2013 ኦክቶበር 12, ቅዳሜ


ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ዐረፉ፤ የቀብር ሥነ ሥርዐቱ ነገ በኢየሩሳሌም ይፈጸማል

  • በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ከሠላሳ ዓመታት በላይ አገልግለዋል
  • ‹‹በጌቴ ሰማኔ፣ በጎልጎታ፣ በዴር አብርሃም ሁሉ ሰፊ ይዞታ እንዳለን በታሪክ ሰፍሯል፡፡ ግብር ለመገበር አቅም ስላነሰን ዴር አብርሃምን ግሪኮች ወሰዱብን፤ ቤተ ልሔም ያለውን ርስታችንን አርመኖች ወስደውታል፤ በዚያ ላይ ያለንን መረጃ በሙሉ ቀደም ሲል አርመንና ግብጾች ወስደው አጥፍተውታል፡፡››
  • ‹‹ግብጾች በጣም ነው የሚከራከሩት፡፡ በዴር ሡልጣን ጉዳይ ግብጾች ያቋቋሙት ትልቅ ኮሚቴ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንም የእኛ ነው ካልን ዴር ሡልጣን ከእጃችን አይወጣም፡፡ ለዚህ ቦታ መርጃ የሚኾን አንዳንድ ፕሮጀክት መዘርጋት አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ ምእመናን እጃችኹን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ዴር ሡልጣን አለን ማለቱ ብቻውን በቂ አይኾንም፡፡››
  • ‹‹ሕዝቡ ከገዳሙ ጎን ቆሞ፣ ገዳሞቻችን እንደ ሌሎቹ በልጽገው ፈጣሪ እንዲያሳየኝ ጸሎቴ ነው፡፡ የዴር ሡልጣን ክርክር ፍጻሜ አግኝቶ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መብቷ እስከ ኾነ ድረስ የኢትዮጵያ ምእመናን ለዴር ሡልጣን መርጃ እንዲኾን አስቦ እንደ ግብጾች አንድ ድርጅት አቋቁሞ ለዚያ ሒሳብ ተከፍቶ እንዳየው እመኛለኹ፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ለጋዜጠኞች የተናገሩት/
His Grace Abune Heryakos
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
(ከ1923 – 2006 ዓ.ም.)
በመጻሕፍተ ሐዲሳት መምህርነታቸው፣ በጸሎትና የተባሕትዎ ሕይወታቸውና መፃዕያትን በሚናገሩበት ሀብተ ትንቢታቸው የሚታወቁት አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ዐርፈዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዐታቸው ነገ፣ ጥቅምት ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከ፲፱፻፷፬ ዓ.ም. ጀምሮ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ባገለገሉበትና በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት አንዱ በኾነው በአልዓዛር ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል፡፡
በቆየባቸው ሕመምና በዕርግና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባረፉት በብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ ለመገኘት የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የባሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ወደ ስፍራው ማምራታቸው ታውቋል፡፡
በፊት ስማቸው አባ ላእከ ማርያም ዐሥራት በኋላ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ተብለው ለማዕርገ ጵጵስና የበቁት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማትን የተመለከቱ ጉዳዮች እንዲያስፈጽሙ በ፲፱፻፹፭ ዓ.ም. ከማኅበረ መነኰሳቱ ተልከው ወደ ኢትዮጵያ በሄዱበት አጋጣሚ ነው፡፡ በወቅቱ ከብፁዕነታቸው ጋራ በአጠቃላይ ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት ተሹመዋል፤ እነርሱም በቀደምት የኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች መንገድ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዙትና በ፳፻፫ ዓ.ም. ያረፉት በገዳማቱ የሊቀ ጳጳሱ ረዳት ብፁዕ አቡነ አብሳዲ እንዲሁም የደቡብ አሜሪካው ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ናቸው፡፡
