2015 ኖቬምበር 30, ሰኞ

ግልጹ ደብዳቤ ለምን የአወዛጋቢነት ቁመና ይሰጠዋል? (የግል ምልከታ)


". . . በቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ሳይሰጣቸው እና ሳያሳውቁ በየድንኳኑና አዳራሹ ጉባኤ የሚያካሂዱ መጻሕፍት፣ መጽሔት እና ጋዜጦች የመዝሙር ጋዜጦች በቤተክርስቲያኒቱ ስም የሚያሳትሙና የሚነግዱ ሁሉ ሕገ-ወጥ ተግባር እየፈጽሙ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የራሳቸውን ዓላማና ፍላጎት እያስተላለፉ ያሉ ተቋማት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውክልና ሳይሰጣቸው ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ድርጅቶች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ ስለኾነ ይኸው ሕገ-ወጥ ተግባራቸው ወደፊት እንዳይቀጥል ለኢ.ቤ.ኤስ የቴሌቪዥን ድርጅት እና የሚድያ አገልግሎት ኅትመት ለሚሰጡ ድርጅቶች እንዲሁም ለሚመለከታቸው ሚኒስቴር መ/ቤቶች በደብዳቤ እንዲገለጽ ኾኖ ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከኾነ ግን በሕግ የተሰጣትን መብቷን ማስከበር የግድ ስለኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕግ አገልግሎት በኩል የሕግ ክትትል እንዲደረግባቸው " ሲል የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በቁጥር ፴፭/፲፬/፳፻፰ በቀን ፳፫/፪/፳፻፰ ዓ.ም. ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በተጻፈ ደብዳቤ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
ይኽንን ደብዳቤ ተከትሎ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ድርጅት በሚል አድራሻ ". . . ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሳይሰጣቸውና በቀጥታ ከኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር እየተካሄደ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት ሊታረም የሚገባ ድርጊት እንደመኾኑ መጠን ቤተ ክርስቲያናችን በሕገ መንግሥቱ የተሰጣትን መብት በመጋፋት በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ ሚድያዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የራሳቸውን ዓላማና ፍላጎት እያስተላለፉ ያሉ ተቋማት እና ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ድርጅቶች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ እና እውቅና ያልተሰጣቸው በመኾኑ ይኸው ሕገ-ወጥ ተግባራቸውን እንዳይቀጥሉ በጥብቅ እያሳሰብን ከአሁን በኋላ ግን ከቤተ ክርስቲያኗ ፈቃድ ሳይሰጣቸው እንደካሁን ቀደም ወደፊት እንዳይቀጥል የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያው ፕሮግራማቸውን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ከኾነ ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበር ሲባል የቴሌቪዥን ድርጅት በሕግ የምንጠይቅ መኾናችንን እየገለጽን. . ." በማለት በቁጥር ፰፻፷፭/ ፳፯፻፹፱/፳፻፷ በቀን ፯/፫/፳፻፷ ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ እገዳ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
በእነዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ደብዳቤዎች ውስጥ እገዳ የተጣለባቸው እነማን ናቸው? የሚለው አወዛጋቢ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ "ሕገ-ወጥ" የሚለው ቃል ሊቀጸል የሚገባው ለእነማን ነው? ከእነዚህ ጋር ማኅበረ ቅዱሳን ሊደመር ይችላልን? ቀድሞውኑስ ለጊዜው የታወቁትን እና እንዲታገዱ የተፈለጉትን በስም ጠቅሶ ወደፊት ሊነሱ የሚችሉትን ደግሞ በጥቅሉ "ፈቃድ የሌላቸው" ማለት አይቻልም ነበርን?
