2014 ኦገስት 8, ዓርብ

ልጆችም ወላጆችም የሚተባበሩበት የፍልሰታ ለማርያም መታሰቢያ ጾምና በዓል


(አለቃ አያሌው ታምሩ)
  • በኢትዮጵያ እመቤታችንን መውደድ በልማድ እንደ ተረት በማይታይ ዓይነት ኹኔታ ተስፋፍቶ የኖረ አይደለም፡፡ ወንድም ሴትም ቢኾኑ እንዳላቸው የእምነት መጠን በእመቤታችን ስም ጸሎት ጸልየው፣ ስእለት ተስለው፣ ምጽዋት አድርገው፣ ዝክርዋን ዘክረው፣ ስምዋን ጠርተው፣ በአማላጅነትዋ ተማፅነው ዐሳባቸው እየተፈጸመላቸው፣ የጎደለው እየሞላላቸው፣ የጠመመው እየተቃናላቸው፣ ድውያን ፈውስ በማግኘት፣ ሠራተኞች ለሥራቸው የተቃና መንገድ በማግኘት፣ መምህራን በሚያስተምሩበት፣ ቅዱሳን ገድላቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜና ምክንያት ኹሉ የእመቤታችንን ረድኤት እያገኙ ስለሔዱና ዛሬም ያው ያልተቋረጠ ስለኾነ ነው፡፡
  • ከቀደሙ ሰዎች ታሪክ ከእስራኤል መሳፍንት አንዱ ለኾነው የዮፍታሔ ልጅ መታሰቢያ ልጆች ወይም ደናግል በየዓመቱ በዓል ሲያከብሩ እንደነበረ ተነግሯል፡፡ (መጽ. መሳ.፲፩፥፵፡፡) እንዲህ ከኾነ ዘንድ ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅትና ሕፃናት፥ ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች የእናታችንን፥ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን መታሰቢያ በየዓመቱ ሲያከብሩ የበለጠ ነገር ፈጽመዋል ማለት ነው፡፡
    *                 *                 *
መሠረተ ቃል፡-
  • ‹‹ተንሥአ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፡፡›› ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ
    ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት፡፡›› (መዝ.፻፴፩፥፰)
  • ‹‹ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎት ኰኵሕ ቅሩበ
    ጥቅም፡፡›› ‹‹አቅራቢያዬ መልካማ ርግቤ ተነሽ ነዪ በግንቡ አጠገብ ወዳለው ወደ ዋሻው
    ጥላ፡፡›› (መኃ.፪፥፲-፲፬)
ቅዱስ እግዚአብሔር ሰው ለመኾን፥ የሰው ልጅ ለመባል ባሰበው የመጀመሪያው የተስፋው መንገድ የምትገኘው፥ ለእናትነት የመረጣት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ኢትዮጵያ በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያን ትሠራለች፤ ልብዋንም በረድኤትዋ ላይ አሳርፋ በቤተ ክርስቲያንዋ ውስጥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት፥ ጸሎት፥ ምጽዋት፥ ስግደት ታቀርባለች፡፡ በእመቤታችን አማላጅነትም ትማልዳለች፡፡ እንዲኹም የማይጠፋ ስም ተሰጥቷታልና በመዝሙር ፵፬ ፥ ፲፪ – ፲፮ በተጻፈው መሠረት ወላጆች ከነልጆቻቸው ተሰብስበው የእመቤታችንን የልደትዋን፥ ጌታን ለመውለድ ብሥራት የመቀበልዋን፥ የመውለድዋን፥ የዕረፍትዋን፥ የትንሣኤዋን፥ የዕርገትዋን በዓል ያከብራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ከፍ ብሎ የሚታየው በብዛት ልጆች ተሳትፎ የሚያደርጉበት የፍልሰታ ጾምና በዓል ነው፡፡ ፍልሰታ የሚለው ቃል የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፣ ኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ቃል ነው፡፡
filseta lemariam
የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን በወለደችበት፣ ስብሐተ መላእክትን በሰማችበት፣ ባየችበት የልደት ወራት አካባቢ በ፷፬ኛ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ከዚኽ ዓለም በሞት ተለይታ ወደ ሰማይ ስትወጣ በሰማይም በምድርም ለሰውም ለመላእክትም ከልጅዋ፣ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጣት ጸጋና ክብር ተገልጧል፡፡ ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በሰማይ በፍጹም ደስታ አስተርእዮ ኾኗል፡፡ በመጀመሪያ ዐብረዋት የኖሩት ልጆችዋ ቅዱሳን ሐዋርያት በሥጋ ያሉት ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰብስበው፣ ከዚኽ ዓለም የተለዩት በአካለ ነፍስ ተገኝተው የዕረፍቷን ጊዜ እየተጠባበቁ ሳሉ፤ እመቤታችን፤ ‹‹ማዕጠንት አምጡ፤ በጸሎትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥሩት፤›› አለቻቸው፡፡ እነርሱም ትእዛዟን በመፈጸም ላይ ሳሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በክብር፥ በጌትነት ተገለጠ፡፡ እናቱንም፤ ‹‹የተወደድሽ እናቴ ሆይ! ዛሬ ድካምና ሕማም ወደሌለበት ወደ ዘለዓለም መንግሥት ላሳርግሽ መጥቻለኹ፤ ወደ እኔ ነዪ፤›› እያለ ሲያነጋግራት ቅድስት ነፍስዋ ከክቡር ሥጋዋ በልጅዋ ሥልጣን ተለየች፤ ልጅዋም በክብር ተቀበላት፡፡ በዚኽ ጊዜም ነቢዩ ዳዊት፤ ‹‹ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤›› እያለ ያመሰግናት ነበር፡፡ ቅዱሳን መላእክት፥ ነቢያት፥ ሐዋርያት፥ ጻድቃን፥ ሰማዕታት በዚያው ከበው ቆመው፤ ‹‹ጸጋን የተመላሽ ሆይ! እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነውና ደስ ይበልሽ፤›› እያሉ ያመሰግኗት ነበር፡፡ በዚኽ ዓይነት ጸጋና ክብር በልጇ ሥልጣን፥ በልጇ ቸርነት ወደ መንግሥተ ሰማያት አሳርገዋታል፤ ‹‹እቴ ሙሽራዬ ከሊባኖስ ከእኔ ጋራ ነዪ፤›› የሚለው ተፈጽሞላታል፡፡ ሥጋዋንም ቅዱሳን ሐዋርያት ለጊዜው ጌቴሴማኒ በተባለ ቦታ አሳርፈውታል፡፡ በሦስተኛው ቀን ግን መላእክት ከዚያ አፍልሰው በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውታል፡፡ ከመቃብር እስከ ተነሣችበትና ፍጹም ዕርገት እስካገኘችበት እስከ ነሐሴ ፲፮ ቀን ለኹለት መቶ አምስት ቀኖች በዚያው ቆይቷል፡፡ በዕለተ ዕረፍቷ ብዙ ተኣምራት ተደርገዋል፡፡ ለድውያን የፈውስ ጸጋ ታድሏል÷ ስሟን ለሚጠሩ ኹሉ ፍጹም በረከት ተሰጥቷል፡፡ የፈውስ ጸጋ ከደረሳቸው አንዱ ታውፋንያ ወይም ሶፎንያስ የሚባለው አይሁዳዊ ነው፡፡
ታሪኩ እንደሚገልጸው፣ እመቤታችን ካረፈች በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በኀዘን ላይ እንዳሉ ለጊዜው በኢየሩሳሌም ያልተገኘውና በሀገረ ስብከቱ የነበረው ቅዱስ ቆማስ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ቅዱሳን መላእክት ሥጋዋን ወደ ገነት ሲያፈልሱ አይቶና ደርሶ ነገሩንም ከመላእክት ተረድቶ ለወንድሞቹ ለሐዋርያት ነግሯቸው ነበር፡፡
ሐዋርያትም ከእመቤታችን በመለያየታቸው እያዘኑ ምስጢሩን ለማወቅ ይጓጉ ስለነበር ጌታ ተገልጾላቸው፤ ‹‹እናቴን አሳያችኋለሁ፤›› የሚል ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ በዚህ ተስፋ ላይ ሳሉም ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፣ ‹‹ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረን በጾም እመቤታችንን እንዲያሳየን ፈጣሪያችንን እንጠይቀው፤›› አላቸው፡፡ እነርሱም ዐሳቡን ተቀብለው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ኹለት ሱባዔ ከጾሙ በኋላ ነሐሴ ፲፮ ቀን ጌታ መላውን ሐዋርያት ወደ ገነት አውጥቶ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረው መቃብር እመቤታችንን ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋሕዶ አንሥቶ ትንሣኤዋንና ዕርገትዋን አሳይቶ ለዓለም ይህንኑ እንዲያስተምሩ አዘዛቸው ይላል፡፡