ከ፲፱፻፷፬ – ፲፱፻፸ ዓ.ም. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ካልዕ ጋራ አብረው ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዙት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በኤጲስ ቆጶስነት ከተሾሙ በኋላ ወደ ኬንያና ጅቡቲ አምርተው ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ከኬንያና ጅቡቲ ተመልሰው የአፋር ሀ/ስብከት ጳጳስ ኾነዋል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ቆይታ በኋላ ለሕክምና ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እስከ ኅልፈታቸው ድረስ ከኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት አንዱ በኾነው በአልዓዛር ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ኖረዋል፡፡
በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በነበራቸው ከ35 ዓመታት በላይ ቆይታ ስለ ቅድስናና የታሪክ ይዞታችን ተጠያቂ ከነበሩት አባቶች አንዱ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣ ቤተ ልሔም ላይ የነበረው ይዞታችን ከግለሰቦች እጅ ተገዝቶ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እጅ ሲገባ ታላቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤ መጋቢም ኾነው አገልግለዋል፡፡
አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የተወለዱት በ፲፱፻፳፫ ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ አካባቢ ነው፡፡ በልጅነታቸው በተወለዱበት ስፍራ የቃል ትምህርት፣ ንባብ፣ ግብረ ዲቁና ተምረዋል፡፡ ከዚያም ወደ ጎጃም በመሻገር የቅኔ ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለዋል፡፡ የቅኔ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደግሞ አማራ ሳይንት ወደሚባለው ስፍራ ወርደው ነው፡፡ እኒህን ትምህርቶች ከተከታተሉ በኋላ ለጊዜው አቁመው ደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ወደሚገኘው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ገብተዋል፡፡ በዚያም በረድእነት አባቶችን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
በዚሁ ገዳም እያሉ አንድ ወቅት የገዳሙ አበ ምኔትና ሌሎች መነኰሳት ያልተገባቡበት ጉዳይ ስለነበር አለመግባባቱን ለመፍታት መነኰሳቱን ተከትለው ወደ ደሴ ይሄዳሉ፡፡ መፍትሔ ባለማግኘቱ ጉዳዩን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለማቅረብ አሁንም መነኮሳቱን ተከትለው አዲስ አበባ ይደርሳሉ፡፡ በዚያው መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ገብተው መጻሕፍተ ነቢያትን ተመርዋል፡፡ ወደ መ/ር ገብረ ማርያም መርሻ ተዛውረው መጻሕፍተ ሐዲሳትን አጥንተዋል፡፡
በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከ፲፱፻፶ – ፶፯ ዓ.ም ከቆዩ በኋላ ወደ ታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ሄደው አለቃ ሞገስ ከተባሉ መምህር ዘንድ ከመጻሕፍተ ሊቃውንት መካከል ቄርሎስንና ዮሐንስ አፈ ወርቅን ተምረዋል፡፡ ሌሎችንም የሊቃውንት መጻሕፍት በጉባኤ ቤት እየተገኙ ሲሰሙ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻም በዚሁ ገዳም የሐዲሳት መምህር እንዲኾኑ ተመርጠው ሐዲሳትን በማስተማር በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን አፍርተዋል፡፡
*          *          *

‹‹ሕዝቡ ከገዳሙ[ዴር ሡልጣን] ጎን ቆሞ ገዳሞቻችን እንደ ሌሎቹ በልጽገው ፈጣሪ እንዲያሳየኝ ጸሎቴ ነው››
/ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጠኛ ከተናገሩት/

ስምዐ ጽድቅ፡- ብፁዕ አባታችን እስኪ ስለ ኢየሩሳሌም ገዳማት የሚያውቁትን ያጫውቱኝ?
