2016 ጃንዋሪ 12, ማክሰኞ

በዲ/ን ታደሰ ወርቁ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ:“የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎውን ከፍታና የእናድሳለን ባዮቹን ዝቅጠት አመልክቶናል”(የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጥምረት)


  • ኑፋቄአቸውን የምንቃወምበት የአሸናፊነት መንገድ ሕጋዊ እና ኦርቶዶክሳዊ ነው
  • ጥርሳቸው ገጦ፣ ጥፍራቸው ፈጥጦ ወደ ሽፍትነት ሜዳ ለመውረድ ተገደዋል
  • ሐሳብን በግድያ ለማሸነፍ መሞከር የተናብልት እና የአረማውያን መንገድ ነው
  • ከዚህ የበለጠ መሥራት፣ ከዚህም የበለጠ መጋደል እንደሚያስፈልግ አሳይቶናል
  • ኹላችን እንደ አንዳችን፣ አንዳችንም እንደ ኹላችን ኾነን በአንድነት እንሥራ!!
*          *          *
Mmr Dn Tadesse Workuታኅሣሥ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ምሽት 2:35፤ ዲያቆን ታደሰ ወርቁን የያዘችው ዲኤክስ መኪና፣ ሽሮ ሜዳ አካባቢ አበጋዝ ሰፈር እየተባለ ወደሚጠራው የኪራይ ቤቱ ጠባብ መተላለፊያ አቅራቢያ አደረሰችው፤ ማኅበረ ጽዮን፣ በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘጋጀው ሳምንታዊ የሠርክ ጉባኤ ላይ አገልግሎ በመመለስ ላይ ነበር፡፡ መምህሩን የሸኘው የማኅበሩ አባል መኪናውን አዙሮ ሲመለስ፣ ዲያቆን ታደሰም ወደ ሰፈሩ በሚያስገባው የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ወደ ቤቱ በማምራት ላይ ነበር፡፡
የስፔን ኤምባሲን የኋላ አጥር ተከትሎ የሚገኘው ጠባቡ መተላለፊያ፣ ግራ እና ቀኙ በዛፎች እና በቁጥቋጦዎች በተሸፈኑ ወጣ ገባ መልክአ ምድራዊ ገጽታዎች መካከል የሚገኝ ሲኾን፣ በመሠራት ላይ ካለ መስጊድና ከሰፈሩ የዕድር ዕቃ ቤት በቀር በቅርበት ምንም የማይታይበት ነው፡፡ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት፣ ከግድያ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች የተፈጸመበት ቦታ በመኾኑም ለምሽት ጉዞ የሚያሰጋ ነው፡፡ ዲ/ን ታደሰም ወደ ውስጥ ዘልቆ የዕድር ቤቱ ግቢ ቀልቁል ከሚታይበት ዳገታማ ስፍራ ሲደርስ ነበር፣ የግድያ ሙከራው የተፈጸመበት፡፡
በመጀመሪያ ከኋላው ከቅርብ ርቀት በተሰነዘረ ሽመል መሳይ ነገር ማጅራቱ አካባቢ መመታቱን የሚናገረው ዲ/ን ታደሰ፣ ወዲያውም ኹለት ሰዎች በመካከላቸው አስገብተው አጥብቀው እንደያዙት ገልጿል፤ ብዙም ሳይቆይ አንዱ በፊት ለፊቱ በመቆም፣“የኛ የፀረ ተሐድሶ ገላጭ፤ አኹን እስኪ ማኅበሯ ታድንኅ እንደኾነ እናያለን፤ እንገድልሃለን” በማለት የፍራፍሬ መቁረጫ መሳይ ስለት ያወጣል፡፡
ስለቱን የተመለከተው ዲ/ን ታደሰም፣ ባለ በሌለ ኃይሉ ግለሰቡን ወደ ኋላው በመገፍተርና የድረሱልኝ ጩኸት በማሰማት፣ የዕድር ቤቱ ግቢ ቁልቁል ወደሚታይበትና የውጭ በሩ ተከፍቶ ወደነበረው ግቢ ሲንደረደር ተንከባልሎ ይወድቃል፤ ከወደቀበት እንደምንም ተነሥቶ የድረሱልኝ ጥሪውን እያሰማ ወደ ግቢው ሲገባም ተደነቃቅፎ ለኹለተኛ ጊዜ ይወድቃል፤ የግቢው ነዋሪዎችም ጩኸቱን ሰምተው ሲወጡ፣ ከዳገቱ የቀሩት ጥቃት አድራሾች ከአካባቢው ይሰወራሉ፤ ዲ/ን ታደሰም ከተጨማሪ የከፋ ጥቃት ተርፎ በነዋሪዎቹ ትብብር በሞባይል ስልኩ በመደወል ከቤተሰቡ ለመገናኘት በቅቷል፡፡
