2015 ኤፕሪል 15, ረቡዕ

ኹራፋተ አምሳሉ ፡- መረጃና ማስረጃ አልባው እንቶፈንቶİ


                                                ዲ/ን ዶክተር መሐሪ ወሰን /ከጅማ/
ዶክተር ደረጄ ዓለማየሁ ይባላሉ፡፡መጋቢት 1992 ዓ.ም. ‹‹ በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ፡- መኢሶን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ›› በሚል ርእስ በአቶ አንዳርጋቸው አሰግድ ተዘጋጅቶ በታተመው መጽሐፍ ውስጥ የጽሑፍ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ይኸውም መቅድም መጻፍ ነበር፡፡ በጻፉት መቅድም ውስጥ በጥላቻ ቁመናው ከኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ጋራ ተመሳሳይ የሆነ ሰውን የጥላቻ ክርክር ጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ጽፈውታል፡፡
በደርግ ዘመን በየጊዜው ጤፍ ከአዲስ አበባ ይጠፋ እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡ በዚያው ዘመን ከአንድ የማውቀው (የተማረ) ሰው ጋር ጨዋታ ጀመርንና ጤፍ የጠፋው በአንቶኖቭ እየተጫነ ወደ ሶቭዬት ኅብረት ስለሚጓዝ ነው፤ አለኝ፡፡ ‹‹ራሽያኖች እንጀራ መብላት ጀመሩ እንዴ?›› ብዬ ጠየቅሁት፡፡ ‹‹አይ ለቮድካ ሊጠቀሙበት ነው፤አለኝ›› መልሶ፡፡ ‹‹ኧረ ተው ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት የሚመረተው ጤፍ በሙሉ ወደ ሶቭዬት ኅብረት ቢጋዝ እዚያ በአንድ ቀን የሚወጣውን ቮድካ ለመጥመቅ አይበቃም፤›› አልኩት፡፡ ‹‹ አይ እንደ ቅመም ሊጠቀሙበት ነው አሉ፤›› አለኝ፡፡ ‹‹ተው እንጂ እንደ ቮድካ፣ እደ ውስኪ ያሉት ስመ ጥሩ መጠጦች ሲጠመቁ ዋናው ጥበብ እኮ ለዘመናት ተለምዶ የቆየ ጣዕማቸው እንዳይቀየር ማድረግ ነው፤ ስለዚህ ገና ያልተለመደ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ቅመም ለመጨመር ምክንያት የሚኖራቸው አይመስለኝም፤ ብዬ ይህን የማይረባ ክርክር ዘጋሁ፡፡ (ደረጀ፤1992፣2)
በዚያን ወቅት ከዚህ ሰው ጋር ሶቭዬት ኅብረት በዓለም አቀፍ ደረጃና በተለይ በሀገራችን የምትከተለውን ፖለቲካ በሚመለከት ተቃሞውን (ኧረ እንደውም ጥላቻውን) ለመጋራት ችግር አልነበረብኝም፤ የሚሉት ዶክተር ደረጄ ዓለማየሁ፤‹‹ለእኔ ግን ይህን አቋም ለማጠናከር ሩሲያን በጤፍ ሌብነት መክሰስ አያስፈልገኝም ነበር፡፡ ይህ ወዳጄ ግን ለሩሲያ ተቃውሞውና ጥላቻው በምንም ላይ ያልተመሠረቱ ግምቶችን ጭምር መሰብሰብ ነበረበት፡፡ ከዚያም አልፎ ሩሲያ የተወሰነው የዓለም ክፍል ጨቋኝና በዝባዥ ነች፤ የጤፍ ሌባ ግን አይደለችም፤ ያለውን (ሁሉ) በሶቭዬት ኅብረት ደጋፊነት ከመክሰስ አይመለስም ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ‹‹መረጃ ላይ መመሥረት ያለበትን ታሪክ ነክ ወይም ፖለቲካ ነክ ክርክር ከእንደዚህ ዓይነት ሰው ጋር ማካኼድ አይቻልም›› ሲሉም አክለው ያስረዳሉ፡፡ (ደረጀ፤1992፣2)
ከዚህ አኳያ ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ከዶክተር ደረጄ ዓለማየሁ ወዳጅ የሚለየው፤ ከዐሥራ ሁለተኛ ክፍል የዘለቀ ትምህርት የሌለው የትምህርት ሽፍታ፣ በሠዓሊነቱም ስሙን እንደማዓረግ ይጠቀምበት ካልሆነ ከተግባሩ የሌለበት እና አማተር ፖለቲከኛ መሆኑ ብቻ እንጂ በጥላቻ ቁመናው በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡
 ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የቱንም ያህል የሥርዓቱን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ጠላትነቱን የሚገልጹ ጽሑፎች ቢጽፍም፣ ቃለ መጠይቆችን ቢሰጥም፣ በኹራፊው አምሳሉ ደረጃ ወርዶ ወያኔን ‹‹የጤፍ ሌባ ነው›› ዓይነት ክስ እስካልከሰሰ ድረስ፤ ዳንኤልን በወያኔነት ከመክሰስ የማይመለስ ኹራፊ መሆኑን የሚያጋልጡ ሦስት ጽሑፎችን ከሰሞኑ አነበብኩ፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ በአይሁዶች መርዘኛ ጥርስ የገባች ሀገር ኢትዮጵያ ! ››በተሰኘ ፀረ ሴማዊነት ርእስነት የለጠፈብንን ነው ፡፡ ሁለተኛ ‹‹የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጠላት ስውሩ ተኩላ ዳንኤል ክብረት›› በሚል ድልዝ ‹ርእስነት› የለጠፈውን የሐሳብ ውራጅ ሲሆን፤ ሢሰልስ ደግሞ ‹‹ዳንኤል ክብረትና ሌላው የወያኔያዊ ተግባሩ መግለጫ›› በሚል የተደባጨ ‹ርእስነት› የሰነቀረውን የአስተሳሰብ ስብራቱ ነው፡፡
በሐሳብ ውራጅ እና በአስተሳሰብ ስብራት ውስጥ የሚገኝ ኹራፊ ፍጥረት መሆኑን ያጋለጠበትን ቁርጥራጮች አንብቤ ስጨርስ ሦስት ዓይነት ስሜቶች ተሰምተውኛል፡፡ የመጀመሪያው የሐዘን ነው፡፡ የወያኔን የጥፋት ሥርዓት በተላላኪነትና በአስተኳሽነት እያገለገሉ የሚገኙት እንደ አምሳሉ ገብረ ኪዳን ዓይነት ኹራፊዎች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልዕልናና ክብር መመለስ አበክረው በሚታገሉት እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያሉትን ቁርጥ የቤተ ክርስቲያንና የሃገር ልጆች በወያኔነት ሲፈርጆ ማየት እጅግ ያሳዝናል፡፡
ሁለተኛው የመደነቅ ነው፡፡ ትናንት ከአጉራ ዘለል ባሕታውያን ነን ከሚሉት ጋራ፣ ዛሬ ደግሞ አሸናፊ መኮንንን ከመሳሰሉት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንና ውጉዛን ጋራ በመወዳጀት የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነት፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ትውፊትና ታሪክ በስውር እየቆነጻጸለ፣ እየቀሰጠ የሚገኘው ጎጠኛው አምሳሉ ገብረ ኪዳን፣ የዘመናችን ርቱዕ ሃይማኖትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ጠበቃ የሆነውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጠላነት ፈርጆ ሃይማኖቱን ሲጠራጠር ከመመልከት በላይ ምን ይደንቅ?
ሦስተኛው ደስታ ነው፡፡ ደስታው ደግሞ ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛው ኹራፊው መምህራችንን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን አጋጣለሁ ብሎ በጻፈው ቁርጥራጭ ራሱን ማጋለጡ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ራሱን በፀረ ወያኔነት ቆብ የገለጠው አምሳሉ ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት እስከ ኤልያስ ገብሩ ያሉትን ወንድሞች እንዲሰልል የተሰጠውን ተልእኮ ሳይጨርስ፤ ከዚህ በኋላሰለአርሱ በተከታታይ እንድንጽፍ ምክንያት የሆነችውን አብሪ ጥይት ተኩሶ እኛን በመጋበዙ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት በተጨባጭ እውነታ የተመሠረቱትን ስሜቶቼን ከግንዛቤ በማስገባት ለዛሬ በዋናነት ሦስቱን ቁርጥራጭ ‹‹ጽሑፎቹን›› ከእውነትነት፣ ከታሪካዊ ሁነት፣ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ከፖለቲካዊ ቅሌት አንፃር ብቻ በመፈተሽ ተጋላጩ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወይስ ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን የሚለው ወሳኝ ጥያቄ በመመለስ ጽሑፌን እደመድማለሁ፡፡
1 - በተቆርቋሪነት መለዮ የተሰነቀረ ኑፋቄ!
ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት አስመልክቶ በፌስ ቡክ ገጽ ላይ፤     ‹‹ … የመውለጃዋ ጊዜ በደረሰ ጊዜ ጌታዋ ፈጣሪዋ የኋላ ልጇ ለመለኮታዊ ክብሩ፣ ለልዑልነቱ፣ ለሁሉን ቻይነቱ፣ ለፈጣሪነቱ፣ ንጹሕ ነገር ፈላጊ፤ ለንጹሐ ባሕርይነቱ በምትስማማ መልኩ ምንም ምክንያት እንዳይገኝባት አድርጎ ንጹሕ ጽዱ ፍጹም ቅድስት አድርጎ ፈጥሮ አዘጋጃትና ሰዓቱ ሲደርስ ያንን ንጹሕ ፍጹም ጽዱ ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት ፤ በዚህ ሥጋውም ዓለሙን ሁሉ ተቤዠው፡፡›› የሚል ኑፋቄን ከእውነተኛው ትምህርት ጋራ የቀየጠ ጽሑፍ አስፍሮ ነበር፡፡
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሦስት መሠረታዊ የኑፋቄ ትምህርቶች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ‹‹የኋላ ልጇ›› የሚለው ነው፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊት ሌላ ልጅ እንደአላት አድርጎ ጌታችንን ‹‹የኋላ ልጇ›› ሲል ኑፋቄውን ጽፏል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት እመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጋና ይግባትና ተከታይም ሆነ ቀዳሚ ከሌለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጪ ሌላ የበኩር ልጅ የላትም፡፡ በዚህም ‹‹ በኩር›› የሚለው ቃል አንድ ወልድ በቀዳማዊ ልደቱም ሆነ በደኀራዊ ልደቱ ተቀዳሚ ተከታይ ተመሳሳይ እኩያ የሌለው መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን እንዲህ አድርጎ ያቀረበውን ኑፋቄያዊ አስተምህሮ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በቤተ ክርስቲያ አስተምህሮ መሠረትነት ‹‹ኦርቶዶክስ መልስ አላት›› በሚል ርእስ ከፕሮቴስታንቶች ለሚነሡ አንዳንድ ጥያቄዎች በሰጠው የመልስ መጽሐፍ ውስጥ እምነቱ የአደረገውን የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነት እደሚከተለው ገልጧል፡፡
‹‹ የበኩር ልጅ ማለት መጀመሪያ የተወለደ ማለት ነው፡፡ ወይም የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ማለት ነው፡፡ ‹ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳትም ማኅፀን የሚከፍት በኩር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ የእኔ ነው፤› ዘፀ. 13 ፥ 2፤ ይህ ትእዛዝ የሚፈጸመው ሌላ ልጅ እስኪወለድ ድረስ ተጠብቆ ሳይሆን ወዲያው ልጅ እንደተወለደ ነው፡፡ ምክንያቱም ያን ልጅ በኩር ለማሰኘት የግድ ሌላ ልጅ በቀጣይ መወለድ የለበትምና፡፡ አባ ሄሮኒመስ ይህንን የበለጠ ሲያብራራው፤‹ ለእናቱ አንድያ የሆነ ልጅ ሁሉ በኩር ነው፤ በኩር ሁሉ ግን አንድያ አይደለም፤›› (ዳንኤል፣2002፣89)
ከዚህም በተጨማሪ ዲያቆን ዳንኤል፤ እመቤታችን ጌታን ከመውለዷ በፊት ይቅርና በኋላም ልጅ እንዳልወለደች፤ የቤተ ክርስቲያችንን ትምህርት መሠረት በማረግ፤‹‹ እመቤታችን… ልጆች ቢኖሯት ኖሮ በአደራነት ለዮሐንስ ወንጌላዊዉ ባልተሰጠች ነበር፡፡ (ዮሐ. 19 ፥ 25) ጌታችን ዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሆኖ ከእመቤታችን እና ከዮሴፍ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ በወጣ ጊዜ ዮሴፍ፣ እመቤታችን እና ጌታችን ብቻ ነበሩ፤ (ሉቃ. 2 ፥ 43)፡፡ በዐሥራ ሁለት ዓመታት ውስጥ ያልተወለዱ ልጆች ከየት ይመጣሉ?›› ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ (ዳንኤል፣2002፣96)
ሁለተኛው የኹራፊው አምሳሉ ኑፋቄ፤‹‹ ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት›› የሚለው ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፤‹‹ሥጋዋን ነሥቶ ወይም ተዋሕዶ›› ይባላል እንጂ በፍጹም ‹‹ሥጋዋን ወርሶ›› አይባልም፡፡ ምስጢረ ተዋሕዶውም በእንዲህ ዓይነት ወሊጥ ቃል ተገልጾም አይታወቅም፡፡ ሲቀጥልም ‹‹ተወለደባት›› አይባልም፡፡ ‹‹ሥጋዋን ነሥቶ ወይም ተዋሕዶ ተወለደ፤›› እንላለን እንጂ ‹‹ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት›› አንልም፡፡ ‹‹ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት›› የምንል ከሆነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤‹‹እንበለ ኅድረት - ያለ ኅድረት፤ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም በነሣው ወይም በተዋሐደው ሥጋ ተወለደ›› የሚለውን የቤተ ክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት ያፋልሳል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነቱን ወሊጠ ቃል አትጠቀምም፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ግን ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን፤‹‹ ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት›› የሚለውን ኑፋቄያዊ ሕፀጽ፤ ‹‹ነገረ ድኅነት›› በሚል ርእስ በአዘጋጀው መጽሐፉ ላይ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን በነሣው ሥጋ‹‹አደረ›› ብላ አታምንም፤ አታስተምርምም፡፡ እንዲህ ብሎ ማስተማር ሥጋ ለቃል ማኅደሩ፣ ልብሱ ሆነ ብሎ ማስተማርም ማመንም ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ፤ ቃል እና ሥጋ እንደ ወዳጅ አብረው ይኖራሉ እንጂ ባሕርያዊና አካላዊ ተዋሕዶ የላቸውም፤ ብሎ እንደ መናፍቁ ንስጥሮስ ማመን ነው፡፡ በመሆኑም ሥጋ የቃል ማደሪያ፤ ቃልም በሥጋ ኀዳሪ አይደሉምና፡፡ በቃልና በሥጋ ተዋሕዶ ኅድረት የለባትም፡፡›› ሲል ያቀናዋል፡፡ (ነገረ ድኅነት፤ 1993፣19)
 የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ትንተና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ስለመሆኑ ሲረጋገጥ ቅዱስ ቄርሎስ በሃይማኖት አበው ያለውን እደሚከተለው መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡
‹‹የባሕርይ አምላክ የሚሆን የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር እርሱ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ ነው ብለን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደ ቃል ከዘመናት አስቀድሞ ከእርሱ ጋር ነበር፡፡ በኋለኛው ዘመንም እርሱ ዳግመኛ ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወለደ፤ የተዋሐደውን የተገዥ ባሕርይንም ራሱ ተዋሐደው እንጂ ሌላ ማኅደር አላደረገም፡፡›› (ሃይማኖተ አበው 77 ፣ 43)
የኹራፊው አማሳሉ ገብረ ኪዳን ሦስተኛው ኑፋቄያዊ ሕፀጽ፤‹‹… በዚህ ሥጋውም ዓለሙን ሁሉ ተቤዠው›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በነገረ ድኅነት ትምህርታችን ትልቁ ኑፋቄ ነው፡፡ ይህም በሁለት መልኩ ይገለጻል፡፡ የመጀመሪያው፤ ‹‹ድኅነተ ዓለም የተፈጸመው በሥጋ ነው›› የሚል ኑፋቄን ሲያመጣ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፤‹‹ ሥጋ መለኮትን ውጦና አጥፍቶ በሩቅ ብእሲ ሥጋ ድኅነት ሆነ›› የሚለውን ኑፋቄ ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ ቤዛ ዓለም አልተፈጸመም እንደማለት ነው፡፡
ቃል ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ ተዋሕዶው ፍልጠት የለበትም፡፡ ተዋሕዶው እንደ ነፍስና ሥጋ ነው፡፡ አንድ ሰው ሁለት ባሕርይ እንደማይባል ሁሉ መለኮትና ሥጋም ከተዋሕዶ በኋላ መንታነት፣ ሁለትነት የለም፡፡ ስለዚህ ሥጋው ብቻ ተነጥሎ ‹‹ዓለሙን ተቤዠው›› ማለት እጅግ ክህደት ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ አለመኖሩን ሲገልጽ፤‹‹ከሥጋዌ በኋላ ይህ የቃል ነው፤ ያኛው የሥጋ ነው አይባልም፡፡… በክርስቶስ ሥጋዌ ምንታዌ የለምና፡፡›› ብሏል፡፡ (ጎርጎርዮስ፤1978፣136-138)
እንግዲህ አይደለም መለኮት በሥጋ ቢዋጥ ቢጠፋ ይቅርና፤ ሥጋ በመለኮት ቢዋጥ ቢጠፋ መለኮት ሊሞት አይችልምና ድኅነተ ዓለም ባልተገኘ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተዋሕዶ ምንታዌ የለበትም፡፡ ከተዋሕዶ በኋላም ‹‹ሥጋ ተቤዠ፤ መለኮት ተቤዠ›› ተብሎ አይነገርም፡፡ ምክንያቱም ቡዐዴን ያስከትላልና፡፡
ታላቁ መምህራችን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይህንን የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኹራፊውን የአምሳሉ ገብረ ኪዳንን ኑፋቄያዊ ሕፀጽ ‹‹ነገረ ድኅነት›› በተባለው መጽሐፉ፤‹‹ቡዐዴ መለየት መለያየት ማለት ነው፡፡ ሁለት ነገሮች አንድ ላይ ከሆኑ በኋላ መለየት መነጠል ሲቻል ቡዐዴ ይባላል፡፡… የክርስቶስ ሰው የመሆን ምስጢር ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ሥጋና መለኮትን ለያይቶ ለየብቻ ይህ መለኮት ነው፡፡ ይህ ሥጋ ነው አይባልም፡፡ እንደ ብረትና እሳት ፍጹም ተዋሕዶ ስለሆነ መነጣጠል አይቻልም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ሰው የሆነው እንበለ ቡዐዴን ነው፡፡›› በማለት ያብራራዋል፡፡ (ነገረ ድኅነት፤1993፣22)
ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የዲያቆን ዳንኤልን ትንታኔ ሊቃዊ ነፍስ ሲዘራበት፤ ‹‹ፍልብያኖስ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መለኮቱና ትስብእቱ የተለያዩ ሁለት አካላት ናቸው፤ ይላል፡፡ እኛ ግን ፈጣሪያችን መለኮትና ትስብእት ከተዋሐዱ በኋላ አንድ አካል አንድ ገጽ እላለን፡፡›› ብሏል፡፡ (መጽሐፈ ምስጢር፤2001፣3)       
