የጠረፋማዋ ቤተ ክርስቲያን

                                                              
እግዚአብሔር በዘመነ ነቢያት ሰው ባጣበት ወቅት ከጠየቃቸው ጥያቄዎች አንዱ ይህ ነው፡፡ ይህ ድምጽ የተሰማው ሰዎች ከፍ ያለ ግምት በሚሰጧቸው ስፍራዎች አልነበረም፡፡ በከብቶች መሰማሪያ በእረኞች መዋያ በሜዳ እንጂ! "የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ" እንዲል፡፡ ኢሳ ፮፥፰። ይህንን ድምጽ እንዲሰማ የተደረገው ነቢዩ ኢሳይያስ የከብቶች እረኛ የነበረ እንጂ ሌላ ማኅበራዊ ኃላፊነት ያለበት ወይም የተጣለበት አልነበረም፡፡
እግዚአብሔር ሥራ ለመሥራት በምድራዊ መዋቅር ትብትብ ውስጥ አይሄድም፡፡ በቀጥታ ተልእኮውን እንዲያስፈጽም የመደበውን ያነጋግራል፣ ያነቃል፣ ይልካል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስን ለዚህ ጥሪ ሲያዘጋጀው በመጀመሪያ በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ታየው፡፡ ኢሳ ፮፥፩። በመቀጠልም በለምጽ ነድዶ የነበረውን ከንፈሩን መልአኩን ልኮ ፈወሰው፡፡ እንዲህ አድርጎ ካዘጋጀው በኋላ የምሥጢረ መንግሥቱ ተካፋይ ይኾን ዘንድ "ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?" የሚለውን ድምጹን አሰማው፡፡
በምድራዊ መስፈርት እና ቁመና በጊዜው ከብት ጠባቂ ከነበረው ከአሞጽ ልጅ ከኢሳይያስ የተሻሉ ሰዎች ጠፍተው አልነበረም፡፡ እነርሱ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አልተመረጡም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራው በደካሞች አድሮ ነው፡፡ አገር ሲያንቀጠቅጥ መሬት ሲያርድ የነበረውን ጎልያድን ለመጣል አንዲት ጠጠር፣ አንዲት ወንጭፍ እና የአሥራ ሁለት ዓመት ብላቴና ቅዱስ ዳዊት በቂ ነበሩ፡፡ ከራስ ጠጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው የታጠቁ ስንት የጦር ስልት የተማሩ ባለ ፈርጣማ ጡንቻ ወታደሮች እያሉ እግዚአብሔር ድሉን በብላቴናው በዳዊት በኩል አደረገው፡፡
ለአራት መቶ ሠላሳ ዘመን ፈርዖናዊው ጽኑ አገዛዝ በእጁ ጭብጥ በእግሩ እርግጥ አድርጎ እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ ሲገዛው የኖረውን ሕዝበ እሥራኤል ነፃ ለማውጣት እግዚአብሔር የመረጠው መሪ በእረኝነት የኢትዮጵያውያንን በግ ሲጠብቅ የነበረውን ሊቀ ነቢያት ሙሴን ነው፡፡ ዓሣ አጥማጅ የነበሩትን ቅዱሳን ሐዋርያት ለእንዴት ያለ ክብር እንደጠራቸው ስናይ፣ ዘማ የነበረችውን መግደላዊት ማርያም ደግሞም ሌላኛዋን በተመሳሳይ ሁኔታ የነበረችውን ማርያም እንተ እፍረትን ስናይ እግዚአብሔር በተናቁት አድሮ የሚሠራው ሥራ ዕጹብ ድንቅ የሚያስብል ነው፡፡