በጀርባው ካነገተው ቦርሳ በተጨማሪ በአንድ እጁ የሞባይል ስልኩን፣ በሌላ እጁ መጽሐፍ ይዞ የነበረው ዲ/ን ታደሰ፣ ከንብረቱ የጎደለ ነገር አለመኖሩን ገልጿል፡፡ የጥቃት አድራሾቹን ገጽታ ለመለየት የሚያስችል በቂ ብርሃን በሰዓቱ ባይኖርም፣ ዓላማቸው ግን የግድያ እንጂ የዘረፋ እንዳልነበር ዲ/ን ታደሰ ያስረዳል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የህልውናዋ ስጋት እንደኾነ በይፋ ዐውጃ እየተዋጋችው ያለችውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ እና ሤራ ለማጋለጥ እና ለማምከን፣ ከአምስት ዓመት በፊት በበጎ ፈቃድ ተሰብስቦ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት ግንባር ቀደም አገልጋዮች አንዱ በኾነው ዲ/ን ታደሰ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ዓላማ፣ በማስፈራራት ተጋድሎውን ለማስተሐቀር ያለመ ሊኾን እንደሚችል፣ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በፌስቡክ ገጹ ዘግቧል፡፡
ዲ/ን ታደሰ በመጠኑ እንደሚያስታውሰው፣ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮቹ፣ “ለዚያ ለያረጋል እንመጣለታለን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይህም ጥቃቱ በዲ/ን ታደሰ ብቻ የማይወሰንና ግቡም በኹነኛ የጥምረቱ አገልጋዮች ላይ ሽብር በመንዛት የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎውን ማክሸፍ እንደኾነ በጉልሕ አሳይቷል፡፡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን ዋነኛ ተዋንያን÷ የወቅቱን ቁመና፣ ስልት እና ሊወሰድ የሚገባውን መንፈሳዊ እና ሕጋዊ መፍትሔ በየቦታው በመረጃ አስደግፎ የሚያብራራው ዲያቆን ታደሰ፣ ይበልጥ የሚታወቀው፡- ዕቅበተ እምነትን ከተቋማዊ ለውጥ አስፈላጊነት ጋር በሚያቆራኙ ትምህርቶቹ ነው፡፡ በዕለቱ፣ በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ያስተማረውም “ኦርቶዶክሳዊ ብልጫ” በሚል ርእስ ነበር፡፡
ዲ/ን ታደሰ፡- በሰሜን፣ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ በሚገኙና የኑፋቄው ሤራ ጸንቶ በሚታይባቸው አህጉረ ስብከት ባለፉት አራት ወራት ብቻ በርእሰ ጉዳዩ ላይ በተዘጋጁ ከደርዘን በላይ ጉባኤያት ተሳትፏል፤ በጉጂ ሊበን ቦረና ሀገረ ስብከት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 18 እና 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በተደረገው ጉባኤ የተመዘገበው ውጤት ግና፣ ለተሞከረበት ግድያ እንደ ቅርብ ምክንያት እየተወሳ ይገኛል፡፡
