2014 ሴፕቴምበር 8, ሰኞ

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን ጋር ያለው ልዩነት መንስኤ እና ትክክለኛ መሰረቱ

 


የዘመን መስፈሪያዎች 
እግዚአብሔር «ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ፣ ለዕለታት፣ ለዘመናትና ለዓመታት ምልክት ይሆኑ ዘንድ» / ዘፍ.1. 14- 15/ የፈጠራቸውን የፀሐይንና የጨረቃን እንቅስቃሴ መሠረት ያደረጉት መስፈሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም፤

ሀ. ዕለት-
አንድ ዕለት አንድ ቀንን /የብርሃን ክፍለ ጊዜን / እና አንድ ሌሊትን /የጨለማ ክፍለ ጊዜን/ ያካተተ ፀሐይ አንድ ጊዜ ከወጣች በኋላ ተመልሳ እስክትወጣ ድረስ ያለውን ጊዜ የያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ዕውቀታችን አንድ ዕለት ምድር በራሷ ዛቢያ አንድ ጊዜ የምትሸከረከርበት ጊዜ ነው፡፡

ለ. ውርኅ-
ወርኅ ማለት በግእዝ ጨረቃ ማለት ነው፡፡ አንድ ወርኅ የሚባለው ጊዜ ሙሉ ጨረቃ ከወጣች በኋላ ድጋሚ እስከምትወጣ ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ በአሁኑ ዕውቀታችን / በጥንቱም ጨምሮ/ ይህ ጨረቃ መሬትን አንድ ጊዜ ዙራ ለመጨረስ የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ አንድ ወር ሃያ   ዘጠኝ ተኩል ዕለታትን ይፈጃል፡፡
   
ሐ. ዓመት-
አንድ ዓመት ማለት መሬት አንድ ጊዜ በፀሐይ ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ ይህም 365 ከ1/4 / ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከሩብ/ ዕለታት ይፈጃል፡፡ይህ ከመታወቁ በፊትም ግን የዓመት ጽንሰ ሓሳብ ነበር፡፡ ፕሮፊሰር ጌታቸው ኃይሌ የፅንሰ ሐሳቡን አመጣጥ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡
ሰዎች ርዝመታቸው እኩል የሆኑ ሁለት  ሻማዎችን ሠሩና ልክ ፀሐይ ስትወጣ /ቀኑ ሲያልቅና ሌሊቱ ሲጀምር/  አንዱን ሻማ አበሩት፡፡ልክ ፀሐይ ስትወጣ እሱን አጠፋና ሌላውን / ሁለተኛውን/ ሻማ አበሩት፤ ጧት ፀሐይ እንደገና ስትወጣ / ሌሊቱ አልቆ ሌላ ቀን ሲጀምር/ ሻማውን አጠፉት፡፡ አሁን እንግዲህ ከየሻማዎቹ /ከሁለቱ ሻማዎች/ ምን ያህል እንደተቃጠለላቸው ሲያስተያዩት ከሁለቱ ሻማዎች የተቃጠለው እኩል አለመሆኑን ተመለከቱ በዚህም የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ እኩል አለመሆኑን ተረዱ፡፡

