ቅዳሜ 7 ኖቬምበር 2015

“ገርፎ የመጮኽ”፡- የተሐድሶዎች የማደናገሪያ ስልት


አትም ኢሜይል
ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ.ም
ክፍል ሁለት
የተሐድሶዎችን እንቅስቃሴ በተመለከተ በክፍል አንድ ዝግጅታችን በማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል በስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጋዜጣ በተከታታይ እየወጣ ያለውን ጽሑፍ አቅርበንላችሁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ክፍል ሁለትን ደግሞ እነሆ፡-
አማናዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ተመሥርታ በሐዋርያት ስብከት ከሰፋችበት ጊዜ ጀምሮ ያለ ፈተና አልጋ በአልጋ የሆነ ሕይወት የመራችበት ጊዜ የለም፣ ወደፊትም አይኖርምም፡፡ በሐዋርያት ዘመን ይሁዳና ቢጽሐሳውያን፣ በሐዋርያውያን አበው ዘመን ግኖስቲኮች፣ በሊቃውንት ዘመን አርዮስ፣ መቅዶንዮስ፣ ንስጥሮስና ልዮን ቤተ ክርስቲያንን ለመፈተን የተነሡ ነበሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ እንደ ተጻራሪዎች አሳብ አሉታዊ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ግን ለምእመናን መንፈሳዊ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ የነበራቸው ብዙ መከራዎችን አሳልፋለች፡፡ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ የሚለው የጌታችንና የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ማረጋገጫ በዚህ ሁሉ በማያቋርጥ ማዕበል ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ድል አድራጊ ሆና ወጀቡን ማለፍ መቻሏ ነው፡፡
04menafikanባለንበት ዘመን ቤተ ክርስቲያንን የማዳከምና ምእመናንን የመንጠቅ ተግባር ለይቶላቸው በሌላ የእምነት ጎራ የተሰለፉ አካላት ተልእኮ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ይህ ተግባር ዛሬ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን እሷ እንደ ሻማ እየቀለጠች ባበራችላቸው፣ በሥጋዊ ፈቃዳቸው የእንጀራ ማብሰያ ያደረጉትን ሙያ ባስተማረቻቸው፣ በጉያዋ ባደጉ፣ የእናት ጡት ነካሽ በሆኑ በራሷ ልጆች የሚፈጸም ሆኗል፡፡ እነዚህ ሰዎች በአለባበሳቸው፣ በአነጋገራቸው (ግእዝ ስለሚጠቅሱ)፣ በአካሔዳቸው (ቤተ ክርስቲያን ስለሚመላለሱ) እና በአገልግሎታቸው (ተአማኒነት ለመፍጠር ስለሚተጉ) ክርስቲያኖች ሊመስሉን ይችላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቀን እስኪወጣ ለማደናገሪያነት የተጠቀሙበት ማስመሰያ ጭምብል እንጂ በእውነት ፊት ሚዛን የሚደፋ መንፈሳዊነት ያለበት ሕይወት አይደለም፡፡ ይህ ድርጊታቸው የሚያስቀርብን ነገር ግላዊ ጥቅም ቢሆን ሁሉን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ማለፍ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን ከውስጥ እስከ ውጪ በተዘረጋ መዋቅር፣ ቤተ ክርስቲያንን እስከ መረከብ፣ ካልተቻለ እስከ መክፈል በሚያደርስ የተቀናጀ ስልት፣ በፕሮቴስታንታዊ በጀት በታገዘ ድጋፍ አምልኮተ እግዚአብሔርን ከምድረ ገጽ ላይ ለማጥፋት የኤልዛቤልን ዕቅድ የሚያስፈጽሙ አካላትን መታገሥ አግባብ ባለመሆኑ ማንነታቸውን ገልጾ ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ መንፈሳዊ ግዴታችን ይሆናል፡፡
እነርሱ መዋቅር ዘርግተው፣ ስልት ነድፈው፣ በጀት መድበው ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት እየሠሩ ያሉት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው፡፡ ከዚህ በፊት በቀረቡ ጥናቶች እንደተገለጸው ተሐድሶዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እስከ መክፈል፣ ከተቻለም እስከ መረከብ ያደርሱናል ብለው የዘረጓቸው ስልቶች አሉ፡፡ እነዚህን ስልቶች እውን ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህ ተሐድሶዎች ከሚጠቀሟቸው መንገዶች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

