2014 ዲሴምበር 11, ሐሙስ

ወእሙሰ ተአቅብ ኩሎ ዘንተ ነገረ ወትወድዮ ውስተ ልባ /እመቤታችን ግን ይህን ሁሉ ነገር ታስተውለው፤ በልቡናዋም ትጠብቀው ነበር፡፡/ሉቃ 2፡51/


ዲ/ን ታደለ ፈንታው
 መግቢያ
አስቀድመን መሪ ኃይለ ቃል አድርገን የተነሣንበት አንቀጽ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ላይ አድሮ የተናገው ቃል ነው፡፡  የእመቤታችን ፍቅር በውስጡ ጥልቅ መሆኑ፣ ነገረ ማርያም የገባው መሆኑ የተገለጠበት ፍካሬ ቃል ነው፡፡ የእርሷስ ፍቅር በሌሎች ሐዋርያትም ላይ አለ፤ በጎላው በተረዳው ለመናገር ያህል ነው እንጂ፡፡

በድርሳነ ኡራኤል ላይ እንደተገለጠው እመቤታችን በቤተ ዮሐንስ ሳለች ወንጌላዊው ከሚያስተምርበት ውሎ ሲመለስ እንደምን ዋልሽ አላት፤ እርሷ ግን አልመለሰችለትም፡፡ የጌታዬ እናት ለምን ዝም አለችኝ ብሎ አርባ ቀን ሱባዔ ያዘ፤ በአርባኛው ቀን መልአኩ ቅዱስ ኡራኤል ተገልጦ እመቤታችንን የልጅሽን ወዳጅ ዮሐንስን ለምን ዝም አልሺው አላት፤ እርስዋም ልጄ ወዳጄ ሰማያዊውን ምሥጢር እያሳየኝ አላየሁትም ነበር አለችው፡፡ የወንጌላውያን ነገር እጅግ ያስደንቃል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ከተነናገረው ገጸ ምንባብ አንዱን ቃል ብቻ ወስደን ብንመለከት ነገረ ማርያም ሊደረስበት የማይችል ሩቅ፣ ሊመረመር የማይችል ረቂቅ፣ ጥልቅ ሰማያዊ ምሥጢር የተቋጠረበት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሉቃስን ወንጌል ከተመለከቱ በኋላ የእመቤታችን የአሳብ ልዕልና  የተገለጠበት ወንጌል መሆኑን መስክረዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አንዱን ሐረግ “ይህንን ሁሉ ነገር” የሚለውን እንመልከት፡፡

ነገር ምንድን ነው)
ነገር ብዙ ነገርን ያመለክታል፤ መጻሕፍት ነገር ሲሉ ልዩ ልዩ ምስጢራትን ያመለክታል፡፡ ለዓብነት ያህል የሚመለከተውን መመልከት ይገባል፡፡

1.    ነገር ምስጢር ነው፡፡
ለብዙ ሰው የማይነገር፣ አንድ ሰው በኅሊናው የሚይዘው፣ በልብ የሚደመጥ በአዕምሮ የሚነከር፣ ልመና፣ ርዳታ፣ ምሥጢር፣ ምሥክርነት፣ የርኅራኄ ሁሉ ቃል፣ ይህንና የመሳሰለው ሁሉ ነገር ይባላል፡፡ የአገራችን ሰው «አንድ ነገር አለኝ´ ሲል ሽምግልና ሊሆን ይችላል፤ ተግሳጽ ሊሆን ይችላል፤ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፤ መልስ ሊሆን ይችላል፤ ቁጣ ሊሆን ይችላል፤ ምሕረት ሊሆን ይችላል፤ ቸርነት ሊሆን ይችላል፤ ይህንንና የመሳሰለው ሁሉ መደቡ ነገር ነው፡፡ ነገር ሰውየው በያዘው መጠን ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልቡና ውስጥ ያስቀመጠው ነገር ብዙ ነውና፡፡

2ኛ. ነገር በሰው ልቡና ውስጥ ያለ አሳብ ነው
የአገራችን ሰው አተያይን አይቶ፤ አካሄድን መርምሮ ይሄ ሰው ነገር ፈልጎኛል ይላል፡፡ ባለው ግንኙነት ላይ ተመሥርቶ ብቀላ ይሁን፣ ጥላቻ፣ መርገም ይሁን፣ ስጦታ፣ ወይም ሌላ፤ ባለው የፍቅር ግንኙነት ላይ ተመሥርቶም ይሁን ከዚህ ውጭ በአንድ ቋንቋ ተጠቃልሎ ነገር ብሎ ይጠራዋል፡፡