ቀደም ብለውም የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ በተለያዩ ወቅቶች የተለያየ መሆኑን ልብ ብለው ነበርና ይህንን ሙከራቸውን ሲቀጥሉ በቀኑና በሌሊቱ ርዘማኔ / በሚቃጠለው የሻማዎቹ መጠን/ መካከል ያለው ልዩነት ከወቅት ወቅት የተለያየ እንደሆነ ተመለከቱ ይህን ሙከራቸውን ሲቀጥሉ ግን በየ182 /ተኩል/ ዕለቱ ቀኑና ሌሊቱ እኩል የሚሆኑባቸው ሁለት ዕለታት በዓመት ውስጥ እንዳሉ ተገነዘቡ፡፡ እነዚህ ዕለታት አንዱ የሙቀት ወራት ከመጀመሩ በፊት የሌላው ደግሞ የቅዝቃዜው ወራት ከመጀመሩ በፊት የሚመጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት አንድ ጊዜ እኩል ሁኖ ደግሞ በዚያው ወቅት እኩል እስከሚሆን ድረስ ያለውን ጊዜ ማለትም / 182 ተኩል + 182 = 365/ ዕለት አንድ ዓመት አሉት፡፡ አሁን ባለን ግንዛቤ ምድር በራሷ ዛቢያ እንደተሽከረከረች በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች፡፡ ምድር በፀሐይ ዙሪያ የምትዞረው ወደ ጎን 23 ተኩል ዲግሪ ያህል አጋድላ ነው፡፡ ይህ የቀንና የሌሊት ርዝመት መለያየትም የሚከሰተው በዚህ ማጋደል ምክንያት ነው፡፡
እንግዲህ በአጠቃላይ ዋናዎቹ የጊዜ / የዘመን/ መስፊሪያዎች ዕለት፣ ወር እና ዓመት ናቸው፡፡ ሦስትቱም ተመላላሽ ክስተቶችን / ለምሳሌ የፀሐይን መውጣት/ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚሀ ተመላላሽ ክስተቶች አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው እስኪከሰቱ የሚፈጁት ዘመን ወይም ጊዜ  ዓውድ ይባላል፡፡ ዓውድ ማለት ዙሪያ፣ ክብ፣ እንደ ቀለበት ዙሮ የሚገጥም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዓውድ ማለት ክስተቶቹ አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው እስኪመጡ ድረስ ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡
በዚህ መሠረት ከላይ ያየናቸው ሦስት መስፈሪያዎች / ዕለት፣ ወርኀ፣ ዓመት/ ዓዕዋዳት / ዓውዶች/ የሚወጡበት ጊዜ ዓውደ ዕለት፣ ዓውደ ወርኀ፣ ዓውደ ዓመት ይባላሉ፡፡
መጀመሪያ ላይ ሰዎች እነዚህን ሦስቱን መስፈሪያዎች /ዓዕዋዳት/ /በተለይም ቀንና እና ወርን/ ለየብቻቸው ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ ከዚህን ያህል ቀን፣ ከዚህን ያህል ወር በኋላ /በፊት/ እያሉ ጊዜን ይለኩ ነበር፡፡
እነዚህ ሦስቱን በቅንብር /በቅንጅት/ ለመጠቀም ሲፈለግ ግን የዘመን አቆጣጠር ስሌት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ወር 29 ከግማሽ ቀን ነው፡፡
እንዲሁ እንዳለ ለመቁጠር ቢፈለግ የመጀመሪያው ወር ጠዋት ላይ ቢጀመር ሁለተኛው ወር ምሽት ላይ ይጀምራል፣ ሦስተኛው ደግሞ ድጋሚ ጠዋት ላይ ይጀምራል፤ ይህን ለመቅረፍ ወሩን ሙሉ  ሰላሳ ቀን ቢያደርጉት ከትክክለኛው ወር /የጨረቃ ዐውድ/ ግማሽ ቀን ይተርፋል፤ 29 ቀን ብቻ ቢያደርጉት ደግሞ ግማሸ ቀን ይጎድላል፡፡ አንድ ዓመት 365 ከሩብ ዕለታት አሉት፡፡
ዓመትን በወራት ለመቁጠር ቢፈለግ፤ ዓመቱን 12 ወር ቢያደርጉት የዓመቱ /የዕለታት ቁጥር /29.5X12=354/ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህም ከትክክለኛው ዓመት /365-354=11/ ዕለታት ያህል ያንሳል፡፡ 13 ወር ቢያደርጉት ዓመቱ /365X13=385.5/ ቀናት ይሆናል ይህም ከትክክለኛው ዓመት /383.5-365=19/ ቀናት ያህል ይበልጣል፡፡
ስለዚህ እነዚህን መስፈሪያዎች በቅንጅት ለመጠቀም ይህንን አለመጣጣም የሚፈታ ቀመር /የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት/ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የዘመን አቆጣጠሮች ተዘጋጅተዋል፡፡



