2013 ኦገስት 15, ሐሙስ

፯. መናፍቃን የሚወገዙት እንዴት ነው?
የመናፍቃን አወጋገዝ ሂደት እንደ ኑፋቄው ዓይነት ነው፡፡ የኑፋቄው ዓይነት ምንድን ነው? የሚለውን ማጤን ይገባል፡፡ ይህም:-
  • የታወቀ ኑፋቄ፣ እና
  • እንግዳ ዓይነት ኑፋቄ
የታወቀ ኑፋቄ - ስንል
ሀ. ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጋር ተቃርኖው ግልጽና የማያሻማ የሆነ ኑፋቄ፣ እና
ለ. ከዚያ በፊት በአካባቢያዊም ሆነ በዓለም አቀፋዊ ጉባኤ የተወገዘ ኑፋቄ ማለታችን ነው፡፡
እንዲህ ያለ ኑፋቄ ይዞ ለሚነሣ ሰው አዲስ ነገረ ሃይማኖታዊ ውይይትና ውሳኔ አያስፈልገውም፡፡ የአርዮስን ኑፋቄ ይዞ ለሚነሣ ግለሰብም ሆነ ቡድን የኒቅያ ጉባኤ በየጊዜው ሲሰበሰብ አይኖርም፤ የንስጥሮስን ኑፋቄ ይዞ ለሚነሣም እንዲሁ የኤፌሶን ጉባኤ በየጊዜው አይሰበሰብም፡፡ በቀደመው ውግዘት እስከ ዕለተ ምጽአት የሚነሡት ሁሉ ተወግዘዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ግልጽ ተቃርኖ የያዘ ኑፋቄ ሁሉ በአጠቃላይ የተወገዘ ነው፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ኑፋቄ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም ያን ኑፋቄ የሚያራምደው ግለሰብ በትክክል ያን ኑፋቄ መያዝ አለመያዙን፣ የሚመለስ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ከተረጋገጠ በኋላ ያ ሰው ከቤተ ክርስቲያን መለየቱ (ማውገዙ) በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ወይም በአገረ ስብከት ደረጃ ሊፈጸም ይችላል፡፡
እንግዳ ዓይነት ኑፋቄ ሲባል ደግሞ በግልጽ ስህተቱ ይህ ነው ለማለት ቀላል ያልሆነና ጉዳዩን ከቤተ ክርስቲያን እምነት አንጻር በጥንቃቄ መመዘን የሚያስፈልገው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን የኑፋቄውን ምንነት፣ ነገረ ሃይማኖታዊ አንድምታውን፣ ጥልቀቱንና ስፋቱን በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ይህን የሚያደርጉትም በሳል የሆነ ነገረ ሃይማኖታዊ እውቀት ያላቸው ሊቃውንት መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የመጨረሻ ውሳኔውን የሚሰጠው የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

፰. መናፍቃን እንዴት ይመለሱ?

ከቤተ ክርስቲያን በኑፋቄ ተወግዘው (ይፋዊ በሆነ ውግዘትም ሆነ ራሳቸውን በኑፋቄ በመለየታቸው) የተለዩ ሰዎች እንዲመለሱ የቤተ ክርስቲያን ናፍቆቷና ምኞቷ ነው፡፡ እንዲወገዙ የሚደረገውም ከላይ እንዳየነው ለራሳቸው ለሰዎቹ ጥቅም ሲባል፣ ነፍሳቸው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን እንድትድን ለመርዳት ሲባል እንጂ እንዲጠፉ አይደለም፡፡ ስለሆነም የመመለሳቸው ዜና ታላቅ የምሥራች ነው፣ ከዚህ የበለጠ ደስታም የለም፡፡ ጌታችን በትምህርቱ የጠፋው ልጅ ሲመለስ ስለሆነው ነገር ሲናገር እንዲህ አለ፡- “አባቱ ለአገልጋዮቹ ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፣ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር፡፡” ሉቃ. 15፡22-24 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድ የጠፋ ልጇ ሲመጣ እንዲህ ደስ ይላታል፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በሰማይ ንስሐ ስለሚገባ አንድ ኃጥእ ደስ ይሰኛሉ፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎችና ተግባሮችም አሉ፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያንን ከመጠበቅ አንጻር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ መናፍቃን የነበሩ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንመለሳለን ሲሉ ሊደረጉ የሚገባቸው ዋና ዋና ጥንቃቄዎችና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፡-
1. መመለሳቸው (ተመልሰናል ማለታቸው) የእውነት ነው? ከልብ ነው? ወይስ ለስልትና ለዘዴ ነው?