ከዲ/ን ታደሰ ጋር በጉባኤው የተሳተፈው የጥምረቱ ተጠቃሽ አባል፣መ/ር ተስፋዬ ሞሲሳ፣ የነጌሌ ቦረና ከተማ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅልፍ አጥቶ የሚንቀሳቀስባት” እንደኾነች ጠቅሷል፡፡ የከተማው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያኑ ሕዋስ፣ ጉባኤውን ለማሰናከል፣በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕዝብየሚያበጣብጥ ፊልም ሊያሳዩ ነው” የሚል የስም ማጥፋት ውንጀላ ለዞን የመንግሥት አካላት እንዲደርስ አደርጎ ነበር፡፡
Tesfaye Mosisa Gubae BorenaMmr Ermias Assefa Gubae Borenaመ/ር ተስፋዬ ሞሲሳ(ከላይ)፤ መ/ር ዘማሪ ኤርሚያስ አሰፋ(ከታች) – በጉጂ ሊበን ቦረና ቅዱስ ገብርኤል ደብር
ይኹንና የደብሩና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ከጥቡዓን ምእመናን ጋር በአንድነት ተግተው በመቀስቀስ ከከተማው ውጭም በገጠር ቀበሌዎች የሚገኙ ካህናትና ምእመናን ሳይቀሩ በነቂስ በተገኙበት ጉባኤ፣ ባለሥልጣናቱ እና የጸጥታ አካሉም ጭምር እንዲታደሙ ተደርጓል፡፡ መምህራኑ÷ ዲ/ን ታደሰ ወርቁ እና መ/ር ተስፋዬ ሞሲሳ፤ መዘምራኑ መ/ር ኤርሚያስ አሰፋ እና ወ/ሪት ኑኃሚን ዘመድኩን በሚደነቅ መግባባት÷ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን ማንነት አጋልጦ ዕርቃን ያወጣ፤ ጉባኤተኛውን ያስቆጨ እና በእንባ ያራጨ፤ ለባለሥልጣናቱ እና ለጸጥታ አካሉም የኑፋቄውን አገራዊ አደጋ ያስገነዘበ አገልግሎት ለመስጠት ችለዋል፡፡
መ/ር ተስፋዬ በፌስቡክ ገጹ እንዳሰፈረው፣ ከከተማም ከገጠርም የመጡት ካህናት፣ ለየአጥቢያቸው ምእመናን ጉዳዩን እንደሚያስረዱ ቃል ገብተዋል፤ የሀገር ሽማግሌዎች በአካል ቀርበውና በስልክም እየደወሉ፣ “ለመፍትሔው ከእኛ የሚጠበቀውን የቤት ሥራ ስጡን” በማለት የሐሳብ ልውውጥ እያደረጉ ነው፤ በኑፋቄው ሕዋስ ተታለው የነበሩ ወጣቶች፣ “እኛ ቤተ ክርስቲያንን የጠቀምን መስሎን ሰለባ ኾነን ነበር፤ አኹን ግን በደንብ ተረድተናል፤” በማለት ከዚኽ በኋላ ደባቸውን ለማጋለጥ አቅማቸው በፈቀደ ከጥምረቱ ጋር በአጋርነት እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል፡፡
ይህንና ይህን መሰል ድሎች የተመዘገቡባቸውን ጉባኤያት፣ ከጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ አህጉረ ስብከት ሲያካሒድ የቆየው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት÷ “በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፉ ውሳኔዎች፣ በየቦታው እየተሰጡ ያሉ ትምህርቶች፣ በመረጃ እየቀረቡ ያሉ ማጋለጦች፣ ከሀገር ቤት እስከ ውጭ፣ ከገጠር እስከ ከተማ እየተደረጉ ያሉ አንድነትን የማጠናከርና ለቤተ ክርስቲያን ዘብ የመቆም እንቅስቃሴዎች ውጤት እያመጡ፣ የብርሃን መልአክ ይመስል የነበረው ሰይጣን ጥርሱ ገጦ፣ ጥፍሩ ፈጥጦ እንዲታይ እያደረገው ነው፤” ብሏል፡፡