በአጭሩ የኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን፤‹፣ … የኋላ ልጇ … ሥጋዋን ወርሶ ተወለደባት ፤ በዚህ ሥጋውም ዓለሙን ተቤዠው፡፡›› የሚለው ፍጹም ኑፋቄያዊ ሕፀጽ፤ ‹‹ዓለምን የተቤዠው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ውላጤ፣ እንበለ ሚጠት፣ እንበለ ኅድረት፣ እንበለ ቡዐዴ፣ እንበለ ትድምርት፣ እንበለ ቱሳኤ በተዋሕዶ ነው፡፡›› ከሚለው ርቱዕ ትምህርት ጋር የሚጋጭ ክህደት ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ከቤተ ክርስቲያናችን መሠረተ እምነት፣ ከሊቃውንቱ (ከቅዱስ ቄርሎስ እና ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ) ትንተና በተቃርኖና በፍንገጣ የቆመው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ነው ወይስ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነትን እምነቱ ያደረገውና በቅዱስ ቄርሎስ እና በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ትንተና የተመሠረተው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው  በሃይማኖት መጠርጠር ያለበት? የቤተ ክርስቲያን ጠላትስ  ማነው? ለእኔ ጠላትም ሆነ ከሐዲው ኹራፊው አምሳሉ ገብ ኪዳን ነው፡፡
ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን መች ከዚህ ኑፋቄያዊ ሕፀጹ ብቻ ተገትቶ፡፡ ከተዘፈቁ አይቀር እንዲህ ነው፤ ‹‹በአይሁዶች መርዘኛ ጥርስ የገባች ሀገር ኢትዮጵያ!›› በሚል ርእስ ተሸካሚነት ፀረ ሴማዊነቱንና ለዚህ ፀራዊ ስሜቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት በማዛባት በገለጠበት በዚያ ማወየቢያ ጽሑፉ ውስጥ ሁለት ትምህርተ ሃይማኖታዊ ርእሰ ጉዳዮችን አዛብቶ አቅርቧል፡፡
የመጀመሪያው፤  ‹‹ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ‹ ለይሁዳ ወለዱ ወለ ዉሉደ ዉሉዱ ይደምሰስ › ትላለች፤›› ተብሎ፤ በማትለውና ግድፈት በተሞላበት ግእዝ የተገለጠው አሳበ ጥቅስ ነው፡፡ ተዛብቶ የቀረበውና ቤተ ክርስቲያን ብላው በማታውቀው (ግእዝ አይሉት አማርኛ) መንገድ የቀረበው አሳበ ጥቅስ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትለው ትክክለኛ ግእዝ ሲቀመጥ፤‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወለ ዉሉደ ወልዱ ይደምሰስ››በሚል ነው፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ በዕለተ ስቅለት ብቻ በቤተ ክርስቲያን የዋለ ሰው እንኳን የማይገድፈውን አሳበ ጥቅስ የገደፈው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ነው፡፡ ይኸው ሰው ነው፤ የአባ ጊዮርጊስን ‹‹ውዳሴ መስቀል››፣ በ‹‹አራቱ ኃያላን›› መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱትን የአቡነ በጸሎተ ሚካኤል፣ የአቡነ ፊልጶስ፣ የአቡነ አኖሬዎስ እና የአቡነ አሮን ገድላትን ተርጉሞና ጥልቅ ጥናታዊ ማብራሪያ የሰጠውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን፤ ያለአንዳች ተጨባጭ ማስረጃ፤ በግእዝ ጨዋነት ለመጠርጠር የዳዳው፡፡
ኹራፊው አምሳሉ ይህ ግድፈቱ ሳያንሰው በዚሁ በገደፈው ግእዙ የራሱን ፀረ ሴማዊ ፍላጎት በመቀንበብ፤ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወለ ዉሉደ ወልዱ ይደምሰስ››በሚል  የሚለውን አሳበ ጥቅስ በዕለተ ዓርብ የምትጠቀመው፤ ‹‹አይሁዶችን ለማውገዝ ነው›› ሲል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በፀረ አይሁድነት ፈርጆ ሊያስፈርጃት ይጣጣራል፡፡
     እውነታው ግን ወዲህ ነው፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ነበር፡፡ ነገር ግን የተመረጠበትን ሐዋርያዊ ተግባር ትቶ ከሰቃልያነ እግዚእ ጋር ተባብሮ ጌታውንና መምህሩን አሳልፎ በመስጠቱ፤ በኋላም በጥፋቱ ተፀፅቶ እንደ ጴጥሮስ ንስሐን ሳይሆን በብልጠት ምሕረትን ስለፈለገና ራሱን ስለገደለ የእርግማን እርግማን ተፈጽሞበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ለመዘከር፤ ልዩ ልዩ መዝሙራትን በማስተዛዘል በሚጸለይበት ጊዜ ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወዉሉዱ ይደምሰስ›› የሚል የመርገም ቃል አዝማች እንዲነገር ታደርጋለች፡፡ ይህንን ለማሳየት በትርዒት መልክ የሚፈጸም ሥርዓትም አላት፡፡ ይኸውም በመቋሚያ ጫፍ ላይ ጧፍ ተደርጎ (ታስሮ) አንደኛውን የዳዊት መዝሙር (መዝ. 1 ፥ 1 - 6) በማስተዛዘል ከተነበበ በኋላ፤ ‹‹ወፍኖቶሙሰ ለኃጥዕ ከመዝ ትጠፍዕ፤ የኃጥዓን መንገድ እንደዚህ ትጠፋለች›› ከሚለው ላይ ሲደረስ፤ ማኅበረ ካህናቱ በያዙት መቋሚያ በአንድ ላይ ውርጂብኝ በማውረድ በመቋሚያው ጫፍ ላይ የታሰረውን ጧፍ መብራት ያጠፉታል፡፡ ጧፍ ሰይጣን በልቡ የገባ የይሁዳ ምሳሌ ነው ፡፡ መቋሚያ የጌታ ምሳሌ ነው ፡፡ መቋሚያ ላይ መታሰሩ በክርስቶስ መሠረትነት ላይ ለሐዋርያነት ለዓለም ብርሃንነት መመረጡን ግን ይህን ክብሩን በማቃለሉ መውደቁን    ያመልክታል፡፡ ቀጥቅጠው ማጥፋታቸው ሰውን ያሳተው ዲያብሎስ በመስቀል ኃይል መመታቱን፣ ድል መነሳቱን ለማዘከር ነው፡፡
በመጨረሻም፤ ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ እንዘተሰብሐ፤ እግዚአብሔርን እናመስግነው የተመሰገነ ምስጉን›› በማለት የክርስቶስን ቤዛነቱን ያበሥራሉ፡፡ (ዐቢይ ጾምና ሰሙነ ሕማማት)፡፡ እናም ኩላዊት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፤ ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወዉሉዱ ይደምሰስ›› የሚለውን አሳበ ጥቅስ የምትጠቀመው ከላይ በገለጥነው አግባብ እንጂ ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን እንዳለው‹‹አይሁዶች ይወገዙበታል›› በሚለው አግባብ አይደለም፡፡
ከዚህ ፀራዊ አስተሳሰብ ብቻ እንኳን ተነሥተን እንፈርጅ (ፍረጃ ተገቢ ባይሆንም) ብንል፤ በፀረ ሴማዊነት እኩይ መንፈስ አብዶ ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ለፀረ ሴማዊነት ወይም ለፀረ አይሁድነት ቅስቀሳ አዛብቶ በመጠቀም፤ ኩላዊት የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በፀረ አይሁድነት ፈርጆ ሊያስፈርጅ እየዳከረ የሚገኘው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ነው እንጂ፤ ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ፤ ‹‹አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፤ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፤ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፡፡›› (ገላ. 3 ፥ 28) ያለውን የፀረ ዘረኛነት መልእክቱን መልእክቷ ያደረገችውን ቤተ ክርስቲያን፤ ከፀራውያን ጠብቆ፣ ፀራዊ አለመሆኗን ላለፉት ሃያ ዓመታት የሰበከው፣ የጻፈውና የተከራከረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አይደለም ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ፤ ‹‹በአይሁዶች መርዘኛ ጥርስ የገባች ሀገር ኢትዮጵያ!›› በሚል ጥላቻዊ ርእስነት በአተተው ጽሑፉ ውስጥ የዘራው ኑፋቄያዊ ሕፀጽ፤‹‹… በሥርዓቱ መሠረት አንድ ካህን በትዳር ሕይወት እያለ ባለቤቱ ወይም ሚስቱ ሰርቃ ከሌላ ወንድ ብትደርስና ከሌላ ወንድ መድረሷን አወቀም አላወቀ ከሌላ ከደረሰች በኋላ እሱ ቢደርስባት ሥልጣነ ክህነቱ ይፈርሳል፡፡ ከዚያ በኋላ በዚያ ሥልጣነ ክህነት መጠራትና ማገልገል አይችልም፤ መቅደስ ውስጥም መግባት ፈጽሞ አይችልም፡፡›› የሚለው ነው፡፡
በየትኛው ሥርዓት መሠረት እንደሆነና የሥርዓቱም ድንጋጌ በየትኛ አንቀጽና ቁጥር እንደሚገኝ ያልገለጸው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን የራሱን ድንጋጌ ‹‹በሥርዓቱ መሠረት›› በሚል ሽፋን የዋሃንን ለማደናገር ቢሞክርም ለዛሬ አልተሳካለትም፡፡ በየትኛውም የሥርዓት መጽሐፋችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት የቅጥፈት ድንጋጌ የለም፡፡
ዐይናማው ሊቅ (ነፍስ ኄር) ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን›› በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ሥልጣነ ክህነትን ከጋብቻ ጋራ ተያይዞ ስለሚፈርስበት ሁኔታ ፍትሕ መንፈሳዊን አንቀጽ ስድስትና ሰባትን መሠረት አድርገው ሲያብራሩ ቄስ ከሆነ፤ ‹‹ሁለት ጊዜ ያገባ፤ ሁለት ሚስት ያለው፤ ከሴሰኛ ሴት የደረሰ፤ በአገልግሎት ምክንያት ሚስቱን የተለየና የፈታ፤ እመነኩሳለሁ፣ ተባሕትዎ እይዛለሁ ብሎ ሚስቱን ያሰናበተ ካህን ከሹመቱ ይሻራል፡፡›› ብለዋል፡፡ ዲያቆን ከሆነ ደግሞ፤‹‹ሁለት ሴት ያገባ፣ ወይም በተሾመ ጊዜ ከሴት ርቄ ንጽሕና ጠብቄ እኖራለሁ ብሎ ተሥሎ ከተሾመ በኋላ ሥዕለቱን አፍርሶ ሚስት ያገባ ወይም ከዘማዊት ሴት የደረሰ፣ ተደብቆ ተክሊል ያደረሰ ወይም እመነኩሳለሁ ተባሕትዎ እይዛለሁ ብሎ ሚስቱን የፈታ ከዲቁናው ማዕረግ ይሻራል፡፡›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፤ 1993፣ 120–123)
ይህን የሊቁን ትንታኔና የፍትሕ መንፈሳዊ ድንጋጌ ይዘን የኹራፊውን የአምሳሉ ገብረ ኪዳንን ግለ ድንጋጌ ስንፈትሽ፤ እውነት አልባ መሆኑን ከመረዳት ባሻገር፤ አንድ ካህን ያለ ራሱ በደል ክህነቱን የሚያጣበት ምንም ዓይነት ቀኖናዊ መሠረት የሌለ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ በሚስቱ ስርቆት ተፈጸመ ቢባልና ይህም በማስረጃ ተረጋገጠ ቢባል በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ሚስቱ በዝሙት ወድቃ ተገኝታለችና ጋብቻው ሊፈርስ ይችላል እንጂ ክህነቱ ሊፈርስ የሚችልበት ምንም ዓይነት ቀኖናዊ መሠረት የለውም፡፡
ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እንዲህ አዛብቶና አጣሞ ያቀረበው የቤተ ክርስቲያን ጠላት ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ነው? ወይስ፤ ዕድሜ ዘመኑን ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዋጋ የከፈለው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት?
ቤተ ክርስቲያን በሥርዓቷ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ብላ የምትጠራቸው መሠረተ ዕምነቷን ያፋለሱትን፣ ሥርዓተ አምልኮዋን ያዛቡትንና ትምህርቷን የቀሰጡትን ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን በተጨባጭ እንደተመለከትነው፤ በነገረ ድኅነት ላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላትን መሠረተ እምነት አፋልሷል፡፡ የሥርዓተ አምልኮዋ ምሰሶ የሆነውን የሥርዓተ ክህነቷን ድንጋጌ አዛብቷል፡፡ የዕለተ ዓርብ ትምህርቷንና ተዕይንቷን በመቀሰጥ ለፀረ ሴማዊ ቅስቀሳው ተጠቅሞበታል፡፡ ይህ ድርጊቱ ደግሞ ከአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንደ አንዱ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡

2 - በታሪክ ‹ተፋለስ› ስም የተገለጠው መንደርተኝነት!
ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን አስቀድመን እንደገለጥነው ሃይማኖታዊ ድቀት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ድቀትም አግኝቶታል፡፡ አሰላለፉም ከወያኔያዊ ማንነቱ እንደሚመነጭ ያረጋገጠልንን ነጥቦችን እንመልከት፡፡
የመጀመሪያው፤ ‹‹ተኩላው፤ ‹‹ስማችሁ የለም›› በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ እጅግ በጣም በሚገርም ድፍረት የወያኔነቱን ተልእኮ ከውኗል፡፡ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ ‹‹የሌለውን ፍለጋ›› በሚል ርእስ በጻፈው ጽሑፍ ላይ… በክብረ ነገሥት ላይ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶ የሚተረከውን በዓለማውያኑ የታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ‹‹ሰሎሞናዊ›› በቤተ ክርስቲያን ደግሞ ‹‹የዳዊት መንግሥት›› እየተባለ የሚጠራውን ሥርዎ መንግሥት በሀገራችን አልነበረም በማለት ክብረ ነገሥትንና ይኼንን የክብረ ነገሥትን ታሪካዊ ትረካ የሚጠቅሱና የሚያረጋግጡ ከገድላት እስከ ድርሳናት፣ ከተአምራት እስከ ፍካሬያት፣ ከሊቃውንት እስከ ትርጓሜያት ያሉትን የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ሐሰተኞች አድርጓቸዋል፡፡›› በሚል ያልተባለውን እንደ ተባሉ አድርጎ ያቀረበው ነጥብ ነው፡፡
በአንደኛ ደረጃ በዚህ በኹራፊው ጽሑፍ ውስጥ የሐቅ (Fact) ችግር አለ፡፡ ይኸውም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት‹‹የሌለውን ፍለጋ›› በሚል ርእስ፤ ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን በመናድ ለተጠመደው ተስፋዬ ገብረ አብ ምላሽ በሰጠበት ጽሑፍ ውስጥ፤ ‹‹… ‹ሰሎሞናዊ› የሚባል የተለየ መንግሥት አልነበረም፡፡ ነገሥታቶቻችን ሁሉ ራሳቸውን ከኢየሩሳሌም ጋር ያያይዙ ነበር፡፡ ዐፄ ካሌብም ከናግራን ዘመቻ መልስ ዘውዳቸውን ኢየሩሳሌም ነው የላኩት፡፡ የዐፄ ገብረ መስቀል ልጅ ሙሴም መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም በኋላም ወደ ሶርያ በመጓዝ በዚያ መንነው ገዳም መሥርተዋል፡፡ ገዳማቸውም ‹‹ሙሴ አል ሐበሽ ገዳም›› ይባላል፡፡ የዛግዌ ነገሥታትም ሰሎሞናውያን የማይሆኑበት ምክንያት የላቸውም፡፡ በገድሎቻቸው ላይ ኢየሩሳሌምን አብዝተው የሚያነሡ፣ ማኅተሞቻቸው ሁሉ የዳዊት ኮከብ የሆኑ፣ በውቅር ቤተ ክርስቲያኖቻቸው የዳዊትን ኮከብ የቀረፁ የዛጉዌ ነገሥታት እንዴት ሰሎሞናውያን አይሆኑም?›› አለ እንጂ ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን፤ ‹‹ሰሎሞናዊ ሥርዎ መንግሥት በሀገራችን አልነበረም›› ብሎ የገለጸው ዓይነት ዐረፍተ ነገር በዲያቆን ዳንኤል ጽሑፍ ውስጥ በጭራሽ የለም፡፡ (ስማችሁ የለም እና ሌሎች፤ 2006፣ 138)
ይህም ቢሆን ዛጉዌያውያንን አግልሎ በራሱ የቆመ ሥርዎ መንግሥት አለመኖሩን ለመግለጥ ነው እንጂ ኹራፊው እንደሚለው፤ ‹‹ገድላቱን የድርሳን መጻሕፍቱንና ትርጓሜያቱን ሐሰተኞች›› ለማስባል አይደለም፡፡ የእነርሱ እውነተኛነት በራሳቸው የሚለካ እንጂ በሌላው ትረካ የሚለካ አይደለም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ፤ በዚህ በኹራፊው ጽሑፍ ውስጥ የእውቀት ችግር እናገኛለን፡፡ ይኸውም ‹‹በዓለማውያን የታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ‹‹ሰሎሞናዊ›› በቤተ ክርስቲያን ደግሞ‹‹የዳዊት መንግሥት›› በማለት ሁለት የተለያዩ ፅንሰ ሐሳቦችን አንድ በማድረግ አቅርቧል፡፡ በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያንም ‹‹ሰሎሞናዊ›› የሚለዉን ቃል እንደምትጠቀመው ሁሉ የታሪክ ጸሐፍቱም ‹‹የዳዊት መንግሥት›› የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ፡፡ አንዱን ቃል ለአንዱ ብቻ መስጠት አይቻልም፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የታሪክ ምሁራኑም ሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ‹‹የዳዊት መንግሥት›› የሚሉት ከዳዊት ዘር ሲወረስ ሲወራረስ የመጣውን ቅብዓ ንግሥና የፈጸምንና ስዩመ እግዚአብሔር ነን ብለው የዳዊትን ኮከብ የመንግሥታቸው መለያ ያደረጉ ነገሥታትን በሙሉ ሲሆን፤ ‹፣ሰሎሞናዊ›› የሚሉት ደግሞ በ1270 ዓ.ም. ተመለሰ የሚባለውን የይኩኖ አምላክን መንግሥት ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያሳያችሁ የእነዚህን ሁለተ ፅንሰ ሐሳቦች ልዩነት ሳያውቅ ነው የጨነገፈ ብዕሩን ለትችት ያነሣው፡፡
በሦስተኛ ደረጃ በዚህ በኹራፊው ጽሑፍ ውስጥ አምታችነት እናያለን፡፡ ይኸውም ‹‹ክብረ ነገሥትን እና ይኼንን የክብረ ነገሥትን ታሪካዊ ትረካ የሚጠቅሱና የሚያረጋግጡ ከገድላት እስከ ድርሳናት፣ ከተአምራት እስከ ፍካሬያት፣ ከሊቃውንት እስከ ትርጓሜያት ያሉትን መጻሕፍት ሐሰተኞች አድርጓቸዋል፡፡›› በሚል አምታቻዊነት ሰብዕና የቀረበው ሐሰት ነው፡፡ በመጀመሪያ ከገድላት እስከ ድርሳናት፣ ከተአምራት እስከ ፍካሬያት፣ ከሊቃውንት እስከ ትርጓሜያት ያሉት መጻሕፍት እውነተኛነትና ትክክለኛነት የሚረጋገጠው በራሳቸው በያዙት አሳበ ቁመና እንጂ በሌላው አሳበ ቁመና አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በይቀጥላል ደግሞ ክብረ ነገሥትን የሚጠቅሱም ሆኑ የሚያረጋግጡ አንተ የጠቀስካቸውን ዓይነት መጻሕፍት እስከ አሁን አልደረስኩባቸውምና የታተሙበትን ዓመተ ምሕረትና ገጻቸውን እየጠቀስክ ብትነግረኝ ጥሩ ነበር፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ ግን ክብረ ነገሥትን የሚጠቅሱ ገድላትም ሆኑ የድርሳን መጻሕፍት፣ የተአምርም ሆኑ የትርጓሜ መጻሕፍት የሉም፡፡ እናም የሌለባቸውን አለባቸው በማለት መጻሕፍቱን ሐሰተኞች ያደረጋቸው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን እንጂ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አይደለም፡፡
ሁለተኛው በታሪክ ‹‹ተፋለሰ›› ስም ጎጣዊ ደዌውን የገለጠበት፤
‹‹ከእነኝህ ክብረ ነገሥት ከሚተርከው የዳዊት (ሰሎሞናዊ) ሥርዎ መንግሥት ትረካ በተለያየ መንገድ ከሚያረጋግጡት ከሚተርኩት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት አንዱ የሆነውን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል ይወስድና አቡነ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣን በመሐል ከገቡት ከዛጉዌ ሥርዎ መንግሥት ተመልሶ ወደ ዳዊት ሥርዎ መንግሥት እንዲመለስ ስለማድረጋቸውና ከይኩኖ አምላክም ለቤተ ክርስቲያን ሲሦ ድርሻ ስለ መስጠታቸው የሚተርከውን የገድላቸውን ክፍል፤ እንዲህ የሚል ነገር በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል ላይ ፈጽሞ የለም ሲል ወያኔያዊ ክሕደቱን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ፈጽሟል፡፡… የደብረ ሊባኖስ ገዳም ያሳተመውን ‹ገድለ ተክለ ሃይማኖት› የሚለውን መጽሐፍ ገልጦ ምዕራፍ 26 ን እና 27 ን ቢያነብ ይኼ ተኩላ ያለአንዳች ፍርሐትና ሐፍረት በድንቁርና ድፍረት የለም ሲል የካደውን ታሪክ እንዳለ ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ ተኩላው በጠቀሳቸውና ባልጠቀሳቸው ታላላቅ ገዳማት ያሉ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድላት ላይም ይኼ ታሪክ በሚገባ አለ፡፡ ተኩላው የለም የሚለው የሌለ መስሎት ወይም እንዳለ ሳያውቅ ቀርቶ እንዳይመስላችሁ በጎሳና በፀረ አማራ መርዘኛ መርፌ ተወግቶ ከተመረዘ በኋላ በወያኔነቱ መሥራት ካለበት ሥራችና ከተሰጠው ተልእኮ አንዱና ዋነኛው በመሆኑ እንጂ፤ … አገው ነኝ ባይ ሆኗል፡፡
ይህንን የክብረ ነገሥትንና የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገድል ታሪክ ውሸት ነው፣ ተረት ነው፣ ፈጠራ ነው ሲል በሱ ቤት ዛጉዬዎች (አገዎች) ወገኖቹ ስለሆኑና የዳዊት (ሰሎሞናዊው) ደግሞ አማራ ስለሆነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካላቸው ቅድስና በአኀት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ካቸው ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት አንጻር በእሳቸው ገድል ላይ ይኼ ነገር ሰፍሮ መገኘቱ የታሪኩን እውነተኛነት ስለሚያረጋግጥ ለእሱና እሱን ለመሰሉት ደግሞ እንዲህ መሆኑ ስለማይመቻቸው ስለማይወዱት ስለማይፈልጉት ነው በገድላቸው የለም ሲል ዐይን ባወጣ የጅል ድፍረት ሸምጥጦ ሊክድ የቻለው፡፡›› የሚለው ማወረቅ ነው፡፡
