2015 ጁን 9, ማክሰኞ

ጾምና የዩኒቨርሲቲዎቻችን አስተዳደር


የሰኔ ጾም መግባትን ተከትሎ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የምግብ ክርክሮች መፈጠራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ ‹የጾም ምግብ ምግብ ይሠራልን› ብለው በሚጠይቁ ተማሪዎችና ‹ያቀረብንላችሁን ብቻ ብሉ› በሚሉ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደሮች መካከል ነው ክርክሩ፡፡
የዩኒቨርሲቲ አስተዳደሮች ይህንን የተማሪዎችን ጥያቄ ላለመቀበል የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች ከሦስት የዘለሉ አይደሉም፡፡ የመጀመሪያው ሃይማኖታዊ አክራሪነትን ከመዋጋት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የአንድ ሰው መጾምና መጸለይ የአክራሪነት መመዘኛዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት መዝገበ ቃላት ሊቀርብ ባይችልም፡፡ መንግሥት መመሪያ ሰጠን እንዳይሉም መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች አክራሪነትን ለመተርጎም የሚያዘጋጃቸው መዛግብት ጾምን የአክራሪነት መግለጫ አድርገው ያቀረቡበት ጊዜ የለም፡፡ አክራሪነት፣ ሽብርተኛነት፣ ጽንፈኛነት የሚሉት ጽንሰ ሐሳቦች በጥንቃቄና ገደብ ባለው ሁኔታ የማይተረጎሙ ከሆነ ለመለጠጥና የተፈለገውን ሁሉ ለማካተት ምቹዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሐሳቦች ለተቋማትና ባለ ሥልጣናት ግላዊ ትርጎማ የተመቹ በመሆናቸው በማሳያዎች፣ በመግለጫዎችና ገደብ ባለው ሁኔታ መተርጎምን የሚጠይቁ ናቸው፡፡

በወጣቶች በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የእምነት አክራሪነት እንዳይፈጠር ከተፈለገ የእምነት አክራሪነትን ከዩኒቨርሲቲዎች ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሁሉንም ሊያግባባ በሚችል ሁኔታ መተርጎምንና ግልጽ የሆኑ ማሳያዎችን ማስቀመጥን ይጠይቃል፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃይማኖት ከባሕል፣ ሥነ ልቡና፣ አመለካከትና አነዋወር ጋር በእጅጉ ድርና ማግ በሆነባቸው ሀገሮች የምዕራባውያንን ወይም የሩቅ ምሥራቆችን አስተሳሰብ ይዞ መጥቶ አክራሪነትን መበየን እንጀራን ምግብ ነው ለማለት በፓስታ መመዘኛ እንደመመዘን ያለ ነው፡፡
ለምሳሌ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ሂጃብ መልበስ ወይም ነጠላ ማድረግ የአክራሪነት መገለጫ ተደርጎ ሲወሰድ ይታያል፡፡ እነዚህ ሁለቱም መሠረታቸው እምነት ቢሆንም በሂደት ግን የሕዝቦች ባሕል ሆነዋል፡፡ አንድ ሰው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነጠላ ወይም ሂጃብ ሲለብስ እየገለጠ ያለው ሃይማኖቱን ነው ወይስ ባሕሉን? የሚለውን ለመወሰን እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲያውም በአንድ ኮሌጅ ውስጥ የኮሌጅ ጥበቃዎች ወደ ግቢው የሚገቡ ተማሪዎችን እያዩ ‹‹አንቺ መስቀለኛ አጣፍተሻልና አስተካክዪ›› እስከማለት የደረሱበትም ቦታ አለ፡፡ ለመሆኑ የአንድን ሰው አለባበስ ሃይማኖታዊ ነው ወይም ባሕላዊ ነው ብሎ የሚወስነው የግቢው ጥበቃ ነውን? በምን ሥልጣን? በየትኛውስ የዕውቀት መጠን? ለምሳሌ አንዲት ልጅ መስቀል የተጠለፈበት የሐበሻ ቀሚስ ለብሳ ወደ ኮሌጅ ግቢ ለመግባት አትችልም ማለት ነው? መስቀል የተነቀሰቺ ልጅስ?