የአይሁድ ዘመን አቆጣጠር

የአይሁድ ዘመን አቆጣጠር እያንዳንዳቸው 29 እና 30 ዕለታት ያሏቸው 12 ወራት አሏቸው፤
ተ.ቁ
የአይሁድ ወራት
የዕለታት ብዛት
ወራቱ በእኛ
1
ኒሳን
30
መጋቢት/ ሚያዝያ
2
ኢያር
29
ሚያዝያ/ ግንቦት
3
ሲዋን
30
ግንቦት/ ሰኔ
4
ታሙዝ
29
ሰኔ/ ሐምሌ
5
አቭ
30
ሐምሌ/ ነሐሴ
6
አሉል
29
ነሐሴ/ መስከረም
7
ኤታኒም
30
መስከረም/ ጥቅምት
8
ቡል
29/30
ጥቀምት/ ኅዳር
9
ከሴሉ
30/29
ኅዳር/ ታህሳስ
10
ጤቤት
29
ታህሳስ/ ጥር
11
ሳባጥ
30
ጥር/ የካቲት
12
አዳር 1
29
የካቲት/ መጋቢት
እነዚህ የዓመቱ 12 ወራት በአጠቃላይ 354 ያህል ብቻ ዕለታት ይኖሯቸዋል፡፡ ይህም በትክክለኛው ዓመት በ11 ዕለታት ያህል ቢያንስም አዲስ ዓመት ይጀምራሉ፡፡ ልዩነቱ በሁለት ዓመታት 22 ዕለታት፣ በሦስት ዓመት ደግሞ 33 ዕለታት ያህል ይሆናል፡፡ ስለዚህ በየሦስት ዓመቱ ከአስራ ሁለተኛው ወር ጳጉሜን በፊት አንድ ሌላ ወር ይጨምሩና ጨምረው የዓመቱን የወራት ቁጥር ዐሥራ ሦስት ያደርጉና ልዩነቱን ያስተካክሉታል፡፡

የኢትዮጵያውያንና የግብጻውያን ዘመን አቆጣጠር

የሀገራችን ኢትዮጵያ እና የጥንት ግብጻውያን /ዛሬም ድረስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትጠቀምበት/ የዘመን አቆጣጠር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለታችንም እኩል ሰላሳ ቀናት ያሏቸው 12 ወራት አሉን፡፡ እነዚህ 12 ወራት / 12X30=360/ ቀናት አሏቸው እነዚህ ቀናት በትክክለኛው ዓመት በ/365.25-360=5.25/ ቀናት ያንሳሉ፡፡ ይህንንም 5 ቀናት / በ4 ዓመት አንድ ጊዜ 6 ቀናት/ ያሏትን 13ኛ ወር በመጨመር ያስተካክሉታል፡፡ የኢትዮጵያውያን እና የግብጻውያን ወሮች ስም እንደሚከተለው ነው፡፡
ተ.ቁ
የግብጽ ወሮች
የኢትዮጵያ ወሮች
1
ቱት/ዩት
መስከረም
2
ባባ/ፓከር
ጥቅምት
3
ሀቱር
ኅዳር
4
ኪሃክ/ከያክ
ታኅሣሥ
5
ጡባ/ቶቢር
ጥር
6
አምሺር/ሜሺር
የካቲት
7
በረምሃት
መጋቢት
8
በርሙዳ
ሚያዝያ
9
በሸንስ
ግንቦት
10
ቦኩሩ
ሰኔ
11
አቢብ
ሐምሌ
12
መስሪ
ነሐሴ
13
ኒሳ/አፓጎሜኔ
ጳጉሜን
/ባሕረ ሐሳብ፣ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ፣ገጽ.65/

የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር

የኢትዮጵያ እምነታዊ ባህል የሚወረሰው በሦስት ዐይነት ጠባይ ነው። አንዱ ሕገ ልቡና ይባላል። ከመጽሐፍ በፊት የነበረ ነው። ከአበው ቃል በቃል የተወረሰ ነው። ሁለተኛው በሕገ ኦሪት ከኦሪት የተቀዳ ነው። ሦስተኛው በሕገ ወንጌል ከወንጌል የተማርነው ነው። እና በሦስት ዐይነት ጠባይ የሚመራ ነው። በዚህ ዐይነት ከወረስናቸው በዓላት ማለት በሦስቱም ጠባያት ከወረስናቸው በዓላት የየራሳቸው መልክ ያላቸው አሉ። ለምሳሌ ልደት፥ ጥምቀት፥ ዕርገት፥ ደብረ ታቦር እነዚህን የመሳሰሉት ከወንጌል የተማርናቸው ናቸው፤ በብሉይ የሉም። ፋሲካ፥ በዓለ ጰራቅሊጦስ ደግሞ ከኦሪት የተማርናቸው ናቸው። የዘመን መለወጫ በዓል ግን ከሕገ ልቡና ቃል በቃል ተምረን፥ በኦሪት የመጽሐፍ መሠረት አግኝተንለት በወንጌልም አጽንተን ይዘነው የኖርነው ሦስት የሥራ ዘመን ክፍል የተላለፈና እዚህ የደረሰ ነው። እኛ የዘመን መለወጫ ብለን በሀገራችን ባህል የምናከብረው ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር የተገኘበት፥ ብርሃን፥ ጊዜ፥ ዕለት፥ ሰዓት የተፈጠሩበት፤ ለብርሃን፥ ለጊዜ፥ ለዕለት፥ ለወር ለዓመት ጥንት መሠረት የሆነ ቀን ነው። ይህንን ሁሉ በማስገኘት እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት፥ ዓለምን በመፍጠር ከሃሊነቱን ያረጋገጠበት ቀን ነው ብለን ነው የምናከብረው። ስለዚህም ጥንተ ብርሃን፥ ጥንተ ዕለት፥ ጥንተ ጊዜ፥ ጥንተ ፍጥረት ርእሰ ዐውደ ዓመት ብለን ነው የምናከብረው። በዚህ ስያሜ በዓሉ ርእሰ ዐውደ ዓመት፥ ቅዱስ ዮሐንስ፥ የዘመን መለወጫ ብለን እናከብረዋለን።
ቅዱስ ዮሐንስ
የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል ሌላው ስሙ ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል። ቅዱስ ዮሐንስ የሚባልበትም ሁለት ጠባይ አለው። አንዱ፤ መጥምቁ ዮሐንስ በሄሮድስ አንቲጳስ ጊዜ ከጳጉሜን ቀን ጀምሮ ታስሮ ሰንብቶ በመስከረም ቀን ዐሳብ ስለ ተቆረጠበትና በመስከረም ቀን እንዲሞት ውሳኔ ስለ ተሰጠበት አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ስለ ሞተ ሊቃውንት ይህንን በዓል እሱ ራሱ ለኦሪትና ለወንጌል መገናኛ መምህር ስለ ነበረ ይህም በዓል ላለፈው ዘመን መሸኛ፥ ለሚመጣው ዘመን መቀበያ እንዲሆን ብለው በመስከረም ቀን እንዲከበር ስላደረጉ በሱ ስም ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል። በሁለተኛው ግን ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ ወንጌላዊ ዮሐንስ የተሰየመበት ስለ ሆነ በአቆጣጠርም ተራ ወደ ኋላ ተመልሶ ቢቈጠር ዓለም የተፈጠረበት ዘመን በዘመነ ዮሐንስ እንዳጋጣሚ ሆኖ ስለሚገኝ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል።

