2018 ኦክቶበር 2, ማክሰኞ


                                   በአውሮጳ  የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ


ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ  የተውጣጡ ካህናት፡” የካህናት አንድነት ማኅበር “ ሊያቋቁሙ እንደሆነ ታወቀ   መስከረም 25 እና  26/ 2011 ዓ.ም በጀርመን ፍራንክፈርት የምሥረታ መርሐ ግብሩን የሚያካሂደው የካህናት አንድነት ማኅበሩ  ከታላቋ ብሪታንያ ጨምሮ ከሁሉም የአውሮጳ ሀገራት በየደብሩ የሚያገለግሉ ካህናት ዲያቆናት እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን  በአንድነት የሚያቋቁሙት ማኅበር መሆኑ  ምንጮች ገልጠዋል።
የካህናት አንድነት ማኅበር ማቋቋም ያስፈለገው አሁን በቅርቡ  የተገኘው የሲኖዶስ አንድነት/የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አንድነት/ ከዚህ በፊት እንደተፈጠረው ዓይነት መከፋፈል ዳግም እንዳይፈጠር እና  ዘመኑን የዋጀና በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የሚገጥማትን  የሉላዊነትን ተጽዕኖ  ተቋቁማ ልጆቿ ምእመናንን በሚገባ መምራት ይቻል ዘንድ  ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ በመሆኑ የካህናት አንድነቱ ማኅበር መቋቋም ወሳኝ መሆኑ  ታምኖበታል። አገልጋዩ ካህናት የምእመናንን አንድነት መጠበቅና የኖላዊነት ተግባራቸውንም  ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመወጣት  እንደሚያስችልም  ታስቦ መሆኑን ምንጮች ገልጠዋል ። የካህናት አንድነት ማኅበር መቋቋሙ የምእመናንን አንድነት ለመጠበቅ ዓይነተኛ አስተዋጸኦ የሚያበረክት መሆኑ የሚታወቅ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገር ሰላምና አንድነት ለኪነ ጥበባት ለሕግና አስተዳደር በራሱ የሚተማመን መንፈሰ ለዕልናው ከፍ ያለ ትውልድ የመፈጠር ከፍተኛ ተግባሯን አጠናክራ ትቀጥል ዘንድ የአገልጋዮቿ  ካህናት  አንድነት ወሳኝ  መሆኑ ስለታመነበት ይህ የካህናት አንድነት ማኅበር  መቋቋም አስፈልጓል ተብሏል ።
በምሥረታ ጉባኤው  ከተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት ከ መስከረም 24/2011 ጀምሮ ወደ ፍራንክፈርት እንደሚገቡ ታውቋል
በምሥረታው መጨረሻም ላይ ታዋቂ እመናን የሰንበት ት.ቤቶች ተወካዮች እና ይህንኑ ዜና የሚዘግቡ የተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚገኙ ታውቋል
ከዚህ ቀደም የካህናት አንድነት ማኅበር በአሜሪካ የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል

2018 ጁላይ 26, ሐሙስ


ሲኖዶሳዊው የዕርቀ ሰላም ስምምነት- በዝርዝር: ኹለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች በእኩል የአባትነት ክብር ያገለግላሉ

• አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ በአንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ትመራለች፤
• 4ኛው ፓትርያርክ በጸሎት እና በቡራኬ፣ 6ኛው ፓትርያርክ በአስተዳደር ሥራ፤
• የኹለቱም ስም፣ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ዓለም ሁሉ ዘወትር በጸሎት ይነሣል፤
• ሰማዕቱ አቡነ ቴዎፍሎስ ለሞት ከተላለፉበት ጀምሮ የቀኖና ጥሰት ተፈጽሟል፤
• ቅ/ሲኖዶስ፣ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ባለማስጠበቁ ልጆቿን ይቅርታ ይጠይቃል፤
†††

• ጥሰቱን ለመከላከልና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ፣ቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ያዘጋጃል፤
• በኹለቱም ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት፣ በጋራ ምልዓተ ጉባኤ ይፈታል፤
• ከልዩነት በኋላ የተሾሙ ቅቡል ናቸው፤አጠራራቸው እንደ ቅደም ተከተላቸው፤
• ለውጭ ቤተ ክርስቲያን፣የየሀገሩን ሕገ መንግሥት ያገናዘበ መመሪያ ይወጣል፤
• የስምምነቱን ተግባራዊነትና የአንድነቱን ፍጹምነት ልኡካን አባቶች ይከታተላሉ፤
†††

1. ስለ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፤

በሀገራችን ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም. በተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ የተነሣ አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሁለት ተከፍላ በሁለት ፓትርያርኮች የሚመሩ አንድ ሲኖዶስ ለሁለት ሲኖዶሶች መፈጠራቸው ግልጽ ነው። በዚህም የተነሣ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ በስደት ዓለም መቆየታቸው ይታወቃል። ስለኾነም የሁለቱን ቅዱሳን ፓትርያርኮች ቀጣይ ኹኔታ በተመለከተ በሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶሶች የተወከሉት የሰላም ልኡካን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም በአደረጉት የጋራ ስብሰባ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ እንደሚከተለው በአንድ ድምፅ ወስነዋል።