የቅዳሴ ማርያም ደራሲ አባ ሕርያቆስ ልቡናየ በጎ ነገርን አወጣ በማለት ድርሰቱን ይጀምራል፡፡ ያ በጎ ነገር በቅዳሴ ማርያም ውስጥ ተጠቃልሎ የቀረበ ነው፡፡ በዚያ ቅዳሴ ውስጥ ምን አለ) ወአነ አየድዕ ቅዳሴሃ ለማርያም አኮ በአብዝኆ አላ በአውኅዶ፡፡ ወአነ አየድዕ ውዳሴሃ ለድንግል አኮ በአንኆ በቃለ ዝንጋዔ አላ በአኅጽሮ ወአነ አየድዕ እበያቲሃ ለድንግል፡፡  እኔም የድንግልን ገናናነነቷን እናገራለሁ በማብዛት አይደለም በማሣነስ ቃል እንጂ ብሎ ነገረ ማርያምን፤ ወእቀውም ዮም በትሕትና  ወበፍቅር  በዛቲ ዕለት ቅድመ ዝንቱ ምስጢር  ብሎ ምስጢረ ቁርባንን፤ ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ  እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ የሕይወት መብልን የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና ከፍ ከፍ እናደርግሻለን በማለት /ምስጢረ ስጋዌን / ነገረ ቅዱሳንን፣ ተልእኮ ሐዋርያትን፣ ምልጃ ጳጳሳትን፣ ነገረ ሊቃውንትን፣ ሃይማኖተ ሠለስቱ ምእትን፣ ሃይማኖታቸው የቀና ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን፣ ደናግልን፣ መነኮሳትን ፣ መኳንንትን ፣ መሳፍንትን፣ በቀናች ሃይማኖት ያረፉ አበውንና እመውን፣ የሃይማኖት አርበኞችን አዳምን፣ አቤልን፣ ሴትን፣ ሄኖክን፣ ኖኅን ሴምን፣ አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዮሴፍን፣ ሙሴን፣ አሮን ካህንን፣ ጌዴዎንን፣ ኢያሱ መስፍንን፣ እሴይን፣ አሚናዳብን፣ ሰሎሞን፣ ኤልያስን፣ ኤልሳዕ ነቢይን፣ ኢሳይያስን፣ ዳንኤልን፣ ዕንባቆምን፣ ሕዝቅኤልን፣ ሚክያስን፣ ሲሎንዲስን፣ ናሖምን፣ ዘካርያስን፣ ያነሣበትን ቃል በመጠቅለል ነገር በማለት ይጠራዋል፡፡ በዚህ የቅዳሴ ቃል ምስጢረ ሥላሴ አለ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም አስቀድሞ ልቡናየ በጎ ነገርን አወጣ ብሎ ነበረ፡፡ በመዝሙረ ዳዊት ስለ ጽድቅ፣ ስለ ክብርና አሳር፣ ስለ ፍቅርና ጥላቻ፣ ስለ ዘላለም ጽድቅና ኩነኔ፣ ስለ ክፋትና በጎነት፣ ስለ መልካምነትና ክፋት፣  ስለ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቁርባን ፣ ምሥጢረ ትንሣዔ ሙታን፣ ሁሉ ተጠቅልሎ ቀርቧል ይህ ሁሉ ምሥጢር በአንድነት ተጠቃልሎ ነገር ይባላል፡፡

3ኛ. ነገር ታሪክ ነው፡፡
መጽሐፍት ነገር ሲሉ ታሪክ ማለታቸው ነው፡፡ ነገረ ማርያም፣ የእመቤታችን ታሪክ የተጠቀለለበት መጽሐፍ ነው፡፡ ነገረ ክርስቶስ የክርስቶስን ነገር የሚናገር፤ ነገረ ሥላሴ የሥላሴን ነገር የሚናገር፣ ነገረ መላእክት፣ እንዲህ እያልን የምንናገረው ነገር ታሪክን የሚናገር ነው፡፡

4ኛ. ነገር ምስጢር ነው
ምሥጢር ብዙ ወገን ነው፡፡ የሚነገርና የሚገለጥ አለ፤ የማይነገርና የማይገለጥ አለ በአንድነት ተጠቃልሎ ነገር በማለት ይጠራል፡፡ ምሥጢር ለሁሉም ወገን አይነገርም፤ ለምሳሌ የሃይማኖት ምሥጢር በእምነት ለተጠሩ፣ ሰማያዊውንና መንፈሳዊውን ነገር ለሚረዱ፣ ከሥጋ ፈቃድና አሳብ በላይ ለሆኑ እንደ መንፈስ ፈቃድ ለሚመላለሱ ወገኖች እንጂ ለሁሉ ሰው የሚነገር አይደለም፡፡ ምሥጢር የማይነገረው በሚከተሉት ዓበይት ምክንያቶች ነው፡፡