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፡- ታሪኩን እንኳ ከሌሎች አባቶች መስማቱ ይሻላል፡፡ እኔ ግን ስለ ገዳማቱ ችግር ላጫውትኽ እችላለኹ፡፡ ገዳሙ ባለፈው ከሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ ጥቅምት ድረስ ብዙ ችግር ደርሶበታል፡፡ መነኰሳት ተደብድበዋል፡፡ በአንድ ግብጻዊ መነኩሴ ምክንያት አባቶች ተንገላትተዋል፡፡ ይህ መነኩሴ እኛ ገዳም ውስጥ ብዙ ዓመት ኖሯል፡፡ ዘንድሮ ግን ሌላ ታሪክ ይዞ አየኹ፡፡ አባቶችን አስደበደበ፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- እኛ ራሳችን ቦታ ስለሰጠነው አይመስልዎትም?
ብፁዕነታቸው፡- ልክ ነኽ፣ እንደዚያ ነው፡፡ በእኛ ገዳም እኮ ብዙ ጊዜ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም ሲቸግረው መጠጊያ የኾነው የእኛ ገዳም ነው፡፡ አንድ ወቅት ኢራቅ እስራኤልን ልትመታ ሮኬት የወረወረች ጊዜ የእርሱ ወገኖች አባረውት ከእኛ መነኮሳት ጋራ ነው ሲመገብ የከረመው፡፡ ከእኛ ገዳም እንደ አንድ አባል ኾኖ ብዙ ስንረዳው ቆይተናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አሁን ያሉት የግብጽ ጳጳስ ምን ተስፋ እንደሰጡት አላውቅም፣ አድርጎት የማያውቀውን ማድረግ ጀመረ፡፡
ከመኖርያ ቤቱ እየወጣ ወደ ራሳቸው ወደ ግብጻውያን ወደ ራሳቸው ገዳም ይሄዳል፡፡ ከዚያ ትንሽ ይቆይና ሦስት አራት ፖሊሶች አጅበውት መጥቶ እኛ ገዳም ወንበሩን ዘርግቶ ይቀመጣል፡፡ ግማሽ ሰዓት ያህል ይቀመጥና ደግሞ ተነሥቶ ወንበሩን አሸክሞ ወደ ቤቱ ይገባል፡፡ እነርሱ በእኛ ገዳም ሊሠሩት ያሰቡት አንድ ነገር እንዳለ ያስታውቃል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጉዳዩን እንደ ቀላል አይተነዋል፡፡ ቀላል ግን አይደለም፡፡
አሁን ለምሳሌ እኛ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አለን፡፡ እዚያ ለሰኔና ለኅዳር ሚካኤል በዓል በምናከብርበት ወቅት ብዙ ሕዝብ ይመጣል፡፡ ቦታ ስለሚጠብ ከግቢ ውጭ ወጥተው ለማስቀደስ ይገደዳሉ፡፡ ግብጻውያን ግን አይፈቅዱላቸውም፡፡ ሊቀ ጳጳሱ አባ ዳንኤል ይባላል፡፡ እርሱ ወጥቶ ያባርራቸዋል፡፡ ለአንድ ሰዓት እንኳ ማስቀደስ እንዳንችል ያደርጋሉ፡፡ ቦታው ላይ ቆመው ካስቀደሱ፣ ነገ ይዞታችን ነው ብለው ይከራከሩናል ብለው በመፍራት ተጠራጣሪ ስለኾኑ አያስቀርቡንም፡፡ የእኛ ግን ምን እንደኾነ ስሜቱን አላውቅም፣ በገዳማችን እየተመላለሰበት ሲፈልግ ወንበሩን ዘርግቶ እየተቀመጠ ይኖራል፡፡
