ረቡዕ 17 ጁን 2015

ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም (ክፍል አንድ)

    



በዲ/ን ዳንኤል ክብረት
      (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
     ውድ የመቅረዝ አንባብያን! እንዴት አላችሁ? ይህ ጽሑፍ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ማኅበረ ቅዱሳን ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ቡኢ ደብረ ሰላም በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ባዘጋጀው የበእንተ ወንጌል መርሐ ግብር ላይ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ ስብከቱ አንድ ሰዓት ከዐሥር ደቂቃ የሚፈጅ ስለኾነ ወደ ጽሑፍ ሲቀየር ትንሽ በዛ ይላል፡፡ በመኾኑም በኹለት ክፍል እንዳቀርበው ተገድጃለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዲ/ን ዳንኤል ሲሰብክም የሚያነብ ስለሚመስል ብዙ የሚደጋገሙ ዐረፍተ ነገሮችን ስለሌሉበት፥ ያስተካከልኩት ነገር ቢኖር በጉባኤው ላልነበረ ሰው የማይረዱ ጥቃቅን ስንኞችን ብቻ ነው፡፡ ስለ ኹሉም መልካም መልካም ንባብ ይኹንላችሁ!!!

 ይህንን ቃል የተናገረው ከዛሬ 700 ዓመት በፊት በደቡብ እስከ ባሌ ድረስ ተዘዋውሮ ያስተማረው፣ ለስብከተ ወንጌል ሲል ሕይወቱን የገበረው፣ በኋላም በቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቅ ፍሬ ያፈራው፣ የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍሬዎች ከኾኑት ከ12ቱ መምህራነ ወንጌል አንዱ የኾነው ታላቁ አኖሬዎስ ነው፡፡ ቅዱስ አኖሬዎስ በባሌ፣ በምዕራብ ሸዋ ኹለት ታላላቅ ገዳማት ነበሩት፡፡ ኹለቱም በ16ኛ መ.ክ.ዘ. መጀመሪያ አጋማሽ ላይ ግራኝ አገሪቱን ባጠፋበት ጊዜ እንደጠፉ እስከ አሁን አልተመለሱም፡፡ አንዱ ገዳሙ ብቻ በደቡብ ወሎ ከደሴ ከተማ 12 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ይኼ ታላቅ ሐዋርያ በደቡብ ኢትዮጵያ ታላቅ ሥራ ከሠሩት 12ቱ መምህራን አንዱ ነው፡፡ እየተዘዋወረ ሲያስተምር በወቅቱ የአከባቢው ገዢ የነበረና ገና ክርስትናን ያልተቀበለ አገረ ገዢው አስጠርቶ፡- “በእኔ አገር እኔ ሳልፈቅድልህ እኔ የማላውቀውን አዲስ ሃይማኖት ለምን ታስተምራለህ? አንተንስ እዚህ ቦታ ምን አመጣህ?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ፡- “ገና እስከማናውቃቸው ቦታዎች ድረስ እንሔዳለን፡፡ በእግዚአብሔር ጉባኤ አንድ የኾንነውን፥ ነገር ግን እኛ በአካል ያላወቅናቸው ወንድሞቻችንን እስክናውቅ ድረስ አንደክምም፡፡ የእግዚአብሔር አገር ሰፊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አገር እስኪያልቅ ድረስ አገልግሎታችን አያልቅም” አለው፡፡ አገረ ገዢውም፡- “ለምን አንድ ቦታ ተቀምጠህ አትሠራም? አገሩን እየዞርክ ለምን ትረብሻለህ?” ብሎ ሲጠይቀው “እኛ’ኮ ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም” አለው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ፍሬ ነገርም ይኼው ነው፤ መሔድ፡፡
