2015 ኤፕሪል 20, ሰኞ

የምናዝነው ስንት ሰው ሲሞት ነው?

በየመን፣ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ስለሚሞቱት ዜጎቻችን የሚሰጡት መንግሥታዊ መግለጫዎች ሁለት ነገር የጎደላቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሰብአዊ ስሜት፡፡ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ስለሌላው ሰብአዊ ፍጡር መከራና ስቃይ ሲሰማ መጀመሪያ አንዳች የኀዘን ስሜት ይሰማዋል፡፡ ከዕውቀት ይልቅ ስሜት ለሰዎች ቅርብ ነውና፡፡ ባለሥልጣን ቢሆን፣ ፖሊስ ቢሆን፣ ዳኛ ቢሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሆን ሰው ነውና ስሜት አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ያዝናል፣ ይከፋዋል፣ ልቡ ይረበሻል፣ ሆዱ ይባባል፣ ኅሊናው ይደማበታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያው ሥራው ማዘን ቀጥሎም ኀዘኑን በወጉ መግለጥ ነው፡፡ 

ሰሞኑን የማያቸው መግለጫዎቻችን ግን የኀዘን ወግ በሀገራችን የሌለ የሚያስመስሉ ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ወደ አደባባይ ወጥተው ለሞቱት ወገኖቻችን እንደ ኢትዮጵያዊነት ኀዘናቸው የሚገልጡት፣ ጥቁር ልብስ ለብሰው የምናያቸው፣ ነጠላ የሚያዘቀዝቁት ስንት ሰው ሲሞትብን ነው? የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ኀዘንኮ ፖለቲካ አይደለም፣ ፓርቲ አይደለም፣ ርእዮተ ዓለም አይደለም፣ ሊብራልም አብዮታዊ ዲሞክራሲም አይደለም፡፡ ኀዘን ሰብአዊነት ነው፡፡ የሚመራቸው ዜጎቹ፣ የሚያሠማራቸው በጎቹ ሲታረዱና ሲሞቱ ኀዘኑን በይፋ የማይገልጥ መሪና እረኛ መቼ ነው ኀዘኑን የሚገልጠው?
ዜጎቹ በሕገ ወጥ መንገድም ይሂዱ በሕጋዊ፣ ድንበር ጥሰውም ይሂዱ በአውሮፕላን ተሳፍረው፤ መጀመሪያ ሰዎች፣ ቀጥሎም የዚህች ሀገር ዜጎች ናቸውና ኀዘን ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው አገኘዋለሁ ብሎ ከሚያስበው ክብር አንዱ በሞቱ ጊዜ የክብር ልቅሶና ኀዘን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአካባቢያቸው ላለመራቅ፣ ከራቁም ለመመለስ ከሚሰጧቸው ምክንያቶች አንዱ ‹በክብር ዐርፎ በክብር መቀበርን፣ የክብር የኀዘን ሥነ ሥርዓትን ማግኘትን› ነው፡፡
ካገሬ እንዳወጣህ አገሬ መልሰኝ
በሹም የታዘዘ አፈር አታልብሰኝ፤
እንኳን የሚቀብረው የሚያዝንለት አጣ
ምን ወግ ማረግ ያያል ካገሩ የወጣ፤
የሚሉት ለዚህ ነበረ፡፡
የመንግሥት አካላት ለምን ይኼንን ለመዘንጋት እንደፈለጉ አልገባኝም፡፡ የደቡብ አፍሪካው ቃጠሎና ግድያ ሲመጣ የሀገራችን ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ብቅ ብለው ‹‹በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ነገር ከልብ እናዝናለን፣ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር ተነጋግረን አስፈላጊውን እናደርጋለን፤ ተመሳሳይ ችግር ለወደፊቱ እንዳይከሰትም አንሠራለን› ዓይነት ሰውነት ያለበት መግለጫ ጠብቄ ነበር፡፡ የለም፡፡ ሲሆን በሀገራችን የልቅሶ ሥነ ሥርዓት መሠረት፡፡ አሁን ደግሞ ዓለም ያወቀው አሸባሪ ‹አይ ሲስ› ኢትዮጵያውያኑን በክርስትና እምነታቸው ብቻ ሲሠዋቸው የተሰጠው መግለጫ ስሜት የሌለበት፣ ማዘን መደሰታቸውን የማይገልጥ፣ እንኳን ሰው እንስሳ የሞተብን የማያስመስል ሆነ፡፡ ከማጣራቱም ከምኑም በፊትኮ ስሜቱ ይቀድማል፡፡፡ አዝናችኋል ወይ? ስትሰሙና ስታዩ ምን ተሰማችሁ? የአሜሪካ መንግሥት እንደዚያ ዓይነት መግለጫ ሲያወጣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ያንን ነው ወይ መስማት ያለብን? ለመሆኑ መሪዎቻችን ኀዘናቸውን የሚገልጡት ምን ስንሆን ነው? ለምንድን ነው ሁሉም ነገር ፖለቲካ የሚሆነው?
