2013 ኖቬምበር 10, እሑድ


ኢሕአዴግ እና የሃይማኖት ነጻነት

FACT Magazine Cover 02(ፋክት መጽሔት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፲፱ ጥቅምት ፳፻፮ ዓ.ም.)
ተመስገን ደሳለኝ
… ኢሠፓ መራሹ መንግሥት በኢሕአዴግ ከተተካ ጥቂት ወራት ቢያልፈውም፣ የተራዘመው የእርስ በርስ ጦርነት ያልደረሰባቸው በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞችን ገና በቅጡ አልተቆጣጠራቸውም፤ በአናቱም በኢሠፓ መንግሥት ሽንፈት ሳቢያ እንዲበተን ከተገደደው የአገሪቱ መደበኛ ወታደር አብዛኛው ከእነትጥቁ የትውልድ መንደሩንና ቤተሰቡን መቀላቀሉ በአገሪቱ ላይ ከባድ ፍርሃት አንብሯል፡፡ በሰላም ወጥቶ ለመመለስ ርግጠኛ መኾን የማይቻልበት ከባቢያዊ አየርም አስፍኗል፡፡ በበርካታ ቦታዎች ተጠንተውና ታቅደው የሚፈጸሙ ወንጀሎችም ከአምስት እስከ ዐሥራ አምስት በሚደርሱ ወታደሮች የተደራጁ ልዩ ልዩ ሕገ ወጥ ቡድኖች በየማዕዘኑ እያቆጠቆጡ መኾኑን አመላክትዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የዐዲስ አበባ ቆዳ ስፋትና የነዋሮዎቿ የአኗኗር ዘይቤን በቀላሉ ለመልመድ የተቸገሩ ተጋዳላዮች ለትንሽ ለትልቁ ግርግር ጠመንጃን እንደ መፍትሔ መምረጣቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡ ጉዳዩ እያሳሰባቸው የሄደው የኢሕአዴግ ዋነኛ መሪዎችም እንዲህ ዐይነቱን አለመረጋጋትና ሥርዐተ አልበኝነት ለመቆጣጠር የመንፈሳዊ መሪዎች አስተዋፅኦ ወሳኝ ስለ መኾኑ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል(እንደ ቀደሙት ሥርዐቶች ኹሉ ለቅቡልነት ከሚጠቀሙበት በተጨማሪ ማለት ነው)፡፡ ይኹንና በመንበሩ ላይ የነበሩት ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ አገር ለቀው እንዲወጡ በመደረጉ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡
ይህ ጊዜ ነው ከ፲፱፻፸፬ ዓ.ም. ጀምሮ [ከኢየሩሳሌም ተሰደው] መኖርያቸውን አሜሪካን አገር ያደረጉ አንድ መንፈሳዊ አባት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የተወሰነው፤ በጥሪው መሠረትም ወደ አገራቸው ሲገቡ መንግሥት የክብር አቀባበል አደረገላቸው፡፡ እኚኽ አባት ዛሬ በመንበረ ፕትርክናው የተሠየሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ነበሩ፡፡ ኾኖም ከሳምንት ሽር ጉድ በኋላ አቡነ ‹‹የኢዲዩ አባል ነበሩ›› የሚል ወሬ በአመራሩ አካባቢ በስፋት መሰራጨቱ ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ አስከተለ፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ኢሕአዴግ እና ኢዲዩ በ፲፱፻፸ዎቹ መጀመርያ ትግራይ እና ጎንደር ውስጥ በርካታ መሥዋዕትነት ያስከፈለ ውጊያ ማድረጋቸው ብቻ አልነበረም፡፡ የመጀመርያዎቹ ሊቀ መንበሮች ስሁል