2016 ማርች 7, ሰኞ

የዐቢይ ጾምን መግባት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ትምህርት


በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 28 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፤- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ይህ ትምህርት የተወሰደው የተወደደ መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በ388 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም መግቢያ ላይ ጀምሮት በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ እየተረጎመ ከጨረሰው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህን ትምህርት ይከታተሉ የነበሩትን ምእመናን ከሊቁ አጠቃላይ ንግግር አንጻር ስናያቸውም የቤት እመቤቶችና በተለያየ የሙያ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች ሲኾኑ የሚማሩትም በዐቢይ ጾም ምንም እኽል ሳይቀምሱ ነው፡፡   
(1) የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ በልጆቿ ስትደምቅእናንተም ጉባኤውን ለመታደም ደስ ብሏችሁ ተሰባስባችሁ ስትመጡ ዐይቼሐሴት አደረግሁኝ፤ ደስም አለኝ፡፡ ፊታችሁ እንዴት በደስታ እንደ ተመላስመለከት ጠቢቡ “ልብ ደስ ሲለው ፊት ይበራል” እንዳለው ልባችሁ ምን ያህልእንደ ተደሰተ ተገነዘብሁኝ /ምሳ.1513/፡፡ በመኾኑም፥ ዛሬ ማለዳ የተነሣሁት ከወትሮው በተለየ ትጋት ነው፡፡ ይኸውም ይህን መንፈሳዊ ደስታ ከእናንተ ጋርእንድካፈልና ቀጣዩ ወራት ቁስለ ነፍሳችሁ ድኅነት የሚያገኝበት ወርሐ ጾመኾኑን አበሥራችሁ ዘንድ ነው፡፡ የኹላችንም ጌታ ልዑል እግዚአብሔር፥ ልክእንደ ደግ አባት ባለፉት ወራት ለሠራነው ኃጢአት ሥርየት እናገኝበት ዘንድ ሽቶመድኃኒት የሚኾን ቅዱስ ጾምን አዘጋጅቶልናልና፡፡

(2) ስለዚህ የነፍሳችን ጠባቂ (እግዚአብሔር) የሕመማችንን ፈውስየምናገኝበትን መድኃኒት ስላዘጋጀልን እያመሰገንን ወርሐ ጾሙን ደስ ብሎንልንቀበለው ይገባናል፡፡ ከእኛ መካከል ጾም በመግባቱ አንድስ እንኳን የሚከፋውወይም የሚበሳጭ ሊኖር አይገባም፡፡ ወርሐ ጾሙን እንዲህ ደስ ተሰኝተንመቀበላችንን ዐይተውም አሕዛብ ይፈሩ፤ አይሁድም ይራዱ፡፡ በእኛና በእነርሱመካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ዐይተውም ይማሩ፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንበዓል የምትሠራው ምእመናን ራሳቸውን መግዛት እንዲችሉ፣ በበጎ ምግባር ያጌጡያሸበረቁ እንዲኾኑ እንደ ኾነ፥ እነርሱ ግን በዓላትን የሚያደርጉት በዘፈንና በስካርይህንም በመሰለ በሌላ ጸያፍ ግብር ለመንከባለል እንደ ኾነ ለይተው ይወቁ፡፡በእርግጥም በዓል ተከበረ የሚባለው፡ሰዎች ነፍሳቸውን ካዳኑበት፣ ውስጣዊሰላምንና ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ ካደረጉበት፣ ዕለት ዕለት ከሚያጋጥማቸው የነፍስመታወክ ካረፉበት፣ ያለ ሁካታና ጋጋታ እንዲሁም እንስሳትን በማረድ ከልክበላይ ከኾነ መብልና መጠጥ ርቀው ያከበሩት እንደ ኾነ ነው፡፡ ከዚህምበተጨማሪ በዓል ተከበረ የሚባለው፡- አርምሞንና ጸጥታን፣ ፍቅርንና ደስታን፣ሰላምንና ራስን መግዛትን፣ እንዲሁም ሌሎች እዚህ መዘርዘር የማንችላቸው ብዙምግባር ትሩፋቶችን ገንዘብ ያደረግንበት እንደ ኾነ ነው፡፡
