2014 ሜይ 31, ቅዳሜ

‹‹የዓመቱ በጎ ሰው›› የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች

የ2006 ዓም ‹‹የዓመቱ በጎ ሰው›› ሽልማት በሰባት ዘርፎች የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ታውቀዋል፡፡ በልዩ ልዩ ዘርፎች ዕውቀትና ተሞክሮ ያላቸው፣ በሞያው ለረዥም ዘመን ያገለገሉ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ደራስያን፣ የዜማ ሰዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የባሕል ባለሞያዎች፣ የሚገኙበት 21 ዳኞች የመጨረሻዎቹን ሰባት ተሸላሚዎች ለመለየት ድምፅ እየሰጡ ነው፡፡ ዳኞቹ እርስ በርሳቸው የማይተዋወቁ ሲሆን በዘርፋቸው የራሳቸውን ድምፅ ብቻ ይሰጣሉ፡፡ የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች የሚታወቁት በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ነው፡፡
የሽልማቱ ዲዛይን የታዋቂው ሰዓሊ የእሸቱ ጥሩነህ ነው፡፡ ‹‹ጀ›› ፊደል ኢትዮጵያዊ ፊደል በመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን የሚወክል ሲሆን ‹በ› ና ‹ሰ› የሚሉ ፊደላት ተቀጣጥለውበታል፡፡ ይህም የበጎ ሰው ሽልማትን የሚገልጥ ነው፡፡ ከላይ ደግሞ የ‹ሽ› ምልክት አለው፡፡ ይህም ሽልማትነቱን ያሳያል፡፡ ከላይ ያለው የፊደሉ ቅጥያ የቁልፍ መክፈቻ ምልክት ያለው ይኼም የተሸላሚዎቹን ቁልፍ ማኅበረሰባዊ ሚና ያመለክታል፡፡ ከፊደሉ ሥር የሚገኘው ደረጃ ደግሞ ተሸላሚዎቹ ደረጃ

2014 ሜይ 24, ቅዳሜ

የአቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ፹ ቀን የቅ/ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት ይዘከራል

***
Alemayehu-atomsa-source-ERTA
ነፍስ ኄር አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ወስመ ጥምቀቱ ገብረ እግዚአብሔር
  • የቀድሞው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ወስመ ጥምቀቱ ገብረ እግዚአብሔር የ፹ ቀን መታሰቢያ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በዛሬው ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከናወናል፡፡
  • በፀረ ሙስና አቋማቸው የሚታወቁት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ወስመ ጥምቀቱ ገብረ እግዚአብሔር፣ በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንደተናፈሰው፣ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት ተከታይ አልነበሩም፡፡
  • በኦሮሚያ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሕግ ባለሞያና በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት ግምቢ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት አባልና የአገልግሎቱ ፍሬ የኾኑት ባለቤታቸው ወ/ሮ ፀሐይ በንቲ እንዲሁም ቤተሰዎቻቸው ብፁዕ አቡነ ኄኖክ ኖላዊ ኄር ኾነው የሚመክሯቸው፣ በቅዱሳን ወዳጅነታቸውና በጽኑ ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ምግባራቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡
  • የዐደባባይ ሰዎችንና የፖሊቲካ ባለሥልጣናትን ፕሮቴስታንታዊ በማድረግና ፕሮቴስታንታዊ ናቸው በሚል ፕሮቴስታንታዊነት ማስፋፋት፣ በኵላዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ በፈጠራ ታሪክ የሚገፋ ጎሳዊ ጥላቻን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን ለአደጋ ለማጋለጥ አድርባይ ፖሊቲከኞችና ጎጠኞች በስፋት የተያያዙት የብተና ፕሮጀክት ነው፡፡
  • ከነፍስ ኄር አቶ ዓለማየሁ የፖሊቲካ አቋም ጋራ ፍቅር ባይኖረንም በዚህ መንፈስ በሐዋርያዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሰነዘረውን የአድርባዮችና ጎጠኞች ሤራና ስልት ማጋለጥ ግን ኦርቶዶክሳዊነታችን ግድ ይለናል፡፡
  • ሐራዊ ምንጮች እንደተረጋገጠው፣ ነፍስ ኄር አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ በሓላፊነት በሠሩባቸው አካባቢዎች ኹሉ በአጥቢያቸው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤያት በአባልነት ተመዝግበው አስተዋፅኦ በማድረግ የምእመንነት ግዴታቸውን የተወጡ ኦርቶዶክሳዊ ነበሩ፡፡
  • በአዲስ አበባ የመካኒሳ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አባል የነበሩት የቅዱሳን ወዳጅ አቶ ዓለማየሁ፣ በስፋት ከሚነገረው መመረዝ ጋራ በተያያዘ በታመሙበት ወቅት በጥያቄአቸው መሠረት የደብረ ሊባኖስ ገዳም አበው መነኰሳት በመኖርያ ቤታቸው እየተገኙ ጸሎት ያደርጉላቸው፣ ጠበልም ያጠምቋቸው ነበር፡፡
  • ሥርዓተ ቀብራቸው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መከናወኑ መንግሥታዊ የቀብር ሥርዓትን ለማሳመር ሳይሆን በሃይማኖታቸው ኦርቶዶክሳዊ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ስለኾኑ ነው!!