ሀ. የሚሰጠው ጥቅም ከሌለ አይነገርም፡፡
ለ. የሚቀበለው ሰው አቅም ከሌለው አይነገርም፡፡
ሐ. ተናጋሪውና ሰሚው በእርግጠኝነት የማይደርሱበት ከሆነ አይነገርም፡

ልደተ ወልድ እም አብ ምጽአተ መንፈስ ቅዱስ እም አብ ኢይትነገር አላ ይትነከር፡፡ የወልድ ከአብ መወለድ፤ የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጽ ይደነቃል እንጂ አይነገርም፡፡ ይህ ሁኔታ በሊቃውንት ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ ይሄንን የሚመስል ሌላም ነገር አለ፡- በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ  የቆጵሮስ  ሊቀጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሦስቱ በእግዚአብሔር የዝምታ ሸማ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢራት በማለት የሚገልጣቸው ነገሮች አሉ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.    የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና
2.    አማኑኤል ጌታን መውለዷ
3.    የማይሞተው አምላክ ሞት ናቸው፡፡

አስቀድመን ካነሣነው ነገር ተነሥተን የምንደርስበት ድምዳሜ አለ እርሱም በመጠን የሚነገር ፣ በመጠን የማይነገርና ፈጽሞ የማይነገር፣ መኖሩን ነው፡፡ ፈጽሞ የማይነገረው ነገር ምክንያቱ መጠኑና ልኩ ስለማይታወቅ ነው፡፡ በመጠን የሚነገር ያልነው በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልና የጌታ እናት በምትሆን በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል የነበረውን ዓይነት ነገር ነው፡፡ ቅድስት ድንግል መልአኩን ሴት ያለ ወንድ ምድር ያለ ዘር ታብቅል የሚለውን ጥያቄ ከየት አገኘኸው ብላ በጠየቀችው ጊዜ የቅዱስ ገብርኤል መልስ የተነገረው በመጠን ነው፡፡ እርሱም «ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለም ´ የሚል ነው፡፡

መልአኩ ከዚህ በላይ መሄድ አልፈለገም፡፡ ሥጋዊ ባሕርይ ሌላ መለኮታዊ ባሕርይ ሌላ ነው፤ በሊቃውንት የሚተነተነው ነገር የሚደነቅ እንጂ የመለኮትን ባሕርይ የሚገልጥ አይደለም፡፡ የተሸፈነ ምሥጢር አለ ሰው ሊረዳው የማይችል፣ የማይገነዘበው ምሥጢር፣ እጹብ እጹብ በማለት የሚያደንቀው ምሥጢር፡፡ አሁን ወደ ዋናው ነገር እንምጣ፡-
እናቱም ይህን ነገር ሁሉ ትጠብቀው ነበር አለ ወንጌላዊው፡፡ ወንጌላዊው ይህን ሁሉ ነገር በማለት የተናገረው ነገር ምንድን ነው)

ይህን ሁሉ ነገር
    ከቤተ መቅደስ ይጀምራል፡፡ አስቀድሞ በቤተ እሥራኤል ደናግል በቤተ መቅደስ የሚቀመጡበት ልማድ አልነበረም፡፡ በርግጥ በኦሪቱ ነቢይት በቤተ መቅደሱ ታዛ ነበረች፡፡ የነቢይቱ በቤተ መቅደስ መኖርና የአምላክ እናት በቤተ መቅደስ መኖር ይለያያል፡፡ ነቢይቱ በቤተ መቅደስ የነበረችው በራሷ ምርጫ ስለ ራሷ ኃጢአት ተገብታ ነው፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በአምላክ ምርጫ ነው፡፡ ነቢይቱ በምናኔ ነው፤ እመቤታችን ግን ካህናቱ ተቀብለው መላእክት ምግቧን አቅርበው ነው፤ ስለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ ኦ ድንግል አኮ ኅብስተ ምድራዌ ዘተሴሰየኪ አላ ኅብስተ ሰማያዌ እምሰማየ ሰማያት ዘበሰለ፡፡ ኦ ድንግል አኮ ስቴ ምድራዊ  ዘሰተይኪ፤ አላ ስቴ ሰማያዊ እምሰማየ ሰማያት ዘተቀድሐ፡፡ ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም ከሰማየ ሰማያት የተገኘ ነው እንጂ፡፡ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ነው አንጂ፡፡ በማለት የሚያመሰግናት፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