ለዐሥራ ኹለቱ የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት የተሰጠው ስያሜም ከመሔድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሐዋርያ ማለት ሒያጅ ማለት ነው፡፡ በሐዋርያነት አገልግሎት ትልቁና የመጀመሪያው ሥራ መሔድ ነው፡፡ ከሚያውቁት ወደማያውቁት፣ ከተከበሩበት ወዳልተከበሩበት፣ በባሕል፡ በቋንቋ፡ በሐሳብ ከሚግባቡት ወደማይግባቡት፣ ከቅርቡ ወደ ሩቁ መሔድ ነው፤ ሐዋርያነት፡፡ ጌታችንም ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ኹለት ትእዛዛት ሰጥጻቸው ነበር፡፡ አንዱ በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ የተመዘገበ ሲኾን ኹለተኛውም “ሒዱና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ነው /ማቴ.28፡20/፡፡ ሦስት ኃላፊነቶችን ነው የተሰጣቸው፡፡ የመጀመሪያው መሔድ ነው፤ ኹለተኛው ማስተማር ነው፤ ሦስተኛው ተምረው ያመኑትን አጥምቆ ደቀ መዝሙር ማድረግ ነው፡፡ በዚሁ የወንጌል ሐሳብ መሠረት ደቀ መዝሙር ማድረግ ማለት ክርስቲያን ማድረግ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ደቀ መዛሙርት በኋላ “መጀመሪያ በአንጾክያ ክርስቲያን ተባሉ” ይላልና /ሐዋ.11፡26/፡፡
ደቀ መዝሙር ማድረግ ክርስቲያን ማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያው ትእዛዛቸው ግን ሒዱ ነው የተባሉት፡፡ “በዚህ በኢየሩሳሌም፣ በምታውቁት ቦታ፣ በለመዳችሁት ቦታ፣ ዓሣ ስታደምጡበት በኖራችሁት ቦታ፣ ቋንቋዉን ባሕሉን በምታውቁት ቦታ፣ ብዙ ዘመዶች፡ ብዙ ወዳጆች ባልዋችሁ ቦታ እንዳትቀመጡ፤ ሒዱ” ነው የተባሉት፡፡ እንዲያውም በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ የመጀመሪያው ሰማዕትነት ሲደርስና ሐዋርያት በየቦታው ሲበተኑ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት “ሒዱና ዓለምን በሙሉ አስተምሩ” የተባሉት ሐዋርያት እንዴት እንደሚኬድ ስለማያውቁትና ለመንገዱም አዲስ ስለነበሩ በዚያች በኢየሩሳሌም ከተማ አንዲት ማኅበር መሥርተው ለ7000 ማኅበረ እስጢፋኖስ ተቀምጠው ነበር፡፡ ከመላው ዓለም የመጡ አይሁድ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩትም አይሁድ አንድ ኾነው እዚያ ነበሩ፡፡ ለብዙ ቀናትም እዛ ተቀመጡ፡፡ በመጨረሻ ግን ቅዱስ እስጢፋኖስ በሰማዕትነት ሲያርፍና በቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና ሲመጣ ኹሉም በየመንገዳቸው ወንጌልን እያስተማሩ ሔዱ፤ ተበተኑ /ሐዋ.8/፡፡ ከኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሱ ከቅዱስ ያዕቆብ በስተቀር ኹሉም ተበተኑ፡፡ ሐዋርያት ብቻ ሳይኾኑ በዛች በማኅበረ ቅዱስ እስጢፋኖስ አማካኝነት የተማሩት ሌሎች ምእመናንም ጭምር አገሪቱን ትተው በሔዱበት ጊዜ በየመንገዳቸው ወንጌልን እያስተማሩ ነው የሔዱት፡፡ ይኼ የሚነግረን የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እኔና እናንተም የተጠራንበት አገልግሎት መሔድ መኾኑን ነው፡፡ ታላቁ አኖሬዎስም “ሒዱ እንጂ ተቀመጡ አልተባልንም” ነው ያለው፡፡
“እንዴት ነው የምንሔደው?” የሚለውን ደግሞ ጌታችን ከማረጉ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በሐዋ.1፡8 ጀምሮ ነግሯቸዋል፡፡ “ሒዱና አስተምሩ ብለኸናል፤ መሔድ ግን ምንድነው? እንዲሁ ዝም ብሎ መሄድ ነውን?” የሚለው የሐዋርያት ጥያቄ ነበርና፡፡ ለዚህ ጌታችን መሠረቱን መሥርቶላቸዋል፡፡ “በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ እስከ ዓለም ዳርቻ ምስክሮቼ ትኾናላችሁ” በማለት፡፡ ይኼን ምስክርነት በአራት ደረጃ በአራት ምዕራፍ ከፍሎ ነው የነገራቸው፡፡ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ እስከ ዓለም ዳርቻ በማለት፡፡ በአንድ ጊዜ ወደ ዓለም ዳርቻ እንዲሔዱ አልነገራቸውም፡፡ በእነዚህ በአራቱ ደረጃዎች ግን እስከ መጨረሻው እስከ ዓም ዳርቻ ድረስ እንዲሔዱ ነግሯቸዋል፡፡ እስኪ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡
በኢየሩሳሌም ማለት ምንድነው?