(3) እንኪያስ እጅግ የምወዳችሁ ምእመናን ሆይከኹሉም በፊትእነዚህን ነገሮች በስፋት እንነጋገርባቸው ዘንድ፣ ዳግመኛም አንዳች የሚረባንንነገር ይዘን ወደ ቤታችን እንመለስ ዘንድ ቃላችንን በታላቅ ትጋትና ጉጉት ኾናችሁትቀበሉት ዘንድ አሳስባችኋለሁ፡፡ ኹላችንም ወደዚህ ጉባኤ ስንመጣ እንዲሁናያለ ዓላማ አይደለም፡፡ ወሬ ለማውራት፣ ምን እንደ ተባለ እንኳን ሳንሰማለማጨብጨብ፣ ከዚያም ምንም የሚረባ ነገርን ሳንይዝ ወደ ቤታችን ለመመለስወደዚህ ጉባኤ አልመጣንም፡፡ እኔም የመጣሁት ለነፍሳችሁ ድኅነት የሚጠቅምአንዳች ነገርን ለመናገር ነው፤ እናንተም ስትመጡ በእኔ በባሪያው አድሮእግዚአብሔር የሚናገረውን ነገር አድምጣችሁ ለመጠቀምና አንዳች የሚረባነገርን ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ለመመለስ ነው፡፡ ተመልከቱ! ቤተ ክርስቲያን ማለትቤተ ድኅነት ናት፡፡ ወደ እርስዋ የሚመጡትም ለችግራቸው ተገቢውን መድኃኒትአግኝተው መሔድ አለባቸው፡፡ ተግባራዊ የኾነ ለውጥ ሳያመጡ ቃለ እግዚአብሔርን መማር ብቻ ምንም ጥቅም እንደሌለው ሲናገርም ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፡- “በእግዚአብሔር ፊት የሚጸድቁት ሕግንየሚያደርጉት እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደሉም” /ሮሜ.213/፡፡ በቃል መነገሩ፣በልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ከፍ ይበልና አምላካችንክርስቶስም ሲያስተምር፡- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ኹሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ብሏል /ማቴ.721/፡፡ ስለዚህ ተወዳጆች ሆይቃሉን በመስማታችን ብቻ አንዳች የምንጠቀመው ነገር ስለሌለ የሰማነውን የምናደርግ እንጂ የምንሰማ ብቻ አንኹን፡፡ እንዲህ ከኾነም እምነታችን ሕይወት ያለው እምነት ይኾናል፡፡
(4) በመኾኑም፥ ስለ ጾም የሚሰጠውን ስብከት ለማዳመጥ እዝነ ልቡናችሁን ክፈቱ፡፡ ከትሕት እና ዓይናፋር ሙሽሪት ጋር አነጻጽሬ እንድነግራችሁ ትወዳላችሁን? ሙሽሪቱን በሰርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች አስቀድመው ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይጠርጉታል፡፡ የቆሸሸ ልብስን የለበሰ ሰው ወደ ሰርጉ አዳራሽ እንዳይገባ ያደርጉታል፡፡ ወደ አዳራሹ መግባት የሚችለው የሰርግ ልብስ የለበሰ ሰው ብቻ ነው፡፡ እናንተም እንዲህ ልታደርጉ ይገባችኋል፡- ልቡናችሁን በማንጻት፣ አብዝቶ ከመብላትና ራስን ካለመግዛት በመራቅ - የምግባር እናት፣ የማስተዋልና የሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ደጀ ልቡናችሁን በመክፈት ልትቀበሏት ይገባችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደ ኾነ ታላቅ ሐሴት ታደርጋላችሁ፤ እርስዋም ቁስለ ነፍሳችሁን ትፈውስላችኋለች፡፡ ሌላ ምሳሌ መስዬ ብነግራችሁ፡- ሐኪሞች በሕሙማን ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻና መርዘኛ ፈሳሽን ማስወገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ ሕሙማኑ ምግበ ሥጋን ከመውሰድ እንዲቈጠቡ ያደርጉዋቸዋል፡፡ ሕሙማኑ ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከሉ ግን ሐኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት የተፈለገውን ያህል ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም የነፍስንና የሥጋን ቁስል የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚህ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለሁ፡፡ ድኅነትን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹህና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፤ እንዲህ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡
(5) የዛሬው ንግግሬ ለአንዳንዶቻችሁ አዲስና እንግዳ እንደሚኾንባችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በዓላማ (ድኅነትን ለማግኘት ብለን) እንጹም እንጂ እንዲሁ የልማድ ባርያዎች አንኹን ብዬ እማልዳችኋለሁ፡፡ በየቀኑ ከልክ በላይ በመብላትና በሆዳምነት የምታገኙት ጥቅም ምንድን ነው? ጥቅምስ ይቅርና ጭራሽ የከፋ ጉዳትን የሚያመጣባችሁ ነው፡፡ ተመልከቱ! ከልክ በላይ በመጠጣትና በመስከር የማስተዋል ልቡና ሲታወር የጾም ጥቅምዋም ምንም ምልክትን ሳያስቀር ያጠፏል፡፡ እስኪ ልጠይቃችሁ፡- እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ብዙ ወይንን ከሚጠጡ፣ በየመሸታ ቤቱ አድረው ፀሐይ ከምትወጣባቸው፣ ለሚያገኛቸው ሰው ኹሉ ደስ ከማያሰኙ፣ ለቤተ ሰቦቻቸው ግድ ከሌላቸው፣ ሕፃን ዐዋቂው ከሚሳለቅባቸው፣ ራሳቸውን ባለመግዛታቸውና ያለጊዜው በኾነ ደስታ ደስ በመሰኘታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን ካጡ ከእነዚህ ሰዎች በላይ ማን ጎስቋላ ሰው አለ? ቅዱስ መጽሐፍስ እንዲህ የሚል አይደለምን?፡- “ሰካሮች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” /1ኛ ቆሮ.6፥10/፡፡ ወዮ! እንደ ጠዋት ጤዛ ለሚጠፋ፥ ያውም እጅግ ከባድ ጉዳትን የሚያመጣ እርካታን ለማግኘት ብለው፥ የዘለዓለምን መንግሥትን የሚያጡት እነዚህ ሰዎች ከሚያገኛቸው መከራ በላይ ምን መከራ አለ?