ዛሬም በእኛ ዘመን በደቡብ ኦሞ እግዚአብሔር እየሠራ ያለው ሥራ ዐዋቂ ነን ብለው የተኮፈሱትን የሚያሳፍር፣ ነገር ግን ለሥራው የሚመቹትን መርጦ፣ ቀስቅሶ እና አነቃቅቶ በሚያስደምም ሁኔታ አዲስ ታሪክ እየጻፈ መኾኑን ልብ ያለው ልብ ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? የሚለውን ጥሪውን ሲያሰማ እንደ ነቢየ ልዑል ኢሳይስ "እነሆኝ እኔ አለሁ" የሚል ፈቃደኝነት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ይህ አገልግሎት እንደዚህ ያሉ ቅን እና ፈቃደኛ አገልጋዮችን ይፈልጋል፡፡
እንዴት ልንሄድ እንችላለን? እኛ ኑሮ አለን፣ ሥራ አለን፣ ልጆች አሉን. . . ወዘተ የሚለው ጥያቄ መመላለሱ አይቀርም፡፡ ግን ባለንበት ኾነን የምንሄድበትን እግዚአብሔር ካመቻቸስ? በአካል መገኘት ያለባቸውን እግዚአብሔር ከያሉበት ቀስቅሶ ሥራ እያሠራቸው ነው፡፡ ቤታቸውን፣ ሥራቸውን፣ ኑሯቸውን ለመተው የማያመነቱ ለቁርጠኛ ተጋድሎ የወሠኑ ልጆቹን እግዚአብሔር እዚያው በሀገሩ አዘጋጅቶ እየሠራ ነው፡፡ ዐይኖቻችን ዐይተዋልና ምስክሮች ነን፡፡ እነርሱ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ለሚለው ምላሽ አላቸው፡፡
እርስዎስ? ለዚህ መልስ መስጠት እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ የምላሽዎ መንገዶች ከሚከተሉት መካከል አንዱ ወይም ሁለቱ ወይመ ከዚያ በላይ ሊኾን ይችላል፡፡
፩. ጉዳዩን ለሌሎች ማጋራት
እገሌ ወእገሌ ሳይባል በሀብት በደመወዝ በዕድሜ በኑሮ በርቀት የማይወሰን ሁሉም ሊያደርገው የሚችል አስተዋጽኦ፡፡ ለዚህ መስነፍ ወይም ሌሎች የሚቀድሙ አጀንዳዎች አሉብኝ ብሎ ሳይናገሩ መቅረት አይገባም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ራሳቸው ከጀመሩት ሌላ አገልግሎት ጋር የሚጋጭ የሚመስላቸው ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያሠማራው እንደ ውስጥ ስሜታቸው ነውና ያም ይህም የጋራ ሥራ ነውና ጥቂት ዕድል ሊነፍጉት አይገባም፡፡ ይህ በራሱ ለመላክ መፍቀድ ነውና!
፪. በሚችሉት መደገፍ
እንደዚህ ሲባል ሁሉም ሰው የሚችለው ጉዳይ አለ ለማለት ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በሀሳብ መርዳት ነው፡፡ ለምሳሌ ትዕዛዙ ባይሌ የተባለ ወንድማችን በሚኖርበት የውጭ ሀገር ኾኖ ጉዳዩን በገጸ ጦማሬ ሲከታተል አንድ በጎ ነገር ብልጭ አደረገ፡፡ እርሱም እንዲህ አለ "እኛ በውጭ የምንኖር ሰዎች በቀላሉ ለመርዳት የምንችልበትን ዘዴ ብናመቻች"፡፡ እኔም ሀሳቡ ሠናይ እንደኾነ ተስማማሁ፡፡ "gofundme" በሚባል ድረ ገጽ መረዳዳት ቀላል እንደኾነ ተረዳሁ፡፡ አንድ ሸክም በትዕዛዙ ላይ እንደጫንሁበት ተሰማኝ፡፡ በተለይ ከግብር ጋር ተያይዞ የሚነሣበትን ጥያቄ ስረዳ! እርሱ ግን ግዴለም መሸከም አለብኝ ስላለኝ ደስ አለኝ፡፡
የዚህ ገጸ ድር ጥቅሙ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች ከአንድ ዶላር ጀምሮ ወደ አንድ ቦታ መላክ መቻላቸው ነው፡፡ ሲፈልጉ ስማቸውን ሳይጠቅሱ ሲያሻቸው ስማቸውን ሳይጠቅሱ እጃቸውን ለመዘርጋት የተመቸ መንገድ ነው፡፡ በዚህም እስካሁን በስድስት ቀናት ውስጥ ይህችን ጦማር እስከለጠፉሁባት ሰከንድ ድረስ ፮፻፵፩ /ስድስት መቶ አርባ አንድ/ ሰዎች መረጃውን ያዳረሱት /share/ ያደረጉት ሲኾን ፲፯ ሰዎች ደግሞ ከ፭ እስከ ፪፻ ዶላር ለግሰዋል፡፡