ገሰሰ እና መሐሪ ተኽሌ(ሙሴ) ‹‹የተገደሉት በኢዲዩ ነው›› የሚለው ወሬ በድርጅቱ ውስጥ ከጫፍ ጫፍ የተናኘና የታመነበት ጉዳይ መኾኑ ነበር፡፡ በዚህም ላይ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ግራ ዘመምነት ተደማምሮ አቡነ ማትያስ በወቅቱ ወደ ታሪክነት ከተቀየረ ዓመታትን ባስቆጠረው ኢዲዩ ተፈርጀው ከታጩበት የፕትርክና መንበር ተገፈተሩ፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር አብላጫውን የትጥቅ ትግል ዘመን በአሜሪካ ያሳለፉት አሰፋ ማሞ እና ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ‹‹ዉድብ›› የሰጠቻቸውን ተልእኮ ተቀብለው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያመሩት፤ እናም ቀድሞም ትውውቅ ወደነበራቸው ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ዘንድ ሄደው ለፕትርክና ወንበር መታጨታቸውን አበሠሯቸው፡፡ በእንዲህ ያለ መንገድ መንግሥት የቀባቸው አቡነ ጳውሎስም እስከ ኅልፈታቸው ድረስ አወዛጋቢ መሪ ኾነው ዘልቀዋል፡፡
(በነገራችን ላይ በአሜሪካ ለመጀመርያ ጊዜ ከሲኖዶሱ ተነጥሎ የቆመ ቤተ ክርስቲያን የመሠረቱት አቡነ ጳውሎስ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ አቡኑ ደርግ ለጥቂት ዓመታት አስሮ ከለቀቃቸው በኋላ ወደ አሜሪካ ሄደው የፈጣሪያቸውን ሰማያዊ መንግሥት ሲሰብኩ ቆይተው የህወሓት ሠራዊት ክንዱ እየበረታ በቁጥጥሩ ሥር ያዋላቸው ከተሞችም እየበዙ ሲሄዱ እርሳቸውም ስብከታቸውን ወደ ትግርኛ ቋንቋ ከመቀየራቸውም በላይ ለ‹ነጻ አውጭ›ው ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ያሰባስቡ ጀመር፡፡ የሥርዐት ለውጥ መደረጉን ተከትሎም በፖሊቲከኞች በተቀነባበረ ሤራ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ቦታ የተለዋወጡት አቡነ መርቆሬዎስም፣ እዚያው አሜሪካ ‹ተተኪ›ያቸው የጀመሩትን ብሔር ተኮርና ከሲኖዶሱ የተገነጠለ ቤተ ክርስቲያን አስፋፍተው ዛሬ ለደረሰበት ‹የጎንደሬ ማርያም›፣ ‹የትግሬ ገብርኤል›. . .ለተሰኘ አሳፋሪ ክፍፍል ዳርገውታል፡፡ በርግጥ ለአቡኑ[አቡነ መርቆሬዎስ] ከአገር መውጣት የኢሕአዴግ እጅ እንዳለበት እንድናምን የሚያስገድደን በቅርቡ ታምራት ላይኔ ‹‹በእኔ ፊርማ ነው ያባረርናቸው›› ማለቱን ዊኪሊክስ ካደረሰን መረጃ በተጨማሪ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ህወሓት በተቆጣጠራቸው በትግራይና ወሎ ነጻ መሬቶች በሚገኙ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎችን ቀስቅሶና አደራጅቶ ፓትርያርኩ ላይ ‹‹ሽጉጥ ታጣቂ ጳጳስ››፣ ‹‹ቀይ ደብተር ያለው/ለኢሠፓ አባላት የሚሰጥ/ የሸንጎ ተወካይ››. . .የመሳሰሉትን መፈክሮች እያሰሙ በተቃውሞ ሰልፍ እንዲያወግዟቸው ማስተባበሩን ስናስታውስ ነው)፡፡
ዛሬስ የሃይማኖት ነጻነት የት ድረስ ነው?
