2015 ዲሴምበር 27, እሑድ

የንግሥ በዓልና ልዩ ጉባኤ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት《 ከሠተ አፉሁ ወልሳኑ ነበበ አእኮቶ ወባረኮ ለእግዚአብሔር መልዐ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ተክለ ሃይማኖት 〉
በባር ዱባይ ”ሚካኤል“ ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ የተመለሱ ምእመናን የክብር አቀባበል ተደረገላቸው


በሊባኖስ የተባበሩት ዐረብ ዔሚሬቶች ና አካባቢው አህጉረ ስብከት በዱባይ ቅዱስ ቶማስና በአላይን ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል አቢያተ ክርስቲያናት የተካሄደው የ15 ቀናት ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጉባኤው ከኅዳር 24 ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 10 ቀን 2008 ዓ.ም የተካሔደ ሲሆን ካለፉት 7 ዓመታት ጀምሮ በየዓመቱ ልዩ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር በሀገረ ስብከቱ አዘጋጅነት ይከናወናል፡፡ በዚህ ዓመት የተከናወነው ጉባኤ ከምንጊዜውም የበለጠ ና የተለየ መሆኑን ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ያስረዳሉ፤ ለማሳያ እንዲሆን አንኳር ነጥቦችን ማቅረቡ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይኼውም፦
*ቁጥራቸው 30 የሚሆኑ ከባር ዱባይ ”ሚካኤል “አዳራሽ የተመለሱ ምዕመናን ይቅርታ በመጠየቅ ወደ እናት ቤተክርስቲያናቸው መመለሳቸው
*ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋት ና ሊወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ ጥናታዊ ጽሑፍ ለምእመናን በይፋ መቅረቡ
*ጉባኤው እንዲደናቀፍ ታቅዶ የነበረው የመናፍቃን ስውር ሤራ መክሸፋ
*በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሚያገለግሉ የአድባራት አስተዳዳሪዎች በጉባኤው ላይ መገኘታቸው ና ጠቃሚ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸው የተለየ ያደርገዋል፡፡
በተለይም በሐራ ጥቃ ተሐድሶ ዘመቻ ላይ ቱባ መረጃ ያካበተው ሰይፍ ዘክልኤ አፉሁ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ መጋበዙ እና ስለ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጉዳት ና አደጋ እንዲሁም ሊወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ በመረጃ የተደገፈ የምስል እና የድምጽ ማስረጃ ተጨባጭ ና አሳማኝ በሆነ መንገድ መቅረቡ ጉባኤውን ውጤታማ አድርጎታል ፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሀገረ ስብከት ትናንት ና ዛሬ
ከዓመታት በፊት በሊባኖስ ና አካባቢው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አህጉረ ስብከት በአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን፣በሻርጃ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተክርሰተቲያን ፣በቤይሩት ደብረ ሲና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ና
