመልሰው መጥተው ግን የስምሪት ማእከል ነው ያቋቋሙት፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም እንዲሁ የተተከለ እንዳይመስላችሁ፡፡ ወደ ደቡቡም፣ ወደ ሰሜኑም፣ ወደ ምዕራቡም፣ ወደ ምሥራቁም ለመሔድ እጅግ እስትራቴጂያዊ ቦታ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ወደ አራቱም አቅጣጫ የሔዱት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳሙን ለወንጌል አገልግሎት እንዲመች አድርገው ስለገደሙት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የስምሪት ቦታ ያስፈልገናል፤ ማእከል፡፡ በሰሜኑም፣ በደቡቡም፣ በምሥራቁም፣ በምዕራቡም የምንኩስና ሕይወትን፣ የአብነት ትምህርትን፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን አንድ ላይ የሚሰጡ ማእከላት ያስፈልጉናል፡፡ ያለ ማእከል ሐዋርያ ማፍራት አንችልም፡፡ ነገሥታቱና መኳንንቱ ገንዘባቸውን ሲያወጡ የነበሩትኮ ዝም ብለው አይደለም፡፡ የሕንፃ ፍቅር ስላላቸው አይደለም፤ በፍጹም አይደለም! ያንን ማእከል አድርጎ ለማስተማር ነው፡፡ ሰዉ እንዲሰበሰብ እንዲሰማ ነው፡፡ እስኪ ገድላቱን አንብቧቸው፡፡ ወይም ሲነበቡ አድምጧቸው፡፡ ወይም ስታነቡ አስተውሏቸው፡፡ ገና ሲጀምሩ “በዚህ ቀን በቅዱስ እገሌ በዓል የተሰበሰባችሁ ወንድሞቼ ሆይ ስሙ፡፡ እገሌ የተባለውን ታሪክ እነግራችኋለሁ” ነው የሚሉት፡፡ ስሙ ለምን አለ? ሕዝቡ ተሰብስቦ ይነበብ ስለነበር፡፡ ዛሬኮ ወደነዚህ ማእከላት መጥተን ከቻልን በሰዓታቱ ተኝተን፣ ጎበዝ ነን ከተባልን ደግሞ እኛ ሌላ መዝሙር እየዘመርን፣ አንዳንዶቻችን የራሳችንን ቴፕ፣ አንዳንዶቻችንም ምን ምን የሚያክል ፍራሽ ለአንድ ሌሊት ይዘን ነው የምንሔደው፡፡ እንዴ! እንዲህ ከሆነ ለምን እንሔዳለን? አባቶቻችን ለንግሥ እንድንሰበሰብ ያደረጉን ዋና ዓላማቸው እንድንሰማ ነው፡፡ ሰምተንም ሐዋርያ እንድንኾን ነው፡፡ ዛሬ እነዚህን ማእከላት መሥራት አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንሠራ ይኼን ታሳቢ ያደረገ መኾን አለበት፡፡ ይኼ ነውኮ ሰማርያ የዓለም ዳርቻ የተባለው!
v  በየቋንቋው የሚያስተምሩ ደቀ መዛሙርትን የማሰማራት ሐዋርያነት፡፡ ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ወደማያውቁት ቋንቋ፣ ወደማያውቁት ባሕል እየሔዱ ማስተማር አይቻልም፤ በአስተርጓሚ እያስተማርን አንችለውም፡፡ አያዛልቅም፡፡ ይልቁንስ ታላቁ ሐዋርያዊ አባት ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳደረገው መኾን አለብን፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንን የኾነው አባ ሰላማ ልሾም ብሎ ስለሔደ ወይም አብርሃና አጽብሃ እንደዚያ ብለው ስለላኩት አይደለም፡፡ የተላከው ጳጳስ ይዞ እንዲመጣ ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ አትናቴዎስ ኹለት ዓመት አስተምሮ ነው ቋንቋውን፣ ባሕሉን በሚያውቀው አገር ጳጳስ አድርጎ ነው የላከው፡፡ ስለዚህ ከየቋንቋው እናምጣ፡፡ ከየባሕሉ እናምጣ፡፡ ከየአከባቢው እናምጣ፡፡ ከየሰዉ እናምጣ፡፡ አምጥተንም እናስተምራቸው፤ አስተምረንም እናሰማራቸው፡፡ በምታውቁት ቋንቋ፣ በምታውቁት ባሕል፣ በምታውቁት አሠራር አስተምሩ እንበላቸው፡፡ ገንዘብ ሲያስፈልጋችሁ እንሰጣለን፤ መጽሐፍ ሲያስፈልጋችሁ እንሰጣለን፤ የማስተማሪያ ነገሮች ሲያስፈልጋችሁ እንሰጣለን፤ ግን እናንተ ሐዋርያት ኹኑ፤ ሒዱ እንበላቸው፡፡ ይኼ ስምሪት ያስፈልጋል ዛሬ፤ የደቀ መዛሙርት ስምሪት፡፡ እነዚህን መጀመሪያ ማሠልጠን ከዚያ ለተልእኳቸው የሚያስፈልጋቸውን መስጠት ከዚያም መጎብኘት ያስፈልጋል፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ስለዚህ እናሰማራ! ከአዲስ አበባ መዘምራን፣ ሰባክያን እየላክን አንችለውም፡፡ በዓመት ልንሠራ የምንችለውን ለምን ወደ ዐሥር ዓመት እናራዝሟለን? ሕዝቡም በቋንቋው ሲነገረው በቀላሉ ደስ ብሎት ነው የሚቀበለው፡፡ ሐዋርያት 72 ቋንቋ የተሰጣቸው አንዱ ዓላማኮ ለዚህ ነው፡፡
ይኼ ነው ኃላፊነታችን! በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ እስከ ዓለም ዳርቻ የተባለው ይኼ ነው፡፡
እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ተሰማርተን፣ 30 60 100 ያማረ ፍሬ አፍርተን፣ ያለ ሐፍረት ቆመን “ጌታ ሆይ! ኹለት መክሊት ሰጥተኸን ነበር፤ እነሆ አራት አደረግነው፡፡ አምስት ሰጥተኸን ነበር፤ እነሆ ዐሥር አደረግነው” የምንልና “ና አንተ ታማኝ ባርያ ወደ ደስታው ግባ” ከተባለው ወገን እንዲያደርገን፣ ያ መክሊቱን ቀብሮ “አንተ ክፉና ሐኬተኛ፤ እኔ ካልዘራሁበት የምሰበስብ ካልተከልኩበት የማጭድ መኾኑን ካወቅክ ለምን ለሌላ አትሰጠውም ነበር? እሳትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወርውሩት” ከተባለው እንዲጠብቀን የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን፤ አሜን!!!  

