ማክሰኞ 23 ሴፕቴምበር 2014

ነገረ መስቀል

  መስከረም ፲፮ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡-                                                                         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ አሜን!!!
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ሥርዓት መሠረት ከመስከረም ፲ እስከ መስከረም ፳፭ ያለው ሳምንት “ዘመነ መስቀል” ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንት ስለ መስቀል ክብር ይነገራል፤ መዝሙረ መስቀልም ይዘመራል፡፡ መስቀል ማለት “ሰቀለ” ከሚል የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን ትርጓሜውም “የተመሳቀለ፣ መስቀለኛ” ማለት ነው፡፡
 መቅድመ ወንጌል እንደሚነግረን፥ አዳም የማይበላውን በልቶ ከእግዚአብሔር አንድነት ከተለየ በኋላ አብዝቶ ያለቅስ ነበር፡፡ በኀጢአቱ ከማዘንና ከማልቀስ በቀርም ሌላ ግዳጅ አልነበረውም፡፡ በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ብዙ መጨነቁን፥ ጸዋትወ መከራዉን ያየው ቸሩ እግዚአብሔር ግን አዘነለት፡፡ “እቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየ - በመስቀሌና በሞቴ አድንኀለኹ” ብሎም ቃል ኪዳን ገባለት /ኪዳነ አዳም ፫፡፫-፮፣ ዘፍ.፫፡፲፭/፡፡ መጽሐፈ ቀሌሜንጦስ እንደሚነግረንም ከ፭ ቀን ተኵል በኋላ እንደሚያድነው ተስፋ ሰጠው፤ ከ፭ ሺሕ ፭ መቶ ዓመታት በኋላ ሲል ነው፡፡ “ነገረ መስቀል” የምንለውም ይኸው ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ነው፡፡

 የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት የተለያዩ ሀገራት ወንጀለኞችን በመስቀል ይቀጡ ነበር፡፡ ሰውን በመስቀል ሰቅሎ መቅጣት የተዠመረውም በፋርሳውያን ዘንድ ነው፡፡ ፋርሳውያን አንድ ወንጀለኛ ነው ያሉትን ሰው ስለምን በመስቀል እንደሚቀጡት ሲገልፁ “ኦዝሙድ” ከተባለው “የምድር አምላክ” ጋር ያያዙታል፡፡ እንደነርሱ አባባል ወንጀለኛው ሰው ቅጣቱን በምድር የተቀበለ እንደኾነ አምላካቸው ይረክሳል፡፡ በመኾኑም አምላካቸው እንዳይረክስ ወንጀለኛው ከመሬት ከፍ ብሎ በመስቀል ይሰቀል ነበር፡፡
 ከፋርሳውያን በተጨማሪ በግብጽ፣ በፊንቄ፣ በግሪክ፣ በሮም፣ በአሶር፣ በካርቴጅና በሕንድ ወንጀለኛ ነው ያሉትን ሰው በመስቀል ሰቅለው ይቀጡ ነበር፡፡ በተለይ ሮማውያን የራሳቸው ዜጋ ያልኾነ “ወንጀለኛን” ይቀጡ የነበረው በመስቀል ነበር፡፡ የራሳቸውን ዜጋ ግን ቶሎ እንዲሞት ከማሰብ አንጻር አንቀው ይገድሉት ነበር፡፡ ለዚህም ጥሩ ማስረጃ የሚኾኑን ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ናቸው፡፡
የመስቀል ዓይነቶች
 እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ማኅበረ ሰቦች “ወንጀለኛ ነው” የሚሉትን ሰው የሚቀጡበት የተለያዩ ዓይነት መስቀሎች ነበርዋቸው፡፡ የታወቁትን ለመጥቀስ ያህልም፡-
v ያልተመሳቀለ መስቀል ( I )
v የእንግሊዘኛው ኤክስ ፊደል ዓይነት መስቀል ( X )፡፡ ይኸውም በተለምዶ የሐዋርያው የቅዱስ እንድርያስ መስቀል ተብሎ ይታወቃል፡፡
v የእንግሊዘኛው ቲ ፊደል ዓይነት መስቀል ( T )፡፡ ይኸውም በተለምዶ የቅዱስ እንጦንስ መስቀል ይባላል፡፡
v የግእዝ ተ ፊደል ዓይነት መስቀል ( † )፡፡ ይኸውም የጌታችን መስቀል የሚባለው ነው፡፡
የመስቀል አተካከል
 እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ማኅበረ ሰቦች ወንጀለኛ ነው ያሉትን ሰው ለመስቀል መስቀሉን በሦስት መንገድ ይተክሉት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ እነርሱም፡-
  ፩ኛ) መዠመርያ መስቀል ይተከላል፡፡ ቀጥሎም የተፈረደበት ሰው በመሰላል ያወጡትና በሚስማር ከግንዱ ጋር ይመቱታል፡፡
  ፪ኛ) ኹለት ግንድ በአንጻር ይተክላሉ፡፡ በግንዶቹም ሠረገላ ይጋደማል፡፡ በሠረገላው ላይም ባለ ሸምቀቆ ገመድ ይቋጠራል፡፡ በመጨረሻም ወንጀለኛው በዚያ ገመድ ታንቆ ይሞታል፡፡
  ፫ኛ) መዠመሪያ መስቀሉ መሬት ላይ ይጋደማል፡፡ በመቀጠል ወንጀለኛው ተጋድሞ በመስቀሉ ላይ ይቸነከራል፡፡ በመጨረሻም መስቀሉ ከወንጀለኛው ጋር ይቆማል፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ኹሉ ቤዛ በመኾን የተሰቀለው በዚሁ መንገድ ነበር፡፡
መስቀል በብሉይ ኪዳን
 ከአዳም ዠምሮ እስከ ፸ ዓ.ም. ያለውን ዜና አይሁድ የጻፈው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን እንደሚነግረን በአይሁድ ማኅበረ ሰብ ዘንድም የተለመደ ነበር፤ መስቀል /ዮሴፍ ወ.ኮ. ፲፯፡፲/፡፡ አይሁዳውያን ርጉም፤ ውጉዝ ነው ያሉትን ሰው በመስቀል ይቀጡ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስንመለከት አይሁድ አንድ ጥፋተኛ ነው ያሉትን ሰው በተለያየ መንገድ ይቀጡት እንደነበር እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ በሰይፍ /ዘጸ.፳፩፡፲፬/፣ በእሳት /ዘሌ.፳፡፲፬/፣ በውግረተ እብን /ዘሌ.፳፡፳፯/፣ በማነቅ /ዘኅ.፳፭፡፬/ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ርጉም፤ ውጉዝ ነው በማለት፥ ከላይ በጠቀስነው መንገድ የገደሉትን ሰው ለመቀጣጫ ሬሳዉን በግንድ ይሰቅሉት ነበር /ዘዳ.፳፩፡፳፪-፳፫/፡፡
 ወንጀለኛውን በመስቀል መቅጣት የፈለጉ እንደኾነ ግን ከመስቀላቸው በፊት ይገርፉታል፡፡ መስቀያውን ተሸክሞ እየተንገላታ ከከተማ ውጪ ወዳለ መስቀያ ቦታ ይወሰዳል፡፡ ሕማሙንም ይረሣ ዘንድ የኢየሩሳሌም ሴቶች ሥቃዩን ለማደንዘዝ መጠጥ ያጠጡታል፡፡ ከዚያም በመስቀሉ ላይ እጆቹንና እግሮቹን ይቸነከራል ወይም በገመድ ይታሠራል፡፡ ከራሱ በላይም ወንጀሉ ይጻፋል፡፡ የተሰቀለው ሰው የሚሞተው ደሙን በማፍሰስ ሳይኾን በልቡ ድካም በመኾኑ ብዙ ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው የምትለየው በኹለተኛው ወይም በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ ቶሎ መግደል የፈለጉ እንደኾነ ግን እግሮቹን ይሰብሩታል፡፡
  ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይኹንና ምንም በደል ያልተገኘበት ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል የተጠቀሙበት መንገድ መስቀል ነበር፡፡ በመኾኑም አስቀድመው ገርፈዉታል፤ መስቀሉን አሸክመው አንገላተዉታል፤ በሰፍነግ ሆምጣጣ ነገር አጠጥተዉታል፡፡ እጆቹንና እግሮቹን ቸንክረዉታል፡፡ ጐኑን በጦር ወግተዉታል፡፡ “ወንጀለኛ ነው” ሲሉም “ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሠ አይሁድ” የሚል ጽሑፍ ከራሱ በላይ ጽፈው ለጥፈዉበታል፡፡ ነገር ግን ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ አንድም በፈቃዱ ቶሎ ስለሞተ እግሩን አልሰበሩትም፡፡