2014 ሜይ 22, ሐሙስግንቦት 12 ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ

                                                                                     በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ

>+"+ እንኩዋን ለዓለም ሁሉ መምሕር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅና ለኢትዮዽያውያኑ ቅዱሳን ተክለ ሃይማኖት ወክርስቶስ ሠምራ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

=>ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው?

=>ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::


2014 ሜይ 19, ሰኞ

ግንቦት 11 ቅዱስ ያሬድ ካህን


  
            በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ
"+ እንኩዋን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ የዕረፍት (የመሰወር) በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

=>ቅዱስ ያሬድ:- ከእግዚአብሔር ያገኘነው አባታችን: ክብራችን: ሞገሳችን ነውና በምን እንመስለዋለን? አንደበቱ ጣፋጭ (ጥዑም): ልቡናው የቅድስና ማሕደር: ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ ነው:: እስከ አርያም ተነጥቆ የማይፈጸም ምሥጢርን የተመገበ ማን እንደርሱ!

+ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት:- "ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ: ሙሉ አካሏ ነው"=>የሊቁ ዜና ሕይወት በጥቂቱ:-
+ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ505 ዓ/ም አክሱም አካባቢ ሲሆን እናቱ ክርስቲና (ታኡክልያ) አባቱ ደግሞ ይስሐቅ (አብድዩ) ይባላሉ:: ሊቁ በሕጻንነቱ ምሥጢር (ትምሕርት) አልገባው ብሎ ይቸገር ነበር:: ትምሕርት እንቢ ያለው ሰነፍ ስለ ነበር አይደለም:: በጥበበ እግዚአብሔር እንጂ::

-ምን ትምሕርት ባይገባው ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: ልቡናው ደግሞ በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር የታሠረ ነበር:: አንድ ቀን ግን መምሕሩ የነገሩት ቀለም አልያዝሕ አለው:: ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ:: ዱላው በጣም ስለተሰማው ቅዱሱ ከመምሕሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው:: ትሏ 6 ጊዜ ወድቃ በ7ኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና:: ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምሕሩ ተመልሶ: ይቅርታ ጠይቆ ትምሕርት ጀመረ::

-ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ:: እግዚአብሔር ደግሞ በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው:: ካህኑ ያሬድ እንዲያ አልገባህ ያለው ምስጢር ተገልጦለት በጥቂት ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ወሰነ::በምሥጢር ባሕርም ይዋኝ ጀመር::

-ያን ጊዜ ሰማያዊ ዜማ አልተገለጠም ነበርና በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት:: 3 መላእክት በወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት:: ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት: ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት:: ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር: ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ:: ይሕንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት::

-ሊቁ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ተመስጦ አክሱም ጽዮን ውስጥ በሃሌታ አመሰገነ:: ሕዝቡና ንጉሡም ከጣዕሙ የተነሳ አደነቁ:: ቅዱስ ያሬድ ለተወሰነ ጊዜ በአክሱምና ደብረ ዳሞ ሲያገለግል ቆይቶ: ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ብሎ ለእመቤታችን አንቀጸ ብርሃንን ደርሶላት ከሃገሩ ወጣ::