2015 ጁን 18, ሐሙስ

በባዕድ ሀገር ስለ እምነቴ እንድመሰክር አብቅቶኛል

                                                    byማኅበረ ቅዱሳን አትም ኢሜይል
    ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም.
                                                                                                                                                  በእንዳለ ደምስስ
11atletአትሌት ካልኢተ አብርሃም ትባላለች፡፡ ገና የ18 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ታይላንድ ውስጥ ለሚገኝ ሃቲያ ዩኒቨርስቲን ወክላ ትሮጣለች፤ ዩኒቨርስቲውም በዲግሪ መርሐ ግብር የሰውነት ማጎልመሻ /Physical Education/ ትምህርት እድል ሰጥቷት በመማር ላይ ትገኛለች፡፡ ከ43 በላይ ታይላንድ ውስጥ በሚደረጉ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከ5 ሺሕ እስከ ግማሽ ማራቶን /21 ኪሎ ሜትር/ ድረስ በመሮጥ 40 ዋንጫዎችንና በርካታ የወርቅ ሜዳልያዎችን ለማግኘት ችላለች፡፡

ታይላንድ ውስጥ በምታደርጋቸው ውድድሮች አሸንፋ ስትገባ ለንጉሱና በቡድሂዝም እምነት ለተቀረጹት ምስሎች እንድትሰግድ ማስጠንቀቂያና መመሪያ ተሰጥቷታል፡፡ ነገር ግን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን ያገኘሁባትን ኦርቶዶክሳዊት እምነቴን አልክድም፤ እናንተም ላቆማችሁት ምስል አልሰግድም!!! በማለት ጸንታ በመቆሟ ትእዛዙንም ተላልፋ በማማተቧ በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች፡፡ እግዚአብሔር ረድቶኝ በባእድ ሀገር ስለ እምነቴ ለመመስከር አብቅቶኛል ትላለች አትሌት ካልኢተ አብርሃም፡፡