ሁለተኛው የሚጎድለው ነገር ደግሞ ፍጥነት ነው፡፡ አትሌቶቻችን በኦሎምፒክ ሲያሸንፉ የባለሥልጣናቱ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ሯጮቹ ቆርጠውት ካለፉት ሪቫን ቀጥሎ የሚመጣ ዜና ነበር፡፡ አትሌቶቹ ደክሟቸው ከመሬት ሳይነሡ የባለሥልጣናቱ መልእክት ለሚዲያ ይደርስ ነበር፡፡ በዚህ የሁላችንም ኀዘን በሆነው ጉዳይ ግን ለምን መዘግየት እንደተመረጠ ግልጽ አይደለም፡፡ ማጣረቱ፣ መረጃ መሰብሰቡ፣ ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ሂደቶችን መሄዱ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ማዘን ግን ጊዜ አይወስድም፡፡ ቪዲዮው ተለቅቋል፡፡ ሲሞቱ እያየን ነው፡፡ መልካቸው የኛው ነው፡፡ አይሲስ የገደላቸው ‹ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች› ብሎ ነው፡፡ የዓለም ሚዲያዎች ያንኑ እያስተጋቡ ነው፡፡ ይኄ ለኀዘን ያንሳል? አፈፍ ብሎ ተነሥቶ ‹በሆነው ነገር እናዝናለን፤ ልባችን ተነክቷል፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፤ ዝርዝሩን በየጊዜው እንነግራችኋለን› ለማለት ስንት ሰዓት ይወስዳል? የደቡብ አፍሪካው ችግር ደረሰ እንደተባለ ሙጋቤን ለውግዘት የቀደማቸው የለም፡፡ የኛዎቹስ የት ሄዱ?
መንፈሳዊ መሪዎችስ የት ናቸው? አንዳንዶቹ ውጭ ሀገር መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡ ሲሆን ይህንን ሲሰሙ አቋርጦ መምጣት፤ ካልሆነም ባሉበት ሆኖ አባታዊ ኀዘንን መግለጥና በእምነቱ የሚገባውን ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ሲኖዶሱስ ምን እየሠራ ነው? አልሰማም ይሆን? ዛሬ ጠዋት ቢያንስ በአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎት መደረግ አልነበረበትም? ባፈው ካይሮ ሄዳችሁ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው ያያችሁት? በጎቹ እረኛ የላቸውም ማለት ነው? አባቶች የሚያዝኑት ምን ሲገጥማቸው ነው? እረኛው የሚያለቅሰው ስንት በጎች ሲታረዱ ነው?
ቤተ ክርስቲያኒቱ ነገሩን በዝምታ የምታልፈው ከሆነ እኛ እንደ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ቀኖና እነዚህን በክርስትናቸው  ምክንያት የተሠው ክርስቲያኖች ‹ሰማዕታተ ሊቢያ› ልንላቸው ይገባል፡፡ የሰማዕትነታቸውንም በዓል ማክበር አለብን፡፡ በስንክሳሩ ማስገባት ባንችል ታሪካቸው በኅዳጉ ማስፈር አለብን፡፡ ማንም ይሁኑ ማን፣ በሚገባ የተማሩም ይሁኑ ያልተማሩ፣ ከመካከላቸው የማያምኑም እንኳን ቢኖሩ የተገደሉበት ምክንያት ክርስትና ነውና ሰማዕታት ናቸው፡፡ ያውም ‹ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት›፡፡ በስንክሳሩ እንደምናነበው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን የክርስቲያኖች መንደርና ቤተ ክርስቲያን እየተወረረ ክርስቲያኖቹ ሲሠው ገና ያልተጠመቁት፣ ነገሩ ያልገባቸው፣ ክርስትናን ለመቀበል ያልወሰኑት ሁሉ አብረው ተሠውተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን የተሠውበት ምክንያት ክርስትና በመሆኑ ሁሉንም ሰማዕታት ብላቸዋለች፡፡ የእነዚህም ክብር እንዲሁ ነው፡፡
እነርሱ በሰማይ ዋጋ አላቸው፡፡ አክሊለ ሰማዕታትንም ተቀብለዋል፡፡ እኛ ግን ሰማዕታቱን ባለማክበራችን ክብር ይጎድልብናል፡፡ ‹በረከታቸው ይደርብን› እንጂ ‹ነፍስ ይማር› አንልም፡፡   

 


 
 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቢያ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ


አትም ኢሜይል
ሚያዝያ 12 ቀን 2007 ዓ.ም.

የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች አቅርበናል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ ሀገር በንጹሐን ወገኖች ላይ ስለተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም ከእኩለ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ የዜና ማሰራጫዎች በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ አካባቢ አይኤስ በተባለ አሸባሪ ቡድን በንጹሐን ወገኖች አሰቃቂ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ዘግበዋል፡፡

ዘገባው ከምንኑም ከምኑ የሌሉበት ንጹሐን ክርስቲያን ወጣቶች በታጠቁና ፍጹም ሰብኣዊነት በሌላቸው አሸባሪዎች ሲገደሉ የሚያሳየው ምስልም በመላው ዓለም እየታየ ይገኛል፡፡

አሰቃቂው ግድያ ስለተፈጸመባቸው ንጹሐን ወጣቶች ዜግነትና ማንነት ግልጽና አስተማማኝ የሆነ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በበርካታ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ሲነገር እንደሚሰማው የዚህ የግፍ ወንጀል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን የዜና ማሰራጫዎቹ አክለው እየገለጹ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈጣሪ የተሰጠች የማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ኃላፊነት በማይሰማቸውና በእነሱ ላይ በማይፈቅዱ ምንም ዓይነት ሰብአዊ ርኅራኄ በሌላቸው እንድትቀጠፍ ስለማትፈቅድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን አሰቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፣ አጥብቃም ታወግዛለች፡፡

ስለዚህ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ተገንዝበው ሁኔታውን በትዕግሥት እንዲጠብቁ፤

እንደዚሁም የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር መሆኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያን የሆኑ ሁሉ እንደቀድሞው በአንድነት በማውገዝ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ኪሣራ እንጂ ምንም ዓይነት ትርፍ የማያገኙ መሆናቸውን በተግባር እንዲያሳዩዋቸው እናሳስባለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ

በሊቢያ የሚኖሩ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ


አትም ኢሜይል

ሚያዝያ 12ቀን 2007ዓ.ም
martyrበሊቢያ የሚኖሩ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም አይ ኤስ አይ ኤስ በተባለው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ክርስቲያን በመሆናቸውና ሃይማኖታችንን አንቀይርም በማለታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ፡፡
አሸባሪ ቡድኑ ካሰሠራጨው ቪዲዮ ለመረዳት እንደተቻለው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖቹ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት በመታረድና ጭንቅለታቸው በጥይት ተፈርክሶ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አሸባሪ ቡድኑ ያሠራጨውን ቪዲዮ መነሻ በማድረግ ባሠራጩት ዘገባ የተገደሉት ክርስቲያኖች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዘመን በአሸባሪ ቡድኑ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት የሚወገዝ ሲሆን፤ ድርጊቱን ለፈጸሙት አካላት እግዚአብሔር ልቡና እንዲሰጣቸው እንጸልያለን፡፡ ክርስቲያን ወንድሞቻችንም ስለ ሃይማኖታቸው ሲሉ ያሳዩት ምስክርነት፣ ስላሳዩት ጥብዓት /ስለ ሃይማኖት መከራን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን/ የወንጌልን ቃል መፈጸም በመሆኑ በእግዚአብሔር መንግሥት የከበሩና በቅዱሳኑ ዘንድ የተመሰገኑ ናቸው፡፡

ይህ በመሆኑም ድርጊቱ በዚህ ዓለም ላለነው ሰዎች እጅግ አሰቃቂ ቢሆንም በክርስቲያን ወንድሞቻችን ክርስቲያናዊ ተግባር እንኮራባቸዋለን፡፡ ጌታችን በደሙ የመሠረታትን፣ ቅዱሳን በደማቸው ያጸኑዋትን ቤተ ክርስቲያን እነሱም በደማቸው መሥክረዋልና፡፡

በመጨረሻም በክርስቲያን ወንድሞቻችን አሰቃቂ ሞት ምክንያት ለገጠማችሁ መሪር ሐዘን ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም በድርጊቱ ላዘናችሁ በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን፡፡

ይህን ጉዳይ እየተከታተልን የምንዘግብ መሆኑንም እንገልጻለን፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...