ያለፉትን አምስት ዓመታት እንቅስቃሴውን በተከታታይ ዙሮች በመገምገም ለቀጣይ የላቀ አገልግሎት በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው ጥምረቱ፣ በዲ/ን ታደሰ ወርቁ ላይ ስለተፈጸመው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያኑ ቅጥረኞች ጥቃት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ÷ በእምነት ስም ተሸፍኖ የነበረው ትክክለኛ ማንነታቸው እንዲገለጥ ማስቻሉን ገልጿል፡፡ ይህም ምእመናን በኑፋቄው መደናገራቸው ቀርቶ፣ የገጠጠ ጥርሱን በተዋሕዶ መዶሻ ለማርገፍ፣ የሾለ ጥፍሩን በመንፈሳዊ ጉጠት ለመንቀል ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አስረድቷል፡፡
ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያኑ በእምነት እና በዕውቀት የበላይነት ድል ተደርገዋል፤ የውንብድና ጥቃታቸውም÷ የነብሩ ጅራት በሚገባ መጨበጡን ያረጋገጠ፤ የተጋድሎውን መንገድ እና ሊከፈል የሚችለውን መሥዋዕትነት ያመላከት የማንቂያ ደወል መኾኑን ጥምረቱ በመግለጫው አሳስቧል፡፡ ይህን በጎችን ሊበላ እና ሊያስበላ የመጣ ነብር ደግሞ መጨበጥ ብቻ ሳይኾን አድክሞ መግደል ስለሚያስፈልግ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች፣ ሊቃውንቱ፣ ገዳማውያኑ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ እና ምእመናኑበአንድነት እንዲነሡ ጥምረቱ ጥሪውን አቅርቧል – “በዲ/ን ታደሰ ወርቁ ላይ የተቃጣው ጥቃት በእኛም ላይ የተቃጣ ነው፤ ኹላችን እንደ አንዳችን፣ አንዳችንም እንደ ኹላችን ኾነን እንሥራ፤” ብሏል በመግለጫው ማጠቃለያ፡፡ የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚኽ በታች ቀርቧል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን

ቀን፡- 29/04/2008 ዓ.ም.
የተጋድሎው ከፍታ እና የእናድሳለን ባዮቹ ዝቅጠት
ከፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት የተሰጠ መግለጫ
በወንድማችን ዲያቆን ታደሰ ወርቁ ላይ በፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ቅጥረኞች፣ ታኅሣሥ 26 ቀን ምሽት በመኖርያ ቤቱ አቅራቢያ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ፣ ሦስት ነገሮችን አመልክቶናል፡፡ የመጀመሪያው፤ ተጋድሎው የደረሰበትን ታላቅ ደረጃ እና እናድሳለን ባዮቹ የወረዱበትን የከፋ ዝቅጠት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ አያሌ መናፍቃን ታይተዋል፡፡ የሐሳብ ክርክር ያደርጋሉ፤ በጉባኤ ቀርበው ይሟገታሉ እንጂ በሐሳብ ያሸነፋቸውን በግድያ ለማሸነፍ አይሞክሩም፡፡ ይህን ሲያደርጉ የኖሩት ተናብልት እና አረማውያን ናቸው፡፡ እነዚህ ግን ለአቅመ መናፍቅነት እንኳን አለመድረሳቸውንና በቀናችው እምነት ላይ የተነሡ ተራ ሽፍቶች መኾናቸውን እኩዩ ሥራቸው አሳይቷል፡፡
ኹለተኛው ደግሞ፣ እነርሱን ለመቃወም እና ለስሕተት ትምህርታቸው ተገቢ መልስ ለመስጠት በእኛ በኩል የተኬደበት መንገድ ኦርቶዶክሳዊ እና ሕጋዊ እንደኾነ አሳይቷል፡፡ የተነቀነቀው የኦርቶዶክስ ዘገር፣ የተወረወረው የተዋሕዶ ጦር መሬት ላይ አልወደቀም፤ የወጋውን ወግቷል!!
