2015 ፌብሩዋሪ 20, ዓርብ

ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ መዝ.88-3

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍተኛ ክብር ትሰጣለች፡፡ ክብሯ ልዕልናዋን ዘውትር በጸሎት፣በምስጋና ትጠራለች፡፡በስሟ በዓላትን ታከብራለች፡፡አጽዋማትን በሰሟ ስይማ ልጆቿ እንዲጾሙ ታረድጋለች፡፡ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ እርሷ የነበራትን የድኅነት ተሳትፎና ቃልኪዳን ትዘክራለች፡፡ በስሟ ጽላት ቀርጻ፣ቤተክርስቲያን ሰይማ፣በስዓላት፣ በመጻሕፍት አማለጅነቷን ክብሯን ለልጅ ልጅ ታስተላልፋለች፡፡
ከስሟ ጋር ዘርፍ /ቅጽል/ በማድረግ ንጽሕናዋን፣ ቅድስናዋን፣ ድንግልናዋን፣ ወዘተ ይወሳል ፣ይጣራል፣ይጸለያል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመስጥረው ከተረጐሙት መካከል፡- ምልዕተ ጸጋ፡- እግዚአብሔር አባታችን አዳምን ከፍጥረት ሁሉ አልቆ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮት ነበር፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ምክንያት የተሰጠው ሙሉ ጸጋ ተገፈፈ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍጥረት ሁሉ ተመርጣ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ እግዚአብሔር የጠበቃት፣ ያደረባት «የከተመባት ረቂቅ ከተማ» መሆኗን መልአኩ በመሰከረበት ቃል «ምልዕተ ጸጋ» እያልን እንጠራታለን፡፡ ሉቃ.1-26፡፡ እመቤታችን የተለየች ናትና «ጸጋ የሞላብሽ» /የጸጋ ግምጃ ቤት/ ተብላለች፡፡
እምነ ጽዮን፡- እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስን አባት «አባታችን ሆይ» ብለን እንደምንጠራው ሁሉ ወላዲተ አምላክንም እናታችን ብለን እንጠራታለን፡፡ ማቴ.6-9፡፡ ቅዱስ ዳዊትም «እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፡ ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል» በማለት እመቤታችን አማናዊት ጽዮን መሆኗን አስረድቷል፡፡ መዝ.86-5፡፡ እምነ ጽዮን ማለት እናታችን ጽዮን ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያይቱ የሰው ልጆች ሁሉ እናት ሔዋን አማካኝነት ከርስታችን ወጥተን መጠጊያ አጥተን ነበር በዳግማዊቱ ሔዋን በድንግል ማርያም ደግሞ ወደ ርስታችን ተመልሰናልና እናታችን ጽዮን እንላታለን፡፡ ጽዮን ማለት አንባ መጠጊያ ማለት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስም ድንግል ማርያምን ጽዮን በማለት ይጠራታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት «እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና ማደሪያውም ትሆን ዘንድ ወድዶአታልና እንዲህ ብሎ ይህች የዘላለም ማደሪያዬ ናትና በዚህች አድራለሁ፡፡» መዝ.131-13፡፡ በማለት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ልዑል እግዚአብሔር ከሴቶች ሁሉ ለይቶ ድንግል ማርያምን ለእናትነት የመረጣት መሆኑንና ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ የወደዳት መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ መዝ.47-12፤86-5፡፡
