2014 ኖቬምበር 29, ቅዳሜ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ ጽዮን


አትም ኢሜይል
 ኅዳር 19 ቀን 2007 ዓ.ም.
tsion mariam 01እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልንከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ በሙሴ በኩል ታዘው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፣ አርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ-ወርቅ፣ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለ መመረጡ ምስክር የሆነችው ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል፡፡(ዕብ.9፡4)

ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የሆነውን ባስልኤልን መረጠ ፡፡(ዘፀ.25፡9) እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋም አንድ ክንድ ተኩል፣ ቁመቷም አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡

በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከሆነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝም አደረጋቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው የሚተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው ፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ በመገለጥ ሰው ከባልንጀራው እንደሚነጋገር ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡ በደመና አምድ ይታያቸው ነበር፡፡(ዘፀ.25፡22፤33፡8-11)

ወደ ትርጓሜው ስንመጣ ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትሆን፣ በውስጡዋ የያዘችው የሕጉ ጽላት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የጌታን እናት ንጽሕናን የሚያመለክት ሲሆን በውጪም በውስጧም በጥሩ ወርቅ መለበጡዋ የቅድስናዋና ድንግል በሕሊና ወድንግል በሥጋ መሆኗን የሚያስረዳን ነው፡፡

ታቦቷን አራት ሌዋውያን ካህናት ይሸከሟት ዘንድ በግራና በቀን በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ሲኖሩአት፤ በነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥ ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮንን ለማንቀሳቀስ ሲፈለግ አራት ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ንሥር፣ ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ላህም፣ ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታል፡፡(ኢሳ.6፡1-5፤ ሕዝ.1፡1-16) እንዲሁም ለአማናዊቷ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም “የምስራች የሚናገሩ፣ ሰላምንም የሚያወሩ፣ የመልካምንም ወሬ፣ መድኃኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም አምላክሽ ነግሦአል የሚሉ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እጅግ ያማሩ ናቸው” የተባለላቸው የእርሱዋንና የጌታችን ስም ተሸክመው የሚሰብኩ ወንጌላውያን አሏት፡፡(ኢሳ.52፡7)

የስርየት መክደኛው ታቹ መቀመጫው ንጹሐን አንስት ላዩ መክደኛው የንጹሐን አበው ግራና ቀኙ የወላጆቹዋ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡ እርሱን በክንፎቻቸው የጋረዱት ኪሩቤል የጠባቂ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡

የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ነው፡፡ ነገር ግን እውነታውን ስንመለከት በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት ሲቀርብ እንዳልነበር እንረዳለን፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ የለበትም፡፡ ይህ በራሱ የሚሰጠን አንድ ማስተዋል አለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በሆነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ስለዚህም ይህ ስፍራ ለዚህ እንደተጠበቀ ወይም በዚህ ምሳሌ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ሥፍራ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህ እንደሆነ ለማመልከት ሲባል ለኃጢአት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ በመንከር ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳን ውስጥ ይረጨው ነበር፡፡(ዘሌዋ.4፡6) ነገር ግን ይህ ደም ከዚያ ስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ ያለበት መሥዋዕት መለኮት የተዋሐደው ነፍስ ግን የተለየው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነውና፡፡

ይህ የስርየት መክደኛ ሌላም ለእኛ የሚያስተላለፈው መልእክት አለው፡፡ መልእክቱም አማናዊው መሥዋዕት መቅረቡ እንደማይቀርና፣ መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር በምህረት በሚገለጥበት በጸጋ ዙፋኑ በጽላቱ ላይ መሆን እንዳለበት ነው፡፡(ዕብ.4፡16) በዚህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና በየስፍራውም ስለስሜ ዕጣንን ያጥናሉ ንጹሕም ቁርባን ያቀርባሉ”(ሚል.1፡11) እንዳለው የስርየት መክደኛው በዓለም ዙሪያ ላለችው አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጽላቱ(ታቦቱ) የሚያርፍበት ስፍራ መንበር ተብሎ ሲጠራ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበትና ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ የሚፈተትበት ደግሞ ጽላት ወይም ታቦት ወይም መሠዊያ ተብሎ ይጠራል፡፡

የስርየት መክደኛው በታቦቱ አናት ላይ መሆኑም ቅዱስ ኤፍሬም “የእኛን ሥጋ ለነሣኸውና ፣ መልሰህ ለእኛ ለሰጠኸን ፣ ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን፡፡ ከእኛ በሆነው ሥጋህ በኩል እጅግ የበዛውን የአንተን ስጦታ ተቀበልን፡፡” ብሎ እንዳመሰገነ፤ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጉምን ይረዳል፡፡

ይህን ድንቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉምን ይበልጥ ለመረዳት አንድ ምሳሌ የሚሆነንን እውነታ እንመልከት፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳር ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ጊዜ በታቦተ ጽዮን ፊት ለእግዚአብሔር በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር፡፡(2ሳሙ.6፡12-17) ይህን ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሞል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስት ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታችንን እናት የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ከእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ በደስታ ዘሎአል(ሰግዶአል)፡፡ (ሉቃ.1፡44) ቅዱስ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት እንዲያ ደስ መሰኘቱና ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱ ለሰው ልጆች ሁሉ የመዳናቸው ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጁዋን ኢየሱስ ክርስቶስን በታቦተ ጽዮን በኩል በማየቱ ነበር፡፡

ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነታ ይጋሩታል ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም፡- “ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት አጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተሰባብሮ ወደቀ፡፡ ታቦተ ጽዮን በተባለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የድል አዋጅ ታወጀ፡፡ በቃል ኪዳኑዋ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንዲሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሳ፡፡

እግዚአብሔር በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በመግለጥ ዳጎንን ሰባብሮ እንደጣለው እንዲሁ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡” (1ሳሙ.5፤6) ሲል ቅዱስ ጀሮም ደግሞ “ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስትና ንጽሕት ነበረች፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥ የሕጉ ጽላት ብቻ እንደነበር እንዲሁ እርሷም በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሃሳብ አልነበራትም፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት ፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ፅላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ቅድስት ነሽ፡፡” ብሎ ሲያመሰግናት፤ የእስክንድርያው ዲዮናስዮስ ደግሞ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይሆን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ ማደሪያ ትሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠችና በመንፈስ ቅዱስ ለእርሱ ማደሪያነት የተዘጋጀች ናት፡፡ የመለኮት ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር የከተመባት ከተማ ሆና ትኖር ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትማለች” በማለት ስለእርሱዋ ይመሰክራል፡፡

አዳም ድኅነቱ ከሴት ወገን በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሆነ ተረድቶ ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም እንደሰጣት እንዲሁ ንጉሥ ዳዊት በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ አምባዬና መጠጊያዬ ነሽ ሲላት “ጽዮን” ብሎ ለድንግል ስያሜን እንደሰጣት በመዝሙራቱ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ጽዮን የንጉሥ ዳዊት ተራራማዋ ከተማ ስትሆን፣ የስሟ ትርጓሜ አምባ፣ መጠጊያ ማለት ነው፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለ ድንግል ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡

ነቢያት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም እንደሚጠቀሙ ወደ ብሉይ ኪዳን ሳንገባ በሐዲስ ኪዳን ብቻ ስለ ጽዮን የተጻፉትን በማንሣት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ ከአይሁድ ወገን የሆኑ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማቆም ሲሉ በክርስቶስ ከማመን ስለተመለሱት ሲጽፍ፡- “እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ አለት አኖራለሁ”(ኢሳ28፡16፣8፡14) አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ስለክርስቶስ የተነገረ ነው በማለት በሮሜ 9፡33 ላይ ጠቅሶት እናገኛለን፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሆነ በዚህ ኃይለ ቃል መረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ አለት የተባለው ክርስቶስ እንደሆነም “እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡”(ሉቃ.2፡34-35) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ አለት የተባለውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን መባሉዋን በእነዚህ ጥቅሶች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

tsion mariam 02ነቢዩ ዳዊትና ኢሳይያስ ጽዮን ከተሰኘች የሙሴ ፅላት ካህኑ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካኝነት አፋዊ ድኅነት እንደተደረገ፣ ከእመቤታችን ከተወለደው አማኑኤል አማናዊ ድኅነት እንዲፈጸምልን “መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኝነትን ያስወግዳል”(መዝ.13፡10፤ኢሳ.59፡20) በማለት ስለክርስቶስ ትንቢትን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ሰጥቶ በሮሜ.11፡26 ላይ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን መሆኑን ማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እርሱ ከእርሱዋ እንጂ ከሌላ አልተወለደምና፡፡ ነገር ግን “መድኃኒት” የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ “መልአኩም እንዲህ አላቸው፡- እነሆ ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ በዳዊት ከተማ መድኅኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ” (ሉቃ.2፡10) በማለት ገልጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ማለት “መድኃኒት ማለት ነው (ማቴ.1፡21) የኢየሱስም እናት ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኑዋን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ነቢያቱ “መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል” ሲሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ምንም እንኳ ቅዱስ ዳዊትና ሌሎች ነቢያት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ለመናገር ሲሉ ጽዮን የሚለውን ስም አብዝተው ይጠቀሙ እንጂ አልፎ አልፎ ግን ጽዮን በማለት ስለ ከተማዋ ተናግረው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ሚክያስ “ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን ትታረሳለች”(ሚክ.3፡12)ይላል፡፡ ይህ በቀጥታ ስለጽዮን ከተማ የተነገረ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን መናገር ሲፈልግ ስለእርሱ የሚናገሩትን ብቻ መርጦ እንደተጠቀመ እንመለከታለን፡፡ እኛም እንዲሁ ለቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩትን አስተውለን ልንለያቸው ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ያልተጻፉ ነገር ግን ጽዮን የሚለውን ስም ይዘው የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አሉና፡፡ ቢሆንም ስለታቦተ ጽዮን የተጻፉ ገቢረ ተአምራት ሁሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ገቢረ ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ተርጉማ ለልጆቹዋ ታስተምራለች፡፡ በኅዳር 21 ቀንም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙት ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ታላላቅ ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር በድኅነታችን ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድርሻ ምን እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ለምሳሌ ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት እንደተከፈለ እንዲሁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ ጥምቀትን በራሱ ጥምቀት በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን እናወሳበታለን(ኢያ.3፤ ማቴ.3፡13-17)፡፡ ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙ ወቅት ታቦተ ጽዮንን ማርከዋት ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት ነበር፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ዳጎኑን በፊቷ ሰባብራ እንደጣለችው እንዲሁ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን ድል መነሳቱን እናወሳበታለን፡፡ ((1ሳሙ.5፤6)