ኢየሩሳሌም ከኦሪት ዘመን ጀምሮ የምትታወቅ የሰላም ከተማ ተብላ የተጠራች ከተማ ናት፡፡ ቤተ መቅደሱም ቤተ መንግሥቱም የነበረባት ከተማ ናት፡፡ የዳዊትና የሰለሞን ከተማ ናት፡፡ የመልከ ጼዴቅ ከተማ ናት፡፡ በክርስትና ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁን የማዳን ሥራ የፈጸመበት (የፈተረደበት፣ የተገረፈበት፣ የተሰቀለበት፣ የሞተበት፣ ከሙታን የተነሣበት፣ ያረገበትና መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት) ሥፍራ ነው፡፡ የመጀመሪያዋም ቤተ ክርስቲያን (ጉባኤ ምእመናን፣ ጉባኤ ካህናት) የተመሠረተባት ቦታ ናት፡፡ ለቅዱሳት ቦታዎች (ለጎልጎታ፣ ለደብረ ዘይት) በጣም ቅርብ ቦታ ናት፡፡ ሐዋርያትም የነበሩት፣ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት፣ አገልግሎታቸውንም የጀመሩት በኢየሩሳሌም ነው፡፡ በኢየሩሳሌም የጀመሩት አገልግሎት ግን በኢየሩሳሌም እንዲጨርሱት አይደለም የታዘዙት፡፡ በዓለም ዳርቻ እንዲጨርሱት ነው የታዘዙት፡፡
ኢየሩሳሌም በዚያን ጊዜ ለክርስትናው ምቹ ናት፡፡ ቢያንስ ብዙ ክርስቲያኖች አሏት፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ያመኑት 3,000 ምእመናን ተጨምረዋል፡፡ ጌታችን መነሣቱን፣ ማረጉን የሚያውቁ ሌሎች ምእመናን አሉ፡፡ ማረፊያቸው ማለትም የማርያም ቤት እዚያ ነው ያለው፡፡ ጸሎት ለማድረግ የጌታችን መቃብር ቅርብ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ቅዱሳን ሐዋርያት በበዓለ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው በ72 ቋንቋ ሲናገሩ ያዩ የሰሙ ምስክሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ይኼ ቦታ ምቹ ነው፡፡ በዚህ ነው ስምሪቱን እንዲጀመር ጌታችን ያዘዘው፡፡
ኢየሩሳሌም ምንድነው? ኢየሩሳሌም ቤተሰብ ነው፡፡ የስብከተ ወንጌል ስምሪት የሚጀመረው ከቤተሰብ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጉባኤ፣ የመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት፣ የመጀመሪያው ትምህርት መሰጠት ያለበት ከባል፣ ከሚስት፣ ከልጆች ነው፤ ከቤተሰብ፡፡ አሁን ብዙዎቻችን በሰርክ ጉባኤ፣ እንደ በእንተ ወንጌልና ሐዊረ ሕይወት ባሉ ጉባኤያት፣ በየገዳማቱ በሚደረጉ ጉዞዎች ልናገኘው የምንሞክረውን ትምህርት በዛ አልነበረም ማግኘት የነበረብን፡፡ ከቤት ውስጥ ነበር ማግኘት የነበረብን፡፡ ይኼኛው (የሰርኩና የሌላው ጉባኤ) ያገኘነውን የምንሠራበት፣ የምናጠናክርበት፤ “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም” እንደተባለ ወንጌል ምግብም ስለኾነ ይበልጥ የምንመገብበት እንጂ አዲስ ዕውቀት፣ መሠረታዊ ትምህርት የምናገኝበት አልነበረም መኾን የነበረበት፡፡ እንዲህ እየኾነ ያለው በኢየሩሳሌም አገልግሎት ስለሌለ ነው እንጂ፡፡ ከቤት ነበር መማር የነበረብን፡፡
ይኼንን ኹላችንም ከምናውቀው አንድ ታሪክ ምሳሌነት እንይ፡፡ ከታላቁ ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፥ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኾነው እንዲወጡ ያደረጋቸው አንዱ መሠረት በቤታቸው ያገኙት ትምህርት ነው፡፡ ገድላቸው እንደሚነግረን በሰባት ዓመታቸው ነው አባታቸው ቁጭ አድርገው ከመዝሙረ ዳዊት ጀምረው ከዚያም ብሉይንና ሐዲስን ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ጭምር ያስተማሯቸው፡፡ እስኪ ስንቶቻችን ነን በቤታችን ብሉይንና ሐዲስን ያለን? ስንቶቻችን ነን በቤታችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚነበብልን ወይም የምናነብ? በስንቶቻችን ቤት ስንክሳር ይነበባል? በስንቶቻችን ቤት ገድለ ቅዱሳን ይነበባል? እዛ ስላልለመድነው ነው’ኮ ከፍ ስንል በቅዱሳት ገድላት ላይ ጥያቄ የምናነሣው፡፡ እንግዳ ትምህርት የሚመስለን ገና ከቤታችን ስላልለመድነው ነው፡፡
