2015 ጁን 12, ዓርብ

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል የሰጠቺው ትኩረት፡- በ14ኛው መክዘ ወንጌል መነሻነት ሲዳሰስ


የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ወንጌል ወደ ግእዝ ቋንቋ መተርጎም የጀመረው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ዘመን፣ የተጠናቀቀው ደግሞ በተሰዓቱ ቅዱሳን መሆኑን ይገልጣሉ[1]፡፡ እስካሁን በተደረጉት ጥናቶች የተገኘው ጥንታዊው የብራና የግእዝ መጽሐፍም የአባ ገሪማ ወንጌል ነው[2]፡፡ ይኼ ከ4-7 መክዘ ባለው ዘመን ውስጥ የተጻፈውና በአድዋ እንዳ አባ አባ ገሪማ ገዳም የሚገኘው ወንጌል ቤተ ክርስቲያኒቱ ወንጌልን ለመተርጎምና ለማስተማር የሰጠቺውን ጥንታዊ ትኩረት አመልካች ነው፡፡ በ6ኛው መከዘ የተነሣው ቅዱስ ያሬድ የደረሰው ድጓ ብሉይ ኪዳንን ከሐዲስ ኪዳን አስተባብሮ የያዘና ጥንታውያን የክርስቲያን ሊቃውንት (ቄርሎስ፣ አትናቴዎስ፣ ባስልዮስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙና ዘኑሲስ) የተረጎሙትን ትርጓሜ በውስጡ ይዞ መገኘቱ መጽሐፍ ቅዱሱ ብቻ ሳይሆን ትርጓሜዎቹም በአኩስም የክርስትና ዘመን በሊቃውንቱ እና በሕዝቡ ዘንድ የታወቁና የተሰበኩ እንደነበር ያሳየናል፡፡ 
የእንዳ አባ ገሪማ ወንጌል

ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን ያደረጉትና የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ነገሥታት የሆኑት ኢዛናና ሳይዛና ክርስትና ሲነሡ ‹አብርሃ እና አጽብሐ› ተብለው መጠራታቸው ወንጌልን ኢትዮጵያውያን የተቀበሉት ‹ብርሃናችን፣ ንጋታችን› ነው ብለው መሆኑን ይጠቁማል፡፡ የመጀመሪያውን ጳጳስ ፍሬምናጦስን የሰየሙበት ‹ከሣቴ ብርሃን› የሚለው ስያሜም የወንጌል መሰበክ እንደ ብርሃን መገለጥ ተደርጎ መወሰዱን ያመለክታል፡፡ ‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ[3]› የሚለውን ቃል ያላወቀ ሕዝብ መቼም  ይህንን ስያሜ አይሰጥም፡፡ ይኼ ስያሜ ከወንጌል ሰባኪነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በዲማና አካባቢዋ ወንጌልን በብርቱ የሰበከው በኪሞስ ‹ተከሥተ ብርሃን› ›ብርሃን ተገለጠ› ተብሎ መጠራቱን ገድለ አቡነ ፊልጶስ ይነግረናል[4]፡፡
  የኢትዮጵያ ነገሥታት በሳንቲሞቻቸው ላይ የመስቀልን ምልክት ካደረጉ የመጀመሪያዎቹ የዓለም ነገሥታት መካከል ናቸው[5]፡፡ በአኩስም በተገኙት ሳንቲሞች በሳንቲሞቻቸው ላይ የመስቀልን ምልክት ያደረጉ ከ17 በላይ የአኩስም ነገሥታት ተገኝተዋል[6]፡፡ ይኼም ክርስትና በኢትዮጵያውያን ውስጥ ቦታ አግኝቶ የዕለት ተዕለት ሕይወት የሆነው ተሰብኮ ሳይውል ሳያድር መሆኑን አመልካች ነው፡፡ እነዚህ ነገሥታት በሳንቲሞቻቸው ላይ ከመስቀል ምልክት በተጨማሪ ስመ እግዚአብሔርን ጽፈዋል፡፡ 
                                                                   የአኩስም ዘመን ሳንቲሞች [7]
የወንጌሉን ሐሳቦች የሚገልጡ ‹ሰላምና ደስታ ለሕዝቡ ይሁን፣ ምሕረትና ሰላም፣ በእግዚአብሔር ጸጋ፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ በክርስቶስ ድል የሚያደርግ› የሚሉትን ቃላትም አስጽፈውም ተገኝተዋል[8]፡፡ ምሕረት፣ ሰላም፣ ምስጋና፣ ጸጋ የሚሉት በአብዛኛው በቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ላይ የምናገኛቸው የሐዲስ ኪዳን ትምህርቶች በሳንቲሞቹ ላይ መጻፋቸው የወንጌሉን ስብከትና የስብከቱን ውጤት ያሳያል፡፡ ድል አድራጊነትን ለክርስቶስ መስጠታቸውም ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅና በሕይወት ውስጥ ቦታ መስጠት ከክርስትና መሰበክ ጀምሮ በሀገሪቱ የነበረ እንጂ የ20ኛው መክዘ ግኝት አለመሆኑን ያሳያል፡፡ 
ኢዛና በሦስት ቋንቋዎች ባስጻፈው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ኢየሱስ ክርስቶስን ‹የሰማይ ጌታ› ብሎ ጠርቶ ድሉ በእርሱ ርዳታ መገኘቱን ይገልጥልናል[9]፡፡ ኢዛና በሌላኛው የድንጋይ ላይ ጽሑፉም ‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ› ሲል በሥላሴ ላይ ያለውን እምነት ገልጧል[10]፡፡ ይህም አሚነ ሥላሴ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረውን ቦታ ይነግረናል[11]፡፡
በዛግዌ ዘመን ወርቃማ ጊዜ ላይ የምናገኘው ቅዱስ ላሊበላ በላስታ ሮሐ የሰማያዊቱንና ምድራዊቱን ኢየሩሳሌም ምሳሌ ሠርቷል፡፡ ይህም ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ ኢየሩሳሌም ሰማያዊትና ኢየሩሳሌም ምድራዊት በማለት የከፈለው ትምህርት መሠረት ያደረገ መሆኑን አመላካች ነው[12]፡፡ ከሠራቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል ‹ቤተ መድኃኔዓለም›፣ ‹ቤተ ዐማኑኤል›፣ ‹ቤተ መስቀል› የወንጌሉ ትምህርት ከሰዎች ኑሮ አልፎ ሥነ ሕንጻ ሲሆን ያሳዩናል፡፡ አንድን ነገር ዐውቆ፣ ያወቀውን አምኖ፣ ያመነውም ተረድቶ፣ በዓይነ ኅሊናም ስሎ ወደ ኪነ ሕንጻ ለመለወጥ ለነገሩ በአእምሮ ውስጥ ጥልቅ ቦታ መስጠትን ይጠይቃል፡፡ የገላትያ ሰዎች ይህንን ሥዕል አጥፍተው ነው በቅዱስ ጳውሎስ የተወቀሱት[13]፡፡ የልደት በዓል በላሊበላ ከጥንት ጀምሮ ያለውን ቦታ ስናይ እነዚህን ሰዎች ክርስቶስን አያውቁትም ብሎ ከመናገር በፊት ዘጠና ዘጠኝ ጊዜ ማሰብ እንደሚገባ ሕያው ምስክር ነው፡፡ 
ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከ700 ዓመታት በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ባደረጉት ስብከት ስመ ክርስቶስን ጠርተው ያስተምሩ፣ ሕዝቡም ክርስቶስን አንዲያውቅ ይሰብኩ እንደነበር የሚያስረዳን በገድላቸው ላይ በተጻፈው የደቡብ ስብከታቸው ውስጥ ከ52 ጊዜ በላይ ስመ ክርስቶስን ጠርተው ሲያስተምሩ ማንበባችን ብቻ ሳይሆን በዳሞት መጀመሪያ የተከሉት ቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ስም መሆኑንም ስናይ ነው፡፡ ወደ ሰሜን ለበለጠ ትምህርትና ተጋድሎ በሄዱ ጊዜ ለዐሥር ዓመት ያገለገሉበት ገዳም ሐይቅን የመሠረቱት አባት ‹ኢየሱስ ሞዓ› ተብለው መጠራታቸው የሚነግረንም ነገር አለ፡፡ ከሐይቅ በፊት ቢያንስ 200 ዓመት ቀድሞ የተሠራው ጥንታዊው የአካባቢው ቤተ ክርስቲያንም ‹እግዚአብሔር አብ› መባሉ የምሥጢረ ሥላሴው ትምህርት ሳይቋረጥ የቀጠለ መሆኑን ያሳያል፡፡  
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመቺባቸው ሁለቱ ቅዳሴያት ‹ቅዳሴ እግዚእ› እና ‹ቅዳሴ ሐዋርያት› ናቸው[14]፡፡ ይህም ለጌታችን ትምህርትና ለሐዋርያት ስብከት የተሰጠውን ቦታ የሚያሳይ ነው፡፡ ምናልባትም ከውጭ የተተረጎሙት ቅዳሴያት እነዚህ ሁለቱ ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በአኩስም ዘመን ከተተረጎሙት የሃይማኖት መጻሕፍት መካከል አንዱ ነገረ ክርስቶስን የሚተነትነው ‹መጽሐፈ ቄርሎስ› መሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ተርጉመው ከተጠቀሙባቸው የሊቃውንት ጸሎቶች መካከል አንዱ የሆነው የአባ ኤፍሬም ውዳሴ ማርያም ከጠቅላላው ይዘት 63 በመቶው ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን እምነት መያዙ የሚነግረን ብዙ ነገር አለ፡፡
ከአኩስም ዘመን ጀምሮ ነገራተ ሕዝብ የሚመዘገቡት በወርቅ ወንጌል ነው፡፡ ራሱ ወንጌሉም ‹ወንጌል ዘወርቅ› ተብሎ መጠራቱ የወንጌሉን ቦታ ይገልጣል፡፡ በእንዳ አባ ገሪማ ወንጌል[15]፣ በደብረ ሊባኖስ ዘሺምዛና ወንጌል[16]፣ በጉንዳ ጉንዶ ወንጌል፣ በሐይቅ እስጢፋኖስ ወንጌል[17]፣ በክብራን ወንጌልና በደብረ ሊባኖስ ወንጌል የምናገኛቸው መረጃዎችም ይህንን ያስረግጡልናል፡፡
የክብራን ገብርኤል ወንጌል( British, Ms. 481)
ከክርስትና መግባት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን የተጠቀሙበት የዘመን መቁጠሪያ አራቱን ዓመታት በአራቱ ወንጌላውያን ስም መጥራቱና የዐቢይ ጾም ስምንቱ እሑዶች ጌታችን በወንጌል ላይ በሠራቸው ሥራዎች መሠረት መሰየማቸው ወንጌልና የወንጌል ትምህርት ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የያዘውን ጽኑ መሠረት አመልካች ነው፡፡ 
እነዚህ ሁሉ ነገሮች  ወንጌል፣ የወንጌል ትምህርትና የወንጌል መሠረት የሆነው ክርስቶስ በኢትዮጵያውያን ጠቅላላ ሕይወት ውስጥ ከሥጋና ደም ጋር የተዋሐዱ እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አለመሆናቸውን ያጠይቁልናል፡፡
ኢትዮጵያውያን ወንጌሉን በሚገባ አስጽፈውታል፣ ተርጉመውታል፣ ሥለውታል፣ አዚመውታል፣ ኪነ ሕንጻ አድርገውታል፣ ተጠርተውበታል፣ ከዚህም አልፈው መሥዋዕት ሆነውለታል፡፡ ወንጌል በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የዕውቀትና የክብር ቦታ ከሚያሳዩን ማስረጃዎች አንዱ ዘመናትን ተሻግረው እኛ እጅ የደረሱት የወንጌል ቅጅዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቅጅዎች በሚገባ የተጻፉ፣ በሐረግ ያሸበረቁ፣ በሥዕል የተገለጡ፣ ትንታኔ የተሰጠባቸው፣ ቀመር የተዘጋጀላቸው፣ ማውጫና ማብራሪያ የተሰጣቸው፣ ወንጌሎቹ በወንጌላውያኑ የተጻፉበትን ቦታና ዘመን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ በ14ኛው መክዘ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተጻፈውን የግእዝ ወንጌል መሠረት አድርገን ነገሩን እንዳስሳለን፡፡
አርባዕቱ ወንጌል ዘደብረ ጊዮርጊስ
መጽሐፉ የሚገኘው በዋልተርስ የሥነ ጥበብ ሙዝየም በቁጥር W 836 ተመዝግቦ ነው፡፡ በብዙ ገጾቹ ላይ ውኃ ፈስሶበት ለማንበብ ያስቸግራል፡፡ በአንድ ወቅት በትግራይ ደብረ መዐር የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ንብረት የነበረው ይኼ ወንጌል 516 የብራና ቅጠሎች ያሉት ነው፡፡ ወንጌሉ በ1973 እኤአ የሮበርትና ናንሲ ኑተር ገንዘብ ሆነ፡፡ በ1996እኤአ ደግሞ የአልተን ደብሊው ጆንስ ፋውንዴሽን ገዝቶ በሙዝየሙ አስቀመጠው፡፡ ወንጌሉን የጻፈው መጥሬ ክርስቶስ የተባለ ጸሐፊ ሲሆን አባ አርከ ሥሉስ በ18ኛው መክዘ ማርያም ጽኩዕ ለሚባል ደብር እንደሰጡት በማቴዎስ ሥዕል ሥር በጻፉት መግለጫ ይናገራል፡፡ ከዚያ በኋላ እንዴት የደብረ መዐር ጊዮርጊስ ንብረት እንደሆነ እንዴትም ከሀገር እንደወጣ አላወቅኩም፡፡
   
የወንጌሉ መግቢያ
                                                                 
መልእክተ አውሳብዮስ
አውሳብዮስ የታወቀውን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ Ecclesiastical History የጻፈ አባት ነው፡፡ በዚህ ወንጌል ላይ አውሳብዮስ ቀርጲያኖስ ለተባለ ሰው አርባዕቱ ወንጌልን በተመለከተ የጻፈው ደብዳቤ ይገኛል፡፡ በደብዳቤው ላይ እንደተገለጠው አሞንስ አሌክሳንድራዊ የሠራውን የወንጌላት ቀመር ሰድዶለታል፡፡ አውሳብዮስም ለቀርጲያኖስ በዚህ ደብዳቤ ይገልጥለታል፡፡

የአውሳብዮስ ደብዳቤ
                                                                        

(1)አራቱ ወንጌላውያን የሚተባበሩበትን፣
(2)ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ የሚተባበሩበትን፣
(3)ማቴዎስ ሉቃስ ዮሐንስ የሚተባበሩበትን፣
(4)ማቴዎስ ማርቆስ ዮሐንስ የሚተባበሩበትን፣
 (5)ማቴዎስና ሉቃስ የሚተባበሩበትን፣
(6)ማቴዎስና ማርቆስ የሚተባበሩበትን፣
(7)ማቴዎስና ዮሐንስ የሚተባበሩበትን፣
(8)ሉቃስና ማርቆስ የሚተባበሩበትን
(9) ሉቃስና ዮሐንስ የሚተባበሩበትን
(10) አራቱንም በየራሳቸው ያላቸውን
ሠለስቱ ወንጌላት(ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ) የሚተባበሩበት