(6) እዚህ ጉባኤ ከተሰበሰባችሁ ምእመናን መካከል አንድም ሰው እንኳን ቢኾን በዚህ ዓይነት ስንፍና መያ’ዝ የለበትም፤ እግዚአብሔር ይህን በፍጹም አይወደውም፡፡ ከዚህ ይልቅ እያንዳንዷን ቀን በትዕግሥትና ራስን በመግዛት እንዲሁም አብዝቶ መብላት ከሚያመጣው የመከራ አውሎ ነፋስ ተጠብቃችሁ ወደ ነፍሳችሁ ወደብ - ይኸውም ወደ እውነተኛ ጾም - ልትደርሱ ይገባችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነም ከእርስዋ የሚገኘውን ጥቅም በብዙ ታገኛላችሁ፡፡ በሌላ አነጋገር አብዝቶ መብላት የብዙ ውርደቶችና ኃጢአቶች ምንጭ እንደ ኾነ ኹሉ ጾምም የብዙ በረከቶችና ክብር ምክንያት ነው፡፡ እንደምታስታውሱት መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሲፈጥር ለነፍሳቸው ድኅነት የሚኾን አንድ መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር፡፡ በመኾኑም፥ ገና ከመነሻው አንሥቶ ለመጀመሪያው ሰው (ለአዳም) አንድ ትእዛዝ ሰጠው፤ እንዲህ በማለት፡- “በገነት ካለው ዛፍ ኹሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” /ዘፍ.2፥16-17/፡፡ ይህ ስለ መብላትና ስለ አለመብላት የተገለጠው ኃይለ ቃል በምሥጢር ስለ ጾም የሚናገር ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰው ይህቺን ትእዛዝ ይጠብቃት ዘንድ ቢታዘዝም እርሱ ግን አልጠበቃትም፡- ራሱን መግዛት አቃተው፤ ባለመታዘዝ ኃጢአት ውስጥ ወደቀ፤ በራሱ ላይም የሞት ፍርድን አመጣ፡፡ እንደምታስታውሱት ዲያብሎስ ክፉ መንፈስና የእኛ ጠላት ስለ ኾነ የመጀመሪያው ሰው አዳም በገነት ሲኖር እንዴት በነጻነት እንደሚኖርና ሥጋ ለብሶ ሳለ እንዴት የመላእክትን ኑሮ በምድር ላይ እንደሚኖር ተመለከተ፡፡ በመኾኑም፥ እንዴት እንደሚጥለው አሰበ፤ ታላቅ የኾነ ተስፋ በመስጠት ከልዕልናው አዋረደው፤ በዚህ ሽንገላዉም የነበረውን ሀብት ኹሉ ሰረቀው፡፡ በመጠን ያለመኖርና ከዓቅም በላይ የኾነን ነገር የመመኘት ክፋቱ ይኽን ያህል ነው፡፡ ጠቢቡ ሰውም ይህንን እንዲህ በማለት ግልፅ አድርጎታል፡- “በዲያብሎስ ቅንአት ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ” /ጥበ.2፥24/፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ገና ከጥንቱ የሞት መግቢያው ራስን አለመግዛት መኾኑን ታያላችሁን? በኋላ ዘመን ላይም መጽሐፍ ቅዱስ አብዝቶ መብላትን እንዴት ደጋግሞ እንደሚነቅፈው አስተውሉ፡፡ በአንድ ስፍራ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡- “ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” /ዘጸ.32፥6/፤ በሌላ ቦታም፡- “በላ፥ ጠጣም፤ ወፈረ፥ ደነደነም፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ” ይላል /ዘዳ.32፥15/፡፡ የሰዶም ኗሪዎችም እንደዚሁ ያን የማይበርድ ቍጣ በራሳቸው ላይ ያመጡት በዚህ ኃጢአት ምክንያት ነው፡፡ ሌላውን በደላቸውን እንኳን ሳንገልጠው የነቢዩን ቃላት አድምጡ፤ እንዲህ ያለውን፡- “የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፡- እንጀራን መጥገብ” /ሕዝ.16፥49/፡፡ በአጭር አነጋገር መብል ብዙውን ጊዜ እንደ ምንጭ ውኃ ነው፤ ወይም የክፋት ኹሉ ሥር ነው፡፡