ስለስደት፤ እንዲሁም ስለ ሩጫ ሕይወቷ እና አስተዳደጓ አነጋግረናታል እንደሚከተለው እናቀርበዋለን፡፡

ስለ አስተዳደግሽ ብታጫውቺን?
የተወለድኩት ከመቀሌ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው አዱግደም በሚባል ቀበሌ ነው፡፡ ያደግሁት ግን መቀሌ ከተማ ከአክስቴ ጋር ነው፡፡ እናቴ ከልጅነቴ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን እንዳድግ አድርጋኛለች፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ እየተከተልኩ፤ እንዲሁም በየዓመቱ በሚከናወኑ የንግሥ በዓላት በመገኘት፤ ቤታችን ለካህናትና ምእመናን ጸበል ጸዲቅ ሲዘጋጅ እያየሁ ነው ያደግሁት፡፡

ወደ ሩጫው እንዴት ገባሽ?
ከአክስቴ ጋር እየኖርኩ በክረምት ወደ እናቴ ስሄድ ግቢያችን ውስጥ ተከራይተው የሚኖሩ ሯጮች ስለነበሩ ስለ ሩጫ ከእነሱ እየሰማሁ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ እየተነሱ ለልምምድ ሲሄዱ አብሬ እየሄድኩ ልብሳቸውን እየጠበቅሁ፤ ቀስ በቀስም ወደ ሩጫው እየተሳብኩ በግሌ ልምምድ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን በቤተሰብ በኩል ተቀባይነት ስላላገኘሁ ከአክስቴ ቤት ወጥቼ አንዲት ትንሽ ቤት ተከራይቼ ትምህርቴን እየተማርኩ የሩጫ ልምምዴንም እየሰራሁ ቀሪውን ጊዜዬን አቅሜ የፈቀደውን የቀን ሥራ፤ አትክልተኛም በሆን እየሠራሁ፤ በቀሪ ትርፍ ጊዜዬም መቀሌ ከተማ በሚገኘው መካነ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ገብቼ መማር ጀመርኩ፡፡

በሰንበት ትምህርት ቤቱ የነበረሽ ቆይታ ምን ይመስል ነበር?
ከ8ኛ ክፍል እስከ 10ኛ ክፍል በራሴ ወጪ እየተማርኩ በሰንበት ትምህርት ቤት በአገልግሎት እየተሳተፍኩ፤ የካህናት ልብሰ ተክህኖ የሰንበት ትምህርት ቤታች አልባሳት እያጠብኩ፤ በሩጫውም ቢሆን በተለያዩ መቀሌ ከተማ ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች መሳተፍ ጀመርኩ፡፡ ሰው ቤት ተቀጥሬም የሰራሁበት ጊዜ አለ፡፡ ይህን ያደረግሁት ሩጫው የሕይወቴ አንድ አካል አድርጌ ስለቆጠርኩት ነው፡፡ በልጅነት ልቦናዬም ቢሆን የሚደርሱብኝን ፈተናዎች መጋፈጥ ጀመርኩ፡፡ ለዚህም ሰንበት ትምህርት ቤቱ ለእኔ የተለየ ድጋፍ ያደርግልኝ ነበር በምክርም ሆነ በሚቸግረኝ ነገር ሁሉ ከጎኔ ነበሩ፡፡ መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡ በአዲሐቂ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10 ክፍል ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ ትምህርቱን አቁሜ ሙሉ ጊዜዬን ለልምምድ፤ ለሥራ እና ለአገልግሎት በማዋል ራሴን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት አደረግሁ፡፡