ዕንቍጣጣሽ
በዚያም ጊዜ የነበሩ ኖኅና ልጆቹ ሰማዩ በደመና በመክበዱ ምክንያት ማየ አይኅ እንደገና ይመጣ ይሆን፥ የጥፋት ውሃ እንደገና ይዘንም ይሆን እያሉ ሲደነግጡ ከርመው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ሙሉ የፀሓይ ብርሃን ስላዩ፥ ምድር በአበባ አሸብርቃ ስለ ተገለጠችና በዚህም የእግዚአብሔርን ቸርነት፥ የቃል ኪዳኑን መጽናት ስለ ተረዱ ይህንን በዓል ቀድሞ ከአባቶቻቸው እንደ ወረሱት ያው ጥንተ ብርሃን፥ ጥንተ ዓመት፥ ጥንተ ዕለት አድርገው አክብረውታል። ሲያከብሩትም እንግጫ ነቅለው፥ አበባ ጐንጕነው መጀመሪያ መሥዋዕት ይሠዉነት ከነበረው ቦታ ሄደው ለእግዚአብሔር ገጸ በረከት አቅርበው ከዚያ በኋላ ግን እርስ በርሳቸው የአበባ ስጦታ በመለዋወጥ አክብረውታል። ሲያከብሩትም ዕንቍጣጣሽ በሚል ቃል እውነት የመልካም ሞኞታቸውን ይገላለጡበት ነበር። ዕንቍጣጣሽ ማለትንም ብዙ ታሪክ ጸሓፊዎች በልዩ ልዩ መልክ ተርጕመውታል። እንዲያውም ንጉሡ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የዕንቍ ቀለበት ሰጥቷት ነበርና «ዕንቍ ለጣትሽ» ማለት ነው ብለው የጻፉ ብዙ ሰዎችም አሉ፤ የሚናገሩም አሉ። ነገሩ ግን እንዲህ አይደለም። ዕንቍጣጣሽ ማለት ተንቈጠቈጠ፥ አንቈጠቈጠ ከሚለው ቃል ተወስዶ ምድር በአበባ አጌጠች፥ ሰማይም በከዋክብት አሸበረቀ እንደ ማለት ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ አምላክ ምድርንም በአበቦች አጎናጸፋት ለማለት የተሰጠ ቃል ነው እንጂ ስለ ሳባ ንግሥት የተሰጠ አይደለም። ሁለተኛም አባቶቻችን ኢትዮጵያን በሙሉ ሀብት ተረክበዋት ነበርና፤ «ዕንቍ ዕጣ ወጣሽ፤» ሲሉ ወደ አገራቸው ሲገቡ ለአገራቸው መታሰቢያ አድርገው የተጠቀሙበት ቃል ነው ይባላል። በመሠረቱ ግን የጥፋት ውሃ ቀርቶ ምድር ጸንታ፥ አበባ ቋጥራ፥ ፍሬ ለመስጠት ተዘጋጅታ መገኘቷን የሚያበሥር ቃል ነው።
መስከረም 
መስከረም የሚባለው ወርም ኖኅ በመርከብ ውሥጥ በነበረ ጊዜ እንደ ዕብራውያን አቈጣጠር ሰባተኛ በሆነው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ መርከቢቱ አራራት ከሚባለው ተራራ ላይ ዐርፋ ምድር ጨብጣለች። በግእዝ ቋንቋ መርከብ መስቀር ይባላል። ከዘመን ብዛት በኋላ «» ወደ «» ተለውጦ መስከረም ተባለ እንጂ መስቀርም ምድር አገኘች፥ መርከብም ምድር ነካች ለማለት የተሰጠ የወሩ ስያሜ ነው።