በየመን መስቀለ ብርሃን ቅዱስ ጊዮርጊስ አድባራት ብቻ አገልግሎቱ የተወሰነ ነበር፡፡ አሁን ግን በዱባይ እና አካባቢው ራስ አልኬማ ደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንና ዓላይን ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፤ በሊባኖስ ሰሜናዊ ክፍል ትራብሎስ ሐመረ ብርሃን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፤ ዝጋርታ ዳግማዊ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት እና በሰሜናዊ ምሥራቅ ዛህሌ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም አቢያተ ክርስቲያናት ተመሥርተዋል፡፡ እንዲሁም በቱርክ የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ በኳታር የቅድስት ሥላሴ ቤ ተክርስቲያን፣ በባሕሬን የኪዳነምሕረት ቤተ ክርሲቲያን፣ በባግዳድ ኢራቅ ና በኪዮት የአቡነ ተክለሃማኖት አቢያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፡፡ በመሆኑም የአድባራቱ ቁጥር ከ ዐራት ወደ ዐሥራ ስድስት ከፍ ማለት ችሏል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በስደት የሚገኙ ምእመናንን የሚያስተምሩ የሚመክሩ የሚያጽናኑ ንስሓን የሚሰጡ ና ቀድሰው የሚያቆርቡ አባቶችን መድቦ ተገቢው አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ለዚህ አገልግሎት የሚመደቡ አባቶችም እንደእየ ትምህርት ብቃታቸው ና መንፈሳዊ ሕይወታቸው አግባብነት እንጅ በትውልድና በአካባቢ በጎጠኝነት ና በቤተዘመድ ጉባኤ የተመደቡ አይደሉም፡፡
ሀገረ ስብከቱ አቢያተ ክርስቲያናትን በማስፋፋት ስብከተ ወንጌልን በሬዲዮ ና በማኅበራዊ መካነ ድሮች በማፋጠን የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማደራጀት ሰበካ ጉባኤን በማጠናከር ከእለት ወደ እለት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕያደገ መምጣቱ ሥራው ይመሰክራል፡፡ከቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ እየተጋበዙ የሚመጡ መምህራንም ከአብነት ትምህርት ቤቶች አስመስክረው የወጡ ና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ናቸው፡፡ከዚህ ጎን ለጎንም መንፈሳዊ ሕይወታቸው የተስተካከለ ሃይማኖታቸው የቀና መሆን አለመሆኑ ይገመገማል፡፡ በተለይ ከወቅታዊው ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ በሽታ መበከል አለመበከላቸው ተጣርቶ እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡ለምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ና ሁለንተናዊ ደኅንነት ትኩረት ይደረጋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለባት ወቅታዊ ተግዳሮት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ደባ መሆኑ የ አደባባይ ምስጢር ከሆነ ከረመ፡፡ ይህን ስውር ደባ ሀገረ ስብከቱ ቀደም ብሎ በመንቃቱ በስብከተ ወንጌል ተልዕኮ በሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት የተለየ ጥንቃቄ ና ክትትልይያደርጋል፡፡ይህ ተግባሩም ለወደፊትም ይቀጥላል፡፡ሀገረ ስብከቱ ከሚያከናውናቸው ወርኃዊ ጉባኤያት በተጨማሪ በየዓመቱ በአይነቱ ልዩ የሆነ ሁሉን አቀፍ ጉባኤ በዱባይ በአቡዳቢ እና በአላይን ያከናውናል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ይህንን ጉባኤ ማዘጋጀት ከጀመረ ድፍን ሰባት ዓመት አስቆጠረ፡፡ በዚህ ዓመትም ከምንጊዜውም በተለየ ሰባተኛ መደበኛ የስብከተ ወንጌል ዓመታዊ ጉባኤውን በዱባይና በዐላይን ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል አከናውኗል፡፡