የሚገርመው ወንበሩን ዘርግቶ ከመቀመጥ አልፎ ወደ እኛ ገዳም ሲገቡ ‹‹የግብጽ ገዳም ነው›› እያለ ያስተዋውቃል፡፡ መነኩሴው ምን ዓላማ እንዳለው አንዳንድ ሰዎች የተረዱት አይመስለኝም፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ግንኮ ያ ሁሉ ርስታችን ተወስዶ ዛሬ በዚህች በተረፈችን ቦታ ላይ መከራችንን ማየታችን የሚገርም ይመስለኛል፡፡
ብፁዕነታቸው፡- ታሪካችን የጥንት ኾኖ ዛሬ በዚህ ኹኔታ መገኘታችንን ስናየው ያስብላል፡፡ አንድ ዝኤብ ብልናኢ የተባለ ደራሲ በጻፈው መጽሐፍ የእኛ ይዞታ የት የት እንዳለ ገልጾአል፡፡ እርሱ እንዲያውም በጌቴ ሰማኔ፣ በጎልጎታ፣ በዴር አብርሃም ሁሉ ሰፊ ቦታ እንዳለን በታሪክ አስፍሮታል፡፡ ዴር አብርሃም የተባለው ቦታ የኢትዮጵያውያን ነበር፡፡ ግብር መገበር አቅቷቸው ግሪኮች ወስደውባቸዋል ብሎ ጽፏል፡፡ መጽሐፉ ከቤቴ አለ፡፡ ይኸም ኾኖ ግን ቦታውን በዘመን ብዛት የእነርሱ ይዞታ ስላደረጉት የእኛ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡
ቤተ ልሔም ያለውን ርስታችንን አርመኖች ወስደውታል፡፡ በዚያ ላይ ያለንን መረጃ በሙሉ ቀደም ሲል አርመንና ግብፆች ወስደው አጥፍተውታል፡፡ በኋላ ግን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት (ከ1944 – 1957 ዓ.ም.) ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ደጃች መሸሻ የሰበሰቡትን መረጃና የቀረውንም ራሳቸው አሰባስበው ክሥ በመመሥረት የተያዙብንን ገዳማት በከፊል ወደ እኛ እንዲመለስ አድርገዋል፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- በቤተ ልሔም ያለንን ይዞታ ያገኘነው በእርስዎ አማካይነት መኾኑን መነኰሳቱ ነግረውኛል፡፡
ብፁዕነታቸው፡- ቤተ ልሔም እኔ መጋቢ ኾኜ በጊዜው የነበሩ ሊቀ ጳጳስ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ስለነበር አልነበሩም፡፡ ለጊዜው ባለቤት የነበረው ዐረቡ በድንገት ተነሥቶ ቦታውን ካልገዛኽ ለሌላ እሸጠዋለኹ ስላሉኝ እኔ ለማኅበሩ ነገርኩና እንግዛ ብለን ተመካከርን፡፡ እንዳልኩኽ ሊቀ ጳጳሱ ኢትዮጵያ ስለነበሩ ለእርሳቸው ደውዬ፣ ቦታውን ሰውዬውን አሁን ካልገዛችኹን ልሸጠው ነው ስላለ በዚያ ላይ የሚሸጠው መሬት ከልዑል ራስ ካሳ ቦታ ጋራ አዋሳኝ ስለኾነ ወደፊት ምናልባት ደግሞ እነርሱ በበጎ አድራጎት መሬታቸውን ቢሰጡን ተያይዞ አንድ አቋም ያለው ትልቅ ቤተ ክርስቲያን መሥራት ይቻላልና እንግዛው አልኋቸው፡፡ እንዲያው ግዙት አሉ፡፡ ያን ጊዜ እኔ ገዳማቱ መጋቤ ነበርኩኝ፡፡ አሁን የሚቀደስባትንና ታች መነኰሳቱ የሚኖሩበትን በእኔ መጋቢነት ተገዛ፡፡ የወዲህኛው ፎቁ ግን በኋላ በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ነው የተገዛው፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ብፁዕ አባታችን፣ በእስራኤል ከሚነገሩት ቋንቋዎች ምን ያህሉን ያውቃሉ?