በዚህ መልክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንጎቿን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለ ልጁዋ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም በእርሱ ስለተሰጠን ሰማያዊ የአገልግሎት ሥርዐት፣ ስለ ታቦት ጥቅምና አገልግሎት፤ ታቦተ ጽዮንንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር በሰፊው እንደምታስተምር መረዳት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በእኛ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር አሜን

2014 ኖቬምበር 26, ረቡዕ

አባ ፊልጶስን ፍለጋ (የመጨረሻው ክፍል)

                                      

መኪናዋ ተገፍታ ለመጨረሻ ጊዜ ስትወጣ
የአካባቢው ገበሬዎችና አሣፍረናቸው የነበሩ ሌሎች ገበሬዎች ተባብረው መኪናዋን በዳገቱ መግፋት ጀመሩ፡፡ ድንበሩ አንዴ ገብቶ መሪ ይዞ ይነዳል፣ አንዴ ወርዶ ጎማውን በካልቾ ይማታል፡፡ ሙሉቀን በትጋትና ተስፋ ባለመቁረጥ መኪናዋን ከፖሊሶቹና ከገበሬዎቹ ጋር ይገፋል፡፡ ቀለመወርቅ መኪናዋን የሚመለከት የሕግ ዐንቀጽ የሚፈልግ ይመስል አንገቱን ደፍቶ አንዳች ነገር ያስሳል፡፡ ኤልያስ መነጽሩን ከፍ እያደረገ ለድንበሩ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ ይህ ሁሉ ግን መኪናዋን ዳገት እንድትወጣ አላስቻላትም፡፡