 በዘመነ ብሉይ ስለ ነገረ መስቀል ብዙ ትንቢት ተነግሯል፤ ብዙ ኅብረ አምሳልም ተመስጥሯል፡፡ ከትንቢቶቹ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
Ø “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው” /መዝ.፶፱፡፬/። ይኸውም ምእመናን በክርስቶስ አምነው ከማየ ሥራዌ ከማየ ድምሳሴ፣ ከኀጢአት፣ ከአምልኮ ጣዖት አምልጠው (ድነው) አጋንንትን፣ መናፍቃንን፣ ፍትወታት እኩያትን በትእምርተ መስቀል ድል እንደሚያደርጉ ሲናገር ነው፡፡
Ø “ከኃሢሦን ተቈርጦ በጐልጐታ የሚተከለው የወይን ሐረግ መድኀኒቴ ነው” /የመኃ.፭፡፩ አንድምታውን ይመልከቱ/፡፡
 ስለ ነገረ መስቀል በኅበረ አምሳል ከተመሰጠሩ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህልም፡-
v አዳም ለጊዜው ከእርሷ እንዳይበላ የተከለከላት ዕፀ ሕይወት /ዘፍ.፫፡፳፪/፣
v ኖኅ ከነቤተ ሰቡ ከማየ ድምሳሴ የዳነባት የመርከብ ዕንጨት /ዘፍ.፮፡፲፬-፳፪/፣
v በይሥሐቅ ፈንታ የሚሠዋውን በግ ታስሮ የተገኘባት ዕፀ ሳቤቅ /ዘፍ.፳፪፡፲፫-፲፱/፣
v ሰዋስወ ያዕቆብ /ዘፍ.፴፡፴፯/፣
v የይሁዳ በትረ መንግሥት /ዘፍ.፵፱፡፲/፣
v በትረ ፋሲካ /ዘጸ.፲፪፡፲፩/፣
v ባሕረ ኤርትራን የከፈለች በትረ ሙሴ /ዘጸ.፲፬፡፲፮/፣
v የማራ ውኃ የጣፈጠበት ዕንጨት /ዘጸ.፲፭፡፳፪-፳፯/፣
v የሙሴ አቋቋም /ዘጸ.፲፯፡፲፩-፲፯/፣
v የእሥራኤላውያን መስቀለኛ የጉዞ ሰልፍ /ዘኅ.፪፡፫-፳፮/፣
v ሙሴ በበረሃ የሰቀለው የአርዌ ብርት /ዘኅ.፳፩፡፰-፱/፣
v የኤልሣዕ ዕንጨት /፪ኛ ነገ.፮፡፩-፯/፣
v የሰሎሞን ዕፀ ሕይወት /ምሳ.፫፡፲፰/፣
v የሕዝቅኤል ትእምርተ ድኅነት /ሕዝ.፱፡፬-፮/፣
v ወቦ ዘተርፈ፡፡
መስቀል በሐዲስ ኪዳን
 ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይኹንና ከጌታችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በኋላ ግን ቅዱስ ሥጋው የተቈረሰበት ክቡር ደሙም የፈሰሰበት ስለኾነ፥ መስቀል ትእምርተ መርገም መኾኑ ቀርቶ የክብርና የበረከት መገለጫ ኾነ፤ ትእምርተ ኀፍረት መኾኑ ቀርቶ የነጻነት ምልክት ኾነ፤ የድኅነትና የሕይወት አርማ ኾነ፡፡ ለዚህም ነው በዘወትር ጸሎታችን “ዓለምን ኹሉ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀል እንሰግዳለን፡፡ መስቀል ኃይላችን ነው፡፡ መስቀል ቤዛችን ነው፡፡ መስቀል የነፍሳችን መድኀኒት ነው፡፡ አይሁድ ይክዱታል፤ እኛ ግን እናምነዋለን፡፡ ያመንንበት እኛም በመስቀሉ እንድናለን፤ ድነናልም” እያልን የምናከብረው፡፡ በዕፅ ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ፤ በዕፀ መስቀል ምክንያትም ሕይወት ወደ ዓለም ገባ፡፡ በዕፅ ምክንያት የሞት ቀንበር በላያችን ላይ ተጫነ፤ በዕፀ መስቀል ምክንያትም ይኸው ቀንበር ተሰበረ፡፡ ዲያብሎስ በዕፅ ምክንያት አዳምን ከነልጆቹ ድል አደረጋቸው፤ ጌታችንም ዲያብሎስን በዕፀ መስቀል ራስ ራሱን ቀጠቀጠው፡፡ ዲያብሎስ እኛን ሲቀጣበት በነበረው ዕፅ፥ ዛሬ ግን እኛ ድል የምናደርገው ኾነናል፡፡ ስለዚህ መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፡፡ ከጥንት የነበሩ አባቶችም ይህን የመሰለ ነገር በድርሳናቶቻቸው ጽፈውልናል፡፡ ለምሳሌ ያህልም፡
·        “በተግባራችን ኹሉ፣ በምንገባበትና በምንወጣበት ጊዜ፣ ልብሳችንን ከመልበሳችን በፊት፣ ከመታጠባችን በፊት፣ በቀንና በማታ ወደ ምግብ በምንቀርብበት ጊዜ፣ መብራት በምናበራበት ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ በምንዠምርበትና በምንፈጽምበት ጊዜ፣ በዕለታዊ ሕይወታችን መደበኛ ሥራችንን በምንዠምርበት ጊዜ በትእምርተ መስቀል ግንባራችንን እናማትባለን፡፡”  /ከ፩፻፰-፪፻፳፭ ዓ.ም. የነበረው ጠርጡለስ/፡፡
