2014 ኦገስት 12, ማክሰኞ

ፍልሰታና ሻደይ

አትም ኢሜይል
ነሐሴ 4 ቀን 2006 ዓ.ም.
ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ በመላው ዓለም የክርስትና እምነት በሐዋርያቱ መሰበክ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሀገራችን የክርስትና እምነት የተሰበከ ሲሆን በተለይም ሀገራችን የሰሜኑ ክፍል በወቅቱ ቀድሞ ክርስትና የተሰበከበትና የሀገሪቱ ዋና ማእከል የነበረ ነው። ይህን ደግሞ ህዝበ ክርስቲያኑ ለረጅም ዘመናት ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጽምባቸው ነበሩ በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና መንፈሳዊ ቁሶች ያስረዳሉ። እነዚህም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ መንፈሳዊ ቅርሶች ናቸው። ከማይዳሰሱ መንፈሳዊ ቅርሶች መካከል የተለያዩ መንፈሳዊ በዓላት የሚከበሩበት ሥርዓት አንዱ ነው።

asendya 01በዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የሻደይ ምስጋና / ጨዋታ አንዱ ሲሆን ልጃገረዶች በአማረ ልብስ ደምቀው አሸንድዬ በሚባል ቄጠማ ጉንጉን ወገባቸውን አስረው የሚያከብሩት ነው። በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃማኖታዊ ይዘት አለው። በዓሉ ከነሐሴ 16 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ ይከበራል። ይህ በዓል በዋግ ኽምራ ሻደይ፣ በላስታ አሸንድዬ፣ በትግራይ አሸንዳ፣ በቆቦ አካባቢ ሶለል፣ በአክሱም አካባቢ ደግሞ ዓይነ ዋሪ እየተባለ ይጠራል።

የሻደይ በዓል ከኦርቶዶክስ ተዋሐዶ እምነት ጋር እየተያያዘ የመጣ ሲሆን አጀማመሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለው፡፡ ከነዚህም መካከል የአዳም ከገነት መባረር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ ከዘመን መለወጫ፣ ከመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቆረጥ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ (ፍልስታ) እና ከመስፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ጋር በማስተሳሰር የሚያስቀምጡት ሲሆን በማኅበረስቡ አባቶችና ሊቃውንቱ ዘንድ ጎልቶ የሚነገረውና የሚተረከው ግን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ (ፍልስታ) በዓልን መሠረት ያደረገ ነው።

አባታችን አዳም በገነት ሳለ ሕግ በመተላለፉ ጸጋ እግዚአብሔር ርቆት እርቃኑን በሆነ ጊዜ አካሉን ለመሸፈን ቅጠል መጠቀሙን ለማሰብ ያች አዳምና ሔዋን ክብራቸውን ተገፈው ከገነት የተባረሩባትን ዕለት በማሰብ በወቅቱ ያገለደሙትን ቅጠል በምልክትነት በመውሰድ የሻደይ ቅጠልን በገመድ ላይ ጎንጉነው በወገባቸው አገልድመው/አስረው/ አዳምና ሔዋን ከገነት ከመውጣታቸው በፊት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ያልጀመሩ ደናግላን ስለነበሩ ያንን በመከተልና በምሳሌነት በመውሰድ ያላገቡ የአገው ልጃገረዶች ተሰባስበው ያችን ዕለት ወይም ቀን በመታሰቢያነት ለመቁጠር ወይም ለመዘከር የሻደይ ጨዋታን መጫወት ወይም ማክበር እንደጀመሩ ይናገራሉ።

ከኖኅ ዘመን ታሪክ ጋር ያለው ግንኙነት ደግሞ ከጥፋት ውኃ በኋላ ውኃው የመጉደሉን ምልክት ርግብ ለኖኅ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣት በምድር ሰላም እነደሆነ የምሥራች አብሥራለች። ከዚሁ ጋር በተገናኘ በዓሉን ያንን ለምለም ቅጠል ወገባቸው ላይ በማሰር ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋገርን ሲሉ ማክበር እንደጀመሩ ከታሪኩ ጋር አያይዘው ያስቀምጡታል።