በዚህ ንባቡ ውስጥ ዲያቆን ዳንኤል ‹‹የሌለውን ፍለጋ›› በሚለው ጽሑፉ በፍጹም ያላለውን ‹‹በገድለ ተክለ ሃይማኖት ውስጥ ስለ ሰሎሞናዊ ሥርዎ መንግሥትና ስለ ሲሦ ድርሻ የሚተርከውን ታሪክ የለም ብሎናል›› ሲል እንደ አለ አድርጎ አቅርቧል፡፡ ዳንኤል ግን፤ ‹‹ከላስታ ወደ ሸዋ የመንግሥት ዝውውር ሲደረግ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐይቅ እስጢፋኖስ በትምሕርት ላይ ነበሩ፤ (የሚጣቅ አማኑኤል ገድለ ተክለ ሃይማኖት እና ገድለ ኢየሱስ ሞአ በዝርዝር እንደሚተርከው) በዚህ የሥልጣን ዝውውር ላይ ይበልጥ ተሳታፊ የነበሩት አቡነ ኢየሱስ ሞአ ዘሐይቅ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሐይቅ የዐቃቤ ሰዓትነት ሥልጣን ነበረው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲሦ መንግሥት አግኝተዋል፤ የሚለው ትረካ፤ መንግሥት ወደ ጎንደር ከተቀየረ በኋላ (በ17ኛው መ. ክ. ዘ.) በተጻፈው በ‹ብዕለ ነገሥት› ላይ  የተገለጠ ነው፡፡ ብዕለ ነገሥት የነገሥታትን ሃብት ለማሳየት የተጻፈ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ነው፤ ከ ይኩኖ አምላክ ጋር ቃል ገብተዋል ተብሎ የተጻፈው፡፡›› አለ አንጂ ስለ ደብረ ሊባኖሱ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ያነሣው ነገር የለም፡፡ ቅጥፈት ይሉታል እንዲህ ነው፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን በገለጸው አግባብ ቢጽፍ እንኳን ስሕተቱ ምኑ ላይ ነው? የገድለ ተክለ ሃይማኖት ብዙ ቅጂዎች እዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ቅጂዎች ውስጥ ደግሞ የመጀመሪያው ወይም ኦሪጂናል የሚባለው የገድለ ተክለ ሃይማኖት ቅጂ በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፈው በተለምዶ ‹የዋልድባው› የሚባለውና በፈረንሳይ ሙዚየም በ‹‹Bib. Nat 138›› መለያ ቁጥር ተመዝግቦ የሚገኘው እና የሐይቅ እስጢፋኖሱ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ በእነዚህ ገድላት ውስጥ ‹‹ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት የተደረገውን ሽግግር ያከናወኑ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ለዋሉት ውለታ ለቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት ተሰጠ›› የሚል  የለም፡፡
ይህ ደግሞ በታሪክ ሊቃውንት ጭምር የተረጋገጠ ታሪካዊ እውነታ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት‹‹Church and State in Ethiopia››በተባለው ታዋቂ መጽሐፋቸው ይህንኑ ሲያረጋግጡ፤ አቶ አበባው አያሌው የተባሉ የታሪክ ምሁር ደግሞ በየካቲት 1998 ዓ.ም. ‹‹በታሪክ ጥናት ትልቁ ወንጀል›› በሚል ርእስ በ‹‹ሐመር›› መጽሔት ላይ በጻፉት መጣጥፍ፤ ‹‹… ዐፄ ይኩኖ አምላክ፤ ‹ ሲሦውን የግዛቴን ክፍል ለቤተ ክርስቲያን እሰጣለሁ፤› ለማለታቸው ምንም ዓይነት የታሪክ ምንጭና ማስረጃ የለም፡፡ ዘውድ ጭነው ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላም እንደ ማንኛውም ንጉሠ ነገሥት ጉልት በመጎለት እና ሕንፃ በማሳነፅ ቤተ ክርስቲያንን ደገፉ እንጂ ከግዛታቸው ሲሦውን ለቤተ ክርስቲያን አልሰጡም፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ተለምዶአዊ አነጋገሮችና አፈ ታሪኮች የተነሣ ለዘመናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአገሪቱ መሬት ሲሦ ባለቤት ተደርጋ ስትጠቀስ ኖራለች፡፡ ታሪካዊ እውነታው ግን ቤተ ክርስቲያኗ መሬት በጉልትነት ይዛ ኖራለች፤ ነገር ግን ይህ በጭራሽ የአገሪቱ ሲሦ መሬት አይደለም፡፡›› በማለት አጽንዖት ሰጥተው ነበር፡፡ /ሐመር፣1998 ፣ /
‹‹ሐመር›› መጽሔትም የገድላቱን ሐቀኛ ትረካ እና የምሁራኑን የታሪክ ትንተና በማስረገጥ (እንግዲህ ኹራፊው አምሳሉ እርምህን አውጣ)፤ ‹‹በአሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በዛግዌና ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥቶች መካከል በነበረው የሥልጣን ሽኩቻ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሁለቱን ተቃራኒ ወገኖች በማስማማት፣ ዘውድ ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት በሰላም እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡ አስቀድሞ ቃል በገባላቸው መሠረት ዐፄ ይኩኖ አምላክ ሲሦውን (1/3ኛውን) የግዛት ክፍል ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቷቸዋል፤ የሚለው አፈ ታሪክ ነው፡፡›› ሲል ይደመድማል፡፡/ዝኒ ከማሁ፣ /
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይህን ገድላዊና ታሪካዊ ምንጭ ያለውን እውነታ በተጠየቃዊ መንገድ ‹‹የሌለውን ፍለጋ›› በተባለው ጽሑፉ፤ ‹‹ተስፋዬም ሆነ ሌሎች እንደሚሉት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከቅድስና ሥራ በቀር የገቡበት ፖለቲካ የለም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ ደብረ አስቦ ሲገቡ ይኩኖ አምላክ በመንበሩ ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን የጠበቃቸው ዘንዶ ይመለክበት የነበረ ዋሻ እንጂ ከሲሦ መንግሥት የተገኘ ግብር አልነበረም፡፡ … ሃያ ስምንት ዓመት በደብረ አስቦ ሲቀመጡም የጎበኛቸው ንጉሥ አልነበረም፡፡ ደቀ መዝሙሮቻቸው ከዝንጀሮ ጋር እየተሻሙ እህል ዘርተው ከማብቀል ውጪ የተለየ ርስት አልነበራቸውም፡፡››ሲል ምሁራዊ ምልከታውን አተመበት፡፡-(ስማችሁ የለም እና ሌሎች፤2006፣139)
3 - በጥላቻ የተለወሰው አማተር ፖለቲከኝነት!
እነዚህን በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ትንታኔዎች ለመገንዘብ የሚያስችለውን አእምሮ በጭፍን ጥላቻ ያጣው እና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹የሌለውን ፍለጋ›› በተባለው ጽሑፉ ያላለውን እንደ አለ አድርጎ በማቀረብ ስምዐ ሐሰት የሆነው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን፤ በዚያ ዘባተሎ ‹‹ጽሑፉ›› ዲያቆን ዳንኤልን በፀረ አማራነት፣ በወያኔነት፣ በድንቁርና ከስሶታል፡፡ ለፀረ አማራነቱ ‹‹አገው›› መሆኑን ሲጠቅስ፤ ለወያኔነቱ ደግሞ የባለቤቱን ‹‹ትግሬነት››ና ‹‹ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥትና ሲሦ መንግሥት የለም›› ብሏል በማለት ጭራሽ በሐሰት በተሞላ የፈጠራ ክስ ነው፡፡
ሊቃውንቱ ‹‹ጨዋ ደፋር ነው›› እንደሚሉት ያለምንም ሐፍረት ያቀረሸውን የጎጠኛነትና የጥላቻ ፖለቲካዊ ቅርሻቱን እንመርምር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ኹራፊው አምሳሉ አገላለጽ ከሆነ ‹‹አገው›› ማለት ፀረ አማራነት ነው፡፡ ኹራፊው አምሳሉ፤ አገዎች ‹‹ፀረ አማራዎች›› ስለሆኑና ዳንኤል ደግሞ አገው ስለሆነ ‹‹ፀረ አማራ›› ነው፤ አለን፡፡ ይህን ከራሱ ከአምሳሉ አመክንዮ አንጻር ስንገለብጠው አማራዎችም ፀረ አገው ናቸው ማለት ነው፡፡ ኹራፊው አምሳሉ ደግሞ ራሱን የአማራ ጠበቃ አድርጎ ስለአቀረበ ፀረ አገው ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዲያቆን ዳንኤል ላይ በጥላቻ የተነሣው ከፀረ አገውነቱ እንጂ የተለየ በደል በ‹‹አገው›› ዳንኤል ላይ ስለአገኘበት አለመሆኑን አረጋገጠ፡፡ ይሁንና ከእውነታ አንፃር ግን ዲያቆን ዳንኤል የአገው ተወላጅ አይደለም፡፡ እኔ አገው ነኝ ብሎም አያውቅም፡፡ ሰለ አንድ ሕዝብ እውነትን ለመናገር ከዛ ሕዝብ መውለድ የግድ አያስፈልግም፡፡ ሰው መሆንና እውነተኛ መሆን ይበቃል፡፡ እነ ሲልቪያ ፓንክረስት ከኢትዮጵያ ምድር የተገኙ ኢትዮጵያውያን ሆነው አይደለም በዚያ በወረራ ዘመን ሰለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አብዝተው የተናገሩት ፡፡ እንግዲህ እግዜር ያሳያችሁ ስለኢትዮጵያዊነት ለመቀባጠር የተነሣው እንዲህ ዓይነቱ ጎጠኛ ነው፡፡
ሲቀጥል ደግሞ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወያኔ ነው ለማለት የጠቀሰው አንደኛ ማስረጃ የባለቤቱን ‹‹ትግሬነት›› ነው፡፡በዚህ ደግሞ የፖለቲካ አቋም ከጎጥ ማንነት እንደሚመነጭ አድርጎ ያቀርባል፡፡ ይህ ደግሞ ትግሬ የሆነ ሁሉ ወያኔ ነው ያስብላል፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የደመ ነፍስ ፍረጃ ደግሞ የኹራፊው አምሳሉ መገለጫ ነው፡፡ ከዚህ ማንነቱ በመነሣት ነው እንግዲህ ዳንኤል ባለቤቱ ትግሬ ስለሆነችና ትግሬ ደግሞ ወያኔ ስለሆነ በባለቤቱ በኩል ‹‹ወይኗል›› የሚል ድንቁርናን የሚሰብከን፡፡ እንግዲህ ትግሬነት ወያኔነት ከሆነና ወያኔነትም በጋብቻ የሚወረስ ከሆነ፤ አደንቃቸዋለሁ የሚላቸው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም የቀድሞ ሚስታቸው ትግሬ ናቸውና ፕሮፍ ወይነው ይሆን?
እንግዲህ በአምሳሉ ትንታኔ መሠረት ትግሬነት ወያኔነት ከሆነ ወያኔን በመቃወም ብቻ በወያኔ እስር ቤት መከራውን እያየ ያለው የነጻነት ታጋዩን አብርሃ ደስታን ወያኔ ልንለው ነው? በተቃውሞ ጎራ ተሰልፈው ለአለፉት ሃያ ዓመታት ወያኔን ሲታገሉ የነበሩት ዶክተር ኃይሉ አርአያ ትግሬ ናቸውና ወያኔ ይሆኑ?