ርእሰ ዐውደ ዓመት 

የምንለው፤ ዐውድ ማለት በግእዙ ቋንቋ ዙሪያ፥ ክብ የሆነ ነገር ማለት ነው። የዓመት ጠቅላላ ቀኖች መሠረታውያን ቀኖች የሚባሉት ሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀኖች ናቸው። እነዚህም በኀምሳ ሁለት ሱባዔ ተከፍለው ለእያንዳንዱ ቀን በዓመት ውስጥ ለሰባቱ ዕለታት ኀምሳ ሁለት ኀምሳ ሁለት ቀን ይደርሳቸዋል። ከነዚህ ቀኖች የተሳሳበ የሴኮንድ፥ የደቂቃ፥ የሰዓት ዕላፊ ተጠራቅሞ ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስተኛዋን የዘመን ማገጣጠሚያ ቀን ያስገኛል። ይህቺ ቀን እንግዲህ ዙሪያ፥ ክብ መግጠሚያ ናት ማለት ነው። በዚህች ቀን አማካይነት ወደ ዐዲሱ ዘመን መጀመሪያ እንተላለፋለን። ይህቺ ቀን ዕለት አዕዋዲት፥ ዕለተ ምርያ የመዘዋወሪያ ቀን ወይም የመጨረሻ ቀን ተብላ ትጠራለች። በአራት ዓመት ደግሞ ከዚህች መሳሳብ የምትገኝ አንዲት ቀን ትመጣለች። ሦስት መቶ ስድሳ ስድስተኛ። ይህቺ ቀን ዕለተ ሰግር ትባላለች። መረማመጃ ማለት ነው። አንድ ቀን ታስተላልፋለች። እንግዲህ እነዚህን ሁለቱን ቀኖች ተከትሎ የሚመጣው ቀን የዘመን መጀመሪያ፥ የዘመን ክብ መነሻና መድረሻ ተብሎ ርእሰ ዐውደ ዓመት ተብሎ በግእዙ ይጠራል። እነዚህ ቀኖች በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ተጠቃለው አንድ ጊዜ የሚገኙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ቍጥር መሠረቱ መጽሐፈ ሔኖክ የሚባለው ነው። መጽሐፈ ሔኖክ በ፲፱፥ ፳፥ ፳፩ እና ፳፪ ምዕራፎች የሚሰጠን የፀሐይን፥ የጨረቃን ጉዞ መነሻ አድርጎ የወሮችን፥ የዕለታትን፥ የዓመታትን መነሻ፥ መድረሻ፥ መዘዋወሪያ ብተታቸውን፥ ጥንታቸውን ነው የሚያሳየው። ስለዚህም በሔኖክ ቍጥር የወር ቀኖች ቍጥር ሠላሳ ናቸው። በሦስት በሦስት ወር ግን አንድ ቀን ትከተላቸዋለች። እና ዓመቱ ለአራት ይከፈላል። በዘጠና አንድ በዘጠና አንድ ቀን። ጠቅላላው ይሄ ድምር ሦስት መቶ ስድሳ ስድስት ቀን ይመጣል። ይህ ካለቀ በኋላ አንዲት ቀን ለዘመን ማገጣጠሚያ ዕለተ ምርያ የምትባለው ትመጣለች። እንግዲህ በኢትዮጵያውያን ቍጥር ወሩ ከሠላሳ አያንስም፤ ከሠላሳ አይተርፍም። ለዓመቱም ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስት ቀን መደበኛው አቆጣጠር ነው ማለት ነው። ይህ ነገር በአውሮፓውያን ቍጥርም አለ። ግን እነሱ ከዓመት ወሮች ሰባቱን ሠላሳ አንድ ሠላሳ አንድ አድርገው አራቱን ደግሞ ሠላሳ ሠላሳ አድርገው አንዷን ወር ሦስቱን ዓመት ሃያ ስምንት፥ በአራተኛው ዓመት ሃያ ዘጠኝአድርገው ያጣጧታል። 
እንግዲህ የአቀማመጡ ለውጥ ካልሆነ በስተቀር በቍጥር አካሄድ ዞሮ ዞሮ የዓመት ቀኖች ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስት ወይም ሦስት መቶ ስድሳ ስድስት በመሆን አንድ ሆነዋል ማለት ነው። ልዩነቱ ግን የአቀማመጥ ለውጥ ነው። በኢትዮጵያ አቈጣጠር ግን ጠቅላላውን ፲፪ ወሮች መደባቸው ሠላሳ ብቻ ነው። እነዚያ በሔኖክ መጽሐፍ በጣልቃ ገብነት የነበሩት አራት ቀኖች ተጠቅለው ጳጉሜን በሚባል በዓመቱ መጨረሻ ላይ ተገኝተዋል። ዐምስተኛዪቱ ቀንም ከእነሱ ጋር ተገኝታለች። ይህም ለቍጥር ተራ ቅምር መቅናት የተደረገ እንጂ ቀኑን የሚለውጥ ምንም ነገር የለበትም። እና ከእነዚህ ቀኖች በኋላ የምናገኘው ቀን ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል። ይህንን በዓል ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ ድረስ የነበሩ ዐሥሩም አበው በዐሥሩ ትውልድ እስከ ማየ አይኅ ድረስ ሲያከብሩት እንደ ቆዩና ኋላም የኖኅ ልጆች ከአባታቸው ተቀብለው ሲያከብሩት እንደ ነበረ ኩፋሌ የተባለው መጽሐፍ በምዕራፍ ያስረዳናል። እንግዲህ ኢትዮጵያ ይህንን ቀን የወረሰችው ከአበው ነው የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።
  