ከመስፍኑ ዮፍታሔ ታሪክ ጋርም ቢሆን የሻደይ በዓል እንዴት ግንኙነት እንዳለው ሲያስቀምጡ ዮፍታሔ ወደ ጦርነት በሔደ ጊዜ በድል ከተመለስ ለአምላኩ መሥዋዕትን ለማቅረብ ስዕለት ገበቶ ነበር። ይህም ከቤቱ ሲመለስ መጀመሪያ የሚቀበለውን እንደሚሠዋ ሲሆን በዚህ ጊዜ ያለ ወትሮዋ ልጁ እየዘፈነች ልትቀበለው ወጣች በዚህም በጣም አዘነ። ልጁም ለአምላኩ የገባውን ስዕለት እንዳያስቀር ሁለት ወር ስለ ድንግልናዋ አልቅሳ ስዕለቱን እንዲፈጽም ጠይቃው ከሁለት ወር በኋላ ስዕለቱን የፈጸመ ሲሆን አባቷ የገባውን ቃል ኪዳን እንዳያጥፍ ያበረታታችውንና መሥዋዕትነትን ለሀገር፣ ለህዝብ፣ ለአባትና ለፈጣሪዋ የከፈለችውን የዮፍታሔን ልጅ በየዓመቱ ለአራት ቀናት ሙሾ በማውጣት አስበው ይውላሉ፡፡ በዚህ መሠረት በበዓሉ ላይ ከሚፈጸሙ ተግበራት ጋር አዛምደው መነሻው ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደሆነ ይናገራሉ። “ጽዮንን ክበቡዋት በዙሪያዋም ተመላለሱ…በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ፣ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ” መዝ 48፥12

የሻደይ በዓል አጀማመርን በተመለክተ ከላይ ከተቀመጡት ታሪኮች በተጨማሪ በአካባቢው ሕዝብና በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቶች ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሣው ታሪክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓል ሲሆን ይኸውም እግዚአብሔር አምላክ ለአዳምና ሔዋን ከ5500 ዘመን በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኃጢያት እሥራት ነጻ እንደሚያወጣቸው በገበላቸው ቃልኪዳን መሠረት አምላክ የተወለደባት እና ትንቢቱ የተፈጸመባት፣ በሔዋን ስህተት ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ በእርሷ ምክንያት ከኃጢያት ባርነት ነጻ የወጣባትና ወደ ቀድሞ ቤቱ ገነት እንዲመለስ ምክንያት የሆነችው የሰው ልጅ መመኪያ የተባለች እመቤት፣ እንደማንኛውም ሰው የተፈቀደላትን እድሜ በምድር ከኖረች በኋላ ሞተ ሥጋን እንደ ሞተች ከመጽሐፍት እንረዳለን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ በኋላ ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ አረገች፡፡