ከላይ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብዬ በደምሳሳው ለመጠቃቀስ እንደሞከርኹት፣ ኢሕአዴግ በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ጣልቃ ማስገባት የጀመረው ክንዱ ሳይፈረጥም ገና በረሓ ላይ ሳለ ነበር፡፡ በዚህ ኹኔታ የተጀመረው ጣልቃ ገብነት ዛሬም ድረስ ተባብሶ ቀጥሏል፤ ምንም እንኳ በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባ በደፈናው ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፲፩ን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ለማስተባበል ቢሞክርም ያለፉት ዓመታት ተጨባጭ ተግባሮቹ የሚመሰክሩት ግልባጩን ነው፡፡ ድርጅቱ ራሱም ቢኾን ጥያቄው በተነሣ ቁጥር ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፲፩ን የሚጠቅሰው ለስሙ እንጂ ሕጉ ተግባራዊ አለመኾኑን ሳይረዳ ቀርቶ አይደለም፤ አቶ ተፈራ ዋልዋም በ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ኅዳር/ታኅሣሥ ወር ከታተመችው ሐመር መጽሔት ጋራ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ጉዳዩን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት የኢሕአዴግን አጭበርባሪነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡-
‹‹ኢሕአዴግ እኮ የሚመራው መንግሥት በደርግም ጊዜ፣ በኃይለ ሥላሴም ጊዜ እንደሚታወቀው ‹የቤተ ክርስቲያን ሥራ አስኪያጅ ሹምልን› ተብሎ ተጠይቆ ‹የለም ራስዋ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትሾማለች እንጂ እንደ ቀድሞው መንግሥት አይሾምላችኁም› የሚል መልስ የሰጠ መንግሥት ነው፡፡››
በሕዝበ ሙስሊሙ ተመርጦ ለእስር የተዳረጉት የኮሚቴ አባላትም በአንድ ወቅት ለሚመለከተው የመንግሥት ባለሥልጣን የጻፉት ደብዳቤ ጣልቃ ገብነቱን በግልጽ ያሳያል፡-
‹‹መንግሥት እንደ መንግሥት ሕዝቡ ተበድዬአለኹ፤ ምርጫ ይካሔድ፤ የመጅሊሱን አመራር አላመንኹበትም፤ ውክልና የለውምና ሕገ ወጥ ነው ያለውን አካል ሕገ ወጥነቱ እንዲረዝም ምርጫውን እርሱው እንዲያካሒድ መወሰን ሕዝብን ግራ አጋቢ ነው፡፡››
ሥርዐቱ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ለማሳመን ይህን ያህል ቢዳክርም በቅርቡ ‹‹የፀረ አክራሪነት ትግል የወቅቱ ኹኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች›› በሚል ርእስ የተዘጋጀው ባለ 44 ገጽ ሰነድ፣ መንግሥት በዘወርዋራ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ሙሉ በሙሉ የሚያምን ኾኖ አግኝቸዋለኹ፤
‹‹የመንግሥት መዋቅራትን ሴኩላር መንግሥት መኾናችንን ዐውቆ የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ የራሱን ሃይማኖት መሠረት ያደረገ አገልግሎት ከመስጠት ሙሉ በሙሉ ያልጸዳ መኾኑን የተለያዩ ጥቂት የማይባሉ ገሃድ የወጡ መገለጫዎች አሉ፡፡ እንዲያውም የትኛውም አክራሪ ኃይል ከመዋቅር(ከመንግሥት) አካል በርታ ሳይባልና ሽፋን ሳይሰጠው የሚንቀሳቀስ እንደሌለ አማኞቹ በገሃድ ይገልጻሉ፡፡››