-ቅዱስ ያሬድ በቀሪ የሕይወቱ ዘመናት:-
1."5" ያሕል መጻሕፍትን ጽፏል
2.በጣና ቂርቆስ: በዙር አባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል
3.በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሃ መላእክትና በተባሕትዎ ኑሯል
-በ576 ዓ/ም በተወለደ በ71 ዓመቱ በዚህች ቀን ተሰውሯል::

-አባቶቻችን:-
-ጥዑመ ልሳን
-ንሕብ
-ሊቀ ሊቃውንት
-የሱራፌል አምሳያ
-የቤተ ክርስቲያን እንዚራ
-ካህነ ስብሐት
-መዘምር ዘበድርሳን
-ማኅሌታይ
-ልዑለ ስብከት
እያሉ ይጠሩታል::

=>የቅዱሱ ጸሎትና በረከት ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን::

=>ግንቦት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን ወማኅሌታይ
2.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
3.ክርስቲናና ይስሐቅ (የቅዱስ ያሬድ ወላጆች)
4.ቅድስት ታውክልያ እናታችን (ንግሥናን ንቃ ሰማዕት የሆነች)
5.ቅድስት ኤፎምያ ሰማዕት
6.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
7.ቅድስት አናሲማ ገዳማዊት
8.አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ
9.አባ አሴር ሰማዕት (ኢትዮዽያዊ)
10.አባ በኪሞስ ጻድቅ


=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና

=>+"+ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ:: እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ:: በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም:: እግዚአብሔር ያውቃል:: ወደ ገነት ተነጠቀ:: ሰውም ሊናገር የማይገባውን: የማይነገረውን ቃል ሰማ:: +"+ (2ቆሮ. 12:2-5)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