እነ ኅሊና መኮንን፣ ያሬድ አራጋው፣ ብንያም ኃይሌ፣ መንገሻ አስፋው፣ ማኂ ማኂ፣ ተስፋ ሥላሴ ጠብቀው፣ ዓለምየ ገብረመድኅን፣ ቡሩክ ተክሉ፣ አስናቀ ኃይሌ፣ ሰሎሜ ካህሣይ በስም የተጠቀሱት ሲኾኑ ሌሎች ፯ቱ ደግሞ ስማቸውን አልነገሩንም፡፡ እነዚህ ሰዎች አስካሁን ፩ሺ፷፭ /አንድ ሺህ ስልሳ አምስት/ ዶላር አስገብተዋል፡፡ ይህ በቀላሉ ለመላክ ፈቃደኛ በኾኑ ሰዎች ለዚሁ አገልግሎት ባሉበት ሳይንቀሳቀሱ የመሠማራት መንገድ ነው፡፡
በሀገር ውስጥ ያሉ ሰዎችም ብዙዎች ስማቸውን ሳይጠቅሱ እየላኩ ሲኾን እንደ ሚካኤል አበበ ያሉ ክርስቲያኖች እስከ ብር ፭ ሺህ በተከፈተው የባንክ አድራሻ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሂደት የተሰበሰበውን ገንዘብ እና ለምን አገልግሎት እንደዋለ በዝርዝር አሳውቃለሁ፡፡ የጂንካ ማዕከልም ጉዳዩን በደስታ ተቀብሎ እያስተናገደው መኾኑን ተረድቻለሁ፡፡ ካሉበት ሳይነቃነቁ ለእግዚአብሔር መላክም እንዲህ ይቻላል፡፡ ለእኔ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ከስብከተ ወንጌል የሚቀድም አንዳች ነገር የለም፡፡ ሌላው ሁሉ ስብከተ ወንጌልን ተከትሎ የሚሠራ እንጂ ነው፡፡
ለዚህ የመላክ አገልግሎት በስፍራው የሚጋደሉት እኅቶች እና ወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን በጥቂቱ በዓይነት ለመዘርዘር ያኽል፡-
ጫካውን አቆራርጠው እስከ ጫፍ ድረስ ለመድረስ ሞተር ብስክሌት፣ በሄዱበት ደርሰው ቃለ እግዚአብሔሩን ለማሰማት ቢቻል በፀሐይ ኃይል የሚሠራ ድምጽ ማጉሊያ ካልኾነም በባትሪ ድንጋይ የሚሠራ ሊኾን ይችላል፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምሮ ሌሎች የማስተማሪያ እና የጸሎት መጻሕፍት፣ ብርድ ልብስ፣ ፍራሽ፣ አንሶላ፣ ቀለብ፣ ደብትር፣ እስክርቢቶ. . . ወዘተ፡፡
የገጸ ጦማር ወዳጆቼ የኾናችሁ በተቻላችሁ ሁሉ ይህንን መልእክት እያስተላለፋችሁ የራሳችሁንም ድርሻ እየተወጣችሁ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ለሚለው ለሥሉስ ቅዱስ ጥያቄ ራሳችሁን በፈቃደኝንት ታቀርቡ ዘንድ መንፈሳዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ከወንጌል የሚቀድም የለም እና ስለወንጌል ጥሪ በማቅረቤ ደስ ይለኛል፡፡
ይለግሱ . . . መረጃውን ያዳርሱ!
እነሆ የባንክ አድራሻ
በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማዕከል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ
የሂሳብ ቁጥር፡ 1000139696038
ስዊፍት ኮድ: CBETETAA
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጂንካ ጌሽ ቅርንጫፍTizazu Bayile በአረብ አገራት ያላችሁ ወንድሞችና እህቶች ማስተር/ክሬዲት ካርድ ካላችሁ እስኪ ይሄን ሊንክ ክፈቱና ያላችሁበትን አገር ፈልጉትhttps://www.gofundme.com/TewahidoInGambela/donate