ሀ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፓትያርክነት ክብርና ደረጃ ወደ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ እንዲመለሱ/እንዲገቡ፤

ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር ቤት ኢትዮጵያ ሲመለሱ በክብር የሚያርፉበትን የመኖሪያ ቦታ በተመለከተ ደረጃውን የጠበቀ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ውስጥ ቦታ ተዘጋጅቶና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ በክብር እንዲቀመጡ፤

ሐ/ የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤

1.1/ ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤

ሀ/ በሕገ ቤተ ክርቲያን መሠረት የአስተዳደር ሥራውን በመሥራት ቅድስት ቤተ ክርስቲንን እንዲመሩ፤

ለ/ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
1.2/ የሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርክ አባቶቻችን ስም በቅደም ተከተል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአለችበት ዓለም ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሣ፤

1.3/ ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በሕይወተ ሥጋ እስከ አሉ ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በእኩልነት የአባትነት ክብራቸውን ጠብቃ እንድትይዝ፤

1.4/ይህ ስምምነት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ፣ የአገር ቤትና የውጭ አገር ሲኖዶስ የሚለው ስም ቀርቶ አንዲት ቤተ ክርስቲያንና አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንዲኾን፤

2. ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት፤

ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃለች። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እንደ ተፈጸመ በልኡካኑ ታምኖበታል። ስለኾነም ለአለፉት ዘመናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር በመጠበቅና በማስጠበቅ በውጭም ኾነ በውስጥ በአገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉና ከጊዜው ጋራ አብሮ በመሔዱ፣ ስለተፈጸመው ጥፋትና ለዘመናት በቤተ ክርስቲያኒቱ መለያየት የተነሣ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ያለፉትንም ኾነ ዛሬ ላይ ያሉትን በጋራ ይቅርታ እንዲጠይቅ የልኡካኑ ጉባዔ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።

ስለኾነም ከሁለቱም ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ ያለፈው የቀኖና ጥሰት ስሕተት ለወደፊቱ እንዳይደገም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሉዓላዊነት ተጠብቆና ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረገ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲዘጋጅ የልኡካኑ ጉባዔ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።

3. ስለ ነባር ሊቃነ ጳጳሳት፤

ከልዩነት በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ በሁለቱ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተፈቶ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶአል።

4. ከልዩነት በኋላ ስለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፤

ከልዩነት በኋላ በሁለቱም ወገኖች የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትን፤ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ፦ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸውና በውጭ ዓለምም ኾነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ጉባዔው በአንድ ድምፅ ተስማምቶአል። ስም አጠራራቸውንም አስመልክቶ እንደ ሹመት ቅደም ተከተላቸው ቀዳማይ፣ ካልዓይ፣ ሣልሳይ… ወዘተ እየተባሉ እንዲጠሩ ጉባዔው በአንድ ድምፅ ወስኖአል።

5. ስለ ቃለ ውግዘት፤

በተፈጠረው ችግር ምክንያት በሁለቱም ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት እንደ ተላለፈ ይታወቃል። ስለሆነም ከዚህ ስምምነት በኋላ ቃለ ውግዘቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲነሣ የሰላም ልዑካኑ በአንድ ድምፅ ወስኖአል።

6. በውጭ ዓለም በስደት የምትገኘውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓላማ ያገናዘበ መዋቅራዊ አስተዳደርን ስለማዘጋጀት፤

እንደሚታወቀው በዘመናችን በየትኛውም ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ በአሉበት ሁሉ ተስፋፍታ ትገኛለች። ይኹን እንጂ በውጭ ዓለም የምትገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋራ አንድነቷን፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ክብሯን ጠብቃ መኖር እንዳለባት ጉባዔው አምኖበታል።

ስለኾነም የየሀገሩን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ የቃለ ዐዋዲውና የሕገ ቤተ ክርስቲያን ገዥነት የሚረጋገጥበት መመሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያዘጋጅ ልኡካኑ በአንድ ድምፅ ወስኗል። እንዲሁም በውጭ ዓለም የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና በመዋቅራዊ አስተዳደር መሠረት ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ በመቀበል በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንድትመራም ወስኖአል።

በተጨማሪም በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል የተደረገውን የዕርቀ ሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግና የሁለቱንም ሲኖዶስ መዋሐድ ፍጹም ለማድረግ እንዲሁም በስደት የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው፥ የቀደመውን ሰላምና አንድነት አጽንተው፥ ሁሉም በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደሩበትን ቅድመ ኹኔታ የሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልኡካን እንዲያዘጋጁና እንዲከታተሉ የሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልኡክ በአንድ ድምፅ ወስኗል።

ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም.
ዋሽንግተን ዲሲ

2018 ጃንዩወሪ 23, ማክሰኞ

ጥምቀት በኖርዌይ ስታቨንገር 2010
                                                           


የጥምቀት በዓል በኖርዌይ
በስደት ሆኖ በተለይ በዓላትን ማክበር በጣም ከባድ ነው ይህንን ከባድ ችግር የሚያውቁት የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች ካህናትና የሰበካ ጉባኤ አባላት እንዲሁም የተወሰኑት በአገልግልቱ ጠለቅ ብለው የሚያገለግሉ ምእመናን ናቸው። በተለይ የአደባባይ በዓላትን ማለትም እንደ ጥምቀትና የመስቀል ደመራበዓላትን ማክበር በጣም ከባድ ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከል በተለይ እንደ ሰሜን አውሮፓ ሀገሮች አካባቢ በጥምቀት በዓል ወቅት ያለው ቅዝቃዜ ተዉኝ ላላየ ሰው በጽሑፍ መግለጥ ከባድ ነው ታቦታቱን አክብሮ አይደለም በአደባባይ አዳራሽ ውስጥ እንኳን ይዞ መውጣት እንዴት ይከብዳል ? ሌላው በተለይ በርከት ያሉ ሕዝበ ክርስቲያን ያሉባቸው አካባቢሆች  ደግሞ ለዚያ ሁሉ የሚሆን አዳራሽ ማግኘቱ ሌላ ስደት ይሆናል ስንቱ ይነገራል
 የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል አዘጋጅ በስታቨንገር ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ወኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ናት።  በኖርዌይ የጥምቀት በዓል በአንድነት ማክበር ከተጀመረ ሰባት ዓመቱን አስቆጥሮአል
፡በስታቨንገር ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ወኪዳነ ምሕረት
፡ክርስቲያን ሳንድ ቅድስት ማርያም
፡በርገን ቅዱስ ሚካኤል
፡ትሮንዳሄም ቅዱስ ጊዮርጊስ አቢያተ ክርስቲያናት በጋራ የጥምቀት በዓልን ያከብራሉ ። የዘንድሮው የትምቀት በዓል ላይ እኔም ተገኝቼ ነበር በጣም ደስ ይል ነበር በተለይ በስደት ደግሞ ደስታው እጥፍ ይሆናል፡፤
 የቅኔው መምህር መጋቤ ምሥጢር አባ ቴዎድሮስ ቅኔ ሲያደርጉ
ስታቫንገር ከሌሎች  የኖርዌይ ከተሞች የአየር ፀባይዋ የተሻለ ነው ቅዝቃዜው ብዙ አይደለም። ዘንድሮ ግን የጥምቀት በዓልን ለማክበር ይመስላል ከተማዋ በበረዶ ተሸፍናለች ፈረንጆቹ የገና በዓላቸውን ሲያከብሩ በረዶ እንዲወርድ ይጸልያሉ  በዓሉ በበረዶ ተሸፍኖ ሲውል ደስ ይላቸዋል  ያንን የለመደ የአየር ፀባይ የኛንም የጥምቀት በዓል ሰዉ ብቻ ሳይሆን ምድሯ ሳይቀር ነጭ ለብሳ ውላለች የደብሩ አስተዳዳሪ እና የስካንድኖቭያ ቤተ ክህነት ዋና ጸሐፊ መጋቤ ምሥጢር አባ ቴዎድሮስ የበዓሉ አዘጋጅ ናቸው ።መጋቤ ምሥጢር አባ ቴዎድሮስ  በማስተባበር  በመሳሰሉት መንፈሳዊ አገልግሎት ገና ከአዲስ አበባ ጀምሮ በሁሉ አባቶች ዘንድ ይታወቃሉ። በኖርዌይ የዘንድሮውንም የጥምቀት  በዓል የአዲስ አበባን ጃንሆይ ሜዳ እስኪመስ ድረስ ነው ዝግጅቱ ካህናቱም ከአሜሪካ ፡ ከጀርመን እና ከዚያው ከኖርዌይ ከተለያዩ ከተሞች በመሰባሰብ  ተከብሯል በማያያዝም የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን መግዛት ይገባናል በማለት በመጋቤ ምሥጢር አባ ቴዎድሮስ አስተባባሪነት አንድ ሚልዮን ክሮነር ለመስጠት  ሕዝቡ ቃል ገብቶአል። በቅርብ ጊዜ ወስጥ ቤተ ክርስቲያን እንደሚገዛም ይጠበቃል ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላው አውሮፓ በየ አቅራቢያው ያሉት አቢያተ ክርስቲያናት በጋራ የጥምቀትን በዓል በጋራ በአንድነት ማክበሩ እየተለመደ መምጣቱእየጎላ መጥቶአልና ሊበረታታ ይገባል።

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...