ቤተ ክርስቲያን እስካሁን በተጓዘችባቸው ዘመናት ሁለቱም ዓይነት ሰዎች በየጊዜው ሲገጥሟት ነበር፤ እነዚህም በአንድ በኩል በእውነት ተጸጽተው የሚመለሱ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ከልባቸው ሳይመለሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተመልሰው በመግባት ብዙ ምእመናንን ለመበረዝና ለማታለል ያመቻቸው ዘንድ በተንኮል ተመልሰናልና ተቀበሉን የሚሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ተመልሰናል ስላሉ ብቻ ዝም ብሎ መቀበል የዋህነት ሳይሆን ጅልነት ስለሆነ በሚገባ ማጣራትና መጠንቀቅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
በኒቅያ ጉባኤ በቅዱሳን አባቶች ተወግዞ የተለየው አርዮስና የኑፋቄ ጓደኞቹ የተለያዩ ሰዎችን በመላክና በውስጥ ለውስጥ በሠሩት የፕሮፓጋንዳ ሥራ በመጨረሻ ላይ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አርዮስን ከፈረደበት ከግዞቱ እንዲወጣና ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲመጣ አደረገው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም እምነቱን በጽሑፍ እንዲያቀርብ አዘዘው፡፡ አርዮስም በፊት የፈጠራቸውን የኑፋቄ ቃላትና ሐረጎች ሁሉ፣ እንዲሁም የተወገዘባቸውን የክህደት አንቀጾች ሁሉ ለጊዜው ወደ ጎን ትቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ያሉና ማንም ሰው ሊቀበላቸው የሚችላቸውን ነገሮች ብቻ ጽፎ “በፊትም ቢሆን ከዚህ የተለየ ሃሳብም ሆነ እምነት አልነበረኝ፣ አሁንም የማምነው ይህን ነው” በማለት ፈርሞ፣ በመሐላ አጽንቶ ሰጠው፡፡ ያ አርዮስ ጽፎ የሰጠው አንቀጸ እምነት እነርሱ (አርዮሳውያን) በፈለጉት መንገድ ሊተረጉሙትና የያዙትን አርዮሳዊ እብደት በቀላሉ በማያጋልጥ መልኩ በፈሊጥ ተሸፍኖ የቀረበ ማታለያ ነበር፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ግን እንዲያ ሲያደርግ ሲያየው አርዮስ በእውነት የተመለሰና ኦርቶዶክሳዊ የሆነ መሰለው፡፡
ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አርዮሳውያን የነበሩ ጳጳሳት አርዮስ በይፋ መጀመሪያ በተወገዘበት በእስክንድርያ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገባና ከምሥጢራት እንዲካፈል የሚል ደብዳቤ ንጉሡ እንዲጽፍላቸው አደረጉና ያን ደብዳቤ ከዛቻና ከማስፈራሪያ ጋር ወደ ቅዱስ አትናቴዎስ ወደ እስክንድርያ እንዲላክ አደረጉ፡፡ ለየአብያተ ክርስቲያናቱም አርዮስና ጓደኞቹ ኦርቶዶክሳውያን መሆናቸውን ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ የመሰከረላቸው ስለሆነ፣ በሲኖዶስም የተወሰነ በመሆኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ወደ ሱታፌ ምሥጢራት ይቀበሏቸው ዘንድ በጥብቅ የሚያሳስብ ደብዳቤ በፍጥነት ላኩ፡፡ የአርዮስ ቀኝ እጅ የነበረው አውሳብዮስ ዘኒቆምድያ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በደብዳቤው ላይ ቅዱስ አትናቴዎስን “ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመለሱ የሚፈልጉትን ሁሉ የማትቀበል ከሆነ እኔ ራሴ ሰው ልኬ ከመንበርህ አወርድሃለሁ” የሚል ዛቻ እንዲላክበት አደረገ፡፡ ብዙ ጊዜ ከታሪክ ስናይ መናፍቃን የፖለቲካ ሰዎችንና ባለ ሥልጣናትን በመዘወርና ከጎናቸው በማሰለፍ በኩል ጠንካሮችና የተሳካላቸው ናቸው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ግን “የክርስቶስ ጠላት የሆነው አርዮስና ኑፋቄው ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ምንም ኅብረት የላቸውም” በማለት በጉባኤ የተወገዘውን አርዮስን በንጉሥ ቀላጤ አልቀበልም አለ፡፡ የቅዱስ አትናቴዎስ ስለ ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት ከአርዮሳዊ ክህደት አቀንቃኞችና ደጋፊዎች ጋር የገባው እልህ አስጨራሽ ትግል በዚህ ሁኔታ እየጠነከረ ሄደ፡፡ ከመንበሩ ስድስት ጊዜ እንዲሳደድና ከአርባ አምስት ዓመት ዘመነ ፕትርክናው አሥራ ሰባት ዓመቱን ያህል በስደትና በእንግልት እንዲያሳልፍ ያደረገው ይህ የአርዮሳውያን ተንኮልና ዘመቻ ነበር፡፡