2014 ሜይ 16, ዓርብ

ምንኩስና

(ክፍል አንድ) በዲያቆን ኤርምያስ ነቢዩ

መነኮሰ ማለት ከዓለም የራቀ፤ መናኝ ማለት ሲሆን የተጀመረውም የአዳም ሰባተኛ ትውልድ በሆነ በሔኖክ ነው።  ይኸውም ይታወቅ ዘንድ የሔኖክ አባት ያሬድ ውሉደ እግዚአብሔር የተባሉት የሴት ልጆች በሰይጣን ወጥመድ ተይዘው፤ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ወጥተው ከደብር ቅዱ ሲወርዱ እንደ ተነሱ በሰማ ጊዜ አስጠርቶ እንዲህ ያለውን ክፉ ሥራ እንዳይሰሩ ተቆጥቷቸው እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ይነግሩናል።  እናንተ የሴት ልጆች፤ ወዮላችሁ፤ ተው፤ የአባታችሁን መሃላ አታፍርሱ።  የ እግዚአብሔርን ት ዕዛዝ የተወ፤ ያባቱን መሐላ ያፈረሰ፤ ከደብር ቅዱስ የወረደ፤ ከአዋልደ ቃየን ጋርም ኃጢአት የሠራ ተመልሶ ወደ ደብር ቅዱስ አይገባም ብሎ መክሯቸው ነበር።  እነርሱ ግን ምክሩን አቃልለው ከደብር ቅዱስ ወርደው ከቃየን ልጆች ጋር ዝሙት እየፈጸሙ ይዘፍኑ ይሳለቁ ጀመር። 
ሔኖክ በዚህ እያዘነ ከኖረ በኋላ ከተወለደ ጀምሮ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሲሆነው ከዓለም ተለይቶ በጾም ጸሎት ጸንቶ ወደ አንጻረ ገነት ሄዶ በግብረ ምንኩስና ኖሯል።  በዚያም ለስድስት ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ብሔረ ሕያዋን አርጓል።  ዘፍ 5፤24 ዕብ 11፤5።  ኤልያስም ሔኖክን አብነት አድርጎ በጾም በትኅርምትና በድንግልና ከኖረ በኋላ በሠረገላ እሳት ወደ ሰማይ አርጓል። 2ኛ ነገ 2፤11 በዚህም መዓስባንና ደናግላን በሥር ዓተ ምንኩስና ጸንተው ንጹሐን የመንፈስ ቅዱስ አርጋብ ሆነው ወደ መንግሥተ ሰማይ ማረጋቸው ከሔኖክና ከኤልያስ ምሳሌነት እንረዳለን። ሔኖክና ኤልያስ መነኮስ ማለት ከዓለም የራቀ በመሆኑ ከዓለም ርቀው የሰሩት የብቸኝነት ሥራቸው መነኮሳት ያሰኛቸዋል።
በተጨማሪም የእግዚአብሔር አገልጋይ (ካህን) ሆኖ ጠጉሩን ሳይላጭ ፤ ጥፍሩን ሳይቆረጥ፤ ጠጅ ሳይጠጣ፤ በስንዴና በወይን እያስታኮተ የኖረው ርዕሰ ባህታዊ መልከ ጼዴቅም ለመነኮሳት አብነታቸው ነው። ዘፍ 14፤ 8-23 ዕብ 7፤1-5።  ለመዓስባን ሥርዓተ ምንኩስናን የጀመረላቸው ሔኖክ ለደናግላን ደግሞ ኤልያስ ነው።  ይኸውም ለአዲስ ኪዳን ምንኩስና መሰረት ነው ማለታችን ነው።  ጌታችን ሐዋርያትንና አርድዕትን የመረጠው ከመዓስባንም ከደናግላንም ነው።  ለሁሉም እክል ሥልጣን በመስጠትም ተካክለው መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ አድርጓል።  ዮሐንስ መጥምቅም ሔኖክንና ኤልያስን አብነት በማድረግ በገዳም ተወስኖ የግመል ጸጉር ለብሶ፤ ወገቡን በጠፍር መታጠቂያ ታጥቆ፤ የማርና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ በግብረ ምንኩስና ጸንቶ ኖሯል።  ማቴ 3፤4 ሉቃ 1፤15
መናፍቃን እንደሚሉት
 ምንኩስና “ሰው ሰራሽ ጽድቅ” ሳይሆን የ እግዚአብሔር ሰዎች ገንዘብ ያደረጉት የ እግዚአብሔር ጸጋ ነው።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤቱን፤ ወንድሙንና እህቱን፤ አባቱንና እናቱን፤ ሚስቱንና ልጆቹን እርሻውንም ሁሉ ትቶ በስሜ አምኖ የተከተለኝ መቶ እጥፍ ይቀበላል። የዘለዓለም ድኅነትም ያገኛል ብሎ ስለ መ ዓረገ ምንኩስና ደገኛነት የተናገረውን ቃል በመዝለል “ምንኩስና ከአምላክ ሕግ የተለየ ከንቱ ሰው ሰራሽ ጽድቅ ነው እያሉ መሣለቅ ከወንጌል ጎዳና መውጣትን ያመለክታል።  ማቴ 19፤29
ቀጥሎም በሉቃስ ወንጌል “አንድ ሰው አቤቱ ልከተልህ እወዳለሁ” ነገር ግን አስቀድሜ የቤቴን ሰዎች እሠራ ዘንድ ፍቀድልኝ ቢለው፦ “ማንም በእጅ ዕርፍን ይዞ እያረሰ ወደ ኋላው የሚመለከት ለ እግዚአብሔር መንግስት የተዘጋጀ አይደለም” ብሎ የመለሰለት ቃል የምንኩስናን ሥር ዓት ለመሥራት መሆኑ የሚታበል አይደለም። ሉቃ 9፤28
የሰው ሃብቱ ልዩ ልዩ ስለሆነ የተቻለው በድንግልና መንኩሶ እንደ ኤልያስ እግዚአብሔርን ያገለግላል።  ያልተቻለው ደግሞ እንደ ሔኖክ ቤት ሠርቶ ሚስት አግብቶ ሕጻናትን ወልዶ ቀጥቶ አሳድጎ በዚህ ዓለም ከኖረ በኋላ ይመነኩሳል።  ይህም ሐዋርያትን አብነት አድርጎ ቤቱን፤ ንብረቱን፤ ሚስቱንና ልጆቹን ትቶ የምናኔን ሥራ ይሠራል ማለት ነው።  በዚህ ዓለም እየኖሩ እግዚአብሄርን ከምንም በላይ ደስ ያሰኙ ሰዎች አሉ።  ነገር ግን ልብ ሳይከፈል በመላ ኃይል እግዚአብሄርን ለማገልገል ምንኩስና መልካም ነው።  ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ  ኃዘን እንድትኖሩ እወዳለሁ፤ ሚስት ያላገባ ሰው በሚያስደስተው ገንዘብ እግዚአብንሔርን ያስበዋልና።  ሚስት ያገባ ግን ሚስቱን በሚያስደስታት ገንዘብ የዚህን ዓለም ንብረት ያስባል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የ እግዚአብሔርና የሰው ፈቃድ ይለያያል።  ያለው ለዚህ ነው።  1ኛ ቆሮ 7፤32-34

