2014 ኤፕሪል 17, ሐሙስ

ዐርብ እና ሰዎቿ

                
                                                                                                                                                                    ዕለተ ዐርብ የፍጥረተ ዓለም መካተቻ፣ ከሳምንቱ ቀኖ
ች ውስጥ የመጨረሸዋ ቀን ናት፡፡ ዕለተ ዐርብ ጌታችን መድኀኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም መድኅን ሆኖ የተሰጠበት፣ ራሱን  መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት የመከራ ሞቱ ዕለት ናት፤ ዕለተ ዐርብ፡፡ዕለተ ዐርብ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃደ ሥጋን ጋሻ ጦር አድርጎ ከሚቃወመን ከፈቃደ ሰይጣን ያድነን ዘንድ ስለ እኛ ኃጢአት ራሱን ለሕማም፣ ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ በቀራንዮ አደባባይ ቅዱስ ሥጋውን የቆረሰበት፤ ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት የመጨረሻዋ ዕለት ናት፤ ዕለተ ዐርብ፡፡ዕለተ ዐርብ እብኖዲ፣ ታኦስ፣ ማስያስና ትሰቡጣ እየተባለ በሥጋዌው ስሞቹ የተጠራው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ዝቅ ከምድር ብቅ ብሎ በተተከለ መስቀል ተሰቅሎ በመስቀሉ 5500 ዘመን ተለያይተው፣ ተራርቀው ይኖሩ የነበሩ ሰውንና እግዚአብሔር፤ ሰውንና መላእክትን፣ ሕዝብንና አሕዛብን ማስታረቁን እና ይኽን የቤዛነት፣ የድኅነተ ዓለም ሥራውን በመስቀል ሞት መፈጸሙን ‹‹ተፈጸመ›› ብሎ ፍጻሜ የሌለውን የምስራች ያወጀበት መልካም ዐርብ /Good Friday/ ናት፤ ዕለተ ዐርብ፡፡ይህች ዕለት በ5500፤ በ34 ዓመተ ዓለም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ተፈጽማ በአማናዊትነት እስክትከበር ድረስ በትንቢት ስትነገር፣ በምሳሌነት ሰትከበር ብዙ ዘመን አሳልፋለች፡፡በትንቢት መነገሯ የተጀመረው አዳም ዕፅ በለስን በልቶ ከገነት ከወጣ በኋላ በሠዋሁት መሥዋዕት፤ ባቀረብኩት ጸሎት እድናለሁ በሚል መሪር እንባ አልቅሶ፤ ከገነት ፍሬ በደሙ ለውሶ መሥዋዕት ስላቀረበ ጌታ ‹‹አዳም አዳም›› ብሎ ጠርቶ ‹‹ይህ ዓለም በዕሩቅ ብእሲ ደም የሚድን አይምሰልህ፤ እኔ 5500 ሲፈጸም ወደ አንተ መጥቼ፣ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅዬ፣ ሥጋዬን ቆርሼ፣ ደሜን አፍስሼ አድንሃለሁ›› ብሎ ጽኑ ተስፋ በሰጠው ጊዜ ነው፡፡ የዚህም ጽኑ ተስፋ ፍጻሜ ዕለት፡- ዕለተ ዐርብ ናት፡፡ከዚህም ጋር አያይዘው ነቢያት<< ስቅልተ ትሬእያ ለሕይወትከ እስራኤል ወኢትትአመና፤ ሕይወትህ ተሰቅላ ታያታለህ፤ አንተ ግን አታምንባትም:: >>ዘዳ. 28/66 እንዲሁም <<..ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ፤ እጄንና እግሬን ቸነከሩኝ::>>መዝ. 22.16 ብለው የተናገሩት እና<< ..ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልየ፣ ወአስተዩኒ ብኀኂዐ ለጽምዕየ፤ በምግቤ ሐሞት ጨመሩበት፤ ብጠማም መጣጣ አጠጡኝ::>> መዝ. 69.21፡፡ እንዲሁም ..ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፤ ደዌያችንን ወስዶ ሕማማችንን ተሸከመ.. ኢሳ. 53/4፣ ‹‹መጠውኩ ዘባንየ ለቅሥፈት፣ ወመልትሕቴየ ለጽፍዐት ወኢሜጥኩ ገጽየ እምኃፍረተ ምራቅ፤ ጀርባዬን ለግርፋት፣ ፊቴን በጥፊ ለመመታት አሳልፌ ሰጠሁ፡፡ አፍሬ ፊቴን አልመለስኩም››ኢሳ. 50/5 ተብለው የተነገሩት ትንቢቶችም በክርስቶስ ጸዋትወ መከራ የተፈጸሙት በዕለተ ዐርብ ነው፡፡በዚህ መልኩ ስለ ዕለተ ዐርብ የተሰጠው አጭር ማብራሪያ የዕለቷን ታላቅነት ከመግለጹም ባሻገር የዕለቷን የመከራ፣ የጭንቅ፣ የምጥ ዕለት መሆኗን በሚገባ ያሰረዳል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በራሱ የቁርጥ ጊዜ እና አደርባዮች እንዲሁም የመከራ ዘመን እና የደስታ ዘመን ወዳጆች የተለዩባት ዕለት መሆኗን ያመለክታል፡፡የሰዎች እውነተኛ ማንነት የሚገለጠው፣ ከገቡት ቃል ይልቅ እስከ ሞት መታመናቸው የሚገለጠው፣ ምንደኛው ከእውነተኛው አገልጋይ ተለይቶ የሚታየው፣ ሥርዐት አክባሪው ሥርዐት ከማያከብረው የሚለየው በዕለተ ዐርብ በመከራ ጊዜ እንጂ በዕለተ ሐሙስ፣ በፋሲካ በደስታ ጊዜ አይደለም፡፡ ደስታ፣ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዝና ባለበትም ሁሉም አለ፡፡እነዚህ ባሉበት የማያረጠርጥ፣ የማያለቀልቅ፣ እጅ የማይነሳና ደጅ የማይጠና የለም፡፡ ሰው ማግኘት የሚቸግረው በዕለተ ዐርብ በመከራ ጊዜ ነው፡፡ እስቲ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሁለት ወገን ማሳያ ልጥቀስ፡፡1. ሕዝበ አይሁድ

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመስቀል ሞት ተላልፎ እስከ ሚሰጥባት ዕለተ ዐርብ ድረስ ብዙዎች ይከተሉት፤ ያደንቁት ነበር፡፡ የእነዚህ ሰዎች መከተልና አድናቆት ዕለተ ሐሙስን ተሻግሮ አርብን መዝለቅ አልቻለም፡፡ በዕለተ ዐርብ በመከራው ሰዓት ከጌታ ጋር አብረው ለመቆም አላስቻላቸውም፡፡ይህ የሰማይና ምድር ጌታ ምንም እንኳን የፈጸመው ቤዛነት እነርሱንም የዋጀ ቢሆንም ቅድመ ዐርብ ያላደረገላቸው ነገር እና ያልሆነላቸው ሁኔታ የለም፡፡ ሲራቡ ምግበ ሥጋን አበርክቶ አብልቷቸዋል፡፡ ሲታመሙ በተአምራት አድኗቸዋል፡፡ በትምህርቱ ምግበ ነፍስ ሆኗቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቤተሰብና ጎረቤት፤ ልጅና ዘመድ፣ እውነተኛ ወዳጅና ጠላት፤ ምንደኛና እውነተኛ አገልጋይ የሚለይባት ዕለተ ዐርብ የመከራ ቀን ስትደርስ ‹‹ስቀለው፣ ስቀለው›› ማለት ጀመሩ፡፡ ከጌታችን ይልቅ ልጆቻቸውን የሚገድልባቸውን፣ ንብረታቸውን የሚዘርፍባቸውን ልበ ጨካኝ የሆነውን ወንበዴ በርባንን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ /ማቴ. 27/15/ከሞት ሊያድናቸው፤ ከመከራ ነፍስ ሊታደጋቸው የመጣውን ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንዲሰቀል በአንድነት ፈረዱበት፡፡ ለምን? እነርሱ ቀድሞም ቢሆን የሐሙስ የፋሲካ ሰዎች እንጂ የዕለተ ዐርብ ሰዎች አይደሉምና፡፡ እነርሱ ቀድሞም የድሎትና የምቾት ዘመን ሰዎች እንጂ የመከራ ዘመን ወዳጆች አይደሉምና፡፡ እነርሱ ቀድሞም ቢሆን የተከተሉት ከሥጋዊ ድካማቸው ስለሚታደጋቸው እንጂ የዓላማና የቁርጥ ዘመን ሰዎች አይደሉምና፡፡ ‹‹ክርስቶስን ስለመምሰል›› በሚል ርእስ የታተመው መጽሐፍ <<ዛሬ ለክርስቶስ የሰማያዊ መንግሥቱ ወዳጆች ብዙ አሉት፡፡ ነገር ግን የመስቀሉ ተሸካሚዎች ጥቂት ናቸው፡፡ የመጽናናት ወዳጆች ብዙ አሉት፤ የመከራ ወዳጆች ግን ጥቂት ናቸው>> ይላል፡፡በዚህ በያዝነው ክፍለ ዘመንም ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት ቅድስት ቤተክርስቲያን ራሷ ክርስቶስ የገጠመውን ዓይነት መከራ እየገጠማት ነው፡፡ ዘመኑም ዕለተ ዐርብ፤ ሰዎቿም ሕዝበ አይሁድ የሆኑባት ይመስላል፡፡ ብዙዎች ዐውደ ምሕረቷንና ደጀ ሰላሟን ተጠቅመው ክብርን አግኝተዋል፤ ዝናውን አትርፈዋል፤ ሀብቱን አግበስብሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደሆነችላቸው ሲሆኑ አይታዩም፡፡ ከዚያ ይልቅ በሥርዐቷ፣ በቀኖናዋና በዶግማዋ ላይ ያልተገራ አንደበታቸው ሲያላቅቁ መመልከት ተለምዷል፡፡ሁሉን ነገር ያደረገችላቸውንና ሁሉን ነገር የሆነችላቸውን እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዐቷን፣ ቀኖናዋን፣ ዶግማዋን እና የዝማሬ ለዘዋንና የስብከት ይትብሐሏን ለፕሮቴስታንት እና በፕሮቴስታንታዊነት ክህደት ለሚሰቅሏት ሰቃዮች አሳልፈው ሰጥተዋታለ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሐሣር ወደ ክብር፣ ከመርገመ ሥጋ ወደ በረከተ ሥጋ፣ ከመርገመ ነፍስ ወደ በረከተ ነፍስ ከሚያሸጋግረው መሠረተ እምነቷና ትምህርቷ ይልቅ ሕዝቡ ምርጫው የሞት መንገድ እንዲሆን የሚያስገድዱ ረበናተ አይሁድ ሆነውባታል፡፡

2. ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ

ካደረበት ፍርሃት የተነሣ የሐሙስ ሰው እንጂ የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን ከተሳናቸው መካከል ሌላኛው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፡፡ምንም እንኳን በኋላ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ተጸጽቶ የንስሐ እንባን ቢያነባም አስቀድሞ ካደረበት ፍርሃት የተነሣ ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ዐርብ ሰው ሊሆንላት አልቻለም፡፡ ቅድመ ዐርብ የነበረው ጀግንነቱ በዕለተ ዐርብ ነጠፈ፡፡

ስምዖን ጴጥሮስ ጌታውን እወድኃለሁ፣ ከአንተ አልለይም፣ ሞትህን ሞቴ ያድርገው እያለ እንዳልማለ፣ እንደ አልተገዘተ ዕለተ ዐርብ የመከራ ሰዓት ስትደርስ መሐላውን አፈረሰ፤ የራሱን ግዛት ተላለፈ፡፡በዚህ መልኩ ይምልለት፣ ይገዘትለት የነበረውን አምላኩን ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ሳለ  አንዲት አይሁድ ወደ እርሱ ቀርባ <<አንተም እኮ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርክ>>ስትለው እርሱ ግን <<የምትይውን ሰው አላውቀውምብሎ  በሁሉ ፊት ካደ፡፡ ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት ‹‹ይኽ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበር››  ስትል እርሱ ዳግመኛም ‹‹ይኽን የምትሉትን ሰው አላውቀውም፤ እንደ ማላውቀውም እውነት ነው››  ብሎ ማለ፡፡ ጥቂትም ቆይተው በዚያ ቆመው የነበሩ አይሁድ ቀርበው ጴጥሮስን ‹‹ከእርሱ ወገን እንደሆንክ አነጋገርህ ይገልጥኃል›› አሉት፡፡ በዚህን ጊዜም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ..ሰውየውን አላውቀውም.. ብሎ ይምል ጀመር፡፡ የያዘውን ጥሎ ..እንዲህ ይጣለኝ፤ የእርሱን ሞት ለእኔ ያድርገው፤ እንዲህ ያለውን ሰው አላውቅም.. በማለት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ካደው፡፡ /ማቴ. 26/69-75/እንግዲህ ይህ ዘመን ለቤተክርስቲያን ዕለተ ዐርብ ሆኖባታል፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ፍርሃት የወለደው ክህደት ብዙዎቹን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መምህራነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ ምእመናንና የማኅበራት አመራር አካላት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ሓላፊዎችና የድርጅት ሥራ አስኪያጆችን ተጠናቷቸዋል፡፡ የቅዱሳ ጴጥሮስ የክህደት ሕይወት፤ ዛሬ እነዚሁ ሰዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የካዱበት ሕይወት ነው፡፡እናት! የዚህች ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፣ሊቃውንት፣ ሰባክያን የቆሎ ትምህርት ቤት እያላቸው፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆች በትምህርት ገበታ ሳላችሁ ከአንዲቷ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደስታዋም በሐዘኗም ላለመለየት፣ መሠረተ እምነቷን፣ ሥርዐተ አምልኮዋንና ትውፊቷን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ እንዳልማላችሁ፣ እንዳልተገዘታችሁና ቃል ኪዳን እንዳልገባችሁ ሁሉ ዛሬ ዘመናዊነት፣ ማግኘት፣ ምንፍቅና፣ ራስ ወዳድነት፣ ጥቅመኝነትና ጎጠኝነት ዕለተ ዐርብ ሆኖባችሁ መሓላችሁን አፈረሳችሁ፣ ግዝታችሁን ተላለፋችሁ፣ ቃል ኪዳናችውን  ቆረጣችሁ፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱን፣ የወሮበሎችና የወንበዴዎች ዋሻ እንድትሆን ፈቀዳችሁ፡፡እናት! የዚህች ታላቅ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዐት፣ ትውፊትና ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እናሸጋግራለን ብላችሁ ማኅበር የመሠረታችሁ እና በዚሁ ማኅበር አመራር የሆናችሁ በዕድሜያችሁም ሆነ በትምህርት ደረጃችሁ ለሰማይ ለምድሩ የከበዳችሁ ፍርሃት የወለደው አጉል አርቆ አሳቢነት ዕለተ ዐርብ ሆኖባችሁ፤ የገባችሁትን ቃልኪዳን አፍርሳችሁ፤ ቤተ ክርስቲያንን ለበላተኞች አሳልፋችሁ ሰጥታችሁ የተቀመጣችሁ xYmSLÆCh#ምን) ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ የአስተዳደር በሽታዎች መድኃኒት መሆን ቢያቅታችሁ ጉልኮስ መሆን ያቅታችሁን? በዚህ ሁኔታ አሟሟች እንዳትሆኑ ያሰጋል፡፡እናት! የዚህች ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርቲያን ልጆች የሆናችሁ ምእመናን ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ሰቃዮች ጋራ እሳት እንደሞቀ ሁሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ትውፊቷንና ሥርዐተ አምልኮዋን በጥርጥር እና በክህደት ለሚሰቅሏት ሰቃልያን ቲፎዞ ሆነን ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የመደፈር፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የመተላለፍ፣ መሠረተ እምነትን የመናድ እሳት ሞቅን፡፡ እኛ ለቤተ ክርስቲያን እንዲህ ከሆንን፤ አይሁድ ለክርስቶስ ከሆኑት በምን ይለያል?