2014 ኤፕሪል 19, ቅዳሜ

የትንሣኤው ትርጉም በዓሉና አከባበሩ




በጠ/ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ምክ/ሓላፊ
  • «ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡
  •  መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
  • «ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡
  •  «ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡
  • «ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡
  • መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
  • «ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡
  • «ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡
  • አንደኛው «ትንሣኤ» ኅሊና ነው፡፡ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር ነው፡፡
  •  ሁለተኛውም «ትንሣኤ» ልቡና ነው፡፡ የዚህም ምስጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡
  •  ሦስተኛው «ትንሣኤ» ለጊዜው የሙታን በሥጋ መነሣት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል፡፡
  • አራተኛው «ትንሣኤ» የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡፡ የእርሰ ትምህርታችንም መሠረት ይኸው እንደሆነ ይታወሳል፤ ብለን ተስፋ አናደርጋለን፡፡
  • ዐምስተኛውና የመጨረሻው «የትንሣኤ» ደረጃም የባሕርይ አምላክ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «ትንሣኤ» መሠረት ያደረገ «ትንሣኤ ዘጉባኤ» ነው፡፡ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡
  • ወደተነሣንበት ዐላማ ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በቃሉም ምስጢር በይዘቱም ስለሚመሳሰሉ ጥላው ምሳሌውም፣ ስለሆነ «ፋሲካ» ተብሎ ይጠራል፡፡
  • «ፋሲካ» ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ «ፌሳሕ» በጽርእ በግሪክኛው «ስኻ» ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና ዐማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ ዕድወት = ማዕዶት፣ በዓለ ናእት = የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር መሸጋገር ማለት ነው፡፡ ነጮቹ በእንግሊዝኛው «ስኦቨር» ይሉታል የዚህም ታሪካዊ መልእክቱ በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደሰታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓል «ትንሣኤ» ተተክቶበታል፡፡
  • ፋሲካ፣ በዓለ ትንሣኤ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ምእመናነ ክርስቶስ ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በእርሱ ትንሣኤ
  • ከኀጢአት ወደ ጽድቅ፣
  • ከኀሳር = ከውርደት ወደክብር፣
  • ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣
  • ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲሰ ሕይወት የተሻገሩበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡

- ክርስቲያኖች የትንሣኤን በዓል በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት ያከብሩታል፡፡ ስለዚህም ከበዓላት ሁሉ የበለጠ ሆኖ ይታያል፡፡

- መድኀኒታችን ሞትን በሞቱ ድል መትቶ፣ ስሙና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ የተነሣው መጋቢት 29 ቀን በ34 ዓ.ም እንደሆነ ታሪከ ቤተ ከርስቲያን ያስረዳል፡፡

- የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው በተነሡት ተከታዮቹ ምእመናን ነው፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዐቱ ይበዛ ይቀነስ እንደሆን እንጂ መከበሩ ተቋርጦ አያውቅም፡፡ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን»

- ሲወርድ ሲወራረድ ከዚህ በደረሰው ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሕማማቱን ስታነብ ሰንብታ ለትንሣኤ እሑድ አጥቢያ ማታ በ2 ሰዓት «ለጸሎት ተሰብሰቡ» የደወል ድምፅ ታሰማለች፡፡

- ካህናቱ ተሰብስበው ሥርዐቱን በጸሎት ይጀምራሉ፡፡ ሕዝቡም ይሰበሰባል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንም ይሞላዋል፡፡

- ካህናቱ ሁሉ ለጸሎተ ፍትሐትም፣ ለሥርዐቱም መዝሙረ ዳዊት፣ ነቢያት፣ ሰሎሞንና ውዳሴ ማርያም ከደገሙ በኋላ «ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ» የሚለውን ግጥማዊ የደስታ መዝሙር ይዘምራሉ፡፡