፩.በሚያውቋቸው ሰዎች በኩል መቅረብ፡- ዛሬ ላይ ተሐድሶ ነን በማለት ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን የሚሉ አካላት የተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ስለነበሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሰዎችን ያውቃሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ፣ በአብነት ትምህርት ቤት ወንበር ዘርግተው የሚያስተምሩ የአብነት መምህራንን፣ በልዩ ልዩ ገዳማት የሚገኙ መናንያንን እና አስተዳዳሪዎችን፣ የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት አስተዳዳሪዎችን፣ መምህራንን እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት አመራሮችንና አባላትን ማወቃቸውና መቅረባቸው በእነርሱ በኩል ተልእኳቸውን የማስፈጸም ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡


01menafikanለምሳሌ በ፲፱፻፺ ዓ.ም ቀኖና ተሰጥቶት ተጸጽቶ በመመለስ ፋንታ በኑፋቄው በመግፋቱ ምክንያት በ፳፻ወ፬ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ ከተወገዙት ፲፮ የተሐድሶ አራማጅ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው፣ አሁንም ኦርቶዶክስ ነኝ በማለት የሚያደናግረው እና በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የሚካሔደውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ የሚመራው ጽጌ ሥጦታው ብዙ የአብነት መምህራንን ለመቀሰጥ ዕድል ያገኘው በአብነት ትምህ ርት ቤት የሚያውቃቸውን ሰዎች በመጠቀም ነው፡፡ መሠረተ ክርስቶስ ቸርችም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማደስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ለአገልግሎት የምፈልጋቸው በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ካህናትን ብቻ ነው ማለቷ የአብነት መምህራንን ለማጥመድ የቤተ ክርስቲያንን ቋንቋ የሚያውቅ አካል አስፈላጊ እንደሆነ በመረዳቷ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን ተሐድሶዎች ከቤተ ክርስቲያኒቷ ቋንቋና ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር መተዋወቃቸው በምእመናን ዘንድ ተቀባይ ነትን በማግኘት ተልእኳቸውን ለማሳካት ምን ያህል ያገዛቸው መሆኑን ነው፡፡

፪.በገንዘብ ማታለል፡- ተሐድሶዎች ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ከምንጩ ላይ መሥራት አለብን ብለው ትኩረት የሰጧቸው አብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይ የሚገኙት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የገንዘብ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ አብነት ትምህርት ቤቶችን ብንወስድ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር የተረሱ የቤተ ክርስቲያን የደም ሥሮች ናቸው፡፡ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከመቀየሩ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ዘመን ከዚህ በፊት እንደነበረው ቁራሽ እየለመኑ መማር የማይታሰብ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያት የአብነት ተማሪዎች ሌሎች የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ትምህርታቸውን መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ መካከል ከአሜሪካና ከአውሮፓ የፕሮቴስታንት ድርጅቶች በሚላክላቸው ገንዘብ ኪሳቸውን ያደለቡት ተሐድሶዎች አንድ አማራጭ ሆነው አብነት ተማሪዎችን ቀረቧቸው፡፡ ተሐድሶዎቹ ለገዳማት፣ ለመንፈሳዊ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ለገጠሪቷ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ዲያቆናትም ተመሳሳይ ድጋፍ እናደርጋለን በሚል ሰበብ እየበረዟቸው ይገኛሉ፡፡ ባለፈው ዓመት አዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ ባካሔዱት ስብሰባ ላይ ማኅበረ ቅዱሳን ያልደረሰባቸውን አብነት ትምህርት ቤቶችን ቀድመን በድጎማ መልክ መቅረብና መያዝ አለብን የሚል አቅጣጫ መንደፋቸውን ተናግረዋል፡፡