ቤተ ክርስቲያንን በመጠጋቴ በልጅነት እድሜዬ መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲኖረኝ፤ እግዘዚአብሔርን መፍራት፤ የቅዱሳን አባቶቻችን ተጋድሎና ታሪክ በተለይም የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገድል ቤተ ክርስቲያኑ ውሰጥ በየቀኑ ስለሚነበብ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ በፈተና እንድጸና አድርጎኛል፡፡ ወደ ንስሓ እና ምስጢራትን ወደመካፈል መራኝ፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን አዲሸሁ እንዲሁም ማይጨው ማእከላት ጋር የነበረሽ ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር?
22atletበሩጫ በነበረኝ ተሳትፎ የመቀሌ ዞንን ወክዬ በ5ሺሕ ሜትር ተወዳድሬ አሸነፍኩ፡፡ ከዚያም ለትግራይ ሻምፒዮና ሽሬ ላይ በተካሄደው ውድድር ተካፍዬ ለፕሮጀክት በመመረጤ አዲሰ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ ስመጣ እንደጠበቅሁት ውጤታማ መሆን ባለመቻሌ አሰልጣኝ ፍለጋ ወደ ዐዲሸሁ ሄድኩኝ፡፡ ዐዲሸሁ እያለሁ ከተከራየሁት ቤት ፊት ለፊት የማኅበሩ ጽ/ቤት ስለነበር ወንድሞችና እህቶችን ማግኘት ቻልኩ፡፡ አንድ ቀን ተከትያቸው ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ አብሬ ሄድኩኝ፡፡ በኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያገለግሉ ስመለከት ቀረብኳቸው ፤ቀስ በቀስ እኔም ከእነሱ ጋር በአገልግሎት መሳተፍ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን ከተወሰኑ ወራት በኋላ ወደ ማይጨው አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከል ለመግባት ስላሰብኩ ወደዚያው ሳመራ ለማእከሉ አሳወቅሁ፡፡ ለማይጨው ማእከል የእኔ መምጣት ተነግሯቸው ስለነበር ፈልገው አግኝተውኝ አገልግሎትንና ልምምዴን ቀጠልኩ፡፡ በደብረ ስብሐት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥም መሳተፍ ጀመርኩ፡፡

በማይጨው ቆይታዬ ከማእከሉ ወንድሞችና እህቶች ብዙ ነገር ተማርኩኝ፡፡ ሰዎችን በክርስትና ሕይወታቸው ጸንተው እንዲኖሩ የመቅረጽ መንፈሳዊ ስጦታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የሚጋጥመኝን የገንዘብ ችግር በመቅረፍ፤ ትክክለኛውን መንገድ በማሳየት ባለውለታዎቼ ናቸው፡፡

በሩጫ ሕይወቴም መሻሻሎችን እንዳሳይና በክልሉ በተደረገ የ5ሺሕና 10ሺህ ሜትር ውድድር ጥሩ ውጤት ማምጣት ቻልኩኝ፡፡ በክለብ ለመታቀፍ ጥረቶችን ባደርግም አልተሳካልኝም፡፡ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመውኛል፡፡ እኔ ግን ክርስትናዬ ስለሚበልጥብኝ፤ ሁል ጊዜ በጎ ጎዳናን ተከትዬ መሄድ ስላለብኝና ከክርስትና መንገድ ሊያስወጡኝ የሚችሉ ክፉ ነገሮችን በመጋፈጤ ወደ ስልጠና ማእከሉ ሳልገባ ቀረሁ፡፡

ተስፋ ሳልቆርጥ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ 2005 ዓ.ም. በፕሮጀክት ታቅፌ ተወዳደርኩ አሸነፍኩ፡፡ የጃን ሜዳ አገር አቋራጭ ውድድርም ተሳትፌ ለማሸነፍ ቻልኩ፡፡ ነገር ግን ትኩረት የሚሰጠኝ በማጣት ተመልሼ ወደ ሀገሬ ሄድኩ፡፡ ሩጫውን እንዳልተወው እሱን ብዬ ብዙ ነገር አጥቼበታለሁ፡፡ በተለይም ቤተሰቦቼን፤ ትምህርቴንና የትውልድ ቦታዬን አሳጥቶኛል፡፡ እለህ ደግሞ ያዘኝ፡፡ አለኝ የምለው ቤተ ክርስቲያንና የማይጨው ማእከል ወንድሞችና እህቶች ናቸው፡፡ የልምምድ አልባሳት የሉኝም፤ ጫማ የለኝም፤ በጣም ተቸገርኩ፡፡