     ዐሥራ አምስት ዐመት ሲሞላት አይሁድ በምቀኝነት ከቤተ መቅደሳችን ትውጣልን አሉ፡፤ ልማደ አንስት በእርሷ እንደሌለ እያወቀች ንጽሕናዋን አልተከላከለችም፤ አልተቃወመችም እኔ እንዲህ ነኝ፣ እንዲያ ነኝ አላለችም፡፡ ቤተ መቅደሱን ለቃላቸው ወጣች ይህን ሁኔታ የሚያውቀው ወንጌላው ጥቅልል አድርጎ ይህንን ሁሉ ነገር በማለት ገለጠው፡፡

    በድንግልና ተወስና አምላኳን ለማገልገል ቁርጥ ኅሊና ኖሯት ሳለ የዐሥራ ሁለቱ ነገደ እሥራኤል በትር ተሰብስቦ ተጸልዮ ዕጣው ለዮሴፍ ወጥቶ ወደ ዮሴፍ ቤት መሄዷን አልተቃወመችም፡፡  በኅሊናዋ ታሰላስለው ነበር፤ ጥያቄ አንስታ አታውቅም፤ ይህን ሁሉ ነገር  በአንክሮ ትከታተለው ነበር፡፡

    የመልአኩ ብስራት ትጸንሲ ሲላት  በድንግልና ለመኖር የወሰነች ስለነበረች ይህ አንዴት ዓይነት ሰላምታ ነው ብላ አሰበች፤ መልአኩ በድንግልና ጸንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲነግራት እንደቃልህ ይደረግልኝ እኔ የእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ ያለችውን ነገር ሁሉ በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

    ከጸነሰች በኋላ ዮሴፍ  መኑ ቀረጸ አክናፈ ድንግልናኪ ብሎ በጠየቃት ጊዜ መልአኩ ገብርኤል አክብሮ ከነገረኝ ነገር በስተቀር ሌላ እንደማላውቅ እግዚአብሔር ያውቃል  የሚለውን ነገር ሁሉ በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

    ከዚያም በኋላ በቤተልሔም አማኑኤል ጌታን ስትወልድ እንስሳት ሲያሟሙቁት፣ እረኞች ሲያገለግሉት፣ ነቢይቱ ሐና ስታመሰግነው፤ ስምዖን በቤተ መቅደስ ስለ ሕፃኑ ትንቢት ሲናገር ይህ ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ምልክት ሆኖ ተሾሟል፤ በአንቺም በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል ሲላት ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

    በስደቱ ጊዜ የደረሰበትን መከራ፣ ረሃቡን፣ ጽሙን፣ ድካሙን በመንገዷ ሁሉ የፈሰሰውን የሕፃናት ደም እየተራመደች ልጇን ይዛ መሰደዷን በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ጉድ እንዴት እንዳወጣት በስደቷ ጊዜ የሽፍታ ባህታዊ አዘጋጅቶ እንዴት ልጇን ተቀብሎ እንዳሻገረላት፣ ደንጋዮች ታንኳ ሆነው እንዴት ባሕርን እንዳሻገሯት  ታስተለው ነበር፡፡ ልጇን ልተተ ሕፃናት ፈጽሞ እንዴት እንዳደገ፣ በነፋስ አውታር በደመና ዐይበት ውኃ ቋጥሮ እንዴት እንዳገለገላት፤ ልጇ በፀሐይ በነፋስ አውታር እንዴት እንደተራመደ እየተመለከተች ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

     በዐሥራ ሁለት ዓመቱ በሊቃውንት መካከል ተገኝቶ ሲከራከር ሊቃውንቱን ሲያስደምም ታስተውለው ነበር፡፡

    ከሊቶስጥራ እስከ ጲላጦስ አደባባይ ከዚያም እስከ ቀራንዮ አደባባይ የተፈጸመበትን ነገር ሁሉ ታስተውለው ነበር፤ ይህ ሁሉ ተጠቅልሎ ለእርሷ ነገር ነበር፡፡ ይሄንንና የመሳሰለውን ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እናቱም ይሄንን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር በማለት የገለጠልን፡፡ ልመናዋ ክብሯ የልጇም ቸርነት ይደርብን አሜን፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...