መድኃኒታችን በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ በመስቀሉ ላይ ሳለ ለፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ «እነኋት እናትህ» በማለት በደቀ መዝሙሩ አማካኝነት እናቱን ድንግል ማርያምን ሥጋውን ለቆረሰላቸው ደሙን ላፈሰሰላቸው ምእመናን እናት ትሆን ዘንድ ሰጥቷታልና ፡፡ ጽዮን የድንግል ማርያም ስም ነውና ጌታችን እናት አድርጎ የሰጠንን እመቤት እምነ ጽዮን /እናታችን ጽዮን/ እንለታለን፡፡
እመ ብርሃን፡- እመ ብርሃን ማለት የብርሃን እናት ማለት ነው፡፡ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» ያለውን ብርሃነ ዓለም /የዓለም ብርሃን/ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን የወለደች ናትና የብርሃን እናቱ /እመ ብርሃን/ ትባላለች፡፡ ዮሐ.8-22፡፡ ጌታውን ይወድድ የነበረና ጌታውም ይወደው የነበረ የከበረ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ዮሐንስ «ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡» በማለት የመሰከረለትን ጌታ በብሥራተ መልአክ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አማናዊውን /እውነተኛውን/ ብርሃን ጌታችንን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጸንሳ የወለደች በመሆኗ እመ ብርሃን እንላታለን፡፡ ሊቁ «እመ ብርሃን አንቲ ነዓብየኪ በስብሐት ወበውዳሴ፡- አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ የብርሃን እናት ነሽና አንቺን በክብር በምስጋና እናገንሻለን» በማለት እንዳመሰገናት፡፡
ሰአሊተ ምሕረት፡- ሰዓሊተ ምሕረት ማለት ምሕረትን የምትለምን ማለት ነው፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ምስክርነት እንደምናገኘው ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘች እመቤት ናትና ልመናዋ /ምልጃ ጸሎቷ/ ይሰማል የእናት ልመና አንገት አያስቀልስ ፊት አያስመልስ ነውና፡፡ ሉቃ.1-30፡፡
በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኙ ቅዱሳን ምሕረት ቸርነትን ለምነው አግኝተዋል፡፡ ዘፍ.18-3፣ 23-32፡፡ እግዚአብሔር ሙሴን በፊቴ ሞገስን ስላገኘህ በስምህ ስላወቅሁህ ስለ ሕዝቡ የለመንኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ ብሎታል፡፡ ዘጸ.33-12-20፡፡ «ስለ ሙሴ ቃልም ዘወትር ለሕዝቡ ይራራላቸው ነበር» ዘጸ.32-11-14፡፡ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ በለመነ ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ ይለው ነበር፡፡ ዘኁ.14-20፡፡ በመልአከ ብሥራት በቅዱስ ገብርኤል «በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻል» ተብሎ የተመሰከረላት ድንግል ማርያም የተሰጣት ሞገስ እንደ እናትነቷ ከሁሉ የበለጠ በመሆኑ አጠያያቂ አይደለምና ሰአሊተ ምሕረት እንላታለን፡፡ ማርያም ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ዠማዕምንት ሰአሊተ ምህረት ለውሉደ ሰብእ፡- ንጽሕት ድንግል ማርያም የታመነች አምላክን የወለደች ናት ለሰዎች ልጆችም የምሕረት አማላጅ ናት» /ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ አንቀጽ 6/
እመቤታችን፡- እመቤት ማለት በአንድ ቤተሰብ መካከል አስተዳዳሪና ሓላፊ የሆነች ታላቅ ሴት ማለት ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን «ማርያም» የሚለውን በምሥጢራዊ ዘይቤ ሲተረጉሙ እግዝእተ ብዙኃን /የብዙኀን እመቤት/ ብለው ተርጉመውልናል፡፡
በአዳምና በሄዋን አማካኝነት ወደ ዓለም የገባውን መርገም የሻረ ጌታ እግዚአብሔር ከእርስዋ በመወለዱ እምቤታችን /የብዙዎች እመቤት/ ትባላለች፡፡ ሮሜ.5-6-11፡፡ እንዲሁም ዓለም ሁሉ በዳነበት በክርስቶስ የማዳን ሥራ ያመን ክርስቲያኖች ሁሉ በክርስቶስ አንድ ቤተሰብ በመሆናችን ቅድስት እናቱ ድንግል ማርያም እመቤታችን ናት፡፡ ዮሐ.19-26፡፡ ልጇ ጌታችን ነውና እርሷም እመቤታችን ናት፡፡ ሉቃ.1-43፡፡
ቤዛዊተ ዓለም፡- የዓለም መድኃኒት ማለት ነው ድንግል ማርያም የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን በመሆኗ ቤዛዊተ ዓለም እንላታለን በልጇ ቤዛነት ድነናልና፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም /ለድኅነተ ዓለም/ በቀራንዮ ኮረብታ የቆረሰው ሥጋ ያፈሰሰው ደም ከድንግል ማርያም የነሣው በመሆኑ ቤዛዊተ ዓለም ትባላለች፡፡ ዕብ.9-22፡፡ የሕያዋን ሁሉ እናት ድንግል ማርያም ለሔዋን ካሣዋ እንደሆነች ሁሉ ለአንስተ ዓለም ሁሉ ካሣ ቤዛ ናት ስድበ አንስትን ወቀሳ ከሰሳ አንስትን አስቀርታለችና፡፡ እንዲሁም ለዓለሙ ሁሉ የምታማልድ በልመናዋ ፍጥረትን የምታስምርና መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታስገባ በመሆኗ ቤዛዊተ ዓለም እንላታለን፡፡
ወላዲተ አምላክ፡- ወላዲተ አምላክ ማለት አምላክን የወለደች ማለት ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡» በማለት የጌታችንን አምላክ ወልደ አምላክነት የድንግል ማርያምን እመ አምላክ ወላዲተ አምላክነት አስረድቶአል፡፡ ሉቃ.1-35 ቅድስት አልሳቤጥም «የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?» ሉቃ.1-44 በማለት እንዳስረዳችው ድንግል ማርያም ጌታችንን የወለደች የጌታችን እናት ናትና ወላዲተ አምላክ እንላታለን፡፡ ድንግል ማርያም «ወላዲተ አምላክ» «አምላክን የወለደች» ተብላ እንድትጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ በ200 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ተዘጋጅቶ በቅዱስ ቄርሎስ አፈ ጉባኤነት የተመራው 3ኛው ዓለም አቀፋዊ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ነው፡፡

