2015 ኤፕሪል 25, ቅዳሜ

ቀጣይ ሥራዎች ምን ሊሆን እንደሚገባ ብንወያይ


   
30 ኢትዮጵያውያን በሊብያ  ሰማእትነትን  ተቀበሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አዘነ . አለቀሰ ዓለም በሙሉ የሃዘን መግለጫ ሰጠ በጣም ግሩም ነው ፡፡ ነገር ግን ቀጣዩ ሥራችን የሚሆነው ምንድነው ?
ቅዱስ  ሲኖዶስ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን  በሚፈቅደው  መልኩ የሚወሰነውን  ውሳኔ ለዓለም እንደሚያሳውቁ ቅዱስ ፓትርያርኩ ባለፈው ገልጠዋል  ይሁን እንጂ
v  .     የተሰውትን 30 ኢትዮጵያውያንን  ሙሉ መረጃ  አሰባስቦ  ለቅዱስ  ሲኖዶስ ማቅረብ  የሚችል ጊዜያዊ  ኮሚት  ቤተክርስቲያናችን ማቋቋም ብትችልና ኮሚቴው መረጃዎችን አጠናክሮ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው  ቢያቀርብየሰማእታቱ  ፎቶ ሌሎችም መረጃዎች  በዚያ መቀመጥ ቢችል ደብሩ ወደፊትም በተመሳሳይ መልኩ ሰማእትነት ለተቀበሉት ኢትዮጵያን ብቻ ቢሆን /አውደ ሰማእታት ቢሆን/
v  አሁን በሊብያ በሕይወት ያሉትን በመርዳት ያሉበትን ሁኔታ በመከታተል የሚያስፈልገውን ሁሉ ከሚመለከተው ጋር ሆኖ የመርዳቱንም ነገር ቢታሰብበት
በአጠቃላይ ቤተክርስቲያቲ ለምትወስነው ቀጣይ ሥራዎች ግብአት ይሆን ዘንድ   ሀሳብ ቢሰጥ!!



















2015 ኤፕሪል 24, ዓርብ

ማኅበረ ቅዱሳን በሊቢያ የተሰዉ ሰማዕታት ቤተሰቦችን በማጽናናት ላይ ይገኛል


አትምኢሜይል
ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም.
002lekso001lekso003lekso004lekso
በሰሜን ሊቢያ ሜድትራንያን ባሕር ዳርቻ በእምነታቸው ምክንያት በግፍ ከተገደሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሚገኙ የሰማዕታት ወላጆች ጋር የማኅበረ ቅዱሳን አመራርና አባላት ሐዘናቸውን እየተካፈሉ ነው፡፡
መርሐ ግብሩ በማኅበሩ መዘምራን ሰማዕታቱን የሚያስብ መዝሙር የቀረበ ሲሆን፤ መዝሙር 118፡ 129 ላይ €œምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፣ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው€ በሚል ርእስ ሰባኬ ወንጌል ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ጸሎተ ምሕላ የተካሄደ ሲሆን ከሰማዕታቱ በረከት ለመሳተፍ የእራት ማብላት ሥነ ሥርዓት በማኅበሩ አስተባባሪነት በቦታው ተካሔዷል፡፡

ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው አይ ኤስ አሸባሪ ቡድን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደላቸው ኢትዮጵያውያን መካከል እስከ አሁን አምስቱ የቂርቆስ አካባቢ ክርስቲያኖች ሆነው ተገኘተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተሰጠ መግለጫ