  የዘመን ቁጥር ልዩነት

ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ የዘመን አቆጣጠር መለያየትን መነሻ እንዲህ በማለት ያብራራሉ፤ «ክብ የሆነ ነገር ሲከብ ከየትኛውም ቦታ መጀመር ይቻላል፤ የዘመን አቆጣጠር /ዓውደ ዓመትም/ ይኸው ነው፡፡ ዋናው ነገር አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ ነው፤ የዘመን አቆጣጠሮቹም ልዩነት መንስኤው ይኸው ነው» ይላሉ፡፡ ባሕረ ሐሳብ፣ ጌታቸው ኃይሌ፣ ገጽ.65/ ለምሳሌነትም ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ጊዜ መነሻ ማድረጋቸውን/ በኋላም ታላቁ እስክንድር የነገሠበት ዘመን የዘመን ቆጠራ መነሻ ሆነው እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ መሐመድና ተከታዮች ከመካ ወደ መዲና ያደረጉትን ስደት መነሻ የሚያደርገው ኢስላማዊ  የዘመን አቆጣጠርም ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡
የአይሁድን አቆጣጠር ትተን ከላይ ያየናቸው ሁለቱ የዘመን አቆጣጠሮች /የምዕራባውያኑ የጁልየስ ጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠርና የኢትዮጵያና የግብጽ አቆጣጠር/ ሁለቱም ዘመንን የሚቆጥሩት ከክርስቶስ ልደት መነሻ አድርገው ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኛ ዛሬ 2006ዓ.ም ነው ስንል እነርሱ ደግሞ 2014 ዓ.ም ነው ይላሉ፡፡ በመካከሉ የ7/8 ዓመታት ልዩነት አለ፡፡ እንግዲህ ጥያቄው ትክክለኛው የትኛው ነው? የሚለው ነው፡፡
ጉዳዩ መጻሕፍትን ሊያጽፍ የሚችልና በእርግጥም የተጻፉበት ቢሆንም ለማሳያ ያክል ሁለት ነገሮች እንመልከት፤

1. አሁን ባለው የምዕራባውያን አቆጣጠር ሄሮድስ የሞተው 4 ዓመት ቅ.ል.ክ ነው፡፡ ሄሮድስ የሞተው ጌታ ተወልዶ በስደት ሦስት ዓመት ያህል በግብጽ ከቆየ በኋላ ነው፡፡ ይህ ማለት በእርሱ አቆጣጠር ጌታ የተወለደው በ7 ዓመት ቅ.ል.ክ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ጌታ በትክክል በተወለደበት በአንድ ዓ.ም እነርሱ ጌታ ሰባት ዓመት ሆኖታል ይላሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት አሁን ካላቸው ቁጥር ላይ ሰባት ዓመት መቀነስ አለባቸው፡፡

2. ፍላቪየስ ጆሴፈስ የተባለው የአይሁድን ታሪክ የጻፈው ሊቅ እንደመሰከረው ጌታ የተወለደበት ዓመት ነው ተብሎ በወንጌል ላይ የተጻፈው የቆጠራ ዓመት /ሕዝቡ ሁሉ የተቆጠረበትን ዘመን /ሉቃ.2.1/ በጎርጎሪያን ዘመን አቆጣጠር «7 ዓመተ እግዚአ /A.D/ ላይ ነው፡፡» በማለት መረጃ ትቶልናል ይህ ማለት ደግሞ ከምዕራባውያኑ ዘመን አቆጣጠር ላይ 7 ዓመቶች የግድ መቀነስ አለበት ማለት ነው፡፡ ያ ሲደረግ ደግሞ የኛን ዘመን አቆጣጠር ያመጣል፡፡