፫.€œአሠልጥኖ€/አሰይጥ
ኖ መመለስ፡- በትውውቅም ሆነ በማታለያ የቀረቧቸውን ሰዎች የጥፋት ዓላማቸውን ለመፈጸም የሚችሉበትን አቅም በሥልጠና ካስታጠቋቸው በኋላ ተልእኳቸውን ሳይረሱ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ተመልሰው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጓቸዋል፡፡ የተሐድሶ ሥልጠናዎችን ወስደው ወይም ሃይማኖታቸውን ትተው ወደ ሌላ በረት ሔደው ከቆዩ በኋላ የጣሉትን ቆብና መስቀል ይዘው ኦርቶዶክሳዊ መስለው የተመለሱ ሰዎች ቁጥር ብዙ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ውጪ ድረስ ሔደው ተምረው የመጡ አሁንም አባ እገሌ፣ ቄስ እገሌ፣ ዲያቆን እገሌ እየተባሉ የሚጠሩ በልብሳቸውና በምላሳቸው ኦርቶዶክሳውያን፣ በልባቸው ግን ፕሮቴስታንት የሆኑ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች አሉ፡፡
02menafikan
፬.ሚዲያዎችን መጠቀም፡- ተሐድሶዎች እንቅስቃሴያቸውን ከግብ ለማድረስ የኅትመት፣ የኤሌክትሮኒክስና የብሮድካስት ሚዲያዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ማን እንዳዘጋጃቸው የማይታወቁ ባለቤት አልባ በራሪ ወረቀቶችን፣ ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችንና መጻሕፍትን እንዲሁም የተለያዩ የምስል ወድምጽ ውጤቶችን በማሠራጨት መርዛቸውን ይረጫሉ፡፡ ድረ ገጾችን፣ የጡመራ መድረኮችን፣ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን መርሐ ግብራትን በመጠቀም ኑፋቄያቸውቸውን እያስፋፉ ይገኛሉ፡፡

፬.፩.ጋዜጦች
ተሐድሶዎች እያሳተሙ ከሚያሠራጯቸውና መርዛቸውን ከሚረጩባቸው ጋዜጦቻቸው መካከል መጥቅዕ፣ በሃይማኖት ቁሙ፣ መርከብ፣ መና ተዋሕዶ፣ እውነት፣ ኖኅተ ብርሃን፣ ከሣቴ ብርሃን፣ ርግብ፣ ንቁ፣ ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

፬.፪.መጽሔቶች

ሌሎች ተሐድሶዎች ኑፋቄያቸውን የሚያሠራጩባቸው የኅትመት ውጤቶች መጽሔቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መጽሔቶች መካከል ጥቂቶቹ አንቀጸ ብርሃን፣ ብሔራዊ ተሐድሶ፣ ከሣቴ ብርሃን ዘኢትዮጵያ፣ ሰላማ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ ጮራ፣ ቤተ ፍቅር፣ ወዘተ ሲሆኑ ከእነዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ ለተሐድሶ እንቅስቃሴው ድጋፍ ሰጪ የሆኑ ጽሑፎችን የሚያቀርቡ ጌሠም፣ ትሪኒቲ፣ ማቴቴስ፣ ካሪዝማ፣ ወዘተ የሚባሉ የፕሮቴስታንት መጽሔቶች አሉ፡፡

፬.፫.መጻሕፍት
03menafikanተሐድሶዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ከአንድ መቶ ሰማንያ (፻፹) በላይ መጻሕፍት ጽፈዋል፡፡ መጽሐፎቻቸው የክርስቶስን አምላክነትና የእመቤታችንን አማላጅነት ክደው የሚያስክዱ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚነቅፉ፣ ቅዱሳንን የሚሳደቡ፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን የሚያጥላሉ ናቸው፡፡ ተሐድሶዎች የግብር አባታቸው የሉተር ልጆች እንጂ ኦርቶዶክሳውያን አለመሆናቸውን መጽሐፎቻቸው ይናገራሉ፡፡ ከቁጥራቸው ብዛት የተነሣ ሁሉንም የተሐድሶ መጻሕፍት መዘርዘር ከባድ ቢሆንም በ፳፻ወ፬ ዓ.ም ከእነ ጽጌ ሥጦታው ጋር የተወገዘው አሸናፊ መኮንን ብቻ ከሃያ አምስት በላይ መጻሕፍትን ጽፏል፡፡ የተለያዩ የብዕር ስሞችን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን መሳደብ የእንጀራ ማብሰያው ያደረገው ሠረቀ ብርሃን ዘወንጌል መስተብቁዕ ዘሙታን፣ የዘመናት እንቆቅልሽ ሲፈታ፣ ማሳቀልና ሎፌ የሚሉ በመርዝ የተሞሉ መጻሕፍትን ጽፏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምእመናንን በስውር መንጠቁ አላጠግባቸው ብሎ ቤተ ክርስቲያንን በግልጽ እየተዋጓት ያሉት ፕሮቴስታንቶችም የተሐድሶ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዳለ እና እንቅስቃሴውም ለእነርሱ ድጋፍ ሰጪ መሆኑን በመጽሐፎቻቸው ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ጸጋአብ በቀለ የተባለ የፕሮቴስታንት ፓስተር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ - ሳታድግ ያረጀች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሚለው መጽሐፉ፣ ዳንኤል ተሾመ የሚባል የመካነ ኢየሱስ ቸርች አባል የሆነ ፕሮቴስታንት የቅርብ ዘመኑ (፲፱፻፸፱-፲፱፻፺፱) የተሐድሶ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚል ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ባዘጋጀው ጽሑፍ እንዲሁም በቀለ ወልደ ኪዳን የተባለ ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?በሚለው መጽሐፉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ገልጸዋል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት የተሐድሶ እንቅስቃሴን ግብና ከፕሮቴስታንት ጋር ያለውን ድርና ማግነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡

፬.፬.ድረ ገጾችና የጡመራ መድረኮች

በዚህ ዘመን ሁሉም ነገር በኤሌክትሮኒክስ መቅረብ የሚችል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተሐድሶዎች ኑፋቄያቸውን ለመዝራት ከተጠቀሙባቸው ስልቶች መካከል አንዱ ድረ ገጾችንና የጡመራ መድረኮችን መጠቀም ነው፡፡ ቁጥራቸ ውን በትክክል ማወቅ ባይቻልም በዛ ያሉ የተሐድሶ የጡመራ መድረኮችና ድረ ገጾች አሉ፡፡ ከእነዚህ ድረ ገጾችና የጡመራ መድረኮች መካከል አባ ሰላማ፣ ጮራ፣ ደጀ ብርሃን፣ የዲያ ቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ፣ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ ዐውደ ምሕረት፣ ማራናታ፣ ቤተ ፍቅርና የዲያቆን አቤኔ ዘር ተክሉ ገጽ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

፭.ተገፋን ብሎ መጮህ፡- ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው፣ ተሐድሶዎች አጥፊዎቹ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ የሚተጉት ራሳቸው ሆነው ሳለ በራሳቸው ድረ ገጾች፣ የጡመራ መድረኮችና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ተገፋን እያሉ ይጮሃሉ፡፡ በ፳፻ወ፮ ዓ.ም የተወሰኑ ዘማርያ አሜሪካ ሔደው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በማኅበረ ቅዱሳን ለተገፉ ሰባክያንና ዘማርያን በሚል ገንዘብ ሲሰበስቡ ነበር፡፡ በ፳፻ወ፬ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ የተወገዘው ማኅበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን የተባለው የተሐድሶ ድርጅት ደግሞ የካቲት ፮ ቀን ፳፻ወ፮ ዓ.ም በቁ ጥር አ/ሰ/ማ/18/262/06 በማኅበረ ቅዱሳን አቀነባባሪነት የተወሰነብን የውግዘት ውሳኔ እንዲነሣልን ስለመጠየቅ ይመለከታል የሚል ደብዳቤ በአድራሻ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አስገብቶ ነበር፡፡ ደብዳቤው ርእሱ እንደሚናገረው ማኅበረ ቅዱሳንን የሚያወግዝና ውግዘታችን ይነሣልን የሚል ነው፡፡ ድርጅቱ በደብዳቤው፡-