እኛም የወጣችውን መኪና በእግር ስንከተል
ቀለመወርቅ ‹ድንጋዩን አንሡ› የሚለው ጥቅስ ትዝ ብሎት ነው መሰል መኪና መንገዱ ውስጥ ገብቶ ጭንቅላት ጭንቅላት የሚያህሉ ድንጋዮችን ማንሣት ጀመረ፡፡ መኪናዋም ጥረቱን አደነቀችለት መሰል ወደላይ የመውጣት ተስፋ ሰጠች፡፡ ገበሬዎቹም ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው ወደ ላይ ገፏት፡፡ ‹ተመስገን› ዋናውን ዳገት እያቃሰተች ወጣችና አፋፍ ላይ ቆመች፡፡ የሁሉም ፊት ከኀዘን ወደ ደስታ፣ ከቀቢጸ ተስፋ ወደ ተስፋ ተቀየረ፡፡
‹‹አይዟችሁ ከዚህ በኋላ ሌላ ዳገት የለም›› አለን አብሮ የነበረው ቆፍጣናና ጉልበታም ገበሬ፡፡ መኪና የገፋበትን ክንዱን እየወዘወዘ፡፡ እውነትም እንዳለው ቀሪው መንገዳችን ሜዳ ነበረ፡፡ ከውስጥ እኛ፤ ከውጭ ገበሬዎቹ ተሣፈርንና ያለፈ ነገራችንን እያነሣን ወደ መዳረሻችን ጉዞ ቀጠልን፡፡ 
መኪናዋ በዳገቱ መጨረሻ ላይ
እነሆ የኳሳ ደረስን፡፡ በመኪና ልንሄድበት የምንችለው የመጨረሻው ቦታ የኳሳ ከተማ ናት፡፡ ሊቀ ካህናቱ የምንሄድበትን በረሃ በሩቁ አመለከቱን፡፡ ‹ልብ የሌላትን መኪና ገፍቶ እዚህ ያደረሰ አምላክ ልብ የሰጠንን እኛን እዚያ ማድረስ አያቅተውም› ብለን አመንን፡፡ የከተማው ፖሊስ ጣቢያ መኪናችንን አቆምን፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች፣ የወረዳው ሊቀ ካህናት፣ ከወረዳው ቤተ ክህነት የመጡ አንድ ሌላ ዳዊት ደጋሚ ካህን እና እኛ አራታችን በእግር ለመገስገስ ተዘጋጀን፡፡ እኒህ ዳዊት ደጋሚ ካህን የሚገርም ተሰጥዖ አላቸው፡፡ እኛ እንሂድ አንሂድ ስንጨነቅ፣ ሰው ሁሉ የመሰለውን እየሰነዘረ ሲከራከር፣ መኪና ስትሄድ፣ መኪና ስትቆም እርሳቸው ዳዊት መድገማቸውን አያቆሙም፡፡ ባይሆን እንደ መሐል ከተማ ሰው ዲፕሎማሲ ባለመቻላቸው ድንበሩ ተቀይሟቸው ነበር፡፡ ‹ምን ያህል መንገድ ይቀረናል?> ሲላቸው መልሳቸው ‹ገና ምኑ ተነካ› ነው፡፡ ‹ሞራል አይሰጡም፤ ተስፋ ያስቆርጣሉ› አለ ድንበሩ፡፡ እርሳቸው እንደሆነ ቁርጥ ያለ የዘመድ ዋጋ ነው የሚያውቁት፡፡
ዳገቱ አለቀ
ከየኳሳ ከተማ ሁለተኛው ምእራፍ ተጀመረ፡፡ በሩቁ የምናቋርጠው በረሃ ተዘርግቷል፡፡ መንገድ ላይ የደብረ ዕንቁ አገልጋይ የሆኑ መሪጌታ ይጠብቁናል፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ ኤልያስ ማንከስ ጀመረ፡፡ ከዚህ ጉዞ ላለመቅረት ብሎ እንጂ እግሩን ኦፕራስዮን አድርጎ ነበር፡፡ ያደረገው ጫማ ሸበጥ ነገር ነው፡፡ 
የወንዝ ዳር ረፍት
ድንበሩና አንደኛው ፖሊስ ከፊት፣ ካህናቱና ሙሉ ቀን ከመካከል፣ ከእነርሱ ቀጥሎ ቀለመወርቅ፣ እኔና ኤልያስ በስተመጨረሻ ‹አዴም ነዲያቸው› እያልን  እንጓዝ ነበር፡፡ የኤልያስ እግር መቁሰል ጀምሯል፡፡
በበረሃው መግቢያ በር
መንደሮችንና እርሻዎችን እያቋረጥን ነበር የምንጓዘው፡፡ አሥር ዓመት የማይሞላቸው ሴትና ወንድ እረኞች እጃቸውን አፋቸው ላይ አድርገው በግርምት ያዩናል፡፡ 
አዲስ ጠረን የሸተታቸው ከብቶች በአጠገባቸው ስናልፍ ቀንዳቸውን ሊፈትሹብን ይፈልጋሉ፡፡ ሰላምታ የማይጓደልባቸው የስማዳ ገበሬዎች ከዐጨዳቸው ላይ ብዲግ እያሉ፣ በሽክና ጠላቸውን ይዘው በመጋበዝ በሰላምታ ያሳልፉናል፡፡ 
የቸሩ የስማዳ ገበሬ ግብዣ
አሁን የመሪጌታ ጥዑመ ልሳን እርሻና መንደር ጋ ደረስን፡፡ እኒህ መሪጌታ ‹በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ› የሚለውን ቃል አክብረው፣ ከተማውን ትተው እዚህ ገጠር ተቀምጠው ደቀ መዛሙርት የሚያፈሩ መሪጌታ ናቸው፡፡ ምርግትናውን ከክህነት፣ ክህነቱንም ከግብርና አስተባብረው እያረሱ ያስተምራሉ፣ እያስተማሩም ያርሳሉ፡፡ ደቀ መዝሙሮቻቸው በአንድ በኩል ለመምህራቸው የጉልበት አገልግሎት ይሰጣሉ፤ በሌላ በኩል ከመምህሩ ዕውቀት ይሸምታሉ፡፡ ተማሪዎቻቸውን በመደዳ ያስቀምጡና በሬያቸውን ይጠምዳሉ፡፡ ወዲያ ሲሄዱ ለአንዱ ቀለም ይነግራሉ፣ ወዲህ ሲመጡም ለሌላው ቀለም ይነግራሉ፡፡ እርሻውም የታደለ ነው፤ ቃለ እግዚአብሔር እየፈሰሰበት ይታረሳል፣ ይዘራል፣ ይታጨዳል፣ ይወቃል፡፡ ይህንን የመሰሉ ሰዎች ያመረቱት እህል እየተቀላቀለበት ሳይሆን አይቀርም ሞሰባችን ረድኤት የነበረው፡፡
እረፍት በመሪጌታ እርሻ አጠገብ
በመሪጌታው እርሻ ጎን ዕረፍት አደረግን፡፡ እግረ መንገዳችንንም እርሳቸውን እንጠብቅ ዘንድ፡፡ የመምህሩ ቤት ከመንገዳችን በስተ ቀኝ ከዛፎቹ ሥር ነው፡፡ ዙርያውን በተማሪዎቻቸው ጎጆዎች ተከብቧል፡፡ አሁን የአጨዳ ጊዜ በመሆኑ ተማሪዎቻቸውን አስተባብረው ወደ አጨዳ ሄደዋል፡፡ አውድማቸው የተቀመጥንበት አካባቢ ነውና እህሉን ወደዚህ ያመጣሉ፡፡ ከባለቤታቸው ጋር እያወጋን ጠበቅናቸው፡፡ እግረ መንገዳቸውን አብረውን ያሉት ካህን ስለ ጌርጌስ ያወጉን ጀመር፡፡ 
አባ ፊልጶስ ከጌርጌስ ወደ ሐቃሊት የመጣበት በረሃ
‹ጌርጌስ ማለት ያ ከማዶ የምታዩት ሜዳማ ተራራ ነው፡፡ በደብረ ዕንቁ እና በጌርጌስ መካከል ታላቅ በረሃ አለ፡፡ ጌርጌስ አጠገብ የጃምባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ያለበት ጋሼና የሚባል ቦታ አለ፡፡› ‹በዜና መዋዕሉ ከጋሼና እስከ ዐንቆ የሚለው ይህንን ነው ማለት ነው› አልኩ፡፡ አቡነ ፊልጶስ ወደ ሐቃሊት ሲመጣ ከአቡነ ሰላማ መተርጉም ጋር የተገናኘው በጌርጌስ መሆኑን ገድሉ ይነግረናል፡፡ ይህቺ ቦታ ከጥንት ጀምሮ የጳጳሳት መቀመጫ ነበረች፡፡ አሁን በትክክልም የአቡነ ፊልጶስን የመጨረሻ ቦታ እያገኘነው ነው ማለት ነው፡፡
የመሪጌታ ተማሪዎች ጎጆ
አንቆስ ማናት? ደብረ ዕንቁ ትሆን? ይህንን እያሰብኩ እያለ፡፡ ያን ጊዜ አንደኛውን ፖሊስ ዝም ብለን ክንቀመጥ ብዬ ‹እንዴው ስለ ሀገሩ ምን ይዘፈናል?› አልኩት፡፡ እርሱም እንዲህ አለኝ
ላሊበላን መሳም በከንቱ ድካም ነው
ከየኳሳ በታች ዐንቆ መጨምጨም ነው
እጅግ የሚገርም ሰምና ወርቅ ቅኔ፡፡ የኳሳ መኪናችንን ያቆምንባት ከተማ ናት፡፡ ‹ከየኳሳ በታች ዐንቆ መጨምጨም ነው› አለ፡፡ ‹ዐንቆ ማናት?› አልኩት፡፡ ‹ዐንቆ ማለት ደብረ ዕንቁ ናት› አለኝ፡፡ እፎይ አልኩ፡፡ ‹ከዐንቆ እስከ ጋሼና› የሚለው ተፈታ ማለት ነው፡፡ ‹ሐቃሊት የተባለችውኮ ደብረ ዕንቁ ናት፤ ሐቃሊት ማለት በበረሃ ያለች ቦታ ማለት ነው› አሉና ካህኑ ይዘረዝሩት ጀመር፡፡ ገርሞኝ ነበር በደስታ የማያቸው፡፡ ‹ሐቃሊት የታለች?› አልኳቸው፡፡ ሐቃሊትን ትንሽ ከሄድን በኋላ ታያታለህ፤ ጌርጌስ ያውልህ፡፡ አቡነ ፊልጶስ የታመመው እዚያ ነው፡፡ ወደ ሐቃሊት የመጣው ታቹን በበረሃው አድርጎ ነው፡፡ በበረሃው ከመጣ በኋላ እዚህ ዳገቱ ላይ ሲደርስ ዐረፈ፡፡ ያረፈበት ቦታ ይኼውልህ፤ አሁን የታቦት ማርገጃ አድርገነዋል›› አሉና አሳዩኝ፡፡ ቦታውን ወድቄ ተሳለምኩት፡፡ ዙርያውን ታጥሮ አንዲት ዛፍ በቅላበታለች፡፡ አካባቢው ለጥ ያለ ሜዳ ነው፡፡ 
የመሪጌታ ተማሪ ነዶ ተሸክሞ
እኒህ ዳዊት ደጋሚ ካህን ብርቱ ናቸው፡፡ መምህሩ እስኪመጡ ተማሪዎቻቸው ያመጡትን የጤፍ ነዶ በአውድማው ላይ ይከምሩላቸው ጀመር፡፡ የቄስና የሴት እንግዳ የለውም ማለት ይኼ ነው፡፡ መምህሩ ነዷቸውን ተሸክመው መጡ፡፡ የተሸከሙትን አወረዱና ሰላም አሉን፡፡ ከእርሳቸው ጋር ወደ ደብረ ዕንቁ ለመሄድ መምጣታችንን ስንነግራቸው በደስታ አብረውን ለመሄድ ተነሡ፡፡ ወደ ቤታቸው ደርሰው ልብሳቸውን ቀየሩና ከእኛ ጋር ተቀላቀሉ፡፡
መሪጌታ ነዶ ተሸክመው
እነሆ አሁን የበረሃውን መንገድ ለማግኘት አባ ፊልጶስ ከጌርጌስ ሲመጣ ባረፈበት ሜዳ በኩል አቋርጠን መንገድ ጀመርን፡፡ መሪጌታ በሁለት ነገር ጠቅመውኛል፡፡ በአንድ በኩል ታሪክና ጨዋታ ዐዋቂ ስለሆኑ መንገዱን ያለ ድካም እንድንጓዝ አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእድሜ ጠገቡ ጃንጥላቸው የስማዳን ፀሐይ መክተውልኛል፡፡ 
ወደ በረሃው ጉዞ
አሁን ኤልያስ እያነከሰ፣ ድንበሩ መሐል መጥቶ ፣ ቀለመወርቅና ሙሉቀን ከካህናቱ ጋር አብሪ ሆነው ወደ ቆላው ልንገባ ነው፡፡ ቆላው ሁለት ተራሮችን ወጥቶ መውረድና ሦስተኛውን ተራራ መውጣት ይጠይቃል፡፡ መሪጌታ አቡነ ፊልጶስ ከጌርጌስ ወደ ሐቃሊት የመጣበትን በረሃ አሳዩን፡፡ ከጎንና ጎን ተራራ ያለበት ገደል ነው፡፡
ከመጀመርያው ተራራ ወርደን
 አሁን ደብረ ሐቃሊት ከሩቁ ትታያለች፡፡ ሲቀርቧት የምትርቅ ሞሰበ ወርቅ የመሰለች ተራራ ናት፡፡ ወደ እርሷ ለመድረስ ግን ሁለት ተራሮች እንደ መቅድም ሆነውላታል፡፡ ታምሯ እርሷ ናት፡፡
ኤልያስ፡- ከሁለት እግር ወደ ሦስት እግር
ወደ ሁለት ሰዓት የፈጀ የመውጣትና የመወረድ ጉዞ በማካሄድ ላይ ነን፡፡ ቆላው ውስጥ፡፡ አሁን የምንሄድበት መንገድ አንድ ሰው ብቻ የሚያሳልፍ የተፈጥሮ ድልድይ ነው፡፡ በግራና በቀኝ ገደል ነው፡፡ ‹ከዚህ የተንከባለለ ወይ በሽሎ ወይ ዓባይ ነው የሚገኘው› ብለውኛል መሪጌታ፡፡ እኛም ከሁለቱ በአንዱ ላለመገኘት በጥንቃቄ መሥመር ሠርተን በመጓዝ ላይ ነን፡፡ አንዱን ተራራ ይህንን በመሰለ እንደ ባሕረ እሳት መንገድ በቀጠነ መሷለኪያ አለፍነውና ሌላ ተራራ ከፊታችን ተገተረ፡፡
ከደብረ ዕንቁ ማዶ የሚገኘው ጌርጌስ ነው
እርሱ ደግሞ ዐለቶች ተሰባስበው በማኅበር የመሠረቱት ነው፡፡ ከዐለቱ በስተጀርባ ተዙሮ ወደ ፊቱ ለመምጣት ከቁጥቋጦና ስለታም ድንጋዮች ጋር ትግል ይጠይቃል፡፡ በዐለቱ ጫፍ ላይ ሆናችሁ የመጣችሁበትን መንገድ ወደታች ስታዩት እናንተ ከጠፈር ጥግ ያላችሁ ነው የሚመስላችሁ፡፡ ሁሉም ነገር የጣት ቁራጭ አክሎ ነው የሚታየው፡፡ ዐለታማውን ተራራ ተጠማዝዘን ወረድነውና ተራራውን ከደብረ ዕንቁ ጋር ወደሚያያይዘው ቀጭን መንገድ ገባን፡፡ ይህም በግራና ቀኝ ገደል ያጀበው፣ ከቅድሙ ሰርጥ ግን ሰፋ የሚል መንገድ ነው፡፡ 
ሁለተኛው ዐለታማ ተራራ
ከባዱ ዳገት ወደ ደብረ ዕንቁ የሚያስወጣው ነው፡፡ ተራራውን እንደ ዘንዶ መጠማዘዝን ይጠይቃል፡፡ ደግነቱ መንገዱ ደልደል ያለ ነው፡፡ ለሃያ ደቂቃ ያህል ከዞርነው በኋላ አንድ ቦታ አገኘን፡፡ ‹ይህ ቦታ ምዕራፈ ወለተ ጴጥሮስ ይባላል› አሉን መሪጌታ ጥዑመ ልሳን፡፡ ‹‹ወለተ ጴጥሮስ ይህንን ገዳም ውኃ በመቅዳት አገልግላለች፤ ውኃ ቀድታ ስትመጣ የምታርፍበት ቦታ ስለሆነ ምዕራፈ ወለተ ጴጥሮስ ተባለ›› አሉን፡፡ ይህ ታሪክ በወለተ ጴጥሮስ ገድል ላይ ተጽፏል፡፡ 
ምእራፈ ወለተ ጴጥሮስ
ምዕራፈ ወለተ ጴጥሮስን ካለፍን ከሃያ ደቂቃ በኋላ የገዳሙን በር አገኘነው፡፡ እነሆ ጉዟችን ወደ መጠናቀቂያው እየደረሰ ነው፡፡ የገዳሙን በር ከዘለቃችሁ በኋላ ሌላ መንገድም ይጠብቃችኋል፡፡ ያውም ተራራማ መንገድ፡፡ ደግነቱ ብዙም ሩቅ አይደለም፡፡ 
ከተራራው ሥር
ፊት ለፊታችን ደብረ ዕንቁ ማርያም ታየችን፡፡ አንቺን ፍለጋ ስንት ጊዜ ለፋን፣ ስንቱንስ ሀገር አቋረጥን፡፡ ስንቱን ተራራና ገደልስ ተሻገርን፡፡ መሪጌታ ቤተ ክርስቲያኑን አስከፈቱልን፤ እኛም ወደ ወስጥ ዘለቅን፡፡ ጸሎት ካደረስን በኋላ ‹ክህነት ያላችሁ ወደ ውስጥ ዝለቁ› አሉ መሪጌታ፡፡ እኛም ወደ ቅድስቱ ዘለቅን፡፡ አቡነ ፊልጶስ ተቀብሮበት የነበረውንም ቦታ ከመንበሩ ሥር አሳዩን፡፡ የአቡነ ፊልጶስ ዐፅም ለ140 ዓመታት የቆየው እዚህ ነበር፡፡ በዐፄ እስክንድር ዘመን (1471-1487 ዓም) በእጨጌ መርሐ ክርስቶስ ጊዜ በእጨጌ መርሐ ክርስቶስ ጥያቄና በንጉሡ ፈቃድ ከደብረ ሐቃሊት ፈልሶ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገባ፡፡ 
አባ ፊልጶስ ያረፈበት ቦታ
ገዳማውያኑ መልካም አቀባበል ነበር ያደረጉልን፤ ገድሉን እያነበቡ ታሪኩን በመንገር፤ ገዳማዊ የሆነውን ምግብ በማቅረብ፤ የበረከቱም ተካፋይ በማድረግ፡፡ ደብረ ዕንቁ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተጠና ብዙ ነገር አላት፡፡ የአቡነ ሰላማ መተርጉም መቀመጫ ነበረችና ምናልባት ጳጳሱ ከአሥራ አንድ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍትን ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተረጎሙት እዚህ ቦታ ይሆን ይሆናል፡፡
ደብረ ሐቃሊት በር ደረስን
 እርሳቸው ለዐረብኛው እንጂ ለግእዙ አዲስ ናቸውና ታላቁን ሥራ የሠሩት በደብረ ዕንቁ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ደብረ ዕንቁ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የተዋሕዶዎች መሸሸጊያና መወያያ በመሆንም ታላቅ ታሪክ አላት፡፡ እነ ዐራት ዓይና ጎሹን የመሳሰሉ የቅርብ ዘመን ሊቃውንትም መፍለቂያ ናት፡፡ በደብረ ዕንቁና በዲማ ጊዮርጊስ ሊቃውንት መካከል የነበረው የዘመናት ግንኙነትም ሊጠና የሚገባው ነገር ነው፡፡
ብቻ እኛ እዚህ ደርሰናል፡፡ በጉዟችን የረዱንን የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከትን፣ የስማዳ ወረዳ ቤተ ክህነትን፣ የስማዳ ወረዳ መስተዳድርን፣ የደብረ ዕንቁ ገዳም አባቶችንና ሌሎችንም እግዚአብሔር ዋጋቸውን ይክፈል እንላለን፡፡ 
ደብረ ዕንቁ ማርያም
እንደነ አቡነ ፊልጶስ ያሉ በቤተ ክርስቲያን ዘላለም የሚያበራ፣ ለትውልዱም የሥነ ምግባርና የሞራል ስንቅ የሚሆን ታሪክ ያላቸው ሰማዕታት አባቶች እንደ አዲስ አበባ ባሉ ታላላቅ ከተሞች ቤተ ክርስቲያን ሊታነጽላቸውና ትውልዱ እንዲያውቃቸው ሊደረግ ይገባል፡፡ 
አባ ፊልጶስ ያረፈበት ቦታ፣ ከመንበሩ ሥር
በአንዳንድ ቅዱሳን ስም አምስትና ስድስት ቤተ ክርስቲያን በአንድ ከተማ ከመትከል ለእነ አቡነ ፊልጶስ አንድ ዕድል መስጠት በታሪክም በሰማይም የሚያስመሰግንና ዋጋ ያለው ተግባር ይሆናል፡፡ በማኅበር ተሰባስበው ክርስቲያናዊ ሥራ የሚሠሩ ወጣቶችም እንደ አቡነ ፊልጶስ  ባሉ አባቶች ስም በመጠራትና ታሪካቸውን ከፍ በማድረግ የበረከታቸው ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ታሪክ ይጋብዛቸዋል፡፡
እረፍት በገዳሙ ግቢ
እነሆ እንደመጣነው ልንመለስ ነው፡፡ ያው ተራራና ገደል፣ ያችው መኪና ይጠብቁናል፡፡
የገዳሙ ግብዣ

ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን የአገልግሎት መንፈስ እና አንድነት ማንም አይበጥሰውም!!

የማኀበረ ቅዱሳን አስተዋጽኦ ሁለት መልክ አለው፡፡ አንደኛው የሚታየውን ነገር መስራቱ ነው፡፡ ለእኔ ግን ሁሌም የሚገርመኝና ማኀበረ ቅዱሳን ውስጥ እንዳገለግል ጉልበት የሚሆነኝ የማይታየው ነገር ነው፡፡ ይሔ ሁሉ ሰው፣ ይሔ ሁሉ ምእመን፣ ይሔ ሁሉ የግቢ ጉባኤ ተማሪ በአንድነት ስለ ቤተክርስቲያን እንዲመክር፣ እንዲያገለግል ያደረገው ማኀበሩ የፈጠረው የአገልግሎት ፍልስፍና ነው፡፡ ዘር፣ የትምህርት ደረጃ፣ ወንዝ፣ ከሀገር ውጭ፣ ከተማ፣ ገጠር ሳይል ሁሉም አኩል ለቤተክርስቲያን እንዲጨነቅ አድርጓል፡፡ ይህን አስብ ሁሌም ጉልበት ይሰጥሃል፡፡ አሁን የቤተክርስቲያን ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንደ ቤተክርስቲያን አባቶች እንዲያስብ ፣ እንዲጨነቅ፣ እንዲሟገት እንዲከራከር ፍልስፍናውን/አስተሳሰቡን የፈጠረው ማኀበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን የአገልግሎት መንፈስና አንድነት ማንም አይበጥሰውም፡፡
(ዶክተር ዘርዓየሁ) ከመጽሔተ ተልዕኮ ዘማኀበረ ቅዱሳን ጋር ባደረገው ቆይታ የተናገረው፡፡

2014 ኖቬምበር 24, ሰኞ

ጾም - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል አራት)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኞ ኅዳር 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 ውድ የመቅረዝ ወዳጆች! እንዴት ዋላችኁ? እንዴት አረፈዳችኁ? እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላምና በጤና አደረሳችኁ፡፡ ዛሬም አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እጅግ ጣፋጭ የኾነ ስብከቱን ቀጥሏል፡፡ የዛሬውን ስብከት የተረጐምንላችኁ የኦሪት ዘፍጥረትን እየተረጐመ ባስተማረው የአራተኛው ቀን ስብከቱ ነው፡፡ ምእመናኑ ወደ ጉባኤው መምጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በየቀኑ ያስቀድሳሉ፤ በየቀኑ ይቈርባሉ፡፡ ቅዳሴውን ካስቀደሱና ከቅዱስ ቁርባኑ ከተሳተፉ በኋላም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሚያስተምራቸው ትምህርት ነፍሳቸውን መግበው ይሔዳሉ፡፡ ይኽን በየቀኑ እያየ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጣም ይደሰታል፡፡ የምእመናኑ ትጋት እያየ ርሱም ማስተማሩን ቀጥሏል፡፡ በተለይ በሦስተኛው ቀን ዶፍ ዝናብ እየዘነበባቸው እንኳን ምእመናኑ አለመበተናቸውን አይቶ ቅዱሱን እጅግ በጣም አስደስቶታል፡፡ በመኾኑም በዛሬው ስብከቱ ይኽን የምእመናኑን ትጋት አይቶ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ ምንም እንኳን ከዛሬ 1600 ዓመታት የተሰበከ ስብከት ቢኾንም ዛሬም አዲስ ነው፤ አይጠገብም፤ ነፍስን ይመልሳል፡፡ እስኪ እኔ ነገር ከማስረዝምባችኁ ከራሱ ከሊቁ አብረን እንማር፡፡ የነቢያትን፣ የሐዋርያትን፣ የሊቃውንትን ጉባኤ የባረከ አምላክ የእኛንም ይባርክልን፡፡ በያለንበት ኾነንም ቃሉን እንድንማር ልቡናችንን ይክፈትልን፡፡ አሜን!!!

እጅግ የምወዳችኁ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! በታላቅ ትጋትና ጉጉት ኾናችኁ በየቀኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣታችኁ እያየኹ ነፍሴ ደስ ተሰኘች፤ ዕለት ዕለትም አምላኬን ስለ እናንተ አመሰግነዋለኹ፡፡ ረሃብ የጤነኝነት ስሜት ነው፤ ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር መጓጓትም በመንፈሳዊ ሕይወት ጤነኛ መኾናችንን የሚያመለክት ነው፡፡ ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይኹንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ፡- “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና” /ማቴ.5፡6/ ያለውም ይኽን የሚያስረዳ ነው፡፡
 እንዴት አድርጌ እንደማመሰግናችኁ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም ጽድቅን ከመራባችኁና ከመጠማታችኁ የተነሣ ብፁዓን ኾናችኁ ሳለ አኹንም ይኽን ማድረጋችኁን አላቆማችኁምና፡፡ ልጆቼ! አባታችን እግዚአብሔር እንዴት እንደሚወደን እያያችኁ ነውን? ከእኛ የሚመጣ ትንሽ መነሣሣት ካለ እግዚአብሔር ከእኛ መነሣሣት በላይ በኾነ በረከት ነው የሚባርከን፡፡ እኛ ትንሽ ፈቃደኞች ስንኾን ርሱ ግን ከእኛ በላይ ብዙ ጸጋና በረከት ይሰጠናል፡፡

እኔም ይኽን እየተመለከትኩ እናንተን ለማስተማር እጓጓለኹ፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለውጥ እንድናመጣ በጣም እጥራለኹ፡፡ ማስተማሬንም እቀጥላለኹ፡፡ እናንተ በመንፈሳዊ ሕይወታችኁ እንድትበረቱ ማንኛውንም ዓይነት መሥዋዕት እከፍላለኹ፡፡ ምክንያቱም እዚኽ ብቻ እንድታቆሙ አልፈልግምና፡፡ ከዚኽም በበለጠ ወደ መንፈሳዊ ከፍታ እንድትወጡ እፈልጋለኹ፡፡ ከዚኽ በበለጠ በምትውሉበት የሥራ ቦታ፣ በምትውሉበት የትምህርት ቦታ አስተማሪዎች እንድትኾኑ እፈልጋለኹ፡፡ ቆማችኁ በማስተማር ሳይኾን መልካም ሥራችኁን አይተው ብዙዎች እንዲማሩ እፈልጋለኹና ትጋቴን ከወትሮው ይልቅ እጨምራለኹ፡፡ ድካሜ በከንቱ እንዳልቀረ እያየኹ ነውና ከዚኽ የበለጠ ማስተማር እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡
 ከምንም በላይ ደስ ያለኝ ደግሞ የዘራነውን ዘር ቀን በቀን እየጐመራ ነው እየሔደ ያለው፡፡ በወንጌል ላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት እንቅፋት አላጋጠመንም፡፡ እንደምታስታውሱት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘሩ ምሳሌ ባስተማረው ትምህርት ከተዘራው ዘር አንድ አራተኛው ብቻ ጥሩ ፍሬ ሲያፈራ ሦስት አራተኛው ግን እንደተጠበቀው አልኾነም፡፡ በመንገድ ዳር ላይ የወደቀው ዘር ወፎች መጥተው በልተዉታል፡፡ ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ የወደቀው ፀሐይ ሲወጣ ጠውልጎ ወዲያው ደርቋል፡፡ በእሾኽ መካከል የወደቀውም እሾኹ አንቆታል፡፡ በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ግን መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ አፈራ /ማቴ.13፡3-8/፡፡
 እኔም ትምህርቴ በመንገድ ዳር፣ ወይም በጭንጫ፣ ወይም በእሾኽ መካከል እንዳልወደቀ እየተመለከትኩ ነውና ትጋቴ እንዲጨምር አደረጋችኁኝ፡፡ መልካም እርሻ ኾናችኋልና በትጋት እንዳስተምራችኁ አድርጋችኁኛል፡፡

 እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! ይኽን ኹሉ የምላችኁ ግን በውዳሴ ከንቱ ላመሰግናችኁ ፈልጌ አይደለም፡፡ ይኽን ኹሉ እንድል ያደረገኝ አንድ ነገር ስለተመለከትኩኝ ነው፡፡ ትናንት በዘነበው ኃይለኛ ዝናብ እንኳን አልተበተናችኁም፡፡ ዝናቡ እየዘነበባችኁም ቢኾን ቃሉን ለመማር ቁጭ ብላችኁ ነበር፡፡ ይኽ ለእኔ ትልቅ መልእክት አለው፡፡ እግዚአብሔር በእኔ በባርያው አድሮ የሚያስተምረውን ትምህርት በሙሉ ልባችኁ ኾናችኁ እየተቀበላችኁ እንደኾነ አሳይቶኛል፡፡ እንድተጋ አድርጋችኁኛል የምለውም ስለዚኹ ነው፡፡

 ቃለ እግዚአብሔርን በማስተዋል የሚያደምጥ ሰው ቃሉ ከልቡናው ትከሻ አይወርድም፡፡ ዘወትር ያስታውሰዋል፡፡ ደግሞም ፈቃደኛ ለኾነ ልብ ማስተማር እንዴት ደስ ይላል መሰላችኁ፡፡ መጽሐፍስ “ፈቃደኛ ለኾነ ልብ የሚያስተምር ሰው ብፁዕ ነው” ብሎ የለ /ሲራክ 25፡9/፡፡ ከጾም ውጤቶች አንዱ ይሔ ነው፡፡ ገና ይኽን ስንዠምር ጾም የነፍስ የሥጋ ቁስልን ትፈውሳለች ያልኳችኁ ይኸው ነበር፡፡ ወዮ! ገና ከአኹኑ ይኸን ያኽል ለውጥ ካየን፥ በሚቀጥሉት ቀናት ትምህርቱን የበለጠ ስንማርና የጾም ወራቱ ሲቀጥልማ እንዴት እንኾን ይኾን? ስለዚኽ የምወዳችኁ ልጆቼ! ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ፡- “በፍርሐትና በመንቀጥቀጥ የራሳችኁን መዳን ፈጽሙ” ብዬ እለምናችኋለኹ /ፊልጵ.2፡12/፡፡ ጠላት ዲያብሎስን በምንም መልኩ ለስንፍና አንጋብዘው፡፡ ከዚኽ የበለጠ እንትጋ እንጂ ከእንግዲኽ ወዲኽ ወደኋላ መመለስ አያስፈልገንም፡፡ ዲያብሎስ አኹን ያፈራነውን ፍሬ እያየ መበሳጨቱ አይቀርም፡፡ ይኽን የያዝነውን ፍሬ ለማስጣልም እንደሚያገሣ አንበሳ ኾኖ በዙርያችን እንደሚዞር በፍጹም መርሳት የለብንም /1ኛ ጴጥ.5፡8/፡፡ ነገር ግን ጠንቃቃዎችና በእግዚአብሔር ቸርነት የምንደገፍ ከኾነ ዲያብሎስ ምንም ሊያደርገን አይችልም፡፡ ችግር የሚኾነው እኛው ወደኋላ ማየት ስንዠምር ነው፡፡

 አያችኁ ልጆቼ! ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ደንታ ቢስ ካልኾንን የምንለብሰው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዲኽ ብርቱ የኾነ የጦር ዕቃ ነው የሚያለብሰን፡፡ ስለዚኽ ኹለንተናችንን (ንግግራችንን፣ አለባበሳችንን፣ አሰማማችንን፣ ማንኛውንም አካሔዳችንን) በእግዚአብሔር ዕቃ ጦር ማለትም በእግዚአብሔር ቃል የምናለብሰው ከኾነ ዲያብሎስ የሚወረውረው ጦር እኛን ሊጐዳን አይችልም፡፡ እንደዉም ተመልሶ ርሱን ነው የሚጐዳው፡፡ 
እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! ብቻ እኛ ፈቃደኞች እንኹን እንጂ፣ ብቻ እኛ በጾም በጸሎት ቃለ እግዚአብሔርንም በማድመጥ እንበርታ እንጂ የእግዚአብሔር ቸርነት እኛን ከብረት በላይ ጠንካራ ነው የሚያደርገን፡፡ አኹን ከእኛ መካከል አንድን ብረት በቦክስ ቢመታ ማን ነው የሚጐዳው? ብረቱ ወይስ እጃችን? ብረቱ ምንም አይኾንም፤ እጃችን ግን በእጅጉ ይጐዳል፡፡ የፈለገ ያኽል ጠንካሮች ብንኾንም ብረትን ማቁሰል አንችልም፡፡ ርሱ ነው የሚያቆስለን፡፡ በእግራችን ይኽን ብረት ብንመታው እኛው ደም በደም ኾነን እንቆስላለን እንጂ ብረቱ ምንም አይኾንም፡፡ ልክ እንደዚኹ እኛም በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ በመቀበል፣ በመልካም ምግባር ኹለንተናችንን የምንከላከል ከኾነ፥ ዲያብሎስ እኛን ለመጉዳት የሚወረውረው ጦር መልሶ የሚጐዳው ራሱ ዲያብሎስን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት ከእኛ ጋር ስለሚኾን ጠላት እግዚአብሔርን አልፎ ሊያጠቃን አይችልም፡፡ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ስለሚኾን ዲያብሎስን ልምሾና ምንም ዓቅም የሌለው ነው የሚያደርገው፡፡

 ስለዚኽ እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! መንፈሳዊ ትጥቅን እንታጠቅ፡፡ ሳንታጠቅ ከጠላት ዲያብሎስ ጋር አንታገል፡፡ ትርፉ መቁሰል አልፎም መሞት ብቻ ነውና፡፡ ስለዚኽ መንፈሳዊውን ትጥቅ ለመታጠቅ የምናደርገው ትጋት ጨምረን እንቀጥልበት ብዬ እለምናችኋለኹ፡፡ የትም ብንሔድ ይኽን መንፈሳዊ ትጥቃችንን ትተን መሔድ የለብንም፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ብንመጣ፣ ወደ ሥራ ቦታ ብንሔድ፣ ወደ ትምህርት ቤት ብንሔድ፣ ወደ ቤታችን ብንሔድ፣ ብንነቃ፣ ብንተኛ ያለዚኽ ትጥቅ መንቀሳቀስ የለብንም፡፡ ትጥቃችንን ይዘን የትም ብንሔድ ጠላት ያጠቃናል ብለን አንሰጋም፡፡ ደግሞም ይኽን ተሸክሞ ለመዞር (ክላሽ፣ መትረየስ፣ ሽጉጥ እንሚባሉት) እንደ ምድራዊ ትጥቆች አይከብድ፡፡ እንደዉም የበለጠ ብሩሃን (ብርሃን የተሞላን) ያደርገናል፡፡ ይኽን ብርሃን እያየም ጠላት ዲያብሎስ ሊያጠቃን አይችልም፡፡ ከእኛ ጋር ያለውን ብርሃን ለማየት ዓይኑ አይችልምና፡፡ እንዲኽ ከኾነም ደጋግሜ እንደነገርኳችኁ በጾም የሚገኘውን የነፍስ የሥጋ ቁስላችንን እናክማለን፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

ጾም - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል ሦስት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ቅዳሜ ኅዳር 13 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ የመቅረዝ ወዳጆች እንዴት ናችኁ? ዛሬም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስብከቱን ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ትምህርቱ ሊቁ ብዙ ነገር አስተምሮናል፡፡ በጾም ወደ እግዚአብሔር የበለጠ እንደምንቀርብ፣ ምሥጢራተ እግዚአብሔርን ለማወቅና ለመረዳት ልቡናችን ብሩህ እንደሚኾን፤ ከዚኽ በተጨማሪ በጾም አዳም ከመደበሉ በፊት በገነት የነበረውን ሕይወት እንደምንለማመደው አስተምሮናል፡፡ ምክንያቱም አዳም ከመበደሉ በፊት የእንስሳት ተዋጽኦዎችን አይበላም ነበር፤ ይኽን መብላት የዠመረው ከበደለ በኋላ ነው፡፡ ሥጋውን የሚያስወፍሩና ነገረ እግዚአብሔርን ከማሰብ የሚያርቁ ተግባራትን አይፈጽምም ነበር፡፡ እኛም በመጾማችን ሥጋችንን እየቀጣን ሳይኾን በገነት የነበረውን አዳምን መስለን የበለጠ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት መንፈሳዊ መንገድ እንደኾነ አስተምሮናል፡፡ ዛሬስ ምን ብሎ ነፍሳችንን ይመግባት ይኾን? የሊድያን ልቡና የከፈተ አምላክ የእኛንም ይክፈትልን አሜን!!!