መቼም ይህን ያነበበ ዜጋ መረጃው የተገኘው በመንግሥት ከተዘጋጀ ሰነድ ሳይኾን በኒዮሊበራሊስት›ነት ከተፈረጁት እነ‹‹ሂዩማን ራይትስዎች›› እና ‹‹አምንስቲ ኢንተርናሽናል›› ቢመስለው አይደንቅም፡፡ ሐቁ ግን ይኸው ነው፡፡ አገዛዙ ላለፉት ኻያ ሁለት ዓመታት መንግሥት እና ሃይማኖት እንዲለያዩ ማድረጉን ሲለፍፍ ከመቆየቱም በላይ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን የዘገቡ ጋዜጠኞችን ከሥሦ ዛሬም ድረስ ፍርድ ቤት እያመላለሳቸው እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ይመስለኛል ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ የሚገኙት የእነ አቡበበከር መሐመድ ክሥ፣ የሼኽ ኑር ሑሴን ግድያ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ውንጀላዎችንና መሰል ፍረጃዎችን አምኖ ለመቀበል የተቸገሩት፡፡
ያም ኾነ ይህ ሃይማኖትን ብቻ ሳይኾን ዕድርና ዕቁብንም ሳይቀር ‹ካልተቆጣጠርኹ ሞቼ እገኛለኹ› በሚል የቁጥጥር ልክፍት የተያዘው ኢሕአዴግ፣ በተለይም 99.6 ድምፅ አግኝቼ አሸንፌአለኹ ብሎ ካወጀበት ከምርጫ ፳፻፪ ማግሥት ጀምሮ ‹‹አናት ላይ ከተቀመጡ መሪዎቻቸው በቀር ሙሉ በሙሉ አልተቆጣጠርናቸውም›› የሚላቸውን የኦርቶዶክስ ክርስትና እና የእስልምና እምነቶችን ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ እየሠራ ለመኾኑ በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡
በ፳፻፫ ዓ.ም. ኅዳር ወር ‹‹የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና የኢትዮጵያ ሕዳሴ›› በሚል ርእስ በአቶ መለስ ዜናዊ ተሰናድቶ የተሰራጨው ጥራዝ፣ የሥርዐቱን ቀጣይ አካሔድና ይህን ኹናቴ የሚያሳይ ከመኾኑም በተጨማሪ ዛሬም ድረስ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ መንግሥት የሚያዘጋጃቸው ሥልጠናዎችም ኾኑ ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻ ሐሳባቸው ይኸው ዳጎስ ያለ ጥራዝ እንደኾነ ይነገራል፡፡
ጥራዙ የእምነት ተቋማትን በተመለከተ ከገጽ 128 – 132 ያካተተው ሐሳብ፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛው ምክንያት ‹‹የሃይማኖት አክራሪነት›› መኾኑን ከጠቃቀሰ በኋላ ችግሩን ‹‹ተኪ የኾነ ልማታዊ አስተሳሰብ›› በማምጣት ማስወገድ እንደሚቻል ይመክራል፡፡ ይህን ከግብ ለማድረስ ደግሞ ሚዲያዎችንና ተያያዥነት ያላቸውን ማኅበራት መጠቀሙ አዋጭ እንደኾነ ይተነትናል፡፡ የኢሕአዴግ አባላት በየእምነት ተቋሞቻቸው ያሉ ማኅበራትን በዐይነ ቁራኛ መከታተል እንዳለባቸውም ያሳስባል፡- ‹‹[የግንባሩ አባላት] ከእምነት ተቋማት ውጭ ባላቸው አደረጃጀት አማካይነት በሰፊው መሥራት አለብን››፡፡ በርግጥም የእስልምና እምነት ተከታዮች ‹‹የሃይማኖት ነጻነት ይከበር›› የሚል ተቃውሟቸውን ባጠናከሩበት ሰሞን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሙስሊም አባላቱን ለብቻ እየሰበሰበ እንቅስቃሴውን የማክሸፍ ሥራ መሥራት ግዴታቸው መኾኑን የሰበከው ከዚኹ አቶ መለስ ዜናዊ አዘጋጅተውት ከነበረው ጥራዝ ነው ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡
ከጣልቃ ገብነት ወደ ጠቅላይ ተቆጣጣሪነት
በዘወርዋራም ቢኾን በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ሙሉ በሙሉ የሚያምነው ከላይ የተጠቀሰው ሰነድ በአገሪቱ ‹‹የሃይማኖት አክራሪነት›› መከሠቱን ካተተ በኋላ ዋነኛ ተጠያቂዎች አድርጎ ያቀረበው እንደወትሮው ኹሉ ለተደጋጋሚ መሸማቀቅ የተዳረጉትን መንፈሳዊ መሪዎችንና ማኅበራትን ሳይኾን የመንግሥት መዋቅርን ነው፡-
