2014 ኦገስት 15, ዓርብ

ደብረ ታቦርና ቡሄ



አትም ኢሜይል
 ነሐሴ 5 ቀን 2006 ዓ.ም.
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት አንዱ የደብረ ታቦር በዓል ነው። በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የሚከበረው ይህ በዓል መሠረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ደብረ ታቦር ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደ ፀሐይ የበራበት፣ ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት፣ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው።
ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር።

ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና፡ ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ማቴ. ፲፯፡፩-፭ በቤተ ክርስቲያን ደብረታቦር ከቤተክርስቲያን ውጭ አከባበሩ ቡሄ እየተባለ የሚከበረው በዓል በሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡ ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፣ ወደ መፀው የሚዘለቅበት ወገግታ ፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፣ የሚሸጋገርበት ወቅት በመሆኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ በዚህ መሰረት የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታየውም በዚህ በዓል አካባቢ ስለሆነ ይቺ ዕለት 'ቡሄ' የሚለውን ስያሜ አገኘ። ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት፣ ብረሃን የታየበት ድምጸ መለኮት የተሰማበት ስለሆነ፤ ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓልም ይባላል፡፡

በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ ይሰነብታሉ። እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ። መነሻ የሆናቸው ትውፊት ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ እረኞችም ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል ፡፡ያንን ለማስታወስ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የሚከበረው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ የንጋት ወጋገን ሲፈናጠቅ ልጆች በከባድ ድምጽና በጅራፍ ጩኸት የሚታጀብ፣ በገደላገደል ስር እንዲያስተጋባ ተደርጎ ብዛት ባላቸው ህጻናት በከፍተኛ ድምጽ የሚዘመር ነው ቡሄ ። የጅራፉ ጩኸትም እግዚአብሔር አብ “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ሲል ሐዋርያት ራሳቸውን ስተው የወደቁበትን የመለኮት ድምፅ ለማስታወስ ነው፡፡

ደብረታቦር ወይም ቡሄ በአብነት ተማሪዎች “ስለ ደብረ ታቦር" እያሉ እህል፣ ፣ ጌሾ ለምነው ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምዕመናን በመጋበዝ በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡ ይህ ትውፊት መምህረ ሐዋርያት የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ይዞ ሄዶ የተገለጠ ምስጢር ስለሆነ ከመምህራቸው ጋር በመሆን በዓለ ደብረ ታቦርን /ቡሄን ያከብራሉ፡፡ ስሙን ይጠራሉ፡፡
የደብረ ታቦር ወይም የቡሄ ግጥሞች
ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና
ያዕቆብ ዮሃንስ ሆ! እንዲሁም ጴጥሮስ
አምላክን አዩት ሆ! ሙሴ ኤልያስ
አባቱም አለ ሆ! ልጄን ስሙት
ቃሌ ነውና ሆ! የወለለድኩት
ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና።
መጣና መጣና ደጅ ልንጥና
መጣና ባመቱ እንዴት ሰነበቱ፣
ክፈት በለዉ በሩን የጌታዪን
ክፈት በለዉ ተነሳ ያንን አንበሳ፣
የመሳሰሉት

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...