መሠረቱ ግን ቀደም ሲል የገለጥነው በመዝሙር ፻፴፩፥፰ ላይ፤ ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤›› የሚለው ነውና እንግዳ ነገር ሊኾን አይችልም፡፡ በዚኹ መሠረት ኢትዮጵያ ይህን ጽሑፍ ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ፣ ‹‹ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ኹሉ ክብርዋ ነው፤ በወርቀ ዘቦ ልብስ ተሸልማለች፤ በኋላዋም ለንጉሥ ደናግልን ይወስዳሉ፤ ባልንጀሮችዋንም ይወስዱልኻል፡፡ በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ፤ ወንዶች ልጆችሽን በዕቅፋቸው፥ ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ያመጡልሻል፤›› ተብሎ በተነገረው የነቢያት ቃል መሠረት ልጆችም ወላጆችም በመተባበር የእመቤታችንን የፍልሰታ ጾምና በዓል ሲጠብቁ ይኖራሉ፡፡
ከቀደሙ ሰዎች ታሪክ ከእስራኤል መሳፍንት አንዱ ለኾነው የዮፍታሔ ልጅ መታሰቢያ ልጆች ወይም ደናግል በየዓመቱ በዓል ሲያከብሩ እንደነበረ ተነግሯል፡፡ (መጽ. መሳ.፲፩፥፵፡፡) እንዲህ ከኾነ ዘንድ ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅትና ሕፃናት፥ ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች የእናታችንን፥ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን መታሰቢያ በየዓመቱ ሲያከብሩ የበለጠ ነገር ፈጽመዋል ማለት ነው፡፡
Filstea LeMariam
ጌታ በሕይወተ ሥጋ በዚኽ ዓለም በነበረበት ጊዜ ሽቱ ለቀባችው ሴት ወንጌል በተሰበከበት ኹሉ ያቺ ሴት የሠራችው እንዲነገርላት÷ ወንጌል በተነበበበት ቦታ ኹሉ እንድትታሰብ ጌታ ቃል ሰጥቷል፡፡ (ማቴ. ፳፮ ÷ ፲፫፡፡) እንግዲህ፤ ‹‹መርጫታለኹና አድርባታለኹ፤›› ሲል ለመሰከረላት አምላክን ለወለደች የተስፋችን መዳረሻ÷ ፍጻሜ÷ የድኅነታችን ምክንያት ለኾነችው ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ክርስቲያን ወንጌል በሚነበብበት÷ አምላክን የመውለዷ ምስክርነት በሚሰጥበት ቦታ ኹሉ ልናስባት ልናከብራት ይገባል፡፡ እኛ ስሟን ብናከብር÷ መታሰቢያዋን ብናደርግ እንጠቀምበታለን እንጂ ለእርሷ የምንጨምርላት ክብር የለም፤ ባናደርግም የምናጎድልባት ነገር የለም፡፡ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ እናቱ እንድትኾን በመምረጥ ከፍጥረት ኹሉ አልቋታል፤ አክብሯታልና፡፡ ስለዚህም፤ ‹‹ባልንጀሮቿን ላንተ ይወስዱልኻል፡፡›› ‹‹በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ፡፡›› ‹‹ለምድር ኹሉ አለቆች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፡፡›› ‹‹ለዘላለም ስምሽን ይጠራሉ፡፡›› ‹‹ጽዮንን ክበቧት ዕቀፏትም፤ በቤቷ ውስጥም በጸሎት ተነጋገሩ፤ ልባችኁን በረድኤትዋ ላይ አሳርፉ፤ ሀብቷን በረከቷን ትካፈላላችኹ፤›› ይላልና፤ በፍቅሩ ተማርከው እርሷን መስለው በድንግልና እግዚአብሔርን ለማገልገል የቆረጡ ደናግል÷ በጸሎት በምስጋና ስሟን የሚጠሩ÷ በልጇ ቸርነት÷ በእርሷ አማላጅነት የሚታመኑ ምእመናን ኹሉ በረከቷን ይሳተፋሉ፤ ልጆቿ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ስለኾነም ኹልጊዜ፤ ‹‹ሰዓሊ ለነ ቅድስት፡፡›› ‹‹ቅድስት ሆይ ለምኝልን፤ አማልጅን፤›› እያልን