‹‹የመንግሥት መዋቅራችን አካል ኾነው አክራሪነቱን በድብቅም በገሃድም የሚደግፍ አካል በፌዴራልም በክልልም ከሞላ ጎደል የሚታወቁ ናቸው፡፡ እነዚኹ አካላት በተቻላቸው ኹሉ በመድረክ ጤናማ እየመሰሉ የሚኖሩ ናቸው፡፡ የፀረ አክራሪነቱን ትግል ማጧጧፍ የሚፈልገውን መዋቅር አካልም ይኹን የሕዝብ አካል በተደራጀና በመረባቸው አማካይነት ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩ፣ የተቋማቸውን ምቹ ኹኔታ ተጠቅመው በፀረ አክራሪነት የሚንቀሳቀሱትን አካል የሚቀጡ፣ አሉባልታ እየፈጠሩ የሚያሸማቅቁ፣ ኾን ብለው ድጋፍ የሚነፍጉና በሐሰት ምስክርም ጭምር ዜጎችን የሚያሳስሩ ናቸው፡፡ የመንግሥትን አቅሞች ተጠቅመው አክራሪነትን የሚያስፋፉና ከአክራሪነት እንቅስቃሴ ጋራ በተለያዩ ጥቅሞች የተሳሰሩ ናቸው፡፡››
እነኾም በእንዲህ ዐይነቱ የውንብድና ተግባር የተሠማሩ ባለሥልጣናት የተሰባሰቡበት፣ ውንብድናው መኖሩንም የሚያምን መንግሥት አንድም ተጠያቂዎቹን ለሕግ አሳልፎ አለመስጠቱ፣ አልያም ሥልጣኑን በፈቃዱ አለመልቀቁ በአገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመረዳት ነቢይነትን አይጠይቅም፡፡ በአናቱም ሥርዐቱ ለሕግ የበላይነት ተገዥ አለመኾኑን የሚያሳየው በዚህ ደረጃ ‹‹ችግሩን ተረድቸዋለኹ›› እያለም እንኳ፣ ዛሬም የቅጣት ብትሩን ያሳረፈው ከመዋቅሩ ጋራ አንዳችም ንክኪ በሌላቸው መንፈሳዊ መሪዎች ላይ መኾኑ ነው፡፡ በርግጥም ይህ ዐይነቱ አሠራር ከዐምባገነን አስተዳደር መገለጫዎች አንዱ ነው፡፡ ኢሕአዴግም ያለፉትን አራት ምርጫዎች ጨምሮ በተለያየ ጊዜ የዴሞክራሲም ኾነ የሰብአዊ መብትን በዐደባባይ መጣስ፣ የሐሰት ክሦችንና ፍረጃዎችን እንደ ምክንያት መጠቀም ነባር ስልቱ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እየዘረዘረ ያለው የፈጠራ ውንጀላ እና ለሙስሊሙ ‹‹መፍትሔ አፈላላጊ›› ተብለው በተመረጡት የኮሚቴ አባላት ላይ የወሰደው ዕመቃ መግፍኤ ይኸው ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ከዚህ ቀደም በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ስለሚፈጸመው የግፍ ግድያዎች ይሰጥ የነበረውን ምክንያት በመንፈሳዊ ሰዎችም ላይ ያለአንዳች የይዘት ለውጥ ለመጠቀም አላመነታም፡፡ እንደሚታወሰው በድኅረ ምርጫ – ፺፯ በአምቦና በኢተያ በታጣቂዎች የተገደሉትን የኦሕኮ አባላት ከተፈጥሮ ሕመም ጋራ አያይዞት ነበር፡፡ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ በተካሔደው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ደግሞ የምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኄኖክ ‹‹ቤጊ›› ወረዳ በመንግሥት ባለሥልጣናት ተፈጸመ ያሉትን ግድያ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ተወካይ፡-
‹‹በቤተ ክርስቲያን 70 ሜትር ርቀት ላይ የሌላ እምነት ተከታዮች የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ መፈቀዱን ከተቃወሙት መካከል አንድ ዲያቆን ተደብድቦ በሦስተኛው ቀን ሕይወቱ ሲያልፍ ‹በወባ በሽታ ነው የሞተው› ተብሎ ለፍርድ ቤቱ የሐሰት ማስረጃ ከዶክተሩ እንዲቀርብ ታዘዘ›› ማለታቸውን መጥቀሱ ለጉዳዩ አስረጅነት በቂ ይመስለኛል፡፡