ከዚህ በላይ ስለ ምንኩስና መዘርዘራችን የ እግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ለማመልከት እንጂ ጥንት አዳምና ሔዋን ወንድና ሴት ሆነው መፈጠራቸውን ፤ በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወንድ አባቱንና እናቱንትቶ ከሚስቱ ጋር ይከተላል፤ ባልና ሚስት አንድ አካል ይሆናሉ።  እንዲህም ከሆነ አንድ አካል እንጂ ሁለት አካል አይባሉም።  እግዚአብሄር አንድ ያደረጋቸውን ሰው አይለያቸውም።  ከዚህስ አስቀድሞ በኦሪት የተጻፈውን አልተመለከታችሁምን?” ብሎ ማስተማሩን በመዘንጋት አይደለም። ዘፍ 3፤24 ማቴ 19፤4-6
ይቆየን...........

2014 ሜይ 7, ረቡዕ

"የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አንደበት"“የእመቤታችን ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ልብስ ለብሼው ተጐናጽፌው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው እያሉ ሲመኙ ከነበሩትና የእመቤታችን ጣዕመ ፍቅሯ ከበዛላቸው ሊቃውንት ውስጥ አንደኛው ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ሲኾን ስለፍቅሯ አርጋኖን፣ ኈኅተ ብርሃን፣ መዐዛ ቅዳሴ፣ እንዚራ ስብሐት፣ ሕይወታ ለማርያም የሚሉ መጻሕፍትን ጽፎላታል፡፡ ስለ ፍቅሯ ታላቅነት ከገለጸው ውስጥ ጥቂቶቹ
1. “ፍቅርኪ ምዉቅ ኤጴሞሰ ልብሱ ለዕሩቅ ኢይትከደኖ እደ ንፉቅ ኢይትረከብ በወርቅ እንበለ ዳእሙ በጽድቅ”
(ለተራቈተው የትከሻው ልብሱ የሚኾን ሙቀት ያለው ፍቅርሽ፤ የመናፍቅ እጅ አይጐናጸፈውም በጽድቅ ካልኾነ በቀር በወርቅ አይገኝም)
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እንደጠቀሰው የእግዚአብሔር ጸጋ የእናቱ በረከት በሃይማኖት እንጂ በወርቅ በብር በጥርጣሬ መንፈስ የሚገኝ ከዚኽ የምናረጋግጠው በዝቶ የሚሰጠው እነቅዱስ ኤፍሬም፣ እነአባ ሕርያቆስ፣ እነቅዱስ ያሬድ እንደ ምግብ ተመግበው የጠገቡት እንደ ልብስ ለብስ ለብሰው የተጐናጸፉት የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር እንደ ሲሞን ያሉ ተጠራጣሪዎች ፈጽመው የማያገኙት እንደኾነ አስረድቷል፡፡
2. “ፍቅርኪ ባዝግና ለዘየዐንቆ በትሕትና ኢይረክቦ እደ ሙስና ወልድኪ ጥዒና ዘያወረዝዎ ለርሥእና”
(በትሕትና ለሚያስረው ሰው ፍቅርሽ ዝርግፍ ወርቅ ነው፤ የጥፋት እጅም አያገኘውም፤ ልጅሽም እርግናን የሚያስጐለምሰው ጤንነት ነው)
3. “ፍቅርኪ ሰንፔር ለዘይርሕቆ ይስሕቦ መንገለ አሚን ያቀርቦ መኑ ከማኪ ምክንያተ ድኂን ዘተውሕቦ”
(ማዕድናትን የመሳብ ባሕርይ ያለው ሰንፔር ፍቅርሽ የሚርቀውን ይስበዋል፤ ወደ ሃይማኖትም ያቀርበዋል፤ የድኅነት ምክንያት የተሰጠው እንዳንቺ ያለ ማነው?)
