2014 ኖቬምበር 6, ሐሙስ

አሁን እንኳን እንንቃ! . . የተሐድሶ መናፍቃን ስውር ሴራ (VCD No 2)

  • «ኦርቶዶክስ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ ነገር ግን የተጫኑባት ገለባዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ተሐድሶ ያስፈልጋታል፤ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን መመለስ አለብን»
  • «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስሕተት ናት፤ ትክክል አይደለችም»
  • ባለአደራዎች የሆኑ ብፁዓን አባቶቻችን ዛሬም ታላቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አንዱ ስልት በአባቶችና በልጆች መካከል መለያየትን መዝራት እንደሆነ ልብ ሊሉት ይገባል
  • የተሐድሶ ኑፋቄው ያልተቋረጠ ጥቃት ዋነኛ ዓላማ፤ ምእመናንን ከእናት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ በማስኰብለል የበግ ለምድ ለለበሰ ተኩላ አሳልፎ መስጠት ነው
ውድ የቤተክርስቲያን የስስት ልጆች ሆይ፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተነገረው ቤተክርስቲያናችንን ለመውረስ ረቀቅ ያለ ዘዴ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ያሉት መናፍቃን የእኛው በሆኑ ግን ለሆዳቸው ባደሩ ጥቂት የማይባሉ ባንዳዎች ሰርገው በመግባት በርካታ ጥፋት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሲነቃባቸውም “ተሀድሶ የለም” እያሉ የዋሁን ህዝብ ሊያታልሉ ይሞክራሉ፤ ስለዚህ እኛ ልጆቿ ልጅነታችንን በምግባራችን ልናረጋግጥና በቃችሁ ብለን ልናስቆማቸው ይገባል፡፡ ይህ ቪድዮ እውነታውን አውቀን እንድንጠነቀቅ በማህበረ ቅዱሳን የተዘጋጀና 4 ክፍሎች ያሉት ሲሆን በመመልከትና ላላዩት እንዲያዩት share በማድረግ እናታችን የምትጠብቅብንን ሀላፊነት እንድንወጣ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት አይለየን፡፡

ስለ ቤተክርስቲያን ካሰቡ ያንቡት ምስሉንም ይመልከቱና የራስዎን ሃላፊነት ብቻ ይወጡ

የተሐድሶ መናፍቃን ስውር ሴራ ክፍል 1

(ስምዐ ጽድቅ ሚያዝያ 1-15 2003 ዓ.ም)  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈቻቸው ዘመናት ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም፡፡ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎቷን በመፈጸም ያለፈችባቸው ዘመናት በፈተናዎች የታጀቡ ናቸው፡፡ የፈተናው ዓይነትና መጠን፣ ጠባይና መገለጫው እንደየጊዜና ሁኔታው እየተፈራረቀባት፤ በቅዱሳን ሰማዕትነት፣ በሊቃውንት መምህራኗ፣ በአባቶች ካህናቷ፣ በአገልጋዮቿ ተጋድሎ ልጆቿ እየተጠብቁ በመሠረቷ ጸንታ ትገኛለች፡፡

የተሐድሶ መናፍቃን ስውር ሴራ ክፍል 2



የተሐድሶ መናፍቃን ስውር ሴራ ክፍል 3


የተሐድሶ መናፍቃን ስውር ሴራ ክፍል 4





አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚያደርሱባት ጥቃት ግፊትና ተፅዕኖ አሁንም ሌላው ፈተና ነው፡፡ ከዚህ ቀደም «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስሕተት ናት፤ ትክክል አይደለችም» በማለት ከውጪ ሆነው ምእመናንን በማጠራጠርና ግራ በማጋባት ሲያስኰበልሉ የነበረው ጥረታቸው እንዳልተሳካ ተረዱት፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያኒቷን ሙሉ በሙሉ ለማዳከምና ሐዋርያዊ ተልእኮዋም ተደናቅፎ ሕልውናዋን ለማሳጣት ለዘመናት የደከሙት ድካም ከግብ እንዳልደረሰ ሲገነዘቡት የተለየ ስልት ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

ትምህርተ ሃይማኖቷ እምነቷና ሥርዐቷ ምሉዕ የሆነውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ርትዕት ሃይማኖት «እናድሳለን» በሚል ስልት ወደ ውስጧ ሠርጐ በመግባት ልጆቿን እስከ ሕንፃ ቤተክርስቲያኗ እንረከባለን ይላሉ፡፡

የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎቻቸውን በማሰማራት በጎቿን በኑፋቄያቸው እያሳሳቱ ከመንጠቅ፣ በተለያዩ ርዳታዎች ስም እየደለሉ ከማስኰብለል ጀምሮ፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዐቷን በማጣጣል፣ ቅዱሳት መጻሕፍቷን በማራከስ፣ መልካም ስምና ገጽታዋን በማጠልሸት የሚያደርጉት የጥፋት ጥረታቸው ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ በእናትነት እቅፏ ውስጥ ጡቷን ጠብተው ማዕዷን ተሳትፈው አድገው፤ ነገር ግን ንጹሕ እናትነቷን ክደው በውስጧ ሆነው በኑፋቄያቸው የሚቦረቡሯት ብዙዎች ናቸው፡፡

የተሐድሶ መናፍቃኑ እንቅስቃሴ፤ ቤተ ክርስቲያንን ለመለወጥ ወራጁ ውኃ ላይ ሳይሆን ምንጩ ላይ መሥራት ነው፤ በሚል ስልት፤ ምንጮች ናቸው የሚሉትን በመለየት ስስ ብልቶች ያሏቸውን መርጠው እየሠሩ ነው፡፡ በእነርሱ አባባል፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወራጁ ውኃ ምእመናን ሕዝበ ክርስቲያኑ፤ ምንጮች ደግሞ፤ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ለማሳካት የዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎቶቿ መሠረቶች የሆኑት፤ ገዳማትና አድባራቷ፣ የሊቃውንቷ፣ አገልጋይ ካህናቷና መምህራነ ወንጌሏ መፍለቂያዎች የሆኑት አብነት ትምህርት ቤቶች፣ መንፈሳዊ ኰሌጆቿ፣ የካህናት ማሠልጠኛዎቿ፣ መምህራኑና ደቀመዛሙርቱ፣ በየደረጃው የሚገኘው የቤተክህነት አስተዳደር ነው፡፡ ሰንበት ት/ቤቶች፣ መንፈሳውያን ማኅበራትና ጽዋ ማኅበራት ሁሉ የዚህ ስልታቸው ማስፈጸሚያ ዒላማዎቻቸው ናቸው፡፡

በእነዚህ ምንጮች ውስጥ ኦርቶዶክሳዊ መስለው ሠርገው እየገቡ፣ ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ሆነው በመታየት፣ በመዋቅሯ ውስጥ ቦታ እየያዙ የተሠወረ ሤራቸውን በስልት ለማስፈጸም ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ቀስ በቀስ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዐት፣ መዋቅራዊ አሠራርና መመሪያ እየጣሱ የትምህርት ጉባኤያቱን ኦርቶዶክሳዊ ላህይና ይዘታቸውን እየቀየሩ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በዐደባባይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን «አሮጊቷ ሣራ መታደስ መለወጥ አለባት» እያሉ ሲያውኳት እንዳልቆዩና ለይቶላቸው እንዳልወጡ ሁሉ፤ አሁን ደግሞ በውስጧ ሆነው ተቆርቋሪ መስለው፤ «ኦርቶዶክስ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ ነገር ግን የተጫኑባት ገለባዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ተሐድሶ ያስፈልጋታል፤ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን መመለስ አለብን» እያሉ በ«ምናለበት» ስብከት እየደለሉ በማታለል ለሃይማኖቱ ግድ የለሽ ምእመን ለመፍጠር ይተጋሉ፡፡