ወደ ታይላንድ ለመሄድ እንዴት ቻልሽ?
44atletበሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት የሚያውቀኝ አንድ ወንድም ከአንዲት ታላንዳዊት የሯጮች ማኔጀር ጋር አገናኘኝ፡፡ በሀገሬ ያልተሳካልኝ በሰው ሀገር እንዴት ይሳካልኛል በማለት ጥያቄውን ለመቀበል ተቸገርኩ፡፡ ነገር ግን ከዋነኛ ዓላማዬ አንዱ የሆነውን በሩጫ አገሬን መወከል ስለነበር ልምድም ለመቅሰም እንደሚረዳኝ በማመን፤ እነሱም በዩኒቨርስቲ ደረጃ እንሚያስተምሩኝና ዩኒቨርስቲውን ወክዬ እንድወዳደር ግፊት ስላደረገችብኝ ወደ ታይላንድ ለመሄድ ወሰንኩ፡፡

ዋነኛ ጭንቀቴ የነበረው ቤተ ክርስስቲያን የሌለበት፤ የእግዚአብሔር ስም የማይጠራበት፤ የንስሓ አባት የሌለበት ስለነበር ሰጋሁ፡፡ የምሥጢር ተካፋይ ስለሆንኩም በጣም አሳሰበኝ፡፡፡ ነገር ግን መሥዋዕትነት መክፈል ስለነበረብኝ ያገኘሁትን እድል ለመጠቀም ወሰንኩ፡፡ ከማኔጀሬ ጋር ሆኜ በአውሮፕላን ከአዲስ አበባ ግብጽ፤ ከግብጽ ባንኮክ፤ ከባንኮክ ሃቲያ ዩኒቨርስተ ለመድረስ ዐራት ቀናት ፈጅቶብናል፡፡ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገብተን ሌሊት 10 ሰዓት ውድድሩ ይካሔዳል፡፡ በጣም ደክሞኛል፤ ምግብ አልበላሁም፤ ከግብጽ ስንነሳ አንድ ኢትዮጵያዊ አግኝቼ ጭማቂ ሰጥቶኝ ስለነበር እሱን በውኃ እየበረዝኩ ጠጥቼ ነው የደረስኩት፡፡

የውድድሩ ሰዓት እየተቃረበ ሲመጣ ማናጀሬ በታይላንድ ሕግ መሠረት ብታሸንፊ በስታድየሙ ውስጥ ለቆሙት ለሀገሪቱ ንጉሥ እና ለቡድሃ እምነት የተቀረጹ ምስሎች መስገድ እንደሚገባኝ ይህ ደግሞ ግዴታ እንደሆነ አስጠነቀቀችኝ፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቴ ሲሸኙኝ ያሰሩልኝ መስቀል፤ ገድለ ጊዮርጊስንና ውዳሴ ማርያምን ይዤ እያለቀስኩ ጸሎት አደረስኩ፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ፍርፋሪ በልቼ፤ የምስጢር ተካፋይ አድርጋንኝ ለምን በእምነቴ ላይ ይመጡብኛል ብዬ ውድድሩ እስኪጀመር ድረስ በጣም አምርሬ አለቀስኩ፡፡ ወደ ውድድሩም ገባሁ፡፡ አንዲት ኢትዮጵያዊትና ኬንያውያን በብዛት ነበሩ፡፡ ነገር ግን በአንደኝነት ውድድሩን ጨረስኩ፡፡

አሸንፌ ስገባም ለድል ያበቃኝን እግዚአብሔር እያመሰገንኩ የተሰጠኝን ማስጠንቀቂያ ለመጋፈጥ በመወሰን አማተብኩ፡፡ ስታድየሙ በሕዝብ የቁጣ ጩኸት ተናጋ፡፡ የለበስኩት የሃቲያ ዩኒቨርስቲ መለያ ነው፤ በሌላ አነጋገር የታይላንድ መለያ እንደለበስኩ አድርገው ስለቆጠሩት እንዴት ለአምላካችንና ለንጉሣችን አትሰግድም በሚል ቁጣቸው አገረሸ፡፡ ዋንጫውንም ስቀበል አማትቤ ተቀበልኩ ቁጣቸው ከመጀመሪያው ባሰ፡፡ ማናጀሬ ለብቻ ወስዳ ለምን እንዲህ እንዳደረግሁ ጠየቀችኝ፡፡