በእርግጥ እንደ ኢ.ቢ.ኤስ. ላሉ ሦስተኛ ወገኖች የተጻፈው መልእክት ተጨማሪ ማብራሪያ ሊፈልግ እንደሚችል ማሰብ አይከብድም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እገዳው ተግባራዊ እንዲኾን ለጻፈው አካል ደግሞ ሙሉ በሙሉ ስለእነማን እንደተጻፈ ለመናገር መደናገር አይጠበቅም፡፡ ደብዳቤው እጁ የገባው የቴሌቪዥን አሠራጭ እነማንን እንደሚመለከት ለማወቅ ግርታ እንደተፈጠረበት ጠቅሶ እስኪታወቅ ድረስ ሥርጭቱን ለማቋረጥ መገደዱን አሳውቋል፡፡ በዚህ ጊዜ ወይ ሁሉንም በቤተ ክርስቲያን ስም መርሐግብር የሚያስተላልፉትን አለበለዚያም እገሌና እገሌ ብሎ መናገር መቻል ያለበት ለእኔ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ነው፡፡
ለዚህ ማብራሪያ የተጠየቀው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግን ጉዳዩን ወደ ቋሚ ሲኖዶስ እንደመራው ታውቋል፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ መነሣት ያለበት እዚህ ላይ ነው፡፡ የሕግ ጥያቄ ተነሥቶ ቢኾን ሕግ ተርጓሚ ወደኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ መምራቱ ምንም የማያሻማ ጉዳይ በኾነ፡፡ ነገር ግን ማንነትን የማጣራት ጥያቄ እንጂ የተነሣው የሕግ ጥያቄ አይደለም፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ በወጣው ደብዳቤ ላይ "ማኅበራት" የሚል ቃል ስላለ ብቻ ሕጋዊ እና ሕገ ወጥ ማኅበራትን በጅምላ እና በአንድ መነጽር መመልከት አይቻልም፡፡
አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ የሚባለው ብኂል ተፈጻሚ የኾነ ይመስላል፡፡ "ማኅበራት" የሚለው ቃል ስላለ ብቻ ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት አብሮ ተጨፍልቆ ሊተረጎም ይችላል? ማኅበረ ቅዱሳን ሕገ ወጥ በሚለው ዘርፍ ፈጽሞ ሊፈረጅ የማይችል እንደኾነ ለመናገር ለእኔ ጥያቄው ከተነሣባት ቅጽበት አልፎ ሊውል ሊያድር መቻሉ አነጋጋሪ ኾኖብኛል፡፡ እንዲህ ለማለት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉኝና፡፡
አንደኛ፡- ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የተዋቀረ ሕጋዊ አካል ስለኾነ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በአንድ መምሪያ ወይም ሀገረ ስብከት ወይንም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያን ላዕላዊ መዋቅር በኾነው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ የተቋቋመ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የተዋቀሩት የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ልማትና ተራድኦ ኮሚሽንን፣ የኪራይ ቤቶችን አስተዳደር፣ የሕጻናትና ቤተ ሰብ መምሪያን፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ከ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ተሰጥቶት በሕጋዊነት ተዋቅሮ እየሠራ ያለ ማኅበር ነው፡፡ ከዚያም በፊት ቢኾን በተለይ ከ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ጀምሮ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና በአበው ሊቃነ ጳጳሳት እስከ ፓትርያርኩ ድረስ ዕውቅና አግኝቶ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ መኾኑ ሊዘነጋ አይችልም፡፡
ይልቁንም ብዙ ጥናት ሲደረግበት ከቆየ በኋላ የማኅበሩ ደንብ በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ጸድቆ በሥራ ላይ የተሰየመ አንድ የእናት ቤተ ክርስቲያን ደጋፊ አካል ኾኖ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በየትኛውም መሥፈርት ይህንን አካል ሕገወጥ የሚል ያልተገባ ቃል መግለጥ አመክንዮአዊ አይኾንም፡፡ ከፍ አድርገን እንመልከተው ከተባለ ማኅበሩን በዚህ ጎራ መሰየም ቅዱስ ሲኖዶስን ከመዝለፍ ጋር ይመሳሰላል፡፡
ስለኾነም የተጻፈው ደብዳቤ በምንም ምክንያት ማኅበረ ቅዱሳንን እንደማይመለከት መናገር በልብ የታሰብን በአንደበት እስከመናገር ድረስ ካለው የጊዜ ክፍተት በላይ ሊውል ሊያድር የሚችል አልነበረም፡፡ ጅብን ሲወጉ አህያን ይጠጉ ዓይነት እንዳይኾን ስጋት አለኝ፡፡ ሕገወጥ የኾኑትን ለመቅጣት ሕጋዊውን ማስደንበር ለምን አስፈለገ?