የኾነው ኾኖ አገዛዙ በዘረጋው ግዙፍ መዋቅሩ ውስጥ ያልታቀፉ ማኅበራትንም ኾነ የሃይማኖት ተቋማትን የስጋት ምንጭ አድርጎ ማየቱ፣ በእምነት ነጻነት ላይ ጣልቃ ለመግባትም ኾነ ምንም ዐይነት ገለልተኛ ተቋማት እንዳይኖሩ ዕንቅልፍ ዐጥቶ መሥራቱን ያሳያል ብዬ አስባለኹ፤ በሚቆጣጠራቸው የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት ሚዲያዎች ቀን ከሌት የፕሮፓጋንዳ ከበሮ የሚመታበት የ‹አክራሪነት› ፍረጃም መነሾው ይኸው ይመስለኛል፡፡ ሰነዱን ከዚህ ቀደም ካየናቸው ለየት የሚያደርገው፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ አሉ ከሚላቸው ወንበዴዎች በተጨማሪ የሚከሥሣቸውን መንፈሳውያን ማኅበራት በደፈናው ‹‹በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉ›› ብሎ አለማለፉ ነው፤ ቃል በቃል እንዲህ ይላልና፡-
‹‹በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ የመሸጉ የትምክህት ኃይሎች ጽንፈኛ የፖሊቲካ ኃይሎች አካል በመኾን በጋዜጣና በመጽሔት ሕዝባችንን ለዐመፅና ለሁከት ለማነሣሣት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡. . .በራሳችንም ኃይል እንደሌላው ሰልፍ ልንወጣ ይገባል በሚል የዐመፅና የሁከት ቅስቀሳ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡››
ይህ ኹኔታ መንግሥት መንፈሳውያን ማኅበራትን ጠቅልሎ ለመቆጣጠር በመፈለጉ ለተቃዋሚዎች ያሠመረውን ‹ቀይ መሥመር› መጣሱን ያሳያል፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትን የፖሊቲካ መሣርያ አድርጎ መጠቀሙ አልበቃ ብሎት ወደ መንፈሳውያን ማኅበራቱ መዞሩ ነው፡፡
በገሃድ እንደሚታወቀው የክርስትና ይኹን የእስልምና እምነት መሪዎች በተለያየ ጊዜ ከሥርዐቱ ጎን ተሰልፈው ‹ናዳን ለመግታት› ያደረጉት አበርክቶ በቀላሉ የሚገመት አለመኾኑ ነው፡፡ በርግጥም ‹‹የቄሣርን ለቄሣር›› በሚል አስተምህሮ የሚያድሩ፣ ደመወዛቸው በምድር ያልኾኑት መንፈሳውያን አባቶች በድኅረ ምርጫ – ፺፯ ሕፃናትን ሳይቀር በጥይት የፈጀውን ሥርዐት ማውገዝ ቀርቶ መምከር ያለመፈለጋቸው ምክንያት ፍርሃት ብቻ ሳይኾን የግል ጥቅምን ታሳቢ ያደረገው ግንኙነታቸው ያሳደረው ተጽዕኖ ይመስለኛል፡፡ ከቅዱሳን መጻሕፍት ይልቅ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ‹አዳኝ› አድርገው የመቀበላቸው መግፍኤ ይኸው ነው፡፡ ኢሕአዴግም ‹ነገረ መለኰት›ን ለሲኖዶሱና ለመጅሊሱ እስከ ማስተማር ድረስ የደፈረው የእነርሱ ለሁለት ጌታ መገዛት ነው – ለገንዘብ እና ለጌታ፡፡
የሲኖዶሱ እና የመንግሥት ፍጥጫ
በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ከፍተኛውን ሥልጣን የሚይዝ ሲኾን ፓትርያርክንም የመሾምና የመሻር ሥልጣን አለው፡፡ ኾኖም ይህ የላዕላይ መዋቅር እስከ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት ድረስ ለእርሳቸውም ኾነ ለሥርዐቱ ሰጥ ለጥ ብሎ የሚገዛ ጥርስ የሌለው አንበሳ በመኾኑ ለትችት ከመዳረጉም በላይ በምእመናን ዘንድ ለመንፈሳውያን አባቶች የሚሰጠው ክብርም ተነስቶት ቆይቷል፡፡
