2013 ኦክቶበር 31, ሐሙስ

                                                                          
Participants of the 32nd SGGA03
 

የምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት ይካሄዳል: የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ መግለጫ

  • ቅ/ሲኖዶስ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት እውነታውንና ትክክለኛውን የሚገልጽ ጽሑፍ እንዲዘጋጅ ለሊቃውንት ጉባኤው ትእዛዝ ሰጠ
  • የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ለምልአተ ጉባኤው ስብሰባ የሰጠው ሽፋን ‹‹የጉርሻ ያህል ነው›› በሚል ተነቀፈ
  • ‹‹ጉባኤው አገር አቀፍ ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍም ነው፤ የምንሰጠው ትምህርት ነው፤ የምንወድቀው የምንነሣው ስለ ሀገር ጉዳይ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን በዐይን የሚታይ በእጅ የሚጨበጥ ታሪክ ነው ያስረከበችው፤ በምን ምክንያት ነው [የአየር ሽፋኑ]ቀለል የሚለው›› /ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ/
  • ‹‹ከባለሥልጣናት[ከመንግሥት] የምናገኛቸውን መልእክቶች እናስተላልፋለን፤ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ እናቶች በሆስፒታል እንዲወልዱ ደጋግማችኹ አስተላልፉን ብለው ነግረውን በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ሺሕ ሕዝብ በተሰበሰበበትና በየአጋጣሚው እናስተላልፋለን፤ እኛም እዚህ ስለ አገር ጉዳይ እንነጋገራለን፤ የምንነጋገረው ግን የሚተላለፈው የጉርሻ ያህል ነው፤ ለሕዝቡ እንዲተላለፍ እንጂ የሚዲያ ሱሰኛ ኾነን አይደለም፤ የሚነገረው ነገር ለሕዝቡ በአግባቡ ቢተላለፍ መልካም ነው›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
Holy SynodTikmit Meeting
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በእያንዳንዱ አህጉረ ስብከት ሓላፊነት እንደሚካሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን በሥሯ ያሉ ምእመኖቿን ቆጥራ መመዝገብ እንድትችል›› የሚካሄደው ይኸው ታላቅ አገራዊ ክንዋኔ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በሚያዘጋጀው ቅጽ አማካይነት እንደሚከናወን ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የገለጸው፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት የምእመናን ቆጠራ ለማካሄድ ከብር 29 ሚልዮን በላይ የበጀት ጥያቄ ለቅ/ሲኖዶስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ማቅረቡን መዘገባችን የሚታወስ ሲኾን ዛሬ በቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ እንደተጠቀሰው፣ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት የሚካሄደውን ቆጠራ ክንውን በቀጣይ የምንመለከተው ይኾናል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት ሁሉም ሰው መጻፍ ሲገባው እውነት ያልኾነውን፣ በማስመሰል የሚነገረውንና የሚጻፈውን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡
በመኾኑም እውነተኛውንና ትክክለኛውን አስተካክሎ ለሕዝብ፣ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል መነሻ ይኾን ዘንድ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የኮሚቴ አባልነት ተጠንቶ የቀረበውን ጽሑፍ ምልአተ ጉባኤው በንባብ ሰምቶ ጉዳዩ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ እንዲቀርብ ትእዛዝ መስጠቱን ቅ/ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ሊቃውንት ጉባኤው ስለ ኢትዮጵያ ታሪካዊነትና ጥንታዊነት በምልአተ ጉባኤው ላይ የተነበበውንና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተዘጋጀውን የመነሻ ጽሑፍ አብራርቶ፣ አስፍቶና አምልቶ ለግንቦት፣ ፳፻፮ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የኾኑ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ እና ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በቅርቡ በተካሄደው ፴፪ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ፥ ኢትዮጵያ ከአይሁድ በፊት ጀምሮ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንታ መኖሯን፣ ክርስትናም ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስቶስ ባረገበት ዓመትና ቅዱሳን ሐዋርያት ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት በ፴፬ ዓ.ም. መኾኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት በማስረዳት ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ጋራ መጠያየቃቸው ይታወሳል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት የጀመረውንና ለዐሥር ቀናት ያህል ሲያካሂድ የቆየውን የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብስባ ዛሬ፣ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ያወጣው ባለ28 ነጥብ መግለጫ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አካትቷል፡-
  • ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ድረስ በባለሞያዎች ተጠንቶ የቀረበውና በስላይድ የታየው የሥራ መዋቅር ወደ ታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም አይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
  • ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት የምታከናውነው ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት በዕቅድ የሚመራ እንዲኾን ለማስቻል በግንቦቱ ርክበ ካህናት ጉባኤ ፳፻፭ ዓ.ም. ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት ለጉባኤው አቅርቦ ጉባኤው ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ ኮሚቴው ያላለቁ ሥራዎችን እንዲቀጥል በማለት መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊ እንደመኾኗ ኹሉ በቀጣይም አጠቃላይ ማኅበራዊም ኾነ መንፈሳዊ ሥራዎቿን በመሪ ዕቅድ በመምራት ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ መቅረፍ እንዲቻል በባለሞያዎች የተጠናውን የመሪ ዕቅድ ዘገባ በመገምገም በቀጣይ ዕቅዱ ዳብሮ በሥራ መተርጎም በሚቻልበት ኹኔታ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • አሁን ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሻሽሎ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት የተሻሻለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲመለከቱት የታደለ ሲኾን እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ታይቶና ሐሳብ ተሰጥቶበት በ፳፻፮ ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት ውይይት እንዲካሄድበት ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
  • በውጭው ዓለም ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ነን በሚል የሚገኙ ወገኖች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
  • በውጭ አገር ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋራ ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም ወደፊት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠናከር ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
  • ገዳማቱን መልሶ ማቋቋምና ማጠናከር ብሎም በነበሩበት ኹኔታ አደራጅቶ ሥራቸውን መቀጠል ይችሉ ዘንድ የሚያመለክት በመምሪያው በኩል ሰፊ ጥናት የተደረገ በመኾኑ ገዳማቱ የሚገኙትም በየአህጉረ ስብከቱ ስለኾነና ብፁዓን አበው የሌሉበት ጥናትም አጥጋቢ ውጤት ስለማይኖረው የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመምሪያው ተጠሪ ጋራ ተገናኝተው ገዳማቱ እንዴት መቋቋምና መልማት እንዳለባቸው ጥናት ይደረግበት በሚለው ጉባኤው ተስማምቶ ጠለቅ ያለ ሐሳብ ከነመፍትሔው አጥንተው ለግንቦት ፳፻፮ ዓ.ም. ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርቡ፡-
1.  ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ – የምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
2.  ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል – የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፣ የሕንፃዎችና ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የበላይ ሓላፊ
3.  ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ – የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመምረጥ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
  • የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን በተመለከተ ኮሌጁን ማጠናከር አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ለኮሌጁ ዋና ዲን እንዲሾም ጉባኤ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ለውጥ ጥናቶች የቅ/ሲኖዶሱን ሙሉ ድጋፍና ባለቤትነት አገኙ፤ በጥናቶቹ ቀጣይ አካሄድ ላይ ምልአተ ጉባኤው የአፈጻጸም አቅጣጫ ሰጥቷል፤ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ዛሬ ያበቃል፤ መግለጫም ይኖራል