ሁለተኛ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ከተፈቀደለት መስመር አፈንግጦ ከኾነ በውስጥ ደብዳቤ ሊገሰጽ የሚገባው በመኾኑ
ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እጅግ በርካታ የኾኑ የደብዳቤ ልውውጦች ከፓትርያርክ ጽ/ቤት እስከ አኅጉረ ስብከት ብሎም እስከ ወረዳ ቤተ ክህነት ሲደረጉ ኖረዋል፡፡ አሁንም በዚያው መልክ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ ሲያለማ እንደተመሰገነው ሁሉ ሲያጠፋም ሊገሠጽ ይገባዋል፡፡ ስለኾነም ጥፋት በፈጸመባቸው ጊዜያት ተግሣጽ ሲሰጠው የኖረ ማኅበር ነው፡፡ ሳያስፈቅድ የቴሌቪዥን መርሐግብር ሲያካሂድ ከተገኘም እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን አካል በሚመለከተው ክፍል ተገቢው እርምጃ ሊወሰድበት የሚችል አካል ነው፡፡ ስለዚህ ለራስ አካል በሦስተኛ ወገን በኩል ትእዛዝ ይተላለፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ እናም ደብዳቤው ማኅበሩን በጭራሽ አይመለከተውም ለማለት አናመነታም፡፡
አሁንም በውስጥ ደብዳቤ ለጊዜው ማጣራት አስፈላጊ ስለኾነ ሥርጭቱን አቁም ቢባል በጸጋ ተቀብሎ ለማስተናገድ ችግር የሌለበት ማኅበር ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ማኅበሩን የማይመለከት ስለኾነ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ይኽኛውን መንገድ እንዳልመረጠ መረዳት ይቻላል፡፡ ሌሎቹ ግን ምንም ዓይነት ሕጋዊ የሚባል ግንኙነት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር ስለሌላቸው የተጻፈው ደብዳቤ በቀጥታ እነርሱን እንደሚመለከት አያወላዳም፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከእነ መፈጠራቸውም ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት እንዳላገኘባቸው ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በጉልበት ወይንም በማን አለብኝነት የቅደስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ስም ይጠቀማሉ፡፡ እነርሱን በተመለከተ ውሣኔው ከማርፈዱ በስተቀር ምንም እንከን የለበትም፡፡
ዘገባ እያቀረበ እና እያስጸደቀ፣ ሂሳቡን እያስመረመረ፣ ትእዛዝ እና መመሪያ እየተቀበለ የእናት ቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ ሰንሰለት ጠብቆ እየሠራ የሚገኝን ማኅበር አድራሻ ከሌላቸው አካላት ጋር መፈረጅ እንዳይመስልም ደጋግሞ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በየአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በየአሕጉረ ስብከቱ ዘገባ ተካትቶ ሥራው የሚነገርለትን ማኅበር ከእነ እገሌ ጋር ጨፍልቆ ማሰብ አይመጥነውም፡፡
ሦስተኛ፡- ማኅበሩ ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ዘርፎች እንዲያስተላልፍ የተፈቀደለት መኾኑ
ቀደም ሲል በጠቀስነው በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. በጸደቀው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ላይ በአንቀጽ ፬ ላይ የማኅበሩ ዓላማና ተግባር በሚለው ርእስ ሥር በቁጥር ፮ ላይ ". . . ትምህርተ ወንጌል በተለያዩ ዘዴዎች በመጽሔቶች፣ በጋዜጦች፣ በበራሪ ጽሑፎች፣ በካሴቶች፣ በኢንተርኔት፣ በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ እና በመሳሰሉት እንዲስፋፋ ማድረግ . . ." የሚል ይገኛል፡፡
ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ኾነ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የወጡት ደብዳቤዎች በቀጥታ የሚመለከቱት ፈቃድ ያልተሰጣቸውን ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱትን መኾኑ ግልጽ ሲኾን ማኅበረ ቅዱሳን ግን በማያሻማ ሁኔታ በማንኛውም የዘመኑ ጥበብ (ቴክኖሎጂ) በሚፈቅደው መንገድ ትምህርተ ወንጌልን ለማሠራጨት ፈቃድ የተሰጠው ገና በማለዳ ነው፡፡ በዚሁም መሠረት ላለፉት ፳፫ ዓመታት በተጠቀሱት መንገዶች ሁሉ ቃለ ወንጌልን ሲያሠራጭ ቆይቷል፡፡ አሁን ምንም የተለየ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ስለዚህ ደብዳቤው በየትኛውም መስፈርት ማኅበረ ቅዱሳንን ሊያካትት እንደማይችል እርግጠኛ መኾን ይገባል፡፡