ዛሬ ብሩህ የኾነ ፊታችኁን እያየኹ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ደስታዬ ግን ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ እንደሚያመጡት ዓይነት ደስታ አይደለም፡፡ የእኔ ደስታ ከዚኽ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም ቃለ እግዚአብሔር የተራበችውን ነፍሳችኁን ለመመገብ እንዴት ተጠራርታችኁ እንደመጣችኁ፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ኹሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሎ የተናገረውን ቃሉን በተግባር ለመፈጸም /ማቴ.4፡4/ ይኽንን በዓል ለማክበርም እንዴት ጓጕታችኁ እንደመጣችኁ ዐይቼ ደስታዬ ልዩ ነው፡፡
 ስለዚኽ ኑ እንደ ገበሬዎች እንኹን ብዬ እለምናችኋለኹ፡፡ ገበሬዎች እርሻቸው እንደለሰለሰ፣ ምንም ዓይነት አረምም እንደሌለ ሲያረጋግጡ እኽል ይዘሩበታል፡፡ እኛም ኑ እንደገበሬዎቹ እንኹን፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት የልቡናችን እርሻ ከለሰለሰ፣ በዚኹ በልቡናችን እርሻ የሚዘራውን ቃለ እግዚአብሔር የሚያንቁትን እንደነ ስልቹነትና ግዴለሽነት የመሰሉ አረሞች ከተነቀሉልን፣ ልቡናችን ሰማያዊ ምሥጢራትን ለመመርመር ብሩህ ከኾነልን፣ ከምድራዊ ነገር ይልቅ ሰማያዊ ነገርን ማስቀደም ከዠመርን ከዛሬ ዠምረን ጠለቅ ባለ መልኩ መማማር እንዠምራለን፡፡ ልቡናችን እንዲኽ በቃለ እግዚአብሔር ከለሰለሰ በኋላ ቃሉን የበለጠ ብንዘራበት ፍሬ ማፍራት የሚችል ይኾናልና፡፡ ጾሙም እየገባ ስለኾነ ስለ ምድራዊ መብልና መጠጥ ማሰብ ስለቀነስን ቃሉን ለማድመጥ ምቹ ነው፡፡ አብዝቶ የበላና የጠጣ ሰው ቃሉን ተማር ብንለው እንዴት ሊሰማን ይችላል? ስለበላው ምግብና ስለጠጣው መጠጥ የሚያስብና ሥጋው ወፍሮ የሚያስቸግረው ሰው እንባችን እንደ (አባይ) ወንዝ እየፈሰሰ ብንነግረውም ደንታ አይሰጠውም፡፡
ስለዚኽ አኹን ቃሉን ለመማር ምቹ ጊዜ ነው፡፡ በቤታችን ውስጥ አንድን ነገር ለቤተሰባችን ማሳመን የምንፈልግ ከኾነ ከቤት ሠራተኛዋ ዠምሮ ኹሉም ሰው ሰላማዊና ለማድመጥ ዝግጁ የኾነበትን ሰዓት መምረጥ አለብን፡፡ ጾም ደግሞ የነፍስ ዕረፍትን የምትሰጥ፣ ሽማግሌዎችን ደስ የምታሰኝ፣ ለወጣቶች ቀና መንገድን የምታስተምር፣ ሰውን ኹሉ ጠንቃቃና አርቆ አሳቢ የምታደርግ፣ በየትኛውም ዕድሜ የሚገኘውን ሰው የምታስጌጥ፣ ኹሉንንም እንደ ዕንቁ ፈርጥ የምታሳምር ናት፡፡ ስለዚኽ ከዛሬ ዠምሮ በከተማችን ምንም ዓይነት ሁካታ አይኑር፤ ዳንኬራ ቤቶች የሚሔድ አይገኝ፤ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ቸልተኛ ሰው አይገኝ፤ እኅቶች አለባበሳቸውን ያስተካክሉ፡፡ ኹሉም ሰው ክርስቲያን ክርስቲያን ይሽተት፡፡ ከትናንትናው ጉባኤ በኋላ ዛሬ ላይ ሳያችኁ ይኽን እመለከታለኹ፡፡ በዚኽም ጾም ምን ያኽል ኃይል እንዳላት አስተዋልኩኝ፡፡ ጾም የሰዎችን አስተሳሰብ እንዴት እንደምትቀይር፣ የገዢዎች ብቻ ሳይኾን የተገዢዎችም፣ የአሠሪዎችም የሠራተኞችም፣ የወንዶችም የሴቶችም፣ የሀብታሙም የድኻውም፣ በአጠቃላይ የሰውን ልቡና እንዴት የማንጻት ኃይል እንዳላት ተገነዘብኩኝ፡፡ ገዢውም ተገዢውም ሲጾም ራሱን ዝቅ ማድረግ ይለማመዳል፡፡ ጾም ድኻውም ሀብታሙም እኩል የምታደርግ መሣሪያ ናት፡፡ በሚጾም ልቡና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ምንም ዓይነት ቦታ የለውም፡፡
 በዚኽ ጉባኤ ላይ የታደማችኁ እጅግ የምወዳችኁ ምእመናን ሆይ! ጾም ለየትኛውም ዓይነት መንፈሳዊና ሥጋዊ በሽታ እንዴት ዓይነት ፍቱን መድኃኒት እንደኾነ ተገነዘባችኁን? ይኽን ከእናንተ እየተመለከትኩ ትጋቴ ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ እጅግ ጨመረ፤ በመኾኑም ልቤ እናንተን ለማስተማር ተነሣሣ፡፡ እግዚአብሔር በእኔ በባርያው አድሮ የሚዘራው ቃል በጭንጫ ላይ ሳይኾን በመልካም እርሻ እየበቀለ እንደኾነ ዐየኹ፡፡ በአጭር ጊዜም ፍሬውን ማየት ችያለኹ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከዚኽ በኋላ እዚያ ለታደሙት ምእመናን በኦሪት ዘልደት (ዘፍጥረት) ምዕራፍ አንድ ቁጥር አንድ እስከ ኹለት ያለውን ኃይለ ቃል ነው የሚተረጕምላቸው፡፡ በነገራችን ላይ በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በዐቢይ ጾም በብዛት የሚተረጐመው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት ነው፡፡ ከስሙ መረዳት እንደምንችለው መጽሐፉ ስለ ብዙ ልደታት የሚናገር ነው፡፡ የሰማይና የምድር ልደት፣ የሰው ልጅ ልደት፣ የሰንበት ልደት፣ የጋብቻ ልደት፣ የኃጢአት ልደት፣ የመሥዋዕት (የድኅነት) ልደት /3፡15/፣ የትንቢት ልደት /3፡15/፣ የሰው ሥልጣን ልደት /9፡1-6/፣ የሀገራት ልደት /11/፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ልደት /12፡1-3/፡፡ በዚያን ጊዜ ወደ ክርስትና ይመጡ የነበሩት አዳዲስ አማንያንም በፋሲካ ነበር የሚጠመቁት፤ ማለትም ዳግም የሚወለዱት፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ጳውሎስ ጥምቀት ማለት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የምንተባበርበት ዳግም አዲስ ልደትም የምናገኝበት እንደኾነ ያስተማረውን ትምህርት በተግባር ለመፈጸም ነው /ሮሜ.6፡4-6/፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የኦሪት ዘፍጥረትን በዚኽ ጊዜ የሚተረጕምላቸው ስለዚኹ ነው፡፡ በዚኽ ዕለት ካስተማረው ትምህርት የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች እናገኛለን፡-
·        እግዚአብሔር ከመዠመሪያ አንሥቶ ለሰው የተናገረው በሰውኛ ቋንቋ እንደኾነ፤
·        ሰው ቢበድልም እንኳ ፍቅሩ አላስችል ብሎት ፍቅራችንን እናድሰው እያለ ከነ አዳም፣ ከነ ቃየን፣ ከነ ኖኅ፣ ከነ አብርሃም (በተለይ ከአብርሃም ጋር በቤቱ እንግዳ ኾኖ በመግባት) ዝቅ ብሎ እንደተጨዋወተ፤
·        ከእስትንፋስ ይልቅ ለሰው ልጆች ቅርብ ኾኖ ሳለ ሰዎች አላስተውል ቢሉት የበለጠ እንዲያውቁት ፈልጐ በሙሴ በኩል ደብዳቤ እንደላከላቸው፤
·        ሙሴም የተቀበለውን ደብዳቤ ለሕዝቡ በየጊዜው ያነብላቸው (ይነግራቸው) እንደነበረ፤
·        ሙሴ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እግዚአብሔር መኾኑን እንደነገራቸው፤ እኛም ይኽን አሜን ብለን ልንቀበል እንደሚገባን፤
·        የእግዚአብሔር አሠራር ከሰው አሠራር ልዩ እንደኾነ፡፡ ለምሳሌ ሰው አንድን ቤት ሲሠራ ከመሠረት እንደሚዠምር ቀጥሎም ጣርያና ግድግዳ እንደሚሠራ፤ እግዚአብሔር ግን ከሰማይ ማለትም ከጣርያው ዠምሮ ቀጥሎም ምድርን ማለትም መሠረቱን እንደፈጠረ፤
·        ሰው ከምድር አፈር ተፈጥሮ ሳለ አፈሩ እንዴት ብሎ ነርቭ፣ አጥንት፣ የደም ቧንቧ፣ ጡንቻ፣ ፀጉር፣ ምላስ፣ ሳንባ፣ ልብ እንደኾነ ስናስብ ልቡናችን ተደንቆ ተደንቆ ዝም ብለን እግዚአብሔርን ማድነቅ ብቻ ሊኾን እንደሚገባና ይኽን ላደረገ ጌታ ምስጋና ብቻ ማቅረብ እንደሚገባን፤
 ይኽንና ይኽን የመሰለ ጣፋጭ ትምህርት ካስተማራቸው በኋላ ሊቁ የሚከተለውን ይነግራቸዋል፡-
እጅግ የምወዳችኁና እዚኽ ጉባኤ ላይ የታደማችኁ ቃሉንም ያዳመጣችኁ ምእመናን ሆይ! አኹን ለጊዜው የትርጓሜው ትምህርታችን ገታ እናድርግና አንድ ነገር ታደርጉ ዘንድ እለምናችኋለኹ፡፡ ወደየቤታችን ስንሔድ ቃሉን ለመተግበር እንጣጣር፡፡ ቃሉን በልቡናችን ጽላት እንቅረጸውና ዘወትር እንደ እንጀራ እንመገበው፡፡ አባቶች ለቤተሰቦቻችኁ ዛሬ የተማርነውን ትምህርት ድገሙላቸው፡፡ እኛቶችም ይኽን ከባሎቻቸው ያድምጡ፡፡ ልጆች ከእናቶቻቸው ይኽን ያድምጡ፡፡ ልጆች ብቻ አይደለም፤ ከቤት ውስጥ ያሉት እንስሳትም ይኽን ያድምጡ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ፣ በዚኽ ጉባኤ የተማርነውን ትምህርት ከቤታችን ሔደን በተግባር የምንኖረውና ቃሉን ደጋግመን የምንበላው ከኾነ ቤታችን ቤተ ክርስቲያን ትኾናለች፡፡ ዲያብሎስም ወደ ቤታችን መግባት አይቻለውም፡፡ የነፍሳችን ጠላት የኾነው ርኵስ መንፈስ ተኖ ይጠፋል፡፡ በርሱ ፈንታም ወደቤታችን መንፈስ ቅዱስ ሰተት ብሎ ይገባል፡፡ ሰላምና ፍቅር፣ አንድነትና መስማማት ወደ ቤታችን ከነጓዛቸው ሰተት ብለው ይገባሉ፡፡ ይኽን ያደረጋችኁ እንደኾነ እኛንም የበለጠ ታተጉናላችኁ፡፡ የቃሉን ምሥጢር የበለጠ እንድናስተምራችኁ ታበረቱናለችኁ፡፡ ገበሬ የዘራውን እኽል ፍሬ ሲያፈራለት አይቶ እጅግ ደስ እንደሚሰኝ ኹሉ እኛም ደስ እንሰኛለን፡፡ ተደጋግፈንም ክርስቲያን ክርስቲያን የምንሸት እንኾናለን፡፡
ስለዚኽ ደጋግሜ እንደነገርኳችኁ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የትም ብንኾን ቸልተኞችና ደንታ ቢሶች ልንኾን አይገባንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲኽ ይላል፡- “መልካሙን ሥራችኁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችኁን እንዲያከብሩ ብርሃናችኁ እንዲኹ በሰው ፊት ይብራ” /ማቴ.5፡16/፡፡ የተማርነውን ትምህርት በተግባር የምንፈጽም ከኾነ በዚኽ ጉባኤ የተማርነው ትምህርት ግቡን መትቷል ማለት ነው፤ ፍሬ አፍርተናል ማለት ነው፤ በእውነት ክርስቶስን መስለነዋል ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም ቅዱስ ያዕቆብ እንደነገረን እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው፤ ሥራም ያለ እምነት እንደዚኹ የሞተ ነው /ያዕ.2፡26/፡፡ የፈለገ ያኽል በእምነታችን ምንም እንከን የሌለን ብንኾን፣ ነገር ግን በተግባራዊ ሕይወታችን ሰነፎችና በኀጢአት ሕይወት የምንኖር ከኾነ ስሕተት የሌለው እምነታችን ምንም አይጠቅመንም፡፡ ልክ እንደዚኹ እውነተኛ እምነት ውስጥ ሳንኖር የፈለገ ያኽል መከራ ብንቀበልም፣ የምድር መልአክ ብንመስልም አይጠቅመንም፡፡ ስለዚኽ በየጊዜው የምንማረው ትምህርት ጊዜአዊ ስሜታችንን የሚያረካ ሳይኾን ሕይወታችንን የሚቀይረው ሊኾን ይገባል፡፡ ጌታችን ሲናገር፡- “ይኽን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ኹሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል” ብሏል /ማቴ.7፡24/፡፡ ይኽ ሰው ልባም የተባለው ቃሉን ስለሰማ ብቻ አይደለም፤ ቃሉን ሰምቶ እንደ ዓቅሙ ለመተግበር ስለሚጣጣር እንጂ፡፡ ቃሉን ሰምቶ ለጊዜው የሚደሰትና “አቤት የዛሬው ጉባኤ ሲያስደስት” ብሎ የማይተገብር ሰው ግን ሰነፍ ሰው ነው፡፡ ይኽ ሰነፍ ሰውም ቤቱን በአሸዋ እንደሠራ ሰው ነው፡፡ ቤቱን በአሸዋ የሠራ ሰው ነፋስ ወይም ጐርፍ ሲመጣ ይፈርሳል፡፡ ፈተና ባጋጠመው ሰዓት ዐለት በተባለው ክርስቶስ ስላልቆመ ይሸነፋል፡፡ ልባም ሰው ግን በእነዚኽ ፈተናዎች የበለጠ ይፈካል፡፡ ክርስቶስን እየመሰለ ይሔዳል፡፡ ልባሙ ሰው ፈተና ባጋጠመው መጠን ከክርስቶስ ጋር ስለሚኾን መልካም ሥራው የበለጠ እየታየ ይሔዳል፡፡ ሰነፍና ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ደንታ የሌለው ክርስቲያን ግን የፈለገ ያኽል እዚኽ ጉባኤ መጥቶ ቁጭ ብሎ ቢማርም ፈተና ባጋጠመው ጊዜ በቀላሉ ይወድቃል፡፡ ፈተናው ከብዶት ሳይኾን እርሱ ሰነፍ ስለኾነ (ክርስቶስ አብሮት ስለሌለ)፡፡
ስለዚኽ የጦር ዕቃችንን እናንሣ፡፡ የአንድ ሳምንት ጿሚዎች ሳንኾን ዘወትር ብርቱዎች እንኹን፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ በፈተና እንጸናለን፡፡ ትዕግሥተኞች እንኾናለን፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ከምናገኘው ደስታ ጋር ስናነጻጽረው የአኹኑ ሕይወታችን ፈተና ምንም እንዳልኾነ እናውቃለን፡፡ አኹን ትዕግሥተኞችና በፈተና የምንጸና ከኾነ 30፣ 60፣ 100 ያማረ ፍሬ ማፍራት እንችላለን፡፡ ቸርና ሰው ወዳጅ እግዚአብሔር በፈተና እንድንጸና ይርዳን፡፡ የይምሰል ሳይኾን የእውነትና እግዚአብሔር የሚወደው የጾም ወራት ያድርግልን፡፡ ዳግም በመጣ ጊዜ የሕይወት ቃል እንዲያሰማን ፈቃዱ ይኹን፡፡ ምስጋና፣ ክብር፣ አኰቴት ለአብ፣ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ይኹን፡፡ አሜን!!!