ብፁዕነታቸው፡- ዕብራይስጥ እችላለኹ፤ ዐረብኛም እንደው ለራሴ እሞካክራለኹ፡፡ በተለይ ዕብራይስጡን እጽፋለኹ፤ አነባለኹኝ፤ በእርሱ ምንም ችግር የለብኝም፤ መጽሐፉም አለኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስም አለኝ፤ የዕብራይስጥ ትርጓሜውም አለኝ፡፡ እርሱን በጊዜው እመለከታለኹኝ፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ታዲያ ዕብራውያን በራሳቸው ቋንቋ የጻፉት የኢትዮጵያ ገዳማትን የተመለከተ ማስረጃ አላገኙም?
ብፁዕነታቸው፡- ሳነብ የእኛ ይዞታ ለመኾኑ የሚያስረዳ ጽሑፍ አግኝቻለኹ፡፡ ብዙ በዕብራይስጥ እንዲያውም ዝኤብ ብልናኢ የሚባለው አንድ አራት መጻሕፍት አሉት፡፡ አንደኛው አሌፍ፣ ሁለተኛው ቤት፣ ሦስተኛው ጊሜል፣ አራተኛው ዳሌት ይባላሉ፡፡ የጌቴ ሰማኔውን ቦታችንን በካርታ ጭምር አውጥቶታል፡፡ ከእመቤታችን መቃብር አጠገብ ነው፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- እርስዎ መጻሕፍት ማንበብ እንደሚወዱ ይነገራል፡፡
ብፁዕነታቸው፡- እዚያ አዲስ አበባ ሳለኹ ብዙ ጊዜ የማሳልፈው ሐይቅ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ቤተ መዘክር እንዲያው ሥራ በማይኖረኝ ቀን ስመለከት ነበር የምውለው፡፡ ትምህርት በማስተምርበት ጊዜ የክረምት ሲዘጋ ሐይቅ ሄጄ ከርሜ ስመለከት ውዬ ወይም ደግሞ ጠቃሚውን በማስታወሻ እየያዝኁ እመጣለኹ፡፡ ማስታወሻዬን እንደው ዝም ብዬ አዲስ አበባ ጥዬው ነው ያለ፡፡ ሌላው ግን ከዚህ ይዤ ልምጣ፣ ያኔ ኬንያ ልጣለው፣ ሌባ ይውሰደው እንጃ ብዙ ነበረ፣ ጠፋብኝ፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ዕብራይስጡንና ግእዙን መጽሐፍ ቅዱስ አገናዝበውታል?
ብፁዕነትዎ፡- እዚህ ማስታወሻ እየያዝኁ ዕብራይስጡን አነባለኹ፡፡ ለነገሩ የቦታውን ይዞታ የሚጠቁሙ ካልኾኑ በስተቀር ሌላው በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው ንባቡ ግን የእነርሱ ሊቃውንት የተረጎሙት ነው፡፡ ጥሩ ነው፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ከምትተረጉመው ጋራ ግን አይሄድም፡፡ የሚተረጉሙት መጻሕፍተ ብሉያትን ነው፤ እርሱንም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለእመቤታችን ሰጥተን የምንተረጉመውን በመጽሐፈ ነቢያት በሌሎችም ያሉትን በሌላ ምስጢር ስለሚተረጉሙት ብዙም አልከታተለውም፡፡
አንድ ያየኹት ትልቅ ነገር፣ አንድምታው ላይ አንድም እያልን የምንተረጉመውን ትርጓሜ እገሌ ተረጎመው አንልም፡፡ እንደው ዝም ብለን አንድም ብለን ትርጓሜ ብቻ ነው፡፡ እነርሱ ግን በዚህ ዘመን የተወለደ፣ በዚህ ዘመን ከእገሌ የተማረ፣ ይህን ያህል ዘመን ቆይቶ ይህን ትርጓሜ ተረጎመ ብለው ስሙንም አገሩንም ሳይቀር እየጠቀሱ ያሰፍሩታል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የእነርሱን