በፍልሰታ ወቅት በዓሉ መከበሩም ለሻደይ ተጨዋቾች ተምሳሌትና የድንግልናቸው አርዓያ የሚያደርጓት ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌቴሰማኔ ወደ ገነት መፍለሱን እንዲሁም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊ የሆኑት መጋቢ ምስጢር ገብረ ሕይወት ኪዳነ ማርያም “በዓሉ በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው በሄዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመከፈቱ ነው። መመኪያቸው ስለሆነች ልጃገረዶች በዓሉን ያከብሩታል ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት በእርሷ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ዕርገቷን መላዕክት በእልልታ፣ በሽብሸባና በዝማሬ ነጫጭ ልብስ ለብሰው አጅበዋት ነበር፡፡ ዕለቱን ፍስለታ ብለን የምንጠራውም ማርያም ከሞት ተነሥታ ማረጓን፣ ሙስና መቃብር አፍልሳ መነሣትዋን ወይም ዕርገቷን በማሰብ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን በነሐሴ 16 ቀን እንደ አዲስ በመላዕክት ሽብሸባ፣ እልልታ፣ ዝማሬና ዝማሜ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ስታርግ እንዳዩ፡፡ በታላቅ ፍስሃ ይመለከቱና በታዓምራቱ ይደነቁም ነበር፡፡ ከዛን ዕለት ጀምሮ ደናግል ቅዱሳን ከመላእክቱ በተመለከቱት ሥርዓት መነሻነት ባህላዊ ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ የወቅቱ መታሰቢየ የሆነውን ለምለሟን ከምድር ሳሮች ሁሉ ረዘም ያለችውን የሻደይ ቅጠል በወገባቸው አስረው እንደ መላአክቱ አክናፍ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ በማሽከርከር እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባሰባስበው በፍቅርና በሐሴት ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ በመጾም ጾሙ ከሚፈታበት ከዳግም ዕርገቷ ነሐሴ 16 ጸሎታቸው ተሰምቶላቸው የፈለጉትን ማየታቸውን ምክንያት በማድረግ እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ በየዓመቱ ማክበር እንደተጀመረ ይነገራል፡፡

እናቶችና እኅቶች በአደባባይ ወጥተው የድንግል ማርያምን ሞትን ድል አርጎ መነሣት ትንሣኤዋንና ዕርገቷን እንደ ነጻነታቸው ቀን ቆጥረው የተለያዩ አልባሳትን በማድረግና ለበዓሉ ክብር በመስጠት ከበሮ አዘጋጅተው አሸነድዬ የተባለውን ቄጠማ በወገባቸው ታጥቀው ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ይዘክራሉ፡፡ በዚህም መሠረት የሻደይ ጨዋታ የፍስልታ በዓል መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እንደተጀመረና በምእመኑ ለረጅም ጊዜ እየተከበረ የኖረ ሃይማኖታዊ በዓል እንደሆነ ይታመናል፡፡

የሻደይ ልጃገረዶች የቡድን አመሠራረት ደብርን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የሻደይ ጨዋታ በዓል በሚያከብሩበት ጊዜ ልጃገረዶች የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን ለብሰው ከበሮ እና ለምስጋናው የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት ተጠራርተው በመጀመሪያ ወደ አጥቢያቸው በመሄድ የቤተ ክርስቲያኑን ደጁን አልፈው ይዘልቃሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑን ደጅ ከተሳለሙ በኋላ የተለያዩ ጣዕመ ዝማሬ እያሰሙ ሦስት ጊዜ ይዞሩና ደጃፉን ተሳልመው በቅጥር ግቢው አመቺ ቦታ ፈልገው ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡ ከበሮአቸውን እየመቱ፣ የታቦቱን ስም እየጠሩ በሚያምር ድምፃቸው፣ ሽብሻቦ፣ ውዝዋዜ፣ ጥልቅ መልእክትን በያዙ ግጥሞች፣ ለዚህ ያደረሳቸውን አምላክና ታቦት ያወድሳሉ፣ ያሞግሳሉ፣ ያከብራሉ፣ ይለማመናሉ፡፡ ምስጋናው ለዚህ ዓመት ያደረሳቸውን አምላክ የሚያመስግኑበት እና ቀጣዩ ዓመትም እንደዚሁ የሰላም፣ የጤና የተድላ እንዲሆን የሚማጸኑበት፣ ተስፋቸውን የሚገልጹበትና ስለት የሚሳሉበት በመሆኑ ምስጋናውን ሞቅ፣ ደመቅ አድርገው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በፍቅር፣ በደስታ፣ በመተሳሰብና በሰላም ይጫወታሉ፡፡ እያንዳንዱ አባል ለእግዚአብሔርና ለደብራቸን ታቦት ያልሆነ እያሉ ጉልበታቸውን፣ ችሎታውንና ልምዳቸውን ሳይቆጥቡ በምስጋናው ይሳተፋሉ።