(7) እንግዲህ አሁን ራስን አለመግዛት እንዴት አደገኛ እንደ ኾነ ተገነዘባችሁን? አሁን ደግሞ ጾም እንዴት ያለ በረከትን እንደሚያመጣ እንመልከት፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አርባ ቀን ስለ ጾመ የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ጽላት ሊቀበል ችሏል /ዘጸ.24፥18/፡፡ ከተራራው ሲወርድ ግን አብዝቶ የሚበላና ኃጢአተኛ የኾነ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕግ ቢቀበል ምንም ትርጉም የለውም በማለት በብዙ ምልጃ የተቀበለውን ጽላት ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበረው /ዘጸ.32፥19/፡፡ በመኾኑም፥ ይህ ታላቅ ነቢይ በሕዝቡ ኃጢአት ምክንያት በሰበረው ጽላት ፈንታ እንደ ቀድሞ ያለ ሌላ ጽላት ለመቀበል አርባ ቀንና አርባ ሌሊት መጾም ነበረበት /ዘጸ.34፥28/፡፡ በእሳት ሠረገላ ተነጥቆ ወደ ሰማያት የተወሰደው፣ እስከ ዛሬ ድረስም ሞትን ያልቀመሰው ታላቁ ነቢይ ኤልያስም ልክ እንደ ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል /1ኛ ነገ.19፥8/፡፡ ልክ እንደዚሁ መንፈሰ ብርቱው ዳንኤልም አያሌ ቀናትን ይጾም ነበር፤ እንደ ሽልማትም እጅግ የሚያስደንቅ ራእይን ተቀብሏል፡- ቍጡዎቹን አንበሶች እንደሚያስለምዳቸው፣ ጥንተ ተፈጥሯቸው ተለውጦ ሳይኾን ከእነ ተናጣቂ ባሕርያቸው እንደ የዋህ በጎች እንደሚኾኑለት ዐየ፡፡ የነነዌ ሰዎችም እንደዚሁ በጾም መድኃኒትነት ከእግዚአብሔር ዘንድም ምሕረትን አግኝቷል፡፡ እንዲያውም በነነዌ የጾሙት ሰዎች ብቻ አልነበሩም፤ እንስሳቱም ጭምር እንጂ፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ሊያደርገው ከተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም /ዮና.3፥10/፡፡ ከብሉያትና ከሐዲሳት እንዲህ በመጾማቸው ምክንያት የተጠቀሙ ብዙ ሰዎችን መጥቀስ እንችላለን - ነገር ግን የኹላችንም ጌታ ወደ አደረገው መምጣት ሲገባን አገልጋዮቹን የምናየው ለምንድን ነው? እንደምታውቁት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል /ማቴ.4፥2፣ ሉቃ.4፥2/፡፡ ሲጾምም ዲያብሎስን ድል አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ይኸውም የጾምን ትጥቅ ልንታጠቅ እንደሚገባንና ከዚህ በምናገኘው ኃይልም ብርቱ የሚኾን ጠላታችንን ድል ማድረግ እንደሚቻለን አርአያ ሲኾነን ነው፡፡
(8) እዚህ ላይ ምናልባት ነገሮችን ጠለቅ አድርጎ የሚመረምርና ሐሳበ ልቡናዉን ንቁ ያደረገ ሰው፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ አገልጋዮቹ አንዲት ቀንስ እንኳን ሳይጨምር የጾመው ስለ ምንድን ነው?” ብሎ ጥያቄ ሊያነሣ ይችላል፡፡ ጌታችን ይህንን ያደረገው ያለ ምክንያት ሳይኾን ከጥበቡና ሰውን ከመውደዱ የተነሣ ነው፡፡ ይኸውም፡- “ወደዚህ ምድር የመጣው ሥጋን ሳይለብስ ነው፤ ሰውም የኾነው በምትሐት ነው” ብለው ለሚነሡ ዐብዳን ሐሳባቸውን ይገታ ዘንድ አስቦ ልክ እንደ አገልጋዮቹ አንዲት ቀንስ እንኳን ሳይጨምር ጾመ፡፡ እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚህ በገቢር ጾሞ ሳለ እንኳን እንደዚህ ያለ ምክንያት የሚያመጡ ከኾነ ከቸርነቱ የተነሣ ሊያመጡት የሚችሉትን ሰበብ አስቀድሞ ባይጥለው’ማ እንደ ምን የከፋ ነቀፋን ባመጡ ነበር? በመኾኑም፥ የእኛን ባሕርይ ገንዘብ እንዳደረገና ከእኛ የራቀ እንዳልኾነ ሲያስተምረን ከቀደሙት አባቶች ሳያተርፍ አርባ ቀን ጾመ፡፡