‹የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም› እንዲሉ ሶርያና ኢራቅን፣ አፍጋኒስታንንና ሊቢያን ያየ ዩኒቨርሲቲ፣ ነጠላ መልበስንና ሂጃብ ማድረግን አክራሪነት ነው ብሎ ለመጨዋት መነሣት አልነበረበትም፡፡ የጾምም ጉዳይ እንዲሁ ነው፡፡ አንድ ሰው ሲጾም ይበልጥ ወደ አርምሞ፣ ይበልጥ ወደ ጽሙና ይገባል፡፡ ከብዙ ነገሮች ይቆጠብ ዘንድ ራሱን ይገዛል፤ አካላዊ ድካምን ተቀብሎ መንፈሳዊ ጥንካሬን ያገኛል፡፡ ጾም የልቡና ትንሣኤን የሚያመጣ ነው፡፡ እንዲያውም ጾም የአክራሪነት ተቃራኒ ነው፡፡ ራስን ለመቅጣት የሚጾም ሰው ዮሌሎችን ጥፋት ለማሰብ ዕድሉ አነስተኛ ነው፡፡ ይልቅስ አክራሪነትን ለመዋጋት ጾምን ማበረታታት አንዱ መፍትሔ ነው፡፡
ሌላው የዩኒቨርሲቲ አስተዳደሮች የሚያነሡት ሐሳብ ሴኩላሪዝምን ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች የእምነት ማስፋፊያዎች አይደሉም፡፡ ትምህርት ዓለማዊ(ሴኩላር) ነው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖታዊ የሆነውን የጾም ጉዳይ አናስተናግድም ነው፡፡ ትክክል ነው ትምህርት ቤቶች መርሐቸው ዓለማዊነት(ሴኩላሪዝም) ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች ሴኩላሪዝምን ይከተላሉ ማለት ግን ሃይማኖት በትምህርት ቤቶች ቦታ የለውም ማለት አይደለም፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሴኩላሪዝምን የተከተለ የትምህር መርሕ አላቸው፡፡ በግቢያቸው ውስጥ ግን ለተማሪዎቹ የማምለኪያ ቦታ ይፈቅዳሉ፡፡
በአሁኑ ዘመን የዓለም መንግሥታት ሴኩላሪዝምን በተመለከተ ሁለት ዓይነት አቅጣጫዎችን ይከተላሉ፡፡ የመጀመሪያው Assertive secularism ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ passive secularism ነው፡፡ አሰርቲቭ ሴኩላሪዝም ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን፣ መገለጫዎችንና ምስሎችን በአደባባይ መጠቀምን፣ ማሳየትንና መግለጥን ይከለክላል፡፡ እምነት ከግላዊ ክበብ ውጭ በይፋ ሕዝባዊ መድረክ እንዳይተገበርም  በጥብቅ ይከታተላል፡፡ ለዚህ የሚጠቀሰው የፈረንሳይና የቱርክ ሴኩላሪዝም ነው፡፡ ፈረንሳይ እኤአ በ2003 ባወጣችው ሕግ በትምህርት ቦታዎች ሂጃብ፣ የአይሁድን ኪፓ፣ ትልልቅ መስቀሎችንና ሌሎች የእምነት ይፋዊ መገለጫዎችን ማድረግን ከልክላ ነበር[1]፡፡ ፓሲቭ ሴኩላሪዝም የሚባለው ደግሞ መንግሥት ምንም ዓይነት የክልከላም ሆነ የፈቃድ ሕግ ሳያወጣ ሰዎች በራሳቸው ፍላጎት ብቻ እምነታቸውን እንዲገልጡ ለራሳቸው ነገሩን መተው ነው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ሴኩላሪዝም ይህንን የሚመስል ነው[2]፡፡
ምንም እንኳን በሴኩላሪዝም ሐሳባቸው ቢለያዩም ሦስቱም መንግሥታት ሴኩላር መንግሥታት ናቸው፡፡ ያም ማለት የሕግና የመንግሥት ሥርዓታቸው ከሃይማኖታዊ ተጽዕኖ ውጭ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ አንድን የተለየ ሃይማኖትን ወይም ደግሞ ፀረ እምነትነተን (Atheism) ኦፊሴላዊ አድርገው አልተቀበሉም፡፡ ብዙ ሊቃውንት ደግሞ ሴኩላር መንግሥትን በሁለት ነገሮች ይበይኑታል፡፡ የመጀመሪያው የመንግሥትና