በጸሎት ልንጠራት ይገባል፡፡ ይልቁንም እኛ ኢትዮጵያውያን በዚኽ ኹኔታ እጅግ በጣም ከፍ ያለ አስተሳሰብና አስተያየት ሊኖረን ያሻል፡፡ ባዕድ ባዕድ ነው፡፡ ሰው ከተባለ የወላጆቹን ክብር የማያስቀድም የለም፤ ለእርሱ የክብሩ መሠረቶች ናቸውና፡፡ አንደበታቸውን የማይገቱ ሰዎች ተላልፈው የወላጆቹን ክብር ቢነኩበት እስከ መሞት ይደርሳል፤ ይህም እንኳ ባይኾን ከዚያ ቀን ጀምሮ የወላጆቹን ክብር ከደፈሩት ሰዎች ጋራ ያለውን አንድነት ያቋርጣል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በመዝሙር ፹፮/፹፯ በተናገረው ቃል÷ ‹‹ወሕዝበ ኢትዮጵያ እለ ተወልዱ በህየ፤ እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፡፡›› ‹‹በዚያው ከተወለዱት ከኢትዮጵያ ሰዎች ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፤›› ብሏል፡፡ እንግዲህ፤ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤›› ከሚለው ቃል ጋራ፤ ‹‹ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፤›› የሚለው ቃል የኢትዮጵያውያንን ዕድል እንደሚያመለክት አያጠራጥርም፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለእመቤታችን የዐሥራት ልጆቿ ናቸው፡፡ እነርሱም ይህን ዐውቀው ክብሯን ጠብቀው ይኖራሉ፡፡
የጾመ ፍልሰታን መታሰቢያ ለመፈጸም ልጆችም ወላጆችም ይተባበራሉ፤ ጾሙ በፍትሕ ነገሥት በአንቀጽ ፲፭ ከተዘረዘሩት አጽዋም አንዱ ነው፡፡ ጾሙ ከፍቅር ጋራ የሚፈጸም ስለሆነ ልጆችም ወላጆችም የሚጾሙት በጉጉት ነው፡፡ ወላጆችም ከባድ ምክንያት ካላጋጠማቸው በስተቀር ከአልጋው ወርደው፣ ከመሬት ላይ ተኝተው ወይም ከቤታቸው ወጥተው በቤተ እግዚአብሔር ዙሪያ ማረፊያ አሰናድተው ከነሐሴ ፩ – ፲፮ ድረስ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያም በመስማት፣ በምጽዋት፣ ቅዳሴ በማስቀደስ በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ይጾሙታል፡፡
ልጆችም ረኀብ ሳይሰማቸው፣ ውኃ ጥም ሳያሸንፋቸው ከሰባት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ያሉ ወንዶችና ሴቶች ሕፃናት እየጾሙ ይቆርባሉ፤ በመጨረሻም ነሐሴ ፲፮ ቀን ወላጆች በዓሉን በሥነ ሥርዓት ሲያከብሩ ልጆችም በልዩ ሥነ ሥርዓት ያከብሩታል፡፡
‹‹አሸንዳ›› የሚባል ሣር ዓይነት ቅጠል አለ፤ ኹኔታው ቀጭን ቢኾንም ቁመቱ ረዘም ያለ ኾኖ ቅርፁ ፊላ ዓይነት ነው፤ ሲነቅሉት ሥሩ ነጭ ነው፡፡ ዛጎል ይመስላል፡፡ በልዩ አሠራር ሠርተው በቀሚሳቸው ላይ ይታጠቁታል፤ እንደ ዘርፍ ኾኖ ወደ ታች ይወርዳል፤ በሚጫወቱበት ጊዜ ዙሪያውን ሲነሣ ክንፍ ይመስላል፡፡ በዚኽ ዓይነት ሥርዓት በዓሉን ሲያከብሩ ይውላሉ፤ በተለይ በገጠር ላሉ ሴቶች ሕፃናት ቆነጃጅት ልዩ በዓላቸው ነው፡፡
Ashenda Ashendaye
አሸንዳ
ከሚባለው ሣር ዓይነት ቅጠል በልዩ አሠራር ሠርተው የሚታጠቁትና ሲጫወቱ ዙሪያውን የመነሣቱ ኹኔታም መላእክት እመቤታችንን ክንፍ ለክንፍ ገጥመው እያመሰገኑ ማሳረጋቸውን ያሳስባል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ምዕራፍ ፮ ላይ ባየው ራእይ÷ ሱራፊ መልአክ በኹለት ክንፍ ፊቱን፣ በኹለት ክንፍ እግሩን ሲሸፍን፣ ኹለት ክንፉን በግራ በቀኝ ዘርግቶ ረብቦ ይታያል የሚለውን ያመለክታል፤ በዓሉንም የአሸንድዬ በዓል ይሉታል፡፡ በእውነት፤ ‹‹ደናግልን ለንጉሥ በኋላዋ ይወስዳሉ፤›› ሲል ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ቃል ልጆች በእመቤታችን ፍቅር እየተኮተኮቱ አድገው ለእግዚአብሔር ቤተሰብ መኾናቸውን ያሳያል፡፡ በዚህ ሥርዓት ያደጉ ልጆችን እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ከእመቤታችን ፍቅር የሚለያቸው የለም፡፡