- ቀጥሎም ምንባባቱና ሌላውም ሥርዐት ከተፈጸመ በኋላ ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ ዲያቆኑ «ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም፣ ወከመ ኀያል ወኅዳገ ወይን፣ ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ = እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደተወው ኀያል ሰውም፣ ጠላቱን በኋላው ገደለ፡፡» የሚለውን የዳዊት መዝሙር ለመስበክ = ለመዘመር ነጭ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አክሊል ደፍቶ፣ የመጾር መስቀል ይዞ፣ እንደእርሱው ነጭ ልብሰ ተክህኖ በለበሱ ደማቅ የጧፍ መብራት በሚያበሩና ድባብ = ጃንጥላ በያዙ ሁለት ዲያቆናት በግራ በቀኝ ታጅቦ ከመቅደስ ብቅ ብሎ በቅድስት ይቆማል፡፡ መዝ. 77-65 ይህም በጌታችን መቃብር በራስጌና በግርጌ በታዩት መላእክት ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ.20-12

ትንሣኤ ዘክርስቶስ - የክርስቶስ ትንሳኤ

                                                          

Nahti Kumsa's photo.



  • ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
  • ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤
  • እንዴት ተነሣ?
  • ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
  • እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?
  • መቃብሩን ማን ከፈተው?


(መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው/ PDF):- ጌታችን  አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ÷ ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስቀርልን ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ÷ ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ይሰብክላቸው ዘንድ ነው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ ለዚህ ነው፥ መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው፤ ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለውም፡፡
ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለው ይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡ መዝ ፲፭÷፲፡፡ ሐዋርያው  ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) እንዲያቀርበን፥ እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት (ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎ በመሰጠት) ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየበመንፈስ ግን ሕያው ሆነ÷ (ያን ሥጋ ነፍስ እንድተለየችው መለኰት አልተለየውምበእርሱም ደግሞ (መለኰት በተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው፤» ብሏል።

 ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
ጌታችን በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ «ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤» የሚለው ቃለ ትንቢት የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ መዝ ፲፭፥፱፡፡ ምሥጢራዊ ትርጉሙም «ወደ መቃብር የወረደ ሥጋዬ በተስፋ ትንሣኤ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር አደረ፤» ማለት ነው፡፡ ተስፋ ትንሣኤውም በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር ወደ መቃብር የወረደ መለኰት ነው፡፡ ነቢዩ ሆሴዕም፡- «÷ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና÷ (በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን ጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነውእርሱም ይፈውሰናል፤ (መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አስወግዶ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋግረናል) እርሱ መትቶናል÷ እርሱም ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፡፡» በማለት ትንሣኤ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሆሴ ÷፲፪፡፡ ይልቁንም ጌታችን ራሱ በመዋዕለ ሥጋዌው፡- ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል፡፡ ማቴ ፲፮÷፳፩፡፡ በገሊላም ሲመላለሱ፡- «ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው÷ ይገድሉትማል÷ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፯÷፳፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ምልክት በጠየቁት ጊዜ፡- «ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ፥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፪፥፴፰-፵።
ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤
ጌታ በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ ይኽንንም ለመረዳት ዕብራውያን ዕለታትን እንዴት እንደሚቆጥሩ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ በሀገራችን የሌሊቱን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ከዋዜማው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ነው÷ የቀኑን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ደግሞ ከማለዳው አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ የሌሊቱ ሰዓት የሚያ ልቀው ከማለዳው አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን፥ የቀኑ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ነው፡፡ የቀኑም የሌሊቱም ዓት ተደምሮ ሃያ አራት ሰዓት ይሆናል፡፡ ሁሉም ሰዓት ዕለቱን ይወክላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እሑድ ዕለት ከሃያ አራቱ ሰዓ በአንዱ ቢወለድ እሑድ ተወለደ ይባላል÷ ቢሞትም እሑድ ሞተ ይባላል፡፡ ዕለቱ በሚጀምርበትም ሰዓት ሆነ፥ በሚያልቅ በት ሰዓት፥ ድርጊቱ ቢፈጸም ሰዓት እንደ አንድ መዓልትና እንደ አንድ ሌሊት ይቆጠራል፡፡ አውሮፓውያን አንድ ብለው ሰዓት መቁጠር የሚጀምሩት በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ነው፡፡ እስከ ሃያ አራት ይቆጥሩና በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን ይጨርሳሉ፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ሲሆን ዜሮ ይሉና እንደገና አንድ ብለው መቁጠር ይጀምራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ከሌሊት እስከ ሌሊት ይቆጥራሉ፡፡ አሜሪካውያን ደግሞ በእኛ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡ ከዚያም በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ ሰባት ሰዓት እንደገና አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡
 ዕብራውያን ግን ዕለትን መቁጠር የሚጀምሩት ከዋዜማው ማለትም በአውሮፓውያን ከአሥራ ሰባት ሰዓት÷ በአሜሪካውያን ከአምስት ሰዓት (P.M.) ÷ በእኛ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ሃያ አራት ሰዓት ቆጥረው አንድ ቀን ይላሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጠው እያንዳንዱ ሰዓት የዕለቱን መዓልትና ሌሊት ይወክላል፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ከመስቀል ወርዶ የተቀበረው ዓርብ ቅዳሜ ከመግባቱ በፊት ነው፡፡ ዓርብ ዕለቱ የሚጀምረው ከዋዜማው ሐሙስ በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ የተቀበረው በዓርብ ሃያ አራት ሰዓት ክልል ውስጥ በመሆኑ እንደ አንድ መዓልትና ሌሊት ይቆጠራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዓርብ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ቅዳሜ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ እሑድ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሰኞ ምሽት ይገባል፡፡ ጌታ የተነሣው በሦስተኛው ቀን እሑድ መንፈቀ ሌሊት ነው።