ሊቁ የጠቀሰው የሰንፔር ደንጊያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለ12 ጊዜያት ሲጠቀስ ይኽ የከበረ ደንጊያ በእጅጉ ብሩህ ሲኾን የራቀውን ኹሉ እንደ ማግኔት ስቦ የማቅረብ ኀይል አለው፤ በተመሳሳይ መልኩ በቅድስት ድንግል ማርያም ጣዕመ ፍቅር እንደ በላዔ ሰብእ ያሉ ወደ ሃይማኖት ተስበው በምልጃዋ በልጇ ቸርነት ድነዋልና ይኽነን ተናገረ፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት የተራቀቀው ይኽ ታላቅ ሊቅ በዚኽ ክፍል ላይ ጠቅልሎ ባንድ ማዕድን በሰንፔር ብቻ መስሎ የተናገረውን ክብሯን በሰኞ የአርጋኖን ምስጋናው ላይ በብዙዎች የከበሩ ማዕድናት በመመሰል ሲተነትነው
“ኦ እግዝእትየ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘበዕብራይስጢ ማሪሃም (ሚርያም)፤ ወካዕበ መሠጠኒ ኅሊናየ ከመ አስተማስለኪ በአእባን ክቡራት…” (በዕብራይስጥ ማሪሃም (ሚርያም) በመባል የተመረጥሽ ድንግል እመቤቴ ማርያም ሆይ ዳግመኛ በከበሩ ደንጊያዎች እመስልሽ ዘንድ ልቡናዬን አነሣሣኝ፤ መረግድ በሚባል ዕንቊን አመሳስዬ እጠራሻለኊ፤ ሕብራቸውም በተራራ ላይ ካለ በረድ በሚነጣ በሄጶዴጤንና በጶዴር መስዬ እጠራሻለኊ ይኸውም ለንጽሕናሽ የሚገባ ምሳሌ ነው፡፡
የጳዝዮን ደንጊያ አንቺ ነሽ፤ የሰንፔር የሶምና የክርስቲሎቤ ደንጊያ አንቺ ነሽ ይኸውም አርአያና አምሳል ዐይንን ለሚያስደስት ብርሃናዊ ደም ግባትሽ ነው፡፡ አሜቴስጢኖስ የሚባል የማዕድን ዐይነት ደንጊያ አንቺ ነሽ፡፡ ኢያሰጲድ ሰርዲኖ ከሚባሉ ማዕድናት የተሠሩ ደንጊያ አንቺ ነሽ ይኽም አርአያና ምሳሌ ክፋት ነቀፋ ለሚያገኘው ቅድስና ጌጥ ነው፡፡ ርኲሰትን ከሚያነጻ እለመቅሊጦስ ከሚባል ማዕድን የተገኘ ደንጊያ አንቺ ነሽ የዓለሙ ኀጢአት ባንቺ ምክንያተ ድኂንነት ነጽቷልና፤ የበደሉ ዝገትም ባንቺ ምክንያተ ድኂንነት ታድሷልና፡፡
ሲጮኽ ለሚያዳምጠው የሚያስደስት የደወል ደንጊያ የቤተ መቅደስ ምርዋ አንቺ ነሽ በሕማም ጭንቀት ጊዜም ቢደውሉት ልትወልድ የምታምጥ ሴት ልቡና ይመሠጣል እስከምትወልድበትም ጊዜ ድረስ የመውለድ ሕማም አይሰማትም፤ እንዲኹም ሰማዕታት የቅድስናሽን ጣዕመ ዜና የልጅሽንም ለቤዛ ዓለም የመስቀሉን አሳዛኝ ዜና በመስማት በሰማዕትነት የሚያገኛቸውን መከራ አያውቋትም፤ የምስክርነታቸው ዋጋ የኾነውን የጽድቅ አክሊል እስከሚቀዳጁበት ድረስ፡፡ አንጥረኞች ብረቶችን የሚያቀልጡበት ብርቱ የአድማስ ደንጊያ አንቺ ነሽ፤ በወሊድ ያልተለወጠ የማኅተመ ድንግልናሽ ኀይል እንደ አድማስ ደንጊያ ጽኑ ነውና) በማለት በእጅጉ አስደናቂ የኾነ ትምህርትን የእመቤታችን ጣዕመ ውዳሴዋ የበዛለት ይኽ ሊቅ አስተምሯል፡፡