በዚህ ጉባኤ የቀረበው የንስጥሮስ የክህደት ትምህርት «ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባትም» የሚል ሲሆን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ንስጥሮሳዊውን ትምህርት አውግዘው ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም የነበረውን አምላክ ለዘመን በሥጋ ስለወለደችው በእውነት አምላክን የወለደች /ወላዲተ አምላክ/ ናት በማለት ትምህርተ ሐዋርያትን አጽንተዋል፡፡

በቤተ ልሔም በከብቶች ግርግም ከድንግል የተወለደው የዓለም ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ድንግል ማርያም ፣ እመ እግዚአብሔር ፣ ወላዲተ አምላክ ተብላ ትጠራለች፡፡ 1ዮሐ.5-20፤ ቲቶ.2-13፡፡

ቅድስተ ቅዱሳን፡- ይህ ስም ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ለሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕናና ቅድስና መገለጫ ሆኖ የተሰጣት ልዩ ስም ነው፡፡ ቅድስተ ቅዱሳን ማለት ከተለዩ የተለየች ከተመረጡ የተመረጠች፣ ከተከበሩ የተከበረች ማለት ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ክፍል ተሰመይኪ ፍቅርተ ኦ ቡርክት እምአንስት አንቲ ውእቱ ዳግሚት ቀመር እንተ ትሰመይ ቅድስተ ቅዱሳን፡- ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ሆይ የተወደድሽ ተባልሽ ከተለዩ የተለየሽ» በማለት ቅድስናዋን መስክሯል /የእሑድ ውዳሴ ማርያም አንቀጽ 1/
ከአንስተ ዓለም ተለይተው ቅድስናን ገንዘብ ያደረጉ በርካታ ሴቶች ቢኖሩም ድንግል ማርያም ግን የነዚህ ሁሉ ፊት አውራሪ /ግንባር ቀደም/ እና ከሌሎች አንስት የተለየች ቅድስት /ቅድስተ ቅዱሳን/ ትባላለች፡፡ «አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ» በማለት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል መስክሮላታል፡፡ ሉቃ.1-28፡፡ ከዚህም ጋር በተግባረ ቃል ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው «የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኲሎሙ ቅዱሳን፡- ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል» / ዘረቡዕ ውዳሴ ማርያም አንቀጽ .7/ በማለት የድንግል ማርያምን ቅድስና መስክሯል፤ ከዚህም የተነሳ በከበረ ስሟ ቅድስተ ቅዱሳን እያልን እንጠራታለን፡፡
ንጽሕተ ንጹሐን፡- ነጽሐ ነጻ ካለው ግሥ የወጣ ሲሆን ንጽሕት ማለትም የነጻች የጠራች ማለት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ንጽሕና «ዘንጹሕ ልቡ ወንጹሕ እደዊሁ፡- እጆቹም ልቡም ንጹሕ የሆነ»፣ «ብፁዓን ንጹሓነ ልብ ወይለብሱ ንጹሐ፡- ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው ንጽሕናን ይለብሳሉ»፣ «ሕያዋት ወንጹሓት፡- ሕያዋንና ንጹሓን»፣ «ንጽሕት ወብርህት፡- የነጻች የምታበራ» በማለት የንጽሕናን ሁኔታ ያስረዳሉ፡፡ መዝ.23፣ ማቴ.5-8፣ ራእ.15፣ ዘሌ.14-4፡፡ ውዳሴ ማርያም ዘአርብ፡፡
በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሴቶች የልማደ አንስት ኃጢአት ሰውነታቸውን ያላጐደፋቸው ወይም ያላረከሳቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሁንና ከገቢረ ኃጢአት ንጹሓን ይሁኑ እንጂ ከነቢብና ከሐልዮ ኃጢአት /በመናገርና በማሰብ ከሚሠራ ኃጢአት/ አልነጹም፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከገቢር ከነቢብ ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ስለሆነች ንጽሕተ ንጹሐን እንላታለን፡፡
ወትረ ድንግል /ዘላለማዊት ድንግል/፡- ቅድስተ ቅዱሳን ወላዲተ አምላክ ማርያም ጌታን ከመጽነሷ በፊት፤ ጌታን በጸነሰች ጊዜ፤ ከጸነሰችም በኋላ፤ ከመውለዷ በፊት፤ በወለደች ጊዜ፣ ከወለደች በኋላ ድንግል ናት ከዚህም የተነሳ ድንግል ዘላለም እንላታለን፡፡ ክህነትን ከነቢይነት ጋር አስተባብሮ የያዘው ሕዝቅኤል ዘላለማዊ ድንግልናዋን መስክሯል፡፡ ሕዝ.44-1-2፡፡
የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ሳዊሮስ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና በተናገረበት ክፍል «አምላክን የወለደች ማርያም ለዘለዓለሙ ድንግል እንደሆነች መውለዷም የማይመረመር ድንቅ እንደሆነ ከወለደችም በኋላ በድንግልና ጸንታ እንደኖረች አስረዳን» በማለት ስለ ዘላለማዊ ድንግልናዋ መስክሯል፡፡ ኢሳ.7.14፤ ሉቃ.1.27፡፡
ድንግል በክልኤ፡- በሁለት ወገን ድንግል ማለት ነው፡፡ በሁለት ወገን በሥጋም በነፍስም በሐልዮ /በሐሳብ/ በገቢር /በመሥራት/ በውስጥ በአፍአ ድንግል መሆኗን ያመለክተናል፡፡
ሌሎች ሰዎች ከገቢር ከነቢብ ቢጠበቁ ከሐልዮ /ከሃሳብ/ ኃጢአት መጠበቅ ግን አይቻላቸውም፡፡ ድንግል ማርያም ግን በሁለት ወገን ንጽሕት ቅድስት ናት ስለዚህ ድንግል በክልኤ /በሁለት ወገን ድንግል/ ትባላለች፡፡