·        “ይህን መስቀል በልቡናችሁ ቅረጹት፤ የነፍሳችን መዳኛ የኾነው ይህንን መስቀል በአንገታችሁ እሰሩት፡፡ ዓለምን ኹሉ የፈወሰ እና ያጣፈጠ፤ ስሕተትን ኹሉ ያስወገደ፤ እውነትን የመለሰ፤ ምድርን ገነት ያደረገ፤ ሰዎችን መላእክት ያደረገ ይህ መስቀል ነው፡፡ በዚሁ መስቀል ምክንያት ዲያብሎስ አስፈሪነቱ ቀርቷል፤ ሞት ወደ እንቅልፍ ተቀይሯል፤ በእኛ ላይ ነግሦ የነበረው የሞት ፍርድ ተወግዶ ከእግራችን በታች ተጥሏል፡፡” /ከ፫፻፵-፯፬፻፯ ዓ.ም. የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡
ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን!!!
የመስቀል በዓል ጥንተ ነገር
  የመስቀል በዓል በየዓመቱ መስከረም ፲፯ በታላቅ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ይኸው በዓል የቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይኾኑ ብሔራዊ በዓልም ኾኖ ይከበራል፡፡ የመስቀል በዓል የሚከበርበት ምክንያት ምን እንደኾነ የታሪክ ድርሳናትን ስንመረምር እንደሚከተለው ነው፡፡ አይሁድ ከጌታችን ስቅለት በኋላ በዕፀ መስቀሉ ይደረግ የነበረውን የተለያየ ተአምራት ሲያዩ ዓይናቸው ቀላ፤ ቅንአት ያዛቸው፡፡ ሰዎች በተአምራቱ ተስበው ወደ አሚን እንዳይመጡም አንድ ተንኰል አሰቡ፡፡ በመኾኑም በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ቀበሩት፡፡ በቦታዉም በአዋጅ የከተማው ኹሉ ጥራጊና ቆሻሻ እንዲደፋበት በማድረግ ተራራ እስኪያክል ድረስ ከመሩበት፡፡ በቀደመው በደላቸው ንስሐ መግባት ሲገባቸው በበደል ላይ በደል ይጨምሩ ነበር፡፡ ኾኖም የሰው ሐሳብ ጊዜአዊ ነውና ጊዜው ሲደርስ መስቀሉ የሚወጣበት ቀን ደረሰ፡፡ በመኾኑም ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር እንዲል ፫፻ ዓመታት አለፈና መፍቀሬ ሃይማኖት ቈስጦንጢኖስ ነገሠ፡፡ እግዚአብሔርም በቈስጠንጢኖስ ልብ ፍቅረ መስቀልን አሳደረ፡፡ በእናቱ በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነትም በ፫፻፳፯ ዓ.ም. ገደማ ተገኘ፡፡
 ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ለማግኘት አባ መቃርስና አረጋዊው ኪራኮስ እንዲሁም ቅዱስ ሚካኤል ባመላካቷት መሠረት ጸሎትና ምህላ አድርሳ ዕጣን የተጨመረበት ደመራን ያስደመረችው መስከረም ፲፮ ነበር፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ስላመለከታትም ቁፋሮ የዠመረችው መስከረም ፲፯ ነበር፡፡ በመጨረሻም መጋቢት ፲ መስቀሉ ተገኘ፡፡ ዛሬ ደመራን ደምረን መስከረም ፲፮ን የምናከብረው ቅድስት ዕሌኒ በኢየሩሳሌም ያሳነጸቻቸውን አብያተ ክርስቲያናት የተባረኩበት ቀን ስለኾ ነው፡፡ መስከረም ፲፯ ደግሞ መስቀሉ ገብቶ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበት ዕለት ነው፡፡
ምንም እንኳን መስቀሉ የተገኘው መጋቢት ዐሥር ቢኾንም ወርኃቱ ወርኃ ፆም ስለኾነና በዐቢይ ፆም ደግሞ ተድላና ደስታ ማድረግ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የተከለከለ ስለኾነ የመስቀሉ በዓል በአበው ውሳኔ ቁፋሮው በተዠመረበትና ቅዳሴ ቤቱ በተከበረበት መስከረም ፲፯ እንዲኾን ተደርጓል፡፡