በአጠቃላይ አርዮሳውያን ያን ንጉሡ ከግዞት መመለሱን እንደ መልካም ካርድ በመጠቀም ከዚያ ቀጥሎ በነበሩት ሃምሳ ዓመታት ያህል ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ሲያውኳትና ሲፈትኗት ኖረዋል፡፡ ነገሥታትን ሳይቀር ከጎናቸው እያሰለፉ ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳትንና ካህናትን ከየመናብርታቸውና አብያተ መቃድሳቸው እያሳደዱ እነርሱ ሲፈነጩባቸው ኖረዋል፡፡ ነገሩ የማታ የማታ እውነት ይረታ ሆነ እንጂ፡፡
ስለዚህ ዛሬም እንመለሳን የሚሉት ሰዎች በትክክል ከልባቸው ነው? ወይስ እንደ ግብር አባቶቻቸው እንደ አርዮሳውያን ውስጥ ገብተው ለመበጥበጥ ነው? የሚለውን በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ “ታሪክ የሚያስተምረው ሰዎች ከታሪክ አለመማራቸውን ነው” የተባለው እንዳይደርስብን ማሰብ ይገባል፡፡ “በሬ ሆይ፣ ሣሩን አየህ እንጂ ገደሉን ሳታይ” እንደ ተባለውም እንዳይሆን እያንዳንዱ ምእመን፣ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ሊያስቡበትና ተገቢውን ነገር ሊያደርጉበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
2. ጉዳዮችን በቡድን ወይም በጅምላ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሰው ደረጃ መመልከትና መለየት፣
እንመለሳለን የሚሉትን ወገኖቻችንን ጉዳያቸውን በእያንዳንዳቸው ማየትና ማጥናት ይገባል እንጂ በጅምላ ከዚህ ወዲያ ወይም ከዚያ መለስ ብሎ ማድረግ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር የሚፈርደው በእያንዳንዱ ሰው እንጂ በቡድን ወይም በጅምላ አይደለም፤ “እስመ አንተ ትፈድዮ ለኩሉ በከመ ምግባሩ - አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ታስረክበዋለህና” እንደ ተባለ፡፡ መዝ. 61፡ እንዲሁም “እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ተብሏልና። ሮሜ 14፡12 ስለሆነም እያንዳንዱን በየግለሰቡ ጥፋቱ ምን አንደ ነበር፣ ለምን እመለሳለሁ እንዳለ፣ ወዘተ በዝርዝር ማጥናትና መወሰን ይገባል እንጂ “እነ እገሌ” በሚል የጅምላ ንስሐ የለምና ይህን ማስታወሱም ተገቢ ነው፡፡
3. ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ (እንዲያፈነግጡ) ያደረጓቸውን ምክንያቶች በሙሉ እንዲዘረዝሩ ማድረግና መመዝገብ፣
አንድ ሰው ዳነ ሲባል ታምሞ የነበረ መሆኑ፣ ተመለሰ ሲባል ደግሞ ወጥቶ ወደ ሌላ ሄዶ የነበረ መሆኑን ያጠይቃልና እንመለሳለን የሚሉት ሰዎች እያንዳንዳቸው ቀድሞ እንዲወጡ ያደረጋቸው ምክንያት ምን እንደ ነበረ በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ በሽታውን ደብቆ እንዲሁ አክሙኝ እንደሚል ሰው መምሰል ይሆናል፡፡ ይህን ማድረግ ግን እንመለሳለን ለሚሉት ሰዎችም፣ ለማኅበረ ምእመናኑም ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፡፡ ያን ኑፋቄ እንደገና ሲያስተምሩ ቢገኙ ማንነታቸውን በግልጽ ለመለየት ይጠቅማል፤ አለበለዚያ “ሞኝን እባብ ሁለት ጊዜ ነከሰው” (መጀመሪያ ሲያይ፣ ሁለተኛ ደግሞ ሲያሳይ) እንደ ተባለው ይሆናል፡፡
4. መመለሳቸውን፣ እንዲሁም ከምን ዓይነት ስህተት እንደ ተመለሱ ለሕዝቡ በይፋ መነገር ይኖርበታል፡፡
መናፍቃን ሲመለሱ በጓዳና ለሌሎች በማይታወቅ ሁኔታ ሳይሆን በግልጽ፣ ምእመናን ሁሉ በሚሰሙበትና በሚያውቁበት መድረክ በይፋ መሆን አለበት፡፡ በፊት የካዱትና ቤተ ክርስቲያንን ያሳጡትና የነቀፉት በይፋ እንደ ነበር ሁሉ ሲመለሱም በይፋ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ስለ መናፍቃን አመላለስ በጻፈው ቀኖና ላይ እንዲህ ይላል፡-


“በማንኛውም መንገድ ቢሆን ከኑፋቄ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመለሱ ሰዎች ምእመናን ባሉበት መሆን አለበት፤ ወደ ምሥጢራት ሊቀርቡ የሚገባቸውም እንዲህ ባለ ይፋዊ ሁኔታ ካለፉ በኋላ ብቻ ነው፡፡” ቀኖና ዘቅዱስ ባስልዮስ፣ ቁ. 1
