ማክሰኞ 18 ፌብሩዋሪ 2014

ተጠቃሚው ማነው?

ማኅበረ ቅዱሳን ለሦስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የአብነት መምህራን ጉባኤ መታገዱን መግለጫዎችና ዜናዎች እያሳወቁን ነው፡፡ የአብነት መምህራን በቤተ ክህነቱ ‹ለአበል የተረሱ፣ ለሹመት የሚታወሱ› ሆነዋል፡፡ ስብሰባ፣ ዐውደ ጥናት፣ ሥልጠና፣ ጉዞ፣ ሲሆን እነርሱን የሚያስታውስ የለም፡፡ የጵጵስና ሹመት ሲመጣ ግን ‹ከእገሌ ይህንን ከእገሌም ያንን ተማርኩ› የሚለው ይበዛል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ የሀገሪቱ ሀገራዊ ዕውቀት ማዕከል መሆናቸው ተረስቶ ይህንን ያህል ዘመን ሲኖሩ ‹ቤት ልሥራላቸው፣ ዘር ልዝራላቸው› ያለ ቤተ ክህነት አልገጠመንም፡፡ እንዲያውም እነ መምሬ በዕውቀቱን እነ አያ ብሩ እየቀደሟቸው ቦታ ቦታውን ይዘውታል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለውጥ አምጭ ሥራ ከሠራባቸው ዘርፎች አንዱ የአብነት ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን እስላም ከክርስቲያኑ የሚመሰክረው ነው፡፡ ለአብነት መምህራን ደመወዝ ከመክፈል ቤት እስከ መሥራት፣ ትምህርት ቤቶቻቸውን ከመገንባት ለተማሪዎቹ ቁሳቁስ እስከ ማቅረብ፣ የጤና መርሐ ግብሮችን ከማከናወን እስከ ካሪኩለም ቀረጻ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
ለአንድ ሊቅ ከቁሳዊ ነገር በላይ መንፈሳዊ ነገሩ ይበልጥበታል፡፡ ጽድቁ፣ ክብሩ፣ ስሙ፣ መዓርጉ፣ ታሪኩ ታላቅ ነገሮች ናቸው፡፡ ከቁሳዊው ድጋፍም ሞራላዊው ድጋፍ ታላቅ ነው፡፡ እነዚህ የአብነት መምህራን ቦታና ዐቅም ወስኗቸው፣ እድሜና አሠራር ገድቧቸው እንዳይቀሩ፤ እርስ በርስ ተገናኝተው እንዲመክሩ፤ አሠራራቸውን እንዲያዘምኑ፣ ዕውቀት እንዲከፋፈሉ፣ ልምድ እንዲለዋወጡ፣ ህልውናቸውን እንዲተዋወቁ፣ ወጥ አሠራር እንዲዘረጉ መደረጉ የሚያስመርቅ እንጂ የሚያስረግም አልነበረም፡፡