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን
‹‹ርትዕት ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ናት››
Addis Ababa sunday school students02
የአ/አ ገዳማትና አድባራት ሰንበት ት/ቤቶች በዛሬው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የጸሎተ ፍትሐት ሥነ ሥርዐት
ራሱን እስላማዊ መንግሥት (አይ ኤስ አይ ኤስ) እያለ የሚጠራው የጨካኝ አረመኔዎች ስብስብ፣ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ላይ ያካሔደው ዘግናኝ ግድያ ሳይበቃው ይህን እኩይ ድርጊቱን በልዩ ልዩ ምክንያት ከአገር ተሰድደው በሊቢያ በነበሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ላይ ፈጽሟል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ‹‹ሃይማኖቱን ገልጦ የማይናገር በክብር የተገለጠ አይኾንም››/ሃይ.አበ. 63÷41/ እንዳለው ‹‹ሃይማኖታችንን አንክድም፤ ማዕተባችንን አንበጥስም›› ባሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ ኢሰብአዊነት በተሞላበት ግፍ አንገታቸውን በሰይፍ በመቅላት እና ጭንቅላታቸውን በጥይት በመበታተክ በጭካኔ አገዳደል ገድሏቸዋል፡፡
ይህ ቡድን ከጨካኝ እና አረመኔ የግድያ ድርጊቱ አንጻር የአባላቱን ሰብአዊ ፍጥረት አጠራጣሪ የሚያደርገው ነው፡፡ እጆቻቸው በደም የተሞሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት፣ ‹‹የሰውን ደም ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ በመንገዳቸው ኃሣር መከራ አለ፤ የፍቅርን መንገድ አያውቋትም፤ በልቡናቸው እግዚአብሔርን መፍራት የለም፤›› እንዳለው ነው፡፡ መዝ. 13(14)÷1-4፡፡
Addis Ababa sunday school students
የአ/አ ገዳማትና አድባራት ሰንበት ት/ቤቶች በዛሬው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የጸሎተ ፍትሐት ሥነ ሥርዐት
ስለኾነም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥር የምንገኝ ሰንበት ት/ቤቶች፡-
  • በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ክርስትናን በማስገደድ እና በመቀሰጥ ለመለወጥ የሚደረገውን ዘመቻ እና እንቅስቃሴ በጥብቅ እንቃወማለን፡፡
  • ራሱን አይ ኤስ አይ ኤስ ብሎ የሚጠራውን ቡድን ድርጊት በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
  • በዚኹ ቡድን እና በቡድኑ የአሸባሪነት ድርጊት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣቸውን የአቋም መግለጫዎች በሙሉ እንቀበላለን፤ በአፈጻጸሙም እንታዘዛለን፡፡
  • በደቡብ አፍሪቃ በዜጎች እና ሌሎችም ወገኖች ላይ የሚፈጸመውን ጥላቻ እና ዘረኝነት የወለደው ግድያ እና ዘረፋ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
  • በአዲስ አበባ ያሉ ሰንበት ት/ቤቶች ኹሉ መርሐ ግብር በማውጣት በየቤተሰቦቻቸው ቤት በመገኘት ሐዘንተኞችን የሚያጽናኑ ይኾናሉ፡፡
ወደፊትም ኹኔታውን እየተከታተልን የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መኾናችንን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን፣ በተጋድሎ ላለፉት ወንድሞቻችን ደግሞ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ልዑል እግዚአብሔር እንዲሰጥልን እንለምናለን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በሃይማኖታችን ያጽናን፤ ለዓለሙም ሰላም ይስጥልን፤ አሜን፡፡
የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

2015 ኤፕሪል 23, ሐሙስ

ተዋሕዶ-በደም

ሚያዝያ 14ቀን 2007ዓ.ም
መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ
0000000000በደም ተመሥርተሽ
በደም ተገንብተሸ
በደም ተዋሕደሽ
በደም ተሰራጭተሸ
ደሙ ብርሃን ሆነን ከጨለማም ወጣን ፡፡
ተዋሕዶ
በደም አጥምቀሽን
በደም አጽንተሸን
ከጌታችን ጋራ አንድ አካል አረግሽን፡:
ተዋሕዶ
በደሙ አክብረሽን
በደሙ አስታርቀሽን
ደሙን ከካሰልን
የደሙን ማኅተም ኃይሉን ተጎናጸፍን፡፡

ተዋሕዶ
በደም ተገዝቼ
በደሙም ነጽቼ
በደሙ ጸንቼ
ኖርኩኝ ረክቼ ደሙን ጠጥቼ ፡፡

ተዋሕዶ
ለዓለም በፈሰሰው ደሙ
ምልክት ዓርማዬ ሲሆን ማኅተሙ
ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ እንዳይችል መልኩን
እንዴት በመከራ አላውቀውም ልበል?