የሚመስል ትርጓሜ አለ – ትርጓሜ ወንጌል ይባላል፡፡ ግእዙ በግእዝ ነው የሚተረጎመው፡፡ በአማርኛ አይደለም፣ ግእዝ በግእዝ ነው፡፡ እርሱ ዓመተ ምሕረት ባይጠቅስም ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቄርሎስ፣ ሳዊሮስ እንዲህ ይሄን ተረጎሙት ይላል፡፡ ሌላው ግን አንድም ብሎ ተርጉሞ ይሄዳል እንጂ እገሌ ነው አይልም፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ብፁዕ አባታችን፣ እርሰዎ የሚኖሩት በአልዓዛር የኢትዮጵያ ገዳም ነው፡፡ እስኪ ስለ ገዳሙ ታሪክ ይንገሩኝ፡፡
ብፁዕነታቸው፡- አልዓዛር በአሁኑ ጊዜ ከተማ ኾኗል፡፡ በፊት ግን መንደርም አልነበረበትም፡፡ በመጀመሪያ ቦታው የተገዛው በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ነው፡፡ ለመቃብር ቦታ ብለው ራቅ አድርገው ነው የገዙት፤ መንደር አልነበረውም፡፡ የገዙበትን ዋጋውን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንዲከፍሉ ጠየቋቸው፤ ንጉሡም ጥያቄውን ተቀብለው ገንዘቡን ሰጧቸው፡፡ በዚህ የተነሣ ገዳሙ በንጉሡ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተገዛ መኾኑን የሚያመለክት ጽሑፍ በድንጋይ ተቀርጾ ቦታው ላይ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡
በወቅቱ ምድረ በዳ ነበር፤ ሰውም ምንም አልነበረም፡፡ በኋላ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ተሹመው መጡ፡፡ እርሳቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠሩ፡፡ አሁን ከዚያ እርሳቸው ቤት ከሠሩ በኋላ መነኰሳት ተለይተው አያውቁም፡፡ እኔም አባ ገብረ ማርያም ኮንታ የሚባሉ አሉ፣ ከእርሳቸው ጋራ አንድ ትንሽ ጎጆ በግላችን መቁነናችንን አጠራቅመን ሠርተን አሁን እዚያ ነው የምንኖር፡፡ በአጠቃላይ በገዳሙ ሁለት ሦስት ነበርን፡፡ አሁን ደግሞ አንድ አራት ኾነናል፡፡ ብዙም ሰው አይኖርበትም፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- እስራኤልና ፍልስጤኤም ሁለት መንግሥት ከኾኑ ቦታው ወደ ማንኛው የሚኾን ይመስልዎታል?
ብፁዕነታቸው፡- አሁን ወደ ማን ክፍል እንደሚኾን አላወቅንም፡፡ ግን ከአጠገቡ መአሌ አዱሚሞ የሚባል ሰፊ ቦታ እስራኤሎች ብዙ ሕዝብ አስፍረውበታል፡፡ ወደ 30 ሺሕ ሰው ይመስለኛል የሰፈረው፡፡ በጣም ጥሩ ቦታ ነው፡፡ ግን ድሮም እዚያ ቤተ ክርስቲያን የተሠራበት ቦታ ነበር፤ እርሱን ለቱሪስት ክፍት አድርገውት ቱሪስት ያየዋል፡፡ ቀድሞ ቤተ ክርስቲያን የነበረበት ፍራሹ ይታያል፡፡ የእኛ ግን እላይ ነው፡፡ የአልዓዛር ቤት ከነበረው ትንሽ ገንጠል ብሎ ወደ ውስጥ ገባ ያለ ነው፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- አልዓዛር በሚገኘው ገዳማችን ችግር ገጥሟችኹ አያውቅም?
