መኪናዋ
ተገፍታ ለመጨረሻ ጊዜ ስትወጣ
|
የአካባቢው ገበሬዎችና አሣፍረናቸው የነበሩ ሌሎች ገበሬዎች ተባብረው መኪናዋን በዳገቱ
መግፋት ጀመሩ፡፡ ድንበሩ አንዴ ገብቶ መሪ ይዞ ይነዳል፣ አንዴ ወርዶ ጎማውን በካልቾ ይማታል፡፡ ሙሉቀን በትጋትና ተስፋ
ባለመቁረጥ መኪናዋን ከፖሊሶቹና ከገበሬዎቹ ጋር ይገፋል፡፡ ቀለመወርቅ መኪናዋን የሚመለከት የሕግ ዐንቀጽ የሚፈልግ ይመስል
አንገቱን ደፍቶ አንዳች ነገር ያስሳል፡፡ ኤልያስ መነጽሩን ከፍ እያደረገ ለድንበሩ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ ይህ ሁሉ ግን
መኪናዋን ዳገት እንድትወጣ አላስቻላትም፡፡
እኛም
የወጣችውን መኪና በእግር ስንከተል
|
ቀለመወርቅ ‹ድንጋዩን አንሡ› የሚለው ጥቅስ ትዝ ብሎት ነው መሰል መኪና መንገዱ
ውስጥ ገብቶ ጭንቅላት ጭንቅላት የሚያህሉ ድንጋዮችን ማንሣት ጀመረ፡፡ መኪናዋም ጥረቱን አደነቀችለት መሰል ወደላይ የመውጣት
ተስፋ ሰጠች፡፡ ገበሬዎቹም ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው ወደ ላይ ገፏት፡፡ ‹ተመስገን› ዋናውን ዳገት እያቃሰተች ወጣችና
አፋፍ ላይ ቆመች፡፡ የሁሉም ፊት ከኀዘን ወደ ደስታ፣ ከቀቢጸ ተስፋ ወደ ተስፋ ተቀየረ፡፡
‹‹አይዟችሁ ከዚህ በኋላ ሌላ ዳገት የለም›› አለን አብሮ የነበረው ቆፍጣናና
ጉልበታም ገበሬ፡፡ መኪና የገፋበትን ክንዱን እየወዘወዘ፡፡ እውነትም እንዳለው ቀሪው መንገዳችን ሜዳ ነበረ፡፡ ከውስጥ እኛ፤
ከውጭ ገበሬዎቹ ተሣፈርንና ያለፈ ነገራችንን እያነሣን ወደ መዳረሻችን ጉዞ ቀጠልን፡፡
መኪናዋ
በዳገቱ መጨረሻ ላይ
|
እነሆ የኳሳ ደረስን፡፡ በመኪና ልንሄድበት የምንችለው የመጨረሻው ቦታ የኳሳ ከተማ
ናት፡፡ ሊቀ ካህናቱ የምንሄድበትን በረሃ በሩቁ አመለከቱን፡፡ ‹ልብ የሌላትን መኪና ገፍቶ እዚህ ያደረሰ አምላክ ልብ የሰጠንን
እኛን እዚያ ማድረስ አያቅተውም› ብለን አመንን፡፡ የከተማው ፖሊስ ጣቢያ መኪናችንን አቆምን፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች፣ የወረዳው ሊቀ
ካህናት፣ ከወረዳው ቤተ ክህነት የመጡ አንድ ሌላ ዳዊት ደጋሚ ካህን እና እኛ አራታችን በእግር ለመገስገስ ተዘጋጀን፡፡ እኒህ
ዳዊት ደጋሚ ካህን የሚገርም ተሰጥዖ አላቸው፡፡ እኛ እንሂድ አንሂድ ስንጨነቅ፣ ሰው ሁሉ የመሰለውን እየሰነዘረ ሲከራከር፣