ጾም - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል ኹለት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ኅዳር 11 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ የመቅረዝ አንባብያን፡፡ በትናንቱ ጕባኤ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ብዙ ነገር አሳስቦን ነበር፡፡ ጉባኤውን ለመታደም ወደ ቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት ከመጣን አይቀር ከነበሽታችን ልንመለስ እንደማይገባ ይልቁንም መንፈሳዊ መድኃኒትን ውጠን ልንመለስ እንደሚገባን፣ የነፍስና የሥጋ መድኃኒት ከምትኾን ከጾም ጋር አብረው የማይሔዱ ነገሮች ምን ምን እንደኾኑ፣ ከእንግዲኽ ወዲኽ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና አውጥታ ጾም ነው ስላለችን ብቻ ሳይኾን በዓላማ ልንጾም እንደሚገባና ሌላ ብዙ ነፍስን የሚያለመልሙ ትምህርቶችን አስተምሮን ነበር፡፡ ምንም እንኳን የዛሬው ትምህርት ለእኛ ኹለተኛ ጕባኤ ቢኾንም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግን ከትናንቱ ጋር በአንድ ቀን ጕባኤ ያስተማረው ነው፡፡ የመዠመሪያው ቀን ስብከቱም ዛሬ ላይ እንጨርሳለን፡፡ በነገራችን ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቁመቱ አጭር ስለነበረ ምእመናኑ ባዘጋጁለት መድረክ ላይ ወጥቶ ነበር የሚያስተምረው፡፡ ዛሬ በየዓውደ ምሕረቱ የምንመለከተው አትሮንስም ከዚያን ጊዜ ዠምሮ አገልገሎት ላይ የዋለ ነው፡፡ መልካም ጕባኤ እንዲኾንልን በመመኘት ፊታችንና መላ ሰውነታችንን ሦስት ጊዜ በማማተብ ትምህርቱን በትጋት ኾነን እንድንማር በድጋሜ ጋበዝናችኁ፡፡
 