ይኹንና በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመርያ በተካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ፴፪ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከመንግሥት የተወከሉ ሓላፊዎች÷ ‹‹የብዝኃነት አያያዝ አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎቹና መፍትሔዎቹ›› በሚል ርእስ ያቀረቡትን ጥናት ተከትሎ ስድስት ጳጳሳት ቀድሞ ባልታየ መልኩ ጠንካራ ተቃውሞ ማቅረባቸው፣ በብዙዎች ዘንድ የሃይማኖት መሪዎች ለመንፈስ ልዕልና ሊገዙ ይኾን? ከምድራዊው ይልቅ ሰማያዊውን ሊመርጡ ይኾን? ‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› የሚለውን አስተምህሮአቸውን ሊተገብሩ ይኾን? የሚል ጥያቄ አጭሯል፡፡
በዕለቱ የመጀመርያው ተናጋሪ የነበሩት የሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በጥናቱ ላይ መቻቻል አስመልክቶ የቀረበውን ድምዳሜ እንዲህ ሲሉ ነበር ያጣጣሉት፡-
‹‹ይኼ አክራሪነት፣ ጽንፈኝነት የሚለውን ቋንቋ እናንተው ናችኹ ያሰማችኹን፤ ከዚህ በፊትም አይታወቅም፣ በደርግም ይኹን በሌላ፡፡ እንደገና ደግሞ ብዙ ጊዜ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት እያላችኹ ዕድሜ ሰጥታችኹ ያበለጸጋችኋቸው እናንተው ናችኹ፡፡››
በርግጥም አቡኑ የተቹት ሥርዐቱ የፕሮፓጋንዳው ፋሽን ያደረገውን ‹‹መቻቻል››ን ብቻ አይደለም፤ ‹‹በመቃብሬ ላይ ነው የሚሻሻለው›› የሚለውን የመሬት ፖሊሲንም ነው፡፡. . . ‹‹በፊት መሬትም ሕዝብም የነገሥታቱ ነበር፤ አሁንስ የማን ነው? ይልቁንም ከአንድ ቤት ‹ግድግዳው የቤቱ ባለቤት ነው፤ ሳሎኑ የመንግሥት ነው› የሚለው ዐዋጅ የአሁን አይደለም እንዴ? ለኢትዮጵያዊነቱ ዋስትና የለውም፤ ይኼ የእኔ ነው የሚለው ከሌለ ምንድን ነው? ይህች የእኔ የኢትዮጵያዊነቴ መገለጫ ናት ካላለ ምንድን ነው ኢትዮጵያዊነት? አሁንም መሬቱም ሕዝቡም የእናንተው ኹኖ ሳለ ለፊቱ፣ ለነገሥታቱ መስጠታችኹ በምን ተመልክተውት ነው?››
የደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እንድርያስም በሚያስተዳድሩት አካባቢ ያለውን የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖን ከዘረዘሩ በኋላ ለተሰነዘረው ፍረጃና ማሸማቀቂያ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡-
‹‹የተበደለ ሰው ሲናገር ‹ፖሊቲካ ተናገረ› እየተባለ የውሸት ውሸት ሲያተራምሱን የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡. . .እንዴ! የመንግሥት ሥልጣን የተረከቡ ወንድሞች የእኛን አፍ፣ የእኛን አንደበት ብቻ ነው እንዴ የሚጠብቁት፤ ለሌሎች ሞራል ይሰጣሉ ማለት ነው?. . .ለምንድን ነው ግን በሽፋንነት የምትጠቀሙብን? መንግሥት እኛን ሽፋን አድርጎ ነው ሲበዘብዘን የምንኖረው፡፡ ሌባውም ቀጣፊውም ሰርጎ ገቡም ሲያጭበረብረን ሲያታኩሰን መንግሥትን ሽፋን አድርጎ ነው፡፡››
የወላይታ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅም በተመሳሳይ መልኩ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ቤተ ክርስቲያኗ ስትቃወም ጉዳዩን ወደ ፖሊቲካ እየቀየሩ ማስፈራራቱ እንደተለመደና ለቀብር ማስፈጸሚያ የሚኾን መሬት ከመስተዳድሩ በሚጠየቅበት ጊዜ የሚሰጠው መልስ በሐሰት መወንጀል እንደኾነ ከገለጹ በኋላ ጉዳዩ መፍትሔ ካላገኘ ሊከተል ስለሚችለው ስጋታቸውን ተናግረዋል፡-
‹‹ ‹የፖሊቲካ ጉዳይ ነው፤ ሕዝብን በሃይማኖት ሽፋን ታንቀሳቅሳላችኹ› እየተባልን እየተሸማቀቅን ያለንበት ኹኔታ ነው ያለው፡፡ ይህን እንዴት ታዩታላችኹ? መቻቻልስ የሚመጣው ከምን አኳያ ነው? ዝም ብለን የምንቀመጥ ከኾነ ምናልባት ሓላፊነት ለመውሰድ ስለሚከብደን ይህን ወርዳችኹ እንድትፈትሹ ለማለት ነው፡፡››