 የመስቀሉ መገኘት ለዓለም ሕዝብ ኹሉ ደስታ ቢኾንም በሌላው ዓለም ደብዛው ጠፍቶ በሃገራችን ግን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቱን እንደጠበቀ አሁንም ይገኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ግማደ መስቀል እስከ አሁን አለ፤ የመስቀል ቅርጽ ባላት በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ገዳም፡፡
መስቀል በኢትዮጵያ
v መስቀልና ኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ ወዳጆች ናቸው፡፡
v  ሀገሪቱ ምዕራፈ መስቀል ልጆቿም የመስቀል ፍሬዎች ናቸው፡፡ በመኾኑም መስቀል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ታላቅ ክብር አለው፡፡
v ከእመቤታችን ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያን ስሙ የሚነሣው ቅዱስ መስቀሉ ነው፡፡ የመዠመሪያው የሥላሴ ስም ነው፡፡
v ቤተ ክርስቲያን ያለመስቀል አይተከልም፡፡
v ቅዱስ ዳዊት “ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን” ለቅዱስ መስቀል የጸጋ ስግደት ይቀርብለታል /መዝ.፻፴፩፡፯/፡፡
v ካህናቶቿ ኹሉ መስቀል ይይዛሉ፤ በቅዱስ መስቀሉ ይባረካሉ፤ ይባርካሉም፡፡
v የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በሙሉ መስቀል ይሳለማሉ፤ በትእምርተ መስቀል ያማትባሉ፤ በመስቀል ይባረካሉ፡፡
v ሰው ያልበላውን አያገሳም፡፡ በመኾኑም ምእመናን በመስቀሉ ላይ በተከፈለው ዋጋ ተገዝተዋልና በአንገታቸው ያስሩታል፡፡ በግንባራቸው፣ በደረታቸው፣ በክንዳቸው ይነቀሱታል፡፡ በአልባሳታቸው ይሥሉታል፤ ይሸለሙታል፡፡
v እንደ ዛሬው አያድርገውና ነገሥታቱ በገንዘባቸው፣ በበትረ መንግሥታቸው፣ በፈረስ ልጓማቸው ትእምርተ መስቀል ነበረ፡፡ ጌጥ አይደለም፤ ሃይማኖታዊ አርማ እንጂ፡፡ የአጼ ይሥሓቅ የደብዳቤያቸው ርእስ መስቀል ነበር፡፡ በላዩ ላይም ኢየሱስ የሚል ጽሑፍ ነበረበት፡፡
v የቤተ ክርስቲያኒቱ ንዋያተ ቅዱሳት አብዛኛዎቹ ባለመስቀል ናቸው፡፡
v መጋቢት ፲ና መስከረም ፲፯ ቀን የሚጠመቁ ልጆቿ (ቤተ ክርስቲያን) ገብረ መስቀል፣ ወልደ መስቀል፣ ብርሃነ መስቀል፣ ኃይለ መስቀል፣ ዐምደ መስቀል፣ ወለተ መስቀል፣ መስቀል ክብራ፣ መስቀል ኃይላ፣ መስቀል ሞገሳ፣ ወቦ ዘተርፈ እያለች ስመ ክርስትና ትሰጣቸዋለች፡፡
v ወሩ በገባ በ፲ የመስቀል በዓል ይታሰባል፡፡
v ከመስከረም ፲፮ እስከ መስከረም ፳፭ ዘመነ መስቀል ተብሎ ስለ ነገረ መስቀል ይነገራል፤ መዝሙረ መስቀልም ይዘመራል፡፡
  አንዳንድ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዕንጨት አምልኮትን የምታቀርብ የሚመስላቸው አሉ፤ ድሮም ነበሩ፡፡ “ለዕንጨት ትሰግዳላችሁን? በዓልስ ታደርጋላችሁን? ለሚሉን ኹሉ እኛም “አዎ! ዕፀ መስቀሉ የክርስቶስ ደም አልቀደሰውምን? ስለዚህ እኛ ለመስቀል የጸጋ ስግደት እንሰግድለታለን” ብለን ከቅዱስ ያሬድ ጋር እንመልስላቸዋለን /ድጓ ዘመስቀል/፡፡
በአጠቃላይ መስቀል በትንቢት የተነገረ፣ በኅብረ አምሳል የተመሰጠረ፣ በክርስቶስ ደም የከበረ፣ ቤዛነትንና ድኅነትን ስለተፈጸመበት እናከብረዋለን፡፡ “መስቀል ኃይላችን፣ መጠጊያችን፣ ሞገሳችን ነው” እያልን እንዘምረለታለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