እንዲህ ካልሆነ ብዙ ችግር ያስከትላል፡፡ እንዲህ ማድረግ ለአጭበርባሪዎችና ለተንኮለኞች መጠቀሚያ ሰፊ በር ይከፍታል፡፡ ነገ ተመልሰው ያንኑ ዓይነት ችግር እንዳይፈጥሩ በይፋ መነገሩ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ አለበለዚያ ውስጥ ውስጡን ምእመናንን እየበከሉ ላለመቀጠላቸው ዋስትና አይኖርም፡፡ መመለሳቸው በይፋ ከተደረገ ግን የቀድሞ ኑፋቄያቸውን እናስተምራለን ቢሉ እንኳ “ተመልሰናል ብላችሁ አልነበረምን? የቀድሞ ስህተታችንን ትተናል ብላችሁ አልነበረምን?” ብሎ ለመጠየቅና በቶሎ ማንነታቸውን ለማወቅ ይረዳል፡፡
5. ከጥንት ጀምሮ የተነሡ የተለያዩ የኑፋቄ መሪዎችንና ዋና ዋና መናፍቃንን በጥንቃቄ ከተዘረዘሩ በኋላ ማውገዝ ይገባቸዋል፣
የሚመለሱ መናፍቃን በእውነት ከመናፍቃን የተለዩና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጋር የተዋሐዱ ስለ መሆናቸው አንዱ ምስክር የሚሆነው ከቀድሞ ጀምሮ የተነሡ ዋና ዋና የኑፋቄ አመንጪዎችን በይፋ ማውገዝ ነው፡፡ ስለሆነም በጥንቃቄ በተዘጋጀ የመናፍቃን ዝርዝር ላይ እነዚያን መናፍቃን ማውገዝና ለዚህም መፈረም ይኖርባቸዋል፡፡
6. እስከ ዛሬ ድረስ በስብከቶቻቸውና በመጻሕፍት ያስተማሯቸውንና የጻፏቸውን የኑፋቄ ትምህርቶች ሁሉ ቀድሞ ኑፋቄው ከተላለፈበት ልሳን ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ እንዲያወግዙና ስህተት መፈጸማቸውን ተቀብለው ከአሁን በኋላ እንደዚያ ዓይነት የስህተት ትምህርት እንደማያስተምሩ በጽሑፍ ቃል መግባት ይኖርባቸዋል፡፡
የስህተት ትምህርቱን በመጽሐፍ ወይም በቪሲዲ ወይም በካሴት እና በመሳሰለው ያስተላለፈ ሰው ስህተቱን ሲያምንና ወደ እውነት ሲመለስ የቀደመውን አስተምህሮውን ስህተትነት መግለጽ የሚገባው በዚያው የስህተት ትምህርቱን ባስተላለፈበት መንገድ (ልሳን - ሚዲያ) ነው፡፡ አለበለዚያ ተደራሽነቱ ተመጣጣኝ አይሆንም፡፡ የስህተት ትምህርቱን በመጽሐፍ የጻፈ ሰው በቃሉ “አጥፍቼ ነበር፣ አሁን ተመልሻለሁ” ቢል መመለሱንና የቀድሞውን አስተምህሮውን ስህተትነት ማመኑን የሰሙት በተናገረበት ጊዜና ቦታ የሚገኙት ሰዎች ብቻ ናቸው፤ ሌሎቹ ግን በመጻሕፍት የተጻፈውን ኑፋቄውን እንጂ በቃል የተናገረውን የሚያውቁበት መንገድ የለም፡፡ እንዲሁም በቃሉ ብቻ “ያ ቀድሞ ያልሁት ስህተት ነው” ብሎ ቢናገር ያ ነገር ከአንድ ትውልድ ያለፈ ሊታወስና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ሊጠቀስ አይቻልም፣ መጽሐፉ ግን ለዘመናት ትውልድን እየተሻገረ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
ስለሆነም በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች አንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመለስ ሰው ቀድሞ የስህተት ትምህርቱን ካስተማረበት የሚዲያ ዓይነትና ተደራሽነት ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ መግለጽ ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ ቀድሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ ለብዙዎች መሰናከያ አድርጎ ያስተማረው እንክርዳድ መበከሉን እየቀጠለና ትውልድ እየተሻገረ ስለሚሄድ ስለ አንዱ ሰው መመለስ እንደምንጨነቀው ሁሉ ይህ ሰው በኑፋቄ ትምህርቱ ስላጠፋቸው ስለ ብዙዎቹም ማሰብ የግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ያ ሰው ያጠፋቸውን የብዙዎቹን ሰዎች ነፍሳት ረስተን ለአንዱ ብቻ የተጨነቅን መስሎን የምናደርገው ነገር ውስጡ ወይ አለመረዳት ወይም ደግሞ ሌላ ነገር እንዳይሆን ማሰብ ይገባል፡፡
7. በእርሱ የኑፋቄ ትምህርት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የወጡትን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ይኖርበታል፡፡
ኑፋቄውን በማስተማሩ ምክንያት ለብዙዎች ከቤተ ክርስቲያን መውጣት ምክንያት የሆነና በነፍሳቸው እንዲሞቱ ያደረገ ሰው ሲመለስ በመጀመሪያ እነዚያ ያጠፋቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ይኖርበታል፡፡ መርቅያን የተባለው መናፍቅ ብዙ ሰዎችን ካጠፋና የራሱን አንጃ መሥርቶ ከኖረ በኋላ በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ በኑፋቄው ተጸጽቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ልመለስ ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከሁሉም አስቀድሞ በመጀመሪያ ማድረግ እንዳለበት የነገሩት ነገር ቢኖር ወደ ስህተት የመራቸውን ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመልስ ነበር፡፡ ያን ለማድረግ በመሯሯጥ ላይ እያለ ታመመና ሞተ፡፡ ይህ በየዘመናቱ እንመለስ ሲሉ በነበሩ ሰዎች ላይ ሲፈጸም የኖረ ቀኖና ነው፡፡ ሽዎችን አጥፍቶ አንድ እርሱ ብቻ ቢመለስ እግዚአብሔር ስለ ጠፉት ስለ ብዙዎቹ ግድ የለውምን? እንዲህ የሚያደርጉትንስ ዝም ብሎ ይመለከታቸዋልን? ስለዚህ ይህን ጉዳይ መዘንጋት አይገባም፣ ለመጥፋታቸው ምክንያት የሆኗቸውን ሰዎች (በእነርሱ ምክንያት የጠፉትን ሁሉንም ለይቶ ማወቅ ባይቻልም እንኳ) ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግና መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡


8. እያንዳንዳቸውን በኦርቶዶክሳዊ መንገድ የሚመራቸው በነገረ ሃይማኖት በሳል የሆኑ አባቶችን መመደብ፣
ኦርቶዶክሳዊነት ከሁሉም በላይ እሳቤው፣ መንፈሱ እንዲገባቸውና እንዲሠርጻቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርቷን ሳያውቁ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊ እሳቤና እይታ እንዲሁም መንፈስ ሳይኖራቸው በሌላ ቅኝት መንፈስ የኖሩ ሰዎች እንደ መሆናቸው እንመለስ ስላሉ ብቻ አብሯቸው የኖረውና የሠረጻቸው የኑፋቄ ትምህርትና መንፈስና እንዲሁ በአንድ ጊዜ ውልቅ ብሎ የሚወድቅ አይደለም፡፡ የያዛቸው የኑፋቄ መንፈስ እንዲለቃቸው፣ እርሾው ጭልጥ ብሎ እንዲጨለጥላቸው ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ጀምበር የሚፈጸም አይደለም፡፡ ጌታችን “ዝንቱ ዘመድ ኢይወጽእ ዘእንበለ በጾም ወበጸሎት - ይህ ዓይነት አብሮ አደግ ክፉ መንፈስ ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም” እንዳለ፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሃይማኖታዊ መንፈስንና እይታን፣ ኦርዶክሳዊ አስተምህሮንና በአጠቃላይ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ምን እንደሆነ በበሰለ እውቀት፣ በእውቀት ብቻም ሳይሆን በሕይወት የሚያስተምራቸው በሳል አባት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቆዳ በማውለቅና ልብስ በመቀየር ብቻ ከኑፋቄ ወደ ኦርቶዶክሳዊነት መመለስ አይቻልም፡፡
ባለፉት የቅርብ ጊዜያት (በ1990ዎቹ ዓመታት) በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ካጣራ በኋላ በሃይማኖት ችግር (በተሐድሶነት) የተጠረጠሩትን ወደ አንዳንድ ቦታዎች ሄደው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲማሩ ተብሎ ነበር፡፡ ከእነዚያ ለቀኖና ተብለው ከተላኩት መካከል ግን አጋጣሚውን ሌላ ጥፋት ለመሥራት እንደ ምቹ አጋጣሚ የተጠቀሙበት ነበሩ፡፡ ከዚህም የተነሣ እየተማሩ ይቆዩ ተብለው ከተላኩት መካከል ሌሎችን የቤተ ክርስቲያን አባቶች አስክደው ወደ እነርሱ የጥፋት መንገድ ለማስገባት የተጠቀሙበት ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ የፕሮቴስታንታዊ ትምህርቶችን በተለያዩ መንገዶች ለማስፋፋት ሲሞክሩ የተደረሰባቸው ነበሩ፡፡ ስለዚህ ያን ጊዜ እንደ ተደረገው እንዲሁ ሁለት ሁለት እያደረጉ ወደ ሆነ ገዳም ወይም ቦታ መላክ ብቻውን ሰዎቹን አይለውጣቸውም፡፡ ስለዚህ በዚህም ከፍተኛ ሥራና ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ “ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል” እንደሚባለው እንዳይሆን፡፡
9. የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ የሚቀበሉ ስለ መሆናቸው ግልጽና ጠንቃቃ የሆነ ቃለ ጉባኤ አዘጋጅቶ እንዲፈርሙ ማድረግ
ይህም አስፈላጊ ነው፡፡ የሰው ነገር ነገ የሚሆነው ስለማይታወቅ ለወደፊቱም ጥሩ መሠረትና ማስረጃ፣ ምስክርም ይሆን ዘንድ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮና ሥርዓት ያለ አንዳች ቅሬታ የሚቀበሉ ስለመሆናቸው ቃለ ጉባኤ ተይዞ በሚዘጋጅ ወረቀት ላይ መፈረም ይኖርባቸዋል፡፡
10. ቀኖና መስጠት - (በመድረክ ላይ ይቀጥላሉ ወይስ አይቀጥሉም?)