በርግጥ ይህንን መሰል ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች ለመሥራት ተገቢ የሆኑ ቢሮክራሲያዊ መንገዶችን አሟጦ መጓዝ፤ ማወቅ ያለበት እንዲያውቅ፣ መስማት ያለበትም እንዲሰማ ማደረግ፣ ማሳመንና ማግባባት፣ በአሠራሩና በዓላማው ላይ ቀደም ብሎ ከሚመለከታቸው ጋር መወያየት ያስፈልጋል፡፡ አንድን ታላቅ መኪና የአንዲት ብሎን መላላትና መውለቅ እንደምታስቆመው ሁሉ የጥቂት ቤተ ክህነታዊ አሠራሮች አለመጠበቅ ታላቁን ዓላማ ሊያደናቅፈው እንደሚችል ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ትናንት እንዲህ ስለሠራን ነው ማለቱ ብዙም አያዋጣም፡፡ ሁልጊዜ ፋሲካ የለምና፡፡
በዚያም ሆነ በዚህ ግን የአብነት መምህራኑ መሰባሰብና በሞያቸውና አገልግሎታቸው ዙሪያ መምከር የሚጠቅመው ማንን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሲሆን ቤተ ክህነቱ ራሱ አስቦ መሥራት ነበረበት፤ ካልሆነም ደግሞ የሚሠሩትን ማትጋትና ማገዝ ይገባው ነበር፡፡ ሁለቱም ግን አልሆኑም፡፡ ማኅበሩ በቤተ ክህነቱ አሠራር ያላከናወናቸው ነገሮች አሉ ከተባለ እንዲያከናውን ማድረግ እንጂ አገር አቋርጠው ወንበር አጥፈው የመጡትን ሊቃውንት ማንገላታት የሚገባ አልነበረም፡፡ ጉባኤው ተስተካክሎ በመካሄዱ የምትጠቀመው ቤተ ክርስቲያን ናት ባለ መደረጉ ግን ከሰይጣን በቀር ተጠቃሚው ማነው
በሌላ በኩልም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና የፓትርያርኩ ጽ/ቤት በጉዳዩ አፈታት ላይ የሄዱበት መንገድም አስገራሚ፣ አስተዛዛቢም ነው፡፡ የማኅበሩ ጽ/ቤት ከቤተ ክህነቱ በ50 ሜትር ርቀት ላይ መኖሩ እየታወቀ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም ሆኑ ፓትርያርኩ ያንን ሁሉ የደብዳቤ ውርጅብኝ ማዝነብ ለምን አስፈለጋቸው? ደግሞስ ጉዳዩ የውስጥ ጉዳይ ነው፤ ለእነዚያ ሁሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመጻፉ ዓላማው ምንድን ነው? አስፈላጊ ከሆነ ልጆቹን ጠርቶ ‹ጉባኤውን አቁሙ› ማለት ይቻል የለም እንዴ? ደግሞስ መጀመሪያውኑ ሳያጣሩ መጻፍ፣ ከዚያ ደግሞ የመሻሪያ ደብዳቤ መጻፍ፣ አከታትሎ ደግሞ የመሻሪያ መሻሪያ መጻፍ የቤተ ክህነቱን ተቋማዊ ኪሣራ ከማሳየት በቀር ሌላ ምን ያሳያል?
የዛሬን አያድርገውና የፓትርያርክ ደብዳቤኮ የእምነት መግለጫ፣ የሚጠቀስ፣ በክብር የሚቀመጥ፣ በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ የሚሠፍር ነበር፡፡ እንዲህ ጊዜ በሰጠ ቁጥር መዥለጥ እየተደረገ የሚጻፍ አልነበረም፡፡ ደግሞስ አንድ አባት ልጆቹን ጠርቶ መምከር እየቻለ ‹‹ልጆቼ እንዲህ ያሉ ናቸው›› ብሎ ለዓለም መንገር ከየት ያመጣነው ሥርዓት ነው? ዓለም ችግሯን ለቤተ ክርስቲያን ታቀርባለች እንጂ ቤተ ክርስቲያን ችግሯን እንዴት ለዓለም አቤት ትላለች?
የሊቃውንቱ መሰባሰብና መወያየት ለቤተ ክርስቲያኒቱ የወንጌል ሥምሪት ወሳኝ ነው፡፡ እንዲያውም ከሲኖዶሱ ጉባኤ በፊት ሊደረግ የሚገባው ነገር ቢኖር የሊቃውንቱ ጉባኤ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርዓትና የትውፊት ጉዳዮች ላይ መክረው የውሳኔ ሃሳቦችን ማቅረብ የነበረባቸው ሊቃውንቱ ናቸው፡፡ ይህ ባለመሆኑም ይመስላል የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አጀንዳዎች ሃይማኖታዊ ከመሆን ይልቅ አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ የሆኑት፡፡ ስንትና ስንት የምእመናን ጥያቄዎች እያሉ የሹመትና የበጀት ጥያቄዎች ዋነኛ መነጋገሪያዎች የሚሆኑት፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንኮ የራስዋን ጳጳሳት እንድትሾም የተሟገቱት ከመላዋ ሀገሪቱ የተሰባሰቡ ሊቃውንት ነበሩ፡፡ ምነው መሠረቱ ተዘነጋ፡፡
አሁንም ሊቃውንቱን ተዋቸው፣ ቤተ ክርስቲያን እንደነርሱ ላሉት ናትና፡፡ በጉባኤያቸው ተገኝቶ መወያየት፣ የጉባኤውን አጀንዳ አብሮ መቅረጽ፣ ጉባኤውን መምራት፣ አሠራሩን ማሳየት ይገባል፣ የአባትም ነው፡፡ የገዛ ሊቃውንቶቻችንን ግን አትሰብሰቡ፣ አትመካከሩ፣ አትወያዩ፣ ችግር አትፍቱ ብሎ ማገድ፣ እምቢ ካላችሁ ‹ለመንግሥት እነግርባችኋለሁ›› ብሎ መንግሥትን ማስፈራሪያ ማድረግ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ ምነው በጎንደሩ የጥምቀት ኤግዚቢሽ የመንግሥት አካላት ሊቃውንቱን ሲያከብሩ ባየን፤ ይህቺ ቤተ ክርስቲያንኮ ያለ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ኖራ ታውቃለች፣ ያለ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ግን የኖረችበት ዘመን የለም፣ አይኖርምም፡፡
አሁንም እጠይቃለሁ፤ የሊቃውንቱን ጉባኤ ማገድ ጥቅሙ ለማን ነው? ባሏን ጎዳሁ ብላ..... እንደተባለው ካልሆነ በቀር፡፡ ሊቃውንቱንም አስተምረው ለወግ ለመዓርግ ባበቋቸው ልጆቻቸው ሲታገዱ ማየት የስምንተኛውን ሺ መግባት ከማሳየት በቀር ሌላ ምን ያሳያል፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...