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ ነገረ ማርያም፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት... ወዘተ እንዲነሣባቸው አይፈልጉም፡፡ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ማስተማር ለሕይወት የማይጠቅም እንደሆነ በመቀስቀስ ከምእመናን ዘንድ ማስረሳትና ሳያውቀው ለተሐድሶ ኑፋቄ ቅሰጣና የስሕተት ትምህርት ልቡን በመስጠት ተገዢ የሆነ ትውልድ መፍጠር በገሀድ የሚታይ ጥረታቸው አካል ነው፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ በአባቶቹ ላይ ያለው እምነትና ተስፋ እንዲሸረሸር፣ አሠረ ክህነቱን፣ ሥርዐተ ምንኩስናን፣ የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደር እንዲጠላ በዚያው ተገፍቶ ጭራሹን ከቤተ ክርስቲያን እቅፍ እንዲወጣ ወይም እንዲኰበልል ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ይሠራሉ፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፤ የዶግማና ሥርዐቷን ድንበር ለማጥፋት፤ መዋቅራዊ የአሠራር ሥርዐቷንና መመሪያዋን በድፍረት እስከመጣስ እየደረሱ ይታያል፡፡ እነዚህን ሁሉ የስሕተት ትምህርቶቻቸውን ለማሠራጨት፤ አድራሻና ባለቤት በሌላቸው የኅትመት ውጤቶች፤ መጻሕፍት፣ በራሪ ወረቀቶች ፣ የድምፅ ወይም የምስል ወድምፅ ካሴቶች ጭምር ይጠቀማሉ፡፡

ይህ የተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ ከግለሰብ ወደ ቡድን፣ ከቡድን ወደ ማኅበር ወይም ድርጅት ከዚያም ወደ ብዙ ድርጅቶች እያደገ መጥቷል፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማደናቀፍና መንፈሳዊ አገልግሎቷን በማወክ ልጆቿንም ለማስኰብለል የሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ ነው፡፡

በሕገ መንግሥታዊው ሥርዐታችን አንድ ዜጋ የፈለገውን እምነት የመከተል መብቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እና ሽፋን በውስጧ ሆኖ እምነቷን፣ ሥርዐትና ትውፊቷን መጣስ እንዲሁም ከመመሪያዋ ውጪ መንፈሳዊ አገልግሎቷን ማወክ፣ ምእመናኗን እያሳሳቱ ማስኰብለል ሕጋዊ ተግባር እንዳልሆነ ሁሉም የሚገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የተሐድሶ ኑፋቄን ሤራ ምንነትና ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት በትክክል መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በክርስቶስ ደም ተመሥርታ በእግዚአብሔር ቸርነት በቀደሙት ቅዱሳን አባቶች መንፈሳዊ ተጋድሎ እዚህ የደረሰች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለአደራዎች የሆኑ ብፁዓን አባቶቻችን ዛሬም ታላቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አንዱ ስልት በአባቶችና በልጆች መካከል መለያየትን መዝራት እንደሆነ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሸሽገው መዋቅሯን ሽፋን አድርገውም ሆነ መልካም ስሟን እየተጠቀሙ ነገር ግን በስውር ተልእኮ ሤራቸውን ለማስፈጸም ቀን ከሌሊት እየተጉ ላሉት አመቺ የሆኑ ክፍተቶችን በጥንቃቄ መድፈን አለባቸው፡፡ በማናቸውም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች የቅዱስ ሲኖዶስን መንፈሳዊ ልዕልናና ሓላፊነት ማስከበር፣ ውሳኔዎቹን ማስፈጸም፣ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ አሠራርና መመሪያዎች ተግባራዊነት መከታተል፣ ውጤታማ ማእከላዊ አሠራርን ማስፈን ይገባል፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዋና ሕግጋቷ ተጠብቆ ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎቷ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን በቁርጠኛነት መቆም አለባቸው፡፡በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሊቃውንትና አገልጋዮች፤ ቆሞሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ዘማርያን ሁሉ፤ በውጭም ሆነ በውስጥ ተደራጅቶ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ልጆች ምእመናንን ለመበተን ያለመታከት እየሠራ ያለውን የተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ ለመግታት ሃይማኖታዊ አደራና ሓላፊነታቸውን ለመወጣት መንቃት ይገባቸዋል፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጣው የተሐድሶ ሤራ አይመለከተኝም ወይም አላውቀውም በሚል ተገልለን የምንቆይበት ጉዳይ አይደለም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ፣ በጾም በጸሎት በመትጋት፤ ምእመናንን መጠበቅ፣ ትምህርተ ሃይማኖቷን ስብከተ ወንጌልን ጠንክሮ ማስተማር፣ ሥርዐቷን፣ ትውፊቷንና ታሪኳን ምእመናን በሚገባ እንዲረዱት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የሰበካ ጉባኤያቱን እንቅስቃሴና አደረጃጀት፣ የሰንበት ት/ቤቶችን የዕለት ተዕለት አገልግሎትና ሒደት መከታተል፤ የገዳማትና አድባራቱን እንቅስቃሴ በቅርብ ማወቅ፤ የአብነት ት/ቤቶቻችንን ሁኔታ ድክመትና ጥንካሬ መገንዘብ፣ ለሚፈጠሩ ችግሮች በሚመለከታቸው የቤተክርስቲያኒቱ አካላትም ሆነ በየሐላፊነት ደረጃቸው መጠን በወቅቱ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ሰንበት ት/ቤቶቻችንና የዓውደ ምሕረት ጉባኤያትን ማጠናከር ስብከተ ወንጌሉን ማስፋፋት ቀሳጮች ገብተው ስውር ተልእኰአቸውን ለማስፈጸም እንዳይጠቀሙበትና ጉዳት እንዳያስከትሉ በቅርብ መቆጣጠር ተገቢ ነው፡፡

የቤተክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመደገፍና ለማጠናከር ሥርዐቷንና መመሪያዋን አክብረው የተቋቋሙ መንፈሳውያን ማኅበራት ለዚህ የተሐድሶ ኑፋቄ እንቅስቃሴ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሰለባ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ አባላቱ ለዚህ የቅሰጣ ተግባር እንዳይጋለጡ መከታተል፣ በትምህርተ ሃይማኖት የሚጠነክሩበትንና በመንፈሳዊ ሕይወት የሚያድጉበትን መንገድ ማመቻችትና ጠንክሮ መሥራት አለባቸው፡፡ ጽዋ ማኅበራትም የተሐድሶ ኑፋቄው ስውር ተልእኮ ዒላማ መሆናቸውን ተገንዝበው የትምህርት ሥርዐታቸውንና የአገልግሎት ሒደታቸውን ሁሉ፤ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐት፣ በአባቶች ትክክለኛ ትምህርትና የቅርብ ክትትል መሠረት እንዲያከናውኑ ያስፈልጋል፡፡

የተሐድሶ ኑፋቄው ያልተቋረጠ ጥቃት ዋነኛ ዓላማ፤ ምእመናንን ከእናት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ በማስኰብለል የበግ ለምድ ለለበሰ ተኩላ አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ለማሳጣት በሚደረገው የጥፋት ተልእኮ ማሰለፍ ነው፡፡ ምእመናን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እናታቸውን ለተሐድሶ ኑፋቄ ሤራ አሳልፈው ላለመስጠት ወይም ሕልውናዋን ለማሳጣት በሚደረገው የጠላት ሤራ ላለመሰለፍ መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ የቅድስት ቤተክርስቲያናቸውን ትክክለኛ ድምፅ በጥንቃቄ ለይተው በመገንዘብ በእምነታቸው ጸንተው ሊቆሙ ይገባል፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ከተሐድሶ ኑፋቄ ሤራና የጥፋት ተልእኮ መጠበቅ፣ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ጸንተን መገኘት የሁላችንም ሓላፊነት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ከተጠያቂነት ለመዳን እንንቃ፡፡


እንደ እግዚሐብሔር መልካም ፍቃድ ማህበረ ቅዱሳን በተሐድሶ ዙሪያ ያዘጋጀውን ‹‹የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተክርስትያ ላይ›› መፅሀፍ ስካን አድርገን በpdf መልክ መፅሀፉን አግኝተው ማንበብ ላልቻሉ ሰዎች ራሳቸውን ፤ ቤተሰባቸውን እና ቤተክርስትያንን ነቅተው እንዲጠብቁ ብሎጋችን ላይ post አድርገነዋል ፡፡



አርዕስት፡-‹‹የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተክርስትያ ላይ››


አዘጋጅ፡- የማህበረ ቅዱሳን ዶክመንቴሽን ክፍል
የታተመበት ጊዜ፡- ሚያዚያ 2003
የገፅ ብዛት:- 103
Soft Copy Size:- 20 MB
ዋጋ:- 15 ብር

 ‹‹እኛ ይህን መፅሀፍ እርስዎ ጋር በማድረስ ሀላፊነታችንን ተወጥተናል እርስዎ ላላነበቡት እንዲያነቡት በማድረግ ሃላፊነትዎን ይወጡ፡፡››

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

‹‹ሀሰት አንናገር እውነትን አንደብቅም››
 

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...