እንዴት ተነሣ?
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ ይህ ኃይልና ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይኽንንም፡- «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ (ሰውነቴን ከሞት አነሣት ዘንድ) አኖራለሁና (በፈቃዴ እሞታለሁና) ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ ለይቼ በገነት÷ ሥጋዬንም በመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ) ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ (ያለ እኔ ፈቃድ የሚፈጸም ምንም ነገር የለም)፡፡ ላኖራት (ነፍሴን በገነት÷ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው) ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ ላነሣት) ሥልጣን አለኝ፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡ ዮሐ ÷፲፯-፲፰፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት÷ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈ ተም፡፡» በማለት መናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ ትንቢት ነበር፡፡ ኢሳ ፶፫፥፯፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ከዚህ የሚመሳሰል ቃል ተናግሯል፡፡ ፩ኛጴጥ ÷፳፴፡፡ በዚህ ዓይነት ነቢያትም ሐዋርያትም የተናገሩለት ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጐ÷ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሥቷል፡፡ እርሱ የትንሣኤና የሕይወት ባለቤት ነውና፡፡ ዮሐ ፲፩÷፳፭፡፡
ይህ እንዲህ ከሆነ÷ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፤» በማለት አይሁድን ከወቀሳቸው በኋላ፡- «እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤» ለምን አለ? የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ ይኽንን ኃይለ ቃል በመያዝ «አብ አስነሣው እንጂ በራሱ አልተነሣም፤» የሚሉ አሉና፡፡ እነዚህም ትርጓሜውን ያልተረዱ ምሥጢሩን ያላስተዋሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያው «እግዚአብሔር አስነሣው፤» ያለው «እግዚአብሔር» የሚለው ስም የሦስቱም መጠሪያ እንጂ የአብ ብቻ አለመሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም፦ ወልድም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ÷ የሐዋ ÷፳፰፡፡ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ÷፪፡፡ ስለዚህ፦ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው፥ «አንዲት በሆነች በአብ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ተነሣ፤ አንድም፦ ወደ መቃብር የወረደ ሥጋ፥ መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ተነሣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሣ፤» ተብሎ ይተረጐማል፥ ይታመናል፡፡ ትንቢተ ነቢያትም የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ÷ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤» ይላል። መዝ ፸፯፥፷፭።
ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
በእስራኤል ባሕል፥ የአባቶቻቸው አፅም ካረፈበት መቃብር፥ የመቀበር ልማድ አላቸው፡፡ ዮሴፍ በግብፅ የእስራ ኤልን ልጆች፡- «እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤» ብሎ ያማላቸው፥ የአባቶቹ የአብርሃም እና የይስሐቅ የያዕቆብም አፅም ካረፈበት ለመቀበር ፈልጐ ነው፡፡ ዘፍ. ÷፳፭፡፡ በቤቴል የነበረውም ሽማግሌ ነቢ ይ፡- «በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤» ብሏል ፡፡  ፩ኛነገ ፲፫÷፴፩፡፡ ጌታችን የተቀበረው እንደ እስራኤል ባሕል የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበት ከአዲስ መቃብር ነው፡፡ ይኸውም ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው፡፡ «ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው÷ ከዓለት በወቀረ በአዲሱ መቃብርም አኖረው÷ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ፤» ይላል ማቴ ፳፯÷፶፱፡፡ ይህም የሆነው እርሱ ባወቀ በርሱ ጥበብ ነው፡፡ እንዲህም በማድረጉ አይሁድ ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው፥ ከነቢዩ ከኤልሳዕ መቃብር ተቀብሮ የነበረው ሰው፥ የነቢዩ አጥንት በነካው ጊዜ፥ በተአምር ተነሥቷል። ፪ኛነገ ፲፫÷፳፡፡ እንግዲህ ጌታችንም፥ ከአንዱ ቅዱስ መቃብር ተቀብሮ ቢሆን ኖሮ፥ ሞትን ድል አድርጐ በሚነሣበት ጊዜ «በራሱ አልተነሣም፥ የቅዱሱ አፅም ነው ያስነሣው፤» ባሉት ነበር፡፡ ይኸንን ምክንያት ለማጥፋት ነው፥ በአዲስ መቃብር የተቀበረው።
እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?
ጌታችንን ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩት በኋላ፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተመልሰው፡- « ጌታ ሆይ÷ ሰው (ክርስቶስ) ገና በሕይወቱ ሳለ፥ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ፥ እንዳለ ትዝ አለን፡፡ እንግዲህ ደቀመዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም  ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ÷ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት፡፡ ጲላጦስም፡- ጠባቆች አሉአችሁ፥ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ፤» አላቸው፡፡ እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ፡፡» ማቴ ፳፯፥ ፷፫÷፷፮፡፡ በታላቅ ድንጋይ የተገጠመው መቃብር፥ ድንጋዩ እንደታተመ፥ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ተነሥቷል፡፡ ይኸውም፦ ምንም የማያግደው መለኰት በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር በመቃብር ስለነበረ ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው፥ በተዋሕዶ፥ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፥ የሥጋም ገንዘብ ለቃል በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ አይሁድ ብዙ ጊዜ በድንጋይ ቀጥቅጠው ሊገድሉት ሲፈልጉ፥ እያዩት ይሰወርባቸው ከእጃቸውም ይወጣ ነበር፡፡ በመካከላቸው አልፎ ሲወጣ አያዩትም ነበር፡፡ ዮሐ ÷፶፱፤ ፲፥፴፱፡፡ ይህም የሆነው፥ እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ፥ መለኰት ሥጋን በመዋሐዱ ነው፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከተዘጋ ቤት በሩ ሳይከፈት የገባው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ ÷፲፱፤ ፳፮፡፡ በልደቱም ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና እንደታተመች የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ÷፲፬፡፡ ማቴ ÷ -፳፫ ሉቃ ÷-፯፡
መቃብሩን ማን ከፈተው?
         ጌታችን የተነሣው መግነዝ ፍቱልኝ፥ መቃብሩን ክፈቱልኝ ሳይል ከሆነ፥ «መቃብሩን ማን ከፈተው? ለምንስ ተከ ፈተ  የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፤ በወንጌል እንደተጻፈው፥ የአይሁድ ሰንበት ቅዳሜ ካለፈ በኋላ፥ እሑድ በማለዳ፥ ፀሐይ ሲወጣ፥ መግደላዊት ማርያም÷ የያዕቆብም እናት ማርያም ሶሎሜም ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ መጥተው ነበር፡፡ ትልቁ ጭንቀታቸው «ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናልየሚል ነበር÷ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደነበር ተመለከቱ፡፡ ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ፡፡ በጐልማሳ አምሳል የተገለጠላቸው የጌታ መልአክ ነው፡፡ እርሱ ግን፡- «አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ፤ ተንሥቷል በዚህ የለም፡፡» አላቸው፡፡ ማር ፲፮÷-፮፡፡ ጌታችን በዝግ መቃብር ከተነሣ በኋላ ባዶ የነበረውን መቃብር የከፈተው ይህ የጌታ መልአክ ነው፡፡ የከፈተበትም ምክንያት በእምነት የመጡ እነዚህ ሴቶች ያልተነሣ መስሏቸው ዘወትር በመመላለስ እንዳይቸገሩ ነው፡፡ አንድም ትንሣኤውን እንዳይጠራጠሩ ነው፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልም «በሰንበትም መጨረሻ የመጀመሪያው ቀን ሲነጋ፥ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ፡፡ መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፡፡ ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ፡፡ እንደ ሞቱም ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፥ እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤» የሚል ተጽፏል፡፡ ማቴ ፳፰÷-፮፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በእርግጠኝነት ትንሣኤውን ያመኑት መልአኩ ወደ ከፈተው መቃብር ገብተው መግነዙን ካዩ በኋላ ነው። ዮሐ ፳፥፯።
በኲረ ትንሣኤ፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለባሕርይ አባቱ፥ ለአብ ለእናቱ ለድንግል ማርያምም የበኵር ልጅ ነው፡፡ ዕብ ÷፮፣ ሉቃ ÷፯፡፡ ለበጎ ነገርም ሁሉ በኵር በመሆኑ የትንሣኤያችንም በኵር እርሱ ነው፡፡ «አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት በሰው (በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ፥ ትንሣኤ ሙታን በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳም በተባለ በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው፤» ይላል፡፡ ፩ኛቆሮ ፲፭÷-፳፫፡፡ በተጨማሪም፡- «በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯልና፥ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፡፡ (ከፍጥረታት በፊት የነበረ÷ የፍጥረታት አለቃ÷ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ ነው) ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በህልውና የነበረ ነው) ሁሉም በእርሱ ተጋጥሟል፡፡ እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርሰቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው፡፡» የሚል አለ፡፡ ቈላ ÷፲፮-፲፰፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም፡- «ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም÷ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት÷ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤» ብሏል። ራእ ፩፥፭።
 በብሉይ ኪዳን እነ ኤልያስ÷ እነ ኤልሳዕ ሙት አስነሥተዋል፡፡ ፩ኛነገ ፲፯፥፳፪ ፪ኛነገ ÷፴፪-፴፰፡፡ በአዲስ ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ የመኰንኑን ልጅ ÷ የመበለቲቱን ልጅ÷ አልዓዛርንም ከሞት አንሥቷቸዋል፡፡ ማቴ ÷፳፭፣ ሉቃ ÷፲፭ ዮሐ ፲፩÷፵፬፡፡ ነፍሱን በመስቀል ላይ በፈቃዱ አሳልፎ በሰጠም ጊዜ አያሌ ሙታን ከእግረ መስቀሉ ተነሥተዋል፡፡ ማቴ ፳፯÷፶፫፡፡ እነዚህ ሁሉ በኵረ ትንሣኤ አልተባሉም፡፡ ምክንያቱም፦ አንደኛ፥ በራሳቸው ኃይል የተነሡ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜ ከኖሩ በኋላ ተመልሰው ሞተው ትንሣኤ ዘጉባኤን የሚጠብቁ ሆነዋል፡፡ ሦስተኛ፥ ፍጡራን ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባሕርይ አምላክ በመሆኑ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ተነሥቷል፡፡ ዳግመኛም አይሞትም፡፡ ይኽንንም፡- «ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደፊት እንዳይሞት፥ ሞትም ወደፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና ÷ መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቷልና፡፡» በማለት ሐዋርያው ገልጦታል፡፡ ሮሜ ÷፱፡፡ ጌታችንም፡- «ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤» ብሏል። ራእ ፩፥፲፰።
ከትንሣኤው በኋላ ለምን ተመገበ?
ጌታችን በተዘጋ ቤት ገብቶ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠ ጊዜ፥ መንፈስ የሚያዩ መስሏቸው ኅሊናቸው ደንግጦ÷ ልባቸውም ፈርቶ ነበር፡፡ እርሱም፡- «ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት÷ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና፥ እኔን ዳስሳችሁ እዩ፤» ካላቸው በኋላ እጆቹንና እግሮቹን አሳይቷቸዋል። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፡- «በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁንአላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ፥ ይላል። ሉቃ ፳፬÷፴፮ -፵፫። ለሦስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ በተገለጠላቸውም ጊዜ አብሯቸው ተመግቧል፡፡ ዮሐ ፳፩÷-፲፬። ይኽንንም ያደረገው ከትንሣኤ በኋላ መብላት መጠጣት ኖሮ አይደለም፡፡ አለማመናቸውን ለመርዳት ነው፡፡ ደቀመዛሙርቱ በተዋሐደው ሥጋ ለመነሣቱ እርግጠኞች እንዲሆኑ ነው፡፡ ከወንጌሉ እንደምንረዳው ደቀመዛሙርቱ ይበልጥ እርግጠኞች የሆኑት ስላዩት ሳይሆን፥ ያቀረቡለትን በመብላቱና በመጠጣቱ ነውና፡፡
ለምን አትንኪኝ አላት?
መግደላዊት ማርያም ገና ሰማይና ምድሩ ሳይላቀቅ፥ በማለዳ፥ ሽቱ ልትቀባው ከመቃብሩ አጠገብ ተገኝታ ነበር። እንደደረሰችም ድንጋዩ ከመቃብሩ አፍ ተፈንቅሎ አየች። ይህች ሴት በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ከባለቤቱ ብትሰማም፥ « እንደተናገረ ተነሥቶ ነው፤» ብላ አላመነችም። ላለማመኗም ምክንያት የሆነው፥ «እኛ ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት ሰረቁት፤» የሚለው የጭፍሮች ወሬ ነው። ጭፍሮቹ እውነትን በሐሰት ለውጠው ይኽንን ያወሩት፥ በገንዘብ ተደልለው ነው፡፡ ማቴ ፳፰÷፲፩-፲፭፡፡ ለዚህ ነው ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ፡- «ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤» ያለቻቸው፡፡ ዮሐ ÷፪፡፡ ከመቃብሩ ራስጌና ግርጌ ሁለት መላእክት ተገልጠውላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽባሏት ጊዜም፥ «ጌታዬን ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤» ብላቸዋለች፡፡ ዮሐ ÷፲፫፡፡ በመጨረሻም ጌታ ራሱ ተገልጦላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽሲላት አላወቀችውም፡፡ ለዚህ ነው፥ አትክልት ጠባቂ መስሏት፡- «ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ፥ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፥ እኔም ወስጄ ሽቱ እንድቀባው፤» ያለችው፡፡ ዮሐ. ÷፲፭፡፡ በዚህን ጊዜ፥ «ማርያም» ብሎ በስሟ ቢጠራት በድምፁ አወቀችውና «ረቡኒ ( መምሕር ሆይአለችው፡፡ መልኩን አይታ፥ ድምፁን ሰምታ÷ ትንሣኤውን አረጋግጣ፥ «አምላኬ» አላላችውም፡፡ ስለዚህ «ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ አትንኪኝ፥ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ (ወደ ደቀመዛሙርቴ) ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ÷ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብሏል፥ ብለሽ ንገሪያቸው፤» አላት፡፡ እንዲህም ማለቱ የእርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መባልና የእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች መባል ፍጹም የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡ እርሱ፥ «አባቴ» ቢል የባሕርይ ልጅ በመሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ግን የጸጋ ልጆች ናቸው፡፡ እርሱ፥ «አምላኬ» ቢል ስለተዋሐደው ሥጋ ነው፡፡ የተዋሐደው የፈጠረውን ሥጋ ነውና ፡፡ እነርሱ ግን «አምላካችሁ» ቢባሉ ፍጡራን ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም እርሱ ፈጣሪ እነርሱ ፍጡራን መሆናቸውን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ቶማስን ግን፡- «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን፤» ብሎታል፡፡ ዮሐ ፳፥፳፯ ፡፡ ምክንያቱም አይቶ፥ ዳስሶ፥ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ የሚያምን ነውና፡፡ አንድም ሥጋውንና ደሙን ለመዳሰስ÷ ለመፈተት፥ የተጠራ የተመረጠም ካህን ነውና፡፡
ተስፋ ትንሣኤ፤
በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እየተኰነኑ በሞተ ነፍስ ተይዘው ወደ ሲኦል ይወርዱ ነበር ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ÷፳፪፡፡ «ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ( እስከ ክርስቶስ) ድረስ ሞት ነገሠ፤» የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ሮሜ ÷፲፬፡፡ ከዚህ የተነሣ እነ አብርሃም እንኳ ሳይቀሩ የወረዱት ወደ ሲኦል ነው፡፡ እነ ኢሳይያስ፡- «ጽድቃችንም ሁሉ እንደመርገም ጨርቅ ነው፤» ያሉት ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ፷፬ ÷፮፡፡ እነ ኤርምያስም፡- «ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም፥ ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፡፡» ብለዋል፡፡ ኤር ፲፪÷፲፫። በዚህ ምክንያት የብሉይ ኪዳን፥ ዘመን ዘመነ ፍዳ÷ ዘመነ ኵነ ÷ ዘመነ ጽልመት ተብሏል፡፡ በዚህ ዘመን እነ ቅዱስ ዳዊት፡- «አንሥእ ኃይለከ÷ ወነዓ አድኅነነ፤ ኃይልህን አንሣ÷ እኛንም ለማዳን (በሥጋ ተገልጸህ÷ ሰው ሁነህ አድነን)» እያሉ ወልድን ተማጽነዋል፡፡ መዝ 79÷ 2 ፡፡ «ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፤ ብርሃንህንና እውነትህን ላክልን፤ (ብርሃን ወልድን÷ እውነት መንፈስ ቅዱስን ላክልን) እነርሱ ይምሩን÷ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ÷ (ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት) ይውሰዱን  » እያሉም አብን ተማጽነዋል፡፡ መዝ ÷፫፡፡ ይህም የሚያመለክተው በዚያ በጨለማ ዘመን ሆነው ተስፋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ እንደነበረ ነው፡፡ በሞት አጠገብ ሕይወት÷ በመቃብር አጠገብ ትንሣኤ እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያደርጋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነውና፡፡ ያንጊዜ ከሲኦል እንደሚወጡ፥ የተዘጋች ገነትም እንደምትከፈትላቸው ያውቃሉና፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ የአዳም ልጆች በጠቅላላ ትንሣኤ ዘጉባኤን በተስፋ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ተስፋ ሃይማኖት እንዲይዙ÷ ምግባር እንዲሠሩ አጽንቷቸዋል፡፡ ምድራዊውን እንዲንቁ፥ ሰማያዊውን እንዲናፍቁ አድርጓቸዋል፡፡ « ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛ ጴጥ ÷፲፫፡፡ ቅዱሳን በሃይማኖት አይተዋታል፡፡ «አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ÷ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና÷ ባሕርም ወደፊት የለም፡፡ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፡፡» ይላል፡፡ ራእ ፳፩÷፫፡፡ እግዚአብሔርም፡- «እነሆ÷ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፥ የቀደሙትም አይታሰቡም÷ ወደ ልብም አይገቡም፡፡ ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ፥ ለዘላለምም ሐሴት አድርጉ፤ እነሆ÷ ኢየሩሳሌምን ለሐሴት÷ ሕዝቧንም ለደስታ እፈጥራለሁና፡፡» ብሏል፡፡ ኢሳ ፷፭፥፲፯።
ሙታን እንዴት ይነሣሉ?
እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና የሚነቃ አድርጐ ፈጥሮታል፡፡ ማንቀላፋቱ የሞት፥ መንቃቱ ደግሞ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩም የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ÷፲፡፡ የሄኖክም ከዓይነ ሞት ተሰውሮ በእግዚአብሔር መወሰድ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ÷፳፬፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላም ትንሣኤን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ የፀሐይ መውጣት የመወለድ÷ የፀሐይ መጥለቅ የመሞት÷ ከጠለቀች በኋላም እንደገና መውጣት የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን እንደሚነሡ በቃልም በተግባርም አስተምሯል፡፡ በቃል - «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ÷ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፡፡» ሲል አስተምሯል፡፡ ዮሐ ÷፳፱፡፡ በተግባርም የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነሥቷል፡፡ ዮሐ ፲፩÷፵፫፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፡- እነ ኢሳይያስ «ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ፡፡» ብለዋል። ኢሳ ፳፮÷፲፱፡፡ እነ ዳንኤልም፡- «በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች (ሁሉም) ይነቃሉ፤ እኵሌቶችም ወደ ዘላለም ሕይወት÷ እኵሌቶችም ወደ እፍረትና ዘላለም ጉስቊልና፡፡» ብለዋል፡፡ ዳን ፲፪÷፪፡፡ በተለይም ለነቢዩ ለሕዝቅኤል፥ እግዚ አብሔር፦ በአፅም የተሞላ ታላቅ ሸለቆ ካሳየው በኋላ፥ «እነዚህ የደረቁ አጥንቶች ተመልሰው በሕይወት የሚኖሩ ይመስ ልሃልንሲል ጠይቆታል፡፡ ሕዝቅኤልም፡- «እግዚአብሔር ሆይ÷ አንተ ታውቃለህ፤» የሚል መልስ ሰጥቶቷል፡፡ በመጨ ረሻም እነዚህ ሁሉ ሕይወት ዘርተው ሲነሡ አይቷል፡፡ ይኸንንም፡- «እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ÷ ትንፋሽም ገባባቸው፥ ሕያዋንም ሆኑ÷ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ፡፡» በማለት ገልጦታል፡፡ ሕዝ ፴፯፥፩-፲፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር «ነገር ግን ሰው፥ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል፡፡» ብሎ ከጠየቀ በኋላ፥ «አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፡፡» ብሏል፡፡ ከዚህም አያይዞ «የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል÷ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም (ክርስቶስ) ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው። ሁለተኛው ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊው እንደሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው ፡፡ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን፡፡» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፲፭÷፴፭-፵፱፡፡ በፊልጵስዩስ መልእክቱም፡- «ክቡር ሥጋውን እንደሚስል የተዋረ ደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» ብሏል፡፡ ፊል ÷፳፩። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም፡- «እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፤» ብሏል፡፡ ፩ኛ ዮሐ ÷፪።
የትንሣኤ ጸጋ፤
         በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል÷ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል ሙታን የነበርን ሕያዋን÷ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን÷ ሥጋውያን የነበርን መንፈሳውያን ሆነናል፡፡ «ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ÷ ድል መንሣትህ የት አለየምንል ሆነናል፡፡ ሆሴ ፲፫÷፲፬ ፩ኛቆሮ ÷፶፭፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና÷ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠ ባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋች ንን ይለውጣል፡፡» የምንል ሆነናል፤ ፊል ፫፥ -፳፩፡፡ ናፍቆታችን ሁሉ በትንሣኤ ያገኘነውን ጸጋ እውን ማድረግ ነው፡፡ «ድንኳን የሚሆነው ምድራዊው መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና÷ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድን ለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛቆሮ ፭፥፩-፪፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ÷ እድፈትም ለሌለበት÷ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ» ብሏል፡፡ ፩ኛጴጥ ÷፫፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም፡- «በሚመጡ ዘመ ናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳ የን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነ ሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።» ብሏል። ኤፌ፪÷-፯።
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡                             
Like · ·

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...