ይህ ጉባኤ እንዳይካሄድ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡ ግን ዓላማቸው ሳይሳካ ጉባኤው በታሰበውና በተፈለገው መንገድ ተከናውኗል፡፡ በተለይ ቁጥራቸው ሠላሳ የሚሆኑ ከአንድ ዲያቆን ጋር በባር ዱባይ «ሚካኤል" ለበርካታ ዓመታት በመናፍቃን ትምህርት ተሰናክለው የነበሩ የዋሀን ምእመናን ወደ ቀደመ ቤታቸው በመመለስ ቤተክርስቲያንን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የሀገረስብከታችን ሊቀ ጳጳስም የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈው በክብር ተቀብለዋቸዋል፡፡ስሕተቱን ፈጽመው የነበሩ ምእመናንም በነበራቸው ቆይታ ደስተኛ እንዳልነበሩ በመግለጽ በባር ዱባይ “ሚካኤል” እየተሰጠ ያለው ትምህረት ፍጹም ክህደት የተሞላው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት ጋር የሚጋጭ መሆኑን በጉባኤው ፊት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በተባበሩተረ ዓረብ ኤሚሬቶች አህጉረ ስብከት የሚገኙ አድባራት ራሱን የቻለ ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመላቸው በአለቃ የሚመራ በሕጋዊ ሰነድ ወጭና ገቢው የሚመዘገብ እንጂ ማንም እንደፈለገ ከመዋቅር ውጭ የሚፈተፍትበት አሠራር የለም፡፡የአድባራቱ ገንዘብ በሓላፊነት ና በተጠያቂነት በሚመለከታቸው የሰበካጉባኤ ባለድርሻ አካላት ይቀመጣል፡፡ይንቀሳቀሳልም፡፡
ከኅዳር 24 ቀን እስከ 30/2008 ዓ.ም ድረስ ሁሉም የአድባራት አለቆች በመሰብሰብ በርካታ ውሳኔዎችን ወስነዋል፡፡ ከውሳኔው መካከልም ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት የጸረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ከሀገረ ስብከት እስከ ዐጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ በመዘርጋት በመዋቅር ታቅፎ ሥራውን እንዲሠራ ተወሰኗል፡፡ ሃይማኖት ካልደፈረሰ ምንጭ ይቀዳ ዘንድ ይገባልና ካህናቱና ምእመናኑ እጅ ለእጅ ተያይዘው መናፍቃንን መታገል እንዲገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ብፅዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአንድ ሀገረ ስብከት የሚገኙ ምእመናን ልጆቻቸውን ከመናፍቃን የመጠበቅ፤ ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት፤ ሰንበት ትምህርት ቤትን የማደራጀት፤ ሰበካጉባኤን የማጠናከር ፤ የመባረክ፤ የማስተማር ና የመጠበቅ ድርሻቸው ከማንም እና ከምንም በላይ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሊቃነ ጳጳሳቶቻችን በገንዘብ ከተደለሉ፤ ለራሳቸው ጥቅም ከቆሙ፤ ከቤተክርስቲያን ይልቅ ለግል ክብራቸው ከተጨነቁ ሥራችን ሁሉ ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎቹ የአባቶችን ደካማ ጎን እያጠኑ በቀሚሳችሁ ሥር ሊወተፋ ይጥራሉ፡፡ ሲፈልጉ በገንዘብ ለመደለል፤ ካልሆነም በከንቱ ውዳሴ ተብትበው ለመያዝ ያደባሉ፡፡ እናም ነቅተንባችኋል በሏቸው፡፡
የሀገረስብከታቸውን ክብር እና ልእልና ጠብቀው ያስጠበቁ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት አሉ፡፡ ስለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ደህንነት እየተሰደቡ እየተነቀፋ ናእየተዛተባቸው እንኳን ስድብ ሰይፍ ቢመጣ ሀገረ ስብከቴን ለነጣቂ ተኩላ ለሐራ ጥቃ ተሐድሶ አሳልፌ አልሰጥም ብለው መከራውን ታግሰው የሚያገለግሉ ሊቃነጳጳሳትን ክብር ያድልልን፡፡
መካከለኛው ምሥራቅን ለመረከብ ከምዕራቡ ዓለም የፕሮቴስታንት ድርጅት ጋር ውል የገባው ሐራ ጥቃ ሕልሙ አልተሳካም ፡፡ ለምን አልተሳካም ? መልሱ ግልጽና አንድ ነው፡፡ እሱም የተዋሕዶ አርበኛው የመናፍቃን መዶሻ ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ በራቸውን ዘግተው መንጋዎቻቸውን ከነጣቂ ተኩላ በመጠበቃቸው ነው፡፡ እናንተ እንደምትሉት ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ እንዲህ ወይም እንዲያ አይደሉም፡፡ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዝክረ አበው በሚለው መጽሔቱ የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ሕይወት አዘጋጅቶ አቅርቧል ፡፡ይህንን መጽሔት መሠረት በማድረግ የ ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስን ታሪክ ትንሽ እንዳስሳለን፡፡
