byማኅበረ ቅዱሳን |
በእንዳለ ደምስስ
አትሌት
ካልኢተ አብርሃም ትባላለች፡፡ ገና የ18 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ታይላንድ ውስጥ ለሚገኝ
ሃቲያ ዩኒቨርስቲን ወክላ ትሮጣለች፤ ዩኒቨርስቲውም በዲግሪ መርሐ ግብር የሰውነት ማጎልመሻ /Physical
Education/ ትምህርት እድል ሰጥቷት በመማር ላይ ትገኛለች፡፡ ከ43 በላይ ታይላንድ ውስጥ በሚደረጉ እንዲሁም
ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከ5 ሺሕ እስከ ግማሽ ማራቶን /21 ኪሎ ሜትር/ ድረስ በመሮጥ 40 ዋንጫዎችንና በርካታ
የወርቅ ሜዳልያዎችን ለማግኘት ችላለች፡፡
ታይላንድ ውስጥ በምታደርጋቸው ውድድሮች አሸንፋ ስትገባ ለንጉሱና በቡድሂዝም እምነት ለተቀረጹት ምስሎች እንድትሰግድ ማስጠንቀቂያና መመሪያ ተሰጥቷታል፡፡ ነገር ግን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን ያገኘሁባትን ኦርቶዶክሳዊት እምነቴን አልክድም፤ እናንተም ላቆማችሁት ምስል አልሰግድም!!! በማለት ጸንታ በመቆሟ ትእዛዙንም ተላልፋ በማማተቧ በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች፡፡ እግዚአብሔር ረድቶኝ በባእድ ሀገር ስለ እምነቴ ለመመስከር አብቅቶኛል ትላለች አትሌት ካልኢተ አብርሃም፡፡
ስለስደት፤ እንዲሁም ስለ ሩጫ ሕይወቷ እና አስተዳደጓ አነጋግረናታል እንደሚከተለው እናቀርበዋለን፡፡
ስለ አስተዳደግሽ ብታጫውቺን?
የተወለድኩት ከመቀሌ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው
አዱግደም በሚባል ቀበሌ ነው፡፡ ያደግሁት ግን መቀሌ ከተማ ከአክስቴ ጋር ነው፡፡ እናቴ ከልጅነቴ ጀምሮ በቤተ
ክርስቲያን እንዳድግ አድርጋኛለች፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ እየተከተልኩ፤ እንዲሁም በየዓመቱ በሚከናወኑ የንግሥ
በዓላት በመገኘት፤ ቤታችን ለካህናትና ምእመናን ጸበል ጸዲቅ ሲዘጋጅ እያየሁ ነው ያደግሁት፡፡
ወደ ሩጫው እንዴት ገባሽ?
ከአክስቴ ጋር እየኖርኩ በክረምት ወደ እናቴ ስሄድ ግቢያችን
ውስጥ ተከራይተው የሚኖሩ ሯጮች ስለነበሩ ስለ ሩጫ ከእነሱ እየሰማሁ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ እየተነሱ ለልምምድ
ሲሄዱ አብሬ እየሄድኩ ልብሳቸውን እየጠበቅሁ፤ ቀስ በቀስም ወደ ሩጫው እየተሳብኩ በግሌ ልምምድ ጀመርኩ፡፡ ነገር
ግን በቤተሰብ በኩል ተቀባይነት ስላላገኘሁ ከአክስቴ ቤት ወጥቼ አንዲት ትንሽ ቤት ተከራይቼ ትምህርቴን እየተማርኩ
የሩጫ ልምምዴንም እየሰራሁ ቀሪውን ጊዜዬን አቅሜ የፈቀደውን የቀን ሥራ፤ አትክልተኛም በሆን እየሠራሁ፤ በቀሪ ትርፍ
ጊዜዬም መቀሌ ከተማ በሚገኘው መካነ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ገብቼ መማር
ጀመርኩ፡፡
በሰንበት ትምህርት ቤቱ የነበረሽ ቆይታ ምን ይመስል ነበር?