መኪና ስትሄድ፣ መኪና ስትቆም እርሳቸው ዳዊት መድገማቸውን አያቆሙም፡፡ ባይሆን እንደ መሐል ከተማ ሰው ዲፕሎማሲ ባለመቻላቸው
ድንበሩ ተቀይሟቸው ነበር፡፡ ‹ምን ያህል መንገድ ይቀረናል?> ሲላቸው መልሳቸው ‹ገና ምኑ ተነካ› ነው፡፡ ‹ሞራል አይሰጡም፤ ተስፋ ያስቆርጣሉ›
አለ ድንበሩ፡፡ እርሳቸው እንደሆነ ቁርጥ ያለ የዘመድ ዋጋ ነው የሚያውቁት፡፡
ዳገቱ
አለቀ
|
ከየኳሳ ከተማ ሁለተኛው ምእራፍ ተጀመረ፡፡ በሩቁ የምናቋርጠው በረሃ ተዘርግቷል፡፡ መንገድ
ላይ የደብረ ዕንቁ አገልጋይ የሆኑ መሪጌታ ይጠብቁናል፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ ኤልያስ ማንከስ ጀመረ፡፡ ከዚህ
ጉዞ ላለመቅረት ብሎ እንጂ እግሩን ኦፕራስዮን አድርጎ ነበር፡፡ ያደረገው ጫማ ሸበጥ ነገር ነው፡፡
የወንዝ
ዳር ረፍት
|
ድንበሩና አንደኛው ፖሊስ
ከፊት፣ ካህናቱና ሙሉ ቀን ከመካከል፣ ከእነርሱ ቀጥሎ ቀለመወርቅ፣ እኔና ኤልያስ በስተመጨረሻ ‹አዴም ነዲያቸው› እያልን እንጓዝ ነበር፡፡ የኤልያስ እግር መቁሰል ጀምሯል፡፡
በበረሃው
መግቢያ በር
|
መንደሮችንና እርሻዎችን እያቋረጥን ነበር የምንጓዘው፡፡ አሥር ዓመት የማይሞላቸው
ሴትና ወንድ እረኞች እጃቸውን አፋቸው ላይ አድርገው በግርምት ያዩናል፡፡
አዲስ ጠረን የሸተታቸው ከብቶች በአጠገባቸው ስናልፍ
ቀንዳቸውን ሊፈትሹብን ይፈልጋሉ፡፡ ሰላምታ የማይጓደልባቸው የስማዳ ገበሬዎች ከዐጨዳቸው ላይ ብዲግ እያሉ፣ በሽክና ጠላቸውን
ይዘው በመጋበዝ በሰላምታ ያሳልፉናል፡፡
የቸሩ
የስማዳ ገበሬ ግብዣ
|
አሁን የመሪጌታ ጥዑመ ልሳን እርሻና መንደር ጋ ደረስን፡፡ እኒህ መሪጌታ ‹በከንቱ
የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ› የሚለውን ቃል አክብረው፣ ከተማውን ትተው እዚህ ገጠር ተቀምጠው ደቀ መዛሙርት የሚያፈሩ መሪጌታ
ናቸው፡፡ ምርግትናውን ከክህነት፣ ክህነቱንም ከግብርና አስተባብረው እያረሱ ያስተምራሉ፣ እያስተማሩም ያርሳሉ፡፡ ደቀ
መዝሙሮቻቸው በአንድ በኩል ለመምህራቸው የጉልበት አገልግሎት ይሰጣሉ፤ በሌላ በኩል ከመምህሩ ዕውቀት ይሸምታሉ፡፡ ተማሪዎቻቸውን
በመደዳ ያስቀምጡና በሬያቸውን ይጠምዳሉ፡፡ ወዲያ ሲሄዱ ለአንዱ ቀለም ይነግራሉ፣ ወዲህ ሲመጡም ለሌላው ቀለም ይነግራሉ፡፡
እርሻውም የታደለ ነው፤ ቃለ እግዚአብሔር እየፈሰሰበት ይታረሳል፣ ይዘራል፣ ይታጨዳል፣ ይወቃል፡፡ ይህንን የመሰሉ ሰዎች
ያመረቱት እህል እየተቀላቀለበት ሳይሆን አይቀርም ሞሰባችን ረድኤት የነበረው፡፡