ተዋሕዶ
ደሙ ይጠራኛል ጽና በርታ እያለ
ምልከት በልቤ ታትሞ ስላለ፡፡
እንዴት ልበጥሰው አላውቅም ልበለው?
መንፈሱ አጽንቶ መንፈሱ ካገዘኝ፡፡
የቀድሞ ማንነት በደሌን ሳያየው
በማተቤ አጸናኝ ለመንግሥቱ አበቃኝ፡፡

ለሰማእታቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተካሔደ፡፡


ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም.
001tselote fitat002tselote fitat004tselote fitat003tselote fitat
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሊቢያ ለተሰዉት ክርስቲያኖች ቀኖናው በሚፈቅደው መሠረት በቅርቡ የሰማእትነትን ክብር እንደምትሰጥ አሰታወቀች
ቅዱስ ጳትርያርኩ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የግብጽ አምባሰደር፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰማእታቱ ቤተሰቦችና ምእመናን በተገኙበት ጸሎተ ፍትሐቱ ተከናውኗል፡
በጸሎተ ፍትሐቱ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራን ሰማእታቱን አስመልከቶ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ያስተላለፉትን መልእክት ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን!
ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡነ ዘበሰማያት
በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ
የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 10*32
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት 
የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ 
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ወጣቶች
ምእመናንና ምእመናት
ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕትነት አብሯት የኖረ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ዘመናት ልጆቿ በግፍ ተገድለው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡

በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በናግራን፣ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት፣ በዐሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አሕመድ፣ በዐሥራ ዘጠነኛውና ሃያኛው ክፍለ ዘመን በውጭ ወራሪ ኃይሎች በርካታ የሰማዕትነት ታሪኮች አልፈዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሁሉም ዘመን የተነሡባት አሳዳዶችና ገዳዮች ከነታሪካቸው ሲጠሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአምላኳ ጥበቃና በልጆቿ ጽናት ሰማዕታቷን አክብራ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ሀብትን እያደለች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች፡፡

ዛሬ እነዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጠባቡ በር ተጉዘው በደማቸው ማሕተም ወደ መንግሥተ ሰማያት የገቡ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት ጽኑ ምስክሮች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ለእነዚህ ልጆቻችን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት የሚገባውን የሰማዕትነት ቀኖና ሥነ ሥርዓት በቅርቡ በማከናወን ለመላው ዓለም ያሳውቃል፡፡

ስለዚህ የክርስቶስ ቤተሰቦች የሆናችሁ ክርስቲያኖች ሁሉ በዚህ አረመኔያዊ ወንጀል ሳትደናገጡ አሸባሪነትን በአንድነት ሆናችሁ በማውገዝና በመከላከል የተጀመረውን ተቃውሞ ትርጉም ባለውና አፋጣኝ በሆነ መንገድ ልንፈጽመው እንደሚገባ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

005tselote fitat006tselote fitat007tselote fitat10tselote fitat
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
አሸባሪነት ሃይማናት የለውም፣ በዕውቀትና በበሳል አእምሮ የሚከናወን ተግባርም አይደለም፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎችም የተረጋጋ ሥነ ልቦና ያላቸው ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ብሶት ያለባቸው ሰዎች እንደሚያደርጉት ያለ የነፃነት ትግልም አይደለም፡፡

ነገር ግን በፍጹም ራስ ወዳድነትና ጭካኔ ላይ የተመሠረተ አስነዋሪ ወንጀል ነው፡፡ የአይ ኤስ አሸባሪዎች የፈጸሙት ወንጀል የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ አስተሳሰብን የማይወክልና የሰውን ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህርይ የጣሰ ተግባር ነው፡፡

ይህንን አስነዋሪ ግፍ ክርስቲያኖችና የሌላ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘውና ሊጸየፈው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የፈጸሙት ተግባር በራሳቸው ላይ ቢፈጸምና በጤናማ ሥነ ልቦና ቢያዩት ኖሮ በወጣቶቻችን ላይ በፈጸሙት ተግባር ልክ እንኳ ቢከፈላቸው እንደማይበቃ አድርገው በራሳቸው ላይ ይፈርዱ ነበር፡፡

ዛሬ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ለሚመስሉት ወገኖቹ ሕይወት፣ ምቾትና ሰላም ደፋ ቀና በሚልበት ዓለም ከሰው የተፈጠሩ የማይመስሉ አረመኔዎች ክቡር የሆነ የሰውን ልጅ ነፍስ ኢሰብኣዊ በሆነ መንገድ ሲቀጥፉ መታየት ምን የሚሉት እምነት ነው?