ትውልድና ዕድገት
የቀድሞ ስማቸው መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረ ሚካኤል ኀይለ ማርያም ይባላል፡፡ የተወለዱት በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ኪሮስ በተባለው አካባቢ በቅዱስ ያሬድ ገዳም ልዩ ስሙ ጢቤላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አቅራቢያ ነው፡፡ሐራ ጥቃዎቹ ግን ፓለቲካዊ ዘዴ በመጠቀም የዘር ሐረጋቸውን ወደሌላ ለመምዘዝ ሞክራችኋል፡፡ ይኼ ግለሰብን ከግለሰብ ጋር ተቋምን ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር የምታጋጬበት አንዱ ስልታችሁ በመሆኑ ስለታወቀባችሁ አትድከሙ ከስራችኋል፡፡
ትምህርት
ከፊደል እስከ ዳዊት ከእኅታቸው ባለቤት ከቀሲስ ቡሩኬ ቦጋለ ተምረዋል፡፡ በቲበር ማርያም ከየኔታ ጥዑመ ልሳን ጸዋትወ ዜማ ተምረዋል፡፡ ከመ/ር ሙሴ መዝገብ ቅዳሴ ተምረዋል፡፡ ከመ/ር ብርሃኑ በደምቢያ ወረዳ ማክሰኝት ስጓጅ ጊዮርጊስ አቋቋም ቀጽለዋል፡፡ ከታላቁ ሊቅ መጋቤ ሀዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ቅኔ ተቀኝተዋል፡፡በ1982 ዓ.ም በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ገዳም ካህናት ማሰልጠኛ ገብተው ከየንታ ሐረገወይን አቋቋሙን አጠባብቀዋል፡፡ በዝዋይ ገዳም ቅኔ ከነአገባቡ ዝማሬ መዋሥዕትና ምዕራፍ ጾመ ድጓ መዝገብ ቅዳሴ ተምረዋል፡፡ የሥነ መለኮት ትምህርቱንም ለማጠናከር በዝዋይ ገዳም ካህናት ማሠልጠኛ ኮርስ ወስደዋል፡፡ በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለስድስት ዓመታት መጻሕፍተ ሐዲሳት ተምረው በዲፐሎማ ተመርቀዋል፡፡
በእርግጥ የቤተክርስቲያን ሙያ ወረቀት አለኝ በማለት ብቻ የሚታለፍ ሥራ አይደለም፡፡ማወቅ አለማወቁ በሂደት የሚገለጥ በተግባር የሚፈተን ሙያ ነው፡፡ ሲጀመር ከሐራ ጥቃዎች ጋር ስለ ዕውቀት ና የቤተክርስቲያን ሙያ መነጋገር ራስን ማውረድ ነው፡፡አንዱ የእናንተ ቡድን ባልተነቃበት በየዋሁ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቆመ አሉ፡፡ ታዲያ ውዳሴ ማርያም ሲታደል ይጀምሩ፤ ለሔዋን ተብሎ ለሐራ ጥቃው በአጋጣሚ ኢየሱስ ደረሰው፡፡ ቀጣዩን እንዳይጸልይ ከየት ያምጣው፡፡ ወዲያው ጌታ ነው ብሎ አረፈው አሉ፡፡ ሌላ ቀን ደግሞ አንዱ ዘመዳችሁ ሊቀጳጳሱ ባሉበት ራት ተበልቶ በል ልጀ ስብሐት ብለህ በዚያው መርቃቸው ብለው ያዙታል፡፡ ሰውየውም አይ ስብሐት ማለት ያለብዎትማ እርስዎ ነዎት ብሎ ሊቀ ጳጳሱን መለሰላቸው አሉ፡፡/አቤት ሲያሳፍር/ ታዲያ ከእናንተ ጋር ስለ ቤተ ክርስቲያን ሙያ ና ስለ ዕውቀት መነጋገር እንዴት ይቻላል፡፡ ዐረበኛን መቻል አለመቻል የዕውቀት ጉዳይ ነው? የኬኒያ ገበሬ እኮ ከስዋለኛ እኩል እንግሊዘኛን ሊናገር ይችላል፡፡ ታዲያ ይኼ ሰው ዐወቀ ወይስ ለመደ ነው ሚባለው? ጠይቃችሁ ለመረዳት ምትፈልጉት ዕውቀት ካላ ራሳችሁን አርማችሁ ከአዳራሽ ውጡ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን ብላችሁ የውርንጫ ድካም ከምትደክሙ ራሳችሁን ለውጡ፡፡ ሕይወታችሁንም አድሱ፡፡
ይኼን ሁሉ ዘመን በትምህርት ቤት አሳልፈው እያለ በየትኛው ጊዚ ወደ ሌላ ሙያ ገብተው ማዕረግ መቀበል ቻሉ? ተሐድሶዎች የኦርቶዶክሳውያን አባቶችን ስም ማጥፋት ተቀዳሚ ዓላማችሁ ስለሆነ ከእናንተ በጎ ነገር መጠበቅ አይቻልም፡፡
ማኅሌት ና ቅዳሴ በብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ ያምራል
ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ ባለፈው ዓመት ግንቦት ሚካኤልን ያከበሩት መርካቶ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ ማኅሌቱን ስቡሕ ብለው የጀመሩት ብፁዕነታቸው ነበሩ፡፡ ከጉሮሯቻው የሚወጣው ድምጽ እጅግ ጣእም ያለው ለመሁኑ ማኅሌታውያኑ ይመሰክራሉ፡፡ ማኅሌቱን ቁመው ቅዳሴ ቀድሰው በዓሉ ተከበረ፡፡ ታዲያ በማኅሌቱ አብሮ ያደረው አንዱ ሊቅ «ይኼ ድሜጥሮስ የሚባል ስም ሰው ይወጣለታል” አለ ተብሎ ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸውም ቢሆን ጠቅሰው ተርጉመው አመስጥረው ማስተማር ያውቁበታል፡፡ ይሄን እውነታ መመስከር ባትችሉ ዝም ብትሉ ምን አለበት፡፡ በአንድ ደብር የሚኖሩ የታወቁ ባለቅኔ ነበሩ አሉ፡፡ አንድ ቀን ቅኔ ሲቀኙ የሰማ አንድ ሰነፍ ተማሪ ሲወጡ ጠብቆ የኔታ የዛሬው ቅኔ ግሩም ነበር አላቸው አሉ፡፡ ሊቁም በስጨት ብለው የእኔን ቅኔ አንተ ከሰማኽውማ ምኑን ተቀኘሁት አሉ ይባላል፡፡ ብለው መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ሲተርኩ ሰምቻለሁ፡፡ ታዲያ እናንተ የሊቃውንቱን ትምህርት በቀላሉ ከተረዳችሁት ምኑን ትምህርት ሆነ? እስኪ ማኅሌታውያኑ የቅዱስ ያሬድ ልጆች ስለ ብፁዕነታቸው ይመስክሩ፡፡ የአብነት መምህራንን እየጋበዙ እንዲያስተምሩ እድሉን መስጠታቸው አንገበገባችሁ፡፡ ዝቋላ ገዳም የከተሙ አባቶችን በመርዳታቸው ቅር አላችሁ፡፡ ደብረሊባኖስ ገዳምን በመደገፋቸው ከፋችሁ፡፡ ደብረ ሐዘሎ ገዳምን በመከባከ ተሸማቀቃችሁ፡፡ ጸረ ሐራ ጥቃ የሆኑ ቀናእያን ወጣት ሰባኪያንንና የነገረ መለኮት ምሩቃንን በመጥራታቸው ከፋችሁ፡፡ የተዋሕዶ መካች የተሐድሶ ጸር ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ በምእመናን የሚወደዱ በአገልጋዮች የሚከበሩ አባት ናቸው፡፡ በረከታቸው ይደርብን፡
መዓርገ ክህነት
ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ በ1975 ዓ.ም በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ገዳም ከብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ዲቁና ተቀብለዋል፡፡ በልጅነት እድሜያቸው በሰሜን ራስ ዳሽን ተራራ ሥር ከሚገኘው ቅዱስ ያሬድ ገዳም የቀሰሙትን የመነኮሳት ሕይወት ወደ ተግባር በመለወጥ ፡በ1987 ዓ.ም በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ገዳም ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጽመዋል፡፡
ጵጵስና
በዐረብ ኤምሪቶች በዱባይ ሻርጃ አጅማን ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው ለሰባት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚያም በአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ዓመት ያህል እንዳገለገሉ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ና የዕውቀት ደረጃቸው ተገምግሞ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው ባልጠበቁትና ባላሰቡት መንገድ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተጠርተው መጡ፡፡ ለምን እንደተፈለጉ የነገሯቸው እንኳን በረከታቸው ይደርብን ና ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ሥልጣንን በመናቅ አይገባኝም ልቆይ ብለው ነበር ፡፡ ሆኖም በብፁዓን አባቶች ምክር እሺ እንዲሉ ተገደዱ፡፡በመሆኑም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ሐምሌ 9 ቀን 1998 ዓ.ም በሊባኖስ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶችና አካባቢው አህጉረ ስብከት ጳጳስ ተብለው ተሹመዋል፡፡
ዘረኝነት ብሎ ጣጣ?
በብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ዘንድ ዘረኝነት ብሎ ጣጣ በፍጹም የለም፡፡ ሙያው ከጋበዘው አገልግሎቱ ካስወደደው ከየትም ቢመጣ አውደ ምሕረቱ ክፍት መሆኑን ሲናገሩ ሰምቻለሁ ፡፡እናንተ ሐራ ጥቃ ተሐድሶዎች ግን ዘረኝነትን የተቃወማችሁበት መንገድ በራሱ ዘረኝነት ነው፡፡
ሀገረስብከቱ የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንጅ የተወሰነ ክልል ብቻ ባለመሆኑ፡ የብሔር ብሔረሰቦች ስብስብ ለማለት በሚያስችል መንገድ አገልጋዮች እንደ ሙያቸው ተመድበው ያገለግላሉ፡፡ለአብነት ያኽልም፦
የሻርጃ ሰ/ም/ ቅ/ማርያም አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት አባ ገሪማ አያልቅበት--------- የደብረ ብርሃን ተወላጅ
የአቡዳቢ ደ/ሰለም መድኀኔ ዓለም አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አባ ወ/ገብርኤል ብርሃነ-- የትግራይ ተወላጅ
የራስ አልኬማ ደብረ ይድራስ ቅ/ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አባ ገ/ሃና ታደሰ-- የወሎ ተወላጅ
የአላይን ደ/ኀይል ቅ/ገብርኤል አስተዳዳሪ መልአከ ኀይል አባ ገ/ማርያም ወ/ሳሙኤል---- የወልቃይት ተወላጅ
የባሕሬን ሐመረ ኖኅ ቅ/ኪዳነ ምሕረት አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት አባ ግርማ ወንድሙ--- የሸዋ ተወላጅ
የኳታር ጽርሐ አርያም አስተዳዳሪ መልአከ አርያም አባ ገ/መድኅን ወ/ ሳሙኤል ------------የአገው ሰቆጣ ተወላጅ
የቱርክ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ተ/ሳሙኤል ወ/ሳሙኤል ---የትግራይ ተወላጅ
የኪዮት ደብረ ምሕረት ተክለሃይማኖት አስተዳዳሪ ሊቀ ማእምራን አባ በርናባስ አበባው ---- የወሎ ተወላጅ
የቤይሩት ደ/ሲና ቅ/ገብርኤል አስተዳዳሪ መልአከ ስብሐት አባ ገ/ሥላሴ ረታ ---- የሐረርጌ ተወላጅ
የዝጋርታ ዳግማዊ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተ/ሃይማኖት አስተዳዳሪ መልአከ ገነት አባ ኀ/ጊዮርጊስ አዳሙ--- የሸዋ ተወላጅ
የዛህሌ ምስካየ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አባ ገ/እግዚአብሔር ኂሩተ አምላክ---- የወሎ ተወላጅ
የትራብሎስ ሐመረ ብርሃን ቅ/ኪዳነ ምሕረት አስተዳዳ ሪመልአከ ብርሃን አባ ገ/መድኅን ንጉሤ--------- የሸዋ ተወላጅ
የቤይረት ደብረ ሲና ቅ/ገብርኦል ካቴድራል ቄሰ ገበዝ መልአከ ምሕረት አባ ገ/ኪዳን እንየው -------------የወልቃይት ተወላጅ