በኢትዮጵያ እመቤታችንን መውደድ በልማድ እንደ ተረት በማይታይ ዓይነት ኹኔታ ተስፋፍቶ የኖረ አይደለም፡፡ ወንድም ሴትም ቢኾኑ እንዳላቸው የእምነት መጠን በእመቤታችን ስም ጸሎት ጸልየው፣ ስእለት ተስለው፣ ምጽዋት አድርገው፣ ዝክርዋን ዘክረው፣ ስምዋን ጠርተው፣ በአማላጅነትዋ ተማፅነው ዐሳባቸው እየተፈጸመላቸው፣ የጎደለው እየሞላላቸው፣ የጠመመው እየተቃናላቸው፣ ድውያን ፈውስ በማግኘት፣ ሠራተኞች ለሥራቸው የተቃና መንገድ በማግኘት፣ መምህራን በሚያስተምሩበት፣ ቅዱሳን ገድላቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜና ምክንያት ኹሉ የእመቤታችንን ረድኤት እያገኙ ስለሔዱና ዛሬም ያው ያልተቋረጠ ስለኾነ ነው፡፡
በረድኤት ከሚያገኙት ተስፋ ሌላ በራሳቸውም ኾነ በሌላ ሰው በኩል በራእይ፣ በሕልም፣ በገሃድ እየተገለጸች የምታደርግላቸው ማጽናናት ልባቸውን የፍቅርዋ ምርኮኛ፣ የረድኤትዋ እስረኛ አድርጎት ይኖራል፡፡ ይህም ለአባቶቻችን ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ ስለ እውነት ምስክርነት ሲባል ይህ ለኹላችንም እንኳ የደረሰ ተስፋ መኾኑን ላረጋግጥላችኹ እወዳለኹ፡፡ ስለዚህ ነው ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅትና ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች ለእመቤታችን በየዓመቱ ከነሐሴ ፩ – ፲፮ ቀን የሚያደርጉትን ጾምና በዓል የበለጠ ያደርገዋል ያልኹት፡፡
በዮሐንስ ራእይ ምዕ. ፲፱ ፥ ፯-፰ ላይ፤ ‹‹የበጉ ሠርግ ደርሷልና ደስ ይበለን፤ ሴቲቱም ተዘጋጅታለች፤ እንድትለብስም ንጹሕ የብርሃን ልብስ ተሰጣት፤ ይኸውም ልብስ የቅዱሳን ክብር ነው፡፡ መጽሐፍ ወደ በጉ ሠርግ የተጠሩ ብፁዓን ናቸው፤ ይህ የእውነት ቃል የእግዚአብሔር ነውና አለኝ፤›› የሚል ተጽፏል፡፡
Aleqa Ayalew Tamiru
አለቃ አያሌው ታምሩ (፲፱፻፲፭ – ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.)
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ተሰሎንቄ በላከው መልእክቱ ምዕ. ፬ ፥ ፲፯ ላይ፤ ‹‹ጌታን ለመቀበል በደመና ወደ አየር እንነጠቃለን፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከጌታ ጋራ ለዘለዓለም እንኖራለን፤›› በማለት የገለጠው ተስፋ ለቅዱሳን በመታደሉ ዮሐንስ በራእዩ ምዕ.፳ ፥ ፱-፲፪ የገለጠው የሰው ኹሉ ትንሣኤ ከመድረሱ አስቀድሞ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የቅድስናን ክብር እንድትጎናጸፍ ልጅዋ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ፈቀደ በእናትነትዋ በመንፈስ ቅዱስ መቀደስን በቅድሚያ እንዳገኘች፤ ዛሬም÷ ኋላም ሞቶ ተነሥቶ በዐዲስ ሕይወት ከጌታ ጋራ መኖርን አግኝታለችና ይህን የሚያምን ልብ ሕያውነትዋን፣ በሕይወት መኖርዋን አምኖ፤ ‹‹በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኘሽ እናታችን፣ እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! ከልጅሽ ለምኚልኝ፤ አማልጂኝ፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መንበር ፊት በምታቀርቢው ጸሎትሽ፣ አማላጅነትሽ አስቢኝ፤›› እያለ ሊጸልይ ይገባዋል፡፡
ምንጭ፡- ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ፤ ፲፱፻፸፱ ዓ.ም.


                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...