እረፍት
በመሪጌታ እርሻ አጠገብ
|
በመሪጌታው እርሻ ጎን ዕረፍት አደረግን፡፡ እግረ መንገዳችንንም እርሳቸውን እንጠብቅ
ዘንድ፡፡ የመምህሩ ቤት ከመንገዳችን በስተ ቀኝ ከዛፎቹ ሥር ነው፡፡ ዙርያውን በተማሪዎቻቸው ጎጆዎች ተከብቧል፡፡ አሁን የአጨዳ
ጊዜ በመሆኑ ተማሪዎቻቸውን አስተባብረው ወደ አጨዳ ሄደዋል፡፡ አውድማቸው የተቀመጥንበት አካባቢ ነውና እህሉን ወደዚህ
ያመጣሉ፡፡ ከባለቤታቸው ጋር እያወጋን ጠበቅናቸው፡፡ እግረ መንገዳቸውን አብረውን ያሉት ካህን ስለ ጌርጌስ ያወጉን ጀመር፡፡
አባ ፊልጶስ
ከጌርጌስ ወደ ሐቃሊት የመጣበት በረሃ
|
‹ጌርጌስ ማለት ያ ከማዶ የምታዩት ሜዳማ ተራራ ነው፡፡ በደብረ ዕንቁ እና በጌርጌስ መካከል ታላቅ በረሃ አለ፡፡ ጌርጌስ
አጠገብ የጃምባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ያለበት ጋሼና የሚባል ቦታ አለ፡፡› ‹በዜና መዋዕሉ ከጋሼና እስከ ዐንቆ የሚለው
ይህንን ነው ማለት ነው› አልኩ፡፡ አቡነ ፊልጶስ ወደ ሐቃሊት ሲመጣ ከአቡነ ሰላማ መተርጉም ጋር የተገናኘው በጌርጌስ መሆኑን
ገድሉ ይነግረናል፡፡ ይህቺ ቦታ ከጥንት ጀምሮ የጳጳሳት መቀመጫ ነበረች፡፡ አሁን በትክክልም የአቡነ ፊልጶስን የመጨረሻ ቦታ
እያገኘነው ነው ማለት ነው፡፡
የመሪጌታ
ተማሪዎች ጎጆ
|
አንቆስ ማናት? ደብረ ዕንቁ ትሆን? ይህንን እያሰብኩ እያለ፡፡ ያን ጊዜ አንደኛውን ፖሊስ ዝም ብለን ክንቀመጥ ብዬ
‹እንዴው ስለ ሀገሩ ምን ይዘፈናል?› አልኩት፡፡ እርሱም እንዲህ አለኝ
ላሊበላን መሳም በከንቱ ድካም ነው
ከየኳሳ በታች ዐንቆ መጨምጨም ነው
እጅግ የሚገርም ሰምና ወርቅ ቅኔ፡፡ የኳሳ መኪናችንን ያቆምንባት ከተማ ናት፡፡ ‹ከየኳሳ
በታች ዐንቆ መጨምጨም ነው› አለ፡፡ ‹ዐንቆ ማናት?› አልኩት፡፡ ‹ዐንቆ ማለት ደብረ ዕንቁ ናት› አለኝ፡፡ እፎይ አልኩ፡፡ ‹ከዐንቆ
እስከ ጋሼና› የሚለው ተፈታ ማለት ነው፡፡ ‹ሐቃሊት የተባለችውኮ ደብረ ዕንቁ ናት፤ ሐቃሊት ማለት በበረሃ ያለች ቦታ ማለት
ነው› አሉና ካህኑ ይዘረዝሩት ጀመር፡፡ ገርሞኝ ነበር በደስታ የማያቸው፡፡ ‹ሐቃሊት የታለች?› አልኳቸው፡፡
ሐቃሊትን ትንሽ ከሄድን በኋላ ታያታለህ፤ ጌርጌስ ያውልህ፡፡ አቡነ ፊልጶስ የታመመው እዚያ ነው፡፡ ወደ ሐቃሊት የመጣው ታቹን
በበረሃው አድርጎ ነው፡፡ በበረሃው ከመጣ በኋላ እዚህ ዳገቱ ላይ ሲደርስ ዐረፈ፡፡ ያረፈበት ቦታ ይኼውልህ፤ አሁን የታቦት