የሐሳብ ክርክሩን ድል አድርጎ ተከራካሪዎቹን ወደ ሽፍትነት ሜዳ እንዲወርዱ አስገድዷቸዋል፡፡ በዚህም በእምነት ተሸፍኖ የነበረው ትክክለኛው ማንነታቸው እንዲገለጥ አስችሏል፡፡ አይሁድም እንዲህ ነበር ያደረጉት፡፡ ጌታችንን በየጉባኤው ተገኝተው መከራከር፣ መሞገት እና መርታት ሲያቅታቸው፤ እውነትን ለመግደል ነበር የተነሡት፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስ አይሁድን በትምህርቱ ሲበልጣቸው በድንጋይ ወደ መውገር ነበር የዘመቱት፡፡
?
የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ዋነኛ አራማጆችንና አቀንቃኞችን የወቅቱን ቁመና የሚያጋልጠው ገለጻ ሲቀርብ
ሦስተኛው ደግሞ፤ ከዚህ የበለጠ መሥራት፣ ከዚህም የበለጠ መጋደል እንደሚያስፈልግ አመልክቷል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፉ ውሳኔዎች፣ በየቦታው እየተሰጡ ያሉ ትምህርቶች፣ በመረጃ እየቀረቡ ያሉ ማጋለጦች፣ ከሀገር ቤት እስከ ውጭ፣ ከገጠር እስከ ከተማ እየተደረጉ ያሉ አንድነትን የማጠናከር እና ለቤተ ክርስቲያን ዘብ የመቆም እንቅስቃሴዎች ውጤት እያመጡ፣ የብርሃን መልአክ ይመስል የነበረውን ሰይጣን ጥርሱ ገጦ፣ ጥፍሩ ፈጥጦ እንዲታይ እያደረገው ነው፡፡ ይህም ደግሞ ምእመናን በኑፋቄው መደናገራቸው ቀርቶ የገጠጠ ጥሩሱን በተዋሕዶ መዶሻ ለማርገፍ፣ የሾለ ጥፍሩን በመንፈሳዊ ጉጠት ለመንቀል ዕድል ፈጥሯል፡፡ በአጠቃላይ ትምህርቱንና መረጃውን በአሳማኝ ኹኔታ መቃወም ሲያቅት አማኙንና አስረጅውን ለመግደል መሞከር የተጋድሎውን ውጤት አመልካች ነውና የሚያበረታ ነው፡፡
አሁን የነብሩ ጅራት በሚገባ መጨበጡ ተረጋግጧል፡፡ ነብሩን አድክሞ መግደል ግን ያስፈልጋል፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክህነቱ የየእርከኑ ሓላፊዎች፣ ሊቃውንቱ፣ ገዳማውያኑ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ እና ምእመናኑ አንድ ኹነው ይህን በጎችን ሊበላና ሊያስበላ የመጣ ነብር ማድከም፣ አድክሞም እንዳይነሣ አድርጎ መግደል አለባቸው፡፡
እነርሱ የሠሩትን መሥራት ከባድ አይደለም፤ እንዲያውም የመጡት በቀላሉ መንገድ ነው፡፡ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይወስድም ብለን ተውነው እንጂ የመጡበትን መንገድ ከነርሱ በበለጠ እናውቅበት ነበር፡፡ ታላቁ አባት ሙሴ ፀሊም፣ በኣቱን ሊዘርፉ የመጡትን ሽፍቶች በያዛቸው ጊዜ÷ ‹‹ዐቅሙ ነበረኝ፤ እናንተ የሠራችሁትን መሥራት ግን ወደተውኹት መንገድ ስለሚመልሰኝ ተውኳችሁ›› ብሎ እንደ ለቀቃቸው፣ የተውነው ዐቅቶን ሳይኾን ወደማንፈልገው መንገድ ስለሚወስደን ብቻ ነው፡፡