ብፁዕነታቸው፡- በጣም ያጋጥመናል፡፡ አሁን አሁን በቅርቡ እንኳ ዐረቦቹ ድንጋይ ይወረውሩብን ነበር፡፡ አሁን ግን አንድ የዐረብ ተወላጅ የሚኾን ዘበኛ ቀጥረን እርሱ ከገባ ጸጥ ብሏል፡፡ ድንጋይ አይወረውሩም፡፡ ግድግዳው ላይ ግን ይለቀልቃሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በረድ ብሏል፡፡ ሰውዬውም ደኅና ልጅ ነው፤ ይጠብቃል፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ገዳሙ በምንድን ነው የሚተዳደረው?
ብፁዕነታቸው፡- ለቦታው ጠባቂዎች ብለው ቦታ እየገዙ፣ ቤት እየሠሩ የሰጡን አሉ፡፡ በዚያ በምናገኘው ኪራይ ነው መነኰሳቱ የምንተዳደር፡፡ በርግጥ ቀድሞ ከኢትዮጵያ ገንዘብ ይላክ ነበር፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ በየሦስት ወሩ 3000 ዶላር ይልኩልን ነበር፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ቤት ነበረን፡፡ እርሱን እንተወው፣ አሁን የለም፡፡ እዚህ ባለው ገንዘብ ነው አሁን የምንተዳደር፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- በሕይወት ዘመንዎ እንዲኾን የሚፈልጉትን ነገር ቢነግሩንና ብናጠናቅቅ?
ብፁዕነታቸው፡- የዴር ሡልጣን ክርክር ፍጻሜ አግኝቶ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መብቷ እስከ ኾነ ድረስ የኢትዮጵያ ምእመናን ለዴር ሡልጣን መርጃ እንዲኾን አስቦ እንደ ግብጾች አንድ ድርጅት አቋቁሞ ለዚያ ሒሳብ ተከፍቶ እንዳየው እመኛለኹ፡፡
ግብጾች አሁን ካየን ጳጳሱ ብቻውን ምን አቅም አለው? ክርስቲያኖች ምእመናኑ ናቸው የሚሟገቱለት፡፡ በዴር ሡልጣን ጉዳይ የግብጽ ክርስቲያኖች ያቋቋሙት ትልቅ ኮሚቴ አላቸው፡፡ ግብጽ ውስጥ መጅልስ የሚሉት ትልቅ ድርጅት አለ፡፡ አሜሪካም እንደዚሁ ድርጅት አቋቁመዋል፡፡ እነርሱ በጣም ነው የሚከራከሩት፡፡ ኢትዮጵያውያንም የእኛ ነው ካልን ዴር ሡልጣን ከእጃችን አይወጣም፡፡ ለዚህ ቦታ መርጃ የሚኾን አንዳንድ ፕሮጀክት መዘርጋት አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ ምእመናን እጃችኹን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ዴር ሡልጣን አለን ማለቱ ብቻውን በቂ አይኾንም፡፡ ጥንት መነኰሳቱ ናቸው በእግራቸው መጥተው ዴር ሡልጣንና ዮርዳኖስን የያዙት፡፡ በኋላ የተነሡ አባቶችም እነ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብም ሌሎችም እነ ዐፄ ዮሐንስም በቃላት ከምንገልጸው በላይ ደክመውበታል፤ እነ ዐፄ ምኒልክም ረድተዋል፡፡ እንደውም ዐፄ ምኒልክም ሙግትም ክሥ ተመሥርቶ ብዙ ክርክር አድርገዋል፡፡
ግን ይሄ ሁሉ ኃይል ለውጤት የሚበቃው፣ ርስታችን ለሁልጊዜ በእጃችን የሚቆየው ምእመናን ሲኖሩበት ነውና ምእመናኑ ለዚህ ቦታ መቆም አለባቸው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ከገዳሙ ጎን ቆሞ፣ ገዳሞቻችን እንደ ሌሎቹ በልጽገው ፈጣሪ እንዲያሳየኝ ጸሎቴ ነው፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣፲ኛ ዓመት ቁጥር ፲፪/ ቅጽ ፲ ቁጥር ፹፬/ መስከረም ፲፱፻፺፮ ዓ.ም
About these ads

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...