የገና
እና የጥምቀት በዓላት ሲደርሱ በምእመናኑ ዘወትር የሚጠየቁ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህን እና መሰል የሕዝቡን
የዘወትር ጥያቄዎች መልስ የያዘ የማያዳግም ጥራዝ ማውጣት ከሊቃውንት ጉባኤ የሚጠበቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ ጉዳዮች አበው
ቀድመው ሥርዓት የሠሩባቸው እና ማብራርያ ብቻ የሚያስፈልጋቸው ናቸውና፡፡ ለዛሬ ሦስቱን ብቻ እንመልስ፡፡
ገና እና ጥምቀት ዓርብ እና ረቡዕ ቢውሉ ይበላባቸዋል ወይስ ይጾማሉ?
ፍትሐ ነገሥት፡ ዳግመኛ በየሳምንቱ ዓርብ እና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ፣ የልደት እና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር /ዐንቀጽ 15፣ ቁ566/
የዓርብን እና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት፣ከጥምቀት እና ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 603/
የገና እና የጥምቀት ቅዳሴ ስንት ሰዓት ነው?
ፍትሐ ነገሥት፡ ስለ ልደት እና ጥምቀት ግን በዚያ ዘመን በኒቂያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዙ /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 595/
ልደት ጋድ አለው?
ፍትሐ ነገሥት፡ የልደት እና የጥምቀት በዓላት ጋድ አላቸው /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 566/
ትንታኔ፡ የገና ጾም 44 ቀናትን ይይዛል፡፡
40 ጾመ ነቢያት
3 ጾመ አብርሃም ሶርያዊ
1 ጋድ
ድምር 44
የገና ጋድ ከጾሙ ተያይዞ የተቀመጠ እንጂ ለብቻው
የተቀመጠ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰሙነ ሕማማት ለብቻው የሚቆጠር ጾም ነው፡፡ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 565/ ነገር ግን
አንድ ሰው ዐቢይ ጾምን ሳይጾም ከርሞ ሕማማትን ለብቻው መጾም አይችልም፡፡ የገናም ጋድ እንዲሁ ነው፡፡
ይህንን ጋድ የልደትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች እንዲጾሙት የተሠራ ነውን?
መልስ፡
በቤተ ክርስቲያን ላልተጠመቁ፣ ለማይቆርቡ፣ ንስሐ ለማይገቡ፣ ለማያስቀድሱ፣ ለማይጾሙ ሰዎች ተብሎ የተሠራ ልዩ
ሥርዓት የለም፡፡ በፍትሐ ነገሥት ዐንቀጽ 15፣ ቁ 565 እንደተገለጠው ሰባቱ አጽዋማት «ለክርስቲያን ሁሉ» የታዘዙ
ናቸው፡፡ ስለዚህም የገናን ጾም ክርስቲያን ሁሉ ጾመው በበዓለ ልደት ሊገድፉ ይገባቸዋል፡፡ ፍትሐ ነገሥት ስለ ገና
ጾም ሲገልጥ «መጀመርያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የልደት በዓል ነው» ይላል /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 568/፡፡ ይህም
ከገና ጾም ተሸርፎ የሚጾም ነገር እንደሌለው ያሳያል፡፡
መልካም በዓል