05menafikanክልላዊ ማኅበር መመሥረት የለባችሁም፣ በአገር አቀፍ የተፈቀደለት ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ስለሆነ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ሁኑ፣ ካልሆናችሁ ግን መናፍቃን ናችሁ፣ ትለያላችሁ በማለት ሲዝትብን የነበረ ማኅበረ ቅዱሳን ከእኔ በቀር ሌላ ማኅበር መኖር የለበትም የሚል አቋም ይዞ በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ራሱን እንደ ልጅ በመቁጠር እኛን ደግሞ እንደ እንጀራ ልጅ እንድንታይና እንድንወገዝ ካለው ጽኑ አቋሙ የተነሣ ምንም ዐይነት የክህደት ትምህርት ሳንማርም ሆነ ሳናስተምር ያለ ምንም መረጃ ይሁን ማስረጃ በአሉቧልታና በትምክህት መናፍቃን ናቸው እያለ በገንዘብ ኀይል በሁሉም ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖር በማድረግ ሳንጠየቅ፣ ሳንመከር፣ ሳንገሠጽ፣ እውነት ይሁን አይሁን ሳይጣራ፣ ቀርበን በወቅቱም ምንም ዕድል ሳይሰጠን በማኅበረ ቅዱሳን ከፍተኛ ተዋናይነት የውግዘት ውሳኔ መተላለፉ አሳዝኖናል ይላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አባ ሰላማና ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በሚባሉት ድረ ገጾቻቸው በ፳፻ወ፬ ዓ.ም ተሐድሶዎች ሲወገዙ፣ ከዚያም በኋላ እነሱን ለማስቆም ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ አገልጋዮቿን የምታሳድድ ቤተ ክርስቲያን እያሉ ስሟን ሲያጠፉ ይሰማሉ፡፡ ለምሳሌ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኑ! እንዋቀስ በሚል ርእስ ባወጣው ጽሑፍ እንደ አለመታደል ሆኖ ሲኖዶሳችን መናፍቃንን በመደገፍ ጻድቃንን ያሳድዳል፤ ቀን ሲደርስ የእግዚአብሔርን ፍርድ እናያለን፤ እስከዚያው እንክርዳዱ ከስንዴው ጋር ተናንቆ ያድጋል፡፡ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቃሉና በመንፈሱ ተሐድሶ ይጎብኝልን፡፡በማለት ጽፈዋል፡፡ ሊያ የሚባል መጽሔት ላይ ደግሞ የወንድሞች ከሣሽ ማኅበረ ቅዱሳን በሚል ርእስ ሰፊ ሐተታ ያለው ጽሑፍ ጽፈው ነበር፡፡

06menafikanየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቁጥር በሰባት ሚሊዮን መቀነሱን በይፋ አምናለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ስትል በአንድ ወገን መንጋው አለመጠበቁንና በዚህ ምክንያት መሰረቁን አምናለች፡፡ በሌላ በኩል ግን ሌሎች ሰረቁኝ፣ ወሰዱብኝ ከማለት ያለፈ ምክንያቱን በሚገባ ያጤነችው አትመስልም፡፡ ሌሎች በውጪ አግኝተው ከወሰዷቸው በላይ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያለ የወንድሞች ከሳሽና አክራሪ ቡድን እኔን አልመሰላችሁምና መናፍቃን ሆናችኋል በሚል ሕገ ወጥ መንገድ ያሳደዳቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ምናልባት ለቁጥሩ መቀነስ የማኅበረ ቅዱሳን እጅም እንዳለበት መታመን አለበት ይላል፡፡ (ሊያ መጽሔት ቅጽ ፪ ቁጥር ፳፮ ሚያዝያ ፳፻ወ፭ ዓ.ም)

እስካሁን ያየነው የአገር ውስጡን ጩኸት ነው፡፡ ተሐድሶዎች ከፕሮቴስታንቶች ጋር በመተባበር ይህንን ጩኸት ዐለም አቀፋዊ አድርገውታል፡፡ ዓላማዬ የክርስቲያኖችን ጭቆና ለዓለም ማሳወቅ ነው የሚል ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር የሚባል አንድ የዜና አውታር አለ፡፡ በቀን ከዐሥር በላይ ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዜናዎች ያወጣል፡፡ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን በደል አውጥቶ አያውቅም፡፡ በሶርያ በየዕለቱ ከሞት ጋር ስለሚታገሉት ኦርቶዶክሳውያን፣ ስለ ፓትርያርኩ ለዐሥራ አምስት ቀናት የሔዱበት አድራሻ አለመታወቅ የዘገበው ነገር አልነበረም፡፡ ያልዘገበው ግን ባለማወቅ ሳይሆን በዓላማ ነው፡፡ ለዚህ ድርጅት ክርስቲያን ማለት ፕሮቴስታንት ነው፡፡ የሚያሰማውም የእነሱን ጩኸት ነው፡፡

07menafikanተቀማጭነቱን አሜሪካ ያደረገ ኦፕን ዶርስ የሚባል ድርጅት አለ፡፡ ድርጅቱ አንድሪው ቫን ደር ቢጅል በሚባል ግለሰብ በ፲፱፻፶፭ የተመሠረተ መንግ ሥታዊ ያልሆነ የክርስቲያን ድርጅት ነው፡፡ እንደ ራሳቸው አገላለጽ በግለሰቦች መዋጮ የሚተዳደር ነው፡፡ ከ፲፱፻፺፩ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጭቆና የሚያደርሱ የአምሳ አገራትን ዝርዝር ያወጣል፡፡ በዚህ ድርጅት ዘገባ መሠረት አገራችን ኢትዮጵያ ክርስቲያኖችን ከሚጨቁኑት አምሳ አገራት መካከል ባለፉት አምስት ዓመታት ማለትም በ2011 ፵፫ኛ፣ በ2012 ፴፰ኛ፣ በ2013 €“፲፭ኛ፣ በ2014€“ ፲፯ኛ እና በ2015€“ ፳፪ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የክርስቲያኖች ጭቆና ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ ነው ይላል፡፡ ይህ አገላለጽ ሲብራራ ተሐድሶዎች ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ የተሻለ ዕድል እያገኙ ነው ማለት ነው፡፡