Holy SynodTikmit Meeting
  • በአገልግሎት ጥራት /በሰው ተኮር ነፍስ የማዳን አገልግሎት/ ምእመናንን ማብዛትና ማጽናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከባይተዋርነትና ጠባቂነት ወደነበራት ሚና መመለስ፣ አስተምህሮዋን ከማይቃረኑ ጋራ ዓለም አቀፍ አጋርነትን በማጠናከር የሰላምና አንድነት ተምሳሌት ማድረግ፣ ለሙስና ችግሮች በንስሐ መንገድ መፍትሔ ማበጀት የቤተ ክርስቲያናችን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ማሕቀፍና ቊልፍ ጉዳዮች ኾነዋል፡፡
  • በቡድን እየተደራጁ የመንግሥትን ወቅታዊ አጀንዳዎች በአሉታዊ መንገድ የሚጠቀሙ አሉባልተኞችና ሙሰኞች እንዲሁም በቤተ ክህነቱ ቢሮክራሲ ውስጥ የተሰገሰጉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ዋነኛ የለውጡ ተግዳሮቶች እንደኾኑና እንደሚኾኑ ተጠቁሟል፡፡
  • የለውጥ አመራር መዋቅሩ፣ አደረጃጀቱና ዝርዝር አሠራሩ ሕገ ወጥ ጥቅምን የሚያስቀር ተገቢ ጥቅምን የሚያጎለብት፣ ማንኛውንም ሠራተኛና አገልጋይ ለለውጡ የሚያበቃ እንጂ የማያፈናቅል መኾኑ በቅ/ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ታምኖበታል፡፡ ካህናት፣ ባለሞያ ሠራተኞች፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምእመናን የለውጡ ግንባር ቀደም አራማጆች ይኾናሉ፡፡
  • ተቋማዊ ለውጡን ለመተግበር÷ ነባሩ የሰው ኃይል የሚበቃበት አዲስ የሰው ኃይል የሚወጣበት የሥራ አመራር ማሠልጠኛ አካዳሚ/የሥልጠና ማእከል/ለመገንባት ጥናቱ ተጠናቆ ዝግጅቱ ተጀምሯል፤ ማእከሉ የድኩማን/አረጋውያን መጦርያና የነዳያን መልሶ ማቋቋሚያም ያካተተ ነው፡፡
  • በአ/አበባ ሀ/ስብከት ለተቋማዊ ለውጥ አመራር ጥናቱ ምቹ ኹኔታ የፈጠሩትና ያስቻሉት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አለጊዜውና አላግባብ በተደረጉ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ሌሎች ሠራተኞች ዝውውሮች ቢገመገሙም ከምደባቸው የመነሣታቸው ዜና ከእውነት የራቀ ነው፡፡
  • በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት አዲስ የሙስና ኔትወርክ ዘርግተው ሕገ ወጥ ሲያጋብሱ በቆዩ ሦስት ሓላፊዎች ላይ ርምጃ ይወሰዳል፤ ሓላፊነታቸው ለቀው ወደ አሜሪካ በሄዱት የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ምትክ አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይሾማል፤ ገለልተኝነታቸው፣ የትምህርት ዝግጅታቸውና አገልግሎታቸው የሚጠቀስላቸው የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ቀጣዩ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሚኾኑ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡
  • የገዳማት አጠቃላይ ወቅታዊ ይዞታና ሥርዐተ ምንኵስናው የሚገኝበትን ኹኔታ ተከታትሎ ለቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርት የሚያቀርብ የሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ በምልአተ ጉባኤው ተደራጀ፤ የዴር ሡልጣን ገዳምን ውዝግብ ለመፍታት ከኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ የሚደራደር በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሚመራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ምልአተ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መተዳደርያ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶሱ ጸድቋል፡፡ ደንቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትና ወጣቶች ጥራትና ወጥነት ባለው ሥርዐተ ትምህርት ተኮትኩተውና በሥነ ምግባር ታንጸው ተተኪዎች ለማድረግ የሚያስችል፣ ሁለገብ አገልግሎታቸውን ለማጠናከር የሚያግዝ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ ሕገ ወጥ ሰባክያንን በመከላከል ስብከተ ወንጌልን በተለያዩ መንገዶች ለማስፋፋት ሰንበት ት/ቤቶችን በይበልጥ የማደራጀት ሥራ ትኩረት ይሰጠዋል
  • ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከነበራቸው የበላይ ሓላፊነት ተነሥተው በበላይ ጠባቂነት ተወስነው ይሠራሉ፤ በኮሌጁ አስተዳደራዊና የፋይናንስ እንቅስቀሴ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣን አይኖራቸውም፤ የኮሌጁ ዋና ዲን በግልጽ ማስታወቂያ በውድድር በሚካሄድ የቅጥር ሥርዐት ይመደባል፡፡
  • የካህናትና ምእመናን ምዝገባ/ቆጠራ/ ለማካሄድ የተያዘው ዕቅድ ተጨማሪ ዝርዝር ጥናት ያስፈልገዋል በሚል እንዲዘገይ ተደረገ፤ የመንግሥት ፈቃደኝነትና የበጀት አቅም እንደ ስጋት ቢጠቀስም የሊቃነ ጳጳሳት ደመወዝ በመቶ ፐርሰንት እንዲጨምር መወሰኑ አነጋጋሪ ኾኗል፡፡
About these ads

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...