ድንግል ወእም፡- እናትም ድንግልም ማለት ነው፡፡ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብሮ መገኘት ለፍጥረታዊ ሰው የማይቻል ቢሆንም ድንግል ማርያም ግን ሁለቱንም አስተባብራ ይዛለችና ድንግል ወእም ትባላለች፡፡
ሴቶች በልጅ ጸጋ ከከበሩ ድንግልናቸውን ያጣሉ በድንግልና ተወስነው ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት ከወሰኑ ደግሞ ከልጅ ጸጋ ይለያሉ፡፡ ሁለቱንም አስተባብረው ይዘው መገኘት አይሆንላቸውም፡፡ ድንግል ማርያም ግን ድንግልናን ከእናትነት እናትንትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ ይዛ የተገኘች በመሆንዋ ድንግል ወእም እናትም ድንግልም ሆናለች፡፡ ሉቃ.1-26-38፡፡
ልጇ ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ /ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው/ ሲባል እንዲኖር እርሷም ድንግል ወእም ስትባል ትኖራለች ስትወልደው ማኅተመ ድነግልናዋ እንዳልተለወጠ ሁሉ ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠም «እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም» እንዳለ፡፡ ሚል.3-6፡፡


ኪዳነ ምሕረት፡- የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግሥት በመመለስ የሰውን ሕይወት ለዘለዓለሙ ለመጠበቅ በመጀመሪያ ከስህተቱ በንስሐ ከተመለሰው ከአዳም፣ ቀጥሎም ከጻድቁ ከኖኅ፣ ከዚያም በእምነትና በምግባሩ ቀናነት የእግዚአብሔር ወዳጅ ተብሎ ከተሰየመው ከአብርሃም.... ከሌሎችም ቅዱሳን ጋር ለመላው የሰው ዘር የሚሆን የምህረትና የበረከት ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡
«ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ» መዝ.88-3 በማለት በተናገረው መሠረት ከምርጦቹ ጋር ቃል ኪዳን የሚያደርግ ልዑል አምላክ ከተመረጡ የተመጠረች በመሆኗ /ዋ/ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የካቲት 16 ቀን ቃል ኪዳን ሰጥቷታል፡፡ ለዚህም በየዓመቱ የካቲት 16ቀን በዓለ ንግሥ ወር በገባ በ16 ቀን ወርኃዊ በዓሏን እናከብራለን፡፡
ይህንንም ለማመልከት ኪዳነ ምሕረት /የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለች/ ትባላለች፡፡ በዚህም ምክንያት፡-
በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ 
ቅድስት ሆይ ለምኝልን
በእንተ ስማ ለማርያም ወዘተ
በማለት የተሰጣትን ቃል ኪዳን መማጸኛ በማድረግ እንጠራታለን፡፡ ምሳሌዋ የሆነች ሐመረ ኖኅ /የኖኅ መርከብ/ በተሰጣት ቃል ኪዳን ከማየ አይኅ /ከጥፋት ውኃ/ ነፍሳትን እንደ አዳነች ቅድስት ድንግል ማርያምም በተሰጣት ቃል ኪዳን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ታድነናለችና ኪዳነ ምሕረት /የምሕረት ቃል ኪዳን/ የተሰጠሽ እንላታለን፡፡


ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ምሥጢራዊና ትርጉም ያላቸው የእመቤታችን ስሞች የተገለጹት /የተነገሩት/ በራሱ በልዑል እግዚአብሔር እንዲሁም በቅዱሳን ነቢያት፣ በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታትና በሌሎችም ቅዱሳን አባቶች ነው፡፡
ይህም ምሥጢር የትምህርተ ሃይማኖት አንዱ አካል ሲሆን እኛም በቅዱሳን የተገለጸውን የእመቤታችንን ምሥጢራዊና ትርጉም ያላቸው ስሞች ተረድተን የትምህርተ ሃይማኖት ዕውቀታችንን ልናሳድግ ቅድስት ድንግል ማርያምንም ልናከብር እንዲገባን መገንዘብ አለብን፡፡ የቅዱሳንም አስተምህሮት ይህ ነውና፡፡
ረድኤቷ፣ በረከቷ፣ አማላጅነቷ አይለየን፡፡


አትምኢሜይል

ቅድስት(የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም.


የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ 
ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኅበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ፡፡

ትርጉም:- ለእግዚአብሔር ተገዙ ስሙንም ጥሩ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው ለስሙም ምስጋናን ስጡ /አቅርቡ/ ሰንበትን አክብሩ እውነትንም አድርጉ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችኹም ተቀመጡ ክርስቶስ ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ፡፡

ምንባባት
መልዕክታት
1ኛ ተሰ.4÷1-12:- አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ÷ በእኛ ዘንድ እንደ ታዘዛችሁ በሚገባ ትሄዱ ዘንድ÷ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኙ ዘንድ÷ ደግሞ እንደ ሄዳችሁ ከፊት ይልቅ በዚሁ ታበዙና ትጨምሩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንነግራችኋለን፤ እንማልዳችኋለንም፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ያዘዝናችሁን ትእዛዝ ታውቃላችሁ፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነውና፤ እርሱም ከዝሙት ትርቁ ዘንድ መቀደሳችሁ ነው፡፡ ሁሉም እያንዳንዱ ገንዘቡን ይወቅ፤ በንጽሕናና በክብርም ይጠብቀው፡፡ እግዚአብሔርን እንደማያውቁት እንደ አረማውያንም በፍትወት ድል አትነሡ፡፡ ይህንም ለማድረግ አትደፋፈሩ፤ በሁሉም ወንድሞቻችሁን አትበድሉ፤ አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁና እንደ አዳኘሁባችሁ÷ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር የሚበቀል ነውና፡፡ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኲሰት አልጠራንምና፡፡ አሁንም የሚክድ÷ መንፈስ ቅዱስን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን የካደ አይደለም፡፡

ባልንጀሮቻችሁን ስለ መውደድ ግን ልንጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ራሳችሁ በእግዚአብሔር የተማራችሁ ናችሁና፡፡ በመቄዶንያ ሁሉ ካሉት ወንድሞቻችን ሁሉ ጋር እንዲሁ ታደርጋላችሁ፤ ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ትበዙና ትጨምሩ ዘንድ÷ ሥራችሁንም ታከናውኑ ዘንድ እንደ አዘዝናችሁም በእጃችሁ ትሠሩ ዘንድ÷ በውጭ ባሉት ሰዎችም ዘንድ ከማንም አንዳች ሳትሹ በሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን፡፡

1ኛጴጥ.1÷13:- ፍጻ. ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ክፉ ምኞት አትከተሉ፡፡ ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” የሚል ተጽፎአልና፡፡ ለሰው ፊትም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርድ አብን የምትጠሩት ከሆነ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ በፍርሃት ኑሩ፡፡

ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ፡፡ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር የታወቀ÷ በኋላ ዘመን ስለ እናንተ የተገለጠ፡፡ ከሙታን ለይቶ በአስነሣው÷ ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ቃል ያመናችሁ÷ አሁንም እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሁን፡፡

ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ ወንድሞቻችሁን ትወድዱ ዘንድ÷ ለእውነት በመታዘዝ ሰውነታችሁን አንጹ፤ እርስ በእርሳችሁም ተፋቀሩ፡፡ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡

ግብረ ሐዋርያት
የሐዋ.10÷17-29፡- ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር፡፡

ተጣርተውም፡- ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ፡፡ ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው÷ “እነሆ÷ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፡፡ ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና፡፡” ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና÷ “እነሆ÷ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው፡፡

እነርሱም÷ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት፡፡ እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ፡፡ በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር፡፡

ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት፡፡ ጴጥሮስም÷ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው፡፡ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው÷”ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ፡፡ አሁንም ስለላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ፡፡”

ምስባክ
መዝ.95÷5 እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ

ትርጉም፦ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ ምስጋና ውበት በፊቱ ቅዱሰነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡

ወንጌል
ማቴ.6÷16-24፡- “በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ እንደ ጾሙ ለሰው ይታዩ ዘንድ መልካቸውን ይለውጣሉና÷ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ እናንተስ በምትጾሙበት ጊዜ ራሳችሁን ቅቡ፤ ፊታችሁንም ታጠቡ፡፡ በስውር ለሚያይ ለአባታችሁ እንጂ÷ ለሰዎች እንደ ጾማችሁ እንዳትታዩ፤ በስውር የሚያያችሁ አባታችሁም ዋጋችሁን በግልይ ይሰጣችኋል፡፡

“ብልና ነቀዝ በሚያበላሹት÷ ሌቦችም ቈፍረው በሚሰርቁበት በምድር ለእናንተ መዝገብ አትሰብስቡ፡፡ ነገር ግን ብልና ነቀዝ የማያበላሹት÷ ሌቦችም ዘፍረው በማይሰርቁት በሰማይ ለእናንተ መዝገብን ሰብስቡ፡፡ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይኖራልና፡፡

“የሰውነትህ መብራቱ ዐይንህ ነው፤ ዐይንህ ብሩህ ቢሆን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል፡፡ ዐይንህ ግን ታማሚ ቢሆን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል፤ በአንተ ላይ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማህ እንዴት ይበዛ! ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አገልጋይ የለም፤ ያለዚያ አንዱን ይወዳል፤ ሁለተኛውንም ይጠላል፤ ወይም ለአንዱ ይታዘዛል፤ለሁለተኛውም አይታዘዝም፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም፡፡

ቅዳሴ
ዘኤጲፋንዮስ
ዐቢይ ውእቱ እግዚአብሔር በዕበዩ ቅዱስ በቅዳሴሁ እኩት በአኮቴቱ ወስቡሕ ስብሐቲሁ . . .
ትርጉም፡- እግዚአብሔር በገናንነቱ ገናና ነው በቅድስናው የተቀደሰ ነው በምስጋናው የተመሰገነ ነው በክብሩም የከበረ ነው. . .

2015 ፌብሩዋሪ 18, ረቡዕ

21 የግብጽ ኮፕት ክርስቲያኖች ሰማእትነት ተቀበሉ


አትም ኢሜይል
የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
egypt copts21 የግብጽ ኮፕት ክርስቲያኖች ራሱን ኢስላሚክ ስቴት /ISIS/ እያለ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን በምሥራቃዊ ሊቢያ ሲርት ውስጥ የካቲት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰማእትነት ተቀበሉ፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በላከው የአምስት ደቂቃ የምሥል ወድምጽ መረጃ አጋቾቹ ሰውነታቸውን በጥቁር አልባሳት በመሸፈን፤ ታጋቾቹን ደግሞ ብርቱካናማ ልብስ በማልበስ ወደ የባሕር ዳርቻ በመውሰድና በጉልበታቸው በማንበርከክ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ አንገታቸውን ቀልተዋቸዋል፡፡

በእምነታቸው ምክንያት የታገቱት እነዚህ የኮፕት ክርስቲያኖች ለሥራ ፍለጋ ከግብጽ ወደ ሊቢያ የሔዱ ሲሆን፤ በታጣቂዎቹ መታገታቸውን ቢቢሲ እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች ዘግበዋል፡፡

የክርስቲያኖቹ መገደል ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፤ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት፤ የሀገራት መሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የመንግሥታት ሓላፊዎች ተቃውሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ “በክርስቲያኖቹ ግድያ ጊዜውን የጠበቀ አጸፋ ለመመለስና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ያሉንን አማራጮች ሁሉ እንድንጠቀም እንገደዳለን” ብለዋል፡፡
 