ስምዖን ጴጥሮስ ከአይሁድ ጋር እሳት እንደሞቀ አልቀረም፡፡ ዘግይቶም ቢሆን የእሳቱ ሙቀት ምቾት ሆኖት የዕለተ ዐርብ ሰው ከመሆን አልገታውም፡፡ ወዲያው ዶሮ ሲጮኽ ..ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ.. ያለው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ትዝ አለው፡፡ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቀሶ አለቀሰ፡፡ ስለበደሉ ተጸጽቶ፣ የንስሐን እንባን አንብቶ በእንባው የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን ቻለ፡፡ በኋላም መንፈስ ቅዱስ ፍርሃትን ቀርፎ ስለጣለለት የማይፈራ ሆኖ ስለክርስቶስ ፍቅር ቁልቁል ተሰቅሎ የሚሞት ሆኗል፡፡በየፈርጁ ከላይ የተጠቀሳችሁ ሊቃነ ጳጳሳት፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ የየመምሪያ ሓላፊዎች፤ የድርጅት ሥራ አስኪያጆች፣ የማኅበራት አመራር አባላትና ምእመናንን ትላንት የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን ካልቻለን ዛሬ መሆንን እንችላለን፡፡ ከሰዓታት በፊት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የዕለተ ዐርብ ሰው ካልሆንን ከሰዓታት በኋላ መሆን እንችላለን፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት የሚነግረን ይኽንኑ ነው፡፡ እርሱ ከሰዓታት በፊት ለጌታው የዕለተ አርብ ሰው መሆን አቅቶት ጌታውን ሦስት ጊዜ ካደው፡፡ ከሰዓታት በኋላ አምላኩ ክርስቶስ የተናገረው ቃል ትዝ ሲለው ግን የንስሓን እንባ አንብቶ መላ ሕይወቱን በእርሱ ዐለትነት ለተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን የዕለተ ዐርብ ሰው ሆኖ በኔሮን አደባበይ ሰማዕት ሆነ፡፡ከእኛም የሚጠበቀው ይኽው ነው፡፡ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የመድፈር፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የመተላለፍና መሠረተ እምነትን የመናድ እሳት ከሚሞቁ ውሉደ አይሁድ ተለይቶ ቤተ ክርቲያን በየጊዜው ያለችንና የነገረችን ቃል እና ሰማያዊ እናትነቷን ማስተወስ ነው፡፡ ይኼኔ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የዕለተ ዐርብ ሰዎች እንሆንላታለን፡፡ ስለ እርሷ መሠረተ እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮ፣ ትውፊትና ታሪክ ቀጣይነት ሰማዕት ለመሆን እንዘጋጃለን፡፡3. ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ

በቅዱስ መጽሐፍ በዚህ መልኩ የዕለተ ዐርብ ሰዎች መሆን አቅቷቸው በየሁኔታው የተገራገጩ ሰዎች የመኖራቸው ያህል መከራው ከጀመሩት ጉዞ ሳያገራግጫቸውና እየሆነ ባለው ሳይሸማቀቁ የዕለተ ዐርብ ሰዎች መሆን የቻሉም አሉ፡፡ከእነዚህ ጥቂት የዕለተ ዐርብ ሰዎች መካከል አንዱ ፍቁረ እግዚእ፣ ወልደ ነጎድጓድ፣ ነባቤ መለኮት፣ አቡቀለምሲስ፣ ቁጽረ ገጽ በመባል የሚታወቀው እና በሕይወቱና በኑሮው ጌታን ለመምሰል ይጥር የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ቅዱስ ዮሐንስ የምሴተ ሐሙስ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ የዕለተ ፋሲካም ሰው ብቻም አልነበረም፡፡ እርሱ የዕለተ ዐርብ ሰውም እንጂ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሁሉም ጌታን ጥለው ሲሔዱ የአይሁድን ዛቻ ሳይፈራ፣ ክርስቶስን በመከተሉ ሊያደርሱበት የሚችሉትን መከራ ሥጋ ሳይሰቀቅ ከእናቱ ድንግል ማርያምና ከጥቂት ቆራጥ ሴቶች ጋራ በእግረ መስቀሉ ሥር በመገኘት የዕለተ ዐርብ ሰው የሆነ ብቸኛ ሐዋርያ ነው፡፡

የክርስትና ሕይወት የመስቀል ጉዞ ነው፡፡ የመስቀለ ጉዞ ደግሞ የሐሙስ ሰው እና የፋሲካ ሰው መሆንን ብቻ ሳይሆን እንደ ቅዱስ ዮሐንስ በጥብዓት የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን የሚጠይቅ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ የአይሁድን ዛቻ ሳይፈራ እና መከራ ሳይሰቀቅ ከጌታው ጋራ እንደቆመ ሁሉ የዚህች ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፤ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ዘማርያን እና ምእመናን ነን የምንል ሁሉ ..ለቤተ ክህነቱ ገዥ.. መደቦች ዛቻና ማስፈራሪያ፤ ለተሐድሶ መናፍቃን ቀረርቶ ሳንበገር በቆራጥነት ለቤተ ክርስቲያን በመከራዋ ዕለት የዕለተ ዐርብ ሰው መሆን ይጠበቅብናል፡፡ቅዱስ የሐንስ የዕለተ ዐርብ ሰው በመሆኑ የተገኘው ቀራንዮ እንጂ የክርስቶስ ከሳሾች በሆኑት በአይሁድ ሸንጎ፣ በጲላጦስ ጓዳ አይደለም፡፡ የዕለተ ዐርብ ሰው ቀራንዮ በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለቅዳሴ፣ ለማኅሌት፣ ለሰዓታት ጉባኤ ዘርግቶ ለማስተማርና ለመማር  እና ስለ ሰላሟ፣ ስለ ዶግማዋ፣ ቀኖናዋና ትውፊቷ መጠበቅ ለመወያየት ይገኛል እንጂ እርሷነቷን ለማጥፋት በሚጎነጉኑ የአድማና የሴራ ሸንጎ አይገኝም፡፡ በውሉዳነ ጲላጦስ ጓዳም አይርመጠመጥም፡፡ የእርሷ ጲላጦስ እና ውሉደ ጲላጦስ ማንና ምን እንደሆነ እናውቃለንና፡፡የዕለተ ዐርብ ሰው የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ የጌታን መከራ ሞት የራሱ መከራ ሞት፤ የጌታን ሕማም የራሱ ሕማም፤ የጌታን በዘንግ መመታትና በጥፊ ፊቱን መጸፋቱን የራሱ መመታትና መጸፋት፤ የጌታን 6666 ጊዜ መገረፍ የራሱ መገረፍ፤ የጌታን በጎዳና መውደቅ መነሣት የራሱ መውደቅ መነሣት፤ የጌታን የእጆቹ መጋፊያና መጋፊያ እስኪጋጠም ወደ ኋላ መታሰር የራሱ መታሰር፤ ከምሰሶ ወደ ምሰሶ መንገላታቱን የራሱ መንገላታት፣ በቅንዋተ መስቀል መቸንከሩን የራሱ መቸንከር አድርጎ በመውሰዱ ከጌታው ከመከራ ሞቱ አልተለየም፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያንም መከራዋን መከራው፤ ስደቷን ስደቱ፤ ውድቀቷን ውድቀቱ፤ ውድመቷን ውድመቱ፤ ውርደቷን ውርደቱ ፤ ጭንቀቷን ጭንቀቱ አድርጎ የሚያስብላት የዕለተ አርብ የመከራ ዘመን ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ ሰንበት ተማሪና ምእመን ዛሬ ያስፈልጓታል፡፡ እርሷ ያጣችው ይኽንን ነውና፡፡ መከራም እየተቀበለች ያለችው በእነዚሁ ነውና፡፡