ለምንድነው እንጀራ ላይ ጥያቄ የማይነሣብን? ብዙዎቻችን በእንጀራ ላይ ጥያቄ የለብንም፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ እንጀራ ላይ ጥያቄ የለውም፡፡ እንደዉም አንድ ሰው ወደ ውጪ ሲሔድ ለመጀመሪያ ከቤተሰብ ላኩልኝ የሚለው እንጀራ ድርቆሽ ነው፡፡ ብዙ ነገር ይረሳል፤ እንጀራንና ሽሮን ግን አይረሳም፡፡ ለምን? ከሕፃንነታችን ጀምሮ፣ አንዳንዶቹ ሱስ ኾነባቸዋል እስኪሉን ድረስ ለእንጀራ ልዩ ፍቅር ያለን ስለ ምንም ምክንያት አይደለም፡፡ እንጀራ ውስጥ ምን ዓይነት ማዕድን እንዳለ እንኳን ያወቅነው በኋላ ነው፡፡ ለእንጀራ ልዩ ፍቅር ያለን እናቶቻችን፣ አባቶቻችን ከልጅነታችን አንሥተው ያጎረሱን ርሱ ስለኾነ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲህ ከቤተሰብ ጀምረን ተምረን ቢኾን በኋላ እንግዶች አንኾንም ነበር፡፡ ለጥቅስ እንግዶች አንኾንም ነበር፡፡ ለስንክሳር፣ ለገድለ ቅዱሳን፣ ለቅዳሴው እንግዶች አንኾንም ነበር፡፡
(ጸጋ ዘአብ) አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በሰባት ዓመታቸው ነው ብሉይንና ሐዲስን ሌሎችንም ቅዱሳት መጻሕፍት ጨምረው ያስተማሯቸው፡፡ በዛ ሰዓት ነው ትምህርት መጀመር የነበረበት፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት’ኮ “አንድ ልጅ ሰባት ዓመት ሲሞላው ጾም ይጀምራል” የሚባለውም ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ትምህርቱም አብሮ ስለሚጀምር ነው፡፡ ትምህርቱም ከጾም፣ ከጸሎት ጋር መኾን ስላለበት ጭምር ነው፡፡ ያ የሰባት ዓመት ዕድሜ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚማርበት፣ በኢየሩሳሌም የሚሰጠውን የወንጌል አገልግሎት የሚጀምርበት ዕድሜ ነው፡፡
ዛሬ ይህን ጽሑፍ የምናነብ ቤተሰቦች ይህን ይዘን መሔድ አለብን፡፡ “ለማስተማር የሚችል ዕውቀት የለንም” ብንል እንኳን በየቤታችን ቅዱሳት መጻሕፍትን አምጥተን እንደ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እራት ከመበላቱ በፊት እንዲያነቡ ማድረግ እንችላለን፡፡ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እራት ከመቅረቡ በፊት (ያውም እንደዛሬ መብራት ሳይኖር) እሳት እየነደደ ወይም ደግሞ ሌሎች በእሳት የሚሠሩ መብራቶች እየነደዱ ልጆች ተነሥተው፣ ልጆች እስኪደርሱ ድረስ ደግሞ የተመደበ ካህን ወይም ዲያቆን ወይም መሪጌታ መጥቶ እዚያ ቤት ውስጥ ወይም ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ የቆሎ ተማሪዎች የምንላቸው የአብነት ተማሪዎች በየቦታው ሲሰማሩ አንዱ ሥራቸው ይኼ ነበር፡፡ እዚያ ቤት ተጠግቶ፣ ምግብ እየተሰጠው፣ እየተማረ፣ ለቤተሰቡ ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበበ፡፡ እራት ከመበላቱ በፊት ገድለ ቅዱሳን፣ ስንክሳር ተነቦ ነው እራት የሚበላው፡፡ 
በባሕላችን አንድ አባባል አለ፤ “እራትና መብራት አይንሳን” የሚል፡፡ ኢትዮጵያውያን ምሳ ስለማይበሉ ነውን? ቁርስ ይንሳን ማለታቸው ነውን? ለምድነው እራት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ለምንድነው? እራትና መብራት የተባለው ባሕላችን የገበሬው ባሕል ነው፡፡ ገበሬው ሲሠራ ነው የሚውለው፡፡ ምሳ የሚባለው በየዋለበት ሥፍራ ነው፡፡ የሚያጭደውም አጨዳ ቦታ፤ የሚያርሰውም እርሻ ቦታ፤ የሚነግደውም የንግዱ ቦታ ነው የሚበላው፡፡ ቤተ ሰብ የሚሰበሰበው እራት ላይ ነው፡፡ ከብት የያዘውም ከብቱን ይዞ ይመጣል፤ አራሹም ከግብርናው ይመለሳል፤ ቤት የዋለውም የቤት ሥራውን ጨርሶ ይጠብቃል፡፡ በኢትዮጵያውያን ባሕል እራት ትልቅ ነው፡፡ ከምግብነት ያለፈ የቤተሰቡን አንድነት የሚያስረዳ ነው፡፡