ማርገጃ አድርገነዋል›› አሉና አሳዩኝ፡፡ ቦታውን ወድቄ ተሳለምኩት፡፡ ዙርያውን ታጥሮ አንዲት ዛፍ በቅላበታለች፡፡ አካባቢው
ለጥ ያለ ሜዳ ነው፡፡
የመሪጌታ ተማሪ ነዶ ተሸክሞ |
እኒህ ዳዊት ደጋሚ ካህን ብርቱ ናቸው፡፡ መምህሩ እስኪመጡ ተማሪዎቻቸው ያመጡትን
የጤፍ ነዶ በአውድማው ላይ ይከምሩላቸው ጀመር፡፡ የቄስና የሴት እንግዳ የለውም ማለት ይኼ ነው፡፡ መምህሩ ነዷቸውን ተሸክመው
መጡ፡፡ የተሸከሙትን አወረዱና ሰላም አሉን፡፡ ከእርሳቸው ጋር ወደ ደብረ ዕንቁ ለመሄድ መምጣታችንን ስንነግራቸው በደስታ
አብረውን ለመሄድ ተነሡ፡፡ ወደ ቤታቸው ደርሰው ልብሳቸውን ቀየሩና ከእኛ ጋር ተቀላቀሉ፡፡
መሪጌታ
ነዶ ተሸክመው
|
እነሆ አሁን የበረሃውን መንገድ ለማግኘት አባ ፊልጶስ ከጌርጌስ ሲመጣ ባረፈበት ሜዳ
በኩል አቋርጠን መንገድ ጀመርን፡፡ መሪጌታ በሁለት ነገር ጠቅመውኛል፡፡ በአንድ በኩል ታሪክና ጨዋታ ዐዋቂ ስለሆኑ መንገዱን
ያለ ድካም እንድንጓዝ አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእድሜ ጠገቡ ጃንጥላቸው የስማዳን ፀሐይ መክተውልኛል፡፡
ወደ በረሃው
ጉዞ
|
አሁን ኤልያስ እያነከሰ፣ ድንበሩ መሐል መጥቶ ፣ ቀለመወርቅና ሙሉቀን ከካህናቱ ጋር አብሪ
ሆነው ወደ ቆላው ልንገባ ነው፡፡ ቆላው ሁለት ተራሮችን ወጥቶ መውረድና ሦስተኛውን ተራራ መውጣት ይጠይቃል፡፡ መሪጌታ አቡነ
ፊልጶስ ከጌርጌስ ወደ ሐቃሊት የመጣበትን በረሃ አሳዩን፡፡ ከጎንና ጎን ተራራ ያለበት ገደል ነው፡፡
ከመጀመርያው ተራራ ወርደን |
አሁን ደብረ ሐቃሊት ከሩቁ
ትታያለች፡፡ ሲቀርቧት የምትርቅ ሞሰበ ወርቅ የመሰለች ተራራ ናት፡፡ ወደ እርሷ ለመድረስ ግን ሁለት ተራሮች እንደ መቅድም
ሆነውላታል፡፡ ታምሯ እርሷ ናት፡፡
ኤልያስ፡-
ከሁለት እግር ወደ ሦስት እግር
|
ወደ ሁለት ሰዓት የፈጀ የመውጣትና የመወረድ ጉዞ በማካሄድ ላይ ነን፡፡ ቆላው
ውስጥ፡፡ አሁን የምንሄድበት መንገድ አንድ ሰው ብቻ የሚያሳልፍ የተፈጥሮ ድልድይ ነው፡፡ በግራና በቀኝ ገደል ነው፡፡ ‹ከዚህ
የተንከባለለ ወይ በሽሎ ወይ ዓባይ ነው የሚገኘው› ብለውኛል መሪጌታ፡፡ እኛም ከሁለቱ በአንዱ ላለመገኘት በጥንቃቄ መሥመር
ሠርተን በመጓዝ ላይ ነን፡፡ አንዱን ተራራ ይህንን በመሰለ እንደ ባሕረ እሳት መንገድ በቀጠነ መሷለኪያ አለፍነውና ሌላ ተራራ
ከፊታችን ተገተረ፡፡
ከደብረ
ዕንቁ ማዶ የሚገኘው ጌርጌስ ነው
|