(በነገራችን ላይ የአጠቃላይ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ በተጠናቀቀ ማግሥት ከማኅበረ ቅዱሳን አመራር ሦስት አባላት ወደ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተጠርተው ዶ/ር ሽፈራውን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ሓላፊዎች ጋራ ውይይት ማድረጋቸውን ከመሥሪያ ቤቱ ምንጮቼ ሰምቻለኹ፡፡ ሚኒስትሩ ከማኅበሩ አመራሮች ጋራ ለመወያየት የተገደዱት ካልተጠበቀው የሲኖዶሱ አባላት ድፍረት ጀርባ ‹የማኅበረ ቅዱሳን እጅ አለበት› የሚል ጥርጣሬ በመያዙ ነው፡፡ በውይይቱም ላይ የተንጸባረቀው የአባላቱ መለሳለስ፣ ማኅበሩን አክራሪ ብለው እንደማያምኑና ከዚህ ቀደም የተሰራጩት ወንጃይ ሰነዶችን ሳይቀር ‹አናውቃቸውም› እስከማለት የደረሰ እንደነበር አረጋግጫለኹ፡፡ ይኹንና ይህ እሳት ማጥፊያ ስልት ከሥርዐቱ ጋራ የቆየ መኾኑ ይታወቃል፤ የማኅበሩ አመራርም ይህ ይጠፋዋል ብዬ ባላስብም፤. . .)
የኾነው ኾኖ [በአጠቃላይ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ] ከፌዴራል ጉዳዮች ከመጡት ሦስት ተወካዮች መካከል አቶ ገዛኽኝ ጥላሁን አብዛኛውን ጥያቄ በተመለከተ የሰጡት ምላሽ የወከሉት መንግሥት ዛሬም በተሳሳተ ታሪክ ንባብ እያሸማቀቀ፣ እያስፈራራ፣ ሕግን እየጠመዘዘ፣ እስር ቤት እየከተተ. . . የፖሊቲካ ጥቅሙን ማስከበር ላይ ያተኮረ መኾኑን ያሳያል፡፡ ሓላፊው ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፉት እንዲህ በማለት ነው፡-
‹‹መጀመርያ ግንዛቤ ላይ እንሥራ በሚል ርምጃ አልወሰድንም፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር ወደ ቃሊቲ መፍትሔ አይኾንም፡፡››
. . .‹ቃሊቲ›ን ምን አመጣው? መቼም ለጣልቃ ገብነቱ ከዚህ የበለጠ ማሳያ መፈለግ ‹ዐውቆ የተኛን. . .› እንደመኾን ነው፡፡ ‹‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› ብሎ መከራከሩም ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ ይመስለኛል፡፡ እናም የተሻለው መንገድ ከላይ በጠቀስኹት ሰነድ ‹‹በየማእከላዊ ኮሚቴው በሚካሄደው የስምሪት ተግባር በፀረ አክራሪነት ትግል ላይ ያለው የእያንዳንዱ ግለሰብ ቁመና መፈተሽ አለበት›› ተብሎ የተገለጸውን ማሳሰቢያ በፍጥነት በመተግበር፣ በቅድሚያ ራስን ከአክራሪነትና አሸባሪነት ማራቅ ነው፡፡ ማረጋገጫ የማይቀርብበትን አፈ ታሪክንም እየለቃቀሙ በአንድ ሃይማኖት ላይ መለጠፉ አስተማሪ አይመስለኝም፡፡
ከዚህ ባለፈ ‹‹የሃይማኖት ኮማንድ ፖስት አቋቁመን ለችግሩ እልባት እንሰጣለን›› የምትሉት ጉዳይ በቀጥታ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ማስገባቱን በዐደባባይ ከማመን ያለፈ የፖሊቲካ ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ጳጳሳቱም ኾኑ ሼኾቹ ሓላፊነትና ግዴታቸው ሰማያዊውን መንግሥት መስበክ እንጂ ከሰላይ አለቆችና ከፖሊስ አዛዦች ጋራ ቢሮ ዘግተው የመንፈስ ልጆቻቸውን ‹‹ትምክህተኛ››፣ ‹‹አሸባሪ››፣ ‹‹አክራሪ››. . .እያሉ እንዲፈርጁ መፈታተኑ ያልታሰበ ሕዝባዊ ቁጣ መቀስቀሱ አይቀርም፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...