ይህ ለአባቶች የሚተው ጉዳይ ቢሆንም እዚህ ላይ ያነሣነው እንዲሁ ለትምህርት ያህል ግን አስፈላጊነቱን ሳይጠቅሱ ማለፍ አይገባም በሚል ነው፡፡ እንዲያውም ፍትሐ ነገሥታችን ለሌላው ሰው ክህደት ምክንያት የሚሆን ሰው ሲመለስ ቀኖናው ከበድ ያለ እንዲሆን ያዝዛል፡-
“ወለዘኢአከሎ ክሕደቱ ባሕቲቱ እስከ ያወጽኦ ለካልኡ እምሃይማኖቱ ወኮነ ምክንያተ ለክህደቱ ይኩን ንስሓሁ ፈድፋደ - የራሱ ክህደት ብቻ አልበቃው ብሎ ባልንጀራውን ከሃይማኖቱ እስኪያወጣው ድረስ ለመካድ ምክንያት ቢሆን ንስሓው ጽኑዕ ይሁን፡፡” አንቀጽ ፳ ቁ. ፯፻፷
ከዚሁም ጋር ገና ተመለስን እንዳሉ “በዚያው በለመድነው ማስተማራችንን እንቀጥላለን፣ ከመድረክ አንወርድም የሚሉ ከሆነም ሌላ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በመጀመሪያ አንድ ሰው ቀኖናውን ሳይጨርስ እንዲያ ማድረግ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ አንድ በኑፋቄ የነበረ ሰው እንዲሁ “ተመልሻለሁ” ስላለ ብቻ በውስጡ የነበረው ኑፋቄ በአንድ ጊዜ በተአምራት በኦርቶዶክሳዊ ትምህርት አይሞላም፡፡ ስለዚህ በመድረክ እቀጥላለሁ ካለ የሚያስተምረው ያንኑ ከመመለሱ በፊት ሲያስተምረው የነበረውን የቀድሞ የስህተት ትምህርት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ከየት ያመጣል? ጌታችን “ኄር ብእሲ እምሠናይ መዝገበ ልቡ ያወጽኣ ለሠናይት ወእኩይሰ ብእሲ እምእኩይ መዝገበ ልቡ ያወጽኣ ለእኪት እስመ እምተረፈ ልብ ይነበብ አፍ - በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና፣ መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል” እንዳለ፡፡ ሉቃ. 6፡45
ታዲያ በኑፋቄ የኖረና ልቡ በዚያ ተሞልቶ፣ ከዚያ ውስጡን ከሞላው ኑፋቄ ለሌሎችም ሲናገር የኖረ ሰው ተመልሻለሁ ስላለ ብቻ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮና መንፈስ በአንድ ጊዜ ውስጡ ይመላበታልን? ይኽ ጌታችን ካስተማረው ትምህርት ጋር የማይሄድ ስለሆነ በሚገባ ሊጤን ይገባዋል፡፡ ተመልሰናል የሚሉት ሰዎች መመለሳቸውና ንስሐቸው የእውነት መሆን አለመሆኑ የሚገለጥበትና የሚፈተንበት አንዱ መንገድም ይኽ ነው፤ የተመለሱት በእውነት ከሆነ ግድ እናስተምር፣ በመድረክ እንቀጥል አይሉም፤ ነገር ግን የተንኮልና የስልት ከሆነ መድረኩ ላይ ካልቀጠልን ብለው የሙጥኝ ይላሉ፡፡
በዚህም ላይ አንድ በእውነተኛ መንፈስ ንስሐ የሚገባ ሰው በመጀመሪያ የሚያሳስበው ነገር እግዚአብሔርን በመበደሉ ይቅር እንዲለው፣ በደሉና ንስሓው እንጂ አሁንም መድረክ ላይ የመቀጠሉ ጉዳይ ሊሆን አይገባውም፡፡ እንመለስ የሚሉ ሰዎች ጭንቀታቸው መድረክ ላይ ስለ መዘመራቸውና ስለ መስበካቸው ከሆነ ጉዳዩ ዓላማን በውጭ ሆኖ ማስፈጸም ስለማይመች ወደ ውስጥ ገብቶ ተሐድሷዊውን ዓላማ ለማስፈጸም የአስገቡኝ ጥያቄ እንጂ የመመለስና የንስሐ ጥያቄ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይኼ የድርድር እንጂ የንስሓ መንገድ አይደለም፡፡ የእንመለሳለን ጥያቄው ትኩረቱ በመድረክ ላይ ስለ መዘመርና ስለ መስበክ ከሆነ ጉዳዩ በእውነትም የእድሜ ማራዘሚያና የተንኮል ስልት እንጂ በቅንነት የተደረገ የእንመለሳለን አካሄድ ሆኖ አይታይም፡፡
11. የሚደረጉትን እያዳንዳቸውን ነገሮች ሁሉ በከፍተኛ ጥንቃቄና ማስተዋል ማድረግ