ይህን አስነዋሪና ከሰው ተራ የሚያወጣቸውን ተግባርስ የወጣቶቹ ወላጆች ሳይቀሩ ዓለም ሁሉ በሚመለከተው ሚዲያ ማሳየት ምን የሚሉት ጭካኔ ነው?

የሰውን ልጅ የቀድሞ ታሪክ አጥፈቶ አዲስ የግፍና የኢሰብኣዊነት ታሪክ ለመሥራት መጣጣርስ ምን የሚሉት አስተሳሰብ ነው?

ስለዚህ አይ ኤስን ጨምሮ በሰብአዊ ፍጡር ሉዓላዊ ክብር ላይ የተቃጣ የአሸባሪነት ወንጀል ያልምንም ቅድመ ሁኔታ ከምድራችን ሊወገድ የሚገባው እኩይ ግብር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ራሳቸውን አይ ኤስ ብለው የሚጠሩት አሸባሪዎች ከዕውቀትና ከሃይማናት የወጡ፣ የልማትና የሰው ልጅ ሰላማዊ ሕይወት ሥጋቶች የሆኑ ቡድኖች በመሆናቸው ዓለም በአንድነት ተባብሮ ሊያቆማቸው ይገባል፣

ምናልባት ቡድኑን በገንዘብና በልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት ካሉም የጥፋት ተባባሪ ከመሆን ሊታቀቡ ይገባል፣

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ለፈጸሙት ወንጀል በነፍሳቸውና በኅሊናቸው ከሚመጣባቸው ዘለዓለማዊ ፍርድ ይድኑ ዘንድ ንሥሓ እንዲገቡ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ቀደም ሲል እንደገለጽነው በመንፈሳዊ ሕይወት ከምናገኘው ዋጋ ሁሉ የሰማዕትነት ዋጋ ተወዳዳሪ የለውም፣

በፍትሕ መንፈሳዊ ወሰማእታትሰ እሉ እሙንቱ ዘይቤ ክርስቶስ በእንቲሆሙ ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አእምኖ በቅድመ አቡነ ዘበሰማያት፣ ወለእመተሳተፍክምዎሙ በጊዜ ኅዘናቲሆሙ ይከውን ለክሙ ስምዕ በእንተ ጻሕቀ ኅሊናክሙ፡፡

ሰማዕታት ማለት እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏቸው ስለ ቁርጥ ሓሳባችሁ ሰማዕትነት ይቆጠርላችኋል፡፡ የተባለላቸው ናቸው፤

ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው ታማኞች ለመድኅኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደማቅ ምስክሮች ናቸው፤

ሰማዕታት በቅዱሳት መጻሕፍት ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፤(ማቴ 10*28) የሚለውን ቃል ተቀብለው ምርጫቸው እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ ያሳዩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡

ሰማዕታት የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው በተባለው መሠረት የመንግሥተ ሰማያትን የክብር አክሊል በጥበብ ጀምረው በደማቸው ምስክርነት የተቀዳጁ ናቸው፡፡

ክብራቸውም አቡቀለምሲስ ዮሐንስ በራእዩ ምዕ 20 ቁጥር 4 ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእርሱ ላይ ለተቀመጡትም ዳኝነት ተሰጣቸው፣ ስለኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቆረጡባቸውን ሰዎችአየሁ ብሎ እንደተናገረው በእግዚአብሔር መንግሥት የማያልፍ አክሊልና የፍርድ ዙፋን የተዘጋጀላቸው ናቸው፡፡

ስለዚህ የእነዚህ ወጣቶች ልጆቻችን ቤተሰቦች የሰማዕታት ቤተሰቦች በመሆናችሁ ልትጽናኑ ይገባል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በደሙ የመሠረታት ወልደ እግዚአብሔር የልጆቿን ነፍስ በክብር እንዲቀበል ትጸልያለች፡፡
ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻችንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች መጽናናትና ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻችንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምንና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች መጽናናትና ብርታትን ይስጥልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ 
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...