ከ8ኛ ክፍል እስከ 10ኛ ክፍል በራሴ ወጪ እየተማርኩ በሰንበት
ትምህርት ቤት በአገልግሎት እየተሳተፍኩ፤ የካህናት ልብሰ ተክህኖ የሰንበት ትምህርት ቤታች አልባሳት እያጠብኩ፤
በሩጫውም ቢሆን በተለያዩ መቀሌ ከተማ ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች መሳተፍ ጀመርኩ፡፡ ሰው ቤት ተቀጥሬም የሰራሁበት
ጊዜ አለ፡፡ ይህን ያደረግሁት ሩጫው የሕይወቴ አንድ አካል አድርጌ ስለቆጠርኩት ነው፡፡ በልጅነት ልቦናዬም ቢሆን
የሚደርሱብኝን ፈተናዎች መጋፈጥ ጀመርኩ፡፡ ለዚህም ሰንበት ትምህርት ቤቱ ለእኔ የተለየ ድጋፍ ያደርግልኝ ነበር
በምክርም ሆነ በሚቸግረኝ ነገር ሁሉ ከጎኔ ነበሩ፡፡ መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡ በአዲሐቂ ሁለተኛ
ደረጃ ትምህርት ቤት የ10 ክፍል ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ ትምህርቱን አቁሜ ሙሉ ጊዜዬን ለልምምድ፤ ለሥራ እና
ለአገልግሎት በማዋል ራሴን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት አደረግሁ፡፡
ቤተ ክርስቲያንን በመጠጋቴ በልጅነት እድሜዬ መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲኖረኝ፤ እግዘዚአብሔርን መፍራት፤ የቅዱሳን አባቶቻችን ተጋድሎና ታሪክ በተለይም የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገድል ቤተ ክርስቲያኑ ውሰጥ በየቀኑ ስለሚነበብ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ በፈተና እንድጸና አድርጎኛል፡፡ ወደ ንስሓ እና ምስጢራትን ወደመካፈል መራኝ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን አዲሸሁ እንዲሁም ማይጨው ማእከላት ጋር የነበረሽ ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር?
በሩጫ
በነበረኝ ተሳትፎ የመቀሌ ዞንን ወክዬ በ5ሺሕ ሜትር ተወዳድሬ አሸነፍኩ፡፡ ከዚያም ለትግራይ ሻምፒዮና ሽሬ ላይ
በተካሄደው ውድድር ተካፍዬ ለፕሮጀክት በመመረጤ አዲሰ አበባ መጣሁ፡፡ አዲስ አበባ ስመጣ እንደጠበቅሁት ውጤታማ
መሆን ባለመቻሌ አሰልጣኝ ፍለጋ ወደ ዐዲሸሁ ሄድኩኝ፡፡ ዐዲሸሁ እያለሁ ከተከራየሁት ቤት ፊት ለፊት የማኅበሩ
ጽ/ቤት ስለነበር ወንድሞችና እህቶችን ማግኘት ቻልኩ፡፡ አንድ ቀን ተከትያቸው ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ አብሬ
ሄድኩኝ፡፡ በኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያገለግሉ ስመለከት ቀረብኳቸው ፤ቀስ በቀስ እኔም ከእነሱ ጋር
በአገልግሎት መሳተፍ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን ከተወሰኑ ወራት በኋላ ወደ ማይጨው አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከል ለመግባት
ስላሰብኩ ወደዚያው ሳመራ ለማእከሉ አሳወቅሁ፡፡ ለማይጨው ማእከል የእኔ መምጣት ተነግሯቸው ስለነበር ፈልገው
አግኝተውኝ አገልግሎትንና ልምምዴን ቀጠልኩ፡፡ በደብረ ስብሐት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት
ትምህርት ቤት ውስጥም መሳተፍ ጀመርኩ፡፡
በማይጨው ቆይታዬ ከማእከሉ ወንድሞችና እህቶች ብዙ ነገር ተማርኩኝ፡፡ ሰዎችን በክርስትና ሕይወታቸው ጸንተው እንዲኖሩ የመቅረጽ መንፈሳዊ ስጦታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የሚጋጥመኝን የገንዘብ ችግር በመቅረፍ፤ ትክክለኛውን መንገድ በማሳየት ባለውለታዎቼ ናቸው፡፡
በሩጫ ሕይወቴም መሻሻሎችን እንዳሳይና በክልሉ በተደረገ የ5ሺሕና 10ሺህ ሜትር ውድድር ጥሩ ውጤት ማምጣት ቻልኩኝ፡፡ በክለብ ለመታቀፍ ጥረቶችን ባደርግም አልተሳካልኝም፡፡ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመውኛል፡፡ እኔ ግን ክርስትናዬ ስለሚበልጥብኝ፤ ሁል ጊዜ በጎ ጎዳናን ተከትዬ መሄድ ስላለብኝና ከክርስትና መንገድ ሊያስወጡኝ የሚችሉ ክፉ ነገሮችን በመጋፈጤ ወደ ስልጠና ማእከሉ ሳልገባ ቀረሁ፡፡
ተስፋ ሳልቆርጥ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ 2005 ዓ.ም. በፕሮጀክት ታቅፌ ተወዳደርኩ አሸነፍኩ፡፡ የጃን ሜዳ አገር አቋራጭ ውድድርም ተሳትፌ ለማሸነፍ ቻልኩ፡፡ ነገር ግን ትኩረት የሚሰጠኝ በማጣት ተመልሼ ወደ ሀገሬ ሄድኩ፡፡ ሩጫውን እንዳልተወው እሱን ብዬ ብዙ ነገር አጥቼበታለሁ፡፡ በተለይም ቤተሰቦቼን፤ ትምህርቴንና የትውልድ ቦታዬን አሳጥቶኛል፡፡ እለህ ደግሞ ያዘኝ፡፡ አለኝ የምለው ቤተ ክርስቲያንና የማይጨው ማእከል ወንድሞችና እህቶች ናቸው፡፡ የልምምድ አልባሳት የሉኝም፤ ጫማ የለኝም፤ በጣም ተቸገርኩ፡፡
ወደ ታይላንድ ለመሄድ እንዴት ቻልሽ?