4. “ፍቅርኪ ሰከለ በልበ ጠቢባን ዘበቈለ እምአፈ ነኪር ሰሰለ መኑ ዘተሀጒለ በጸሎትኪ ዘተወከለ”
(በብልኆች ልብ የበቀለ ፍቅርሽ አፈራ ከእምነት ከተለየ ሰው አንደበትም ራቀ፤ በጸሎትሽ ከታመነ ሰው የጠፋ ማነው?)
5. “ፍቅርኪ መጽሐፍ ዘኢያነብቦ ቈላፍ ዘይሜንነኪ በጸሪፍ ኢይጸድቅ በአፍ ወያንኅሎ ነደ ሰይፍ”
(ፍቅርሽ ያልተገዘረ ሰው የማያነብበው መጽሐፍ ነው፤ በመንቀፍ የሚንቅሽ ሰውም በአንደበት አይጸድቅም፤ የሰይፍ እሳትም ያፈርሰዋል?)
6. “ፍቅርኪ ኀየለ ከመ ዘዐቢይ ፈለግ መሊኦ እስከ ድንጋግ በጊዜ ጽምዑ ኢይሰትዮ ጸዋግ”
(ፍቅርሽ እስከ ከንፈሩ መልቶ እንደሚፈስስ የታላቅ ወንዝ ፈሳሽ በረታ፤ ክፉ ሰውም በጥማቱ ጊዜ አይጠጣውም)
7. “ሐሊበ ፍቅርኪ እግዝእትየ በዝቀ ኅሊናየ ተቶስሐ እምገይበ ከናፍር ዘተቀድሐ ለብእሲ ኀጥእ ዘይመይጦ በንስሓ”
(እመቤቴ ሆይ በደለኛውን ሰው ወደ ንሥሓ የሚመልሰው ከከንፈሮች ማሰሮ የተቀዳ የፍቅርሽ ወተት በዐሳቤ ማድጋ ተጨመረ)
ይኽ ከቊ140-143 የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሯ ጣዕመ ፍቅሯ የበዛለት ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በጠቢባን ልብ ውስጥ ስለሚያፈራው ከመናፍቃን ልቡና ስለተለየው፤ በቅዱሳን ልቡና የታተመውና የተጻፈው የልቡናቸውን የክፋት ሸለፈት ባልተቈረጡት ዘንድ ግን ፈጽሞ ስለራቀው፤ በፍጹማኑ ልቡና ግን እንደ ታላቅ ወንዝ ውሃ ማዕበል በመላ ሰውነታቸው ተሰራጭቶ እንደ ውሃ የሚጐነጩትና የሚረኩበት ፍቅሯ በክፉዎች ዘንድ ግን ፈጽሞ የማይታሰብ እንደኾነ እንደ ወርቅ አንከብሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ ከገለጸ በኋላ “እመቤቴ ሆይ በደለኛውን ሰው ወደ ንሥሓ የሚመልሰው ከከንፈሮች ማሰሮ የተቀዳ የፍቅርሽ ወተት በዐሳቤ ማድጋ ተጨመረ” በማለት በርሱ ኅሊና ውስጥ የበዛ ፍቅሯን በጥልቀት ገልጾታል፡፡ ይኸውም በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ገድል ላይ እንደምናነብበው ይኽ ሊቅ ከዕለታት ባንዳቸው በእመቤታችን ሥዕል ሥር ወድቆ በሚጸልይበት ጊዜ ከእመቤታችን ሥዕል ተአምራታዊ ወተት ሲንጠባጠብ አይቶ ያንንም በቀመሰው ጊዜ ልቡ ብሩህ ኾኖለት “ኆኅተ ብርሃን” የሚል አስደናቂ የነገረ ማርያምን መጽሐፍ ጽፎላታል፡፡
ይኽ ልዩ ፍቅሯ በልቡናቸው በዝቶ እንዲያድር እንደ አባ ጊዮርጊስ የተመኙ ብዙዎች ቅዱሳን አሉ ለምሳሌ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሸክላ ሠርቶ ከሚያገኘው ገቢ ላይ ለዕለት ጒርሡ ብቻ እያስቀረ የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሯ ይጸናበት ነበርና በርሷ ስም ይመጸውት ነበር፤ እመቤታችንንም በእጅጉ ከመውደዱ የተነሣ ከሉቃስ ወንጌል “ወበሳድስን፣ ጸሎተ ማርያም” አውጥቶ በዕድሜዋ ልክ 64 64 ጊዜ እየጸለየ “የእመቤታችን ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ልብስ ለብሼው ተጐናጽፌው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው እያለ ሲመኝ ይኽነን ተምኔቱን አይታ ወደ ልጇ አሳስባ እልፍ ከአራት ሺሕ ድርሰት በመድረስ “አኀዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ” (አቤቱ የጸጋኽን ማዕበል ሞገድ ግታልኝ) አስኪል ደርሷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ልክ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም “የእመቤታችን ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ልብስ ለብሼው ተጐናጽፌው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው” እያለ ይመኝ ለነበረው ለትሑቱ ለአባ ሕርያቆስም ፍቅሯን አብዝታለት ቅዳሴ ማርያሟን እንዲደርስ ባርካዋለችና ሊቁ ከዚኽ ኹሉ በመነሣት የጣዕመ ፍቅሯን ታላቅነት በዚኽ ክፍል ላይ አስፍቶ ጻፈ፡፡
ስለዚኽ ልዩ ፍቅሯ ዳግመኛ በሰኞ የአርጋኖን መጽሐፉ ላይ “ወዘንተ ኲሎ አእሚርየ ኀሠሥኩ ኪያኪ ለረዲኦትየ ወተፈሣሕኩ በፍርቃንኪ ወበፍርቃነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልድኪ…” (ይኽነንም ኹሉ ዐውቄ ለርዳታዬ አንቺን ፈለግኊ፤ በአንቺና በልጅሽ በኢሱ ክርስቶስ ምስጋና ፈጽሜ ደስ ተሰኘኊ፤ ፍቅርሽም በሰውነቴ አዳራሽነት ፈጽሞ ተዘረጋ እጅግም ከፍ ከፍ አለ በዛም፤ እንደ ወንዝ ፈሳሽም መላኝ፤ በክረምት ወራት እንደ ግዮን ወንዝ፤ በአዝመራ ወራት እንደ ጤግሮስ ፈሳሽ፤ በእሸት ወራት እንደ ኤፍራጥስ ወንዝ፤ በእንጭጭ በጨርቋ ጊዜ እንደ ኤፌሶን ፈሳሽ፤ ጉምም በምድር ላይ እንዲጐተት ደመናም በአየር ላይ እንዲረብ ፍቅርሽ በእኔ ዘንድ ኾነ አንቺም በተድላዬ ጊዜ ሽልማት ኾንሽኝ፤ በደስታዬ ጊዜ ክብ ዘውዴ ኀቲም ቀለበቴ ነሽ፤ በሐሳቤም ኹሉ አንቺን አደንቃለኊ እንዲኽም እላለኊ፤ እግዚአብሔር የሰው ልጅ ለምትኾን ለድንግል ማርያም ምን ያኽል ጸጋና ክብርን ሰጣት) በማለት አመስግኗታል፡፡
ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ጣዕመ ፍቅሯን ያበዛችለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእኛም ፍቅሯን እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ባሕር አሸዋ ታብዛልን አሜን፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...