   በመንፈሳዊ ሕይወት ቸልተኛ መኾንና ለራስ ሕይወት ግድ አለመስጠት የብዙ ኃጢአቶች ምክንያት እንዲኹም ነጸብራቅ ነው፡፡ ልክ እንደዚኹ ጾምም የብዙ በረከት ምክንያት እንዲኹም ነጸብራቅ ነው፡፡ እንደምታስታውሱት አዳም በገነት በነበረ ጊዜ ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ቸልተኛና ግድ የሌለው እንዳይኾን ብሎ ልዑል እግዚአብሔር አንድ ትእዛዝ ሰጥቶት ነበር፡፡ እንዲኽ በማለት፡- “ከገነት ዛፍ ኹሉ ትብላለኅ፤ ነገር ግን መልካሙንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” /ዘፍ.2፡16-17/፡፡ እዚህ ጋር “ብላ፤ አትብላ” የሚለው የሚለው ትእዛዝ በምሳሌ ስለ ጾም ጥቅም የሚያስረዳ ነው፡፡  የሰው ልጅ ግን ይህቺን አንዲት ትእዛዝ ለመጠበቅ አልታዘዝ አለ፤ ትዕግሥት አጣ፤ ሞትንም በራሱ ላይ አመጣ፡፡ የሰው ልጆች ጠላትና ክፉ መንፈስ የኾነው ዲያብሎስም እንደምታስታውሱት አዳም በገነት የአታክልት ስፍራ ደስ ብሎት እንደ ሰማያውያን መላዕክት ኾኖ እየኖረ ስለነበረ ቀናበት፡፡ አምላክ ትኾናለህ ብሎም አታለለውና የነበረውን ቅድስና እንኳን አሳጣው፡፡ አያችኁ ልጆቼ! ያለንን ቅዱስ ነገር በአግባቡ ሳንይዝ ይልቁንም ሌላ ከዚኽ የበለጠ ነገር መመኘት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰው “በዲያብሎስ ቅንኣት ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ” ያለንም እኮ ስለዚኹ ምክንያት ነው /ጥበብ 2፡24/፡፡ እንግዲኽ ሞት ወደ ሰው ልጆች እንዴት በስንፍና እንደመጣ እያስተዋላችኁ ነው ልጆቼ? በኋላ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍም በመንፈሳዊ ሕይወት መድከምን እንዴት እንደሚነቅፍ እንመልከት፡- “ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” /ዘጸ.32፡6/፤ “ወፈረ፤ ደነደነ፤ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ” /ዘዳ.32፡15/፡፡ የሰዶም ኗሪዎችም የዲን እሳት ዘንቦባቸው የጠፉት ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው እጅግ ቸልተኞች ስለነበሩና ለመብልና ለመጠጥ ሰፊ ቦታን ስለ ሰጡ ነው፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለዚኹ ጉዳይ ሲነግረን እንዲኽ ብሏል፡- “የሰዶም ኃጢአት ይኽ ነበረ፤ ትዕቢት እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት” /ሕዝ.16፡49/፡፡ በአጭር አነጋገር አብዝቶ መብላትና መጠጣት፣ ጾምን ችላ ማለት የብዙ ኃጢአቶች ምክንያት ነው፡፡
 እንግዲኽ ራስን አለመግዛት እንዴት አደገኛ እንደኾነ አያችኁ? አኹን ደግሞ ጾም እንዴት በረከትን እንደሚያመጣ እንመልከት፡፡ ሙሴ 40 ቀን ስለጾመ የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ጽላት ተቀበለ /ዘጸ.24፡18/፡፡ ከተራራው ሲወርድ ግን የሕዝቡን ኃጢአት ተመለከተና ኃጢአተኛ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕግ መቀበል አይችልም ሲል ብስንት መለማመጥ የተቀበለውን ጽላት ወርውሮ ሰበረው፡፡ ይኽ ታላቅ ነቢይ በተሰበረው ፋንታ ሌላ ጽላት ለመቀበል 40 ቀናት ነው የጾመው /ዘጸ.34፡28/፡፡ ታላቁ ነቢይ ኤልያስም ልክ እንደ ሙሴ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሟል፡፡ እንዲኽ በመጾሙም በእሳት ሠረገላ ተነጥቆ ወደ ሰማይ ተወሰደ፤ እስከ አኹን ድረስም አልሞተም፡፡ እጅግ አስደናቂ የኾነው ሰው ነቢዩ ዳንኤልም እጅግ ብዙ ቀናትን ይጾም ስለነበረ ተንኰለኞች ወደ አንበሳ ጕድጓድ እንኳን ቢጥሉት አንበሶች ሊበሉት አልቻሉም፡፡ አንበሶቹ ለነቢዩ ዳንኤል እንደ በጐች ነበሩ፡፡ አንበሶቹ በግ የኾኑት ግን ተፈጥሯቸው ተለውጦ በግ በመኾን ሳይኾን ዳንኤልን ሳይበሉት ከነተናጣቂ ተፈጥሯቸው ሳሉ ነው፡፡ የነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቁጣ ያስቀሩት በመጾማቸው ነው፡፡ እንደዉም በነነዌ የጾሙት ሰዎች ብቻ አልነበሩም፤ እንስሳቱም ጭምር እንጂ፡፡ በዚኽም ምክንያት እግዚአብሔር ሊያደርገው ከተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም /ዮናስ 3፡10/፡፡ ከብሉይና ከሐዲስ ኪዳን እንዲኽ በመጾማቸው የተጠቀሙ ብዙ ሰዎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ነገር ግን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገው ነገር ኹላችንንም የሚያስተምር ነውና እሱን ብንመለከት፡፡ ኹላችኁም እንደምታውቁት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሟል /ማቴ.4/፡፡ ሲጾምም ዲያብሎስን ድል አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ጌታችን ይኽን ያደረገበት ምክንያት ዲያብሎስን ለማሸነፍ እኛም የጾምን ትጥቅ መታጠቅ እንዳለብን ሲያስተምረን ነው፡፡
እዚኽ ጋር ምናልባት ከእናንተ መካከል፡- “አባታችን! ቅድም እንደነገርከን እነ ሙሴ፣ እነ ኤልያስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ ሙሴና እንደ ኤልያስ አንዲት ቀን እንኳን ሳይጨምር መጾሙ ለምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይኽን ያደረገው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ጌታችን እንዲኽ የጾመው እኛን በጣም ስለሚወደን ነው፡፡ ምክንያቱም ሲዠምርም የእኛን ሥጋ ሳይዋሐድ መምጣት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም ስለሚወደን ሥጋችንን ተዋሐደ፤ ከእኛ ከሰዎች ያልራቀ መኾኑን ሲያስረዳንም ጾመ፡፡
 እንግዲኽ ከላይ ለማየት እንደቻልነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሌሎችም ቅዱሳንም በመጾማቸው ምክንያት ዲያብሎስን አሸንፈውታል፡፡ በተለይ ቅዱሳኑ በመጾማቸው ምክንያት ለሥጋቸውም ለነፍሳቸውም ብዙ ጥቅምን አግኝተዉበታል፡፡
 ስለዚኽ እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! የጾም ጥቅም እንዴት ትልቅ እንደኾነ እየተማርንና እየተመለከትን ሳለ የጾም ወራት ሲቃረብ ደስ ብሎን ልንቀበለውና ንቁዎች ኾነን እጅግ ብዙ ጥቅምን ልናገኝበት ይገባናል ብዬ እማልዳችኋለኹ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳን የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል” ብሎ እንዳስተማረን /2ኛ ቆሮ.4፡16/ ጾም ሲገባ እጅግ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ከዚኽ የሐዋርያው ቃል እንደምንረዳው ጾም ማለት ነፍሳችን የበለጠ የምትወፍርበት መንገድ ነው ማለት ነው፡፡ እንጀራ ሥጋችን እንዲወፍር እንደሚያደርገው ኹሉ ጾም ደግሞ ነፍሳችን እንድትወፍር ያደርጋታል፡፡ ጾምን የምታዘወትር ነፍስ ከእግዚአብሔር ጋር ያላት ቀረቤታ እጅግ ስለሚጨምር ገና በዚኽ ምድር ሳለች ቅድስና በቅድስና እየጨመረች፣ ምሥጢራተ እግዚአብሔርን እያስተዋለች፣ የመንግሥተ ሰማያትን ጣዕም እየቀመሰች ትሔዳለች፡፡ እጅግ ብዙ ጭነትን የተሸከመች መርከብ ባሕሩንና ወጀቡን ማለፍ እንደሚያቅታት ኹሉ መብልና መጠጥ የሚያበዛ ሰውም የዚኽን ዓለም ወጀብ ማለፍ አይችልም፡፡ ቀለል ያለና ተመጣጣኝ የኾነ ጭነትን የያዘች መርከብ ግን ብዙ ችግር ሳይገጥማት የታሰበላት ቦታ በታሰበላት ጊዜ  ትደርሳለች፡፡ መብልና መጠጥን ሳያበዛ ጾም የሚወድ ክርስቲያንም ንቃተ ኅሊናው ብሩህ ነው፡፡ በዚኽ ምድር በሚያጋጥሙት ችግሮችም በቀላሉ እጅ አይሰጥም፡፡ ዛሬ ላይ በዚኽ ምድር የሚያጋጥሙት ጊዜያዊ ችግሮች እንደ ጥላና ሕልም እንደሚያልፉ ይገነዘባል፡፡ እንዲኽ እንዳናስብና በዚኽ ምድር በሚያጋጥሙን ጥቃቅን ችግሮች እንድንጨናነቅ የሚያደርጉን በመንፈሳዊ ሕይወታችን እጅግ ቸልተኞች ስንኾን ነው፡፡ ምክንያቱም የዘወትር ሐሳባችን መብልና መጠጥ ላይ ከኾነ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ደካሞች ነው የምንኾነው፡፡ ሥጋችን ይወፍራል፡፡ የማሰብና የማመዛዘን ዓቅማችን ይቀንሳል፡፡ ለነፍሳችን ምንም በማይጠቅም እንተ ፈንቶ ነገርም ተጠምደን እንውላለን፡፡  
 ስለዚኽ እጅግ የምወዳችኁ ምእመናን ሆይ! በጊዜያዊ ነገር ብቻ እየተጠመድን በመንፈሳዊ ሕይወታችን ቸልተኞች አንኹን ብዬ እለምናችኋለኹ፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ቸልተኞች ስንኾን የምንጐዳው በሚመጣው ዓለም ብቻ አይደለም፡፡ በዚኽ ምድር ሳለንም በመብልና በመጠጥ ብዛት ምክንያት የሚመጡ ብዙ በሽታዎች ተጠቂዎች ነው የምንኾነው፡፡ እኛ በሐዲስ ኪዳን ያለን ክርስቲያኖች ነን፡፡ በዚያ በጨለማው የብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች እንኳን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ቸልተኞች እንዳይኾኑ ይልቁንም ጾምን እንዲያዘወትሩ ይነገራቸው ነበርና እባካችኁ ቸልተኞች አንኹን ብዬ እለምናችኋለኹ፡፡ እስኪ አምላካችን እግዚአብሔር ምን እንደሚለን እናድምጥ፡- “ክፉውን ቀን ከእናንተ ለምታርቁ፣ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ፣ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፣ በምንጣፋችኁም ላይ ተደላድላችኁ ለምትቀመጡ፣ ከበጐችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፣ በመሰንቆም ድምፅ ለምትንጫጩ፣ እንደ ዳዊትም የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፣ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፣ እጅግ ባማረ ሽቱም ለምትቀቡ፣ ስለዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችኁ” /አሞጽ.6፡3-6/፡፡ ልጆቼ! እግዚአብሔር በነቢዩ አሞጽ አድሮ እስራኤላውያንን እንዴት አድርጐ እንደወቀሳቸው፣ መብልንና መጠጥን ሲያበዙ እንዴት አድርጐ እንደገሠፃቸው አያችኁን? እንደዉም በደንብ አስተውላችኁት ከኾነ አብዝተው መብላታቸውንና መጠጣታቸውን ብቻ አይደለም የወቀሳቸው፡፡ ጨምሮም እነዚኽ ሰዎች ከዚኽ በላይ ደስታ እንደሌላቸው፥ ደስታቸው ግን እንደ ጧት ጤዛ ብዙ እንደማይቆይ ነግሯቸዋል፡፡
 አኹን በዚኽ ምድር ላይ የምንመለከታቸው ነገሮች ልክ እንደዚኽ የሚጠፉ ናቸው፡፡ ክብርም በሉት፣ ሥልጣንም በሉት፣ ሀብትና ንብረትም በሉት፣ የምናገኛቸው መልካም አጋጣሚዎችም በሉት፣ ኹሉም ጠፊዎች ናቸው፡፡ ከእነዚኽ አንዱ ስንኳ ዘለዓለማዊ የለም፡፡ ኹሉም እንደ ወራጅ ውኃ የሚያልፉ ናቸው፡፡ የሙጥኝ ብለን ልንይዛቸው ብንሞክር እንኳን ብዙ ልናቆያቸው አንችልም፡፡ የምንቀረው ባዶአችን ነው፡፡ መንፈሳዊ ነገሮቻችን ግን የእነዚኽ ተቃራኒ ናቸው፡፡ እንደ ጽኑ ዐለት አይንቀሳቀሱም፤ ትተዉን አይሔዱም፡፡ በጊዜ ብዛት አይበላሹም (Expire date የላቸውም)፡፡ እስኪ አኹን ልጠይቃችኁ ልጆቼ! የማይጠፋውን ሀብት በሚጠፋው ሀብት የምንቀይረው እንዴት ብንደነዝዝ ነው? ዘለዓለማዊውን ደስታችን በዘለዓለማዊ ለቅሶ፣ ዘለዓለማዊውን ሕይወት በጊዜያዊ ሕይወት፣ ዘለዓለማዊውን ሀብታችን በሚጠፋ ሀብት መቀየራችን ምን ዓይነት ስንፍና ቢይዘን ነው?
 ስለዚኽ በዚኽ ጕባኤ የታደማችኁ ኹላችኁም ምእመናን ሆይ! እለምናችኋለኹ፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ተገቢውን ትኵረት እንስጠው፡፡ ለምድራዊ ነገር ፈጣን ኾነን ሳለ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ሰነፎች አንኹን፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ጠንካሮች እንድንኾን የምታደርገንን ጾምንም እንውደዳት፡፡ ከርሷ ጋር ያሉት ሌሎች በጐ ምግባራትንም (ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት፣ ወዘተ) እንውደዳቸው፡፡ ከዛሬ በኋላ አዲስ የአኗኗር ስልትን (Renewed Life style) እንዠምር፡፡ በየቀኑ መልካም ምግባራትን መሥራት የሚያስደስተን እንኹን፡፡ በዚኽ በምንቀበለው ጾም ብዙ መንፈሳዊ ተግባራትን እናድርግና ራሳችንን በሰማያዊ ክብር እናስጊጥ፡፡ እንዲኽ የምናደርግ ከኾነ ጾሙ ሲፈታ ወደ ቅዱስ ሥጋውና ወደ ክቡር ደሙ ሳናፍር መቅረብ ይቻለናል፡፡ በልቡናችን ውስጥ የነበረውን ቆሻሻ ኹሉ ስለምናስወግድ ንጹሓን ኾነን ከዚያ ሰማያዊ ማዕድ ተሳታፊዎች መኾን እንችላለን፡፡ ከዚያም በጐ ምግባራችን የማይጠፋና ኃይልን ስለሚያገኝ በመጨረሻው ቀን ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን የሚለውን የሕይወት ቃል መስማት እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ስለማይለየን ሕይወታችን በጸሎትና በምልጃ የተሞላ ይኾናል፡፡ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን መኖር ይቻለናል፡፡ ይኽን እንድናደርግ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!!

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...