ይኼ ቀመር ከጥንት ጀምሮ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት በቤተ ክርስቲያናችን ይሰጥ እንደነበረ ያመለክታል፡፡ አራቱን ወንጌላውያን በየራሳቸው በትርጓሜ ከማጥናት ባለፈ አራቱ የሚገናኙበትንና የሚለያዩበትን እየተነተኑ በቀመር ማጥናቱ ለምን ተለዩ? የሚል ጥያቄ በአጥኝዎቹ ዘንድ ተነሥቶ እንደነበረ ያሳያል፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ ሊቃውንቱ የደከሙትን ድካምም በየትርጓሜው ውስጥ የምናየው ነው፡፡ ‹ማቴዎስ እንዲህ አለ፤ ማርቆስም እንዲህ ብሏል፣ ሉቃስም እንዲህ ይላል፣ እንደምን ነው ቢሉ› የሚለው ዓይነት፡፡
ይህ ቀመር በመልእክተ አውሳብዮስ እንደተገለጠው የሚለያዩበትንና የሚገናኙበትን ለማጥናት ብቻ ሳይሆን አንዱን የወንጌል ታሪክ በተመለከተ በአራቱም ወንጌላውያን ያለውን ሐሳብ ለማየት የሚያገለግል፣ ከዚህም በላይ የወንጌሉን ልዩ ልዩ ክፍሎች በየታሪካቸው ዘውግ ለማጥናትና በቃል ለመያዝም የሚያስችል ነው፡፡
አርእስት
በአራቱም ወንጌሎች ላይ በየአንዳንዱ ምእራፍ ምን ምን ይዘት እንዳለ የሚያሳይ ርእስ አላቸው ፡፡ ርእሱ የሚጻፈው በላይኛው የብራናው ኅዳግ ላይ ሲሆን በርእሱ የተገለጠው የመጽሐፉ ክፍል የሚጀምርበት ቦታ ልዩ ምልክት በቀይ ቀለም ተደርጎበታል፡፡ ምልክቱ በሥዕሉ ላይ እንደምናየው ከላይ ቀለበት ያለው ወራጅ መሥመር ይደረግና መሐል ወገቡ ላይ የX ምልክት ይደረጋል፡፡ ይህም ወንጌሉን በጉዳይ በጉዳይ ከፋፍሎ የመማርና የማስተማር ባሕል እንደነበረ ያሳያል፡፡
  የአርእስት አሰጣጥ
   እንስሳት
በወንጌሉ ውስጥ የወንጌሉን ሐሳብ የሚገልጡ የእንስሳት ሥዕሎች አሉ፡፡ የመጀመሪያዋ ፒኮክ ወፍ ናት፡፡ የፒኮክ ወፍ በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ ትንሣኤ ሙታንን የምታመለክት ነበረች፡፡ ሌላዋ ደግሞ ጳልቃን ወይም ፔሊካን ተብላ የምትጠራው ስትሆን እርሷም ዛሬም ድረስ በትርጓሜያችን እንደሚነገረው የትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ናት፡፡ ሌላም አንድ ወፍ አለች፡፡ ማን እንደሆነችና ትርጉሟንም ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ሌላዋ ሰጎን ናት፡፡ ሰጎን የክርስቲያኖችና የመንፈስ ቅዱስን ግንኙነት ለማሳየት የምትመሰል ወፍ ናት፡፡ ከወፎች በተለየ የምናገኘው እንስሳ በግ ነው፡፤ እርሱም የታረደው የክርስቶስ ምሳሌ ነው[18]፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት ወፎች(ፒኮክ)
                                                 
     ሰጎን

                                                                           
ምልክቶች
ከላይ ካየነው የ‹ቶ›[19] መሰል ምልክት በተጨማሪ ትምህርቱን፣ ተግሣጹን፣ ተአምሩን ለማመልከት ልዩ ልዩ ምልክቶችን ማድረጉን አውሳብዮስ ይገልጣል፡፡ በመጽሐፉም ውስጥ ያንን በመከተል በግራና በቀኝ በሚገኙ ኅዳጎች ላይ ምልክቶች ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአውሳብዮስ ቀመር ላይ ለእያንዳንዱ ቀመር የተሰጠው ቁጥር በወንጌሉ ውስጥም  በሚገኙበት በሚገኙበት ቦታ በቀይ ቀለም ቁጥሩ በግእዝ ተጽፏል፡፤ ይህም የወንጌላቱን ጥናት የሚያቀል ነው፡፡
  