እርሱ ደግሞ ዐለቶች ተሰባስበው በማኅበር የመሠረቱት ነው፡፡ ከዐለቱ በስተጀርባ ተዙሮ
ወደ ፊቱ ለመምጣት ከቁጥቋጦና ስለታም ድንጋዮች ጋር ትግል ይጠይቃል፡፡ በዐለቱ ጫፍ ላይ ሆናችሁ የመጣችሁበትን መንገድ ወደታች
ስታዩት እናንተ ከጠፈር ጥግ ያላችሁ ነው የሚመስላችሁ፡፡ ሁሉም ነገር የጣት ቁራጭ አክሎ ነው የሚታየው፡፡ ዐለታማውን ተራራ
ተጠማዝዘን ወረድነውና ተራራውን ከደብረ ዕንቁ ጋር ወደሚያያይዘው ቀጭን መንገድ ገባን፡፡ ይህም በግራና ቀኝ ገደል ያጀበው፣
ከቅድሙ ሰርጥ ግን ሰፋ የሚል መንገድ ነው፡፡
ሁለተኛው
ዐለታማ ተራራ
|
ከባዱ ዳገት ወደ ደብረ ዕንቁ የሚያስወጣው ነው፡፡ ተራራውን እንደ ዘንዶ መጠማዘዝን
ይጠይቃል፡፡ ደግነቱ መንገዱ ደልደል ያለ ነው፡፡ ለሃያ ደቂቃ ያህል ከዞርነው በኋላ አንድ ቦታ አገኘን፡፡ ‹ይህ ቦታ ምዕራፈ
ወለተ ጴጥሮስ ይባላል› አሉን መሪጌታ ጥዑመ ልሳን፡፡ ‹‹ወለተ ጴጥሮስ ይህንን ገዳም ውኃ በመቅዳት አገልግላለች፤ ውኃ ቀድታ
ስትመጣ የምታርፍበት ቦታ ስለሆነ ምዕራፈ ወለተ ጴጥሮስ ተባለ›› አሉን፡፡ ይህ ታሪክ በወለተ ጴጥሮስ ገድል ላይ ተጽፏል፡፡
ምእራፈ
ወለተ ጴጥሮስ
|
ምዕራፈ ወለተ ጴጥሮስን ካለፍን ከሃያ ደቂቃ በኋላ የገዳሙን በር አገኘነው፡፡ እነሆ
ጉዟችን ወደ መጠናቀቂያው እየደረሰ ነው፡፡ የገዳሙን በር ከዘለቃችሁ በኋላ ሌላ መንገድም ይጠብቃችኋል፡፡ ያውም ተራራማ
መንገድ፡፡ ደግነቱ ብዙም ሩቅ አይደለም፡፡
ከተራራው
ሥር
|
ፊት ለፊታችን ደብረ ዕንቁ ማርያም ታየችን፡፡ አንቺን ፍለጋ ስንት ጊዜ ለፋን፣
ስንቱንስ ሀገር አቋረጥን፡፡ ስንቱን ተራራና ገደልስ ተሻገርን፡፡ መሪጌታ ቤተ ክርስቲያኑን አስከፈቱልን፤ እኛም ወደ ወስጥ
ዘለቅን፡፡ ጸሎት ካደረስን በኋላ ‹ክህነት ያላችሁ ወደ ውስጥ ዝለቁ› አሉ መሪጌታ፡፡ እኛም ወደ ቅድስቱ ዘለቅን፡፡ አቡነ
ፊልጶስ ተቀብሮበት የነበረውንም ቦታ ከመንበሩ ሥር አሳዩን፡፡ የአቡነ ፊልጶስ ዐፅም ለ140 ዓመታት የቆየው እዚህ ነበር፡፡
በዐፄ እስክንድር ዘመን (1471-1487 ዓም) በእጨጌ መርሐ ክርስቶስ ጊዜ በእጨጌ መርሐ ክርስቶስ ጥያቄና በንጉሡ ፈቃድ
ከደብረ ሐቃሊት ፈልሶ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገባ፡፡
አባ ፊልጶስ
ያረፈበት ቦታ
|
ገዳማውያኑ መልካም አቀባበል ነበር ያደረጉልን፤ ገድሉን እያነበቡ ታሪኩን በመንገር፤