የጠፉትን መቀበል ተገቢና መልካም ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሂደት የሚደረጉት እያንዳንዳቸው ነገሮች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቷ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ያላት ቁርጠኝነትና ድርጊቶቹ በኅብረተሰቡ ሥነ ልቡናዊና ሃይማኖታዊ አረዳድና መንፈስ ላይ ሸርሻሪ መሆን አለመሆናቸውን መጠየቅና በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ መናፍቃን የነበሩትን መቀበል የቤተ ክርስቲያንን እምነት መሸርሸር ተደርጎ እንዳይታይ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ አለበለዚያ አንዱን እገነባለሁ ሲሉ ሌላውን ማፍረስ እንዳይሆን፡፡
እነዚህ ነገሮች በሚሆኑበት ጊዜ የሕዝቡን አረዳድና ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ገና ለገና ለወደፊቱ ይጠቅማል በማለት በጊዜው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ውሳኔና ድርጊት ውስጥ መግባት አደገኛ ነው፡፡ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አርቆ ማየት ያስፈልጋል፣ ጭምብሎቻቸውን ገልጦ ትክክለኛ ማንነታቸውንና አደጋውን መረዳትና መለየት ያስፈልጋል፡፡
“ሰላም ሰላም” በሚል ቃል ብቻ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያንን ውሳጣዊ ሰላም፣ እንዲሁም ጊዜያዊ ችግር የፈታንና ያቃለልን ሲመስለን ለወደፊቱ ችግር እያወሳሰብንና እያቆላለፍን እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርብ ጊዜ በዘመናችን ከስድስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ በሆነችው በሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሆነውን አሳዛኝ ነገር ልንረሳው አይገባንም፡፡ በዋናነት በአንግሊካን ፕሮቴስታንት ቸርች (በእንግሊዝ ቤ/ክ) ቀያሽነትና አስፈጻሚነት በውስጣቸው ተፈልፍለው ያደጉት ተሐድሶዎች ገና ከመጀመሪያው ጉዳዩን የተረዱ አባቶችና ምእመናን ለይተው የማውገዝና የማጥራት ሥራ ሊሠሩ ሲሉ ተሐድሶዎቹ የእንመለሳን፣ የአስታርቁን ሽምግልና በተለያዩ ሰዎች በኩል ይልኩባቸው ነበር፡፡ በሽምግልናው ይሳተፉ የነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲሁ በሽፍኑ እርቅ ማን ይጠላል፣ ሰላም ምን ክፋት አለው በሚሉ መሸፈኛዎች የተታለሉና ምን እያደረጉ እንደሆኑ የማያውቁ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አስታረቁ ተብለው ስም ለማሰርና ጀብድ እንደ ሠሩ ለመቆጠር ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ራሳቸውን በአስታራቂነት ጎራ ሲመድቡ እነርሱ ከሌሎቹ የተሻሉ አስተዋዮችና ያላከረሩ ብልሆች እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥሩ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዋናዎቹ ከጀርባ ሽማግሌዎቹን የሚልኳቸውና በሽምግልናውም ውስጥ ዋናውን ሥራ ይሠሩ የነበሩት ጥቂቶቹ ግን ዓላማው ገብቷቸው ተሐድሶዎቹ በደንብ ሳይጠነክሩና ሳይጎለምሱ፣ ብዙዎችን ወደ እነርሱ ጎራ ሳይለውጡ እንዳይወጡ እንደ እድሜ ማራዘሚያ ስልት ለመጠቀም ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት ሳይወገዙ “እርቅ”፣ “ይቅርታ፣ “ንስሐ” እየተባለ ውስጥ ውስጡን ብዙ ካህናትንና ምእመናንን ከመለመሉና ከቀሰጡ በኋላ ራሳችንን የቻልንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለው ሲያስቡ መላዋን ቤተ ክርስቲያን መቆጣጠር ስላልቻሉ በይገባኛል የቤተ ክርስቲያኒቱን ነገር ሁሉ በፍርድ ቤት ተካፍለው ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውስጡን ተሐድሶ ያደረጓቸውን ካህናትና