 ከእውነታ አንፃር ደግሞ እስቲ እንመልከት፤ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ባለቤት ወ/ሮ ጽላት ጌታቸው ትባላለች፡፡ ምንም እንኳን ትግሬ መሆን ነውር ባይሆንምትግሬ አይደለችም፡፡ የአማራ ተወላጅ ከሆኑ ቤተሰቦች የተገኘች፣ አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገች፣ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡ ለማንኛውም ‹‹ጽላት›› በሚል የሚጠሩ ሁሉ ትግሬዎች ናቸው ከተባለ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ታቦታቱን ማደሪያ ያደረጉት ጽላቶች  ሁሉ ትግሬዎች ናቸው ማለት ነው? ይህ ደግሞ ‹‹ትግሬነት ወያኔነት ነው›› በሚለው የአምሳሉ ስሌት ከተኼደ ታቦታቱ ሁሉ ‹‹ወያኔዎች›› ናቸው ያስብላለል፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ክሕደት ነው፡፡ ስለዚህ አምሳሉ ገብረ ኪዳን ከሐዲ ነው ያስብላል፡፡
ሌላው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹ወያኔ ነው›› ለማለት እንደ ማስረጃ የጠቀሰው ‹‹ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥትና ሲሦ መንግሥት የለም›› ብሏል፤ የሚለውን ነው፡፡ ይህን ከሦስት አቅጣጫ እንፈትሸው፡፡ የመጀመሪያው ከወያኔ የታሪክ ትንተና አቋም አንፃር ነው፡፡ ወያኔ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደሚለው፤ ‹‹ሰሎሞናዊ የሚባል የተለየ መንግሥት አልነበረንም፡፡ ሲሦ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት በኩል አልተሰጠም፤›› አይልም፡፡ ወያኔ ‹‹አዲስ ራእይ›› በተባለው ንድፈ አሳባዊ መጽሔቱም ሆነ ለኢንዶክትሪኔሽን በአዘጋጀው መጻሕፍቱ፤ ‹‹በሰሎሞናዊው እና በዛግዌ ሥርወ መንግሥታት መካከል በነበረው ሽኩቻ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለይኩኖ አምላክ አድልተውና ይኩኖ አምላክም የሸዋ ሰው ስለሆነ ለዘራቸው አድልተው መንግሥትን ከዛዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት እንዲሸጋገር አድርገዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት በዋሉት ውለታ ለቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት ተሰጠ፡፡›› ነው የሚለው፡፡ ይህ ደግሞ ተስፋዬ ገብረ አብ፤ ‹‹የስደተኛው ማስታወሻ›› በተሰኘ መጽሐፉ ውስጥ፤ ‹‹የፍስሐ ጽዮን ፖለቲካ›› በሚል ርእስ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከጻፈውና የዚህ ጽሑፍ ቀጥታ ቅጂ ወይም ፎቶ ኮፒ ከሆነው ከኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን አቋም ጋር አንድ ነው፡፡
ስለዚህ በኹራፊው ስሌት መሠረት የአቋም ተጋሪነት የሚያወይን ከሆነ ከወያኔ አቋም በተቃራኒ፤ ‹‹ሰሎሞናዊ የሚባል የተለየ ሥርወ መንግሥት አልነበረንም፡፡ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት በኩል ሲሦ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያን አልተሰጠም፡፡›› ያለው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሳይሆን፤ የወያኔን አቋም የራሳቸው አቋም አድረገው፤ ‹‹በዛግዌ እና ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥታት መካከል በነበረው ሽኩቻ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለይኩኖ አምላክ አድልተውና ይኩኖ አምላክም የሸዋ ሰው ስለሆነ ለዘራቸው አድልተው መንግሥትን ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት እንዲሸጋገር አድርገዋል፡፡ ለዚህም ውለታ ለቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት ተሰጥቷቸዋል፡፡›› ያሉት ተስፋዬ ገብረ አብ እና ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ናቸው፤ የወየኑት ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ከታሪክ ምሁራኑ ትንታኔ አንፃር ነው፡፡ አስቀድመን በስም የጠቀስናቸው ፕሮፌሰር ታደሠ ታምራት፤ ‹‹Church and State in Ethiopia›› በሚል ርእስ ከዛሬ አርባ ሦስት ዓመታት በፊት በአሳተሙት መጽሐፋቸው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት አቶ አበባው አያሌው ደግሞ፤ ‹‹በታሪክ ጥናት ትልቁ ወንጀል›› በተሰኘ ርእስ ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት በ‹‹ሐመር›› መጽሔት ላይ በጻፉት መጣጥፍ፤ ስለ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት እና ሲሦ መንግሥት፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከሚያራምዳቸው አቋሞች ጋር ተመሳሳይ አቋሞችን አራምደዋል፡፡ እንግዲህ በኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ስሌት መሠረት የዲያቆን ዳንኤልን ታሪካዊ ትንታኔ ምሁራዊ ምልከታን ያጎናጸፉትን እነዚህን የታሪክ ምሁራን ወይነዋል ልንል ነው?
ሦስተኛው ከ‹‹ሐመር›› መጽሔት ምልከታ አንፃር ነው፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ‹‹ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለዘራቸው አድልተው መንግሥት ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት እንዲሸጋገር አድርገዋል፡፡ በውለታም ለቤተ ክርስቲያን ሲሦ መሬት ተሰጥቷቸዋል፤›› የሚለውን ትረካ አጽንዖት ሰጥቶ ‹‹የለም›› ያለውን፤ ‹‹ሐመር›› መጽሔት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ‹‹አፈ ታሪክ›› ብሎታል፡፡ ስለዚህ በኹራፊው በአምሳሉ ገብረ ኪዳን የፍረጃ ስሌት መሠረት ‹‹ሐመር›› መጽሔት እንዲህ በማለቷ ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት የወያኔ ልሳን   ነበረች ልንል ነው? የፖለቲካ ድንቁርና ይሉታል ይኼ ነው፡፡
ከላይ ከጠቀስናቸው የፍረጃ ነጥቦች ባሻገር ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን፤ ‹‹የወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚ ነው›› ለሚለው አሉባልታው እንደ ማስረጃ የጠቀሰው፤ ‹‹የቅዱስ ሲኖዶስ መንበር አይሰደድም›› የሚለውን አቋም ነው፡፡ ይኼ አቋም ደግሞ የዲያቆን ዳንኤል አቋም ብቻ ሳይሆን የማኅበረ ቅዱሳንም የጸና አቋም ነው፡፡ የማኅበረ ቅዱሳንም ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና የእውነተኞቹ ኦርቶዶክሳውያን ምሁራን አቋምም ነው፡፡
ከዛሬ ሃያ ሦስት ዓመታት በፊት በዲያስጶራነት የሚገኙት አበው፤ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ስደተኛ ሲኖዶስ አቋቁመናል፤›› ብለው ሲያውጁ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ‹‹ሐመረ ጽድቅ›› በተሰኘው ልዩ ዕትሙ ተቋቋመ ስለተባው ‹‹ስደተኛ ሲኖዶስ›› የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና ከመንበራቸው የተሰደዱ ቅዱሳን አባቶችን አብነት በመጥቀስ፤ ‹‹የቅዱስ ሲኖዶስ መንበር አይሰደድም›› የሚለውን አቋሙን ግልጽ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ይሁንና ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ማኅበረ ቅዱሳን በ1997 ዓ.ም ‹‹ሰው እንጂ መንበር አይሰደድም›› የሚለውን ሃይማኖታዊ አቋሙን ለመተንተንና ለኦርቶዶክሳውያን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከአዘጋጀው ጽሑፍ ውስጥ፤ ምንም ዓይነት ምንጭ ሳይጠቅስ ራሱ እንዳዘጋጀው ጽሑፍ አድርጎ ያለ መልኩ ‹‹የስደት ሲኖዶስ›› መቋቋምን ትክክለኛነት ለማስረዳት ሲጠቀምበት አስተዋልኩ፡፡ በዚህም የዚህን ሰው ጤነኛነት በእጅጉ ተጠራጠርኩ፡፡ ያለ አንዳች ሐፍረት ደግሞ፤ ‹‹ለአራት ኪሎ አባቶች በመጽሔት ላይ መልስ ስሰጣቸው፤ እሽ የሳቸው (ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ) መሰደድ እንደ ጥፋት አይቆጠር ሲኖዶስ ግን አይሰደድም መንበረ ፓትርያርክም አይሰደድም ብለው እዚያ ማቋቋማቸው ትክክል አይደለም፤ ማለት አመጡ፡፡ እኔም አስከተልኩና… ›› እያለ ይቀጥልና፤ ‹‹ድርጊቱ ፀረ ክርስትና ነው›› በማለት ጎጣዊ ዝምድና የወለደውን ርካሽ ፖለቲካውን ይደሰኩራል፡፡ በመጀመሪያ በ‹‹አራት ኪሎ ያሉት አባቶች›› ያላቸው አባቶቻችን በየትኛውም ኦፊሴላዊ መግለጫዎቻቸው ሆነ በሌላ ‹‹የአቡነ መርቆርዮስ መሰደድ እንደ ጥፋት አይቆጠርም፤ ይቆጠራልምም፤›› ብለው አያውቁም፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የኹራፊው የአምሳሉ ገብረ ኪዳን ጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምኑ ነውና ነው ‹‹የአቡነ መርቆርዮስ መሰደድ እንደ ጥፋት አይቆጠርም›› የሚል መግለጫ የሚሰጠው?  ማንስ አንብቦት ነው? ማንስ እሱነቱን አውቆ ነው? ይህ መቼም እጅግ ሲበዛ አቅምን እና ደረጃን አለማወቅ ድፍረት ነው፡፡
ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና፤ ከማኅበረ ቅዱሳን ባሻገር ‹‹መንበር አይሰደድም›› የሚለውን የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ሃይማኖታዊ አቋም በመጋራት ‹‹መንበር ይሰደዳል›› የሚለውን ፖለቲካዊ አቋም በመንቀፍ ከጻፉት ምሁራን አንዱ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከዛሬ ሰባት ዓመታት በፊት፤ ‹‹ በግሌ ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ አንዳፍታ ላውጋችሁ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለው ነበር ፡፡
‹‹ … መሠረታዊውና ዋናው ጥያቄ ግን ይህ ነው ፤ ሲኖዶስ እንደቤተ ክርስቲያን ፓርላማ ከታየ አሜሪካ ላይ የሚቋቋመው ሲኖዶስ የየትኛው ቤተ ክርስቲያን ፓርላማ ለመሆን ነው ?ለአንድ አገር ከአንድ የበለጠ ፓርላማ ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ ለአንድ ቤተ ክርስሰቲያንም ከአንድ የበለጠ ሲኖዶስ ሊኖራት አይችልም ፡፡ ሲኖዶስ ፈጣሪዎቹ መፍትሔ አድርገው ያዩት ሌላ ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም ነው ፡፡ እንግዲህ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግል መሆኑ ቀርቶ የነሱን ሲኖዶስ የምታገለግል ቤተ ክርስቲያን ሊፈጥሩ ነው ፡፡ … አሁን ደግሞ የስደተኞቹን ጳጳሳት ፍትወት ለማርካት ሌላ ግንጠላ ሊያመጡባት ተማምለው ተነሥተዋል ፡፡ …ጎጠኛ መሆን ቤተ ክርስቲያንን መክዳት መሆኑን ጎጠኞች ተከታዮቻቸው የተገነዘቡት አይመስለኝም ፡፡ ›› /ጌታቸው ኀይሌ፣2000 ፣251 /
ይኼንኑ አቋማቸውን በማጠናከር ደግሞ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ‹‹እናት ቤተ ክርስቲያናችን አልተከፈለችም›› በሚል ርእስ በጻፉት መጣጥፍ ላይ እንደሚከተለው ብለው ነበር፡፡
‹‹ለአንድ ቤተ ክርስቲያን የሚኖራት አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ አመራር ብቻ ነው፡፡  ይህንን ሕግ ሁለት ሲኖዶስ የፈጠሩት አዲስ አበባ ያሉትና ስደተኞቹ ካህናት ያውቁታል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ያለነው ሕዝበ ክርስቲያን፣ ካህናቱን ጨምሮ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደተኞች ነን፡፡ የምናደርገው ትግል ሀገራችን ነጻ ሆና እንድንኖርባት ነው እንጅ፤ ይህን ካላገኘን ብለን በተሰደድንበት ዓለም ኢትዮጵያዊ መንግሥትና ኢትዮጵያዊት ቤተ ክርስቲያን ልናቋቁም አይደለም፡፡ ስለዚህ የተሰደዱትን ካህናት የምጠይቃቸው፤‹‹የእኛን ሲኖዶስ ተከተሉ›› እያሉ ሕዝብ ማስጨነቃቸውንና የመከፋፈል ምክንያት መሆናቸውን ትተው፤ የድዮስጶራው ሕዝብ ወያኔን ሲቃወም ተጨማሪ ኃይል እንዲሆኑ ነው፡፡ ‹‹የእኛን ሲኖዶስ ተከተሉ›› ማለት የሃይማኖት ስደተኞች ሳንሆን፤ የሃይማኖት ስደተኞች ሁኑ፤ ከኢትዮጵያው ሕዝበ ክርስቲያን ተለዩ፤›› ማለት ነው፡፡ ብዙዎች የሚከተሏችሁ ወያኔ የተጠቃላቸው መስሏቸው ቢቸግራቸው ነው እንጂ፤ ኢትዮጵያ ካለው ሕዝበ ክርስቲያን መለየት ፈልጎ አይደለም፡፡ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ማእከል ከሕዝቡ መካከል መሆን እንዳለበት መካድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ በሕዝብ መሐል ያለውን የኢትዮጵያውን ጭቁን ሲኖዶስና ቤተ ክርስቲያንን አመራር ታግሎ፣ ከወያኔ እጅ ነጻ አውጥቶ ከመውሰድ ይልቅ፤ ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ሲኖዶስ ማቋቋም ሕጋዊ አለመሆኑን ሲኖዶስ አቋቋሚዎቹ ያውቁታል፡፡ መፍትሔ አድርገው ያዩት የኢትዮጵያውን ሲኖዶስ፤ ‹ሕገ ወጥ› እነሱ ያቋቋሙትን፤ ‹ሕጋዊ› ማለት ነው፡፡ ግን ሁለቱም ሕገ ወጥ ናቸው፡፡ ልዩነቱ የኢትዮጵያው ሲኖዶስ ‹ሕገ ወጥ› የሆነው መንግሥት አስገድዶት ሲሆን፤ የውጪዎቹ ካህናት ሲኖዶስ ያቋቋሙት በስደተኛው ሕዝብ ብዛትና ብሶት በመጠቀም ነው፡፡ በወያኔ ጭቆና የተሰደደው ሕዝብ ብዙ ባይሆን፤ ስዱዳን ጳጳሳት ምንም ብዙ ቢሆኑ ብቻቸውን ሲኖዶስ አያቋቁሙም ነበር፡፡ በሲኖዶስ ስም የተደራጁት ለአገልግሎት እንዲመቻቸው ብቻ ከሆነ፤ ሕገ ወጥ ሲኖዶስ ሳያቋቁሙ የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠትና ሕዝበ ክርስቲያኑን አስተባብሮ የወያኔን ክንድ መመከት ይቻላል፡፡ ሕገ ወጥ ሲኖዶስ ማቋቋም ግን ሕዝብ ስለሚከፋፍል መንበሩን ከመልቀቅ የከፋ ጥፋት መጨመር ነው፡፡›› (ጌታቸው ኃይሌ፤2004፣4-5)
እንግዲህ ‹‹መንበር ይሰደዳል›› ብሎ ፖለቲካዊ አቋም ከያዘው ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ተለይቶ፤‹‹መንበር አይሰደድም›› ብሎ ሃይማኖታዊ አቋም የያዘውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚ የሚያሰኘው ከሆነ፤ ኹራፊው ራሱ እንዳለው በየጊዜው የወያኔ ጅራፍ የሚያርፍበት ማኅበረ ቅዱሳን፤ ‹‹መንበር አይሰደድም›› የሚል ሃይማኖታዊ አቋም አለውና የወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚ ነውን? ከተጠረጠሩ በአማራ ብሔርተኛነት እና በፀረ ወያኔነት ይጠረጠሩ ካልሆነ በስተቀር በወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚነት በፍጹም የማይጠረጠሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፤‹‹መንበር አይሰደድም፤ ሕገ ወጥ ሲኖዶስ ማቋቋም ግን ሕዝብ ስለሚከፋፍል መንበሩን ከመልቀቅ የከፋ ሌላ ጥፋት መጨመር ነው፡፡›› የሚለውን ሃይማኖታዊ አቋም በፖለቲካ ተዋስዖ/Discourse / ተንትነው ያቀረቡት የወያኔ ተልእኮ አስፈጻሚ ስለሆኑ ይሆን? ከኹራፊዉ አምሳሉ ገብረ ኪዳን ውጪ ሌላ ሰው አዎን የሚል ያለ አይመስለኝም፡፡
4- አቅጣጫ የሳተና በተቃርኖ የተሞላ የሴራ ትንተና!
ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ኢስላማዊውን ነቢይ ‹‹መሐመድ ›› ብሎ ዘርጥጦ የጠራቸውን፤ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ኢስላማዊ ነቢይነታቸውን አክብሩ ‹‹ነቢዩ መሐመድ ›› ብሎ መጥራቱን እንደ ጥፋት በመቁጠር በ‹‹ደፋርነት›› ከስሱታል  ፡፡
በኢስላም አስተምህሮ አለማመን እና የእነርሱን ነቢያት አለመቀበል አንድ ነገር ሆኖ መሪያቸውን ክብረ ነክ በሆነ አጠራር መጥራትን ትክክል የሚያደርግ የክርስትና አስተምህሮ የለም ፡፡ሌላው ቢቀር ሰብአዊ ፍጡርነታቸው ያስከብራቸዋል ፡፡ ዲያቆን ዳንኤልም የፈጸመው ይህንኑ ነው ፡፡ ኹራፊው እንዳደረገው መሆን ግን ኢ ክርስትና ነው ፡፡
ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ምን ያህል ሚዛኑን የሳተ መሆኑን የሚያርጋግጥል በአንድ በኩል የሙስሊም ወንድሞቻችን ነቢይ የሆኑትን ነቢዩ መሐመድን በቃለ አክብሩ አትጥሯቸው ፤‹‹ መሐመድ በሉት›› እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ከወያኔ ጋር የሚያደርጉትን ስላማዊ ትግል ለተንሻፈፈው ፖለቲካዊ ፍትወቱ ይጠቀምበታል ፡፡ መሪያቸውን እየዘረጠጡና ክብር እየነሱ በዲያቆን ዳንኤል የኦሪት ፍየልነት  የሰላማዊ ትግላቸው ተከባካቢና ጠባቂ ሆኖ መገለጥ አይቻልም ፡፡በተወሰኑ ሰዎች ዘንድ ተችሉም ከሆነ እጅግ ሲበዛ ሞራለቢስነት ነው ፡፡ወያኔስ የሚያደርገው ይህንኑ አይደለም ፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹አክራሪ እስልምና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስቸጋሪ ፈተና ›› በተሰኘው ጥልቅ ጥናታዊ ወረቀቱ  የክርስትናችን አስቸጋሪ ፈተና ‹‹ አክራሪ አስልምና ›› አለ እንጂ ኹራፊው አምሳሉ ‹‹የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጠላት ስውሩ ተኩላ ዳንኤል›› በተሰኘው ግልብ ጹሑፉ ላይ እንደተመለከተው የክርስትናችን አደጋ ‹‹ ከፊሉ እስላም ነው ›› አላለም ፡፡የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጥናት ለራሱ ለእስልምናውም ፈተና የሆኑትን አክራሪዎችን የክርስታናችን ፈተና አድርጉ ሲያቀርብ ፤የኹራፊው አምሳሉ ግልብ ጹሑፍ ግን ‹‹እስላም የሆነ ሁሉ አክራሪ ነው ›› በሚል ስሌት መሠረት ‹‹ ከፊሉ እስላም ››በሚል አገላጽ የክርስትናችን አደጋ ግማሹ ሙስሊም ሙሉ በሙሉ  እንደሆነ አድርጉ አቅርቧል፡፡ ሰለዚህ ኹራፊው አለ በሚለው ክርስቲያኑንና ሙሲሊሙን የማፋጠጥ የወያኔ ሴራ ሰተት ብሎ የገባው ኹራፊው እንጂ ዲያቆኑ አይደለም ማለት ነው ፡፡