ከቤተ ክርስቲያን መልስ በአካባቢው ወዳሉት ትልልቅ አባቶች ዘንድ ሄደው በመዘመር ምርቃን ይቀበላሉ። ከዚያ መልስ ወደ ተራራማ ስፍራ በመውጣት ክብ ሠርተው ይዘምራሉ፡፡ ከዝማሬያቸው ውስጥ ግጥሞቹ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ግጥሞች ከግለሰባዊ ስሜት ወይም ከግለሰብ ውዳሴ የራቁ ናቸው፡፡ የቡድን አመሠራረታቸው ደብርን መሠረት ያደረገ በመሆኑ አንዱ ቡድን ከሌላው ቡድን የተሻለ መሆኑን ለማሳየት ፣ የደብሩን ኃያልነት፣ ደብራቸውን እንደማያስደፍሩና እንደሚጠብቁ በምስጋናቸው ይገልጻሉ፡፡

የወከሉትን ደብር ታቦት ስም እየጠሩ ለአባት እናት፣ ለቤተሰብ ጤና፣ ጸጋ፣ ሀብት፣ ሰላም በአጠቃላይ መልካሙን ሁሉ እንዲያድላቸው ይማጸናሉ፡፡ አደራውን ለታቦቱ ይሰጣሉ፡፡ ለዚህም ዜማውና ግጥሙ ተመሳሳይ ቢሆንም የወከሉትን ደብር ስም ብቻ በማቀያየር በተመሳሳይ ዜማና መወደስ እና መማጸን በሁሉም የሻደይ ተጨዋች ቡድኖች ይታይል፡፡ ልጃገረዶቹ በዚህ የምስጋና ጊዜ የሚሰበሰቡትን ሥጦታዎች ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ።

የሻደይ ምስጋና/ጨዋታ በዚህ መልኩ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በማመስገን ከፍከፍ በማድረግ ዕርገቷን በማሰብ የአምላክ እናት አማልጅን እያሉ ስሟን በመጥራትና በማክበር የሚከናወን በመሆኑ ይህንን ሃይማኖታዊ መሠረትነት ያለውን ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ከሁላችን ይጠበቃል። የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡
  • ምንጭ፡-ሰቆጣ ማእከል ሚዲያ ክፍል

ዘመኑን የዋጁ በሥልጠና የታገዙ ካህናት እንደሚያስፈልጉ ሊቀጳጳሱ ገለጡ

 የደቡብ ትግራይ ማይጨው እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሐምሌ 29 2006 ዓ.ም ከማይጨው ከተማ እና ዙሪያው  አድባራትና ገዳማት ለተውጣጡ ከ70 በላይ የሚሆኑ  ካህናትን ለ15 ቀናት ያህል ሰልጥነው በተመረቁ  ዕለት ሊቀጳጳሱ እንደተናገሩት ዘመኑ የተወሳሰበ ከመሆኑ የተነሳ  ዘመኑን የዋጁ በተለያዩ ጊዜያት በሥልጠና  የታገዙ ካህናት  ያስፈልጋሉ ሲሉ በምርቃቱ ላይ ተናገሩ፡፡ ስልጠናው የተዘጋጀው በነገረ መለኮት ምሩቃን መንፈሳዊ ማኅበር እና በደቡብ ትግራይ ማይጨው ሀገረ ስብከት ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡ ሥልጠናው ትምህርተ ኖሎት፤ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፤ የስብከት ዘዴ እና ሌሎችንም  ያካተተ መሆኑ ታውቆአል ፡፡ደፊትም በዚሁ ምልኩ ሥልጠናዎች ለካህናቱ እንደሚሰጥ ሊቀጳጳሱ አስታውሰዋል፡፡




                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...