(9) እጅግ የምወዳችሁ ምእመናን ሆይ! የጾም ጥቅምዋ ምን ያህል የበዛ እንደ ኾነና ነፍሳችን ከዚህ ብዙ ጥቅምን እንደምታገኝ ከጌታችን እና ከአገልጋዮቹ ተምረናል፡፡ ስለኾነም የጾም ወራት ሲቃረብ ግድየለሽነትንና ሞራለ ቢስነትን ከእኛ አስወግደን ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ፡- “የውጭው ሰውነታችን ይበልጥ ሲጠፋ የውስጡ ሰውነታችን ይበልጥ ይታደሳል” ብሎ እንዳስተማረን እጅግ ደስ ተሰኝተን ልንቀበለው ይገባናል ብዬ እማልዳችኋለሁ /2ኛ ቆሮ.4፥16/፡፡ ጾም የነፍስ ምግብ ነው፡፡ ምግበ ሥጋ ሰውነታችን እንዲወፍር እንደሚያደርግ ኹሉ ጾምም ነፍስን ያበረታል፤ ፈጣንና መንፈሳዊ ክንፍን ይሰጣታል፤ ወደ ሰማያዊ ምሥጢር ገብታ በፅሞና እንድትያዝ ያደርጋታል፤ የዚህን ዓለም ተድላና ደስታ እንድትንቅ ያስችላታል፡፡ ቀላል ጭነትን የተሸከሙ መርከቦች ፈጥነው ባሕሩን እንደሚሻገሩ፣ እጅግ ብዙ ጭነትን የተሸከሙት ግን ባሕሩንና ወጀቡን ቶሎ ማለፍ እንደሚያቅታቸው ኹሉ ልክ እንደዚሁ ጾምም ውሳጣዊ ዓይናችን እንዲበራ፣ የዚህ ዓለም ፈተናዎችን በቀላሉ መቋቋም እንድንችል፣ ወደ ሰማያዊ ምሥጢር እንድንገባ በዚያም ስላሉ አይነገሬ በረከቶችን እንድናስብ፣ በዚህ ዓለም ላይ ያሉት ኹሉም ነገሮች እንደ ጠዋት ጤዛ ፈጥነው የሚያልፉ እንደ ኾኑ እንድንገነዘብ ታደርለች፡፡ ከዚሁ በተቃራኒ አብዝቶ መብላትና ራስን አለመግዛት ደግሞ አእምሯችን የጠፋ፣ ሥጋችን የወፈረ፤ ውስጣችን በእግር ብረት የተጠፈረ፣ በዚህ ኹሉ ተከበንም እጅግ በከፉ ምግባራት የተያዝን፣ የዘለዓለማዊ ሕይወታችን ጠላቶች ኾነን እንድንጓዝ ያደርጉናል፡፡
(10) ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ! መብልንና ራስን አለመግዛት ተከትለው የሚመጡትን ኃጣውእ በማወቅ ከድኅነታችን ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ቸልተኞች አንኹን፡፡ ራስን አለመግዛት አእምሮን እንደሚያጠፋና አብዝተን ልንጋደለው እንደሚገባን፣ ይህን ያደረግን እንደኾነም አክሊል ሽልማቱ የበዛ እንደ ኾነ የተማርነው በዘመነ ሐዲስ ብቻ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን በዚያ በጨለማ የተቀመጡ፣ የብዙ ጧፎች ጥገኛ የነበሩ፣ ሕፃንን ቀስ በቀስ ወተት አስትተው ፅኑ መብልን እንደሚያስለምዱት ቀስ በቀስ ወደ አማናዊ ብርሃን የተሻገሩ ቢኾኑም፥ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ሰዎችም አብዝተው እንዲበሉ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ ራስን አለመግዛት ይህን ያህል አደገኛ እንደ ኾነ ስነግራችሁ የራሴ ሐሳብ እንዳይመስላችሁ ግን ነቢዩ የተናገረውን አድምጡ፤ እንዲህ በማለት፡- “ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለሚተኙ፣ በምንጣፋቸው ደስ ለሚሰኙ፣ ከፍየሎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለሚመገቡ፣ ከበገናው ድምጽ ጋር አስተባብረው ለሚያጨበጭቡ ሰዎች፣ በጽዋ የቀላ ወይንን ለሚጠጡ፣ እጅግ ባማረ ሽቱም ለሚቀቡ - ይኸውም ለዘለዓለም የሚኖርና የማያልፍ ለሚመስላቸው ወዮላቸው” /አሞ.6፥3-6/፡፡ እንግዲህ ነቢዩ፡- በስንፍና፣ በፍትወትና መብልን በማብዛት የነበሩትን አይሁዳውያንን እንዴት አድርጎ እንደወቀሳቸውና እንደገሠፃቸው ተመለከታችሁን? ኃይለ ቃላቱን በደንብ አስተውሏቸው፡- አብዝተው መብላታቸውንና መጠጣታቸውን ከወቀሳቸው በኋላ እንዲህ ብሎ ይጨምራልና፡- “ይኸውም ለዘለዓለም የሚኖርና የማያልፍ ለሚመስላቸው፡፡” ይህም ማለት፡- ደስታቸውና ፈንጠዝያቸው የሚያበቃው በከንፈራቸውና በላንቃቸው ላይ ብቻ ነው፤ ከዚያ ወዲያ መሔድ አይችልም፡፡ ደስታው ከመገኘቱ የሚጠፋ ነው፤ የሚያገኛቸው ምረረ ገሃነም ግን መቼም መች የሚያበቃ አይደለም፤ ፍጻሜ ያለው አይደለም፡፡ “ለዘለዓለም የሚኖርና የማያልፍ ለሚመስላቸው” የሚለው ደስታ ገና ከመገኘቱ የሚጠፋ መኾኑን አማናዊ ትርጓሜ የምናውቀው ያኔ ነው፡፡ 
(11) አሁን በዚህ ምድር ላይ የምንመለከታቸው የሰው ሰውኛና ሥጋዊ ነገሮች ልክ እንደ ደስታውና ፈንጠዝያው የሚጠፉ ናቸው፡፡ ክብርና ሥልጣን፣ ሀብትና ንብረት፣ በዚህ ዓለም ላይ የምናገኛቸው ብልጽግናዎች ኹሉ ጸንተው የሚኖሩ አይደሉም፡፡ ኹሉም ከወራጅ ውኃ በፈጠነ ፍጥነት የሚያልፉ ናቸው እንጂ ከእነዚህ አንዱስ እንኳን ዘለዓለማዊ የለም፡፡ የሙጥኝ ብሎ ሊይዛቸው የሚሞክር ሰው እንኳን በፍጹም ሊያቆያቸው አይችልም፤ የሚቀረው ባዶውን ነው፡፡ መንፈሳዊ ነገሮች ግን እንደዚህ አይደሉም፤ የዚህ ተቃራኒ ናቸው እንጂ፡- እንደ ጽኑ ዐለት የማይንቀሳቀሱ ናቸው፤ ሕልፈት ውላጤ የለባቸውም፡፡ ታዲያ ጸንቶ የሚኖረውን እጠፋ እጠፋ በሚለው፣ የማይነቃነቀውን በሚንገዳገደው፣ ዘለዓለማዊዉን በጊዜያዊው፣ የማያልፈውን በሚያልፈው፣ ዘለዓለማዊ ደስታ የሚሰጠዉን ዘለዓለማዊ ስቃይ በሚሰጠው መቀየራችን እንደ ምን ያለ ሞኝነት ነው?
(12) ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ! ድኅነተ ሥጋን ድኅነተ ነፍስን እናገኝ ዘንድ ራስን አለመግዛትን ከእኛ ዘንድ እናርቀው፤ ጾምንና ከእርስዋ ጋር ያሉትን ሌሎች በጎ ምግባራትን እንውደዳቸው፤ ከዛሬ አንሥተን አዲስ ኑሮን እንጀምር፤ ዕለት ዕለት በጎ ምግባራትን መሥራትም የሚያስደስተን እንኹን፡፡ እንዲህ መንፈሳዊ ተግባራትን የምንፈጽምና የበጎ ምግባር ሀብትን አከማችተን ዐቢይ ጾሙን የምናሳልፍ ከኾንንም ወደ ጌታ ቀን (በዓለ ትንሣኤ) ለመድረስ የተገባን እንኾናለን፤ ወደዚያ ወደ አስደናቂው ማዕድ (ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ) መቅረብ ይቻለናል፡፡ በጌታችን ቸርነትና ሰው ወዳጁ አምላካችን ክርስቶስን ደስ ባሰኙ ቅዱሳን ጸሎትና ምልጃም ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡ ከእርሱም ጋር ለባሕርይ አባቱ ለአብ፣ ለባሕርይ ሕይወቱ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር፣ ኃይልና ጌትነት ይኹን፤ ዛሬም ዘወትርም እስከ ትውልደ ትውልድ ድረስ አሜን፡፡†††
ምንጭ፡- ኦሪት ዘፍጥረት፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው፣

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...