በደንቡ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ትምህርተ ወንጌልን ለማስፋፋት ተፈቅዶለታል፡፡ ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ የሚለው ብዙ ዘርፎችን የሚያካትት ሲኾን ከእነዚህም መካከል አንደኛው የቴሌቪዥን ሥርጭት ይገኝበታል፡፡ ስለዚህ የፈቃድን ጉዳይ በማኅበሩ ላይ ማንሣት ተገቢ አይኾንም፡፡
ይሁን እንጂ ደብዳቤው የተጻፈለት አካል ጥያቄውን ማንሣቱ ስህተት አለበት ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እነዚህን ከላይ የተነሡትን መሠረታዊ ነጥቦች ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ፈጣን ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ጀምበር እስክትጠልቅ የሚያቆይ ምንም ዓይነት ብዥታ ወይንም ግርታ ሊፈጠርበት በማይችለው ጉዳይ ላይ ውሎ ማደሩ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነውና አሁንም ሌሎች ተጨማሪ ቀናት እንዳይባክኑ ቢደረግ ሠናይ ነው፡፡
የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ በዚህች አጋጣሚ ሰርጎ ለመግባት በር የሚከፈትላቸው አካላት መኖራቸው ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ክፍተቱን እንደ በጎ አጋጣሚ በመውሰድ በቴሌቪዥን ጣቢያው ለመጠቀም በርካታ ተቃራኒ አካላት ማሰፍሰፋቸው እየተሰማ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው የቤተ ክርስቲያን ጠላት ተብሎ የተወገዘው "የከሣቴ ብርሃን" ሐራጥቃ ተሐድሶ ይገኝበታል፡፡ ከእርሱም ባሻገር ከነባሮቹ በቤተ ክርስቲያን ነጋዴዎችም በኩል ሌላ የፍቀዱልን ውስጣዊ ግፊት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ስለኾነም፡-
፩. የማጣራቱ ጉዳይ ቶሎ እልባት አለማግኘቱ ዕድሉን ለሌሎች በሰፊው መክፈት ይኾናልና በፍጥነት ውሣኔ ቢሰጠው እና ማኅበሩ ወደጀመረው አገልግሎት እንዲቀጥል ቢደረግ፡፡
፪. ግርግሩን ምክንያት በማድረግ በደብዳቤው የታገዱት ሁለት አካላት ፈቃድ እንዲሰጣቸው አንዳንድ ሰዎች ሀሳብ እያቀረቡ እንደኾነ መሰማቱ ከፍተኛ ተቃውሞ እያስነሳ ይገኛል፡፡ ለማኅበረ ቅዱሳን በመፍቀድ ሰበብ ሌሎችም የዚህ ጽዋ ተቃማሽ እንዲኾኑ ለማድረግ ያደቡ ሰዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ይኽ ከተደረገ ግን ማጣፊያ የሚያጥረው ስህተት ይኾናል፡፡ ስለዚህ ደግመው ደጋግመው አባቶች እዲያስቡበት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ከሚደረግ የማኅበረ ቅዱሳንም አገልግሎት ቢዘገይ እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቱም ለእነዚያ ሰዎች ሙሉ ዕውቅና ከመስጠት የማይተናነስ ድርጊት ስለሚኾን፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ ጊዜ በኾነች ሰበዝ ልክ የተሰፋችን አለላ ነጥሎ ለማውጣት ስንቸገር ዐውቃለሁና፡፡
፫. በተጻፉት ደብዳቤዎች ውስጥ "ሕገ-ወጥ" የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ሲጠቀስ እንመለከታለን፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ኾነ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እነዚህን ደብዳቤዎች ሲጽፉ ሕገወጥ የኾኑ አካላት መኖራቸውን ያረጋግጣል፡፡ እነዚህ ሕገወጥ እየተባሉ የተጠሩት አካላት አሁን ተመልሰው ሕጋዊ የሚኾኑበት መንገድ ሊኖር አይችልም፡፡ ጥንትም ሕገወጥ ተብለዋልና፡፡ ማኅበራት የሚለው ቃልም የተጠቀሰው ከእነርሱ መካካል ማኅበር መሥርተናል እያሉ የሚናገሩ በመኖራቸው የተጠቀሰ ቃል እንጂ ነው፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...