ይኼ የእኛ ባሕል ብቻ አይደለም፡፡ በባሕል የምንዛመዳቸው ሌሎች ምሥራቃውያንም ከምሳና ከቁርስ በላይ ትልቁ ትኩረታቸው እራት ነው፡፡ ጌታችንም በምሴተ ሐሙስ ሥጋዉንና ደሙን ለሐዋርያት የሰጠው በቁርስ አይደለም፤ በምሳ ሰዓት አይደለም፤ በእራት ነው፡፡ “የመጨረሻው እራት” የምንለውም ለዚያ ነው፡፡
እራት በእኛ ባሕል ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የቤተሰቡ መሰብሰቢያ ነው፡፡ በዚያ ሰዓት ነው ቅዱሳት መጻሕፍት ይነበቡ የነበሩት፡፡ ዛሬ ይኼ ቤተሰብ ስለጠፋ ነው ብዙዎቻችን እያወቅነው፣ ፍቅሩ እያለን፣ እየወደድን መልስ ያጣነው፡፡ እመቤታችንን ማመን፣ ስለ እመቤታችን መቆርቆር፣ የእመቤታችን ስም ሲነሣ ደማችን እንዴት እንደሚሞቅ ኹላችንም እናውቋለን፡፡ ይኼንን የሚቃወሙ ሰዎች ኹለትና ሦስት ነገር ይዘው ሲመጡ ግን የሚኾን መልስ ያጣነው ፍቅሩ ጠፍቶብን አይደለም፡፡ ይኼ የቤተሰብ ማለትም ኢየሩሳሌም ውስጥ መሰጠት የነበረበት የወንጌል አገልግሎት ስለተቋረጠ ነው፡፡
ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሳ 40 እና 50 ሚልዮን ሕዝብ የሰበሰበችው እንዲህ እኛ እንደምናደርገው ዓይነት ጉባኤ አዘጋጅታ አይደለም፡፡ በቤተሰብ የሚያስተምሩ መምህራን ስለነበሯት ነው፡፡ የሌሎች ቅዱሳንንም ታሪክ ብናይ እንደዚህ ነው፡፡
(ጸጋ ዘአብ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን) እስከ 15 ዓመታቸው ድረስ ለ8 ዓመታት ያህል ቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምረው ነው ወደ ሊቀ ጳጳሱ የወሰዷቸው፡፡ “አሁን አውቀሃል፤ አሁን ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል አለብህ” ብለው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ያፈሩት ራሳቸው ጸጋ ዘአብ ናቸው፡፡ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን ይህን የሚያፈራ ቤተሰብ አለን ወይ? “ልጄ መማር አለበት፤ ማወቅ አለበት፤ ነገ ወጥተህ መድረክ ላይ ወንጌል የምታስተምረው አንተ ነህ፤ ነገ ዲያቆን ካህን ጳጳስ ኾነህ የምታገለግለው አንተ ነህ፤ ነገ በገዳማት ገብተህ መናኝ መነኮሴ የምትኾነው አንተ ነህ፤ ነገ በየመሥሪያ ቤትህ ቁጭ ብለህ የቢሮ ሥራህን ስትሠራ የሃይማኖት ጉዳይ ሲመጣ ልክ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምትመሰክረው አንተ ነህ” የምንል አለን ወይ?
ቅዱስ ጊዮርጊስኮ አባቱ ከልጅነቱ አንሥቶ አስተምሮ ስላሳደገው ነው የአባቱን መንግሥት ልረከብ ብሎ ሲሔድ ሰባዎቹ ነገሥታት እግዚአብሔር ላይ ሲያላግጡና ጣዖታትን ሲያመልኩ ሲያይ “አይ! ይኼን መንግሥት ተቀብዬ’ማ ሃይማኖቴን አልተውም” ብሎ ምስክርነትን መስጠት የጀመረው፡፡ ለምንድነው ዛሬ የቢሮ ሠራተኛው፣ የጥበቃ ሠራተኛው፣ ፖሊሱ፣ ዳኛው፣ ሹፌሩ፣ ፓይለቱ፣ ራዳቱ፣ ነጋዴው ምስክር መኾን ያቃተን? ፍላጎቱ ስለሌለን ነውን? አይደለም፡፡ ፍቅሩ ስለሌለን ነውን? አይደለም፡፡ ግን አልሠለጠንም፡፡
“አይ እዚ ጋር እንኳን ቀይ መስመር አለ” ነው ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ፡፡ “እዚህ ድረስ የአባቴን መንግሥት ለመውሰድ መጥቻለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ግን ቀይ መስመር ይሰመራል፡፡” ክርስትና ይኼ ነው የሚፈልገው፤ ከዚህም በላይ፡፡ (ይህን) የሚል ነጋዴ፣ የሚል ባለሥልጣን፣ የሚል ምሁር፣ የሚል ሳይንቲስት ማፍራት የሚቻለው በቤተሰብ ውስጥ በሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡ እኛ ቢያልፈን እንኳን፣ ዛሬ ይህን ጽሑፍ የምናነብ ሰዎች አልፎናል ብለን ብንጸጸት እንኳን ብዙዎቻችን ግን እንዳያልፋቸው ማድረግ አያቅተንም፡፡
ከዛ ነው መጀመር ያለበት፡፡ ሕፃናት ላይ ይበልጥ መሠረታችንን መመሥራት ያለብን፡፡ ሕፃናትን ነው ማነፅ ያለብን፡፡ እነርሱ በሚገባ ከተማሩ ጉባኤያት ባይደረግ እንኳን፣ ማይክሮፎን ባይተከል እንኳን፣ አዳራሾች ባይዘጋጁ እንኳን ምንም ጉዳት የለውም፡፡ ምንም ጉዳት የለውም!!!