በሰንበት
ትምህርት ቤት አገልግሎት የሚያውቀኝ አንድ ወንድም ከአንዲት ታላንዳዊት የሯጮች ማኔጀር ጋር አገናኘኝ፡፡ በሀገሬ
ያልተሳካልኝ በሰው ሀገር እንዴት ይሳካልኛል በማለት ጥያቄውን ለመቀበል ተቸገርኩ፡፡ ነገር ግን ከዋነኛ ዓላማዬ
አንዱ የሆነውን በሩጫ አገሬን መወከል ስለነበር ልምድም ለመቅሰም እንደሚረዳኝ በማመን፤ እነሱም በዩኒቨርስቲ ደረጃ
እንሚያስተምሩኝና ዩኒቨርስቲውን ወክዬ እንድወዳደር ግፊት ስላደረገችብኝ ወደ ታይላንድ ለመሄድ ወሰንኩ፡፡
ዋነኛ ጭንቀቴ የነበረው ቤተ ክርስስቲያን የሌለበት፤ የእግዚአብሔር ስም የማይጠራበት፤ የንስሓ አባት የሌለበት ስለነበር ሰጋሁ፡፡ የምሥጢር ተካፋይ ስለሆንኩም በጣም አሳሰበኝ፡፡፡ ነገር ግን መሥዋዕትነት መክፈል ስለነበረብኝ ያገኘሁትን እድል ለመጠቀም ወሰንኩ፡፡ ከማኔጀሬ ጋር ሆኜ በአውሮፕላን ከአዲስ አበባ ግብጽ፤ ከግብጽ ባንኮክ፤ ከባንኮክ ሃቲያ ዩኒቨርስተ ለመድረስ ዐራት ቀናት ፈጅቶብናል፡፡ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገብተን ሌሊት 10 ሰዓት ውድድሩ ይካሔዳል፡፡ በጣም ደክሞኛል፤ ምግብ አልበላሁም፤ ከግብጽ ስንነሳ አንድ ኢትዮጵያዊ አግኝቼ ጭማቂ ሰጥቶኝ ስለነበር እሱን በውኃ እየበረዝኩ ጠጥቼ ነው የደረስኩት፡፡
የውድድሩ ሰዓት እየተቃረበ ሲመጣ ማናጀሬ በታይላንድ ሕግ መሠረት ብታሸንፊ በስታድየሙ ውስጥ ለቆሙት ለሀገሪቱ ንጉሥ እና ለቡድሃ እምነት የተቀረጹ ምስሎች መስገድ እንደሚገባኝ ይህ ደግሞ ግዴታ እንደሆነ አስጠነቀቀችኝ፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቴ ሲሸኙኝ ያሰሩልኝ መስቀል፤ ገድለ ጊዮርጊስንና ውዳሴ ማርያምን ይዤ እያለቀስኩ ጸሎት አደረስኩ፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ፍርፋሪ በልቼ፤ የምስጢር ተካፋይ አድርጋንኝ ለምን በእምነቴ ላይ ይመጡብኛል ብዬ ውድድሩ እስኪጀመር ድረስ በጣም አምርሬ አለቀስኩ፡፡ ወደ ውድድሩም ገባሁ፡፡ አንዲት ኢትዮጵያዊትና ኬንያውያን በብዛት ነበሩ፡፡ ነገር ግን በአንደኝነት ውድድሩን ጨረስኩ፡፡
አሸንፌ ስገባም ለድል ያበቃኝን እግዚአብሔር እያመሰገንኩ የተሰጠኝን ማስጠንቀቂያ ለመጋፈጥ በመወሰን አማተብኩ፡፡ ስታድየሙ በሕዝብ የቁጣ ጩኸት ተናጋ፡፡ የለበስኩት የሃቲያ ዩኒቨርስቲ መለያ ነው፤ በሌላ አነጋገር የታይላንድ መለያ እንደለበስኩ አድርገው ስለቆጠሩት እንዴት ለአምላካችንና ለንጉሣችን አትሰግድም በሚል ቁጣቸው አገረሸ፡፡ ዋንጫውንም ስቀበል አማትቤ ተቀበልኩ ቁጣቸው ከመጀመሪያው ባሰ፡፡ ማናጀሬ ለብቻ ወስዳ ለምን እንዲህ እንዳደረግሁ ጠየቀችኝ፡፡