አንድ በጌታው የተናደደ ውሻ ከሰውዬው ጋር ትግል ይገጥማል፡፡ ውሻው ከሰው ጋር በመኖሩ ውሻነቱን ዘንግቶ ነበርና እንደ ውሻ ትቶ እንደ ሰው በኹለት እግሩ ቆሞ በኹለት እግሩ የሰውየውን አንገት አነቀው፤ ሰውዬውም እንደ ዐቅሙ ታገለ፤ በመጨረሻም ውሻው ሰውዬውን በትግል አሸንፎ ጣለው፤ ሰውዬውም የሞት ሞቱን ይበረታና የውሻውን ጆሮ በጥርሱ ይነክሰዋል፤ ውሻውም ‹ጎሽ የረሳኹትን አስታወስከኝ› ይልና በጥርሱ ቦጫጭቆ ቦጫጭቆ ጣለው፤ ይባላል፡፡
Tekle Sawiros Sunday SchoolDn Tadesse Worku Debra Zeit
ለምን ወደዚህ የዘቀጠ ውንብድና እንደገባችሁ እናውቀዋለን፡፡ የሚቀርቡት ነገሮች ጠንከር እና ጠጠር አሉ፡፡ በመረጃ እና በማስረጃ ተጠናከሩ፡፡ ከስሜታዊነት ይልቅ ወደ መንፈሳዊነት፣ ከሞቅታ ይልቅ ወደ ዕውቀት አደሉ፡፡ በምድር የጠበቃችሁት ነገር በሰማይ መጣ፡፡ አይተባበሩም ብላችሁ ያሰባችኋቸው አካላት ሳይቀሩ ነገሩ አስተባበራቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ለቤተ ክርስቲያን የህልውና ስጋት መኾኑን በማመን አቋም ይዞና መዋቅር ዘርግቶ ተነቃነቀ፡፡ ይህን ስታዩ የማያዋጣችኹን የእምነት እና የዕውቀት ክርክር ትታችኹ ወደለመዳችኹት ውንብድና ወረዳችኹ፡፡ መንፈሳዊ እና ሕጋዊ ስላልኾነ እንጂ ‹‹ከመጣሽ ማርያም ታምጣሽ›› የሚሏችሁ ብዙዎች ነበሩ፡፡   
በፈጸማችሁት ውንብድና የሰጣችሁን መልእክት፣ ያላሰባችሁበትን ውጤት የሚያመጣ ነው፡፡ በወንድማችን ዲያቆን ታደሰ ወርቁ ላይ የቃጣችሁት ጥቃት፤ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአበው ካህናት፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት መስፋፋትና መጠናከር ሲሉ ዘብ በቆሙት ኹሉ ላይ የተቃጣ ነው፡፡ መንገዳችሁን አሳይቶናል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችንን ከጥቃት ለመታደግ ስንል ሕጋዊ የመከላከል አግባቦችን አሟጠን ለመጠቀም በኹሉም መስክ ተዘጋጅተን እንጠብቃችኋለን፡፡
መስቀል ተሰላጢን መያዝ ቀላል ነው፡፡ ለእኛ የማንቂያው ደወል÷ የተጋድሎውን መንገድ እና ሊከፈል የሚችለውን መሥዋዕትነት ስላሳየንኹላችን እንደ አንዳችን፣ አንዳችንም እንደ ኹላችን ኾነን እንሠራለን!!
የአባቶቻችን አምላክ በቀናች ሃይማኖታችን ያጽናን፤ አሜን፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...