እስኪ አስቡት! ሰንበቴው፣ ጽዋው፣ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓቱ፣ የንግሥ ሥነ ሥርዓቱ ባይኖር ኖሮ በእኛ ስንፍና ምንድን ነበር የምንኾነው? የበእንተ ወንጌል ወይም የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ለማዘጋጀት ስንት ጊዜ ነው ማስታወቂያ የሚነገረው? ቁልቢ ገብርኤል ለመሔድ ግን ማስታወቂያ ያስፈልጋል? በነሐሴ 24 የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ንግሥ ለመሔድ ምንም ማስታወቂያ አያስፈልግም፡፡ መስከረም 21 ላይ ግሸን ለመሔድ ምንም ማስታወቂያ አያስፈልግም፡፡ ባይኾን “በዚህ ቦታ ተመዝገቡ” ለማለት ካልኾነ በስተቀር እንጂ ያን ቀን የግሸን በዓል እንደኾነ ኹሉም ያውቃል፡፡ ይህንን መሠረት ባይመሠርቱና በደማችን ውስጥ ባይተከል ኖሮ በየትኛው ኔትወርክ ነበር የምናመጣው? በየትኛው ማስታወቂያ ነበር ሰውን የምንሰበስበው? በየትኛው አሠራራችን ነበር ይህን የምናመጣው? ይህን ከታች ስለሠሩት ነው፡፡
በኢየሩሳሌም ማለት ይኼ ነው፡፡ ቤተሰብ ውስጥ ባልና ሚስት ሐዋርያ ኾነው ሲያስተምሩ ማለት ነው፡፡ እናትና አባት ለልጆቻቸው ሐዋርያ ሲኾኑ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፋቸው ኹለቱም መልእክቶቹ እየደጋገመ የሚናገረው ቃል አለ፡፡ የጢሞቴዎስ አያቱንና እናቱን ያነሣል፡፡ “ይህም እመነት ቀድሞ በኤትህ በሎይድ እናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፤ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቻለሁ” ብሎታል /2ኛ ጢሞ.1፡5/፡፡ ይኼስ ምንድነው የሚነግረን ቅዱስ ጢሞቴዎስ እንዲሁ የመጣ አይደለም፡፡ አያቱም እናቱም ያስተማሩት ትምህርት፣ በሕይወት አርአያ ኾነው ያሳዩት ሕይወት ነው በልቡ ውስጥ ያለው፡፡
ወላጆች መጾም ያለባቸው ለራሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ የሚጾሙ ልጆች ማፍራት ከፈለግን የሚጾሙ ወላጆች መኖር አለባቸው፡፡ ወላጆች ቤት ውስጥ መጸለይ ያለባቸው ለራሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ የሚጸልዩ ልጆች ማፍራት ከፈለግን የሚጸልዩ ወላጆች ማፍራት አለብን፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ልጆቹ አብረው የሚጾሙት፡፡ ከካህኑ በፊት እናትና አባታቸውን ነዋ ያወቁት! ከሰባኪው በፊት እናትና አባታቸውን ነዋ ያወቁት! ስለዚህ እናታቸው ስትጾም ይጾማሉ፡፡
ለምን ይመስላችኋል ብዙ ወጣቶች 14 እና 15 ዓመት ሲሞላቸው በልጅነታቸው በፍልሰታም በምንም ስናቆርባቸው የነበረውን ቁርባን የሚተዉት? ልጆች ኾነው እናመጣቸዋለን፡፡ 15 ዓመት ሲሞላቸው ግን እምቢ ይላሉ፡፡ ለምን? እኛ ስንቆርብ አላዩማ! ስለዚህ የማደግ ምልክቱ የሚመስላቸው ቁርባንን ማቆም ነው፡፡ ሰው ቁርባን ተወ ማለት አደገ ማለት ነው፡፡ ወላጆቻቸው ስላደጉ ነዋ የማይቆርቡት፡፡ እንደዉም በብዙ ቤተ ክርስቲያን “ቅዳሴ ማለት የማይቆርቡ ወላጆች የሚቆርቡ ልጆች የሚያቆርቡበት ነው፡፡” ወላጆች አይቆርቡም፤ ልጆች ግን ይቆርባሉ፡፡ ቅዳሴው ያልተማረ የሚያስተምርበት፤ ያልቆረበ የሚያቆርብበት ብቸኛ ቦታ ነው፡፡ እየቆረብን ቢኾን እነርሱም አብረው ይመጡና ይቆርቡ ነበር፡፡