ሃይማኖት መለያየት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ የእምነት ነጻነት ነው[3]፡፡ በብዙ ሴኩላር መንግሥታት የመንግሥትና እምነት መለያየት በሕገ መንግሥት የተገለጠ አይደለም፤ ትግበራውን በአጽንዖት የመከታተል ሁኔታም የለም(It is not a practical issue)፡፡ በተቃራኒው የእምነት ነጻነትን በተመለከተ ግን በሕገ መንግሥት ግልጽ በሆነ ሁኔታ የሚቀመጥ ተግባዊነቱንም በአጽዖት የሚከታተሉት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ከመንግሥትና እምነት መለያየት ይልቅ የእምነት ነጻነት መከበር ዋነኛው የሕዝቦች ጥያቄ መሆኑን ነው፡፡ የሦስቱም መንግሥታት ልዩነት የመጣው ይህንን የእምነት ነጻነት የመተርጎም ላይ ነው፡፡
 የኢትዮጵያ መንግሥት ብሎም የትምህርት ተቋማት የትኛውን ዓይነት የሴኩላሪዝም መንገድ እንደሚከተሉ ግልጽ አይደለም፡፡ አሰርቲቭ ሴኩላሪዝምን ነው እንዳንል መንግሥት ራሱ የእምነት በዓላትን በብሔራዊ ቴሌቭዥን ሲያስተላልፍ ይታያል፤ በፓርላማውም የእምነት መገለጫ ልብሶችን የለበሱ ተወካዮች ይታያሉ፡፡ ፓሲቭ ሴኩላሪዝምን ነው እንዳይባልም በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ክልከላዎች አሉ፡፡ የአሰርቲቭ ሴኩላሪዝም ዋናው ዓላማ እምነትን ከሕዝባዊ መድረክ(public sphere) ለማውጣት ይሁነኝ ብሎ መሥራት (comprehensive doctrine) ሲሆን የፓሲቭ ሴኩላሪዝም ሚና ግን መንግሥት በልዩ ልዩ እምነቶች ውስጥ ያለውን የገለልተኛነት ሚና አጽንቶ መጠበቅ ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ እምነቶች፣ ባሕሎችና ልማዶች ባሉባት ሀገር፤ ሃይማኖት ትምህርት ብቻ ሳይሆን ባሕል፣ የቀን አቆጣጠር፣ አለባበስ፣ የአስተሳሰብ ቅኝትና የአነዋወር መንገድ በሆነባት ሀገር፤ በባሕልና እምነት መካከል የተቆረጠ መሥመር ለማስመር በሚያስቸግር ማኅበረሰብ ውስጥ፤ መንግሥትም ሆነ የትምህርት ተቋማት ቢከተሉት የሚመከረው ፓሲቭ ሴኩላሪዝምን ነው፡፡ አንደኛው በእምነቱ ምክንያት በሌላው ላይ ተጽዕኖ የማያደርግ ከሆነ፣ መንግሥታዊ ሥራን፣ ሕጋዊ ሂደትንና የመማር ማስተማር ሂደቱን ትርጉም ባለው መጠን እስካላወከ ድረስ፣ ተቋማቱም ይሁነኝ ተብሎ ለሚደረግ የእምነት ማስፋፋት ሥራ[4] መድረክ እስካልሆኑ ድረስ ፓሲቭ ሴኩላሪዝም ለኢትዮጵያ ተመራጭ ነው፡፡
ጾምን ከዚህ አንጻር የተመለከትነው እንደሆነ በምንም መልኩ ይሁነኝ ተብሎ በኮሌጅ ውስጥ የሚደረግ የሃይማኖት ማስፋፋት እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ሰዎች ተሰብስበው ሊማሩና ሊጸልዩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ተሰብስቦ መጾም ግን አይቻልም፡፡ ጾም ግላዊ ስለሆነ፡፡ በተመሳሳይ የጾም ወቅት የሚሳተፉ ሰዎች ግን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሙስሊምና ክርስቲያን ተማሪዎች ዘንድ በኮሌጆች የሚታየውም ይኼው ነው፡፡ በአንድ ተመሳሳይ የጾም ወቅት የሚደረግ ሱታፌ፡፡ በርግጥ ይሄ የጾ ሐሳብ  እምነትን ግላዊ ብቻ ለማድረግ ከሚያስበው አመለካከት ይለያል፡፡ ምዕራባውያን ‹እምነት ግላዊ ብቻ ነው› ብለው የሚቀበሉት ሐሳብ በፕሮቴስታንት የእምነት አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እምነት ግላዊ ምርጫ አለው፡፡ በግላዊ ወሳኔም የሚከተሉት ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ግላዊ ምርጫና ውሳኔ በኅብረት መግለጥና መሳተፍ የሚጠይቅበት ጊዜ ግን አለ፡፡ በኦርቶዶክስ፣ በካቶሊክ፣ በእስልምናና በይሁዲ እምነቶች ዘንድ ግላዊ የሆኑ የእምነት ሕይወቶችና ሕዝባዊ(ማኅበራዊ) የሆኑ የእምነት ሕይወቶችም አሉ፡፡ የረመዳን ጾምና የሑዳዴ ጾም የዚህ ማኅበራዊ የእምነት ክበብ መገለጫዎች ናቸው፡፡
ትምህርት ቤቶች የጋራ ሱታፌን የሚጠይቁትን ማኅበራዊ የእምነት ክዋኔዎችን መከልከል የለባቸውም፡፡ ምናልባት የጋራ ክዋኔ(Public demonstration) የሚጠይቁ ማኅበራዊ ክዋኔዎች ላይ እንደየሁኔታው ተዐቅቦ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፡፡[5] ጾም ግን የጋራ ሱታፌን እንጅ ክዋኔን አይጠይቅም፡፡ የጋራ ሱታፌውም የሚመጣው በተመሳሳይ ወቅት በተመሳሳይ ሥርዓት ስለሚጾም ነው፡፡
ሃይማኖታዊ እሴቶችን በተመለከተ የክልከላን አሠራር ከመከተል የገለልተኛነትን አሠራር መከተሉ የሚጠቅመው ሃይማኖታዊ እሴቶች ዛሬ ዛሬ በኮሌጅ ተማሪዎች ዘንድ በአደገኛነት እየመጡ ያሉትን የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚነት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ የትምህርት ግዴለሽነት፣ በጊዜያዊ ጥቅሞችና ደስታዎች ዘላቂ መሥመርን መሳት፣ የጠባብነትና የጎጠኝነት አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን ለመከላከል የላቀ ሚና ስለሚኖራቸው ጭምር ነው፡፡ የትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ አፈጻጸሙ ውስብስብ ከሚሆነው አሰርቲቭ ሴኩላሪዝም ይልቅ ፓሲቭ ሴኩላሪዝምን ቢከተሉ ሃይማኖት በማኅበረሰቡ ውስጥ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት መንገዱን ያመቻቻሉ፡፡ የነገው ትውልድም ብዙኅነትን በአዎንታዊ መልክ ለምዶትና ገንዘብ አድርጎት ከዩኒቨርሲቲ እንዲወጣ ያደርጉታል፡፡ እንዲያውም ዩኒቨርሲቲዎች እንደሌሎች የመንግሥት ተቋማት የሃይማኖትን ጉዳይ በ‹የለሁበትም› መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ ምሁራዊ ውይይት እንዲደረግበት መንገድ ቢከፍቱ አንዱ ስለሌላው በጎውን የማወቅና ልዩነቱን ተቀብሎ በሰላም ለመኖር እንዲችል ያደርጉ ነበር፡፡ ሰው በጠባዩ የማያውቀውን ነገር ይፈራዋል፣ ይሠጋዋልም፡፡ የእምነት ጉዳዮችን በምሁራዊ መንገድ በማየት መተዋወቁ ቢፈጠር ፍርሃትና ሥጋቱን ለማስወገድ በተቻለ ነበር፡፤ የትምህርት ተቋማት ሴኩላር መሆንም ለዚህ ነበር ዋናው ጥቅሙ፡፡ ጾም ለመከልከል አልነበረም፡፡  
     ሌላው የዩኒቨርሲቲ አስተዳደሮች የሚያነሡት መከራከሪያ ‹‹የተለያዩ ቡድኖችን ፍላጎት በአነስተኛ የኢኮኖሚ ዐቅም ውስጥ ማሟላት ስለማንችል በዩኒቨርሲቲው ዐቅም ላይ የተመሠረተ አንድ ወጥ መርሐ ግብር ብቻ ነው የምንከተለው›› የሚል ነው፡፡ በርግጥ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ አውሮፓና አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለእምነቶቹ ሁሉ የማምለኪያ ቦታ ለመስጠት የሚያስችል ዐቅም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የጾም ምግብ ለማዘጋጀት የሚያስችል አቅም አላቸው፡፡ በሁለት ምክንያት፡፡ የመጀመሪያው የኦርቶዶክስም ሆኑ የሙስሊም የጾም ወቅቶች ጊዜያቸው የታወቀ ነው፡፡ ለጋራ አስተዳደር አስቸጋሪ አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጾም ምግብን ማዘጋጀት ለአንድ ዩኒቨርሲቲ ከፍስክ ምግብ ይልቅ ርካሽ ነው፡፡ ይህም የዩኒቨርሲቲውን በጀት የሚያቃውስ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደጉም ነው፡፡ የተማሪዎቹ ጥያቄ ከምንበላው ምግብ የሥጋ፣ የቅቤ፣ የወተትና የዕንቁላል ነገር ተቀንሶ አትክልትና ሽሮ ይሰጠን ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ክርክር ደግሞ በጾም ሥጋ ካልበላችሁ የሚል ነው፡፡     
በዚህ ሰሞን ያለው ሁኔታ እንኳን ብንመለከት አንድ ኮሌጅ ሦስት የምግብ መርሐ ግብር ብቻ ይጠበቅበታል፡፡ ለሙስሊም ተማሪዎች የማፍጠሪያ ምግብ ማዘጋጀት(ያም ቢሆን ቀድሞ የሚሰጣቸውን የቁርስና የምሳ ነገር ትቶ እራት ላይ ማቅረብ እንጂ አዲስ ነገር አልጠየቁትም)፣ ለኦርቶዶክስ ተማሪዎች የጾም ምግብ ማዘጋጀት፣ ለሌሎች ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው መርሐ ግብር መሠረት ማዘጋጀት፡፡ ዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ሠራተኞችንና ቁሳቁሶችን ለማቅረብ በጀት የለኝም ካለ እንኳን ተማሪዎች ሲጾሙ በተውት በጀት መጠቀም ይችላል፡፡ ቅንነቱ ካለ፡፡ ለዚያውስ ቢሆን ‹ለስሟ መጠሪያ ቁና ሰፋቺ› ሆኖ ነው እንጂ ኮሌጅ ውስጥ ስንት ቀን ሥጋ ተበልቶ ነው?
በአሁኑ ዘመን ሥጋን የማይመገቡ ማኅበረሰቦች በዓለም ላይ እየተፈጠሩ ነው፡፡ በብዙ ቦታዎችም ለእነርሱ የሚሆኑ ምግቦች ይዘጋጃሉ፡፡ ታላላቅ ሆቴሎች፣ የግብዣ ቦታዎች፣ መንግሥታዊ ሥነ ሥርዓቶች፣ በዓሎች፣ የአውሮፕላን ጉዞዎች፣ ወዘተ ሥጋ ለማይመገቡ ሰዎች የተለየ ምግብ ማዘጋጀታቸውን በይፋና በኩራት ይገልጡታል፡፡ ጉዳዩንም ከመብትና ለተጠቃሚ የተመቸ ከባቢ ከመፍጠር አንጻር ያዩታል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም እነዚህ ሥጋ የማይበሉ ማኅበረሰቦች ቢፈጠሩባቸው ሥጋ የመብላት ግዴታ አለብህ ሊሉ ነው? ብዙዎቹ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሹመኞች ለትምህርት ወይም ለሥልጠና አለበለዚያም ለልምድ ልውውጥ ወደ ውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ሄደው ነበር፡፡ የተማሪዎችን ፍላጎቶች እንዴት ከትምህርት ቤት ፖሊሲ ጋር በተጣጣመና ማንንም በማይጎረብጥ መልኩ እንደሚያስተናግዱት አላዩምን? 
መካነ አእምሮ የሆነው ዩኒቨርሲቲ ጾምን የመሰሉ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ከእምነት ነጻነትና ተገቢውን አገልግሎት ከማግኘት መብት አንጻር እጅግ በሠለጠነ መንገድ ተርጉሞ በቀላሉ ችግሩን መፍታት ካቃተው ‹መካነ አእምሮ› ከሚለው ቃል ውስጥ ‹ካ› እንዲጠብቅ ያደርገዋል፡፡ 
Posted by ዳንኤል ክብረት

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...