አዲሱ ርእስ የሚጀምርበት የ‹ቶ› መሰል ምልክት
                                                  
    ሥዕል
በያንዳንዱ ወንጌላዊ መግቢያ ላይ የወንጌላዊው ሥዕል አለ፡፡
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ
                                                                   

የማቴዎስ ወንጌል ከመጀመሩ በፊት ደግሞ የጌታችንን ሥነ ስቅለት(በጉ ከመስቀሉ በላይ ይታያል)[20] የሚያሳይ ጥንታዊ ሥዕል፣
 
   የሥነ ስቅለቱ ሥዕል፣ ክርስቶስ በበግ መስለውት
                                                     

 የጌታችንን ትንሣኤ የሚያሳይ ሥዕል(በሁለት ሴቶች መካከል ሆኖ)፣
የጌታ ትንሣ፣ ቅዱሳት አንስት ግራና ቀኝ
የጌታችን ዕርገትና በዙፋኑ ላይ መቀመጥን የሚያሳዩ ሥዕሎች አሉ፡፡ 
 ጌታችን ዐርጎ በዙፋኑ ሲቀመጥ
ከዚህም በተጨማሪ ጸሐፊው የአርባዕቱን ወንጌል ኅብረት በዲያግራም ገልጦታል፡፡ 
 
 የአርባዕቱ ወንጌልን አንድነት ለመግለጥ የተሳለ ዲያግራም
የመጻሕፍቱ ክፍሎች ማውጫ
ከማርቆስ ወንጌል ጀምሮ የመጻፍቱን ልዩ ልዩ አርዕስት ለማውጣት የሚያስችል ማውጫ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ማውጫዎቹ የመጽሐፉን ገጽ የሚጠቀሙ ሳይሆኑ ጉዳዩንና ቅደም ተከተሉን ብቻ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የማቴዎስ ወንጌል ማውጫ

መሥፈርና መቁጠር
ወንጌሉ የእያንዳንዱን ወንጌላውያን አርእስተ ነገር ቆጥሮና ሠፍሮ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሠረት
ጠቅላላ የወንጌላውያኑ አርእስተ ነገር 218 ሲሆን
ማቴዎስ 68
ማርቆስ 48
ሉቃስ 83
ዮሐንስ 19
እንዳላቸው ያትታል፡፡ ጠቅላላ ቃሎቻቸውም 90 ሺ 700 (፺፻፯፻) መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ይህም ነገር የወንጌሉ ጥናት ከ600 ዓመታት በፊት የደረሰበትን ደረጃ የሚገልጥ ነው፡፡
 
የማርቆስ ወንጌልን የአርእስት ቁጥር የሚያሳይ መረጃ
ማጠቃለያ
ከላይ ያየናቸውን ነጥቦች ስንመረምራቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌለ ክርስቶስ ትምህርትና ጥናት የነበራትን ዋጋ፣ ከዚህም በላይ ለወንጌሉ ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላትንም ቦታ የሚያሳይ ታሪካዊ መረጃ ነው፡፡ ወንጌሉን ይህንን ያህል ሠፍሮና ቀጥሮ፣ ተንትኖና አፍታቶ ለማወቅ የተፈለገውም የሚያስገኘው ምድራዊ ጥቅም ኑሮ አልነበረም፡፡ ክርስቶስን ዐውቆ በክርስቶስ መንገድ ለመኖር ስለተፈለገ እንጂ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያፈራቻቸው ቅዱሳንም ይህንን በመሰለው የወንጌል ትምህርት ታንጸውና በስለው የወጡ እንደነበሩ የ13ኛው መክዘን የሐይቅ እስጢፋኖስ ወንጌል ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ ጋር፣ የደብረ መጣዕን ወንጌል ከአባ ሊባኖስ ታሪክ ጋር፣ የክብራንን ወንጌል ከአባ ዘዮሐንስ ታሪክ ጋር፣ አያይዞ ማሰብ ይቻላል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ወንጌል አልሰበከችም፣ ክርስቶስንም አታውቀውም ብሎ እንደመናገር ያለ ከባድ ኃጢአት ሊኖር አይችልም፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...