ይኼ ነው የመጀመሪያው መሔድ ማለት፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ነው መሔድ የሚጀመረው፡፡ ሰው’ኮ ዝም ብሎ ከኾነ ቦታ አይሔድም፡፡ አንድ ሰው ሒድ ቢባል ካለበት ነው የሚነሣው፡፡ መነሻችን ቤተሰብ ስለፈረሰ ነው ትልቁ ችግር፡፡ አሁን መመለስ ያለብን ወደዚህ ነው፡፡ በስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ውስጥ መካተት ያለበት ይኸው ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ የጽዋ ማኅበራት አላችሁ፤ ጉዞ ማኅበራት ውስጥ ያላችሁ አላችሁ፤ ሰንበቴው ውስጥ ያላችሁ አላችሁ፤ በተለያየ ማኅበራት ውስጥ ያላችሁ ሰዎች አላችሁ፡፡ ይህን ጽሑፍ አንብበን ስንጨርስ ማሰብ ያለብን ቤተሰብ ውስጥስ ምን እንሥራ? የሚል መኾን አለበት፡፡ እናት’ኮ ወደ ጉባኤ ትሔዳለች፤ ልጅ ግን አይሔድም፡፡ ባሎች ለብቻ ይሰበሰባሉ፤ ሚስቶች የሉም፡፡ አባቱ “ገብርኤል ነው” ብሎት ሲሔድ ነው እንጂ የሚያውቀው የት እንደሚሔድ አያውቅም፡፡ ለብቻው ነዋ የሔደው፡፡ እነርሱም ቤት ጽዋው ሲደረግ ለምን እየተደረገ እንደኾነ የሚነግረው ሰው የለም፡፡ እንደዉም ብዙ ልጆች ከቤታቸው ውስጥ የጽዋ መርሐ ግብር ሲደረግ፡- “እንግዶች ስለሚመጡ እንዳትበጠብጡ፤ ከዚህ ከመኝታ ቤት እንዳትወጡ፤ ውጭ ከኾናችሁም እንዳትገቡ፤ ድምጻችሁን እንዳታወጡ” ነው የሚባሉት፡፡ ቁጣው ነው የሚተርፋቸው፡፡ ስለዚህ ሌላ ነገር የተፈጠረ ነው የሚመስላቸው፡፡ “ዛሬ ቅዱስ ገብርኤልን ነው የምዘክረው፡፡ ዛሬ ተክለ ሃይማኖት ነው የምዘክረው፡፡ ዛሬ እመቤታችንን የምዘክርበት ምክንያት ይኼ ነው፡፡ አንተም ስታድግ ከእኔ ቀጥለህ ነው የምትሔደው፡፡ እንዲህ ብታደርጊ እንዲህ ነው” ብሎ የሚነግራቸው ሰው የለም፡፡
የብዙዎቹ በአዲስ አበባ ሰንበቴዎች ላይ የተደረገ ጥናት የሚነግረን ይኼ ነው፡፡ ከአጼ ምንሊክ ጀምሮ የተመሠረቱ ሰንበቴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሥላሴ ካቴድራል አጠገብ ያለው የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ሰንበቴ ከ100 ዓመት በላይ ኾኖታል፡፡ እነዚህ ሰንበቴዎች ከፊታቸው የተጋረጠው አደጋ ሰንበቴውን የመሠረቱት ወላጆች ልጆቸ እየተተኩ አይደለም፡፡ በረከታቸው ይደርብንና ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልእ ይህን በተመለከተ ያስተማሩት ትልቁ ትምህርት፡- “ወደ ሰንበቴውና ወደ ጽዋው ጠላውን፣ ዳቦውን፣ ቆሎውን ይዛችሁ ስትሔዱ እናንተ አትያዙት፡፡ ጠላውን አንድ ልጅ፣ ዳቦውን አንድ ልጅ፣ቆሎውን አንድ ልጅ ተሸክሞ ይሒድ፡፡ ይግባ፤ ይይ፡፡ ይኼ የአንተ ሰንበቴ ነው፡፡ ነገ ትወርሷለህ በሉት” የሚል ነው፡፡ ይኼን ያደረገ ሰው ስለሌለ የሚወርሰው ታጣ፡፡  
እኛ እንኳን ማንበብ ባንችል መጻሕፍቱን ገዝተንላቸው እንዲያነቡ የማናደርጋቸው ለምንድነው? በውድ ዋጋ ከፍለን ትምህርት ቤቶች ውስጥ የምናስተምራቸው ይኼንን ጭምር እንዲያነቡ አይደለም እንዴ? ፊዚክስና ኬሚስትሪ ብቻ እንዲያነቡ ነውን? ይኼንንም ጭምር እንዲያነቡ’ኮ ነው፡፡ ቆመው ማንበብ መልመድ አለባቸው፡፡ “ዛሬ አንተ ነህ ተረኛ፤ ዛሬ አንቺ ነሽ ተረኛ” ልንላቸው ይገባል፡፡ ኹለት፣ ሦስት ልጆች ባሉበት ቤት “አንተ የቅዱስ ሚካኤልን ትዘክራለህ፤ አንቺ ደግሞ እመቤታችንን ትዘክሪያለሽ፤ አንተ ደግሞ ተክለ ሃይማኖትን ትዘክራለህ፤ እኔ ደግሞ እገሌን እዘክራለሁ” ብለን ተካፍለን ካደረግን ልጆች ከልጅነታቸው አንሥቶ ፍቅረ ቅዱሳን ያድርባቸዋል፡፡ ይጠይቃሉ፡፡ “ለምንድነው በ24 ተክለ ሃይማኖት የኾነው?” ይላሉ፡፡ ይረዳሉ፡፡ “ለምንድነው ግን የቅዱስ ሚካኤል በዓል በ12 የሚውለው?” ይላሉ፡፡ ይረዳሉ፡፡ ማስረዳት ከቻልን ማስረዳት፡፡ ማስረዳት ካልቻልን ደግሞ “ይኼው መጽሐፉ አንብብ፤ እንደውም አንብብና ለኹላችንም ትነግረናለህ” እያልን ልናሳድጋቸው ይገባል፡፡ ሃይማኖታቸውን መመስከር፣ ስለ ቅዱሳን መናገር፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን መናገር በእናትና በአባታቸው ፊት ይለምዳሉ፡፡ ነገ ትምህርት ቤት ቢሔዱ፣ ሌላ ትልቅ ቦታም ቢሔዱ ስለ ሃይማኖታቸው በየጉባኤው፣ በየወርክሾፑ፣ በየሚድያው የማይኾን ነገር ሲነገራቸው ዝም አይሉም፡፡ “አይ! እዚህ ጋር ሐሳብ አለኝ፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም፡፡ ይኼ ሥርዓት አይደለም፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ አይደለም፡፡ አንተ እንደምትለው አይደለም!” ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ይኾናሉ፡፡
ይኼ ስለጠፋ ነው ዛሬ ብዙ ቦታ ላይ የቤተ ክርስቲያን ስም ሲጠፋ እንኳን እያወቅነው፣ እየተናደድን፣ ፀጉራችንን እየነጨን ዝም የምንለው፡፡ “እንደው እግዚአብሔር ያሳይህ” እያልን እየረገምን ዝም የምንውለው ለዚሁ ነው፡፡
ኢየሩሳሌም ማለት ግን ይኼ ነው፡፡ በምታውቁት ቦታ፣ ስለ እኔ መናገር በማይቸግራችሁ ቦታ ጀምሩ ማለት ነው፡፡ ለሐዋርያት ከይሁዳ፣ ከሰማርያ፣ ከዓለም ዳርቻ ይልቅ በኢየሩሳሌም መመስከር ቀላል ነበር፡፡ ምስክር አለ፤ ማስረጃ አለ፤ ቦታው እዛው ነው፤ ሌላም ብዙ ምስክር መጥራት ይቻላል፡፡ እኛም በቤተሰባችን ውስጥ መመስከር ቀላል ነው፡፡ እንዲህ በአደባባይ ከመውጣታችን በፊት ከቤተሰባችን ውስጥ ነው ሃይማኖት ገንዘብ መደረግ ያለበት፡፡ ጸሎት እዛ ነው መለመድ ያለበት፡፡ ጾም እዛ ነው መለመድ ያለበት፡፡ ምጽዋቱ’ኮ እዛ ነው መለመድ ያለበት፡፡ በየቤታችን ሙዳዬ ምጽዋት አስቀምጠን ልጆች ከጸሎት በኋላ ገንዘብ እያስቀመጡ፥ ያንን የሙዳዬ ምጽዋት ገንዘብ ይዘው ነው እሑድ ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ የሚመጸውቱት፡፡ እንዲህ ከኾነ የሚሰጡ ልጆች እናፈራለን፡፡ እንዲህ ካልኾነ ግን ሙዳዬ ምጽዋትን የሚሰብሩ ልጆችን እናፈራለን፡፡ ከየት ያምጡት ታዲያ? ዛሬ’ኮ “ሙዳዬ ምጽዋት ምንድነው?” ቢባል “ገንዘብ በውስጡ ያለበት፤ ተሰብሮም ያ ገንዘብ የሚወሰድበት፤ እንደዉም ምንዛሪ ያለበት” ነው የሚመስላቸው፡፡ የሚሰጥ ነው የሚለውን እኛ ነን ማስተማር ያለብን፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት ዐቢይ ጾምና ፍልሰታ ላይ ቤተሰብ የማይጠቀሙበትን ልብስ ይሰበስቡና ኪዳነ ምሕረት በዓል ሲኾን ወይም ደግሞ የትንሣኤ በዓል ከመኾኑ በፊት ወስደው ለነዳያን ይሰጡ ነበር፡፡ ልጆቻችን ይህንን ነው በኢየሩሳሌም ማስተማር ያለብን፡፡ እንዲህ የምናደርግ ከኾነ ለሌላው ማዘን፣ ለሌላው መራራት ለምደው ያድጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ልጆች ካፈራን ቤታችን ውስጥ ሳንቲም የሚሰርቅ የሚነካ የለም፤ ቤታችን ውስጥ ርህራሄ ይኖራል፡፡ ይኼ ነው በኢየሩሳሌም የተባለው፡፡ የፈረሰውም ይኼ ነው፡፡
በይሁዳ እንቀጥላለን...    

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...