ተቋሙ በ2013 ባወጣው ዘገባው ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ የሚል ቃል አስቀምጧል፡-

Ethiopia has a complex mix of persecution dynamics.Ecclesiastical arrogance is the country historical persecution dynamic. For years, the Ethiopian Orthodox Church (EOC) has been seriously persecuting believers who have left their ranks or joined the renewal movements within the EOC. (World Watch List 2013)

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሆነ ጭቆና የሚካሔድባት አገር ናት፡፡ ቤተ ክህነታዊ እብሪትየአገሪቱ ታሪካዊ የጭቆና መታወቂያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ወጥተው አዲስ የመጣውን የፕሮቴስታንት እምነት እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ የተሐድሶውን ጎራ የተቀላቀሉትን አማኞች ክፉኛ ትጨቁናለች፡፡ካለ በኋላ ቀጥሎ፡-

The fanatic group inside the EOC (€˜Mahibere Kidusan) is a growing threat for non-traditional Protestants and renewal movements within the EOC. The group allegedly wants to control the government policies to restrict the activities of other religions. Mahibere Kidusan is currently riding high. (World Watch List 2013)

08menafikanበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው አክራሪ ቡድን ለፕሮቴስታንቶች እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ላሉ ተሐድሶዎች ታላቅ ሥጋት ነው፡፡ ቡድኑ ሌሎች የእምነት ቤቶች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ለመገደብ የመንግሥትን ፖሊሲዎች በጥብቅ መቆጣጠር በጥብቅ ይፈልጋል፡፡  በአሁኑ ጊዜ ማኅበሩ በፍጥነት እያንሠራራ ነው፡፡

2013 ማለት በኢትዮጵያ ተሐድሶ ዎች የተወገዙበት ዓመት ማግስት ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው እየተጨቆንን ነው የሚለው ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ እንዲሆን እና ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንዲይዝ ለማድረግ የሞከሩት፡፡ ተሐድሶዎች የዘረጉት መስመር የት እንደሚደርስ ወይም ተሐድሶው በማን ግፊት እየተመራ እንደሆነ ይህ አገላለጽ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ ኦርቶዶክስ ሳይሆኑ ኦርቶዶክስ ነን በማለት የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለመቀየር ብሎም ቤተ ክርስቲያንን ለመክፈል የሚሠሩ ወገኖች ቁጥራቸው በርከት ባሉባቸው ቦታዎች ኦርቶዶክሶችን በማሸማቀቅ፣ በማስፈራራትና በመዝለፍ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የተነሡት እነርሱ ሆነው ሳለ ራሳቸው የሠሩትን ግፍና በደል ለቤተ ክርስቲያን አድርገው ተሳደድን ብለው ይጮሃሉ፡፡ ብዙዎቻችንም ዐውቀንም ይሁን ሳናውቅ የእነርሱ ጩኸት ደጋፊዎችና ጠበቆች እየሆን ነው፡፡ የራስን አጥብቆ መያዝና ለሌላ ወገን አላስደፍርም ማለት ማስወቀስና ማስተቸት ከጀመረ ቆይቷል፡፡

እነርሱ እነዚህን መንገዶች ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም፣ ዶግማና ቀኖናዋን የመቆነጻጸል ተግባራቸውን ቀጥለውበታል፡፡ እኛ ይህ ሁሉ ሲፈጸም ምን ያከናወንነው ተግባር አለ ተብለን ራሳችንን ብንጠየቅ መልሳችን ምንም የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ የችግሩን አሳሳቢነትና የአደጋውን አስከፊነት ጠንቅቀን ማወቅና መንገዶቻቸውን ለመዝጋት የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ይገባናል፡፡ እነርሱ በገንዘብ ለማታለል ምቹ ሁኔታ ያገኙት እኛ አብነት ትምህርት ቤቶችን እና ገዳማትን ባለመደገፋችን መሆኑን መረዳት አለብን፡፡

ይቆየን

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...