የቤይሩት ደብረሲና ቅ/ገብርኤል ጸሐፊና ስብክተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ መጋቤ ሃይማኖት መ/ር ኅሩይ ባየ-- የጎንደር ተወላጅ
የቤይሩት ደ/ሲና ቅ/ገብርኤል አገልጋይ ሊቀ ዲያቆን ጸጋ ዘአብ ጌታነህ ------------------------------------- የአሰላ ተወላጅ ናቸው፡፡
በዓረቡ ዓለም የሚኖሩ በርካታ እኅቶቻችን በስነ ልቡናዊ ቀውስ እና በክፉ መንፈስ ይፈተናሉ፡፡ቤተክርስቲያንም ምስካየ ኅዙናን ስለሆነች በሥጋም በነፍስም መጠጊያችን በመሆኗ ሲታመሙ ይፈወሱባታል፡፡ ሲያዝኑ ይጽናኑባታል፡፡ ምክር ፈልገው አይዞሽ ባይ ሽተው ሲመጡ በትዕግሥት ተቀብሎ ጥምቀት ለፈለጉ ጥምቀት ምክር ለሚሹ ምክር የመስጠት ሓላፊነት የቤተክርስቲያን አባቶች መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ብፁዕ አባታችን አቡነ ድሜጥሮስም የልጆችን ችግር በውል ተገንዝበው ካዘኑት ጋር አዝነው ችግራቸውን አድምጠው ለሕመምተኞች ጸሎተ ቀንዲል አድርሰው ቅብዓ ቅዱስ ለምእመናን በይፋና በግልጥ በግንባራቸው ላይ ሊቀቡ ይችላሉ ፡፡ ይህን የማድረግ መንፈሳዊ ግዴታም አለባቸው፡፡ ይህን ሲያደርጉ አውሬው ተቆጣ በግብር ልጆቹ በእናንተ ላይ አድሮ ይሳደብ ጀመረ ፡፡አውሬው ቢቆጣ ቢሳደብ ና ቢዝት ወደ ኋላ አንልም፡፡ ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ መክፈል ያለብንን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁዎች ነን፡፡ውሾች ይጮኻሉ ግመሎች ይሄዳሉ፡፡
ስለ ስድቡ ምን እንበል?
ፈጣሪውን ፍጡር ያላችሁ
ተማላጁን ማላጅ ለማለት የደፈራችሁ
ጻድቃንን የረገማችሁ
ሰማዕታትን የጠላችሁ
ክብሯን አማላጅነቷን የማርያምን የካዳችሁ
በታቦቱ ያፌዛችሁ
በትውፊታችን የተሳለቃችሁ
ቤተክርስቲያንን ለምእራባውያን ለመሸጥ ያደፈጣችሁ
ከቶ ምን እንጠብቅ እኛ ከእናንተ የመርገም አፎች
የአርዮስ የንስጥሮስ የሉተር የግብር ልጆች                                                                                    
የዲያብሎስ ማደሪያ የእነ ሰባልዮስ አሽከሮች
ድሜጥሮስን ብትሰድቡት ንጽሕናውን ብትዋሹት
እንደ አባቱ ድሜጥሮስ ማእጠንቱን ይዞ ይገባል
ወደ ደመራው ገብቶ በእሳቱ ይራመዳል
ስለ ሁሉም ይጸልያል በመስቀሉም ይባርካል
ምንም ብትሉ ምንም ከቶ ምንም አንሆንም
ለስድብ ለአሉባልታ ጊዜችንን አንሸጥም
መጋቤ ሃይማኖት መ/ር ኅሩይ ባየ/B.Th and BA/
ሊባኖስ ቤይሩት
ስልክ+ 96170531056
e-mail hiruybaye21@gmail.com

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...