መጽሐፈ ጤፉት ለኅትመት በቃች


አትም ኢሜይል
መስከረም 12 ቀን 2007 ዓ.ም.
መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ
a tefut 2007 1የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ግሸን ደብረ ከርቤ መቀመጡንና ሌሎችንም ታሪኮች ያያዘው መጽሐፈ ጤፉት በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት አማካይነት ከግእዝ ወደ አማርኛ ተተረጉማ ለኅትመት በቃች፡፡

መጸሐፉ በሰባት ምዕራፎች ተከፍሎ የቀረበ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ በዐፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት የነበረውን የግብጻውያንና የኢትዮጵያውያንን ግንኙነት የሚገልጽ ነው፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ በዐፄ ዳዊት አማካይነት ቅዱስ መስቀሉ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በዐፄ ዳዊት ግዛት ስለመቀመጡ ይናገራል፡፡

ሦስተኛው ምዕራፍ ስለ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብና ቅዱስ መስቀሉን ወደ መስቀለኛው የአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ ስለማስቀመጣቸው በስፋት ይገልጻል፡፡ ዐራተኛው ምዕራፍ ከቅዱስ መስቀሉና መስቀሉ ስለተቀመጠባት የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ደብር ክብር ጋር ተያይዞ በንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ የተጻፉት ደብዳቤዎችን አካትቷል፡፡

አምስተኛውና ስድስተኛው ምዕራፎች ግሸን ደብረ ከርቤ ጌታችን በተሰቀለበት በቅዱስ መስቀሉ መክበሩንና ለቦታው ስለተሰጠው ቃል ኪዳን ይዳስሳል፡፡ ሰባተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ መስቀሉ በክብር የተቀመጠበትን የግሸን ደብረ ከርቤ አምባና የአካባቢው ሹማምንት ስለተሰጣቸው ትእዛዛትና ሌሎችንም መረጃዎች ያብራራል፡፡

ሊቀ ሊቃውንት ተክለ ማርቆስ ብርሃኑ የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ደብር አስተዳዳሪ ስለ መጽሐፉ መታተም ሲገልጹ “መጽሐፈ ጤፉት ለበርካታ ዓመታት የቤተክርስቲያናችንን የታሪክ፣የቀኖና፣ የሥርዐትና ሌሎችም ሰነድ ይዛ በክብር ተጠብቃ የቆየችና በየዓመቱ በውስጧ የዘችው ቃልኪዳን እየተነበበ የኖረ ሲሆን አሁን ታትሞ ለምዕመናን እንዲደርስ መደረጉ የሀገርንና የቤተክርስቲያን ታሪክ አውቀን ሥርዐቱንና ቃል ኪዳኑን ጠብቀን ለቦታው የሚገባውን ክብር እንድንሰጥ ያስችላል፡፡” ብለዋል፡፡

a tefut 2007 2መጽሐፈ ጤፉት በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካይነት እንደተጻፈና በየዓመቱ፤ በተለይም በመስከረም 21 እና መጋቢት 10 ቀን የመስቀሉ አመጣጥና በግሸን ደብረ ከርቤ ስለተሰጠው ቃል ኪዳን በመተርጎም ለምእመናን ይሰማል፡፡

መጽሐፈ ጤፉትን ማግኘት የሚፈልጉ በግሸን ደብረ ከርቤና በአዲስ አበባ በ0911238610፣ 0911616880 በመደወል ማግኘት እንደሚቻል ከመጽሐፉ የኅትመት አስተባባሪዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...