በተያያዘ ዜና የግብጽ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖቹን ሰማእትነት ለማዘከር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናቷ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ጾም፤ ጸሎትና ቅዳሴ እንዲደረግ አውጃለች፡፡

2015 ፌብሩዋሪ 17, ማክሰኞ

የዘወረደ ምንባብ (ዕብ.13÷7-17)


አትምኢሜይል
የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም የሚኖር እርሱ ነውና፡፡

 ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያአልተጠቀሙምና፡፡ ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤ ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር፡፡

ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ፡፡ አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን÷ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ፡፡ በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም የምትመጣውን እንሻለን እንጂ፡፡ በውኑ እንግዲህ በሰሙ አናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡


 (ያዕ.4÷6 )
ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡


 (ሐዋ.25÷13- ) 
ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡ በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው÷ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ፡፡ በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ፡፡ አኔም፡- ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም÷ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው፡፡

ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ÷ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ፡፡ የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ÷ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው÷ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤ ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት፡፡” አግሪጳም ፊስጦስን÷ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወደለሁ” አለው፤ ፊስጦስም÷ “እንግደያስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው፡፡


በማግሥቱም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጡ፤ ከመሳፍንቱና ከከተማው ታላላቅ ሰዎች ጋርም ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ፊስጦስም እንዲህ አለ÷ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ÷ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ወንድሞቻችን ሁላችሁ÷ ስሙ፤ አይሁድ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው በኢየሩሳሌምም ሆነ በዚህ እየጮሁ የለመኑኝ ይህ የምታዩት ሰው እነሆ፡፡ እኔ ግን ለሞት የሚያደርሰው በደል እንዳልሠራ እጅግ መርምሬ÷ እርሱም ራሱ ወደ ቄሣር ይግባኝ ማለትን ስለወደደ እንግዲህ ልልከው ቈርጫለሁ፡፡ ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የታወቀ ነገር የለኝም፡፡ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን አገኝ ዘንድ ወደ እናንተ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ ወደ አንተ አመጣሁት፡፡ የበደሉ ደብዳበቤ ሳይኖር እስረኛን ወደ ንጉሥ መላክ አይገባምና፤ ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል፡፡”



ነፍስና ሥጋ የውል ስምምነት ተፈራረሙ

አትምኢሜይል


የካቲት 10ቀን 2007ዓ.ም. 
በመ/ርት ጸደቀወርቅ አሥራት
ነፍስና ሥጋ እንደከዚህ በፊቱ ለሚጠብቃቸው ከባድ የሥራ ኃላፊነትና አለመግባባት የውል ስምምነት ተፈራረሙ። የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት በዚህ ሣምንት የገባውን የዐቢይ ፆም ምክንያት በማድረግ ነው።

በውሉ ሥነ ሥርዐት ላይ ነፍስ እንደገለጸችው ከዚህ በፊት በአጽዋማት ጊዜ በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ውሉ ጠቃሚነቱ የጎላ ነው። ባለፉት ዓመታት ሥጋ የአጽዋማትን ወቅት ጠብቆ ነፍስ ተገቢውን ድርሻ እንዳትወጣ እንቅፋት እየሆነ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸው ስምምነቱ በመካከላችው ሰላም እንዲሰፍን ምክንያት ይሆናል ያሉን በስምምነቱ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት የነፍስ አባት ናቸው።
ከፊርማው ሥነ ሥርዐት በኋላ ባነጋገርነው ወቅት ስምምነቱን ተቀብሎ የነፍስን ሥራ ሳይቃወም ሊገዛላት መዘጋጀቱን ሥጋም ቢሆን አልሸሸገም። በሥነ ሥርዐቱ ላይ የተገኙት ሌሎች ምዕመናንም ሥጋን በቃልህ ያጽናህ እያሉ ከስብሰባው አዳራሽ ሲወጡ እንደተሰሙ “ሪፖርተራችን” ዘግቦልናል።

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...