እንዳሸንፍ ለረዳኝ አምላኬ ምስጋና ነው ያቀረብኩት፡፡ ለማላውቀውና እናንተ ላቆማችሁት ምስል አልሰግድም!! ካልፈለጋችሁኝ ወደ ሀገሬ መልሱኝ ብዬ በአቋሜ ጸናሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆን ፈተና ሊገጥምህ ይችላል ነገር ግን መቋቋም ግዴታ ነው፤ ከክርስትና የተማርኩት ይህንን ነው፡፡ በባእድ ሀገር ብሆንም እምነቴን የሚያስክደኝ እንደሌለ ማሳየት ይጠበቅብኛል፡፡ ለዚህ ለዚህ ለምን ክርስቲያን ሆንኩ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለተጋደለላት፤ ቅዱሳን አባቶቼ በጽናት የቆሙላትን ስለ እውነተኛዋ እምነቴ እንዳልመሰክር ምን ሊያግደኝ ይችላል፡፡ በአቋሜ መጽናቴን በመረዳታቸውና እኔንም ማጣት ስላልፈለጉ በእምነቴ ላይ እንዳይመጡብኝ ተስማማን፡፡

ዩኒቨርስቲው የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርትንና ተጓዳኝ ትምህርቶችን እየተማርኩ መኖሪያና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ ቁሳ ቁሶችን አሟልተውልኝ እኖራለሁ፤ ልምምድ አደርጋለሁ፤ ውድድር ሲኖር እወዳደራለሁ፤ ማናጀሬ ከተለያዩ ሀገራት በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ እንድሳተፍ ታደርጋለች፡፡ እሰካሁን 43 እና ከዚያ በላይ ውድድሮችን አድርጌ 40ዎቹን በአንደኝነት ነው ያጠናቀቅሁት፡፡

ውድድሮቹ አልበዙብሽም?
የውድድሮቹ መብዛት በጣም አድካሚ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተወዳድሬ ጥሩ ውጤት በማምጣት ስሜን ማስመዝገብ ስለምፈልግ፤ ወደፊትም ለሀገሬ ኢትዮጵያ መወዳደር ስለምፈልግ የተሻለ ልምድና ሰዓት ማስመዝገብ ይጠበቅብኛል፡፡

ታይላንድ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ለማግኘት አልሞከርሽም?
በስምንት ወራ ቆይታዬ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው ያገኘሁት፡፡ በሀገሩ ውስጥ ኢትዮጵያዊም፤ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ የንስሓ አባት ማግኘት አይቻልም፡፡ በዚህ ብዙ ተጎድቻለሁ፡፡

33atletካገኘሻቸው ዋንጫዎችና ሜዳልያዎች ለማኅበረ ቅዱሳን ማይጨው ማእከል፤ መቀሌ ለሚገኘው መካነ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለማይጨው ደብረ ስብሃት ቅድስት ሥላሴ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሰጥተሻል፡፡ ምክንያትሽ ምንድነው?
ሃይማኖቴን እንዳውቅ፤ ፈተና ቢገጥመኝ በትእግስት እንዳልፍ፤ የቅዱሳን አባቶቼን ተጋድሎና ስለ እምነታቸው የከፈሉት መሥዋዕትነት እንድረዳ በሕይወት እነሱን እንድመስል ስለረዱኝ፤ እንዲሁም በሥጋዊ ሕይወቴ በችግሬ ሰዓት የደረሱልኝ ሰለሆነ ባለውለታዎቼ ናቸው፡፡ ለውጤቴ ማማር የእነሱ ድርሻ ስላለበት ነው፡፡

በንግግርሽ ውስጥ ሁሌም ቅዱስ ጊዮርጊስን ትጠሪያለሽ ምሥጢሩ ምንድነው?
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሕይወቴ ውሰጥ ያደረገልንኝ ዘርዝሬ መጨረስ አልችልም፡፡ የሚገጥሙኝ ፈተናዎችን ሁሉ ያለፍኩት በእሱ አማላጅነትና ፈጥኖ ደራሽነት ነው፡፡ ከሕፃንነቴ ጀምሮ ገድሉን እየሰማሁ ነው ያደግሁት፡፡ ታይላንድ ከመጣሁ በኋላም ስሜን የልዳው ኮኮብ ብዬ ነው የሰየምኩት፡፡ ይህ ድፍረት ነው ልባል እችል ይሆናል ካለኝ ፍቅር የተነሳ ያደረገረሁት እንጂ በትዕቢት አላደረግሁትም፡፡

ስደትን እንዴት ትገልጪዋለሽ?
ኢትዮጵያዊነትህን፤ ሃይማኖትህን፤ ቤተ ክርስቲያንን፤ ባሕልህን፤ ሕዝብህን ታጣለህ፡፡ በሄድክበት ዝና ልታገኝ ትችላለህ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ቤተ ክርስቲያን ትናፍቅሃለች፡፡ እግዚአብሔር ይፍታህ የሚል በሌለበት ደስታ ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን አላማህን እስክታሳካ ተፈትነህ ማለፍ አለብህ፡፡ በጣም የሚገርምህ ለቤተ ክርስቲያን ያለህ ፍቅር በስደት ስትኖር ይጨምራል፡፡ የኔ የምለው ሰው ስለሌለ በትርፍ ጊዜ እመቤታችንንን፤ ቅዱስ ጊዮርጊስን እየተማጸንኩ ከእነሱ ጋር እነጋገራለሁ፡፡ በባእድ ሀገር ቋንቋዬ እነሱ ናቸው፡፡ በየቀኑ ማታ ማታ ጸሎት አድርጌ ከመተኛቴ በፊት መኖሪያዬ ካለበት የሕንፃ ማማ ላይ ወጥቼ ፊቴን ወደ ምሥራቅ አዙሬ ኢትዮጵያዊው አቡነ ተክለ ሃማኖት ሆይ ይፍቱኝ እያልኩ ወደ ክፍሌ እመለሳለሁ፡፡

እስቲ ከገጠመኞችሽ አንዱን አካፍዪን?

ማናጀሬ ልጇ ከትምህርት ቤት ለሦስት ቀናት ወደ ቤት ሳይመለስ ሲቀርባት ማታ ጸሎት እያደረግሁ መጥታ እባክሽ ልጄ ወደ ቤት ከመጣ ሦስተኛ ቀኑ ነው፡፡ ለምትወጂው አምላክሽና ለልዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለምኚልኝ ብላ ሻማ ሳበራ ስለምታይ ሻማ ይዛ መጥታ እራሷ ያበራችበት ጊዜ አልረሳውም፡፡

የወደፊት እቅደሽ ምንድነው?

ኢትዮጵያሀገሬን በዓለም አቀፍ ውድድሮች መወከልና ጥሩ ውጤት ማምጣት እፈልጋለሁ፤ ለዚህም ነው ጠንክሬ በመሥራት ላይ የምገኘው፡፡

የምታስተላልፊው መልእክት?
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖር፤ ማገልገል ለሥጋም ሆነ ለነፍስም የሚጠቅም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መልካም የሆነውን ሁሉ ዐቅፋ የያዘች ናት፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድጠጋ ከማር ከወተት የሚጣፍጠውን ቃለ እግዚአብሔር ትመግበናለች፤ ፈተናም ቢመጣ በእቅፍዋ ታስጠልለናለች፡፡ ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ የሚያሳጣንም አንዳች ነገር የለም ነው የምለው፡፡

በመጨረሻም ከጎኔ በመሆን ለረዱኝ ወላጅ እናቴና ቤተሰቦቼ፤ ለሰንበት ትምህርት ቤቴ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማኅበረ ቅዱሳን ማይጨውና ዐዲሸሁ ወረዳ ማእከላት፤ እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎች ለረዱኝ ሁሉ ምስጋና ይድረሳቸው፡፡+++

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...