ምእመናን ይዘው በመውጣት የራሳቸውን የተሐድሶ ቤተ እምነት መሥርተዋል፡፡ እነዚህም “ማር ቶማ ቸርች” ይባላሉ፡፡ ምሥራቃዊ ፕሮቴስታንትም (Oriental Protestant) ይሏቸዋል፡፡ እርቁንና ሽምግልናውን እየተቀበሉ ተወግዘው እንዳይለዩ ሲደግፉና ሓሳብ ሲሰጡ፣ በጊዜው ጊዜ ተወግዘው እንዲለዩና ምእመናን እንዲያውቋቸው ለማድረግ ይጥሩ የነበሩ ጳጳሳትንና ምእመናንን እየለመኑና እያግባቡ “እርቅ፣ ሰላም፣ አንድነት” በሚሉ ቃላት ተታለው ሲያታልሉ የነበሩት ጳጳሳትና ምእመናን ግን የኋላ ኋላ ጥቅም የሌው ጸጸት ብቻ ነበር ያተረፉት፡፡ ነገሩ ጅብ ከሄደ ሆነባቸው፡፡
ስለሆነም ይህ ጉዳይ አንድ ጊዜ ከመቁረጥ በፊት አሥር ጊዜ፣ ካስፈለገም ከዚያም በላይ፣ መለካት የሚያስፈልገው ጠንካራ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁ በይሁን ይሁን፣ በምናለበት፣ ያለ ማስተዋልና ያለ አርቆ ማሰብ የሚደረግ ነገር በኋላ በእግዚአብሔርም ዘንድ፣ በትውልድም ዘንድ ያስጠይቃልና መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ይኼው የሕንድ ቤተ ክርስቲያን የደረሰባትን አሳዛኝ ነገር እኛ እያዘንን እንደምንጠቅሰው፣ ሌላውም ዛሬም ወደፊትም እንደ አሳዛኝ ታሪክ ማሳያ እያደረገ እንደሚጠቅሰው ሁሉ የእኛ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን በዚህ ጉዳይ ላይ ከፊታችን የሚሠሩት ሥራም በበጎም ሆነ በክፉ ተጠቃሽ ነው፡፡ ግን በአስተዋይነት የተሠራ መልካም ሥራ ሆኖ በበጎ ታሪክነትና በአስተማሪነቱ የሚጠቀስ ይሆን? ወይስ በስህተትና “በእነርሱ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ” በሚል ማስፈራሪያነት? ውጤቱን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ግን ከአፍንጫ ሥር ያለውንና ከፊት የቀረበውን ብቻ አሽትቶና አይቶ የሚወሰን ሳይሆን ወደ ኋላ ከዘመነ ሐዋርያት አንሥቶ የነበረው ታሪከ ቤተ ክርስቲያንና አስተምህሮን፣ አሁን ደግሞ ያለንበትን ጠቅላላና ዝርዝር ተጨባጭ ሁኔታ፣ ወደፊትም በእግዚአብሔርና በትውልድ ያለብንን ኃላፊነት ታሳቢ ያደረገ ቀኖናዊ ሂደት ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፣ እንዲኖርም እንፈልጋለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁላችንም ናትና እያንዳንዳችንም ችላ ሳንል፣ “እንዳረጉ ያድርጉት፣ እኔ ምን አገባኝ” ሳንል የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ቀኖናዊነት በጠበቀና ባገናዘበ መልኩ የየድርሻችንን እንወጣ፡፡
  • “ከወዳጆችህ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጠላቶችህም ጋር እንኳ ሳይቀር በሰላም ኑር፤ ነገር ግን እንዲህ የምልህ ካንተ ከግል ጠላቶችህ ጋር እንጂ ከእግዚአብሔርና ከቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ጋር አይደለም፡፡”አንድ ገዳማዊ አባት ለአንድ በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ላይ ለነበረ ሌላ አባት ከጻፈው መልእክት ላይ የተወሰደ
  •  “ሰውን ከእግዚአብሔር ከሚለየው አጉል ሰላም ይልቅ ከእግዚአብሔር የማይለየው ጦርነት ይሻላል፤ ስሜታዊ ከሆነና ለቤተ ክርስቲያን ዘለቄታዊ ጉዳት ከሚኖረው ስምምነትና አንድነት ይልቅ ስለ ሃይማኖት መጠበቅ ዘለቄታዊ ጠቀሜታ የሚኖረውና ለዚህ ሲባል የሚሆን አለመስማማት ይሻላል፡፡”
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ ትምህርት 2፡82

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...