2013 ኦክቶበር 30, ረቡዕ


                                         

Ethiopian_Orhodox church bilden addis_Abeba_2

                                   የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቋመ፤ የዕጩዎችን ዝርዝር ለርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ያቀርባል

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው፣ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ዘጠነኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫ የሚያስፈጽም አስመራጭ ኮሚቴ ሠየመ፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ስድስት ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ሲኾን የትግራይ፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋና ኦሮሚያ አህጉረ ስብከትን በመወከል የተመረጡ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት÷ ከትግራይ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ከወሎ የደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ከጎንደር የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ከጎጃም የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ከሸዋ የከምባታ ሐዲያ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እና ከኦሮሚያ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በአስመራጭ ኮሚቴ አባልነት ተሠይመዋል፡፡
ዕጩዎችን በሕገ ቤተ ክርስቲያን ለኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በወጣው መስፈርት ብቻና ብቻ ለይቶ እንዲያቀርብ በምልአተ ጉባኤው ከባድ አደራ የተጣለበት አስመራጭ ኮሚቴው÷ ከመስፈርቱ ውጭ ጎጠኝነትን ጨምሮ በተለያዩ መደለያዎች ሢመተ ኤጲስ ቆጶስነትን ለማግኘት ካሰፈሰፉ ቆሞሳት እንዲጠበቅ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው በመምረጫ መስፈርቱ መሠረት የዕጩዎችን ማንነት ከመለየት ባሻገር ከበጀት፣ ከመንበረ ጵጵስና እና ከጽ/ቤቶች መሟላት አኳያ ኤጲስ ቆጶሳቱ ሊመደቡባቸው የሚገቡ አህጉረ ስብከትን በቅደም ተከተል በመለየት ብዛታቸውን የመወሰን ሥራም እንደሚሠራ ተገልጧል፡፡
በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ በሚሰጠው ቢሮ ሥራውን የሚያከናውነው አስመራጭ ኮሚቴው፣ በሥራው ወራት የፍትሕ መንፈሳዊ ድንጋጌ እንደሚያዝዘውና በተሻሻለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ሕግ እንደተመለከተው ተቀባይነት ያለው የግልጽነት መርሕ በመከተልና የልዩ ልዩ ውጫዊ አካላት ጣልቃ ገብነቶችንና ተጽዕኖዎችን በመከላከል አደራውን መወጣት ይኖርበታል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን ጨርሶ ሪፖርቱን የሚያቀርበው ለመጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሲኾን ሥርዐተ ሢመቱም የምልአተ ጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ እንደሚፈጸም ተመልክቷል፡፡
የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሌሎች መረጃዎችን ወደፊት እንደምናቀርብ ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...