ገዳማዊ የሆነውን ምግብ በማቅረብ፤ የበረከቱም ተካፋይ በማድረግ፡፡ ደብረ ዕንቁ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተጠና ብዙ ነገር አላት፡፡
የአቡነ ሰላማ መተርጉም መቀመጫ ነበረችና ምናልባት ጳጳሱ ከአሥራ አንድ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍትን ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተረጎሙት
እዚህ ቦታ ይሆን ይሆናል፡፡
ደብረ
ሐቃሊት በር ደረስን
|
እርሳቸው ለዐረብኛው እንጂ ለግእዙ አዲስ ናቸውና ታላቁን ሥራ የሠሩት በደብረ ዕንቁ የተሰባሰቡ
ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ደብረ ዕንቁ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የተዋሕዶዎች መሸሸጊያና መወያያ በመሆንም ታላቅ
ታሪክ አላት፡፡ እነ ዐራት ዓይና ጎሹን የመሳሰሉ የቅርብ ዘመን ሊቃውንትም መፍለቂያ ናት፡፡ በደብረ ዕንቁና በዲማ ጊዮርጊስ
ሊቃውንት መካከል የነበረው የዘመናት ግንኙነትም ሊጠና የሚገባው ነገር ነው፡፡
ብቻ እኛ እዚህ ደርሰናል፡፡ በጉዟችን የረዱንን የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከትን፣
የስማዳ ወረዳ ቤተ ክህነትን፣ የስማዳ ወረዳ መስተዳድርን፣ የደብረ ዕንቁ ገዳም አባቶችንና ሌሎችንም እግዚአብሔር ዋጋቸውን
ይክፈል እንላለን፡፡
ደብረ
ዕንቁ ማርያም
|
እንደነ አቡነ ፊልጶስ ያሉ በቤተ ክርስቲያን ዘላለም የሚያበራ፣ ለትውልዱም የሥነ ምግባርና የሞራል ስንቅ
የሚሆን ታሪክ ያላቸው ሰማዕታት አባቶች እንደ አዲስ አበባ ባሉ ታላላቅ ከተሞች ቤተ ክርስቲያን ሊታነጽላቸውና ትውልዱ
እንዲያውቃቸው ሊደረግ ይገባል፡፡
አባ ፊልጶስ
ያረፈበት ቦታ፣ ከመንበሩ ሥር
|
በአንዳንድ ቅዱሳን ስም አምስትና ስድስት ቤተ ክርስቲያን በአንድ ከተማ ከመትከል ለእነ አቡነ
ፊልጶስ አንድ ዕድል መስጠት በታሪክም በሰማይም የሚያስመሰግንና ዋጋ ያለው ተግባር ይሆናል፡፡ በማኅበር ተሰባስበው ክርስቲያናዊ
ሥራ የሚሠሩ ወጣቶችም እንደ አቡነ ፊልጶስ ባሉ አባቶች ስም
በመጠራትና ታሪካቸውን ከፍ በማድረግ የበረከታቸው ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ታሪክ ይጋብዛቸዋል፡፡
እረፍት
በገዳሙ ግቢ
|
እነሆ እንደመጣነው ልንመለስ ነው፡፡ ያው ተራራና ገደል፣ ያችው መኪና ይጠብቁናል፡፡
የገዳሙ
ግብዣ
|