ኹራፊው አቅጣጫ የሳተበትና በተቃርኖ የተሞላበት ሌላው ነጥብ ‹‹ ‹አራቱ ኀያላን › የሚለውን መጽሐፍ ያዘጋጀበት ምክንያት የአማራ ነገሥታትን ስምን ለማጥፋት በማሰብ ነው ፡፡ ›› የሚለው ነው ፡፡ይኸው ሰው ‹‹ አራቱ ኀያላን የሚለው መጽሐፍ የተጻፈው የአማራ ነገሥታትን ስም ለማጥፋት በማሰብ ነው ›› ብሎ ከደመደመ በኃላ ይህንኑ አገላለጹንእና ሰለዲያቆን ዳንኤል ያለውን የሐሰት ክስ በመቃርን ‹‹ዲ/ን ዳንኤል እየሠራ ያለው ሥራ በእውነት አጅግ የሚያስመሰግነው ነው ፡፡ … የዚህ መጽሐፍ (የአራቱ ኀያላን መጽሐፍ ማለቱ ነው) ዋነኛ ዓላማው የሚመስለኝ በዚህ ዘመን ያሉ አባቶች መንፈሳዊና ግብረ ገባዊ ብቃት ከቀድሞቹ አባቶቻችን ጋራ ሲነጻጻር ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማሳየትና የቀደሙቱ አባቶቻችንን የዓላማ ጽናት በአርአያነት እንዲወስዱ ማድረግ የሚሞክር ወይም መሆን አለበት ፡፡ ›› በማለት ያፈርሰዋል ፡፡
ኹራፊው በመርሕ ላይ የተመሠረተ ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ የማያደርግ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል ፡፡ የትኛውንም አሙን በየትኛውም ጊዜ ለመተው በቂ ምክንያትና ማሰብ አያስፈልገውም ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን ሲያወድስና ዲያቆን ዳንኤልን ሲያራክስ ምክንያት የለውም ፤ተስፋዩ ገብር አብን ደግፎ ፣ዲያቆን ዳንኤልን ሲቃወም ተጠየቅ የለውም ፤አቶ ኤርሚያስን ደግፎ፣ዲያቆን ዳንኤልን ሲቃወም አመክንዩ የለውም ፡፡በጭፍን ይደግፋል፤ በጭፍን ይቃወማል ፡፡ ለእርሱ መውደድና መጥላት በቂ ነው ፡፡ የዘመናችን ‹‹ድንግል በክልኤ›› እንግዲህ ይህ ነው ፡፡
ከዚሁ ጋራ በተጨባጭ የማውቀውን እንደሱሯጽ (as side issue)ልንገራችው ፡፡ኹራፊው አምሳሉ በተለይ ከአቶ ኤርሚያስም ለተስፋዬ የተሰጠው ምላሽ ያንገበገበው ስለ ሁለት ነገር ነው ፡፡አንደኛው በ1990ዎቹ ውስጥ የካድሬነት መልማይ የጡት አባት በመሆን ትንሽ የወያኔን ፍርፋሪ እንዲያገኘ ያደረገው ተስፋዬ ነበር ፡፡ሁለተኛው ሥራ በፈታባቸው ዓመታት ውስጥ እንጀራ የሆኑት የተስፋዬ የጥፋት መጻሕፍት ነበሩ ፤አሁን ደግሞ የአቶ ኤርሚያስ መጽሐፍ፡፡እኛም በመጽሐፍ ቅርጽ እያዘጋጀ የሚሸጣቸውን ፎቶ ኮፒ ‹መጽሐፍ› ገዝተን ያነበብ ነው እርሱ ከአሰማራቸው መጻሕፍት አዟሪዎች ነበር ፡፡ከእነዚህ በቀጥጣ ከማውቃቸው መረጃዎች ተነሰቼ ስደመደም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስቀድሞ ለተስፋዬ በኃላ ለአቶ ኤርሚያስ በሰጠው ጹሑፍ መደምደሚያ ላይ‹‹ ሌላውንም ነገር የሚነግሩን እንዲህ ሐሰት ይዘው ነው ማለት ነው›› ማለቱ አስቆጥቱታል ማለት ነው ፡፡ ዲያቆን ዳንኤል እንዲህ መደምደሙ መጻሕፍቱ በሰፊው ተሰራጭተው፣ ሰዉ አንብቧቸው ፣የሥርዐቱን ፀረ ዲሞክራሲያዊነት እንዳይረዱና የተአማኔነት ችግር እንዲገጥማቸው ሊያደርግ ይችላል ከሚል በጎ መንፈስ ሳይሆንመጻሕፍቱን መረጃ ተአማኔነት ዋጋ በማሳጣት ገዥ ሊያሳጣኝ ይችላል ከሚል ጥቅመኝነት የመነጨ ቁጣ ይመስለኛል ፡፡
ኹራፊው አምሰሉ ገብረ ኪዳን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹በአገሪቱ ስላለው ሰብአዊ መብት ገፈፋ፣ ስለሙስና መሰራፋት፣ ሰለኑሮ ውድነት፣ እምነትን በነጻነት የማራመድ መብት ማጣትን፣በዋልድባም ሆኑ በሌሎች ገዳማት ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ላይ  አልጻፈም፤እንደጸሐፊ አይደለም እንደ ዜጋ እንኳን በእነዚህ ነገሮች ላይ አንድም ነገር ተናግሮ ተንፍሶ አያውቅም ፡፡ ››ሲልም በሐሰት ይከሰዋል ፡፡ክሱ ምን ያህል በሐሰት የተሞላ መሆኑን ለማረጋገጥ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹የሃይማኖት ፖሊሲ ፣ሕግና ተቋም የሌላት ሃይማኖተኛ ሀገር ፣‹‹ውልድብና ›› እና ኢውልድብና››፣ዝቋላ ሀገሩ የትነው? ፣100% ፣እኔ በሞትኩ በማግስቱ ፣ለምጣዱ ሲባል ፣‹‹ስኳሬ›› ‹‹ዘይቴ›› ፣ከ2000 ዓመት በኃላ እንደ አዲስ እንመዘገባለን ፣እንደ አዲስም እንታወቃለን ፣መጀመሪያ ሰው ነኝ ››በሚል ርእሶች ያዘጋጃቸውን እነዚህን ጹሑፎች ብቻ ማንበብ በቂ ነው ፡፡በርግጥ ጹሑፎቹ ወያኔን በሐሳብ ልዕልና ይሞግታሉ እንጂ እንደኹራፊው ‹‹ወያኔ የጤፍ ዱቄት ሌባ ነው›› ዐይነት ተራ አሉባልታዎች አይደሉም፡፡ የኹራፊው የ‹‹እንዲህ ››አላለም ‹ፖለቲካ› ጨዋታ የጨዋዎቹ በመሆኑ እዚህ ጋ አልሠራም ፡፡
ማጠቃለያ
ኹራፊው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ‹‹ዳንኤል ክብረትና ሌላው የወያኔያዊ ተግባሩ መገለጫ! ››በሚል ርእስ በለጠፈብን ማወረቅ ጹሑፉ ‹‹በሀገሬ ፣በቤተ ክርስቲያንና በዚህ ውድ ሕዝብ ሸፍጦች ሲፈጸሙ አልችልም ፡፡ … ዘለፋው ይገርማችሃል እንዴ ! እውነቴን ነው የምላቹህ ፈንጅ በእጄ ቢኖር አንድ ሰው የማስተርፍ አይምሰለኝም ፡፡›› ብሎንም ነበር ፡፡
የሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ ነውረኛና በሐስት መርዝ የተለወሰውን ዘለፋውን በተግባር ያዋለው ለሀገሩ ፣ለቤተ ክርስቲያኑና ለውድ ሕዝቡ በሚደክመው በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ነው ፡፡ በሕሊናውም በፈንጅ ያጋየው ይኼንኑ የሀገር ፣የቤተ ክርስቲያንና የሕዝብ ባለውለታ የሆነውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው ፡፡ ነስፍ ገዳይነት የሚጀምረው በሕሊና ገዳይነት ነውና የዲያቆን ዳንኤል ክብረት አጥፊው ነፍስ በላው አምሳሉ ገብረ ኪዳን ነው ማለት ነው ፡፡ ይህ ደግሞ ከሞራል ተጠያቂነት ባሻገር የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላል ፡፡
ይሁንና ያልሆነው ግን ያለውን ነው ፡፡ ‹‹ በሀገሬ ፣በቤተ ክርስቲያንና በውድ ሕዝቧ ሸፍጥ ሲፈጸም አልችልም፤ በፈንጅ ነው የምፈጀው ›› እያለና እየቀባጠረ በፀረ ወያኔ ቆብ ከወያኔ ባልተናነሰ በወያኔያዊ መንገድ በሀራችን ሕዝብ አብሮነት ላይ ሸፍጥ እየፈጸመ የሚገኘው ተስፋዬ ገብረ አብን አይደለም በፈንጅ በብዕር ምንም አላለውም ፡፡ ተስፋዬ ‹‹ የቡርቃ ዝምታ ›› በተሰኘው መጽሐፉ ኦሮሞውንና ትግሬውን በአማራው ላይ ቀስቅሶበታል ፤ ‹‹በጋዜጠኛው ፣ በደራሲውና በስደተኛው ማስታወሻ ››በተሰኙ እኩይ መጻሕፍቱ አማራው ፣ ኦሮሞውና ሌላው ጎሳ በትግሬው ላይ እንዲነሳሳ ዘምቷል፤ ‹‹ የጀሚላ እናት ›› በተሰኘው ሰይጣናዊ መጽሐፉ ደግሞ ኦሮሞው በኢትዮጵያዊነት መቃብር ላይ ኦርቶዶክሳዊነትን እንዲቀብር አጥብቆ ሰብኳል ፡፡ዳሩ ግን የኹራፊው አምሳሉ ዶልዶም ብዕር የተሰበቀው ለእንዲህ ዐይነቱ ፀረ ኢትዮጵያዊነትና ኦርቶዶክሳዊነት ሳይሆን በኢትዮጵያዊውና በኦርቶዶክሳዊው በዲያቆን ዳንኤል ነው ፤ኹራፊው በፀረ ወያኔያዊ ለምድ የተገለጠ የወያኔ ተኩላ የሚያሰኘውም አንዱ ይህ ነው ፡፡
 በ‹‹ቤተ ክርስቲያኔ ሸፍጥ ሲፈጸም አልችልም፤በፈንጅነው የምፈጀው ›› ባዬ ኹራፊው አምሳሉ በፀረ ወያኔነት ካባ የታጀለውና የሻቢያ የጥፋት እጅ የሆነው ተስፋዬ ገብር አብ ‹‹የስደተኛው ማስታወሻ ››በተሰኘው የጥፋት መጽሐፉ የቤተ ክርስቲያናችን የመካከለኛው ዘመን የሐዋርያዊ አገልግሎት ማዕዘን በሆኑትን በጻዲቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ ‹‹የፍስሐ ጽዮን ፖለቲካ ››በሚል ርእስ በጻፈው ነውረኛ ጹሑፉ ሲሳለቅ  ምንም ሳይለው፣ በጸሎት ብዛት የተቆረጠውን እግራቸውን ‹‹ሰይጣን ፈንግሏቸው የተቆረጠ ነው››ብሎ ሲጽፍ ሳያንገበግበው ፣ዲያቆን ዳንኤል  ክብረት ‹‹የሌለውን ፍለጋ ›› በተሰኘው ጹሑፉ ‹‹ተስፋዬ‹የፍስሐ ጽዮን ፖለቲካ› በሚል ርእስ ሰለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የማያውቀውን ነገር ጽል፡፡ሰለማያውቀው ነገር የጻፈው ባለማወቁ ብቻ አይመስለኝም ፡፡አንድም ለማወቅ ባለመፈለጉ፣አሊያም ሆን ብሎ የማፍረስ ዓላማ ይዞ ይመስለኛል ፡፡›› ብሎ መልስ መስጠቱ አጥወለወለው፤ዳግም ለተስፋዬ ድፍረት ‹‹… ሰባት ዓመት ሙሉ ለጸሎት የቆሙበት እግራቸው በጸሎት ብዛት በመቆረጡ እንጂ ሰይጣን ‹‹ ፈንግሏቸው›› አለመሆኑን ኤርትራውያን እናቶች በሚገባ ያውቁታል፡፡..››ብሎ የሰጠው መልስም አንገበገበው፡፡እንግዲህ ይህ ሰው ነው ራሱን የኢትዩጵያዊነትና ኦርቶዶክሳዊነት ጠበቃ አድርጉ የሚቆጥረው ፡፡ እረ እፈር ሊባል የሚገባ ሰው ነው ፡፡
በመጨረሻ አንድ ነገር ብቻ ልበል ፡፡ ዶክተር ደረጄ በመቅድም ጹሑፋቸው እንደተመለከቱት የተቃውሞ ፖለቲካን ክርክርን በጤፍ ዱቄት ሌብነት ደረጃ አውርዶ ከሚያስበውና ይህንኑ የማያደርጉትን በወያኔነት ከሚፈርጀው ኹራፊ ጋር  ‹‹መረጃ ላይ መመሥረት ያለበትን ታሪክ ነክ ወይም ፖለቲካ ነክ ክርክር  ማካኼድ አይቻልም›› ፡፡ ይህም ጹሑፍ ሲዘጋጅ ይህን በመገንዘብና ኹራፊው ያዋረደውን አንባቢ በማክበር የተቃውሞ ፖለቲካን ክርክርን  ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ነው እንጂ ኹራፊውን በማሰብ አይደለም ፡፡ ሆኖም ግን የኹራፊው አምሳሉ ማወረቅ ጹሐፎች በርግጠኝነት አንድ ቁም ነገር ያስተምራሉ ፡፡ ይኸውም አንድ ጹሑፍ እንዴት እንደማይጻፍ!!




                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...