እንዳሸንፍ ለረዳኝ አምላኬ ምስጋና ነው ያቀረብኩት፡፡ ለማላውቀውና እናንተ ላቆማችሁት ምስል አልሰግድም!! ካልፈለጋችሁኝ ወደ ሀገሬ መልሱኝ ብዬ በአቋሜ ጸናሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆን ፈተና ሊገጥምህ ይችላል ነገር ግን መቋቋም ግዴታ ነው፤ ከክርስትና የተማርኩት ይህንን ነው፡፡ በባእድ ሀገር ብሆንም እምነቴን የሚያስክደኝ እንደሌለ ማሳየት ይጠበቅብኛል፡፡ ለዚህ ለዚህ ለምን ክርስቲያን ሆንኩ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለተጋደለላት፤ ቅዱሳን አባቶቼ በጽናት የቆሙላትን ስለ እውነተኛዋ እምነቴ እንዳልመሰክር ምን ሊያግደኝ ይችላል፡፡ በአቋሜ መጽናቴን በመረዳታቸውና እኔንም ማጣት ስላልፈለጉ በእምነቴ ላይ እንዳይመጡብኝ ተስማማን፡፡
ዩኒቨርስቲው የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርትንና ተጓዳኝ ትምህርቶችን እየተማርኩ መኖሪያና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ ቁሳ ቁሶችን አሟልተውልኝ እኖራለሁ፤ ልምምድ አደርጋለሁ፤ ውድድር ሲኖር እወዳደራለሁ፤ ማናጀሬ ከተለያዩ ሀገራት በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ እንድሳተፍ ታደርጋለች፡፡ እሰካሁን 43 እና ከዚያ በላይ ውድድሮችን አድርጌ 40ዎቹን በአንደኝነት ነው ያጠናቀቅሁት፡፡
ውድድሮቹ አልበዙብሽም?
የውድድሮቹ መብዛት በጣም አድካሚ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ነገር
ግን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተወዳድሬ ጥሩ ውጤት በማምጣት ስሜን ማስመዝገብ ስለምፈልግ፤ ወደፊትም ለሀገሬ
ኢትዮጵያ መወዳደር ስለምፈልግ የተሻለ ልምድና ሰዓት ማስመዝገብ ይጠበቅብኛል፡፡
ታይላንድ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ለማግኘት አልሞከርሽም?
በስምንት ወራ ቆይታዬ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው ያገኘሁት፡፡ በሀገሩ ውስጥ ኢትዮጵያዊም፤ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ የንስሓ አባት ማግኘት አይቻልም፡፡ በዚህ ብዙ ተጎድቻለሁ፡፡
ካገኘሻቸው ዋንጫዎችና ሜዳልያዎች ለማኅበረ ቅዱሳን ማይጨው ማእከል፤ መቀሌ ለሚገኘው መካነ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለማይጨው ደብረ ስብሃት ቅድስት ሥላሴ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሰጥተሻል፡፡ ምክንያትሽ ምንድነው?
ሃይማኖቴን እንዳውቅ፤ ፈተና ቢገጥመኝ በትእግስት እንዳልፍ፤
የቅዱሳን አባቶቼን ተጋድሎና ስለ እምነታቸው የከፈሉት መሥዋዕትነት እንድረዳ በሕይወት እነሱን እንድመስል ስለረዱኝ፤
እንዲሁም በሥጋዊ ሕይወቴ በችግሬ ሰዓት የደረሱልኝ ሰለሆነ ባለውለታዎቼ ናቸው፡፡ ለውጤቴ ማማር የእነሱ ድርሻ
ስላለበት ነው፡፡
በንግግርሽ ውስጥ ሁሌም ቅዱስ ጊዮርጊስን ትጠሪያለሽ ምሥጢሩ ምንድነው?