እኛ ለዚህች ታላቅ ቤተክርስቲያን  የደስታ ዘመን፣ የፍስሐ ዘመን እና የደመወዝና የአበል ሰዎች ብቻ ከሆንላት ከአሕዛብ ከመናፈቃን በምን ተለየንላት? እነዚህ ሰዎች ከሰሙነ ሕማማቱ፣ ከጾሙና ከስግደቱ የሉበትም ከፋሲካው፣ ከደስታው ግን አሉበት፡፡ እኛ የዚህች ቤተ ክርስቲያን የደስታዋ፣ የፋሲካው ተካፋይ ብቻ ከሆንን ልጆች መሆናችን እምኑ ላይ ነው? የደስታዋ ተካፋይ መሆን የምንችለው በሕማሟም ተካፋይ ስንሆን ብቻ ነው፡፡ እኛን ከእነርሱ የሚለየንም ይኸው የዕለተ ዐርብ ሰዎች መሆናችን ነው፡፡የዕለተ ዐርብ ሰው ቀራንዮ ወጥቶ ባዶ እጁን አይመለስም፡፡ የዕለተ ዐረብ ሰው የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ የድርሻውን ለመወጣት ቀራንዮ ወጥቶ ባዶ እጁን ያለዋጋ አልተመለሰም፡፡ ከስጦታ በላይ ስጦታ፤ ከዋጋ በላይ ዋጋ የሆነች ድንግል ማርያምን ይዞ ተመልሷል፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዕለተ ዐርብ ሰዎች ከሆንላት ዋጋችንን የማናገኝበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ቁም ነገሩ የድርሻን ለመወጣት ቀራንዮ በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘወትር መገኘት ብቻ ነው፡፡ቁም ነገሩ ቢያንስ እንደቀሬናው ሰምዖን ከአይሁድ ምክር፣ ክፋት ላለመግባት መሰወር ዋጋ አለው፡፡ እርሱ ነገር ሁሉ ተፈጽሞ ሰላም ይሆናል ብሎ ከተሰወረበት ሲወጣ አይሁድ አገኙት፡፡ በክፋታቸው እና በተንኮላቸው ስላልተባበረ <<አንተም የእርሱ ወገን ነህ ››በማለት ይቀጡት ዘንድ መስቀሉን አሸከሙት፡፡ እነርሱ የቀጡት መሰላቸው እንጂ ንጹሕ ልቦናን ገንዘብ በማድረጉ የሰውን ዋጋ የማያስቀር እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ እንዲሳተፍ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ ፈቀደለት፡፡ /ማቴ. 27/32/እግዚአብሔር በዚህ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን የዕለተ አርብ ሰው ለሚሆኑላት ዋጋቸውን እንደ ሰምዖን ቀሬና አያስቀርም፡፡ ሲሰጥም ልክ እንደ ሰምዖን ቀሬና በረቂቅ ጥበብ ለጊዜው ማንም በማያስተውለው መንገድ ነው፡፡ መመለስ የሚገባው ጥያቄ ግን ስንቶቻችን ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እና ከቅጥረኞቻቸው ምክር፣ ክፋት ላለመግባት ተሰወርን?እንዲህም ተባለ እንዲያ ለእኔ ግን ዕለተ ዐርብ ይች ናት፡፡ ሰዎቿም ይኽን ይመሰላሉ፡፡ ለእኔ የአሁኗ ቤተ ክርስቲያንም ይህች ናት፡፡ የሰዎቿም ስብጥር እንዲሁ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ወዴት ታመራ ይሆን?

                                                                                                                                             መልካም በዓል፡፡ (2004ዓ.ም )

Like · ·

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...