የዘመን መለወጫ ቀን ልዩነት

ሁለተኛው ጉዳይ የዘመን መለወጫ ወርና ዕለት ልዩነት ነው፡፡ እኛ መስከረም  1 አዲስ ዓመት ስንጀምር እነርሱ በ January 1 / በእኛ ታኅሣሥ 23/ አዲስ ዓመት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ከየት የመጣ ልዩነት ነው?
የእኛ እና የግብጻውያን አቆጣጠር እዚህ ጉዳይ ላይ ከአይሁድ አቆጣጠር ጋር ይስማማል፡፡ በአይሁድ አቆጣጠር የመጀመሪያው ወር ኒሳን የሚባለው /በእኛ መጋቢት/ ሚያዝያ/ ነው፡፡
«ይህ ወር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ይሁናችሁ፣ በዚህም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የአንድ ዓመት ተባዕት ላይ ወስደው ይረዱ፡፡ . . .»/ዘፀ.12.1-14/ ተብሎ የተሰጣቸውን የፋሲካ በዓል የሚያከብሩት በዚህ ወር ነው፡፡
ይሁን እንጂ አዲስ የዓመት በዓል አድርገው የሚያከብሩት «የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁናችሁ፡፡ በዚሁ በመለከት ድምጽ የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ መስዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት» /ዘሌ.13.23-25/ ተብሎ የተሰጣቸው የሮሽ ሆሻና፣/የመለከት በዓል ወይም በዓለ መጥቅዕ/ ተብሎ የሚጠራው በዓል ነው፡፡ ይህም ማለት አዲስ ዓመት የሚያከብሩት በሰባተኛው ወር በኢታኒም ወር /በእኛ መስከረም ጥቅምት/ ነው፡፡
በቤተክርስቲያናችንም ትምህርት ዓለም የተፈጠረው መጋቢት 29 ቀን ነው፡፡ መስከረም ደግሞ ከመጋቢት ጀምሮ ሲቆጠር ሰባተኛው ወር ነው፡፡ ይህም ከአይሁድ ዘመን አቆጣጠር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
አይሁድስ ቢሆኑ የመጀመሪያው ወር እያለ አዲስ ዓመትን ለምን በሰባተኛው ወር ያከብራሉ ለሚለው ጥያቄ ሁለት ዓይነት ምላሾች /ምክንያቶች/ ይሰጣሉ፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት «ሰባተኛው ወር ኖኅ ከመርከብ የወጣበት ወር በመሆኑ ይህ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ተደርጎ መከበር በመጀመሩ ነው» የሚል ነው፡፡ በዘመን መለወጫ ዕለት ልጃገረዶች አበባ እና ለምለም ሣር መያዛቸው ርግቢቱ ለኖኅ ካመጣችው ለምለም ወይራ /ቄጠማ/ ጋር ተያይዞ የተጀመረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ መስከረም የቀንና የዕለቱ ርዝመት እኩል የሚሆኑበት ወር በመሆኑ ነው የሚል ነው፡፡ የመስከረም 1 ቀን ስንክሳር «የተባረከ የመስከረም ወር የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ርእስ ነው፤ የቀኑ ሰዓትም ከሌሊቱ ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ሁለት ነው» ይላል፡፡
እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባው ሌላው ጉዳይ በቤተክርስቲያናችን ትምህርት እመቤታችን ጌታን የጸነሰችው መጋቢት 29 ቀን ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ጳዉሎስ ፣የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ» /ገላ.4.4/ እንዳለው የ5500 ዘመኑ ፍጻሜ /ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ/ ነው፡፡
ጽንሰትን መጋቢት 29 ካልን በኋላ ልደትን ታህሣሥ 29 ቀን እናከብራለን፡፡ ከመጋቢት 29 እስከ ታህሣሥ 29 ድረስ 9 ወር ከ5 ቀን ነው፡፡ /ጳጉሜን ጨምሮ/፡፡ ጳጉሜ 6 በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ ታህሣሥ 28 ቀን ልደት ስለሚከበር አሁንም በመሐሉ ያለው ጊዜ 9 ወር ከአምስት ቀን ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ  

በመጨረሻም የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ፍፁም መፅሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የሚቆጥር መሆኑን እንጂ እንደ ዘመኑ ነገስታት ፍላጎት በታሪክ ክስተትን መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ከተረዳን ይህንን ሃሳባችንን የሚያጠናክርልን የሳምንታንት እና የወራት ስያሜዎቻችንን እንዲሁም የልሎቹ የቀን አቆጣጠር ምንጭን ከ እዚህ በታች ባሉት ሰንጠረዦች እንመልከት።ለምሳሌ እነኚህ የሳምንታንት ልዩነቶች አውሮፓውያን ከጥንት ከነበረ አምልኮት ጋር የትዛመደ ሲሆን የእኛ ግን እግዚአብሔር አለምን መፍጠር ከጀመረ የመጀመርያ ቀን ስንል እሁድ ማለታችንን ሁለተኛ ቀን ስንል ሰኑይ (ሰኞ) ማለታችንን ወዘተ እንረዳለን።
ማኅበረ ቅዱሳን አውደ-ርዕይ 2000 ዓም
ማኅበረ ቅዱሳን አውደ-ርዕይ 2000 ዓም

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...