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሕይወቴ ውሰጥ ያደረገልንኝ ዘርዝሬ መጨረስ
አልችልም፡፡ የሚገጥሙኝ ፈተናዎችን ሁሉ ያለፍኩት በእሱ አማላጅነትና ፈጥኖ ደራሽነት ነው፡፡ ከሕፃንነቴ ጀምሮ
ገድሉን እየሰማሁ ነው ያደግሁት፡፡ ታይላንድ ከመጣሁ በኋላም ስሜን የልዳው ኮኮብ ብዬ ነው የሰየምኩት፡፡ ይህ
ድፍረት ነው ልባል እችል ይሆናል ካለኝ ፍቅር የተነሳ ያደረገረሁት እንጂ በትዕቢት አላደረግሁትም፡፡
ስደትን እንዴት ትገልጪዋለሽ?
ኢትዮጵያዊነትህን፤ ሃይማኖትህን፤ ቤተ ክርስቲያንን፤ ባሕልህን፤
ሕዝብህን ታጣለህ፡፡ በሄድክበት ዝና ልታገኝ ትችላለህ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ቤተ ክርስቲያን ትናፍቅሃለች፡፡
እግዚአብሔር ይፍታህ የሚል በሌለበት ደስታ ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን አላማህን እስክታሳካ ተፈትነህ ማለፍ
አለብህ፡፡ በጣም የሚገርምህ ለቤተ ክርስቲያን ያለህ ፍቅር በስደት ስትኖር ይጨምራል፡፡ የኔ የምለው ሰው ስለሌለ
በትርፍ ጊዜ እመቤታችንንን፤ ቅዱስ ጊዮርጊስን እየተማጸንኩ ከእነሱ ጋር እነጋገራለሁ፡፡ በባእድ ሀገር ቋንቋዬ እነሱ
ናቸው፡፡ በየቀኑ ማታ ማታ ጸሎት አድርጌ ከመተኛቴ በፊት መኖሪያዬ ካለበት የሕንፃ ማማ ላይ ወጥቼ ፊቴን ወደ
ምሥራቅ አዙሬ ኢትዮጵያዊው አቡነ ተክለ ሃማኖት ሆይ ይፍቱኝ እያልኩ ወደ ክፍሌ እመለሳለሁ፡፡
እስቲ ከገጠመኞችሽ አንዱን አካፍዪን?
ማናጀሬ ልጇ ከትምህርት ቤት ለሦስት ቀናት ወደ ቤት ሳይመለስ ሲቀርባት ማታ ጸሎት እያደረግሁ መጥታ እባክሽ ልጄ ወደ ቤት ከመጣ ሦስተኛ ቀኑ ነው፡፡ ለምትወጂው አምላክሽና ለልዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለምኚልኝ ብላ ሻማ ሳበራ ስለምታይ ሻማ ይዛ መጥታ እራሷ ያበራችበት ጊዜ አልረሳውም፡፡
የወደፊት እቅደሽ ምንድነው?
ኢትዮጵያሀገሬን በዓለም አቀፍ ውድድሮች መወከልና ጥሩ ውጤት ማምጣት እፈልጋለሁ፤ ለዚህም ነው ጠንክሬ በመሥራት ላይ የምገኘው፡፡
የምታስተላልፊው መልእክት?
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖር፤ ማገልገል ለሥጋም ሆነ ለነፍስም
የሚጠቅም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መልካም የሆነውን ሁሉ ዐቅፋ የያዘች ናት፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድጠጋ ከማር
ከወተት የሚጣፍጠውን ቃለ እግዚአብሔር ትመግበናለች፤ ፈተናም ቢመጣ በእቅፍዋ ታስጠልለናለች፡፡ ወደ እግዚአብሔር
እንቅረብ የሚያሳጣንም አንዳች ነገር የለም ነው የምለው፡፡
በመጨረሻም ከጎኔ በመሆን ለረዱኝ ወላጅ እናቴና ቤተሰቦቼ፤ ለሰንበት ትምህርት ቤቴ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማኅበረ ቅዱሳን ማይጨውና ዐዲሸሁ ወረዳ ማእከላት፤ እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎች ለረዱኝ ሁሉ ምስጋና ይድረሳቸው፡፡+++